አንድነት ፓርቲ “የሚሊዮኖች ድምፅ ለህሊና እስረኞች” የሚል ዘመቻ ማዘጋጀቱን ይፋ አደረገ
አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ (አንድነት) ፓርቲ ከህዳር 14 እስከ 20 ቀን 2007 ዓ.ም. የሚቆይ “የሚሊዮኖች ድምፅ ለህሊና እስረኞች” የሚል የሶሻል ሚዲያ ዘመቻ አዘጋጅቷል። በዚህ ዘመቻ ለመንግስት ባለስልጣናት፣ ለታዋቂ ግለሰቦች፣ ለዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተቋማትና ለልዩ ልዩ የሚዲያ ድርጅቶች በኢንተርኔትና በሶሻል ሚዲያ በኩል መልዕክት በመላክ በሀገራችን ያሉት የፖለቲካ እስረኞች ሁኔታና አያያዝ በተመለከተ መረጃ በመስጠት ተገቢ የሆነ አያያዝ እንዲኖራቸው፤ ከእስር እንዲፈቱ፣ በሰላማዊ መንገድ የሚታገሉትን ማሰርና ማዋከብ እንዲቆም በመንግስት ላይ አዎንታዊ ተፅዕኖ ለመፍጠር ያለመ እንደሆነ ፓርቲው አስታውቋል። በዚህ ዘመቻ ላይ ሁሉም የዘመቻው ደጋፊና በሀገሪቱ ዴሞክራሲያው ስርዓት እንዲመሰረትና የዜጎች ሰብዓዊ መብት እንዲከበር የሚሹ ሁሉ ከላይ ለተጠቀሱት ግልሰቦችና ተቋማትን ጨምሮ ሚሊዮኖች ለሚያውቁትና ተፅዕኖ ማሳደር ይችላል ለሚሉት ሰው ሁሉ መልዕክት በኢንተርኔትና በሶሻል ሚዲያ በመላክ ድምፃቸውን ያሰሙ ዘንድ ዛሬ ህዳር 11 ቀን 2007 ዓ.ም. አዲስ አበባ በሚገኘው ዋና ጽህፈት ቤቱ በሰጠው መግለጫ ጥሪውን አቅርቧል፡፡
ፓርቲው ከዚህ በፊት ከህዝቢ ከፍተኛ ድፍ ያስገኘለትን “የሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነት” እና “…ለመሬት ባለቤትነት” የሚሉ የተለያዩ ህዝባዊ ስብሰባዎችን እና የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፎችን አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞች ማድረጉ ይታወቃል፡፡ የዛሬውን ሙሉ ዝርዝር መግለጫ ከታች ይመልከቱ፡፡
አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት)
UNITY FOR DEMOCRACY AND JUSTICE PARTY (UDJ)
ምርጫ ሲባል አማራጭ ሳያሳጡ መሆን ይኖርበታል!!!
ከአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ
በሀገራችን ኢትዮጵያ ለአምስተኛ ጊዜ ሀገራዊ ምርጫ እንደሚደረግ በመንግስት በኩል በከፍተኛ ደረጃ የፕሮፓጋንዳ መሳሪያ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል፡፡ ነገር ግን ከዚህ በፊት የተከናወኑት አራት ምርጫዎች ያየን እንደሆነ በሀገራችን የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ግንባታ ወደፊት ሊወስዱ እንዳልቻሉ እሙን ነው፡፡ ይህም ሆኖ የኢትዮጵያ ህዝብ ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ያለውን ፍላጎት በተለያየ መንገድ ሲገልፅ ቆይቷል፡፡ በተቃራኒው መንግስትና ገዢው ፓርቲ በፍፁም መለየት በሚያስቸግር ሁኔታ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታ ሆነው ተቀናጅተው ለአንድ ለአውራ ፓርቲ ግንባታ እየሰሩ እንደሆነ ከማንም የተሰወረ አይደለም፡፡ ይህ የመንግሥትና የገዢው ፓርቲ ተግባር ምርጫን ያለ አማራጭ እንዲሆነ እያደረገው እንደሆነ ለመረዳት አስቸጋሪ አይደለም፡፡
በቅርቡ የአንድነት ፓርቲ አባላት ላይ በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች ዘመቻ በሚባል ደረጃ እየተካሄደ ያለው አፈናና እስር፤ ከዚህም ባሻገር ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከህዝብ ጋር እንዳይገናኙ ክልከላውና ወከባው ተጠናከሮ መቀጠሉ፤ ገዥው ቡድን የምር ተቃዋሚ ፓርቲ ናቸው ብሎ የሚያስባቸው ፓርቲዎች ለማዳከምና ከምርጫው ውድድር ውጪ ለማድረግ ያለው ቁርጥ አቋም የሚያሳይ ነው። ይህ የገዢው ቡድን አካሄድ በሀገራችን ዴሞክራሲያዊ የሆነ የመድበለ ፓርቲ ስርዓት እንዲመሰረት ፍላጎት እንደሌለው በደንብ የሚያረጋግጥ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብ ነፃና ፍትሐዊ በሆነ ምርጫ የሚፈልገውን ፓርቲ እንዲመርጥ እድል ሊጠሰው ሲገባ በሥርዓቱ በእኩል ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ እንዳያካሄድ የተለያዩ ጫናዎች እየተደረጉበት የሚካሄዱት ምርጫዎች ሁሉ ትርጉም አልባ እየሆኑ ይገኛሉ፡፡ ይህ የገዢው ቡድን ሀላፊነት የጎደለው እንቅስቃሴ በተግባር የሚደግፈው ከሠላማዊ ትግል ይልቅ የኃይልና የአመፅ መንገድ እንደሚሆን የተረዳ አይመስልም፤ ይልቁንም በሠላማዊ መንገድ እየተንቀሳቀሱ ያሉትን ፓርቲዎች ወደ አላስፈላጊ መስመር በመግፋት ሀገራችን ወደ ብጥብጥና ወደ እርስ በእርስ ጦርነት እንድትገባ የሚያደርግ ሁኔታ እየተከተለ ነው የሚገኘው። በሥልጣን ላይ ያሉት ወገኖች ይህ አሳሳቢ ሁኔታ በትክክል እንዳያዩ ጭፍን የሥልጣን ጥም ጋርዷቸዋል፡፡
በቀጣይ ግንቦት 16 ቀን 2007 ዓ.ም. የሚደረገው ምርጫም በመንግስት በኩል የመድበለ ፓርቲን ስርዓት ለማጎልበት ምንም ዓይነት ምቹ ሁኔታ እንዳይፈጠር ከአሁኑ የተለያዩ እንቅፋቶችን በመደርደር ላይ ነው። የአንድነት አመራሮችና አባላት በግፍ በማሰር ፓርቲው በምርጫው እንዳይሳተፍ ከፍተኛ የሆነ ጫና እየተደረገ ቢሆንም አንድነት ፓርቲ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ሆኖ ህዝቡ እንዲሳተፍ በመቀስቀስና በማበረታታት የተዘጋውን የዴሞክራሲ በር በምርጫ ካርዱ ሊያስከፍት እንደሚችል ከፍተኛ እምነት አለው፡፡
ከሁሉም በላይ ደግሞ እንደከዚህ ቀደሙ ኢህአዴግ ደጋፊዎቼ የሚላቸውን ብቻ በመራጭነት አስመዝግቦ ምርጫ የሚያደርግበት ሁኔታ ማብቃት ይኖርበታል ብለን እናምናለን፡፡ ይህ ተግባራዊ እንዲሆን በእኛ በኩል ደጋፊዎቻችን በመራጭነት እንዲመዘገቡ ከማበረታት ጀምሮ የህዝብና የፓርቲ ታዛቢ በመሆን የምርጫ ሂደቱን በሙሉ በንቃት እንዲከታተል እንዲሳተፍ የበኩላችንን ጥረት በማድረግ የ2007 ሀገራዊ ምርጫ ከጅማሮው ህዝባዊ እንዲሆን ትግላችንን እንቀጥላለን፡፡ ይህ እርምጃም ህዝቡን የስልጣን ባለቤት ለማድረግ ወሳኝ እርምጃ ነው የሚል እምነት አለን፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብ በገዥው ቡድን መልካም ፍቃድ ወይም በማንኛውም ውጫዊ ተፅዕኖ የፖለቲካ ምህዳሩን እንደማይሰፋ ሊገነዘብ ይገባል። ምህዳሩ የሚሰፋውና ትክክለኛ የሆነ ዴሞክራሲያዊ ለውጥ የሚኖረው ህዝቡ በጠቅላላ ከፍርሀት ቆፈን ተላቆ በሙሉ ልብ ለመብቱ ሲቆም፣ ለፓርቲዎች ተገቢው ድጋፍ ሲሰጥ፤ ከፍ ሲልም ወደ ትግሉ ሲቀላቀል መሆኑ መገንዘብ ያስፈልጋል።
በዚህ አጋጣሚ አንድነት ፓርቲ ከህዳር 14 እስከ 20 ቀን 2007 ዓ.ም. የሚቆይ “የሚሊዮኖች ድምፅ ለህሊና እስረኞች” የሚል የሶሻል ሚዲያ ዘመቻ አዘጋጅቷል። በዚህ ዘመቻ ለመንግስት ባለስልጣናት፣ ለታዋቂ ግለሰቦች፣ ለዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተቋማትና ለልዩ ልዩ የሚዲያ ድርጅቶች በኢንተርኔትና በሶሻል ሚዲያ በእኩል መልዕክት በመላክ በሀገራችን ያሉት የፖለቲካ እስረኞች ሁኔታና አያያዝ በተመለከተ መረጃ በመስጠት ተገቢ የሆነ አያያዝ እንዲኖራቸው፤ ከእስር እንዲፈቱ፣ በሰላማዊ መንገድ የሚታሉትን ማሰርና ማዋከብ እንዲቆም በመንግስት ላይ አዎንታዊ ተፅዕኖ ለመፍጠር ያለመ ነው። በዚህ ዘመቻ ላይ ሚሊዮኖች ለሚያውቁትና ተፅዕኖ ማሳደር ይችላል ለሚሉት ሰው ሁሉ መልዕክት በኢተርኔትና በሶሻል ሚዲያ በመላክ ድምፃቸውን ያሰሙ ዘንድ ጥሪያችንን እናቀርባለን።
አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት)
ህዳር 11 ቀን 2007 ዓ.ም.
አዲስ አበባ
………..//………//…………
ምርጫ 2007 እና የ‹‹ተመራጩ›› አምባገነን ጉዞ
ጌታቸው ሺፈራው
በየ ዘመኑ የመንግስት ስርዓቶች ይቀያየራሉ፡፡ የህዝብ አመለካከት አድማስና የሚፈልገው ስርዓትም እንዲሁ፡፡ ይህን ሁሉ በሚገባው መንገድ ለመምራት ደግሞ ገዥዎች ለወቅቱ ሁኔታ የሚያወጣቸውን የአገዛዝ ስርዓት ይዘረጋሉ፡፡ በተለይ ከህዝብም ሆነ ከሌላ አካላት ስልጣንና ህይወታቸውንም እያጡ የሚገኙት አምባገነኖች ስልጣናቸውን ለማቆየት የሚደረግን ብልጣብልጥ መንገድ ሁሉ መከተላቸው የተለመደ ሆኗል፡፡ በአሁኑ ወቅት ምርጫ ዘመናዊ ፖለቲካ መለኪያ ነው፡፡ ነገር ግን ምርጫ አምባገነኖችን ስልጣን የሚያሳጣ በመሆኑ በሙሉ ልባቸው ወደ ምርጫ መግባትን አይደፍሩም፡፡ ከዚህ ይልቅ በስመ ምርጫ፣ አምባገነንነታቸውን፣ አፋኝነታቸውን ያጠናክራሉ፡፡ እነዚህን አብዛኛዎቹ ብልጣብልጦች ምርጫን እየጠሉ በስመ ምርጫ ስልጣናቸውን የሚያራዝሙ አምባገነኖች ‹‹ተመራጭ አምባገነኖች›› ይሏቸዋል፡፡
ይህ አይነት ስርዓት ከአፍሪካዎቹ ዚምባብዌ፣ ኢትዮጵያ፣ ሱዳን፣ ዩናጋዳ እስከ ቱርክ ኢራንና ሩሲያ ድረስ ያለውን የብልጣብልጦች ‹‹መንግስት›› የሚያጠቃልል ነው፡፡ በእርግጥ በአፍሪካው በተለይም ደግሞ በኢትዮጵያ ገዥው ፓርቲ ደህንነትና መከላከያ ሰራዊቱን በቀኝ እጁ ምርጫን ደግሞ በግራው አንጠልጥሎ ወደ ‹‹ምረጡኝ›› የሚገባበትና ያልፈለገው ነገር ሲከሰት ‹‹ጨዋታ ፈረሰ!›› የሚልበት በመሆኑ ‹‹ተመራጭ አምባገነን/አፋኝ›› የሚባለውን መስፈርትም ብዙም የሚያሟላ አይደለም፡፡ ብልጣብልጥነትን ይልቅ ግትርነት፣ ማን አለብኝነት፣ አሊያም እኔ ከሞት ሰርዶ አይብቀል አይነት የአህያዋ አስተሳሰብ የተጠናወተው ነው ማለት ይቀላል፡፡
ምርጫው ከመጀመሪያው እስከመጨረሻው፣ በህዝብ ገንዘብ አባላት፣ ተለጣፊ ተቃዋሚዎችን፣ ሚዲያ አደራጅቶ አማራጭ አልባ ‹ተመራጭ›› ከመሆን እስከ ማጭበርበር፣ በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ቢሸነፍ በሀይል የምርጫ ድምጽ በመንጠቅ ምርጫውን ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው የሚቆጣጠረው ስልጣን ላይ ያለው ‹‹ተመራጭ›› አምባገነን/አፋኝ ስርዓት አይነተኛ ባህሪ ነው፡፡
ህገ መንግስት፣ ፍርድ ቤት፣ ምርጫ ቦርድ፣ ሚዲያ (የግል የሚባሉትን ይጨምራል)፣ ተቃዋሚዎቹም እንዳይንቀሳቀሱ ነገር ግን ለእርዳታ ለጋሾች የመድብለ ፓርቲ ስርዓት እንዳለ፣ ህዝብም አማራጭ እንዳለው ነገር ግን እንደማይመርጣቸው ለማሳየት ተቋማትን እያዳከመ ለመግዛት ይጥራል፡፡ እነዚህ ተቋማት ስርዓቱ የሚፈልገው ግብ ይደርስ ዘንድ የቲፎዞነት ሚና ከተወጡ ደግሞ በማያሸልመው እየሸለመ፣ በማያስደጉመው ተግባራቸው እየደጎመ በአሯሯጭነት ያስቀጥላቸዋል፡፡ ይህን በእኛ አገር በግልጽ የምናስተውለው ነው፡፡ ኢህአዴግ ፓርቲም መንግስትም ሆኖ የህዝብን ሀብት ‹‹የጋራ ምክር ቤት›› ውስጥ ተካተው ለምርጫው በአሯሯጭነት ለተሰለፉት፣ አብዛኛው የፓርቲው ካቢኔ በአንድ ሰው ለተያዘባቸው ፓርቲዎች ከ100 ሺህ እስከ 390 ሺህ ብር አከፋፍሏል፡፡ በምርጫ ሊቀናቀኑት የሚችሉትን ግን አመራሮቻቸውን እያሰረ፣ ጽ/ቤት እንዳያገኙ፣ ሰላማዊ ሰልፍና ስብሰባ እንዳያካሂዱ በሀይል እያገደ ከአሁኑ ምርጫውንና እድሜውን ለመወሰን እየጣረ ነው፡፡
እንደ አጠቃላይ ግን ተመራጭ አምባገነንነት/አፋኝነት በምርጫ ስም የሌለን ምርጫ ምርጫ እንዳለ፣ ያላሸነፉትን ምርጫ አጭበርብረውም ሆነ ድምጽ ቀምተው በህጋዊ መንግድ እንዳሸነፉ፣ ነጻ ያልሆኑትን ተቋማት ነጻ እንደሆኑ በማስመሰል ስልጣናቸውን በማራዘም የተካኑ ስርዓቶች መገለጫ ነው፡፡ ብልጣብልጥ ነው ባይባልም ኢህአዴግ ይህን ስልት በዋነኛነት እየተከተሉት ከሚገኙት አፋኞች መካከል የግንባር ቀደምነቱን ቦታ ለመያዝ እየተንደረደረ ነው፡፡
‹‹ተመራጩ›› ኢህአዴግና ምርጫ 2007
ለኢህአዴግ ምርጫ 2007 ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ወሳኝ ይመስለኛል፡፡ በአንድ በኩል ለዴሞክራሲ ጭላንጭል በር ከፍቶ የነበረው ምርጫ 97 በአሳዛኝ መልኩ ካለቀ በኋላ ህዝቡ ላይ የተፈጠረውን የምርጫ ፍዘት (apathy) በማጠናከር ነገር ግን ለተወሰነው የማህበረሰብ ክፍል በምርጫ የሚያምን፣ ተመርጦም የሚመራ ለማስመሰል ይጠቀምበታል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ አብዛኛውን በጀት የሚሰበስብበትን አሁን አሁን የኢህአዴግን ሪፖርት ሳይቀር (የኢኮኖሚ እድገት….የመሳሰሉትን የስታስቲክ ባለስልጣን የተጋገረ ሪፖርት) እንደሪፖርት ማየት የተገደደውን የ‹‹ዓለም አቀፍ›› ማህበረሰብ ለማሞኘትም ይጠቀምበታል፡፡ ምርጫ ለስልጣኑ አደጋ እንደሆነ በምርጫ 97 በደንብ ተምሮበታልና እውነተኛ ምርጫ ግን እንዲኖር ይፈቅዳል ማለት ዘበት ነው፡፡
ያም ሆኖ የ2007 ዓ.ም ምርጫ ለኢህአዴግ አስፈላጊ የሆነውን ያህል መስቀለኛ መንገድ ላይም የሚጥል ነው፡፡ በአንድ በኩል ቀደም ብሎ ያወጀውን የ‹‹አውራ ፓርቲ››ነት እንዲሁም በዓለም አቀፍ ማህበረሰቡም ዘንድ ‹‹ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ›› ያደረገ ተብሎ ቅቡልነት ለማግኘት ይጠቅመዋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ህዝብንም ሆነ ዓለም አቀፍ ማህበረሰቡን ‹‹ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ አድርጌ አሸንፌያለሁ›› ብሎ እንደሚያሞኘው ለምርጫ የሚያበቃ ምህዳር መዘርጋቱ እራሱን አጋልጦ መስጠት ይሆንበታል፡፡
በመሆኑም በህዝቡም ሆነ በዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ዘንድ ቢቻል ነጻና ፍትሃዊ የሚመስል ‹‹ምርጫ›› እንዲኖር ይፈልጋል፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ ነጻና ፍትሃዊ በሚመስል ምርጫ ውስጥም አደጋ የሚያደርሱበት አካላት ላይ ቅድመ ዝግጅት ማድረግ አለበት፡፡ ለገዥው ፓርቲ በምርጫው ቀጥተኛ አደጋዎች ተቃዋሚ ፓርቲዎች ናቸው፡፡ ከፓርቲዎቹ ባሻገር ሲቪክ ማህራት፣ ሚዲያ፣ ነጋዴው ማህበረሰብ፣ ሌላው ህዝብ፣ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች በምርጫው ወቅት ተጽዕኖ ከማሳደር ጀምሮ ለስልጣኑ አደጋ አድርጎ ይቆጥራቸዋል፡፡ ነገር ግን ዋነኛዎቹ ተቀናቃኞች ተቃዋሚዎች እንደመሆናቸው ትልቁን ስራ የሚሰራው በእነሱ ዙሪያ ነው፡፡
ተቃዋሚዎቹ በምርጫ 1997 ኢህአዴግን ካስበረገጉት ማግስት ኢህአዴግ መስራት የጀመረው ‹‹ተቃዋሚዎችን ከህዝብ መነጠል፣ ተቃዋሚዎችን ራቁታቸውን ማስቀረት…..›› በሚል አዲስ ‹‹ስልት›› ነው፡፡ በምርጫ 97 ሲቪክ ማህበራት ንቁ ተሳትፎ በማድረግ ለምርጫ ስርዓቱ የራሳቸውን አስተዋጽኦ በማድረጋቸው ምርጫ 97 በኋላ እነሱን የሚያስቆምበት መላ ዘየደ፡፡ የሲቪህ ማህበራት አዋጅ በመሳሪያነት የተጠቀመበት አንዱ ስልት ነው፡፡ ሲቪክ ማህበረሰቦች ለኢትዮጵያ ዴሞክራሲ፣ ኢኮኖሚና ሌሎችም ጉዳዮች ላይ የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ቢኖርም ይህ ሁሉ ከስልጣኑ የማይበልጥበት ገዥው ፓርቲ በአዋጁ መሰረት እንዳይንቀሳቀሱ በማገድ ‹‹ተቃዋሚዎችን ራቁታቸውን›› የሚያስቀርበት እንደ አንድ ትልቅ ስልት ወሰደው፡፡ በእርግጥ ይህ ከስልጣን ጥማት የመነጨው የገዥው ፓርቲ ስልት ተቃዋሚዎቹን ብቻ ሳይሆን አገሪቱንም ጭምር ራቁቷን የማስቀረት ስልት ነው፡፡
ሚዲያ ተቃዋሚዎች መግለጫ የሚያወጡበት፣ ፖለቲከኞች በቃለ መጠይቅም ሆነ በአስተያየት መልክ ሀሳባቸውን ለህዝብ የሚያደርሱበት፣ ስለ ፓርቲዎችና እንቅስቃሴዎቻቸው ዜናዎች የሚተላለፉበት በመሆኑ ኢህአዴግ የተቃዋሚዎች ጋሻ አድርጎ ይወስዳቸዋል፡፡ ከዚህ አለፍ ሲል ደግሞ ልሳኖቻቸው አድርጎ ይከሳቸዋል፡፡ በመሆኑም የሚዲያ አዋጅ በማውጣት ሚዲያዎቹ በስርዓቱ ላይ ጠንከር ያለ ትችት እንዳይሰነዘር በስም ማጥፋትና በመሳሰሉት ማጥመድ ጀመረ፡፡ ይህ አልበቃ ሲልም ጋዜጠኞችን በማስፈራራት አገር ጥለው እንዲሰደዱ አደረገ፣ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ማተሚያ ቤት እንዳያገኙ ተደረገ፡፡ በቅርቡ ደግሞ የራሱን መዋቅር በማደራጀት በተለይ የግል ጋዜጦችና መጽሄቶች ወደ ክፍለ ሀገር እንዳይከፋፈሉ አከፋፋዮችን በራሱ አደረጃጀት ማዋቀሩ ተሰምቷል፡፡ ይህ አማራጭ መረጃን ለህዝብ የሚያደርሱ ሚዲያዎችን በማፈን ተቃዋሚዎችን ‹‹ራቁታቸውን የማስቀረት›› ለ40ና 50 አመት የታቀደው የ‹‹አውራነት›› በአጭር ጊዜ ደግሞ የ2007 ቅድመ ዝግጅት አንዱ አካል ነው፡፡
ይህ ሁሉ ግን በቂ አይደለም፡፡ ጋዜጠኞችን፣ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራርና አባላትን፣ የሲቪክ ማህበራትና የኃይማኖት መሪዎችን፣ አርሶ አደሮችን፣ ነጋዴዎችን፣ መምህራንን፣ ተማሪዎችን…..በአጠቃላይ ከተቃዋሚዎች ጋርም ሆኖም ይሆን በግል ስርዓቱን የተቃወመ አሊያም ይቃወማል ተብሎ የታሰበን ‹‹ከህዝብ የሚነጥልበት›› አዋጅ አስፈላጊ ነበር፡፡ ለዛም ሲባል የጸረ ሽብር ህጉ ወጣ፡፡ በዚህ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራር፣ ጋዜጠኛ፣ የኃይማኖትና የሲቪክ ማህበረሰብ መሪ፣ አርሶ አደር ‹‹አሸባሪ›› ተብሎ በሚከሰስበት ህግ በርካቶች ለእስር ተዳርገዋል፡፡
በአንጻሩ በዚሁ ህግ የታሰሩት አውሮፓውያን በወራት ውስጥ ተለቀዋል፡፡ ምንም ለውጥ አያመጡም የተባሉት የተገንጣይ ቡድን አባላት በፓርላማ አሸባሪ ተብለው አዋጁ ይቅርታ የሚሰጥበት ምንም አንቀጽ ሳይኖረው፣ ፓርላማውም ‹‹አሸባሪነታቸውን›› ሳይሽር በጓዳ እርቅ ወደ አገር ቤት ገብተዋል፡፡ በዚህ ህግ የከሰሷቸውን እነ አንዳርጋቸው ጽጌን በሚሊዮን ዶላር ከየመን እንዳላመጡ በድንገት አዲስ አበባ የተገኙትን ‹‹አሸባሪዎች›› በ24 ሰዓት ‹‹ውጡልን!›› ብለው ለምነዋል፡፡ ይህ የሚያሳየው አዋጅ፣ ህግ….ተብሎ ለስርዓቱ መግዢያ መሳሪያ፣ መጠቀሚያና ያለ አማራጭ ‹‹ማስመረጫ›› መሆኑን ነው፡፡
የጸረ ሽብር አዋጅ ከየትኛውም አዋጅ በላይ ‹‹ተቃዋሚዎችን ራቁታቸውን ማስቀረት›› የተሰኘውን የኢህአዴግ ስልት ለማስፈጸም መጠቀሚያ መሳሪያ ሆኗል፡፡ እነ አንዱዓለም አራጌ፣ ናትናኤል መኮንን፣ አበበ ቀስቶ፣ …. ተቃዋሚዎቹ ጋር እየሄደ ስለ ሰላማዊ ትግል ያስተምር የነበረውና ስለ ለውጥ ትንታኔ የሚሰጠው እስክንድር ነጋ፣ ውብሸት ታየ፣ ርዕዮት ዓለሙ…… በማሰር ተቃዋሚዎችን ራቁት የማስቀረት ስልት ለመተግበር ሞክሯል፡፡ የተቀውሞ ጎራው፣ ሚዲያው ተቀዛቀዘ ሲባል እንደገና ሲጠናከር ደግሞ ሀብታሙ አያሌው፣ አብርሃ ደስታ፣ የሽዋስ አሰፋ፣ ዳንኤል ሺበሽ፣ የዞን ዘጠኝ ጦማሪያንና ጋዜጠኞችን አስሮበታል፡፡ ከባለፈው ሳምንት ጀምሮ ደግሞ በየ ክፍለ ሀገሩ የሚገኙ የአንድነት፣ የመኢአድ፣ የሰማያዊና የአረናን ጠንካራ አመራሮችና አባላት በጸረ ሽብር ህጉ እየከሰሰ እያሰረ ይገኛል፡፡ አዲስ አበባም ሆነ በየ ክፍለ ሀገሩ የሚገኙ ጠንካራ አባላትንና አመራሮች ላይ የሚደረገው እርምጃ አሁንም እንደሚቀጥል ነው መረጃዎች የሚያመለክቱት፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ምርጫ የሚመስል ምርጫ አካሂዶ በህዝብ ዘንድም ሆነ በለጋሾች ‹‹ተመራጭ›› ለመምሰል ነው፡፡
የቀድሞው የኮሚኒኬሽን ሚኒስትር ድኤታ አቶ ኤርምያስ ለገሰ በመጽሃፉም ኢህአዴግ በ1997 ውድድሩን ቀድሞ ክፍት ማድረጉ በአመራሩ ዘንድ ስህተት መሆኑ እንደታመነበት ጽፏል፡፡ ምርጫ 2007 ዓ.ም እንደ 1997 ዓ.ም ይሆናል ባይባልም ቢያንስ ለተወሰነ ጊዜም (ለአንድ ሳምንትም ይሁን ወር) ምርጫውን ምርጫ ለማስመሰል የተወሰኑ ክርክሮች እንዲኖሩ ማድረግ፣ ሰላማዊ ሰልፍና ስብሰባዎችን በመጠኑ መፍቀዱ የማይቀር ነው፡፡ በእነዚህ ቀናትም ቢሆን ግን በተለያዩ ብሶቶች የተወጠረው ህዝብ በእሱ ላይ እንደሚነሳበት ያውቃል፡፡ በመሆኑም እስከዛው ህዝብን ያደራጃሉ የሚባሉት ተቃዋሚዎች መዳከም (ራቁታቸውን መቅረት) አለባቸው፣ ሚዲያዎችም ከገበያ መውጣት ይገባቸዋል፡፡ በእነሱ ምትክ ደግሞ ስመ ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ እየተከፈላቸው ተቃዋሚዎችን የሚያብጠለጥሉ ሚዲያዎች ወደ ገበያው እንደሚመጡ ይደረጋል፡፡ እንዲህ ከሆነ ብቻ ነው ኢህአዴግ ‹‹ተመርጦ›› ለቀጣዮቹ 40ና 50 አመታት ሊገዛ የሚችለው፡፡ ይህ ደግሞ ኢህአዴግ ከአቶ መለስ የወረሰው እውነተኛውን አማራጭ አሳጥቶ በግድ የመመረጥ የ‹‹ተመራጭ›› አፋኝነት ‹‹ሌጋሲ›› ነው፡፡
እነ ሙባረክ፣ ቤል አሊ፣ ኮምፓወሬ በዚህ ብልጣብልጥነት በርከት ላሉ ጊዜያት ስልጣን ላይ ቆይተው በመጨረሻ ያላሰቡት ደርሶባቸዋል፡፡ ከብልጣብልጥነት ይልቅ ግትርነቱ የሚያጠቃው የኢህአዴግ እንደሌሎቹ ‹‹ቀን እስኪጥለው›› ድረስ የ‹‹ተመራጭ›› አፋኝነቱ ጉዞ እንደቀጠለ ነው፡፡ እንደ ‹‹ተመራጩ አፋኝ›› ስርዓት እቅድ ከሆነ ደግሞ ለ50 አመታት ይቀጥላል፡፡
ኢ/ር ግዛቸው ሽፈራው በገዛ ፍቃዳቸው ሥልጣናቸውን ሲለቁ፤ አቶ በላይ ፍቃዱ ቀጣዩ ፕሬዘዳንት በመሆን ተመርጠዋል
የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) ብሔራዊ ምክር ቤት ዛሬ ጥቅምት 2 ቀን 2007 ዓ.ም. በነበረው ስብሰባ ፕሬዚዳንቱ ኢ/ር ግዛቸው ሽፈራው ሪፖርት ካቀረቡ በኋላ፤ ከውስጥና ከውጭ በተፈጠሩ አንዳንድ የማያሰሩ ችግሮች፣ ካለባቸው የሥራ ጫና እና ፓርቲው ወደፊት አንድነቱን ጠብቆ ለ2007 ምርጫ አሸናፊ ሆኖ እንዲወጣ በማሰብ ስልጣናቸውን በቃዳቸው መልቀቃቸውን ይፋ ማድረጋቸው ተጠቁሟል፡፡
ምክር ቤቱም በፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ መሰረት የፕሬዘዳንቱን ጥያቄ በአድናቆት ተቀብሎ፤ ፓርቲውን በፕሬዘዳንትነት በመምራት መጪውን ምርጫ ውጤታማ ለማድረግ እንዲያስችል 1ኛ. አቶ በላይ ፈቃዱ፣2ኛ. አቶ ደረጀ ኃይሉ እና 3ኛ. አቶ ትዕግስቱ አወሉን በዕጩነት በማቅረብ፤አቶ በላይ ፈቃዱን በፕሬዘዳንት መርጧል፡፡ ምርጫውም በምስጢር ድምፅ አሰጣጥ እዛው በፓርቲው ምክር ቤት የተከናወነ ሲሆን፤በመጨረሻም አቶ በላይ ፈቃዱ በከፍተኛ ድምፅ ማሸነፋቸው መረጃዎች አመልክተዋል፡፡
ከምርጫው ውጤት በኋላ አቶ በላይ በቀጣይ የስልጣን ጊዜያቸው ፓርቲውን ለመምራት ቃለ መሐላ የፈፀሙ መሆናቸውን የፍኖተ ነፃነት ዘገባ ያስረዳል፡፡ አቶ በላይ ጠንካራ የፖለቲካ ልምድና ተሳትፎ ካላቸው የፓርቲው ወጣት አመራሮች መካከል በውጤታማነት ከሚጠቀሱት አንዱ እንደሆኑ የተጠቆመ ሲሆን፤የትምህርት ደረጃቸውም በስታስቲክስ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የመጀመሪያ ድግሪ (BSc) እና በኢኮኖሚ ፖሊሲ አናሊስስ የማስተርስ ድግሪ (MSc) ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ያላቸው ሲሆን፤ በስራ ልምዳቸውም በተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አገልግለዋል፡፡ አቶ በላይ ወደ ፓርቲው ፕሬዘዳንትነት ከመምጣታቸው በፊት፤ በራሳቸው የጥናትና ምርምር ድርጅት በማኔጂንግ ዳይሬክተርነት ያገለግሉ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡
ፓርቲው መጪውን 2007 ዓ.ም. ምርጫ እንዲያሸንፍ ትልቅ ሚና ይኖራቸዋል በሚል ከአባላትና ከደጋፊዎች ትልቅ ተስፋ እንደተጣለባቸውና ኃላፊነታቸውንም በስኬት ሊወጡ እንደሚችሉ ተገምቷል፡፡
ማሰርና ማሳደድ መፍትሄ ይሆናል?
ብስራት ወልደሚካኤል
afrosonb@gmail.com
በቀድሞ ታጣቂዎች እንደ ጭራቅና አውሬ ይሳል የነበረው የደርግ ስርዓት ወድቆ ስልጣን በአማፂዓን እጅ ከገባ 23 ዓመታት አልፈዋል፡፡ ነገር ግን የታሰበው ለውጥ ዛሬም ቢሆን መናፈቁን አልተወም፡፡ ምክኔቱም ያኔ ማሰር ነበር፤ ዛሬም ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ ያኔም መወንጀልና መፈረጅ ነበር ዛሬ ግን ተባብሷል፡፡ ለእኔ ከድሮ የተለየ ተቀይሮ ያገኘሁት በዋናነት የመሪዎች ስምና ልብሳቸው እንጂ ስራቸው ያው ነው፡፡
በዘመነ ደርግ ጠባብነትና ዘረኝነትን እንዲሁም ኢትዮጵያ ላይ ጥላቻ ያላቸውን በሙሉ ስልጣኑን ሊቀናቀኑ ካሰቡት እኩል በጠላትነት ይፈረጃሉ፡፡ በዘመነ ኢህአዴግ ደግሞ ኢትዮጵያዊነትን ማስቀደምና ለኢትዮጵያውያን በእኩል ዓይን መቆምና መቆርቆር እንደ ወንጀል ይታያል፡፡ሁለቱም ወደ ስልጣን ሲወጡ በጠብመንጃ ሲሆን፤ ስልጣናቸውንም ያስጠበቁትን የሚያስጠብቁት እንዲ በጦር መሳሪያ ነው፡፡ምን አለፋችሁ፤ ልዩነቱን “…ጃሃ ያስተሰርያል” የሚለው የአርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን (የቴዲ አፍሮ) ሙዚቃ በደንብ ይገልፀዋል፡፡
በሁለቱ መካከል ያለው መሰረታዊ ልዩነት ደርግ የማይፈልገውን ነገር በግልፅ በአዋጅ ይደነግጋል፤ከአዋጅ ወይም ህግ ውጭ ይቀጣል፡፡ ኢህአዴግ ደግሞ የሚፈልገውንም ሆነ የማይፈልገውን በህገ መንግስት እውቅና ሰጥቶ የማይፈልገውን በሌላ አዋጅ ይቀጣል፣ያስራል፡፡ ልዩነታቸው የመሪዎች ስም፣ የለበሱት ልብስና አካሄዳቸው እንጂ መሰረታዊ የልዩነት ባህርይ አይታይባቸውም፡፡ ለዚህም አሁን በስልጣን ላይ ያለው ኢህአዴግ ከደርግ በባሰ ያከናወናቸውን እና እያከናወናቸው ካሉት አሉታዊ ተግባራት መካከል በዋናነት የእስር ዘመቻውን ማንሳቱ በቂ ነው፡፡
በተለይ በምርጫ 1997 ዓ.ም. ኢህአዴግ በአደባባይ መሸነፉን እና የህዝብን ድምፅ መቀማቱን የሚያሳብ በርካታ ተግባራትን ሲያከናውን ዋናው ገመናውን የሚያጋልጡና በአብዛኛው ህዝብ ዘንድ ተቀባይነትና ተወዳጅነት ያላቸውን በሰበብ አስባቡ አስሮ ማሰቃየትን እንደ ትልቅ አማራጭ መጠቀም ጀመረ፡፡ ለዚህ በምርጫው ያሸነፉት የቀድሞ ቅንጅት አመራሮችን ከወነጀለበት በኢትዮጵያ 2000 ዓ.ም. ዋዜማ ከእስር ከፈታ በኋላ አዲሱ ቀዳሚ እስረኛ አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ነበር፤ የእስርዓ ምዕት ኢትዮጵያ ጅማሮ እስረኛ፡፡ ይህም አዲስ አበባና አስመራን ጨምሮበመላው ዓለም ጥያቄና ተቃውሞ ከማስነሳቱ በተጨማሪ ከእስር ሲፈታም የህዝብ ድጋፍ በመላው ዓለም ተጠናክሮ እስከዛሬም ድረስ ዘልቋል፡፡
ከዚህ በኋላ የኢህአዴግ ጥላቻ እየተባባሰ፣ ለስልጣን ያለው ጥማት ሰርክ እንደ አዲስ ወይን እየጣመው ይሄድ ጀመር፡፡ ከስልጣናቸው በዕድሜ ይፍታህ የተሰናበቱት ሟቹ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ በስልጣናቸው እስከ መቃብር አፋፍ ዋስትና ይሆናል ያሏቸውን አፋኝ ህጎች ፀድቀው ተግባር ላይ እንዲውሉ ቀን ከሌት ኳተኑ፡፡ በዚህም የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኀበራት አዋጅ፣ የፕሬስ አዋጅ፣ የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅ፣…ይገኙበታል፡፡
በተለይ በተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶች እና የነፃ ጋዜጠኞች ከፍተኛ ተቃውሞ የገጠመው የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅ ሰኔ 30 ቀን 2001 ዓ.ም. ፀድቆ ለምርጫ 2002 ዓ.ም. ማፈኛ ተዘጋጀ፡፡ የዚህም ገፈት የዴሞክራሲ እንቅስቃሴዎችን ገድቦ የነበረውን ተስፋ መቀመቅ ውስጥ ከተተው፡፡ ከዚህ በኋላ በየካቲት 2003 ዓ.ም. በቱኒዚያ መሐመድ ቡዓዚዝ የተጀመረው የአረቡ ፀደይ አብዮት በሰሜን አፍሪካን እና መካከለኛ ምስራቅ አረብ ሀገሮች መቀጣጠሉን የተመለከቱት አቶ መለስና ተከታዮቻቸውና አጋሮቻቸው በኢትዮጵያም ይከሰታል በሚል የአስር አደኑንን አጣደፉት፡፡
የአረቡን አብዮት ተከትሎ በኢትዮጵያ የእስር ሰንሰለቱን የጀመሩት እንደ ታሰበው ጋዜጠኞች እና የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ናቸው፡፡ በቀዳሚነትም በወርሃ ሰኔ 12 ቀን 2004 ዓ.ም. ከፖለቲከኛ አቶ ዘሪሁን ገ/እግዚአብሔር፣ ሰኔ 14 ቀን 2003 ዓ.ም. ደግሞ ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ፣ ርዕዮት አለሙ፤ ከዚያም በክረምት 2003 ዓ.ም. የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህርና የኦፌኮ/መድረክ አመራር አቶ በቀለ ገርባና አቶ ኦልባና ሌሊሳ የእስር ሰለባ ሆኑ፡፡
ሌላው ከኢትዮጵያውያን በተጨማሪ ሁለት ሲውድናውያን ጋዜጠኞች ማርቲን ሸብይ እና ጆሃን ፐርሰን ሽብርተኝነትን ደግፈዋል በሚል በዚሁ የፀረ-ሽብርተኝነት ሰለባ በመሆን ከ14 ወራት የሰቆቃ እስር በኋላ በዓለም አቀፉ ማኀበረሰብ ጫና መስከረም 1 ቀን 2004 ዓ.ም.ተለቀዋል፡፡ በመቀጠል መስከረም 3 ቀን 2004 ዓ.ም. ደግሞ ታዋቂው የፖለቲካ ተንታኝ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፣በብዙ ወጣቶች ዘንድ በቅንነቱና ፍቅርን በመስጠት እንዲሁም ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልን አጥብቆ በመደገፍ የሚከራከረው የአንድነት/መድረክ አመራር አቶ አንዱዓለም አራጌ እና ሌሎች የአንድነት ፓርቲ አመራሮች አቶ ናትናኤል መኮንን፣አቶ ዮሐንስ ተረፈና ሻምበል የሺዋስ ይሁንዓለምንና አቶ አንዱዓለም አያሌውን ጨምሮ አቶ ክንፈ ሚካኤል ደበበና ሌሎች ሰዎችም በሽብርተኝነት ስም ወደ ወህኒ ወረዱ፡፡ በዚህም አፍቃሬ መንበር አቶ መለስ የፈሩትን የአረቡን አብዮት በዚህ ያለፉ ይመስል ጀብደኝነት ተሰምቷቸው፤ ተጠርጣሪዎቹ ገና በፍርድ ቤት ብይን ሳይሰጥባቸው አሸባሪዎች ናቸው ሲሉ ለተወካዮቻቸው አረጋገጡ፡፡
ያሰሯቸው ላይ ቀድመው ወንጀለኛ በማለት ፍርድ በመስጠት መከራን የደገሱት አቶ መለስ ባልጠበቁት ሁኔታ በጠና ታመው በአውሮፓ ቤልጄየም ብራሰልስ አንድ የዩኒቨርስቲ ሪፈራል ሆስፒታል ተኙ፡፡ በመጨረሻም እንደ ሆስፒታሉ ምንጮች ከሆነ ሐምሌ 13 ቀን 2004 ዓ.ም. እንደወጡ ላይለመሱ ብዙ ለመኖር ያሰቡበትን በ21 ዓመታት የስልጣን ዘመናቸው እንደ ግል ርስታቸው ያስቡት የነበረውን ቤተመንግስት ጥለው እስከወዲያኛው ተሰናበቱ፡፡
ይሁን እንጂ አጋሮቻቸውና የቅርብ የኢህአዴግ አመራሮች መታመማቸውን እንኳ ለህዝብ ሳይገልፁ በድንገት የሞቱትን ሰውዬ ከጋዜጠኞች ጥያቄ ቢበረታባቸው በቅርቡ ተመልሰው ስራ ይጀምራሉ የሚል መልስ ሰጡ፡፡ በኋላም የተባለው ሳይሆን ፈጣሪ የወሰነው ሞት እርግጥ መሆኑ እና ነሐሴ 14 ቀን 2004 ዓ.ም. ሌሊት እንዳረፉ ተደርጎ ነሐሴ 15 ቀን 2004 ዓ.ም. ማለዳ አንድ ለእናቱ በሆነው ሀገሪቱ ቴሌቪዥን ኢቴቭ ይፋ ተደረገ፡፡ ከዚያም ነሐሴ 27 ቀን 2004 ዓ.ም. ግብዓተ መሬታቸው እንደ ተከናወነ በግብረ-አበሮቻቸውና በመንግስት ሹማምንት ከተገለፀ በኋላ “…የመለስን ራዕይ እናስቀጥላለን!” የሚል መፈክር መሰማት ጀመረ፤የተባለው ራዕይ ኑዛዜ አሁንም ባያበቃም፡፡
በርግጥ አቶ መለስ ራዕይ ነበራቸው ከተባለ፤ እስከ ህልፈታቸው ድረስ የትኛውንም መንገድ ተጠቅመው ከቤተመንግስት ሳይወጡ ተቀናቃኞቻቸውን በማሰርና በማጥፋት በስልጣን መቆየት ነው፡፡ ነበራቸው የተባለው ራዕይ አሳቸው ሲሞቱ አብሮ ሞቷል፡፡ ይህ ደግሞ ራዕይ ሳይሆን የስልጣን ጥም እንጂ ህዝባዊና ሀገራዊ አይደለም፡፡ ተከታዮቻቸውም እናስቀጥላለን ያሉት ይህንኑ በመሆኑ ልክ እንደሳቸው ተመሳሳይ ድርጊት መፈፀሙትን እንደ ትክክለኛ እና ቅዱስ ተግባር ማከናወን ጀመሩ፡፡ ለአብነትም መጪውን ምርጫ 2007 ዓ.ም. ተከትሎ ለኢህአዴግና አመራሮቹ ስልጣን ማክተሚያ ምክንያት ይሆናሉ ብለው ያሰቧቸውን ማጥመድ፣ ማሰርና መፈረጁን ተያያዙት፡፡ የዚህ ሰለባ ከሆኑት መካከል በሚያዝያ 2006 ዓ.ም. መጨረሻ አካባቢ ጋዜጠኛ አስማማው ኃይለጊዮርጊስ፣ ጋዜጠኛ ተስፋዓለም ወልደየስ፣ ጋዜጠኛ ኤዶም ካሳዬና ጋዜጠኛ አዚዛ መሐመድ፤ እንዲሁም የኢትዮጵያው ዞን 9 ብሎገሮች በፈቃዱ ኃይሉ፣ዘለዓለም ክብረት፣ አቤል ዋበላ፣ ማህሌት ፋንታሁን፣አጥናፍ ብርሃኔ እና ናትናኤል ፈለቀ ቀዳሚዎቹ ናቸው፡፡
በ2004ዓ.ም. ዛሬም ድረስ ምላሽ እንዳላገኘ የሚነገርለት የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ጥያቄ ጋር በተያያዘ የሙስሊሙ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት፣ጋዜጠኛ ዩሱፍ ጌታቸውና ጋዜጠኛ ሰለሞን ከበደ ታስረው እስካሁን በወህኒ ቤት ይገኛሉ፡፡ ምንም እንኳ ጉዳያቸው በፍርድ ቤት የተያዘ ቢሆንም እስካሁን ብይንም ሆነ እልባት አላገኘም፡፡ ይሄ ሁሉ በአቶ መለስ አገዛዝ ዘመን የተጀመረ እስር ነው፡፡
በመቀጠልም በሀገር ውስጥ የኢህአዴግ መንግስት እውቅና ያልተቸረውና በሽብርተኝነት የተፈረጀው የግንቦት 7 የፖለቲካ ማኀበር ዋና ፀሐፊ የነበሩት አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ በየመን ፀጥታ ኃይሎች ታግተው ለኢትዮጵያው ገዥ ተላልፈው ተሰጥተዋል፡፡ አቶ አንዳርጋቸው ቀደም ሲል የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ አድርጋችኋል በሚል በነ ጄነራል ተፈራ ማሞ ክስ መዝገብ ከነ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ጋር በሌሉበት የሞት ፍርድ ተፈርዶባቸውል፡፡ የሞት ፍርድ ተፍርዶባቸው የነበሩት አቶ አንዳርጋቸው እንደገና በ2005 ዓ.ም. ደግሞ በነ አንዱኣለም አራጌና ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ክስ በሌሉበት የዕድሜ ልክ ፅኑ እስራት ተፈርዶባቸዋል፡፡ ይሁን አንጂ ወደፊት ትናው ክስ ተፈፃሚ እንደሚሆንና በቀጣይ ስለሚኖረው የፍርድ ሂደት ዕድሜ ከሰጠን አብረን የምናየው ነው ሚሆነው፡፡
ከላይ የተጠቀሰው እንዳለ እስሩ ተጠናክሮ በመቀጠል በሀገር ውስጥ በገዥው ስርዓት ህጋዊ እውቅና ተችሯቸው የሚንቀሳቀሱየፖለቲካ ፓርቲ ወጣት አመራሮች ተለቅመው ታሰሩ፡፡ እነኚህም መካከል በማኀበራዊ ሚዲያ የተለያዩ በሳል ፅሑፎችን በመፃፍ የሚታወቀው፣ የመቀሌ ዩኒቨርስቲ መምህርና የዓረና ትግራይ/መድረክ አመራር አቶ አብርሃ ደስታ፤ ከአንድነት ፓርቲ አመራሮች አቶ ሀብታሙ አያሌውና አቶ ዳንኤል ሺበሺ እንዲሁም ከሰማያዊ ፓርቲ አቶ የሺዋስ አሰፋ ይገኙበታል፡፡አራቱም ወጣት ፖለቲከኞች በፓርቲያቸውም ይሁን በሀገሪቱ ሰለማዊ የፖለቲካ ትግል በጎ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች መሆናቸው ይነገርላቸዋል፡፡
ሌላው እየተወሰደ ያለውን እስር በመሸሽ ከምርጫ 1997 ዓ.ም. ወዲህ ከ2005 ዓ.ም.ጀምሮ እስከ ያዝነው 2006 ዓ.ም. ድረስ ኢትዮጵያውያን ጋዜጠኞች ተሰደዋል፡፡ ለዚህም በዋነኝነት እንደ አስረጂ ሊጠቀስ የሚችለው በአሁን ሰዓት በጅምላ እየተፈፀመ ያለው እስር ነው፡፡ በአቶ መለስ ዜናዊ የስልጣን ዘመን የተጀመረው የጋዜጠኞችና ብሎገሮች እስር በአሁን ወቅት ሶስት የውጭ ዜጎችን ጨምሮ 20 የደረሰ ሲሆን፤ ከላይ በስም ከተጠቀሱት የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች በተጨማሪ በርካታ የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ ማኀበር አባላትም በእስር ላይ ይገኛሉ፡፡ ይሄ ደግሞ ዴሞክራሲያዊ መብቶች ዝግ ከነበሩበት የደርግ ጊዜ ጋር ሲነፃፀር፤ በኢህአዴግ ጊዜ 20 ጋዜጠኞችና ብሎገሮችን በማሰር በሀገሪቱ ታሪክ ቀዳሚውን አሉታዊ ስፍራ እንድይዝ ያደርገዋል፡፡ በዚህም በፀታ ኃይሉና በፍትህ ተቋማቱ ላይ ተጨማሪ የስራ ጫና ከመፍጠር በዘለለ የታሰበውን የፖለቲካ ትርፍ ያስገኛል ተብሎ አይጠበቅም፡፡
እንደ ገዥው ስርዓት አመራሮች፣ ደጋፊዎችና የፀጥታ ኃይሎች ገለፃ ከሆነ እስሩ የሚቆም አይደለም፡፡ በቀጣይ የዚህ ሰለባ ማን እንደሚሆን ባይታወቅም፤ እንደተባለው የሚተገበር ከሆነ በድጋሚ ቀሪ ጋዜጠኞች እና ፖለቲካኖች የእስር ስለባው ሊሆኑ እንደሚችሉ አያጠያይቅም፡፡ ምክንያቱም ከሌላው በተሻለ መብቶቻቸውን እየተገበሩና እየተጠቀሙ ማኀበረሰቡ ላይ በጎ ተፅዕኖ በመፍጠር የስርዓቱ ስልጣን ፈተና ይተረጎማሉና፡፡ አቶ መለስ ከመሞታቸው በፊት ምርጫ ሲደርስና ለስልጣናቸው የሚያሰጋቸው ነገር ብልጭ ሲልባቸው የሚወስዷቸው ርምጃዎች አሁን በስልጣን ላይ ባሉ ተከታዮቻቸው ተጠናክረው መቀጠላቸው አንዱ የመለስ ራዕይ ነው ሊያስብል ይችላል፡፡ ይህም አመራሮቹ እናስቀጥለዋለን ያሉት የአቶ መለስ ራዕይ አንዱ አካል ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ ምክንያቱም ያኔ በሳቸው ዘመን የተጀመረው ዛሬም በቃ ሊባልና መቋጫ ሊበጅለት አልቻለምና፡፡
አሁን በመንግስት አመራሮች ኢትዮጵያውያን ጋዜጠኞች፣ ብሎገሮችና ፖለቲካኞች ላይ ትኩረት ያደረገ የእስር ዘመቻ ከዚህ በፊት እንደ ተወዳጅ ነጠላ ዜማ ሲዜም የነበረውን “የመለስን ራዕይ እናስቀጥላለን” አባባል የሚታየው የእስር ዘመቻ መሆኑን በማሳበቅ በደጋፊዎቻቸው እንደ ሊቀ ሊቃውንትና ባለራዕይ የተወሰዱት ሟቹ ሰውዬ እንዲኮነኑ ማድረጉ አይቀርም፡፡ በየትኛውም ዓለም እንደሚታየው የፖለቲካ ርምጃና ተሞክሮ ሰዎችን ያውም ዜጎችን አሸባሪ ብሎ ማሰር በስልጣን ለመቆየትም ሆነ ለመረጋጋት መፍትሄ ሊሆን አይችልም፡፡ እንዲህ ዓይነት ርምጅ መፍትሔ ቢሆን ኖሮ የሊቢያው መሪ ኮሎኔል ሙዓመር ጋዳፊ፣ የግብፁ ሆስኒ ሙባረክ፣የየመኑ ዓሊ አብደላ ሳላህ በስልጣን ላይ መቆየት በቻሉ ነበር፤ግን አልሆነም፡፡
ነገርን ግን የህዝቡን ቁጣ በመቀስቀስ በውርደት ከስልጣን እንዲወርዱ አስገደዳቸው እንጂ መፍትሄ አልሆናቸውም፡፡ ስለዚህ በስልጣን ለመቆየት ጉጉቱ ካለ እንኳ የዜጎችን መብት፣ፍላጎትና ጥቅም ማክበርና ማስጠበቅ የተሻለ አማራጭ ነው፡፡ መፍትሔውን ልክ እንደ ጥሎ ማለፍና ፍፃሜ የአትሌቲክስ ውድድር ዜጎችን በማሰርና እንዲሰደዱ በማድረግ ዙሩን ማክረር ታምቆ የቆየውን የህዝብን ስሜት ባልተጠበቀ ሰዓት እንዲፈነዳ በማድረግ ሌላ ችግር ሊወልድ ይችላል፡፡የሚፈራው ችግር የሚከሰት ከሆነ ደግሞ የበለጠ ለገዥዎችም፣ ለህቡም ሆነ ለሀገሪቱ አሉታዊ ተፅዕኖ ማስከተሉ እሙን ነው፡፡
የኢትዮጵያ እውነታ እና ቀጣይ ዕጣ ፈንታ
ብስራት ወልደሚካኤል
afrosonb@gmail.com
ኢትዮጵያን በገሃዱ ዓለም ላያትና በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ለተመለከታት እራሱን በሁለት የተለያየ ዓለም ውስጥ ሆኖ ያገኘዋል፡፡ ለዚህም በኢቴቪ የሚመለከቷት ኢትዮጵያ አረንጓዴ፣ ለምለም የጥጋብ ምድር፣ የህዝቡን ኑሮ እየቀየሩ ያሉ የተንቆጠቆጡ ህንፃዎች፣ መንግስት በፈጠረላቸው ምቹ ሁኔታ የበለፀጉ ምንዱባንን፣የተለያዩ በስኬት በተጠናቀቁ የልማት ፕሮጀክቶች የሚደሰቱ ነዋሪዎች፣የገዥው ፓርቲ ታታሪነትና የሌሎች ተፎካካሪ ፓርቲዎች ድክመት፣…ይመለከታሉ፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፤ ኢትዮጵያዊነት ሁሉ ፈተና ውስጥ የገባበት ዓይነት ሁኔታንም መመልከት እተለመደ መጥቷል፡፡
በገሃዱ ዓለም ያለው ትክክለኛው ኢትዮጵያ እውነታን ለተመለከተና እየተመለከተ ላለ ከላይ ከተጠቀሰው በእጅጉ ይለያል፡፡ ምንም እንኳ አብዛኞቹ የህንፃ ባለቤቶች የገዥው ስርዓት ቁንጮዎች፤ በተለይ በአዲስ አበባ የህወሓት ቁልፍ ሰዎች ንብረት ሲሆን አልፎ አልፎ ግን የስርዓቱ ታማኝ እና የነባር ነጋዴዎችም ህንፃ መኖሩ ባይካድም፡፡ የሀገሪቱም የኑሮ ምቾትና ዕድገት እየተለካ ያለውም የህዝብን ሀብት በሙስና በሚበዘብዙ ባለስልጣናትና ከላይ በተጠቀሱ ነጋዴዎች ልኬት ነው፡፡
በተለይም አሁን ያለውን የአብዛኛውን ኢትዮጵያዊ ነባራዊ ሁኔታ የተመለከትን እንደሆነ፤ በህልም ዓለም ተስፋ ውስጥ የሚዋኝ አካልን መመልከት አዲሰ አይደለም፤ ብሩ ቀንን በመናፈቅ፡፡ ከዛ ውጭ በስደት ዓለም ባሉ ቤተሰቦቻቸው ድጎማ ህይወታቸውንእያቆዩ ያሉትን እንደ ዕድለኛ በመቁጠር፡፡በርግጥ የመንገድ መሰረተልማት ጥገናዎች እየተከናወኑ ነው፤ አንድ ፖለቲካና ኢኮኖሚ ጠንካራ ማኀበረሰብ የመመስረት የፍቅር መንገድ ባይገነባም ቀድሞየነበረውን ፍቅርና አንድነት ለማፍረስ የሚወጣው ወጪ፣የሚባክነው ጊዜና ጉልበት ሲሰላ ብዙ ውጤታማ የማኀበረሰብ አገልግሎት ፕሮጀክቶችን መገንባት ይቻል ነበር፡፡
ቀሪው የኢትዮጵያ ህዝብ ግን ተሻለ ቀንን በጨለመ ተስፋ ውስጥ ሆኖ፤ ግማሹ በአስከፊው የሞት መንገድ የእግር ስደትን ምርጫው አድርጓል፡፡ በእግር ከሚሰደዱት ደግሞ ብዙዎቹ መንገድ ላይ ህይወታቸው ሲያልፍ፣ የቀሩት ግን እጅግ ከዘግናኝ ፈተና በኋላ ያሰቡበት ይደርሳሉ፡፡ የUNCHR መረጃዎች እና የተለያዩ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከሆነ፤እያየሁ ከምሞት በተስፋ እየተጓዝኩ ልሙት በሚል ምሬት አሁንም የስደተኞች ቁጥር በእጅጉን ጨምሯል፡፡ በየሄዱበት ሀገርም ጥገኝነት ከመጠየቅ ለዘመናት ያለምንም ስራ ፈቃድ ተደብቆ ቀናትን እስከማሳለፍ ድረስ፡፡ የዚህ ሁሉ መሰረቱ ደግሞ ያለው የፖለቲካ ስርዓት ውጤት መሆኑ ከማንም የሚደበቅ አይደለም፡፡ በአሁን ሰዓት በሀገሪቱ በተለያየ አቅጣጫዎች ቀን የሚጠብቁ የታመቁ ስሜቶች በስፋት እየተስተዋሉ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት በመላ ሀገሪቱ ከፍተኛ ውጥረት እየተፈጠረ ሲሆን ፤ከወዲሁ በሁሉም ባለድርሻ አካል መፍትሄ ካልተበጀለት ነገ ምን ሊፈጠር እንደሚችል ደግሞ ከወዲሁ መገመት አያስቸግርም፡፡ በተለይ የማኀበራዊ፣ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ቀውሶች ተባብሰው መቀጠላቸው ችግሮችን የበለጠ ውስብስብ አድርጎታል፡፡
ማኀበራዊ ሁኔታ
በአሁን ወቅት በተለያየ የሀገሪቱ አካባቢ የማኀበራዊ ቀውስ ችግሮች ይታያለሁ፡፡ ከነዚህም መካከል ዜጎች የመኖሪያ ቤትም ሆነ የመኖሪያ ቤት የመስሪያ ቦታን ለማግኘት እንደድሮ ኢትዮጵያዊ ዜግነት መኖር ብቻውን በቂ አይደለም፡፡ ከዜግነት ይልቅ የገዥው ፓርቲ አባል ወይንም ዋነኛ ደገፊ መሆን ይጠበቅበታል፡፡ አለበለዚያ መሬት የመንግስት ነው በሚል ፈሊጥ መንግስት ማን እንደሆነ እንኳ ለመለየት አስቸጋሪ በሆነበት በዚህ ወቅት እጅግ ውድ በሆነ የሊዝ (የመሬት ኪራይ) ክፍያ ማዘጋጀትን ይጠይቃል፤ይሄ ደግሞ ሀገር ውስጥ ለሚኳትን ኢትዮጵያዊ በቀላሉ የሚሞከር አይደለም፡፡
ከመጠለያ በመቀጠል የጤና ዋስትና ጉዳይም እንዲሁ ከዕለት ወደዕለት እየተባባሰ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ዋነኛ ምክንያት የባለሙያዎች ለህዝቡ ያላቸው ተደራሽነት አነስተኛ መሆን እና በሙያው በቂ ክህሎትአለመኖር፣ በበቂ ሁኔታ የህክምና ቁሳቁስ በየህዝብ ህክምና ተቋማት በበቂ ሁኔታ አለመኖር ዋነኛው ችግር ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ሐኪሞች በሙያቸው ከተመረቁ በኋላ ለሚሰጡት አገልግሎት ተመጣጣን ክፍያ አለማግኘት ፣ በጤና ተቋማት በቂ የውሃ፣ የመብራትና ተያያዥ ግብዓቶች በበቂ ሁኔታ አለመኖር ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ እነኝህ ችግሮች እያሉ እንኳ መንግስት በጤና ሽፋን እና አገልግሎት ውጤታማ ነኝ ይላል፡፡ እውነታው ግን በየጊዜው ከህክምና ጋር በሚፈጠሩ ችግሮች የሚሞቱ ህፃናትና እናቶችን ቁጥር ቀንሰናል በሚል የመረጃ መጋገር በስተቀር ችግሩ አሁንም እንዳለ ነው፡፡
በየቀበሌው የተለያዩ አነስተኛ የጤናአገልግሎት መስጫ ተቋማት መገንባታቸው በአዎንታዊ ጎን የሚታይ ቢሆንም፤ ከቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት በስተቀር አገልግሎት ሰጪ ባለሙያዎች ላይ እና የህክምና መገልገያ መሳሪያዎች ላይ በቀላሉ መሻሻል የሚገባቸው በርካታ ችግሮች ይስተዋላሉ፡፡ በዕርዳታ የመጡ የህክምና መገልገያ ማሽኖች እንኳ ገና ስራ ሳይጀምሩ ተበላሽተዋል ተብለው የትና መቼ እንዲሁም ለማን አገልግሎት እንደሚሰጡ የማይታወቅበት ደረጃ ላይ ተደርሷል፡፡ ለዚህም በሀገሪቱ ትልቁ ሆስፒታል ጥቁር አንበሳ የነበሩ የኩላሊት ማጠበያ ማሽን፣ የካንሰር ምርመራ እና ህክምና ፣ ፊዚዮቴራፒ እና ሲቲስካን የት እንዳሉ አይታወቁም፤ ዜጎች ግን በከፍተኛ ወጪ ወደ ውጭ ሀገር ሄደው ይታከማሉ፤አቅሙ የሌላቸው ደግሞ መኖር አየቻሉ ህይወታቸው ያልፋል፡፡ ደረጃቸውን የጠበቁና የአገልግሎት መቆያ ጊዜያቸውተጠበቀ መድኃኒቶች አለመኖርና አገልግሎት ጊዜያቸው ያለፈባቸው ምንም ለማያውቁ ታካሚዎች እየተሸጠ መሆኑም ሌላው ራስ ምታት ነው፡፡
የኃይማኖት ነፃነት ማጣት ጉዳይም በሰፊው እየታየ ያለ አንዱ የማኀበራዊ ቀውስ ክስተት ነው፡፡ ለዚህም በኢትዮጵያ ሙስሊሞች እና ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ክርስቲያኖች ላይ በተደጋጋሚ እየተፈፀመ ያለው የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ሀገሪቱን ውጥረት ውስጥ መክተቱ አልቀረም፡፡ በተለይ ገዥው ስርዓት በሁሉም ኃይማኖቶች መሪዎች የኢህአዴግ ሰዎች እንዲሆኑለማድረግ የሚያደርገው እንቅስቃሴ ከኃይማኖቱ ተካታዮች ቅሬታ ቢፈጥርምይህንን በግልፅ ተቃውሞ የጀመሩት ግን ሙስሊሞች ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ ተያያዥ ችግሮች እስካሁን ችግሩ አልተፈቱም፤በተለይ የሙስሊሙ ማበረሰብ ጥያቄው ባለመመለሱ ተቃውሞውእንደቀጠለ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ ጭራሽ ከመንግስት የማይጠበቅ ሙስሊሙን እና ክርስቲያኑን ሊያጋጩ የሚችሉ እንደ “ጅሃዳዊ ሃረካት” የመሳሰሉ የተለያዩ ዘጋፊ ፊልሞች ተሰርተው በኢቴቪ በመሰራጨት ህዝቡን ስጋት ውስጥ ቢጥሉም፤ በክርስት እና በእስልምና ኃይማኖት ተከታዮች መካከል የነበረውን ኢትዮጵያዊ አንድነት ለመፈታተን እየተሞከረ ይገኛል፡፡ ምንም እንኳ በኃይማኖቱ ተከታዮች ተቀባይነት ባይኖረውም፡፡
የትምህርት ጥራት በተለይም እንደቀድሞው በሀገር አቀፍም ሆነ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ የሆኑ ተማሪዎችን የማፍራት ዕድሉ ቢኖርም ስርዓቱ በዘርፉ የሚከተለው ፖሊሲ እውን ሊያደርግ አልቻለም፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በየከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የአካዳሚክ ነፃነት መጥፋት እና በማስተማርም ሆነ በአስተዳደራዊው ዘርፍ የስርዓቱ ታማኞች ብቻ እንዲኖሩ የሚደረገው ጥረት ደግሞ የትምህርት ጥራቱን በመጉዳቱ የሚፈለገውን ውጤታማ የተማረ ኃይል ማፍራት እንደሎተሪ የሚቆጠርበት ጊዜ ተደርሷል፡፡ በዚህም ምክንያት ለዓመታት ለፍተው በየዓመቱ ከተለያዩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚመረቁ ተማሪዎች ስራ አጥ ሆነው መኳተናቸው እና ለድንጋይ ጠረባ መታጨታቸው ፖሊሲውና ስርዓቱ የፈጠሩት ችግር ለመሆኑ ምስክር አያሻም፡፡
በሀገሪቱ ያለው የኑሮ ውድነት በተለይም የምግብ ዋጋ መናር፣በቂ የትራንስፖርት አገልግሎት አለመኖር፣ የውሃ፣ መብራት እናየስልክተደጋጋሚ መቋረጥ እና ተደራሽነት በአግባቡ አለመኖር ሌላው ችግር ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ዜጎች እርስ በርስ በችግሮቻቸው ዙሪያ እንኳ እንዳይወያዩ እና መፍትሄ እንዳያበጁ አንድ ለአምስት በሚል ሁሉም ዜጋ በኢህአዴግ ጥብቅ ቁጥጥር ስር እንዲሆን ተደርጓል፤ እየተደረገም ነው፡፡ ዕድሮችና የኃይማኖት ተቋማት ከማኀበራዊ አገልግሎት ይልቅ የገዥው ስርዓት ፖለቲካ ማራመጃ እስከመሆን በመድረሳቸው የተቋቋሙለትን ዓላማ በመሳት ህዝባዊ አመኔታ በማሳጣት እና ጥርጣሬ በመፍጠር ዜጎችን እሴት አልባ የማድረግ ማኀበራዊ ቀውስ ተፈጥሯል፡፡
የኢኮኖሚ ሁኔታ
የሀገሪቱ የንግድ ስርዓትና ገበያ በጥቂት ግለሰቦች እና ድርጅቶች በመውደቁ የኢኮኖሚውን መስክ አደጋ ላይ ጥሎታል፡፡ እዚህ ላይ ትውልደ ኢትዮጵያዊ በዜግነት ግን ሳውዲዓረቢያዊ የሆኑትሼህ መሐመድ ሁሴን አሊ ዓላሙዲን ብንመለከት የኢህአዴግ ቀኝ እጅ ሲሆኑ፤ ከሀገሪቱ ባንክ ከፍተኛው ብድር የተሰጣቸው ግለሰብም ናቸው፡፡ይሁን እንጂ በግለሰብ ደረጃ በርካታ ቦታዎችንና የተፈጥሮ ሃብቶችን ሆን ተብሎ ከዜጎች ተነጥቆ ግለሰቡ በሞኖፖል እንዲዙ ተደርጓል፡፡ ነገር ግን ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በብድር መልክ የወሰዱትን ከፍተና ብድር በአግባቡና በወቅቱ እንዳልመለሱ ቢነገርም የተወሰደ እርምጃ ግን የለም፡፡
ሌሎች ከስርዓቱ ጋር ድንገት ብቅ ያሉ በተለይ የህወሓት ልዩ ጥበቃና ድጋፍ የሚደረግላቸው በርካታ ግለሰቦችም ድንገት ከሰማይ እንደወረደ የተሰጣቸው ምንጩ ባልታወቀ ሃብት በአንዴ የህዝብን ኑሮ በመፈታተን የኢኮኖሚ ቀውስ እንዲፈጠር ዋነኛ ምክንያት ሆነዋል፡፡
በድርጅት ደረጃ የተመለከትን እንደሆነ ደግሞ የገዥው ኢህአዴግ የንግድ ድርጅቶች የሆኑት የህወሓቱ ኤፈርት፣ የኦህዴዱ ዲንሾ፣ የብአዴኑ ጥረት እና የደኢህዴኑ ወንዶ የተባሉ ግዙፍ የንግድ ኩባንያዎች የሀገሪቱን የገበያ ስርዓት በማወክ ከዚህ ቀደም ዜጎች በአግባቡ ሲያገለግሉ ነበሩና የተረጋጋ የንግድ ስርዓት የፈጠሩት በርካታ ነጋዴዎች ከገበያ ውጭ እንዲሆኑ ተደርጓል፡፡ ነባር ነጋዴዎችም ከስርዓቱ የንግድ እና የግብር ኢፍትሃዊ ስርዓት በመሸሽ በደቡብ ሱዳን፣ በደቡብ አፍሪካ እና በዱባይ ገንዘባቸውን ማንቀሳቀስ መጀመራቸው የውጭ ባለሃብቶችስ በኢትዮጵያ እንዴት ደፍረው ኢንቨስት ሊያደርጉ እንደሚችሉ ለመገመት ያስቸግራል፡፡
በአነስተኛና መካከለኛ ንግድ የተሰማሩ ግለሰቦች ላ ደግሞ ስርዓቱ የራሴ የሚላቸውን ሰዎች ለማሳደግ ሲል እጅግ የማይመጣጠን ከፍተኛ ግብር በመጣል ከገበያ ውጭ እንዲሆኑ እየተደረገ ሲሆን፤ ችግሩን ተቋቁመው የሚሰሩትም የደህንነት ስጋት እንደተጋረጠባቸው ይነገራል፡፡ በዚህም ነጋዴው በራሱ ላይ የሚፈጠረውን ችግር በቀጥታ ወደ ሸማቹ ህብረተሰብ ማውረዱ አልቀረም፡፡
በተለይ በአሁን ወቅት እጅግ ፈተኛ በሆነ ወቅት ከዓለም ገበያ ዋጋ ጋር ባልተመጣጠነ መልኩ ከጎረቤት ሱዳን በቅርብ ርቀት ተጉዞ የሚመጣው ነዳጅ በየጊዜው ከፍተኛ የዋጋ እየተደረገ ሲሆን ፤ይህም በቀጥታ የሀገሪቱ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ላይ የራሱ የሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳርፏል፡፡ መንግስት ነዳጅ ላይ ለረጅም ዘመናት ሲደረግ የነበረውን ድጎማ ከማንሳቱ በተጨማሪ ሌላ ዋጋ መጨመሩ እስካሁን እንቆቅልሽ ሆኗል፡፡ በተለይ በአዲስ አበባ በአንበሳ የከተማ አውቶብስ ላይ እንኳ በአንዴ እስከ 25 ሳንቲም ጭማሪ ተደርጓል፡፡ በቤት ፍጆታ፣ በአገር አቋራጭ፣ በጭነት እና በከተማ የታክሲ አገልግሎት ላይ ከፍተኛ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ደግሞ ሌላው ችግር ነው፡፡
የሸቀጦች ዋጋ በየጊዜው መጨመር ደግሞ የበለጠ በኢትዮጵያ ላይ መኖር እጅግ ከባድ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ የነኚህ ድምር ውጤት በመላ ሀገሪቱ ላይ ከፍተኛ የኢኮኖሚ አለመረጋጋትን ፈጥሯል፡፡ በዚህም ምክንያት ዜጎች በቀን አንዴ መመገብን እንደመልካም አጋጣሚ የሚቆጥሩ ዜጎች መኖራቸው ሀገሪቱ በገሃዱ ዓለም ወዴት እየሄደች እንደሆነ ለማወቅ የግድ ሊቅ መሆንን አይጠይቅም፡፡ በተለይ እ.አ.አ.በ2013 ዓለም አቀፍ ጥናቶች እንሳታወቁት ከሆነ፤ዜጎቿ በቂ እና የተመጣጠነ ምግብ ከማያገኙ የዓለም ሀገሮች መካከል ኢትዮጵያውያ አንዲትን ሀገር ብቻ በመቅደም የመጨረሻ ደረጃ ላይ የምትገኝ አድርጓታል፡፡ ስለዚህ በምግብ እንኳ ዜጎች እራሳቸውን እንዲችሉ እየተደረገ ያለው አሰራር በ23 ዓመታት እንኳ ውጤታማ አለመሆኑ ዋነኛ የፖሊሲ ችግር መሆኑን ያመላክታል፡፡
የፖለቲካ አለመረጋጋት
ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ሞት በኋላ በገዥው ስርዓት ባሉ ፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል አለመረጋጋትመፈጠሩ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ መንገድ ዜጎችም በፖለቲካ ህይወታቸው እንዳይረጋጉ መደረጉ ሀገሪቱን ከድጡ ወደማጡ ወስዶታል፡፡ ይህን ተከትሎ የገዥው አመራሮች ተፎካካሪያቸውም ላይ ሆነ ችግሮቻቸውን የሚናገሩትን እንደጠላት በመቁጠር የነበረውን አለመረጋጋት ይበልጥ አባብሶታል፡፡ በአሁን ሰዓት አይታወቅም፤አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ የጠቅላይ ሚኒስትርነቱን መንበር ቢቆናጠጡም፤ በተግባር ሀገሪቱን በትክክልም ማን እየመራት እንደሆነ በርግጠኝነት መናገር ይከብዳል፡፡ በዚህም ስርዓቱ ወይም መለኮት አሊያም አየር እስኪመስል ድረስ ሁለት እና ከዛ በላይ ሆናችሁ በምታደርጉት እንቅስቃሴ ሁሉ እኔም እገኛለሁ/መገኘት አለብኝ ዓይነት አስተሳሰብ ተፀናውቶት ዜጎችን መፈናፈኛ አሳጥቷቸዋል፡፡ ይሄም በኢትዮጵያ ሌላ ዘግናኝና የአፈና ስርዓት መንገሱን ያሳያል፡፡
ስርዓቱን የሚዘውሩትም ቢሆኑ መሰረታቸውበጠባብ ፖለቲካዊ ዘረኝነት ቡድን ላይ የተንጠለጠለ በመሆኑ፤በተለይ ወጣቶች በሀገር አቀፍም ሆነ በዓለም አቀፍ እንኳ ተወዳዳሪ ሆነው እንዳይታዩ በቅድሚያ በዘርና በቋንቋ በመከፋፈል የኢትዮጵያዊነት ስነልቦናውንጎድተውታል፡፡ በዚህም ምክንያት ወጣቱ እራሱን አጥብቦ በብሔር ስም በጠባብ ወሰን ውስጥ እንዲቀር በማድረጉ ተወዳዳሪ መሆን ያልቻሉ በርካታ ወጣቶች ቢመረቁም አብዛኞቹ ስራ አጥ ናቸው፡፡ ከዚህ በተቃራኒ ደግሞ የስርዓቱ ጠባቂና አቀንቃኝ አንድ የወረዳ አስተዳደር ከውሎ አበል ውጭ እስከ 4,000 ብር ወርሃዊ ደመወዝ ሲከፈለው ለበርካታ ዓመታት ተምሮ ዜጎችን የሚቀርፅ አንድ ፕሮፌሰር ደመወዝ ደግሞ ያለምንም የቀን ውሎ አበል ወርሃዊ ደመወዙ ከ5,000 ብር አይበልጥም፡፡ 7 ዓመታትን በትምህርት ያሳለፉ የህክምና ተማሪዎችም ያለምንም ውሎ አበል ወርሃዊ ደመወዛቸው በአማካይ ከ3,000 ብር አይበልጥም፡፡
በተለይ በአሁን ወቅት ኢትዮጵያውያን የህክምና ዶክተሮች ከ4,400 እንደማይበልጡ፤ ከነዚህም ውስጥ በሀገር ውስጥ ለ90 ሚሊዮን ህዝብ አገልግሎት እየሰጡ ያሉት ከ700 እንደማይበልጡ ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡ ቀሪዎቹ 3,700 ዶክተሮች የፖለቲካውና በኢኮኖሚው ጫና ምክንያት በስደት እየኖሩ ይገኛሉ፡፡
ዜጎች በፖለቲካዊ አመለካከታቸው አሸባሪ የሚል ቅፅል ስም እየተሰጣቸው በእስር የሚማቅቁ በርካቶች ሲሆኑ፤ የወጣቶች ቁጥር ደግሞ አብላጫውን አሀዝ ይይዛል፡፡ በዚህም ምክንያት ብልሹ አሰራርን እና በዜጎች መካከል የሚፈጠር አድሎዓዊ አሰራርን የሚቃወሙ፣ በህግ የተሰጠ እና ተፈጥሯዊ መብቶች ለዜጎች እንዲከበሩ አበክረው የሚጠይቁና የጠየቁ ፖለቲከኞችና ጋዜጠኞች ለእስር ተዳርገዋል፡፡ ከነዚህም መካከል ከጋዜጠኞች እስክንድር ነጋ፣ ውብሸት ታዬ፣ ርዕዮት ዓለሙ፣ ሰለሞን ከበደ እና ዩሱፍ ጌታቸውን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ከፖለቲከኞች ደግሞ አንዱዓለም አራጌ፣ በቀለ ገርባ (የእስር ጊዜው ቢጠናቀቅም እስካሁን ያልተፈታ)፣ ናትናኤል መኮንን፣ ኦልባና ሌሊሳን በጥቂቱ ማንሳት ይቻላል፡፡
በቅርቡ ደግሞ መጪውን ምርጫ 2007ዓ.ም. ታሳቢ በማድረግ በሰፊው የነፃውፕሬስ ጋዜጠኞችን እና ፖለቲካኞችን ለማሰር አሊያም ለመወንጀል በህዝብ ግብር በሚተዳደሩ መገናኛ ብዙኃን ማስፈራሪያውና ዛቻው ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ በሌላው የዓለም ሀገር የህዝባዊ አስተዳደር ምርጫ የሚደረገው ህዝቡ የሀገሪቱ ከፍተኛ የስልጣን ባለቤቱ መሆኑን ከማረጋገጥ ባለፈ የዜጎችን እስር፣ ግድያ ስደትና ጭንቀት ለመቀነስ ነው፡፡ በአንፃሩ በኢትዮጵያ ምርጫ ሲመጣ ደግሞ በተለይ በገዥው ፓርቲ የሚፈፀም እስር፣ ግድያ፣ ስደት እና ጭንቀት ከሌሎች ግዚያቶች በበለጠ ተጠናክሮ የሚቀጥልበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ለዚህም ከሰሞኑ በገዥው አመራሮችና ዋነኛ የጥቅም ተጋሪ ደጋፊዎቻቸው በአደባባይ የሌለውን እና ያልተፈጠረውን የቀለም አብዮት በሚል ዲስኩር የሚፈፀሙ ማስፈራሪያዎች እና ዛቻዎች ምርጫ 2007 ዓ.ም. ከመድረሱ በፊት ሊወሰድ ስለታሰበው እኩይ ተግባር አመላካች ነው፡፡ ስለዚህ ንፁሃን ዜጎች በምርጫ ወቅት በሰበብ አስባቡ የሚታሰሩ፣ የሚገደሉ፣ የሚሰደዱና የሚሰቃዩ ከሆነ ምርጫው ከገንዘብ፣ ከጊዜና ከውድ የሰው ህይወት ብክነት በስተቀር አስፈላጊነት አጠያያቂ ነው፡፡
ከላይ በተጠቀሱት ምክንያቶች በመላ ሀገሪቱ አሁን ያለው የፖለቲካ ድባብ እጅግ ውጥረት የበዛበት፣ ያልተረጋጋና እና አስፈሪ ሁኔታ መኖሩን ከማመላከት በተጨማሪ፤ በገዥው ፓርቲ ባሉ አመራሮች መካከልየራስ መተማመን ስሜት አለመኖሩን እና እርስ በርስ እንኳ አለመተማመን እና አለመረጋጋትንም ያሳያል፡፡ በዚህም ምክንያት በአራቱም የሀገሪቱ አቅጣጫዎች የሰላማዊ የፖለቲካ ትግሉ ታፍኗል በሚል ወደ ትጥቅ ትግል የገቡ አልታጡም፡፡ ለዚህም የትግራዩ ትህዴን፣የአፋሩ አርዱፍ፣ የኦሮሚያው ኦነግ፣ የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሉ ኦብነግ፣በደቡብ የሲዳማው ሲአግ፣ በጋምቤላ እና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ያሉትን እና ሌሎች ሀገር አቀፍ የትጥቅ ትግል የሚያደርጉ እንደነ አርበኞች ግንባር እና ግንቦት ሰባትን ማንሳት ይቻላል፡፡
በአጠቃላይ ከሐረሪ ክልል፣ ከድሬዳዋ እና አዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር በስተቀር በሁሉም የሀገሪቱ ክልሎች የትጥቅ ትግል እየተደረገ ይገኛል፡፡ የዚህ ሁሉ መነሻው ደግሞ በሀገሪቱ ለሁሉም ዜጎች እኩል የሆነ የውድድር መድረክ አለመኖሩ፣ ህዝባዊ ነፃ የመንግስት (ዴሞክራሲያዊ) አስተዳደር አለመኖሩ፣ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች አለመከበር፣ ነፃነትና ገለልተኛ ህዝባዊ ወይም መንግስታዊ የዴሞክራሲ ተቋማት ባለመኖራቸው የተፈጠረ ነው፡፡ ምናልባት የተጠቀሱት ችግሮች አፋጣን መፍትሄ ካላገኙ እና ልክ እንደ ሱዳን ሀገሪቱ ወደ ብሔራዊ እርቅ ካልገባች ውሎ ቢያድርም የታፈነው ህዝባዊ ተቃውሞ ወደ አደባባይ አመፅ ሊቀየር ይችላል፡፡ አሁን ለው የዓለም ነባራዊ ሁኔታ ደግሞ ሰላማዊ የአደባባይ ህዝባዊ አመፁን በቀላሉ በጦር መሳሪያ ብቻ ለማቆም ቢሞከር እንኳ ካለው አስከፊ ችግር የተነሳ ህዝባዊ አመፁ ተጠናክሮ ከመቀጠል ባለፈ ሊቆም አይችልም፡፡
ሌላው በሀገሪቱ ህግ ተቋቁመው የፖለቲካ ትግል የሚያደርጉ እና እያደረጉ ያሉት ከፍተኛ ዋጋ እየከፈሉ ቢሆንም፤ እርስ በርስ ተስማምተው በሚያሰራቸውቸው አጀንዳ እንኳ አንድ ሆነው መስራት ባለመቻላቸውበሀገሪቱ እና በህዝቡ የነፃነት እንቅስቃሴ ላይ ጥቁር ጥላ ማጥላታቸው አልቀረም፡፡ ምክንያቱም በፖለቲካ ፓርቲዎች ስም በገዥው ስርዓት የሚደገፉ እንዳሉ ሆነው ለህዝብ ቆመናል የሚሉየተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶች መካከል ያለው የስልጣን ጥም በፈጠረው አለመተማመን እና ጥርጣሬ የራሳቸውንም ሆነ የተከታዮቻቸውን ዕጣ ፈንታቸው እስርና ግድያ ማድረጉ የአደባባይ ምስጢር ነውና፡፡ በአጠቃላይ አሁን ባለው የሀገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ የማይካድ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማኀበራዊ ቀውስ ተፈጥሯል፡፡ ይሄንንም ለማሻሻል ሁሉም ኢትዮጵያዊ ከእርስ በርስ ጥላቻ፣ ቂም በቀል፣ጥርጣሬና አለመተማን በመውጣት ፤ሁሉም ኢትዮጵያዊበመፈቃቀርና በመከባበር ለሁሉም ዜጋ መብትና ጥቅም በአንድነት መቆም ይኖርበታል፡፡ አለበለዚያ የህዝቡ ሰቆቃና መከራ እየቀጠለ መጪውን ጊዜ ዕጣ ፈንታ የበለጠ አስከፊና አስፈሪ ያደርገዋል፡፡