Tag Archives: TPLF/EPRDF democracy

የተቃዋሚ ፓርቲዎች አመራሮች ቅጣት ተላለፈባቸው

᎐ተጨማሪ ቅጣትም ይጠብቃቸዋል፡፡
• “እኛ የደፈርነው ችሎት አሻንጉሊት ችሎት ነው” አብርሃ ደስታ
• “ችሎቱ ላይ ያጨበጨብነው በማፌዝ ሳይሆን በምሬት ነው”  የሺዋስ አሰፋ
• “ፍትህ ተጠምተናል፣ ፍትህ ለኢትዮጵያ ህዝብ!”  ዳንኤል   ሺበሽ

politician prisoners

በዘለዓለም ወርቃገኘሁ የክስ መዝገብ የሽብር ክስ ተመስርቶባቸው ከስምንት ወራት በላይ በእስር ላይ የሚገኙት የሰማያዊ፣ የአንድነት እንዲሁም የዓረና ትግራይ ፓርቲዎች አመራሮች ‹ችሎት በመድፈር ወንጀል› ጥፋተኛ በመባላቸው ዛሬ መጋቢት 1 ቀን 2007 ዓ.ም በልደታ ከፍተኛው ፍርድ ቤት በዋለው ችሎት በሦስቱ አመራሮች ላይ እያንዳንዳቸው በሰባት ወራት እስራት እንዲቀጡ ተወስኖባቸዋል፡፡

የካቲት 26 ቀን 2007 ዓ.ም ተከሳሾች በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደተፈጸመባቸውና ንብረትም እንደተወሰደባቸው በመግለጽ አቅርበውት ለነበረው አቤቱታ ፍርድ ቤቱ የማረሚያ ቤቱን ምላሽ ሙሉ ለሙሉ በመቀበል አቤቱታቸውን ውድቅ ማድረጉን ተከትሎ 5ኛ ተከሳሽ አቶ የሺዋስ አሰፋ በማጨብጨቡና 3ኛ ተከሳሽ አብርሃ ደስታና 4ኛ ተከሳሽ አቶ ዳንኤል ሺበሽ ሳይፈቀድላቸው ‹‹ጥሩ ፍርድ፣ ጥሩ ብይን›› በማለት አቶ የሺዋስን በመደገፍ ችሎት ደፍረዋል ተብለው ጥፋተኛ መሰኘታቸው ይታወሳል፡፡ በዚህ መሰረት ፍርድ ቤቱ ለዛሬ የቅጣት ውሳኔ ለመስጠት  ተሰይሞ በአብርሃ ደስታ፣ በየሺዋስ አሰፋ እና ዳንኤል ሺበሽ ላይ የ7 ወራት እስራት በይኖባቸዋል፡፡ ሦስቱም ተከሳሾች ፍርድ ቤቱ የሰጠውን ውሳኔ በመቃወም ድጋሜ ችሎት ውስጥ አጨብጭበዋል፡፡ በዚህም ድጋሜ ጥፋተኛ ተብለዋል፤ ከሁለት ቀናት በኋላም የቅጣት ውሳኔ ይወሰንባቸዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ሦስቱ ተከሳሾች ‹‹እድል ስጡን እንናገር፣ አቤቱታም አለን ተቀበሉን›› ቢሉም ፍርድ ቤቱ ሊሰማቸው አልፈለገም፡፡

በተለይ ዳንኤል ሺበሺ ‹‹ሌላ አቤቱታ አለኝ፣ ፍርድ ቤቱ ያዳምጠኝ›› ብሏል፡፡ ፍርድ ቤቱ አሁንም ችሎቱ ላይ እያፌዛችሁ ነው በሚል ጥፋተኛ ሲላቸው ሦስቱም አመራሮች ፍርድ ቤቱን ማስፈቀድ ሳያስፈልጋቸው አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ ‹‹እኛ የደፈርነው ችሎት አሻንጉሊት ችሎት ነው፡፡ ‹Already› የተደፈረ ችሎት ነው›› ሲል አብርሃ ደስታ ተናግሯል፡፡ በዚህ ጊዜ ዳኞቹ ጣልቃ በመግባት፣ ‹‹የምትናገረው ነገር እንደገና ወደ ማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ የሚወስድህ ጉዳይ ነው፤ ምርመራ ይደረግበታል›› ሲሉ አብርሃ በበኩሉ ‹‹አሁንስ ቢሆን የምናገረውን ፖሊስ እየሰማ አይደለምን?›› ሲል መልሷል፡፡ አቶ የሺዋስ አሰፋ በበኩሉ ‹‹ከስምንት ወር በላይ ታፍነናል፡፡ በህግ አይደለም የተያዝነው፡፡ ደግሞ ማጨብጨባችን በችሎቱ ከማፌዝ ሳይሆን ከምሬት በመነጨ ነው፡፡ ህገ-መንግስታዊ  መብታችን ተጥሷል፡፡ እኔ ለምሳሌ የሰማያዊ ፓርቲ አባል በመሆኔ ነው የታሰርኩት፡፡›› ብሏል፡፡

አቶ ዳንኤል ሺበሽ ድግሞ ‹‹አሁንም ችሎት ደፍራችኋል ካላችሁ ቅጣቱን ጨምሩብንና ሸኙን፡፡ በእርግጥ ዳኞች ላይ ያለውን ጫና እንረዳለን፡፡›› ሲል ችሎት ውስጥ ተናግሯል፡፡
በዚህ ሁኔታ በተከሳሾችና በችሎቱ መካከል ያለው አለመግባባት ሲጨምር ዳኞቹ መጋቢት 3/2007 ዓ.ም ለሁለተኛ ጊዜ የቅጣት ውሳኔ እንደሚሰጥ በመጥቀስ ሦስቱ ተከሳሾች ከችሎት በፖሊስ እንዲወጡ ተደርገዋል፡፡ ከችሎት እየወጡ እያሉም አቶ ዳንኤል ሺበሽ ‹‹ፍትህ ተጠምተናል፤ ፍትህ ለኢትዮጵያ ህዝብ!›› እያለ ችሎቱን ለቅቆ ወጥቷል፡፡

በሌላ በኩል ሦስቱ ተከሳሾች ከችሎት መውጣታቸውን ተከትሎ፣ከዚህ ቀደም በማረሚያ ቤቱ ላይ በቀረበው አቤቱታ ዳኞች በሰጡት አስተያየት ላይ አቤቱታ አቅርቦ እንደነበር በማስታወስ አቤቱታው እንዲመዘገብለት የጠየቀው አቶ ሀብታሙ አያሌው፣ ‹‹በበኩሌ ያሉኝን መረጃዎች እያቀረብኩ ስነ-ስርዓቱን አክብሬ ክርክሩን አቀጥላለሁ›› ሲል ተናግሯል፡፡
ምንጭ፡- ነገረ- ኢትዮጵያ

በኢትዮጵያ መንግሥት የሳይበር ጥቃት መፈፀሙ ይፋ ተደረገ

የኢትዮጵያ መንግስት የመረጃ ጠለፋ መፈጸሙን እንደገፋበት ሂዩማን ራይትስ ዎች ተናገረ፡፡ የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ ድርጅት ዛሬ ይፋ አንዳደረገው ከሆነ መንግስት ቀስ በቀስ ጋዜጠኞችን ጸጥ ያደርጋል እንዲሁም የዲጂታል ጥቃት ይፈጽማል ሲል ገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ የመረጃ ስለላ ተቋም

የኢትዮጵያ የመረጃ ስለላ ተቋም

ባለፈው አመት “ዘይ ኖው ኤቭሪቲንግ ዊ ዱ፤የኢንተርኔትና የቴሌኮም ስለላ በኢትዮጵያ” ሲል ቡድኑ ባወጣው ዘገባ የኢትዮጲያ መንግስት በዜጎቹ ላይ የቴሌኮምና የመረጃ መረብ እያንዳንዱን ሚስጥራቸውን ይበረብራል ማለቱ አይዘነጋም፡፡

ዘንድሮም በተመሳሳይ መንግስት ይህን ድርጊት መፈጸሙን አጠናክሮ እንደቀጠለ የሚናገረው ቡድኑ በውጪ የሚኖሩ ነጻ ጋዜጠኞች ላይ ሳይቀር የሳይበር ጥቃት ይፈጽማል በማለት አትቷል፡፡

መሰረቱን በካናዳ ቶሮንቶ ያደረገ አንድ ገለልተኛ አጥኚ ቡድን ሰሞኑን በአንድ የሚዲያ ተቋም ላይ መንግስት የሳይበር ጥቃት መፈጸሙን ማረጋገጡን የሚገልጸው ሂዩማን ራይትስ ዎች ለኢትዮጵያ መንግስት የመረጃ መረብ መጥለፊያና ጥቃት መፈጸሚያ ምርቶችን የሚሸጡ አለም አቀፍ ኩባኒያዎች ድርጊቱን እንዲያጣሩ፤ድርጊቱን ፈጻሚው መንግስትም በአስቸኳይ ከድርጊቱ እንዲታቀብ አሳስቧል፡፡

ይህን የሂዩማን ራይትስዎች መረጃ ተከትሎ በርካታ አለም አቀፍ ሚዲያዎች ባወጡት ዘገባ የኢትዮጵያን መንግስት አውግዘዋል፡፡

ባለፈው አመት የኢትዮጵያ መንግስት ከአንድ የጣሊያን የደህንነት ተቋም በውጪ የሚኖሩ ጋዜጠኞችን ለመሰለል የሶውትዌር ምርት እንደገዛ በአንድ ገለልተኛ ቡድን ምርመራ መረጋገጡን በመጥቀስ ዘገባውን የሚጀምረው ማዘርቦርድ የተባለው የወሬ ምንጭ ይሁን እንጂ ዘንድሮም በተመሳሳይ መንግስት የሳይበር ጥቃቱን ቀጥሎበታል ሲል ያትታል፡፡ በዚህም ሰለባ ከሆኑት መካከል የኢትዮጵያ ሳተላይት ሬዲዮና ቴሌቪዥን(ኢሳት) እንዲሁም በውጭ የሚኖሩና በስራ ላይ ያሉ የኢትዮጵያውያን ነፃው ፕሬስ ጋዜጠኞች እንደሚገኙበት መዘገቡ አይዘነጋም፡፡

ይህን በሚመለከት ተመሳሳይ ዘገባ ይዞ የወጣው ዋሽንግተን ፖስት በበኩሉ የኢትዮጵያ መንግስት በውጪ ያሉ ነጻ ጋዜጠኞችን በሽብር ይከሳል አልፎ ተርፎም የሚያሰራጯቸውን የሚዲያ አገልግሎቶች ጃም በማድረግና በሳይበር ጥቃቶች ለማፈን ይሞክራል ማለቱን ድሬ ቲዩብ ዘግቧል፡፡

በአዲስ አበባና በክልሎች በርካታ ኢትዮጵውያን ሙስሊሞች በመንግሥት እየታሰሩ መሆኑ ተሰማ

Ethio-muslims protest

ከጥር 2004 ዓ.ም. ጀምሮ በሀገር አቀፍ ደረጃ በይፋ የኃይማኖት ነፃነት መብትና ህገ-መንግሥቱ እንዲከበር፤ በሰላማዊ መንገድ እየጠየቁ የሚገኙት የኢትዮጵያ ሙስሊሙ ማኀበረሰብ  የመንግሥትን ህገወጥ እርምጃ ተቃውሞ መቀጠሉን ተከትሎ፤አሁንም በያዝነው የካቲት 2007 ዓ.ም. ከየቤቱና ከስራ ቦታ ጭምር የጅምላ እስሩ ተጠናክሮ መቀጠሉን ከአዲስ አበባና ከተለያዩ የክልል ከተሞች የሚመጡ መረጃዎች ጠቁመዋል፡፡ በተለይ በአዲስ አበባ የመንግሥትን ያይል እርምጃ እና የኃይማኖት ነፃነት መብታቸው እንዲከበርና መንግሥትም ከኃይማኖት ጣልቃ ገብነት እንዲወጣ በተደጋጋሚ መጠየቃቸውን ተከትሎ ሰሞኑን የጅምላ እስር እየተካሄደ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

Anuwar mosque protest

የጅምላ እስሩ እየተከናወነ የሚገኘው መንግሥት በመጪው ምርጫ 2007 ዓ.ም. ከሙስሊሙ ማኀበረሰብ ድጋፍ እንደሌለው በመረዳቱና በርካቶችም የድምፅ መስጫ በረቀት መውሰዳቸው የደረሰው መረጃ አስደንግጦት እንደሆነ ቢጠቆምም፤ ከመንግሥት በኩል ግን እየተወሰደ ስላለው የጅምላ እስር የተሰጠ  ምንም ዓይነት ማብራሪያም ሆነ ምላሽ ማግኘት አልተቻለም፡፡ በተለይ ሰሞኑን በተወሰደውና እየተወሰደ ባለው የጅምላ እስር ተጠናክሮ መቀጠሉን ከመጠቆም ባለፈ፤እስካሁን ምን ያህል ሰዎች እንደታሰሩ ግን ለማወቅ አልተቻለም፡፡

ከዚህ ቀደም መንግሥት የኢትዮጵያ ሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴው ጋር ሲደራደር ቆይቶ፤ በመጨረሻም በጅምላ በማሰር የሽብር ክስ መስርቶባቸው የኮሚቴው አባላት ያለምንም ፍትህ እስካሁን በእስር ላይ እንደሚገኙ ይታወቃል፡፡

ከምርጫው ውጭ እንዲሆን የተደረገው አንድነት ፓርቲ በምርጫ ቦርድ ላይ ያቀረበው ክስ ለየካቲት 27 ተቀጠረ!

 udj

አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) በብሔራዊ ምርቻ ቦርድ አማካንነት ከግንቦቱ 2007 ዓ.ም.  ሀገር አቀፍ ምርጫ ውጭ እንዲሆን መደረጉን በመቃወም  በፌደራሉ ከፍኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ  በፍትሐ ብሔር 11ኛ ችሎት የመሰረተው ክስ ለየካቲት 27 ቀን 2007 ዓ.ም. ጠዋት ተቀጠረ፡፡

ይህንንም በተመለከተ ፓርቲው በማኀበራዊ ሚዲያ ገፁ ላይ “ህገ ወጥ በሆነ መንገድ በምርጫ ቦርድ እና በኢህአዴግ ሴራ ለእነ አቶ ትዕግስቱ አወሉ በኃይል ተላልፎ መሰጠቱ የሚታወቅ ነው። በዚህም ምክንያት ህጋዊው የአንድነት አመራር በምርጫ ቦርድ ላይ ክስ መስርተዋል፤ ፍርድ ቤቱ ልደታ በሚገኘው ከፍተኛ ፍርድ ቤት 11ኛ ፍትሀ ብሔር ችሎት ለየካቲት 27 ከጠዋቱ 3:30 ጉዳዩን ለማየት ቀጠሮ ሰጥተዋል፤ በመሆኑም በቅርብ የምንገኝ የአንድነት አባላትና ደጋፊዎች በችሎቱ ላይ በአካል በመገኘት ለህጋዊው አንድነት ያለንን አጋርነት እንድናሳይ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።” ብሏል፡፡

ብሔራዊ ምርጫ ቦር ከተመሰረተ ጀምሮ ከገዠው ህወሓት/ኢህአዴግ ጋር ጠንካራ ተፎካካሪ ናቸው ተብለው የሚገመቱትንና በከደፍተኛ ደረጃ የህዝብ ተቀባይነት ያላቸውን  የፖለቲካ ፓርቲዎች በተለይም ከዚህ በፊት የኦሮሞ ብሔራዊ ኮንግረንስ(ኦብኮ)ን ያፈረሰ ሲሆን፤ በቅርቡ ደግሞ የግንቦቱ ምርጫ 2007 ዓ.ም. ዋዜማ ላይ  አንድነት ፓርቲን እና መኢአድን በማፍረስ ምርጫ ቦርድ ያፈረሳቸውን ፓርቲዎች ስም ለፈለጋቸው ሰዎች መስጠቱን ማሳወቁ ይታወሳል፡፡

የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ለግንቦቱ ምርጫ 2007ዓ.ም. በዕጩነት እንዳይቀርቡ ተደረገ

  • “ምርጫ በህዝብ ፍላጎት ሳይሆን በሎተሪ ሆኗል” ኢ/ር ይልቃል ጌትነት
ይልቃል ጌትነት (የወቅቱ የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር)

ይልቃል ጌትነት (የወቅቱ የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር)

አዲስ አበባ ከተማ ወረዳ 5 ለመጭው ምርጫ ለተወካዮች ምክር ቤት ሰማያዊ ፓርቲን ወክለው ሊቀርቡ የነበሩት የፓርቲው ሊቀመንበር ኢ/ር ይልቃል ጌትነት “ከቀረቡት 17 ዕጩዎች መካከል በተጣለ ዕጣ ወድቀዋል” በመባላቸው ለመጭው ምርጫ በዕጩነት እንዳይቀርቡ መደረጋቸውን ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡ ኢ/ር ይልቃል በዕጩነት በቀረቡበት ወረዳ 5 የምርጫ ጣቢያ ኢህአዴግ፣ የትግስቱ አንድነት፣ ቅንጅትን ጨምሮ ሌሎች ስድስት የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ያለ ምንም ዕጣ አልፈዋል የተባለ ሲሆን “የሚያልፉት በዕጣ ነው” የተባሉት ሰማያዊን ጨምሮ 11 የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች መካከል ሰማያዊና ሌሎች አራት የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች “ዕጣ አልወጣላቸውም፡፡” ተብሏል፡፡

ስለ ጉዳዩ ያነጋገርናቸው የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ኢ/ር ይልቃል ጌትነት “ሰማያዊ ህዝብ ውስጥ በሰፊው እየገባና እያንቀሳቀሰ ያለ ግንባር ቀደም ፓርቲ ነው፡፡ እንደ ኢህአዴግ ያሉን ጨምሮ ዕጣ ውስጥ አይገቡም፡፡ ሰማያዊ ደግሞ ይህ ነው የሚባል እንቅስቃሴ ከማያደርጉት ፓርቲዎች ጋር ዕጣ ውስጥ ገብቶ ወደቀ መባሉ ዴሞክራሲ ከጅምሩ ጀምሮ የህዝብ ድምጽ ሆኖ እያለ በእኛ አገር ሎተሪ ሆኗል ማለት ነው፡፡” ብለዋል

ሊቀመንበሩ አክለውም ‹‹ሂደቱ ምንም ይሁን ምን አንድን ፓርቲ ወይንም ተወካይን ህዝብ ነው መምረጥ ያለበት፡፡ ህዝብ የሚፈልገውና የሚመረጥ ፓርቲ ነው ለምርጫ መቅረብ ያለበት፡፡ አሁን ግን እየተባለ ያለው በአንድ በኩል ህዝብ የማይፈልገው ያለ ዕጣ ሲገባ፣ በሌላ በኩል ህዝብ የሚፈልገው ሰማያዊን የመሰለ ፓርቲ ዕጣ ውስጥ ገብቶ አላለፈም እየተባለ ነው፡፡ በአንድ በኩል ህዝብ የተማረረባቸው ያለ ቅድመ ሁኔታ ህዝብን እንደሚያንቀሳቅስ የሚታወቀው ሰማያዊ ደግሞ ህዝብ ስፈለገው አሊያም በጥንካሬው ሳይሆን በሎተሪ ወድቀሃል ተብሏል›› ሂደቱ የተሳሳተ ነው ማለታቸውን ጨምሮ ነገረ-ኢትዮጵያ ዘግቧል፡፡