Daily Archives: November 14th, 2014

በሊባኖስ ብርቱካን ተረፈች ፣በኦማን አልማዝ የአካል ጉዳተኛ ሆነች !

ነቢዩ ሲራክ (ከሳውዲ ዓረቢያ)

የማለዳ ወግ

የተረፈችው የእህት ብርቱካን ጉዳይ …
በሃገረ ሊባኖሰ ቤሩት ከ4ኛ ፎቅ ወድቃ የተረፈችው እህት ብርቱካን ጤንነት የተስተካከለና ከድካም ህመሟ ሙሉ በሙሉ እያገገመች መሆኑን መረጃዎች ማምሻውን ደርሰውኛል ። የቆንስል ሃላፊዎች አልማዝን ሲያነጋግሯት በሊባኖስ ቆይታ ስራ መስራት እንጅ ወደ ሀገር ቤት መመለስ እንደማትፈልግ እንደገለጸችላቸው አምባሳደር ሐሊማ ሙሃመድ አጫውተውኛል። በቀጣይ ቀናትም ህክምና እየወሰደች ያለችበትን መካስድ ሆስፒታልን ለቃ እንደምትወጣ ፣ በቤሩት የቆንስል መጠለያ ሆና ህክምናና ጉዳይዋን እንደምትከታተል ተረድቻለሁ !

ተስፋ የቆረጡት ኢትዮጵያውያን አስተያየት …

lenanonበብርቱካን ጉዳይ ዙሪያ ያነጋገርኳቸው ብዙ ነዋሪዎች የቆንስል ተዋካዮች ላይ እምነት እንደሌላቸው ይገልጻሉ ። እንደ አማራጭም የብርቱካንን ጉዳይ በጠበቃ አስይዘው ለመከራከር የሚቻልበትን ንገድ ለማፈላለግ ስራ መሰራት አለበት ሲሉ ” የቆንስል ሃላፊዎችን ዲስኩር ማመን ትቶ የተለመደው የነዋሪውን ትብብር ማስተባበር ያሻል ” ይላሉ። ለምን በመንግስት ተወካዮቻችን እምነት አጣችሁ? ማለቴ አልቀረም ፣ ምላሻቸው ዘርዘር ያለ መረጃና ማስረጃ ያለው እውነት ይመስላል። አንድ ያሉኝን ብቻ ላንሳው … በሃገራ ባንዴራ ስር ፣ በቆንስሏ በር በጥጋበኛ “ጀብራሬ” አረብ እየተጎተተች ስትደበደብ የቆንስል ሀላፊዎች ምንም አለማድረጋቸው ፣ ከዚያም ሃኪም ቤት በገባች በቀናት ልዩነት ” ራሷን በራሷ ገደለች !” መርዶ ነጋሪና ሬሳ ተቀባይና ላኪ ከመሆን ያለፈ ስራ የመብት ማስጠበቅ ስራ በቆንስል መስሪያ ቤቱ አለመሰራቱን ያጣቅሳሉ። ከዚሁ ጋር በተዛማጅ ከአንድ ወር በፊት እዚያው ሊባኖስ “የአሰሪዋን ህጻን ልጅ አፍና ገድላለች! ” በሚል በፍርድ ውሳኔ ያልተሰጠው ጉዳይ በመገናኛ ብዙሃን ቀርቦ ነበር። በቀረበው መረጃ ስማችን ጎደፈ ። ዳሩ ግን የቀረበው መረጃ ኢትዮጵያዊቷ ወንጀለኛ አለመሆኗ ፍንጭ ሰጠ ፣ የራሳቸው ዜጎች ከሳሽ ባቀረበው መረጃና ማስረጃ ተመርኩዘው የተገላቢጦሹን አሳዩት ። ይህ ሁሉ ሲሆን የመንግስት ተወካዮቻችን ከሳሽን ወደ ተከሳሽነት የሚያሸጋግረውን መረጃ እንኳ ይዘው ታሳሪዋ ኢትዮጵያዊት እህት በዋስ መብቷ ተጠብቆ በውጭ ሆና እንድትከራከር አለማድረጋቸው በቆንስሉ የብርቱካን ክትትል ላይ የረባ ውጤት የማምጣት አቅም እንደሌላቸው ማሳያ ነው በማለት የሰላ ሂስና ወቀሳ ያቀርባሉ ።

የተስፈኞቹ ኢትዮጵያውያን አስተያየት …

” በቤሩት የቆንስል መ/ቤት ከበፊቱ የተሻለ ለውጥ ይታያል! ” ያሉኝ ወገኖች ፣ ለውጥ ለመምጣቱና ለመታየቱ የሚያቀርቧቸው ጥቃቅን የቆንስል ግልጋሎት አሰጣጥ መረጃዎች ናቸው ። ያም ሆኖ የመስራት አቅሙ የላቸውም ያሉኝ የሚያነሱትን ” …የከዚህ በፊቱን የአለም ደቻሳና ሌላው ሌላው አሳዛኝ የመብት ጥበቃ ጉድለት “ያለፈው አለፈ ፣ ይሁን !” ቢባል አሁን ድረስ እንዳልተሻሻሉ ብዙ ማሳያ አለ። ከወር በፊት በነፍስ ግድያ ወንጀል ያለ ተጨባጭ መረጃ የታሰረችውን እህት ቆንስሉ አያማክሯትም ። ለዋስ መብቷን አላስጠበቁላትም። ” በማለት “የቀረበውን የሰላ ሂስ ” ለውጥ አለ! ” ባዮች በተጨበጠ መከራከሪያ መላሽ ለመስጠት አልተቻላቸውም ። ብቻ የቀረበውን ወቀሳ ሳያስተባብሉ ” በለውጥ ተስፋ ከማድረግ የተሻለ ነገር የለም! ” በማለት የቆንሰል መ/ቤቱ የብርቱካንን ጉዳይ በቅርብ ተካታትሎ ውል እንደሚያስይዘው ያላቸውን ተስፋ አጋርተውኛል ! …ቀጣዩ ምን ሊሆን እንደሚችል መገመት ቢቸግርም ዛሬ የእህት ብርቱካንን በአሰቃቂ ሁኔታ መውደቅና ከከፋ አደጋ መትረፏ በሊባኖስ ቤሩት ካሉት ባለፈ በአለም ዙሪያ ሆነን ጉዳዩን በቅርብ ለተከታተልን ሁሉ እፎይታ ሆኗል … ተመስገን ነው ! እናም ” ያገባናል ” ባዮች በእህት ብርቱካን ሰናይ ዜና ተደስተን ፊታችን ወደ ሌላዋ ግፉዕ ማዞር ግድ ብሎን ወደ አልማዝን እንርዳ ” ዘመቻችን ፊታችን መዞራችን እውነት ነው!

የአካል ጉዳተኛዋ የአልማዝ ጉዳይ …

ህዳር 2 ቀን 2007 ምሽት በሊባኖስ የብርቱካንን ከፎቅ መውደቅ አሳዛኝ ዜና ስሰማ በሌላኛው አረብ ሀገር በኦማን የመኪና አደጋ ደርሶባት የአካል ጉዳተኛ በሆነችው በእህት አልማዝ ጉዳይ ተወጥሬ ነበር። ከተለያዩ አረብ ሃገራት እና በሃገር ቤት በማህበራዊ መገናኛዎች ተገናኝተን የተውጣጣን ወደ ስድስት የምንደርስ ወንድምና እህቶች ባንድ እየመከርን ነው። አላማችን ከመረጃ ልውውጡ ባለፈ የወገናችን እንባ በተግባር መጥረጉም “ያገባናል !” ብለን ነው። የእህት አልማዝን እርዳታ ለማሳካት ማድረግ ስላለብን ጉዳይ እየመከርን ባለበት ወቅት ከቤሩት የብርቱካን አደጋና “አትተርፍም!” የተባለ መረጃ ደረሰኝ … ሌላዋን የአረብ ሃገር ኦማን ጉስቁል እህት አልማዝን አሰብኳት …

እህት አልማዝ የአረብ ሃገሩ ስደት ሲነሳ ከመንግስት ጀምሮ እስከ ግለሰብ የእኛ ቀጥተኛና ቀጥተኛ ያልሆነ ድጋፍ እህቶቻችን አደጋ ላይ ጥሏቸዋል።በህግ ሽፋን ተሰጥቷቸው በሚንቀሳቀሱ ወሮበላ ህግ ይጣሳል ፣ ለህዝብ ቆመናል በሚሉ የመንግስት ተቋማት ህግ ይጣሳል ፣ በመልካም አስተዳደር እጦት ፣ በሙስና ህይወታችን ከፍቷል ፣ በተለያያየ መንገድ በአረበወ ሃገራት ለገነነው “ዘመናዊ ባርነት ” ድጋፍ እያደረግን እያበረታታን ነው ። ይህን ማለቴ ያለነገር አይደለም ፣ በአረቡ ሃገር በኦማን አካሏ ተሰናክሎ የእኛን እርዳታ ጠባቂ የሆነችውን እህት አልማዝ አበሳ አስታውሼ ብዙውን አውጥቸ አወረድኩት …

…አልማዝ አንድ ፍሬ ጉብል ሳለች ካላቻ ጋብቻ ትዳርን ሳታውቀው መስርታ ልጅ ወልዳ ነበር ፣ ብዙም ሳይቆይ ጉብሏ እናት ሆነች ፣ ኑሮ አልሞላ አልሳካ ብሏት ወደ አረብ ሀገር ወደ ኦማን ተሰደደች … ሙሉ አካሏን ይዛ ለስራ ብላ በራ ከሄደችበት ኦማን ሞስካት ብዙም ሳትቆይ ለመኪና አደጋ ተጋለጠች ፣ ሆስፒታል ገባች ፣ ለወራት በህክምና ስትረዳ ብትቆይም አዕምሮዋ ፣ እግሯና እጇ ብሎም መላ አካሏ የከፋ ጉዳት ደረሰባቸው ፣ አይሆኑ ሆነች: ( ከሃገር ቤት ጀምሮ በአረብ ሀገራት ብርቱ መረብ ያላቸው ደላሎች እህት አልማዝ ሆስፒታል ከገባች በኋላም በጉዳቷ ለመጠቀም መስገብገባቸውን ጠልቆ መረጃ መሰብሰብ አሞኛል ፣ ዛሬ ወደ ክፉዎች ባለ ጊዜ ደላላ ባለጸጎች መሰሪ ምግባር ዳሰሳ አልገባም ! … እህት አልማዝ በተስፋ አቢሲኒያ በጎ አድራጊ ቡድን አባላት ፣ በተለይም በመስራቹ ብርቱ ወንድም በወዳጀ በመሳይ አክሊሉ ( በኑቢያ ኩሽ ቀዳማዊ ) እና በወዳጆቹ ብርታት በአሳር በመከራ ሃገር ቤት ገብታለች ። መቄዶንያ የአረጋውያን ደጋፊ በጎ አድራጊ ቡድን ትብብርም መጠለያም ተሰጥቷታል ። … እህት አልማዝ እዚህ ላይ ደርሳለች … ይህም ተመስገን ነው!

ይህም ሁሉ ሆኖ የአልጋ ቁራኛ የሆነችው አልማዝ ” ከህመም ጉዳቷ የምታገግምበት ተስፋ አለ ” በመባሉ የእርዳታ ስራ ተጀምሯል ፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ በተጀመረው እርዳታ እዚህ ሳውዲ አረቢያ ውስጥ ያለውን እርዳታ ለማስተባበር ሃላፊነት ከወሰድኩ ቀናት ወዲህ ወገኖች አልማዝን ለመርዳት ያሳዪት መነቃቃት እጅግ በጣም አበረታች ሆኖ ቀጥሏል። በኮንትራት ስራ በየአረቡ ቤት የሚሰሩ እህቶቸ የ “ነግ በኔ ” ብለው በሰብአዊነት እያደረጉት ያለው መተባበር ውስጥን ስሜት የሚያረካ ለመሆኑ እማኝ ለመሆን ታድያለሁ ! የቤት ቆሻሻ ለመጣል መውጫ ቀዳዳውን ፈልገው ያላቸውን ለአልማዝ ለማካፈል ያሳዩት ቅንነት ፍጹም በቃላት ልገለጽ የማይቻለኝን ኩራት፣ በእህቶቼ እንድጎናጸፈው ዘንድ ምክንያት ሆኖኛል ! ድምጻዊ ጆሲ እንደ ሀውስ ያን ሰሞን እርዳታ ለማሰባሰብ ሲሞክር በገጠመውና በሆነው በግኖ ይመስለኛል ” ለመስጠት መሰጠት ያስፈልጋል! ” ማለቱ በእኔም ላይ ደርሶ እውነት ነው ብያለሁ ! ለእኔ እርዳታ ማድረግ ትርጉሙ ገንዘብ መስጠት ብቻ አይደለም ፣ ቀና ማሰብ ፣ መረጃ መለዋወጥ ፣ ሌላ ተዛማች ተጎጅውን የሚደግፍ ስራ መስራት ፣ የሚረዳን አለመቃወም ፣ ገንዘብ ከመስጠት ባለፈ ለተጎጅው ወገን ወገናዊ አብሮነት ፍቅር መግለጫ ነው… ባይ ነኝ !

ለማንኛውም ብርቱካን በሊባኖስ ተረፈች ፣ እሰየው ነው! እህት አልማዝ በኦማን ተሰናክላ እንዳትቀር ወገናዊ ትብብራችን ትሻለችና እናስብበት ! በዚህ የበጎነት መንገድ በመጓዝ በጠና የተጎዱ ወገኖቻችን በመደገፍ ልንታደጋቸው ካልቻልን ከንፈር መምጠጡ ብቻ እንዳላዋጣን ከእኛ በላይ የሚያውቀው የለም ! እናም የዜጎቹን መብት እንዲያስከብር መንግስትን ስንወተውት የዝሆን ጀሮ ሰጥቶ አልሰማን ቢልም ጩኸት በደላችን እስኪሰማ እየጮህንም ቢሆን በመደጋገፉ የተጎዱትን እየነቀስን በማውጣት የቻልነውን መስራት የዜግነት ውዴታ ግዴታ ነው ባይ ነኝ !

ሁሉም ለበጎ ነው !

ህዳር 5 ቀን 2007 ዓም

 

አክሱም የሚገኘው ፅላተ ሙሴ ተሰርቋል መባሉ ፍጹም ሐሰት ነው – የቤተክርስቲያኗ አስተዳዳሪ

ከዛሬ 3 ሺህ ዓመታት በፊት የጠቢቡ ንጉስ ሰሎሞን ልጅ በሆነው ቀዳማዊ ምኒልክ ዘመን ወደ ኢትዮጵያ የመጣው የሙሴ ፅላት መዘረፉን በተለያዩ የማህበራዊ ድረገፆች እና መገናኛ ብዙኃን ተዘግቧል፡፡ ይሁን እንጂ የርዕሰ አድባራት ወገዳማት አክሱም ጽዮን ማርያም ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ እና ማዕከላዊ አክሱም ሀገረ ስብከት ዋና ስራ አስኪያጅ ንብረእድ አባ ገ/ህይወት ገ/ሚካኤል በበኩላቸው የተባለው ጉዳይ ከእውነት የራቀ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

axumለፖሊስም ሆነ ለጠቅላይ ቤተ ክህነት እንዲሁም ለሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስና ለፓትርያርኩ ጽ/ቤት ይህን መሰሉን ሪፖርት አላቀረብንም ያሉት አስተዳዳሪው፤ ወሬው ከየት መጥቶ እንደተወራ አናውቅም ብለዋል፡፡

የአክሱም ጽዮን ማርያም ታቦት በቤተክርስቲያኒቱ ከጥቂት ሰዎች በስተቀር ማንም ሊያየው በማይችለው እና በጥንቃቄ ቦታ እንደሚቀመጥም አስተዳዳሪው ተናግረዋል፡፡ አስተዳዳሪው ጉዳዩንም ለብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በስልክ ደውለው እንደነገሯቸው ተናግረዋል፡፡

ጽላቱ በቤተክርስቲያኒቱ ጠባቂዎች እና በመንግስት የፖሊስ ሃይሎች ከፍተኛ ጥበቃ እየተደረገለት ነው ያሉት አስተዳዳሪው ህዝቡ በቀጣይ የሚከበረውን አክሱም ጽዮን ክብረ በአልን በተረጋጋ መንፈስ እንዲያከብር ጥሪ አቅርበዋል፡፡

 

ምንጭ፡- ድሬ ቲዩብ

ጅማ አንድ እናት እስከነልጃቸው በአሰቃቂ ሁኔታ በፖሊሶች ተገደሉ

ካለፈው አንድ ወር ጀምሮ በአካባቢው የሰፈሩ የፌደራል ፖሊስ አባላት በህዝቡ ላይ የሚወስዱት እርምጃ እየተባባሰ መጥቶ ረቡዕ ሌሊት ለሃሙስ አጥቢያ ፣ ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ የፌደራል ፖሊሶች ወደ አንድ ወጣት መኖሪያ ቤት ሰብረው በመግባት እርሱንና እናቱን በአምስት አምስት ጥይኦች በአሰቃቂ ሁኔታ ገድለው ወደ ካምፓቸው አምርተዋል። የከተማው ህዝብ ተቃውሞውን ለማሰማት ሃሙስ ጠዋት ወደ አደባባይ ቢወጣም የጠበቀው የፖሊስ ዱላ ነው።

jimmaየመረጃ ምንጮች እንደገለፁት ከሆነ ወ/ሮ መንበረ የተባሉ የከተማዋ ነዋሪ በሆቴል አገልግሎት ኑሮአቸውን የሚገፉና በአካባቢው ህብረተሰብ ዘንድ የሚከበሩ ልጃቸው ዮናስም እንዲሁ በጸባዩ ምስጉን የሆነ የገዢው ፓርቲ ተቃዋሚ ነው። የፌደራል ፖሊሶች ወደ ወ/ሮ መንበረ ሆቴል ገብተው ሲጠጡ ከቆዩ በሁዋላ አንከፍልም በማለት መውጣታቸው ያበሳጨው ልጃቸው ወጣት ዮናስ ” የዚህ መንግስት አገልጋዮች ስለሆናችሁ ነው” በሚል ተናግሮአቸዋል። ወታደሮቹ ምንም ሳይሉ ወደ ካምፓቸው ካመሩ በሁዋላ ፣ ሌሊት ላይ መሳሪያቸውን ይዘው በመምጣት የዮናስ እናትን ቤት በር ሰብረው በመግባት ዮናስን በ5 ጥይት ደብድበውታል። እናቱ ወ/ሮ መንበረ ” እባካችሁ ልጄን አትገደሉብኝ” ሲሉዋቸው ፖሊሶቹ እርሳቸውንም በ5 ጥይቶች ገድለዋቸው ወደ ካምፓቸው ተመልሰዋል።

ድርጊቱ ያስቆጣቸው የከተማዋ ነዋሪዎች ከቀበር በፊት የተቃውሞ ሰልፍ ቢያደርጉም፣ በፖሊሶች ዱላ ተደብድበው ተበታትነዋል። ጅማ ጧት አካባቢ በተኩስ ስትናወጥ መዋሉዋንም ነዋሪዎች ተናግረዋል። በጉዳዩ ዙሪያ አንድ የጅማ ነዋሪ አነጋግረናል ከአንድ ሳምንት በፊት አንዋር የተባለ ወጣት በጩቤ በአሰቃቂ ሁኔታ ከተገደለ በሁዋላ ህዝብ ድርጊቱን ለመቃወም ወደ አደባባይ ቢወጣም በተመሳሳይ መልኩ በፖሊሶች ተደብድቦ ተባሯል።

ከአንድ ወር በፊት ደግሞ ኬኔዲ መንገሻ የሚባል አዲስ ቅጥር የመንግስት ሰራተኛ በፖሊሶች ተገድሏል። በአካባቢው የሰፈረው የፌደራል ፖሊስ በህዝቡ ላይ የሚወስደው እርምጃ መጨመሩ ህዝቡ በስጋት እንዲኖር አድርጎታል። ነዋሪዎች እንደሚሉት ሁኔታው ከአቅማቸው በላይ እየሆነ ነው።

የመረጃ  ምንጩ በጉዳዩ ዙሪያ ከከተማው ፖሊስ ለማጣራት ያደረገው ጥረት እንዳልተሳካ ተጠቁሟል፡፡

ምንጭ፡-ኢሳት ሬዲዮና ቴሌቪዥን

%d bloggers like this: