Daily Archives: November 28th, 2014

የ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር ለአዳሩ ሰልፍ የእውቅና ደብዳቤ አስገባ

 • ቦታው መስቀል አደባባይ እንዲሆን ወስኗል

  የ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር ከህዳር 27/2007 ዓ.ም እስከ ህዳር 28/2007 ዓ.ም ለሚደረገው የአዳር ሰላማዊ ሰልፍ ዛሬ ህዳር 18/2007 ዓ.ም ለአዲስ አበባ አስተዳደር የሰላማዊ ሰልፍና ስብሰባ ማሳወቂያ ክፍል የእውቅና ደብዳቤ አስገባ፡፡

  ደደደደደደደለሰላማዊ ሰልፍና ስብሰባ ማሳወቂያ ክፍል የገባው ደብዳቤ በሰማያዊ፣ መኢዴፓ እና ኢብአፓ ተፈርሞ የገባ ሲሆን የእውቅና ደብዳቤውንም ኢንጅነር ይልቃል ጌትነት የሰማያዊ ፓርቲና የትብብሩ ሊቀመንበር፣ የከንባታ ህዝቦች ሊቀመንበርና የትብብብሩ ም/ሊቀመንበር አቶ ኤርጫፎ ኤርጌሎ፣ አቶ ግርማ በቀለ ከኦሞ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅትና የትብብሩ ፀኃፊ እና የመኢዴፓ ሊቀመንበርና የትብብሩ ገንዘብ ያዥ አቶ ኑሪ ሙደሲር አስገብተዋል፡፡

  የትብብሩ አመራሮች ወደ ሰላማዊ ሰልፍና ስብሰባ ማሳወቂያ ክፍሉ በሄዱበት ወቅት የአቶ ማርቆስ ተወካይ ለሆኑት አቶ ፈለቀ አበበ ደብዳቤውን ለመስጠት ጥረት ቢያደርጉም ተወካዩ ‹‹የከንቲባ ጉዳዮች ጽ/ቤ ኃላፊ አቶ አሰግድ ጌታቸው የለም፡፡ እሱ ካልመራበት መቀበል አንችልም›› በሚል ደብዳቤውን አልቀበልም እንዳሏቸው ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡ አመራሮቹ ወደ አቶ አሰግድ ቢሮ ቢያቀኑም እንዳላገኙዋቸው ጨምረው ገልጸዋል፡፡

  ሆኖም የትብብሩ አመራሮች ደብዳቤ መስጠት እንጂ ደብዳቤ ማስመራት የሰራተኞቹ እንጂ የእነሱ ስራ እንዳልሆነ በመግለጽ ደብዳቤውን ዛሬ ህዳር 18/2007 ዓ.ም ታመዋል የተባሉት የአቶ ማርቆስ ተወካይ የሆኑት አቶ ፈለቀ ቢሮ በአራት ምስክሮች ፊት አስቀምጠው መምጣታቸውን አስረድተዋል፡፡ አመራሮቹ የእውቅና ደብዳቤውን አቶ ፈለቀ ቢሮ አስቀምጠው ከመውጣታቸውም ባሻገር በኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት በፈጣን መልዕክት (ኢ ኤም ኤስ) በሪኮመንዴ ቁጥር eg157416502et መላካቸውን ገልጸዋል፡፡

  የአዳር ሰላማዊ ሰልፉ ህዳር 27 ከጠዋቱ 3 ሰዓት ተጀምሮ ህዳር 28 ከቀኑ 6 ሰዓት ላይ እንደሚጠናቀቅ የሚጠበቅ ሲሆን ቦታውም መስቀል አደባባይ ላይ እንደሚሆን መወሰኑ ታውቋል፡፡

  የትብብሩ አመራሮች የእውቅና ደብዳቤውን ለማስገባት በሄዱበት ወቅት በቦታው የትብብሩ አመራሮች የሚያውቋቸው ደህንነቶች ባለ ጉዳይ በመምሰል ይመላለሱ እንደነበርና ፖሊሶችም ይከታተሉ እንደነበር መግለፃቸውን የነገረ-ኢትዮጵያ ዘገባ አመልክቷል፡፡

የማያዳምጥና የማያነብ መንግስት እድሜው ስንት ነው?

ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ

bedlu“መንገዱ በዚህ ወር ይጠናቀቃል፤ ባቡሩ በዚህ ወር ስራ ይጀምራል” ይሉናል፡፡ መንገዱ ወዴት ያደርሳል? ባቡሩ ወዴት ይወስዳል? ልጆቻችን ወጥተው የማይገቡበት መንገድ፣ የማይሳፈሩበት ባቡር ምን ያደርጋል? መንገዱ ሲሰፋ፣ መጓጓዣው ሲበረክት የልጆቻችን ፍርሀት፣ የእኛ የወላጆች ጭንቀት ከመበርከቱ በቀር ትርፉ ምንድነው?

ቁሳዊ ልማት ብቻውን ማህበረሰባዊ እድገት አያመጣም፤ ቀውስ ካልሆነ በቀር፡፡ የማህበረሰብህን . . . የነገ ወራሽህን. . የወጣቱን አስተሳሰብና አሰራር ሳታለማ (ሳትለውጥ) ታክሲ ብታመጣ፣ ወንዝ ውሀ ስትቀዳ፣ ጫካ እንጨት ስትለቅም ትደፈር የነበረችውን ልጃገረድ፣ ታክሲ ውስጥ ታስደፍራታለህ፤ ነገም ባቡር ውስጥ (ዛሬ በህንድ ሀገር ባቡር ማለት ብዙ የማያስከፍል ፔንሲዮን ነው)፡፡ እኛ ሀገር ብዙ መንገድ ብዙ ወንጀል፣ ሰፊ ኢንቨስትመንት ሰፊ ዝርፊያ፣ ትልቅ ባለስልጣን ትልቅ ዘራፊ ከማለት የተለየ ፍቺ የሚኖረው መቼ ነው?

“ልማታዊ መንግስት ነን፣ ኒዎ ሊብራሊዝምን እንቃወማለን” ይሉናል፡፡ በልማት ስም ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብታችንን አንጠፍጥፈው ወሰዱት፡፡ ይበጃል ያልነውን ስንጽፍና ስንናገር ጸረ ልማት ይሉናል፡፡ ደፈር ብለን መብታችንን ከጠየቅን አሸባሪ ይሉናል፡፡ በየእስር ቤቱ ያጉሩናል፤ ድንበር አሻግረው ያሰድዱናል፡፡ መብታችንንና የመናገር ነጻነታችን ልማታዊ ላሉት መንግስት ጭዳ አደረጉት፡፡

“ልማታዊ አይደላችሁም! ኒዎ ሊብራል ናችሁ አንላቸዋለን፡፡ የምትኖሩበት ቤት፣ የምትነዱት መኪና፣ ልጆቻችሁ የሚማሩበት ትምህርት ቤት (ሀገር)፣ የምትገበያዩበት ሱፐር ማርኬት፣ የምትዝናኑበት ሪዞሪት. . . የልማታዊነት ሳይሆን የኒዎ ሊብራሎች መገለጫ ነው፡፡” እንላቸዋለን፡፡

“ዝም በሉ! የምንላችሁን አሜን ብላችሁ ተቀበሉ” ይሉናል፡፡ ማተሚያ ቤቱ የእነሱ ነው፤ ራዲዮና ኢቲቪው የእነሱ ነው፤ አዋጅና መመሪያ የሚጥልብን ፓርላማ የእነሱ ነው፡፡ አዋጅ ጣሳችሁ፣ አሸበራችሁ፣ እራለ የሚይዘን ፖሊስ የእነሱ ነው፤ ከፖሊሶቹ ተቀብሎ የሚፈርድብን ፍርድ ቤት የነሱ ነው፡፡ ያለ ወንጀሉ ተከስሶ የሚፈረድበት ዜጋ እሱ ራሱ የራሱ አይደለም፡፡ ራሳችንም የእነሱ ነን፡፡ የእኛ የሆነው ተስፋችን ብቻ ነው! ለሀገራችንና ለወገናችን ያለንን ብሩህ ተስፋ ምንም ሊያስረው አይችልም፡፡ የኔ ተስፋ ልጆቼ ውስጥ፣ ያልተወለደው የልጆቼ ልጆች . . . . . ውስጥ አለ፡፡ ተስፋ የሚታሰረው፣ የሚሞተው እርኩስ፣ ለሀገርና ለወገን የማይበጅ ሲሆን ብቻ ነው፡፡

ዛሬ አትጻፉ ተብለናል፡፡ አትናገሩ ተብለናል፡፡ አንጽፍም፡፡ አንናገርም፡፡ ከተማው ጭር ብሏል፡፡ ሀገሩ ጭር ብሏል፡፡ መንግስትም ጭርታው ተስማምቶታል፡፡ እኛ ግን አንጽፍም እንጂ እንነበባለን፤ አንናገርም እንጂ እንደመጣለን፡፡ የማያነበንና የማያዳምጠን የኢህአዴግ መንግስት ብቻ ነው፡፡ አንድ መንግስት ህዝቡን ሳያዳምጥና ሳያነብ ምን ያህል እድሜ ይኖራል? እንጃ! . . . . . አንድ ቀን መንግስት ህዝብን ማንበብ፣ ህዝብን ማዳመጥ ግዴታው ይሆናል፡፡ አቤት ታዲያ ያኔ የሚያነበው መአት! የሚያዳምጠው ቁጣ! ያኔ ማንም መንግስትን መሆን አይመኝም፡፡ እውነቴን እኮ ነው፣ አሁን 1983 ዛሬ ቢሆን ደርግን መሆን የሚመኝ አለ?

 

በርካታ የአንድነት ፓርቲ አባላትና አመራሮች በቃሊቲ እስር ቤት ታግተው መለቀቃቸው ተገለፀ

የአንድነት ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አስራት አብርሃምን ጨምሮ ከ40 ያላነሱ  የፓርቲው አባላት ቃሊቲ እስር ቤት መታገታቸው ተገለፀ፡፡

አንድነት ፓርቲ  ለአንድ ሳምንት የሚቆይ “የሚሊዮኖች ድምፅ ለህሊና እስረኞች” በሚል መሪ ቃል ከህዳር 14 ጀምሮ እያካሄደ ያለው የማህበራዊ ሚዲያ ንቅናቄ አካል የሆነውን የህሊና እስረኞችን የመጎብኘት መርሀ-ግብር ለመሳተፍ አመራሮቹና አባላቱ ወደ ቃሊቲ እስር አቅንተው ነበር፡፡  የአንድነት ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አስራት አብርሃም  እና የፓርቲው የአዲስ አበባ ሰብሳቢ አቶ ነገሰ ተፈረደኝን  ጨምሮ ከ40 ያላነሱ የአንድነት ፓርቲ አባላት ለግዜው ባልታወቀ ምክንያት  በእስር ቤቱ ግዜያዊ ማቆያ እንዲገቡ መደረጋቸውን  የፍኖተ ነፃነት ዘገባ አመልክቷል፡፡

kalitiበተለይ እገታውን በተመለከተ የአንድነት ለዴሞክራሲ እና ለፍትህ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ የሆኑት አቶ አስራት አብርሃም ተናገሩት እንደታለው ከሆነው ‹‹እነእስክንድርንና አንዷለምን መጠየቅ አትችሉም ተባልን፡፡ ከዚያም ‹‹ለምን?›› ብለን ስንጠይቅ በዋናው በር በኩል ኃላፊውን አነጋግሩ የሚል መልስ ተሠጠን፡፡ እኛም ይህንን አምነን ሄድን፡፡ ነገር ግን በተባለው በር ስንደርስ በቁጥጥር ሥር ውላችኋል ብለውን መታወቂያችንን ከመዘገቡ በኋላ በአንድ ክፍል ውስጥ ለጊዜው ታገተው እንደነበር ሚኒሊክ ሳልሳዊ ዘግቧል፡፡ በመጨረሻም በኮንቴይነር ውስጥ ታግተው የነበሩት እስረኛ ጠያቂዎች ከበድ ያለ ፍተሻ ተደርጎላቸው ከቃሊቲ ግቢ እንዲወጡ የተደረገ ሲሆን፤ይህ እስከተዘገበበት ድረስ ወጣት ትዕግስት ካሳዬ የተባለች የአዲስ አበባ የፓርቲው አመራር ግን ከእገታው እንዳልተለቀቀች ምንጮች ጠቁመዋል፡፡

እስረኞችን ሊጠይቁ የሄዱ የአንድነት አባላት በዛሬው እለት በአከባቢው የጠበቃቸው የደህንነት ቡድን በእያንዳንዱ ላይ ፍተሻ በማድረግ በኪሳቸው የነበረውን የአንድነት ፓርቲ ወረቀት እንዲሁም አንዲት ሴት የአንድነት አባል ፎት ልትነሳ መሞከር በሚል በተፈጠረ ሰበብ እንዲሁም በአባላቶቹ እጅ የተገኙት የፍኖተ ነፃነት እትሞች መቀማታቸው ተጠቁሟል፡፡ ይህ የተፈፀመው በቶዮታ ነጭ ዲኤክስ መኪና ተጭነው የመጡት የደህንነት አባላት እስረኛ ሊጠይቁ የሄዱትን በቁጥጥር ስር ካዋሉ በኋላ ስም ዝርዝራቸውን መዝግበው በመውሰድ እንዲፈቱ ትእዛዝ ሰጥተው ደህንነቶቹ መመለሳቸውን እና ከአንዲት አባል በስተቀር ሌሎች መለቀቃቸው ተጠቁሟል፡፡

 

 

%d bloggers like this: