Daily Archives: November 17th, 2014

ፓርቲዎች ትብብሩን በመቀላቀል የተቃውሞ ጎራውን እንዲያጠናክሩ ጥሪ ቀረበ

ገዥው ፓርቲ ራሱን ለለውጥ እንዲያዘጋጅ ተጠይቋል
በትናንትናው ዕለት ህዳር 7 ቀን 2007 ዓ.ም ሰብሰባ ጠርቶ በገዥው ፓርቲ ደህንነቶችና ፖሊስ የተበተነበት የ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር የኢትዮጵያ ችግር ከአንድ ፓርቲ አቅም በላይ በመሆኑ በትብብሩ ምስረታ ወቅት የነበሩትንና ሌሎቹም ፓርቲዎች ትብብሩን በመቀላቀል የተቃውሞ ጎራውን እንዲያጠናክሩ ዛሬ ባወጣው መግለጫ ጥሪ አቅርቧል፡፡

መግለጫው አክሎም አገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የአገራቸውንና የዜግነት ክብራቸውን ለማስመለስ በቀጣይነት ለሚደረገው ሰላማዊ ትግል ጥሪ አወንታዊ ምላሽ በመስጠት በጋራ ‹‹በቃን›› ብለው እንዲነሱ ጥሪ አቅርቧል፡፡ በአንጻሩ የፖሊስ ኃይልና ሌሎች አስፈጻሚ አካላት በገዥው ፓርቲ ሴራ ተጠልፈው ከሰላማዊ ዜጎች ጋር እንዳይጋጩና ህገ መንግስቱንም እንዲያከብሩ እንዲሁም ገዥው ፓርቲም ካለበት ፍርሃትና ስጋት ወጥቶ ለለውጥ ዝግጁ እንዲሆን ትብብሩ አሳስቧል፡፡

በሌላ በኩል ‹‹በህዝብ ሀብት የሚተዳደሩት መገናኛ ብዙሃን ሙሉ በሙሉ በመንግስት ቁጥጥር ስር ውለው ገዥውን ፓርቲ ከማገልገል አልፈው በሰላማዊ ትግል የፖለቲካ ኃይሎች ላይ አፍራሽ ፕሮፖጋንዳ›› እንደሚነዙ ያስታወሰው ትብብሩ በአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጭ የሚገኙ የመገናኛ ብዙሃን ስላደረጉት አወንታዊ አስተዋጽኦ አመስግኗል፡፡ በቀጣይም ለህዝብ በመወገን ከጎኑ እንዲቆሙ ጥሪ መቅረቡ ተገለፀ፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር ለእሁዱ ህዳር 7 ቀን 2007 ዓ.ም ጠርቶት ለነበረው የአደባባይ ህዝባዊ ስብሰባ አርብ ህዳር 5/2007 ዓ.ም በቅስቀሳ ላይ እንደነበሩ የታሰሩት ሁለት የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች 10 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ተሰጠባቸው፡፡ በቅስቀሳ ላይ በነበሩበት ወቅት የታሳሩት የብሄራዊ ምክር ቤት አባል አቶ ዮሴፍ ተሻገር እንዲሁም አቶ ሲሳይ በዳኔ ዛሬ ሾላ አካባቢ በሚገኝ ችሎት ቀርበው የ10 ቀን ቀነ ቀጠሮ ተሰጥቶባቸዋል፡፡

ፖሊስ በታሳሪዎቹ ላይ ‹‹ላልተፈቀደ ስብሰባ ህገ ወጥ ወረቀት ሲበትኑ ተገኝተዋል፡፡ ለህዝብ አሰራጭተዋል፡፡ የእውቅና ደብዳቤ ብንጠይቃቸው ሊሰጡን አልቻሉም፡፡ ቋሚ መኖሪያም የላቸውም፡፡ ሌሎች የምናጣራቸው መረጃዎች አሉ፡፡›› በሚል የ14 ቀን ቀጠሮ እንዲሰጥለት ጠይቆ የነበር ሲሆን ታሳሪዎቹ በበኩላቸው ፖሊስ የእውቅና ወረቀቱን ተቀብሎ መደበቁን፣ ቋሚ መኖሪያና ቤተሰብ እንዳላቸው፣ የህጋዊ ፓርቲ አመራሮች በመሆናቸው በየትኛውም ጊዜ ቢጠሩ እንደሚመጡ ጠቅሰው የዋስትና መብታቸው እንዲከበር ቢከራከሩም ዳኛው የ10 ቀን ቀነ ቀጠሮ ሰጥቶባቸዋል፡፡ ታሳሪዎቹ ሲቀሰቅሱ በነበሩበት ወቅት ፓርቲው ለሰላማዊ ሰልፍና ስብሰበባ ያሳወቀበትን ደብዳቤ ይዘው እንደነበር የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት አቶ ዮናታን ተስፋዬ ገልጸዋል፡፡

በተመሳሳይ ቅስቀሳ ላይ የታሰሩት የአዲስ አበባ ከተማ ም/ሰብሳቢና የምርጫ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ አባል ወጣት ማቲያስ መኩሪያ እና የምርጫ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ አባል ወጣት ሳምሶን ግዛቸው ‹‹በሽብርተኝነት›› ክስ የ7 ቀን የጊዜ ቀጠሮ እንደተሰጠባቸው ይታወሳል፡፡ አቶ ዮሴፍ ተሸገርና አቶ ሲሳይ በዳኔ በአሁኑ ወቅት ቤላ ፖሊስ ጣቢያ ታስረው ይገኛሉ ሲል የነገረ ኢትዮጵያ ሪፖርተር ዘግቧል፡፡

%d bloggers like this: