Daily Archives: November 4th, 2014

የኢህአዴግ መንግስት በሰሜን ጎንደር የአንድነት ፓርቲ አመራሮችን ማሰሩ ተገለፀ

gon1በዛሬው ዕለት ጥቅምት 25 ቀን 2007 ዓ.ም. ከለሊቱ 11:00 ሰዓት ላይ በሰሜን ጎንደር ዞን በምዕራብ አምርማጭሆ አብርሃ ጅራ ከተማ የአንድነት ሰብሳቢ የሆኑት አቶ አንጋው ተገኝ እና የወረዳው ሌላ አመራር አባላት አቶ አባይ ዘውዱ እና አቶ እንግዳው ዋኘው የፌደራል ፖሊሶች የቤታቸውን በር ገንጥለው በመግባት እየደበደቡ ወደ ፖሊስ ጣቢያ እንደወሰዷቸው ተጠቁሟል፡፡ ይህንንም ተከትሎ የአካባቢው ነዋሪም ወደ ሌላ ቦታ እንዳይወስዷቸው ፖሊስ ጣቢያውን ከቦ እየጠበቀ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።

በተያያዘ ዜና በዛው ሰሜን ጎንደር ዞን በመተማ ከተማ የአንድነት ሰብሳቢ የሆኑት አቶ በላይነህ ሲሳይ በፖሊሶች በዛሬው ዕለት ከለሊቱ 11:00 ሰዓት በፖሊሶች ወዳልታወቀ ቦታ መወሰዳቸውን መረጃዎች አመልክተዋል።

ባለፈው ሳምንት በተመሳሳይ መልኩ በወላይታ ዞን የአንድነት አመራሮችም ከፍተኛ ድብደባና ወከባ እንደደረሰባቸው በፍኖተ ነፃነት የተዘገበ ሲሆን፤ መንግስት በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚገኙ የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ በተለይም የአንድነት አመራሮች ላይ በኢህአዴግ የሚፈጠረው ጫና እንደቀጠለ መሆኑን የፓርቲው ልሳን ዘገባ ያመለክታል፡፡

gon2ከዚህ ቀደምም አቶ አንዱዓለም አራጌ፣ አቶ ናትናኤል መኮንን፣ አቶ የሺዋስ ይሁንዓለሙ፣ ሻምበል ዮሐንስ ተረፈ፣ አቶ አንዱዓለም አያሌው ፤በቅርቡ ደግሞ አቶ ዳንኤል ሺበሺ፣ አቶ ሀብታሙ አያሌው ከአረና እና ሰማያዊ
ፓርቲ አመራር ከሆኑት አቶ አብርሃ ደስታና አቶ የሺዋስ አሰፋ ጋር መታሰራቸው አይዘነጋም፡፡

የዞን 9 ብሎገሮችና ጋዜጠኞች ለሳምንት ተለዋጭ ቀነ ቀጠሮ ተጠየቀባቸው

ዛሬ ጥቅምት 25 ቀን 2007 ዓ.ም በፌደራሉ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 9ኛ ወንጀል ችሎት ለ10ኛ ጊዜ ችሎት የቀረቡት የዞን 9 ብሎገሮችና 3ቱ ጋዜጠኞች ለሳምንት ህዳር 3 ቀን 2007 ዓ.ም ተለዋጭ ቀነ ቀጠሮ ተሰጠ፡፡
ፍርድ ቤቱ ዛሬ በብሎገሮቹና በጋዜጠኞቹ ቀደም ሲል የቀረበውን የክስ ማሻሻያ አቤቱታ መርምሮ ውሳኔ ይሰጣል ተብሎ የተጠበቀ ቢሆንም፣ ምርመራው አላለቀም በሚል ምክንያት ለሳምንት አጭር ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

zone9በዛሬው ችሎት ላይ ከተሰየሙት ዳኞች መካከል ሁለቱ አዲሶች በመሆናቸው ምክንያት ተለዋጭ ቀጠሮ መሰጠቱን ጠበቃ አምሃ መኮንን ገልጸዋል፡፡ ከዳኞቹ በተጨማሪ ችሎት ክፍሉም በመቀየሩ ክፍሉ ጠባብ ነው በሚል፣ የተከሳሽ ቤተሰቦችና ጋዜጠኞች ችሎት መግባት አለመቻላቸውም ታውቋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ በነገው ዕለት ጠቅላይ ፍርድ ቤት በተከሳሾች ዋስትና ጉዳይ ውሳኔ ለመስጠት ቀጠሮ መያዙን አቶ አምሃ ጨምረው አስረድተዋል፡፡
ሌላው በተከሳሾች በኩል ሁለቱ ሴት ተከሳሾች ኤዶም ካሳዬ እና ማህሌት ፋንታሁን በቃሊቲ በሚገኘው ወህኒ ቤት ላይ ያነሱትን የመብት ጥሰት አቤቱታ በተመለከተ የእስር ቤቱ አስተዳደር በቀጣይ ቀጠሮ፤ ድጋሚ ቀርቦ እንዲያስረዳ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ ሁለቱ ተከሳሾች በቀን ለ10 ደቂቃ ብቻ ስማቸው ቀድሞ በተመዘገቡ 6 የቀርብ ቤተሰቦች ብቻ እየተጎበኙ እንደሚገኙ ይታወቃል፡፡

ምንጭ፡- ነገረ-ኢትዮጵያ

 

%d bloggers like this: