የጋዜጠኞቹ እና ብሎገሮቹ አቤቱታዎች ውድቅ ተደረጉ
በሶልያና ሽመልስ የክስ መዝገብ የሽብር ክስ ተመስርቶባቸው የሚገኙት የዞን ዘጠኝ ጦማርያንና ሦስቱ ወዳጅ ጋዜጠኞች መጋቢት 15 ቀን 2007 ዓ.ም ከሰዓት 8፡00 የፌደራሉ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት ቀርበዋል፡፡
መዝገቡ ተቀጥሮ የነበረው ተከሳሾች ባቀረቧቸው ሁለት አቤቱታዎች ላይ ፍርድ ቤቱ መርምሮ ብይን ለመስጠት ነበር፡፡ በዚህም አንደኛ አቃቤ ህግ በተከሳሾች ላይ አለኝ ካለው ማስረጃ ዝርዝር ውስጥ 12 የኦዲዮ-ቪዲዮ ሲዲዎች አያይዞ ያቀረበ ቢሆንም፣ ሲዲዎቹ ለተከሳሾች እስካሁን ባለመድረሳቸው ተከሳሾች የቀረበባቸውን ማስረጃ ተመልክተው መልስ ለማዘጋጀት ሲዲዎቹ እንዲሰጧቸው ያቀረቡት አቤቱታ ሲሆን፣ ሁለተኛው ጉዳይ ደግሞ 4ኛ ተከሳሽ ማህሌት ፋንታሁን እና 9ኛ ተከሳሽ ኤዶም ካሳዬ በቃሊቲ እስር ቤት አስተዳደር ላይ ከጎብኝዎቻቸው መከልከል ጋር በተያያዘ አቅርበውት በነበረው አቤቱታ ላይ ብይን መስጠት ነበር፡፡ ፍርድ ቤቱም ሁለቱንም አቤቱታዎች ውድቅ አድርጓል፡፡
የሲዲ ማስረጃውን በተመለከተ አቃቤ ህግ ማስረጃዎችን ኢግዚቪት ብሎ ስላስመዘገበ አሁን በዚህ ደረጃ ሲዲዎቹ ለተከሳሾች የሚደርሱበት አግባብ የለም በሚል ፍርድ ቤቱ የተከሳሾችን አቤቱታ እንዳልተቀበለው ገልፀዋል፡፡ በመሆኑም ተከሳሾች ማስረጃ በመስማት ሂደት ወቅት ማስረጃዎችን እየተመለከቱ መልስ እንዲሰጡ እንጂ ቀድሞ እጃቸው የሚደርስበት አሰራር የለም ብሏል ፍርድ ቤቱ፡፡
ፍርድ ቤቱ የቃሊቲ እስር ቤት አስተዳደር ላይ በሁለቱ ሴት ተከሳሾች የቀረበውን አቤቱታም ሳይቀበለው ቀርቷል፡፡ በተከሳሾች የቀረበውን አቤቱታ እና የእስር ቤቱ አስተዳደር የሰጠውን መልስ መመልከቱን የገለጸው ፍርድ ቤቱ፣ “ለቀረበው አቤቱታ ማስረጃ ተያይዞ ያልቀረበ በመሆኑ…” በሚል አቤቱታውን ቅድቅ አድርጓል፡፡ ጦማርያኑ እና ጋዜጠኞች ላይ የአቃቤ ህግ ምስክሮች ከሰኞ መጋቢት 21 ቀን 2007 ጀምሮ ለሦሰት ቀናት ይሰማሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የነገረ-ኢትዮጵያ ዘገባ አመልክቷል፡፡
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጆች ሹመት ፓትርያርኩንና ረዳት ሊቀ ጳጳሱን እያወዛገበ ነው
- ረዳት ሊቀ ጳጳሱ የፓትርያርኩን ምደባዎች በደብዳቤ ተቃውመዋል
- ቋሚ ሲኖዶሱ የጠቅላይ ቤተክህነቱ ሥራ አስኪያጁ ያቀረቡትን አቤቱታ መመልከት ጀምሯል
ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አዲስ ዋና ሥራ አስኪያጅ እና ምክትል ሥራ ስኪያጅ መሾማቸውን ተከትሎ ከሀገረ ስብከቱ ረዳት ሊቀ ጳጳስ እና ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ተቃውሞ እንደገጠማቸው ተገለጸ፡፡ኹለቱ ሥራ አስኪያጆች ለሀገረ ስብከቱ መመደባቸው የተገለጸው፣ ከትላንት በስቲያ ኀሙስ ከፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት ለጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ በደብዳቤ በተሰጠ መመሪያ ነው፡፡የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የፓትርያርኩ ልዩ ሀገረ ስብከት እንደኾነና ከረዳት ሊቀ ጳጳሱ ጀምሮ በሀገረ ስብከቱ የሚመደቡ ኃላፊዎችን የመምረጥና የመመደብ ጉዳይ ከብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ጋራ መያያዙን፣ በዚህም መሠረት ሲሠራ እንደቆየ በመመሪያው የተጠቀሰ ሲኾን፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ለኹለቱ ሥዩማን ሥራ አስኪያጆች ምደባቸውን የሚገልጽ ደብዳቤ እንዲያደርሷቸውና ሥራቸውን እንዲጀምሩ ይደረግ ዘንድ ይጠይቃል፡፡ ለጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ በአድራሻ የተጻፈው ይኸው ደብዳቤ፣ በሀገረ ስብከቱ የፓትርያርኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስ ለኾኑት ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ በግልባጭ እንዲያውቁት መደረጉ ተገልጧል፡፡
ረዳት ሊቀ ጳጳሱ የሥራ አስኪያጆቹ ሹመት ከሕገ ቤተ ክርስቲያን፣ ከቃለ ዐዋዲው እና ከሀገሪቱ የሕግ አሠራር ውጭ መኾኑን በመግለጽ ምደባውን በትላንትናው ዕለት ለፓትርያርኩ በጻፉት ደብዳቤ የተቃወሙ ሲኾን፣ ፓትርያርኩ ከሕግ አግባብ ውጭ የሰጡትን መመሪያ እንደገና እንዲያጤኑት መጠየቃቸውም ታውቋል፡፡ በሕገ ቤተ ክርስቲያኑ መሠረት፣ የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ እና ምክትል ሥራ አስኪያጅ ተጠሪነታቸው ለረዳት ሊቀ ጳጳሱ እንጂ ለፓትርያርኩ ኾኖ እንደማያውቅና ሊኾንም እንደማይችል የገለጹት አቡነ ቀሌምንጦስ፣ የፓትርያርኩ አካሔድና የሥራ አስኪያጆች ምርጫ “የሕግ ድጋፍ የሌለው፣ ያልተለመደና የቤተ ክርስቲያኒቱን መዋቅራዊ አሠራር በእጅጉ የሚፃረር ነው” ብለዋል፡፡ አቡነ ማትያስ የሰጡት መመሪያ ተቀባይነት የሚኖረውም ተሿሚዎቹ በሀገረ ስብከቱ ረዳት ሊቀ ጳጳስ ተመርጠው ከቀረቡ በኋላ ምርጫቸው ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ጋር የጋራ ስምምነት ተደርሶበት በፓትርያርኩ ሲሾሙ እንደኾነ በተቃውሟቸው አስረድተዋል፡፡ ፓትርያርኩ ከልዩ ጽ/ቤታቸው በሰጡት መመሪያና በሥራ አስኪያጆች ምርጫዎቻቸው እንደማይስማሙና ምደባውንም ለማስተናገድ እንደሚቸገሩ ያስታወቁት ረዳት ሊቀ ጳጳሱ፣ “ይህ አሠራር ከትዝብት ላይ የሚጥል መኾኑን ተረድተውልን ለቤተ ክርስቲያን ሰላማዊ አሠራርና ለኹላችንም ሰላም ሲባል ውሳኔዎን እንደገና እንዲያጤኑ በታላቅ አክብሮት አሳስባለኹ” ብለዋል – በተቃውሞ ደብዳቤአቸው፡፡
የፓትርያርኩን መመሪያ እንዲያስፈጽሙ በአቡነ ማትያስ መመሪያ የተሰጣቸው የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቡነ ማቴዎስ በበኩላቸው፣ ትላንት ከቀትር በፊት በተደረገው የቋሚ ሲኖዶሱ ሳምንታዊ ስብሰባ መመሪያውን በመቃወም አስተያየታቸውን በቃል ማቅረባቸው ተጠቁሟል፡፡
ስብሰባውን በሊቀ መንበርነት የሚመሩት ፓትርያርኩም አጀንዳው ውሳኔአቸውን የሰጡበት በመኾኑ መታየት የለበትም በሚል ቢቃወሙም ቋሚ ሲኖዶሱ ዋና ሥራ አስኪያጁ ተቃውሟቸውን በጽሑፍ እንዲያቀርቡ ማዘዙ ተገልጧል፡፡ ከትላንት በስቲያ በድንገት ይፋ የኾነው የሀገረ ስብከቱ ተተኪ ሥራ አስኪያጆች ምደባ፥ ‹‹የመልካም አስተዳደር ሒደቱን ማቀላጠፍ›› በሚል ከኹሉ አቀፍ የትምህርት ዝግጅት፣ ከሥነ ምግባርና ከብሔር ተዋፅኦ መስፈርቶች አንጻር ፓትርያርኩንና ረዳት ሊቀ ጳጳሳቸውን ላለፉት ሦስት ወራት ሲያወዛግብ መክረሙን የዜናው ምንጮች ተናግረዋል፡፡
ምንጭ፡- አዲስ አድማስ ጋዜጣ
“ተወይኖብኛል… በዶ/ር አድማሱ ፀጋዬ ተልዕኮ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተባርሬአለሁ”
ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ ከሦስት አሥርት ዓመታት የአሜሪካ ቆይታ በኋላ በሚሌኒየሙ መባቻ ወደ አገራቸው ተመልሰው ላለፉት ሰባት ዓመታት በማስተማር ሥራ ላይ ቆይተዋል፡፡ ምሁሩ በዋናነት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፍልስፍና መምህር ቢኾኑም በሕግ ፋክልቲ፣ በሴንተር ፎር ሂዩማን ራይትስ፣ በኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም፣ በአምስት ኪሎ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ፋክልቲ፣ በቴአትሪካል አርትስና በያሬድ የሙዚቃ ት/ቤትም አስተምረዋል፡፡ ለሰባት ተከታታይ ዓመታት በተጠቀሱት የትምህርት መስኮች በተለያየ ጊዜ ሲያስተምሩ ቢቆዩም ከጠየቁት የዓመት ዕረፍት (sabbatical leave) ጋር ተያይዞ ከዩኒቨርስቲው መሰናበታቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ አዲስ አድማስ ጋዜጣ በጉዳዩ ዙሪያ ከዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ ጋር ተከታዩን አጭር ቃለምልልስ አድርጓል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ እና በእርስዎ መካከል ምንድን ነው የተፈጠረው?
ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ አስተዳደር ጋር በኹለት ጥያቄዎች ዙሪያ የማይታረቅ ልዩነት ተፈጥሯል፡፡ በመጀመሪያ የዩኒቨርስቲው የሴኔት ሕግና የቅጥር ውሌ ላይ በግልጽ እንደሰፈረው÷ አንድ መምህር ለስድስት ዓመት በተከታታይ ከአስተማረ፣ ለአገለገለበት ዘመን የአንድ ዓመት የጥናትና ምርምር ዕረፍት (sabbatical leave) እንደሚሰጠው ተደንግጓል፡፡ ኾኖም ግን ዩኒቨርስቲው ‹‹የጡረታ ሥርዓተ – ሒደቱን አላሟላኽም›› በሚል በሕጉ ፊት የማይጸና ሰበብ ፈጥረው ይገባኻል ብለው ከፈቀዱልኝ በኋላ መልሰው ነጥቀውኛል፡፡ ለማንኛውም መምህር ሥርዓተ ሒደቱን የማስፈጸም ሓላፊነት የሰው ሀብት አስተዳደሩ ድርሻ ኾኖ ሳለ፣ እኔን ተጠያቂ ማድረጋቸው ብዙዎችን አስገርሟል::
በነገራችን ላይ የጥናት ዕረፍት ፈቃዴን የጠየቅኹት ከሦስት ዓመት በፊት፣ ስድሳ ዓመት ሳይሞላኝ ነበር፡፡ በየሰበቡ ሲጓተት ስለቆየ ወደ ስድሳ ዓመቱ ገደብ ደረስኹ፡፡ ጉዳዩ ወደ ማኅበራዊ ፍርድ ቤት ከመሔዱ አስቀድሞ ውስጣዊ ተቋማዊ መፍትሔ ለማበጀት ወደ ዩኒቨርስቲው የቦርድ ሰብሳቢ ቀርቦ ምላሽ ስጠባበቅ ከሦስት ወራት በላይ ተቆጥረዋል፡፡
የሥራ ውሌን በተመለከተ፣ የፍልስፍና ትምህርት ክፍል የእኔን የአገልግሎት ቆይታ እንደሚፈልግና በተለይም በቅርቡ ለሚጀምረው የሦስተኛ ዲግሪ መርሐ ግብር ተሳትፎዬ እንደሚጠቅም በሙሉ ድምፅ ተስማምቶ በመወሰኑ ውሌ እንዲራዘም ለማኅበራዊ ሳይንስ ኮሌጅ አካዳሚክ ኮሚሽን ጽፎልኝ ነበር፡፡ የማኅበራዊ ሳይንስ ትምህርት ክፍል ሓላፊዎች በተሰበሰቡበት፣ ኮሚሽኑ ጉዳዩን በአጀንዳ ይዞ ከተወያየበት በኋላ የፍልስፍና ትምህርት ክፍሉን ጥያቄ ዳግመኛ በሙሉ ድምፅ ተስማምቶበት፣ ውሳኔው በማኅበራዊ ሳይንስ ኮሌጅ ዲኑ በፕ/ር ወልደ አምላክ በዕውቀት በኩል የዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት ይኹንታቸውን እንዲሰጡበት(እንዲያጸድቁት) ተጠይቆ ነበር፡፡ ፕሬዝዳንቱ ግን ከአራት ወራት ያኽል ቸልተኝነት በኋላ ‹‹ወረቀቱ ይመጣለታል›› በሚል ለተከታዩ ሴሚስተር እንዳልደለደል በአዲሱ ዲን በኩል ለትምህርት ክፍሉ ሊቀ መንበር መመሪያ አስተላለፉ፡፡ መመሪያው የእኔን መሰል ጥያቄ ባቀረቡ ሌሎች መምህራን ላይም የተላለፈ ነበር፡፡ ከሦስት ወራት በላይ ደመወዜን ይዘው መክፈል ከአቆሙ በኋላ ‹‹ለሚመጣው ሴሚስተር አትመድቡት›› ማለት በአካዳሚያ ቋንቋ ግለሰቡ ተሰናብቷል ማለት ነው፡፡
በመሠረቱ፣ የትምህርት ክፍሌና አካዳሚክ ኮሚሽኑ የሥራ ውሌን መራዘም ተስማምተው ላቀረቡት ጥያቄ ሲኾን እንደወጉ ማጽደቅ አልያም በአስቸኳይ ውሳኔን ማሳወቅ ሲገባ፣ ፕሬዝዳንቱ ከሦስት ወራት በላይ ማቆየታቸው ኢ-ሕጋዊ ነው፤ ሕጉን ጠብቆ በወጉ ለቀረበ ጥያቄ ከሦስት ወራት በላይ ምላሽ አለመስጠት እብሪት፣ ትዕቢትና ማናለብኝነት እንጂ ሌላ ሊኾን አይችልም፤ በተመሳሳይ ወቅት አንድ ዐይነት ጥያቄ በደብዳቤ ከአቀረብነው መምህራን መካከል፣ ለምሳሌ ከኛው ትምህርት ክፍል ዶ/ር በቀለ ጉተማ በሥራው እንዲቀጥል በቃል ትእዛዝ ፈቅደው፣ ለእኔ በአግባቡ ውሳኔ ሳይሰጡ ‹በሚቀጥለው ሴሚስተር እንዳትመድቡት’ ማለት የአድልዎ አቀራረብ ብቻ ሳይኾን በዘፈቀደና በግፊት የሚካሔድ አመራር መኾኑን ያረጋግጣል፡፡ በሌላ በኩል፣ ፕሬዝዳንቱ ዶ/ር አድማሱ ዩኒቨርስቲውን ለመምራት ያላቸውን ብቃት ከዚህ ቀደም በአደባባይ ስለጠየቅኹ በቂም በቀልና ኹን ብለው እኔን ለመጉዳት የደረሱበት ውሳኔ ነው፡፡
የጥናትና ምርምር ዕረፍት(sabbatical leave) በተመለከተ በጊዜው የኮሌጁ ዲን የነበሩት ዶ/ር ገብሬ ይንቴሶ፤ የፕሬዝዳንቱን ፍላጎት ተከትለው ከላይ እንደጠቀስኹት የሰጡኝን ፈቃድ መልሰው ነጥቀውኛል፡፡ ጉዳዩን ለማየት ሥልጣን ወዳለው ፍርድ ቤት ከማምራቴ በፊት፣ የፕሬዝዳንቱን ምላሽ ከወዲኹ ባውቀውም አቤቱታዬን የግድ ለእርሳቸው ማቅረብ ነበረብኝ፡፡
በኮሌጁ የቀድሞ ዲን ውሳኔ ላይ ከዐሥር ገጽ ያላነሰ አባሪ ሰነዶች አያይዤ ጠዋት ላቀረብኹት አቤቱታ፣ ከቀትር በኋላ ‹‹በጥልቅ መርምረን›› በሚል በአንድ መሥመር የኮሌጁ ውሳኔ እንደማይሻር የሚገልጽ ፌዝና የቀልድ ምላሽ ነው የተሰጠኝ፡፡ ይህ የሚያሳየው ፕሬዝዳንቱ ለዩኒቨርስቲው መምህራን ከበሬታ የሌላቸውና አመራራቸውም ከሞራላዊነት የተራቆተ መኾኑን ነው፡፡ እኔ ግን ታዋቂው አርበኛ አበበ አረጋይ በአንድ ወቅት በፋሽስት ጣልያንና በባንዳ ለተከቡበት የተራቡ ጭፍሮቻቸው ‹‹ሞተን አንጠብቃቸውም፤ ተረጋግታችኹ ብሉ›› እንዳሉት፣ ከማባረር ያልተናነሰ የዘገየ አንድ ብጣሽ ወረቀት ገና ለገና ይመጣል ብዬ ሞቼ አልጠብቃቸውም፡፡
ከዚህ ቀደም የጡረታ ጊዜያቸው ደርሶ ለማራዘም የተፈቀደላቸው መምህራን አሉ ? ማለትም በዩኒቨርስቲው አሠራር የጡረታ ጊዜያቸው የደረሰ መምህራን ውላቸውን ማራዘም ይችላሉ?
በተለምዶ ስድሳ ዓመት የሞላቸው መምህራን የውል ማራዘሚያ ጊዜ ይጠይቃሉ፡፡ እኔ የማውቃቸውና በተደጋጋሚ የተጨመረላቸው መምህራንም አሉ፡፡ በጣም አስገራሚና በግቢው አነጋጋሪ የኾነው የእኔና የዶ/ር መረራ ጉዲና የውል ማራዘሚያ ጊዜ መከልከሉ ነው፡፡
ግን የዚህ ኹሉ መነሻ ምንድን ነው ብለው ይገምታሉ?
ከኹሉ በፊት የእኔ መከልከልና መሰናበት ከፖሊቲካ እይታ አኳያ የመነጨ መኾኑ የታወቀ ነው፡፡
ማለት…
በዩኒቨርስቲው በማስተማር ሥራ በቆየኹባቸው ባለፉት ሰባት ዓመታት፣ በጽሑፍና በተለያዩ መድረኮች የማደርጋቸው የዐደባባይ አእምሯዊ እንቅስቃሴዎች አልተወደዱም፡፡ እንዲያውም ለሹመኞች ቅርበት ያላቸው አንዳንድ ወዳጆቼ እንዳጫወቱኝ፣ ‹‹ዳኛቸው፣ ዩኒቨርስቲውን እንደ ደጀንና ገዥ መሬት ተጠቅሞ መድፍ ሲተኩስብን ቆይቷል›› ተብዬአለኹ፡፡ በርግጥ ይህ ዓይነቱ አቋም ከተወሰደ በኋላ በሥራ ገበታዬ እንድቀጥል አለመደረጉ አይገርመኝም፡፡
ከዩኒቨርስቲው በዚኽ መልኩ ሲሰናበቱ ምን ተሰማዎ?
እንደ እውነቱ ከኾነ የተደበላለቀ ስሜት ነው በውስጤ የተፈጠረው፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ፣ ይህ ነገር ከሰባት ዓመት በኋላ መኾኑ አስደስቶኛል። ይኸውም የመጣኹበትን የማስተማር ዓላማ ከሌሎች ባልደረቦቼ ጋር በመኾን ለመስኩ ተተኪና ምሉዕ የኾኑ ተማሪዎች ለማፍራት በመብቃታችን አስደስቶኛል፡፡ ይህ ክልከላና ስንብት በቂ ምሩቃን ባላፈራንበት ከሦስትና ከአራት ዓመት በፊት ቢከሠት ኖሮ አዝን ነበር፡፡ በኹለተኛ ደረጃ፣ ‹የዓመት ዕረፍት(ሳባቲካል) አይሰጥኽም፤ ከእንግዲኽ ማስተማርም አትችልም› ስባል ለራሴ በጥልቀት ተሰምቶኝ ያልኹት፣ ‹‹አኹን ገና ኢትዮጵያዊ ኾንኩ፤ ኢትዮጵያዊ ማለት መብቱ የሚረገጥ ማለት ነው›› የሚል ነበር፡፡ በዚኽ ሰባት ዓመት ቆይታዬ ከአሜሪካ ሳልፈታ ይዠው የመጣኹት የነፃነትና የመብት አቅዋም፣ ከአገራችን ፖሊቲካዊ ነባራዊ ዕቀባ በተፃራሪው እንደ ልቤ እንድተችና ያለገደብ እንድናገር አስችሎኝ ነበር፡፡ አኹን ግን ሥርዓቱ ‹ይኼ አሜሪካ አይደለም፤ እንደ ጎረቤትኽ ሳይኾን እንደቤትኽ እደር› ብሎኛል፡፡ ይህን ስል ግን፣ እኔ በዕድሜዬ የምወልዳቸው ልጆች በኾነ ባልኾነ ክሥ ወኅኒ ቤት ተወርውረው ባሉበት ኹኔታ ከሥራ አባረሩኝ ብዬ የማለቅስ ሰው አይደለኹም፡፡ በእኒኽ ብሩህ ተስፋ ባላቸው ወጣቶች ላይ ከደረሰው አንጻር ሲታይ መብቴ መረገጡ እውነት ቢኾንም፣ የአገራችን ተረት ‹‹እናቱ ውኃ ልትቀዳ የወረደች ልጅና እናቱ የሞተችበት ልጅ አንድ ጋር ቆመው ያለቅሳሉ›› እንደሚባለው ይመስልብኛል፡፡
በመጨረሻም በአንድ በኩል፣ በውጭ ለብዙ ዓመት ቆይቼ ስመጣ የኢትዮጵያ ሕዝብ የት ከረምክ ሳይለኝ፣ ችሎታዬ በሚፈቅድልኝ ቦታ ሥራ ሰጠኝ፡፡ ለዚኽ ትልቅ ምስጋና ነው የማቀርበው፡፡ ኾኖም በሌላ በኩል የውስጥ አስተዳደሩና የውጭ የፖሊቲካ ኃይሎች በመተባበር መክረው ከሕዝብ ባገኘኹት ቸርነት ላይ ወይነውብኛል!
ከዚኽ በኋላስ ምን ዓይነት ሥራ ላይ ለማተኮር ያስባሉ?
ይህን ጥያቄ ዴሞክራሲና የሕግ የበላይነት ባለበት አገር ብትጠይቀኝ ኖሮ፣ ጉዳዩ በራሴ የሚወሰን በመኾኑ አኹኑኑ እመልስልኽ ነበር፤ ነገር ግን እንደ ቤትኽ እደር ተብዬአለኹና የጥያቄው ምላሽ በእኔ ብቻ የሚወሰን አይደለም፡፡ እንዲያውም ጥያቄው በአንድ ወቅት ዐፄ ኃይለ ሥላሴ አሉ የተባለውን ያስታውሰኛል፡፡ አንድ ሹም ጃንሆይ ፊት ቀርበው የንጉሡ ትችትና ተግሣጽ ሲገጥማቸው፣ ‹‹እንዲያውም ግርማዊ ሆይ፣ የሰጡኝ ሹመት ይቅርብኝ፤ የአባቴን ርስት እያረስኩ እኖራለኹ›› አሏቸው፡፡ ጃንሆይም ወዲያው ‹‹እርሱንም እኛ ስንፈቅድ ነው…›› አሉ ይባላል፡፡
እኔም እንደ አቅሜ ለመሥራት ፍላጎት ቢኖረኝም፣ በቀጣይ ምን መሥራት እንደምችልና እንደማልችል ብያኔው በመሠረቱ ከእኔ ውጭ ነው፡፡ በተቻለኝ መጠን ግን በአለችኝ ቀሪ ዕድሜ አገሬን ለማገልገል ዝግጁ ነኝ፡ በዚኹ አጋጣሚ በቅርቡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሚገኝበትን ተቋማዊ ኹኔታ በተመለከተ አንድ ጽሑፍ እንደማቀርብ ከወዲኹ ለማሳወቅ እወዳለኹ፡፡
ምንጭ፡-አዲስ አድማስ ጋዜጣ
የማለዳ ወግ … ለሃጅ ጸሎት መጥቶ ሳውዲ የቀረው ገበሬ እንግልት
ነብዩ ሲራክ
(ከሳውዲ ዓረቢያ)
ወንድም ራያ ጀማል የ5 ወንድ እና የ3 ሴት ልጆች ጎልማሳ አባት ነው። ወደ ሳውዲ የመጣው ድህነት ፣ የኑሮ ውድነት ፣ የፖለቲካው ሙቀት አለያም የተሻለ ኑሮ ፍለጋ ገፍቶት አይደለም ። ሳውዲ የመጣው ፣ በእስልምና እምነቱ በሚያዘው መሰረት በህይወት ዘመኑ የሚጠበቅበትን ለማድረግ ከብቶቹን ሽጦ የሃጅ ጸሎት ለማድረግ ነበር … ዳሩ ግና የጅማው ገበሬ ራያ ጀማል እንደ ቀሩት ጓደኞቹ ጸሎቱን አድርጎ ለመመለስ አልቀናውም! ከሀጃጅ ጓደኞቹ ተለይቶ ከቤተሰብ እንደራቀ ፣ ላለፉት ሁለት አመት ከመንፈቅ ገደማ ሳውዲ በእንግልት ጊዜውን ሊገፋ ግድ ብሎታል ። ምክንያቱም የሃጅ ጸሎቱን ከውኖ መካ ውስጥ መኪና አደጋ ደረሰበትና ነው !
የራያ ጀማል ጉዳት …
ራያ ጀማል በደረሰበት የመኪና ግጭት የተለያየ የአካሉ ክፍል በጠና ስለተጎዳ በከፍተኛ ህክምና መካ ውስጥ ለሁለት አመት ተኩል ገደማ በሳውዲ የመንግስት ሆስፒታል ሲረዳ ቆይቷል። የመጓጓዣ የማረፊያና የኢንሹራንስ እስከ 55 ሽህ ብር የሚደርስ ገንዘብ ከፍሏቸው ለጸሎት ያማጡት የሃጅ ኮሚቴዎችም ሆኑ የጅዳ ቆንስል ራያ ጀማልን ሊረዱት ቀርቶ ሊያዩት አልቻሉም! ይህ የሆነው ስለ ራያ ጀማል መረጃ ስላልነበራቸው አይመስለኝም ፣ ይህን ስል መረጃው እንደነበራቸው እኔም መረጃ አለኝና ነው!
ለሃጅ ጸሎት መጥቶ ስለደረሰበት የመኪና አደጋ በያዝነው ሳምንት የ50 ኢዩቬልዩ በአሉን ባከበረው የጀርመን ራዲዮ ዜናውን አቅርበነው ነበርና የቆንስሉም የሃጅ ኮሚቴ ኃላፊዎች ያውቃሉ ! ከዚህ ሁሉ በኋላም ልክ የዛሬ አንድ አመት ገደማ የጅዳ ቆንስል ተወካይ ራያ ጀማል በነበረበት የሽሻ ሆስፒታል ለሌላ ጉዳይ ሄደው አግኝተውትም እንደነበር ተገፊው ወንድም አጫውቶኛል ። ተወካዩ ራያ ጀማልን ስላጋጠመው የመኪና አደጋ በዝርዝር ጠይቀውት መመለሳቸውን ከተጎጅው ጋር በያዝነው ሳምንት ባንድ ምሽት ከወደቀበት የጅዳ ቆንስል አካባቢ በሚገኘው የአንድ አረብ ሃብታም አጥር ኩርትም ብሎ ባገኘሁት አጋጣሚ አጫውቶኛል። ይህ ሁሉ ሆኖ የዜጎች ጉዳይ የሚለመከታቸው የቆንስል ኃላፊዎች ራያ ጀማልም ሆነ ጉዳዩ የት ደረሰ ? ብለው አልጠየቁም !
ራያ ጀማልን ሳገኘው …
የወንድም ራያ ጀማልን ወደ ጅዳ መምጣትና አቤቱታ የማቅረቡ መረጃ ደረሰኝ ። ፈልጌ አጣሁት ። አንድ ምሽት ወደ ኮሚኒቲ ካፍቴሪያ ሳዘግም ከግቢው ውጭ ባለ አጥር ታዛ ተኝቶ አየሁት ። ራያ ጀማል ነው ግን አላልኩም። ተጠግቸ ለማነጋገር ብሞክርም መተኛቱን ተረዳሁና ትቸው ሄድኩ። በካፍቴሪያ አካባቢ ስለወደቀው ወንድም ጠየቅኩ ፣ ራያ ጀማል ለመሆኑ በቂ ምልክቱ በምርኩዝ “ክራንች ” እየታገዘ እንደሚመላለስ ሲነገረኝ አገግሞ ከመካ ሽሻ ሆስፒታል የወጣው ራያ ጀማል መሆኑን ተረዳሁ።
ራያ ጀማልን በቀጣዩ ቀን አግኝቸው አወጋን ። ከሁለት አመት በላይ በሳውዲ የመንግስት ሃኪም ቤት በህክምና ሲረዳ የቆየው ኢትዮጵያዊ በቀኝ ጎኑ ደገፍ በሚልባት ምርኩዝ “ክራንች” እየታገዘ ፣ አያነከስ ጉዳዩን ለማስፈጸም ላይ ታች ይላል። ፍትህ ሊያገኝና ወደ ሀገሩ ሊሸኝ ፣ የሞት መርዶውን ሰምተው ያለቀሱ ቤተሰቡን ተሰናክሎም ቢሆን ይቀላቀል ዘንድ ተስፋ ሰንቆ ከመጣበት ቤቱ የሚደግፈውም ሆነ ፣ ለጎኑ ማሳረፊያ መጠለያ የሚሰጠው አጥቷል ። የገዛ ሃገሩ ሰዎች ክብር አልሰጠነውምና በዚህ ሙቀት ከቆንስሉ ርቆ ባለው የአረብ ግንብ ጠጋ ብሎ ውሎ ያድራል …
ራያ ጀማልን ከፍ ሲል ኢትዮጵያዊነቱ ፣ ዝቅ ሲል ቋንቋውን የሚናገሩት የቀየው ልጆች ሞልተው ተርፈዋል ፣ ሁላችንም ግን ጉዳቱን እንኳ ጠጋ ብለን መጠየቅ ገዶናል ። አቅም የለሾቹ በጥድፊያው ብንወጠር ጧትና ማታ የሚያዩት የቆንስል ዲፕሎማቶችና የልማት ማህበር አባላት ብሶቱን ሰምተው ለምን ጨከኑበት ? ማለቴ አልቀረም …መልስ የለኝምና አዘንኩ !
የወንድም ራያ ጀማልን ጉዳይ በቅርብ ርቀት ላለፉት ሁለት ሳምንታት ላላነሰ ጊዜ ስከታተል ቆየሁ ። ጉዳዩ በቆንስ ኃላፊዎች በኩል ለጉዳይ ፈጻሚው ተላልፎ ጉዳዩ ሲንከባለል ቢሰነብትም ወደ መጨረሻ ራያ ጀማል ወደ ሀገሩ ለመላክ መወሰኑና ቲኬት ኮሚኒቲው እንዲያቀርብ ትብብር በቆንስል ሸሪፍ የመጠየቁ መረጃ ከአንድ የኮሚኒቲ የምክር ቤት አባል መረጃው ደረሰኝ ።
( በዚህ ዙሪያ ትናንት ባቀረብኩት ተመሳሳይ መረጃ ቅሬታ ያቀረቡልኝ አንድ ጠቋሚ ሃሳብ በመቀበል ሳጣራ ግን ቆንድል ሸሪፍ ኬሩ ራያ የ ጀማል የቲኬት ጥያቄውን ለኮሚኒቲ እንዲያቀርብ በስሙ ደበዳቤ ጽፈው ማዘጋጀታቸውንና ለኮሚኒቲው ምክትል በስልክ “ተባበሩት “ማለታቸውን ማረጋገጥ ችያለሁ)
ከቆንስሉ ግቢ ለቀን ወደ ኮሚኒቲ ጉዳዩን ለማጣራት ራያና እኔ ተያይዘን ስንወጣ ከቆንስሉ ባለጉዳዮች መግቢያ በር ነጻ ግልጋሎት የሚሰጡትን የድርጅትና የኦሮሞ ልማት ማህበር አባል ጋር ተገናኘን ። ሳያቸው በስጨት አልኩና ስማቸውን ጠርቸ ” የዚህ ወንድም ጉዳይ ወደ ሃገሩ ለመላክ ሲወሰን አንድም እንደ ዜጋ አለያም እንደ ተወላጅ ለምን መብቱን ማስከበር ለምን ተሳናችሁ? ” ስል ጠየቅኳቸው ። ግራ ተጋብተው …” ይህ ወንድም እንደ ተገልጋይ ሲወጣ ሲገባ ከማየት ውጭ ታሪኩን አላውቅም! ” ብለው ሲመልሱልኝ ራያን እንዲጠይቁት አድርጌ በኦሮምኛ አውርተው ጨረሱ ፣ወደኔ መለስ ብለው ” እውነት እልሃለሁ ፣ ምንም አይነት መረጃ የለኝም!” በማለት በአግርሞት መልሰውልኝ በእንግልቱ ዙሪያ ስናወጋ ሌላው የጅዳ ኮሚኒቲና የኦሮምያ ድርብ ስልጣን ያላቸው እድሜ ጠገብ ወዳጀን አገኘኋቸው …
ለኃላፊው ኮሚኒቲውም ቲኬት እንዲያቀርብ መጠየቁን በማውሳት “ራያው ጀማል ጉዳዩን ሳይጨርስ ለምን ቲኬት ለመስጠት ተስማማችሁ? ” ብየ ጠየቅኳቸው ። ኃላፊውም ስለ ቲኬቱ ጥያቄው መቅረቡን ከማመን ባለፈ በጉዳዩ ላይ ውሳኔ አለመሰጠቱን ጠቁመው ጉዳዩን ከቆንስል ሸሪፍ ኬሩ ጋር እየተነጋገሩበት እንደሆነ ጠቁመውኛል ። ከእኒህ ወዳጀ ጋር ውይይታችን እንደቀጠልን ወደ ካፍቴርያው አመራን። በድጋሜ ከራያ ጀማል ማግኘት አለባቸው የምለውን መረጃ ጠይቀው እንዲረዱ አደረግኩ ። መጠለያን በሚመለከትም ሃላፊነቱን ቆንስሉ ከወሰደ መጠጊያ እንደማይጠፋ በመጠቆም ፈቃድ ያመጡልኝ ዘንድም አሳሰብኳቸው ። ከሰነበተበት ሜዳ ወደ የግል መጠለያ ለመውሰድ ፍቃዱን እንደሚጠይቁልኝ አጫወቱኝ ። ኃላፊው የሰጡኝን ምላሽ ሁሉንም ለማመን ሞከሬ እንዲከታተሉት ጭምር ተመካክረን ተለያየን !
ይህ ከሆነ ከአንድ ቀን በኋላ የኦሮሞ ተወላጆች ማህበር አመታዊ በአላቸውን ሊያከብሩ ስለ አከባበሩ ዝግጅት መክረው ሲወጡ የኦሮሞው ተወላጅ ኢትዮጵያዊ ራያ ጀማል ጉዳይ በተሰብሳቢዎች ተነስቶ ራያ ጀማልን ማነጋገራቸውን ሰማሁ ። ሁሉም በሆነው አዝነው በተለይም የድርጅት አባላቱ በቁጭት ለመፍትሄው ከቆንስሉ ጋር እንደሚመክሩ ጠቁመው ፣ ማረፊያ እስኪ ያዘጋጁለት በቆንስሉ ግቢ እንዲያድር አድረገው ተለያዩ ።
መሽቶ ነጋ ፣ የተባለው ደረሰ ፣ ቃል የገቡት የውሃ ሽታ ሆነው ቀሩ ! ባዩት ያዘኑት ሰብዕና አስገድዷቸው ለወንድም ራያ ጀማል ጎኑን የሚያሳርፍባት ፍራሽና መላብስ እንባቸውን እያዘሩ አቀብለውት ብቻ አልሄዱም ። እስከ ዛሬ ደረስ አደየመጡ ይጠይቁታል ! ራያ ጀማል ከዚያች ቀን በኋላ በኦሮሚያ ማህበር አባላት የዚያች ምሽት ተማጽኖ ከኮሚኒቲው ግቢ ማደር ቢችልም በቀጣዩ ቀናት ከቆንስሉና ከኮሚኒ ቲው ግቢ እንዳያድር ተከለከለ ! ወንድም ራያ ጀማል ያገገመው ስብራቱ በእንግልቱ እየተቀሰቀሰ እየወጋው እየተሰቃየ ነው ። ከሃገሩ ባንዴራ የቅርብ ርቀት ባሉት የአረብ ሃብታሞች አጥር ታዛ ኑሮን በመከራ በመግፋት ላይ ነው !
“ጉዳዩ ተሸፋፍኖ ሊሄድ ነው!” ብለን የሰጋነው የራያ ጀማል ጉዳይ ብዙዎቻችን ያስቆጨ ቢሆንም ዛሬ ነገሮች ተቀያይረዋል ብየ ነበር ከቀናት በፊት ። ይህንንም ያልኩት የቆንስሉ ጉዳይ ፈጻሚ አቶ መሃዲና ወንድም ራያ ጀማል ወደ መካ በማቅናት ከመካ ትራፊክ ፖሊስ ጋር የመነጋገራቸውን ሰናይ መረጃ ሰምቸ ነበርና ነው … እቀጥልበታለሁ ብየ ጉዳዩን በእንጥልጥል የተውኩት ጉዳይ ፈጻሚውና ወንድም ራያ ጀማል ከመካው ጉዞ ያገኙትን ውጤት ይዠ ለማምጣት ይቻለኛልና ነበር ። አነሆ ጉዳዩ የተያዘበትን የመካ ትራፊክ ፖሊስን ያነጋገሩት ጉዳይ ፈጻሚ የራያን መዝገብ አስቀርበው የገጨውን መኪና ባለቤት በስልክ ማነጋገራቸውን ተገፊው ወንድም አጫውቶኛል። ከዚህ ቀደም ራያ በሆስፒታል እያለ 10 ሽህ የሳውዲ ሪያል ሊሰጡት ፈቃደኛ ሆነው የነበሩት ሳውዲ ዛሬ 3 ሽህ ሪያል ካሳ ሊከፍሉ ፍቃደኛ መሆናቸውን መግለጻቸው ይህም ካልተቀበሉ ወደ ፍርድ ቤት መሄድ እንደሚችሉ መነገራቸውን ራያ ጀማል ገልጾልኛል። ወንድም ራያ ከአመት በፊት የሆነውን እያስታወሰ ይህው ሳውዲ የገጨው መኪና ባለቤት ወደ ሆስፒታል መጥተው “10 ሽህ ሪያል ካሳ ልክፈልህ እና ሹፊሬ ከእስር ይፈታ !” ብለው የሆስፒታሉ ዶክተሮች መቃወማቸውን ይናገራል። ምክንያታቸው ደግሞ “ጉዳቱ ከፍተኛ በመሆኑ በክፍያው ማነስ የተነሳ ኢንባሲ ቢጠይቀን አደጋ እንወድቃለን” በማለት ዶክተሮች ፈቃደኛ ባለመሆናቸውን ጉዳዩ መጨናገፉን ራያ ጀማል ከኦሮምኛና አረብኛውን ከአማርኛ ጋር እየቀላቀለ በቁጭት አጫውቶኛል።
ትናንት ምሽት ወንድም ራያ ጀማልን ደጋግሞ ስልክ ደውሎ እንድጎበኘው ጠይቆኝ ላነጋግረው ሄድኩ …ጉዳዩን ሰምቶ ብዙዎች ተስፋ ሰጥተነው የነበረው ተስፋ ተሟጦበት አገኘሁት ። ዛሬስ ምን አዲስ ነገር አለ ምን ሆንል አልኩት!
” አይይ አቶ ነቢዩ ትናንትና ዛሬ ሙቀቱም ነው መሰል ወገቤን መላ የተጎዳ አካሌን ይጠዘጥዘኛል፣ ያመኛል፣ ማረፊያ የለኝም ፣ ሜዳ ላይ ለ18 ቀናት ስሰቃይ ማረፊያ ያልሰጡኝ የሚረዱኝ አይመስለኝም ፣ ጉዳየን አሁን አንደዚህ በሜዳ ላይ ሆኘ በፍርድ ቤት ለመከታተል አልችልም!
እዚህ ላይ ራያ ጀማል አደጋ ከደረሰበት ጊዜ ጀምሮ አይተውት የማያውቁት የሃጅ ኮሚቴ ሃላፊዎችም ሆኑ የጅዳ ቆንስል የት ነበሩ? አልልም ። የጅዳን ኮሚኒቲ ቲኬት ከመጠየቁ በፊት መደረግ የነበረበት ጉዳይ ለምን ክትትል አልተደረገም ? አልልም ! የራያ ጀማል ጉዳይ አይነት እና ከዚያም የከፉ የመብት ጥሰቶች ተፈጽመው ቆንስል መስሪያ ቤቱ እያሸማገለ የጨረሳቸው ጉዳዮች በርካታ ናቸው። ያም ሆኖ ጉዳትን ከግምት ያሰረገባ ሽምግልና ነበር ብሎ ለማናገር እንቸገራለን። ይህ ካልሆነ ደግሞ ቢቀር ይሻላል። የመብት ጥሰትን በተልካሻ ካሳ ከማሸማገል ወደ ተገቢ ህጋዊ ፍርድ ቤት ማድረስ ይቀላልና ቢታሰብበት መልካም ነው ። ይህ ከማድግ ባለፈ እያሸማገሉ ጉዳዩን ሸፋፍኖ ተበዳይን ወደ ሀገር መሸኘት ሊቆም ይገባል ! ትናንት በቆንስል መስሪያ ቤቱ ዙሪያ የምናውቀው ፣ ጩኸን ማስቆም ያልቻልነው ጉዳይ በሽፍንፍንና በግዴለሽነት ዛሬ ሁነኛ ኃላፊ መጥተው ነገሮች እየተስተካከሉ ባለበት ሁኔታ በደል በቆዩት ዲፕሎማቶችና በሰራተኞች በእንዝላልነትና በሽፍንፍን ሲያልፍ ማየት ግን ነፍሴ አትፈቅድም !
በራያ ጀማል ጉዳይ እሱ እንዳለው ወራት የሚጨርሰውን ጉዳዩን እዚህ ሆኖ ለመከታተል ይከብዳል። ማረፊያ የለውምና ለከፋ ችግር ላይ ነው ። ራያ ጀማል ያለው ተጨባጭ አማራጭ አንድም መሄድና ወክልና መላክ ፣ መጠላያ አግኝቶ ጉዳዩን መከታተል ፣ ይህ ካልሆነም የሚሰጡትን ተቀብሎ ወደ ቀየው መቀላቀል ብቻ ነው። በእኒህ ውስብስብ አማራጮች ላይ ብቻውን ይወስን ለማለት የሚከብደው የሚሰጠው ሀሳብ ከችግር ጭንቀቱ አንጻር ይሆናልና ተበዳዩ ይጎዳል። የቆንስል ሃላፊዎችና የሚመለከታቸው በዚህ ረገድ አማራጮችን ከህግ አንጻር ተመልክተውና አዋቂ አመካክረው አስፈላጊውን ድጋፍ ቢያደርጉለት ቤተሰቡን በትኖ ለከፋ አደጋ በተዳረገው ወንድም ነፍስ መታደግ መቻል በምድርም በሰማይ ጽድቁ ለራስ ነው! ስለ ራያ ጀማል የማጠቃለው መብቱ እናስከብርለት ፣ የቻልን እንደ አቅማችን እንርዳው በማለት ነው ፣ የምለው ከዚህ ያለፈ አይደለም !
የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች ከዋናው ክሳቸው ውጪ ለሁለተኛ ጊዜ የእስራት ቅጣት ተጣለባቸው
ታምሩ ጽጌ
–አመራሮቹ ቅጣታቸውን በጭብጨባ ተቀብለዋል
የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት የሰጠውን ብይን በጭብጨባ በመቃወማቸው፣ ‹‹ፍርድ ቤትን በመድፈር ወንጀል›› በአንድ ሳምንት ውስጥ ሁለት ጊዜ የእስራት ቅጣት የተወሰነባቸው የአንድነት፣ የአረናና ሰማያዊ ፓርቲዎች አመራሮች፣ ሁለተኛውንም ቅጣት ረዘም ላሉ ሰከንዶች በማጨብጨብ ውሳኔውን ተቃወሙ፡፡
የአንድነት አመራር አቶ ዳንኤል ሽበሺና የሰማያዊ ፓርቲ አመራር አቶ የሺዋስ አሰፋ እያንዳንዳቸው በሰባት ወራት ቀላል እስራት ሲቀጡ፣ ‹‹አሻንጉሊት ፍርድ ቤት›› በማለት ፍርድ ቤቱን ተሳድበዋል የተባሉት የአረና ፓርቲ አመራር አቶ አብርሃ ደስታ፣ በዘጠኝ ወራት እስራት እንዲቀጡ ፍርድ ቤቱ መጋቢት 3 ቀን 2007 ዓ.ም. ውሳኔ ሰጥቷል፡፡
አመራሮቹ ከሦስት ቀናት በፊት ማለትም ሁለተኛው የእስራት ቅጣት ከተወሰነባቸው መጋቢት 1 ቀን 2007 ዓ.ም. በፊት ጥፋተኛ በተባሉበት ፍርድ ቤትን የመድፈር ወንጀል (የካቲት 26 ቀን 2007 ዓ.ም.) እያንዳንዳቸው በሰባት ወራት እስራት እንዲቀጡ መወሰኑ ይታወሳል፡፡ በመሆኑም በአንድ ሳምንት ውስጥ የአንድነትና የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች እያንዳንዳቸው በ14 ወራት እስራት ሲቀጡ፣ የአረና ፓርቲ አመራር አቶ አብርሃ ደስታ በድምሩ 16 ወራት ተቀጥተዋል፡፡
በሽብርተኝነት ወንጀል ክስ ተመሥርቶባቸው በማረሚያ ቤት እስር ላይ የሚገኙት እነዚሁ አመራሮች፣ ለፍርድ ቤቱ ያቀረቡት አቤቱታ በብይን ውድቅ ሲደረግባቸው ተቃውሞአቸውን በችሎቱ ውስጥ በጭብጨባ በመግለጻቸው የችሎቱን ሥራ በማወክ፣ ፍርድ ቤቱን በማንጓጠጥና ተራ ስድብ በመሳደብ፣ በአጠቃላይ ፍርድ ቤት በመድፈር ወንጀል ጥፋተኛ የተባሉ ሲሆን፣ የቅጣት ማቅለያ አስተያየትም አልሰጡም፡፡
የመጀመሪያው ቅጣት መጋቢት 1 ቀን 2007 ዓ.ም. ሲጣልባቸው ከማጨብጨባቸውም በተጨማሪ፣ ፍርድ ቤቱን ‹‹አሻንጉሊት ፍርድ ቤት›› በማለት በመሳደባቸው፣ ባለተለመደ ሁኔታ የፍርድ ቤቱን አሠራር ማወካቸውን ፍርድ ቤቱ በውሳኔው አስረድቷል፡፡ ፍርድ ቤቱ አመራሮቹ ያደረጉትን ፍርድ ቤት የማወክ ተግባር ሲመረምረው ከባድ የወንጀል ድርጊት ሥር የሚወድቅ ሆኖ እንዳገኘው አስታውቋል፡፡ ነገር ግን ዓቃቤ ሕግም ባላመለከተበት ጉዳይ የቅጣት ማክበጃ አስተያየት እንደማይሰጥ በመግለጹ፣ የወንጀል ድርጊቱን ዝቅተኛ በሚል መያዙን ፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡ በመሆኑም በአመራሮቹ ላይ ከላይ የተገለጸውን የእስራት ቅጣት መወሰኑን ግልጽ አድርጓል፡፡ ፍርድ ቤቱ ውሳኔውን ሲያስታውቅ ቅጣት የተጣለባቸው አመራሮቹ ረዘም ላሉ ሰከንዶች ያጨበጨቡ ቢሆንም በዝምታ አልፏቸዋል፡፡ እነሱ በተከሰሱበት የሽብርተኝነት ወንጀል ከተከሰሱት ውስጥ ሰባተኛ ተከሳሽ አቶ አብርሃም ሰለሞን ክሱ እንዲሻሻል ባቀረቡት መቃወሚያ መሠረት ዓቃቤ ሕግ ማሻሻሉ በመረጋገጡ፣ አሥሩም ተጠርጣሪዎች የእምነት ክህደት ቃላቸውን እንዲሰጡ ለመጋቢት 10 ቀን 2007 ዓ.ም. ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡
ምንጭ፡- ሪፖርተር ጋዜጣ





