Daily Archives: March 10th, 2015

ጠበቃ ተማም አባቡልጉ ድብደባ ተፈፀመባቸው

የህግ ባለሙያና ጠበቃ ተማም አባቡልጉ

የህግ ባለሙያና ጠበቃ ተማም አባቡልጉ

በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት በዘለዓለም ወርቃገኘው የክስ መዝገብ የተከሰሱት የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጉዳይ በመያዝ የሕግ አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙት ጠበቃ ተማም አባቡልጉ ድብደባ ተፈፀመባቸው፡፡ ድብደባው የተፈፀመባቸው ዛሬ መጋቢት 1 ቀን 2007 ዓ..ም. እነ አብርሃ ደስታ በነበራቸው የፍርደ ቤት ቀጠሮ ተገኝተው የሚጠበቅባቸውን የሕግ አገልግሎት ሰጥተው ከፍርደ ቤት ከወጡ በኋላ ብሔራዊ አረቄ ፋብሪካ አካባቢ ወደ አዋሳ ለሌላ የህግ አገልግሎት ለመስጠት እያመሩ በነበረበት ወቅት በማያውቁት ግለሰብ ድብደባ እንደተፈፀመባቸው ከስፍራው የደረሰን መረጃ አመልክታል፡፡

ደብዳቢው ግለሰቡ ድብደባ ከፈፀመ በኋላ እሮጦ ለማምለጥ ሲሞክር በአካባቢው በነበሩ ሰዎች ትብብር የተያዘ ሲሆን፤ በወቅቱም ደብዳቢው የአእምሮ ችግር እንዳለበት ለመምሰል ከሞከረ በኋላ የብአዴን-ኢህአዴግ አባል እንደሆነና 400 ብርም እንደተከፈለው መናገሩን እንዲሁም አዲስ አበባ ለቡ አካባቢ 105 ካሬ ሜትር ቦታ ተሰጥቶት ቤት እየሰራ እንደሆነ መግለፁን በስፍራው የነበሩ የዓይን እማኞች ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ ጠበቃ ተማም ነገ አዋሳ ላይ ሌላ የነ ጋዜጠኛ ጌታቸው ወርቁ የፍርድ ቤት ጉዳይ ስላለ ዛሬ የግድ ሄደው ማደር ስለነበረባቸው ደብዳቢውን እንዲለቀቅ አድርገው ወደ አዋሳ ማምራታቸው ታውቋል፡፡

ጠበቃ ተማም ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጉዳይ በተጨማሪ የሙስሊም መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴዎችን፣ የተለያዩ ጋዜጠኞችን፣በሀገር ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ ተቋማትን እና ሌሎች በርካታ የህግ ነክ ጉዳዮችን በተመለከተ ለማኀበረሰቡ አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡ ከጥብቅና አገልግሎት በተጨማሪ በተለያዩ ጋዜጦች የህግ ነክ ጉዳዮችን በተመለከተ ይፅፉ እንደነበር አይዘነጋም፡፡ በዚህም ከመንግሥትና ከስርዓቱ ደጋፊዎች ከፍተኛ ጫና እየተደረገባቸው እንደሆነ ይታወቃል፡፡

የተቃዋሚ ፓርቲዎች አመራሮች ቅጣት ተላለፈባቸው

᎐ተጨማሪ ቅጣትም ይጠብቃቸዋል፡፡
• “እኛ የደፈርነው ችሎት አሻንጉሊት ችሎት ነው” አብርሃ ደስታ
• “ችሎቱ ላይ ያጨበጨብነው በማፌዝ ሳይሆን በምሬት ነው”  የሺዋስ አሰፋ
• “ፍትህ ተጠምተናል፣ ፍትህ ለኢትዮጵያ ህዝብ!”  ዳንኤል   ሺበሽ

politician prisoners

በዘለዓለም ወርቃገኘሁ የክስ መዝገብ የሽብር ክስ ተመስርቶባቸው ከስምንት ወራት በላይ በእስር ላይ የሚገኙት የሰማያዊ፣ የአንድነት እንዲሁም የዓረና ትግራይ ፓርቲዎች አመራሮች ‹ችሎት በመድፈር ወንጀል› ጥፋተኛ በመባላቸው ዛሬ መጋቢት 1 ቀን 2007 ዓ.ም በልደታ ከፍተኛው ፍርድ ቤት በዋለው ችሎት በሦስቱ አመራሮች ላይ እያንዳንዳቸው በሰባት ወራት እስራት እንዲቀጡ ተወስኖባቸዋል፡፡

የካቲት 26 ቀን 2007 ዓ.ም ተከሳሾች በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደተፈጸመባቸውና ንብረትም እንደተወሰደባቸው በመግለጽ አቅርበውት ለነበረው አቤቱታ ፍርድ ቤቱ የማረሚያ ቤቱን ምላሽ ሙሉ ለሙሉ በመቀበል አቤቱታቸውን ውድቅ ማድረጉን ተከትሎ 5ኛ ተከሳሽ አቶ የሺዋስ አሰፋ በማጨብጨቡና 3ኛ ተከሳሽ አብርሃ ደስታና 4ኛ ተከሳሽ አቶ ዳንኤል ሺበሽ ሳይፈቀድላቸው ‹‹ጥሩ ፍርድ፣ ጥሩ ብይን›› በማለት አቶ የሺዋስን በመደገፍ ችሎት ደፍረዋል ተብለው ጥፋተኛ መሰኘታቸው ይታወሳል፡፡ በዚህ መሰረት ፍርድ ቤቱ ለዛሬ የቅጣት ውሳኔ ለመስጠት  ተሰይሞ በአብርሃ ደስታ፣ በየሺዋስ አሰፋ እና ዳንኤል ሺበሽ ላይ የ7 ወራት እስራት በይኖባቸዋል፡፡ ሦስቱም ተከሳሾች ፍርድ ቤቱ የሰጠውን ውሳኔ በመቃወም ድጋሜ ችሎት ውስጥ አጨብጭበዋል፡፡ በዚህም ድጋሜ ጥፋተኛ ተብለዋል፤ ከሁለት ቀናት በኋላም የቅጣት ውሳኔ ይወሰንባቸዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ሦስቱ ተከሳሾች ‹‹እድል ስጡን እንናገር፣ አቤቱታም አለን ተቀበሉን›› ቢሉም ፍርድ ቤቱ ሊሰማቸው አልፈለገም፡፡

በተለይ ዳንኤል ሺበሺ ‹‹ሌላ አቤቱታ አለኝ፣ ፍርድ ቤቱ ያዳምጠኝ›› ብሏል፡፡ ፍርድ ቤቱ አሁንም ችሎቱ ላይ እያፌዛችሁ ነው በሚል ጥፋተኛ ሲላቸው ሦስቱም አመራሮች ፍርድ ቤቱን ማስፈቀድ ሳያስፈልጋቸው አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ ‹‹እኛ የደፈርነው ችሎት አሻንጉሊት ችሎት ነው፡፡ ‹Already› የተደፈረ ችሎት ነው›› ሲል አብርሃ ደስታ ተናግሯል፡፡ በዚህ ጊዜ ዳኞቹ ጣልቃ በመግባት፣ ‹‹የምትናገረው ነገር እንደገና ወደ ማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ የሚወስድህ ጉዳይ ነው፤ ምርመራ ይደረግበታል›› ሲሉ አብርሃ በበኩሉ ‹‹አሁንስ ቢሆን የምናገረውን ፖሊስ እየሰማ አይደለምን?›› ሲል መልሷል፡፡ አቶ የሺዋስ አሰፋ በበኩሉ ‹‹ከስምንት ወር በላይ ታፍነናል፡፡ በህግ አይደለም የተያዝነው፡፡ ደግሞ ማጨብጨባችን በችሎቱ ከማፌዝ ሳይሆን ከምሬት በመነጨ ነው፡፡ ህገ-መንግስታዊ  መብታችን ተጥሷል፡፡ እኔ ለምሳሌ የሰማያዊ ፓርቲ አባል በመሆኔ ነው የታሰርኩት፡፡›› ብሏል፡፡

አቶ ዳንኤል ሺበሽ ድግሞ ‹‹አሁንም ችሎት ደፍራችኋል ካላችሁ ቅጣቱን ጨምሩብንና ሸኙን፡፡ በእርግጥ ዳኞች ላይ ያለውን ጫና እንረዳለን፡፡›› ሲል ችሎት ውስጥ ተናግሯል፡፡
በዚህ ሁኔታ በተከሳሾችና በችሎቱ መካከል ያለው አለመግባባት ሲጨምር ዳኞቹ መጋቢት 3/2007 ዓ.ም ለሁለተኛ ጊዜ የቅጣት ውሳኔ እንደሚሰጥ በመጥቀስ ሦስቱ ተከሳሾች ከችሎት በፖሊስ እንዲወጡ ተደርገዋል፡፡ ከችሎት እየወጡ እያሉም አቶ ዳንኤል ሺበሽ ‹‹ፍትህ ተጠምተናል፤ ፍትህ ለኢትዮጵያ ህዝብ!›› እያለ ችሎቱን ለቅቆ ወጥቷል፡፡

በሌላ በኩል ሦስቱ ተከሳሾች ከችሎት መውጣታቸውን ተከትሎ፣ከዚህ ቀደም በማረሚያ ቤቱ ላይ በቀረበው አቤቱታ ዳኞች በሰጡት አስተያየት ላይ አቤቱታ አቅርቦ እንደነበር በማስታወስ አቤቱታው እንዲመዘገብለት የጠየቀው አቶ ሀብታሙ አያሌው፣ ‹‹በበኩሌ ያሉኝን መረጃዎች እያቀረብኩ ስነ-ስርዓቱን አክብሬ ክርክሩን አቀጥላለሁ›› ሲል ተናግሯል፡፡
ምንጭ፡- ነገረ- ኢትዮጵያ

የኢሬቻ በዓል በደብረ ዝቋላ እንደሚከበር የተላለፈው ዘገባ ማስተባበያ እንዲሰጥበት ተወሰነ

  • ለአፈጻጸሙ የወረዳው እና የዞኑ አስተዳደር ባለሥልጣናት ሓላፊነት ወስደዋል
  • ከመጋቢት ክብረ በዓል በፊት ማስተባበያው እንዲተላለፍ ከስምምነት ተደርሷል
  • ከኹሉም አካላት የተውጣጣ የሽማግሌዎች ኮሚቴ የችግሩን ቆስቋሾች ያጣራል
  • በክብረ በዓሉ ቀን የተጠናከረ ጥበቃ እንዲደረግ መመሪያ ተሰጥቷል
  ዝቋላ አቡነ ገብረመንፈስቅዱስ ገዳም

  ዝቋላ አቡነ ገብረመንፈስቅዱስ ገዳም

  ደብረዘይት/ቢሾፍቱ አካባቢ በሚገኘውና ከ800 ዓመታት ዕድሜ በላይ ባስቆጠረውና በየዓመቱ መጋቢት 5 የሚከበረው ታሪካዊው ደብረ ከዋክብት ዝቋላ አቡነ ገብረመንፈስቅዱስ ገዳም የኢሬቻ በዓል ይከበራል በሚል በክልሉ ፕሬዘዳንት አቶ ሙክታር ከድር በተፃፈና በፀደቀ ደብዳቤ ማስታወቂያና ዜና ተላልፏል መባሉን ተከትሎ በአካባቢው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ኃይማኖት ተከታዮች፣ የሀገረ ስብከቱና የገዳሙ አስተዳዳሪ ለኦሮሚያ ክልል መስተዳደር፣ ለዞኑና ለወረዳው ለሚለከታቸው አካላት ቅሬታ አቅርበው ነበር፡፡ በዚህም መሰረት ፓትርያርኩ ብፁዕ አቡነ ማትያስ ቤተክርስቲያኗን በመወከል ጉዳዩ በህዝቡ መካከል ሆን ብሎ ግጭት ለመቀስቀስና አለመግባባት ለመፍጠር የተደረገ በመሆኑ ቤተክርስቲያኗ ድርጊቱን እንደምትቃወም የሚገልፅ ቅሬታ ለክልሉ መስተዳደር መላካቸው ታውቋል፡፡

  ማስታወቂያውና ዜናው እንዲተላለፍ የተደረገው በክልሉ አበገዳ ተወካዮች ስም ቢሆንም፤ አባገዳዎቹ እነሱ ይህንን ማስታወቂያም እንደማያውቁትና እንደማይመለከታቸው በመግለፅ በሁኔታው መገረማቸው ተጠቁሟል፡፡ ስለሆነም የኢሬቻ በዓል በደብረ ከዋክብት ዝቋላ ገዳም እንደሚከበር የተላለፈው ዘገባና ማስታወቂያ ማስተባበያ እንዲሰጥበት መወሰኑ ሰሞኑን ከክልሉ ባህልና ቱሪዝም የወጡ መረጃዎች አመልክተዋል፡፡ ይህንንም በተመለከተ ሐራ ዘተዋህዶ በአጭሩ የሚከተለውን አጠናቅሮታል፡፡

  • ለእኛ አዲስ ነገር ነው፤ እዚኽ ቦታ ኢሬቻ የለም፤ በአራት ወይም በስምንት ዓመት አንዴ ዝናም እምቢ እንዳይለን ገዳሙን አስፈቅደን ከምንፈጽመው ሥርዐት ውጭ በተነገረው መልኩ የሚከበር በዓል የለም፡፡ ያስተላለፉት መጠየቅ አለባቸው፡፡(የአባ ገዳ ተወካዮች)
  • ህብረተሰቡን ከእኛ ጋራ ሊያጣሉ የሚፈልጉ ግለሰብ አመራሮች አሉ፡፡ለተላለፈው መልእክት ሓላፊነት የሚወስድ አካል ካልተገኘ፣ የመጋቢት ክብረ በዓል ከመድረሱ በፊት በስሕተት የተላለፈ መኾኑ ይገለጽልን፡፡(የገዳሙ አስተዳደር)
  • እናንተ ሰላም ፍጠሩ፤ [በክብረ በዓሉ] ከተለመደው ውጭ አንዳችም የሚደረግ አይኖርም፤ ጥበቃውም እንዲጠናከር ይደረጋል፤የተላለፈውን ዘገባ አጣርተን በኦሮምኛ እና በአማርኛ ማስተባበያ እንዲሰጥበት እናደርጋለን፡፡(የዞን የአስተዳደርና ፀጥታ ኃላፊዎች)

የማለዳ ወግ…ለተሃድሶ ጀማሪዎች ለጅዳ ቆንሰል ተማጽኖየ !

 * ፖለቲካውን እንደርስበታለን መብት በማስከበሩ ላይ በርቱ

ነብዩ ሲራክ

ነብዩ ሲራክ

ሰሞነኛ ወጋችን ፍተሻ ፣ አሰሳ ፣ ማጣራት ሆነና ልብን በሃዘን የሚሰብሩት ጩኸት እንዳይረሳ ሰጋሁ ። ለነገሩ የሳውዲ መገናኛ ብዙሃን በሚለቋቸው መረጃዎች ልክ መረጃ ተለዋውጠናል ባይባልም ፣ ያለፈውን አመትና የቆየውን ሁከት የሚያሳይ የቆየ ተንቀሳቃሽ ምስል እየለጠፉ የቆየነው አዲስ ነው ሳይሉና ሳያሳውቁን መረጃውን የሚለቁ የራሳቸን ሰዎች ተበራክተዋል። በዚህም ፍተሻ አለ የለም ወደሚለው አተካራ እየተዶልን ይመስላል። ተወደደም ተጠላ የሰው ሃገር የሰው ነው ፣ ሳውዲዎች በሃገራቸው ሰማይ ስር እንኳንስ በአደባባይ በተናገሩት ጊዜ ባሻቸው ጊዜ ህገ ወጥ ያሉትን ይዘው የማባረር መብት አላቸው ። አለመቀደም ነው እንጅ ሲላቸው ም የጠራረጉትን ጠራርገው ሲያበቁ ሁሉ ትተው የምህረት አዋጅ ሲሉ እናውቃለን ። ይህ ሲወርድ ሲዋረድ የምናውቀው አሰራራቸው ነው ። የዘንድሮውን ለየት የሚያፈርገው ” የምህረት አዋጅ የሚባል ነገር አይታሰብም “ማለቱ አይደለም ። ይልቁንም ስራቸውን በጣም በተረጋጋ ሁኔታ የመብት ጥሰት እንዳይኖርና ማህበራዊ ገጾች ጥሰቱን እየተቀባበሉ እንዳያወግዟቸው በጥንቃቄ እየተሰራ መሆኑን ልብ ብለን የግንባር ስጋ ከመሆን ካመለጥን መልካም ነው !

ከሰሞነኛው መረጃ ቅበላ ጎን ለጎን በተለያዪ አላባቢዎች ያሉ ወዳጆቸ ከሚያደርሱኝ መረጃዎች መካከል ሰሞነኛው የአፈሳ ፣ እስራት ፣ ማጣራቱ መረጃ ከአዕምሮየ አላዳፍን ያላቸውን የሚያሙ ግን ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገባ ጉዳዮችን ማንሳት ወደድኩ ! ለዚህ የማለዳ ወግ መነሻ የሆነኝ ባሳለፍነው ሳምንት የዲያስፖራ ምክር ቤት የሚሉትን ለማቋቋም ከተሰበሰቡት የድርጅት ሰዎች አጠራርና የህዝብ ውክልና ጉዳይ ነው። ከአንድ አፍቃሬ ህወሃት ወዳጀ ጋር በዚህ ዙሪያ ስናወጋ ” ያን ሰሞን ተሃድሶ አድራጊውን ቆንስል እንዳላመሰገንክ ዛሬ በዲያስፖራው ጉዳይ ነካከህው! ” ነበር … ቀድሞውንም አሁንም በማይረባውና በማንግባባበትን የፖለቲካ ጉዳይ እንደርስበታለን መብት በማስከበሩ ላይ ግን ኢህአዴግ ምንቴስ ሳንል እንትጋ ፣ በርቱ እንበርታ ስል ባደረግነው ማሳረጊያ ተገወባባን … እናም ሰሞነኛ የመረጃ ግብአቱ ቦታውን ሳያጣብበው ለተገፋት የወገኖቻችን መብት እንደጋገፍ እንበርታ ስል የደረሰኝን መረጃ ተከትሎ በውስጤ ከሚጉላሉት ብዙ አሳዛኝ ታሪኮችን በጨረፍታ ዳስሸ መብት በማስከበሩ ረገድ መስማት የጀመሩት የጅዳ ቆንስል ተወካዮቻችንን ለመብታችን መከበር ጽኑልን ስለ መማጸን ፈለግኩ …

የሰሚራ ጉዳት …
ባሳለፍነው አንድ ቀር ገደማ በጥይት ተመታ በቢሻ ሆስፒታል በጥይት ተመታ ቆስላ በሆስፒታል ስለምትገኘው እህት ጉዳይ በማህበራዊ መረጃ መረቡ በኩል መረጃው ሲሰራጭ እኔም እጅ ገባ ። ብዙም ሳይቆይ በየድህረ ገጾች ተለቀቀ ። እኔም መረጃውን ለማጣራት ያፈረግኩት ሙከራ በተሳካ ማግስት በጅዳ የጅዳ ቆንስል መስሪያ ቤት ወደ ቦታው በማቅናት ተጎጅዋን ማግኘታቸውን፣ ማነጋገራቸውንና ጉዳዩን እየተከታተሉት የመሆኑን የምስራች አበሰሩን ፣ ደስም አለን! ምስጋናም አቀረብን !

ይህ ከሆነ ከሳምንት በኋላ የሰሚራን ጉዳይ ለመከታተል ስሞክር በመረጃ አሰባሰቡ ዙሪያ ያልጠበቅኩት ችግር መከሰቱን ሰማሁ ፣ ረፋዱ ላይ ወደ ጅዳ ቆብስል ጎራ በማለት ጉዳዩን ከያዙት ዲፕሎማት የደረሰኝን መረጃ መሰረት በማድረግ ለማጣራት ብሞክርም ሃላፊው ለስራ ስለወጡ ማግኘት አልቻልኩም ። ያም ሆኖ በቦታው ላገኘኋቸው መልዕክቴን አስተላልፊ ተመለስኩ ! ይህ በእንዲህ እንዳለ በጉዳዩ ዙሪያ ያናከርኩት አንድ ወዳጀ በደረሰኝ መረጃ ዙሪያ አንድ ወንድም ዘርዘር ያለ መረጃ ያለው መልዕክት ከነ ተንቀሳቃሽ ፊልም ጭምር የያዘ መረጃ ማስተላለፉን ጠቆመኝ ። መረጃውን ከያዘው ወንድም መረጃ ትመለከቱት ዘንድ ከዚህ ገሰር አያይዠዋለሁ !

ሩቅያ …
ከወራት በፊት እዚህ ጅዳ ውስጥ በአንድ ት/ቤት የቅርብ ርቀት በተከሰተ የመኪና አደጋ የአሰሪዎቿን ልጆች ለማዳን ስትል ለከባድ አደጋ የተጋለጠች ሩቅያ የተባከች እህት አሳዛኝ ታሪክ አውቃለሁ። የሩቅያ ታሪክ በአረብ መገናኛ ብዙሃን ሳይቀር ቀርቧል። ከአደጋው በኋላ ራሷን የማታውቀው ሩቅያ በአንድ ሆስፒታል ለወራት ስትታከም ቆይታ ” ከህመሟ አገግማለች !” ተብሎ ከሆስፒታል ወጥታለች ። ያለ ወገን ደገሰፊ አምስት እህት ወንድሞችዋን የምታስተምር ትጉህ ክጅ አግር ናት ሰሚራ። ለህክምና ብትወጣም እርዳታ በማድረግ አንዳንድ ኢትዮጵያውያን ነዋሪዎች ግን አልረሷትም ። አደጋ ያደረሰባት ደግሞ ከእስር ወጥቷል ። እንዴት ወጣ አይታወቅም ። በውል ቋሚ የሆነ የሚደግፍ የሚረዳት ግን የለም ። ጉዳዩን በፊት ገጼ ካቀረብኩት በኋላ ለጅዳ ቆንስል አሳውቄ ነበር ። በወቅቱ ሄደው ጠይቀዋታል።እየተመላለሱም ጉዳዩን የተከታተሉ መሆኑን የገለጹልኝ የጅዳ ቆንስል ባለደረባ የሩቅያን ጉዳይ እንዳልረሱት ከቀናት በፊት አጫውተውኛል ። ይሁን … ብዙዎች ግን የሩቅያ ጉዳይ ተድበስብሶ እንዳይቀር እንማጸናለን !

መሐመድ …
መሃመድ ይባላል ፣ በ3 አመት የብላቴና እድሜው ድክ ድክ እያለ ለቀላል ቀዶ ህክምና ወደ ሃኪም ቤት ገባ ፣ ከቀዶ ጥገናው ክፍል ከገባ ከሰአታት በኋላ ከቀዶ ህክምናው ቢወጣም አልነቃ አለ። ሰአታት ተቆጠሩ ፣ ቀኖች ሲከተሉ ጉዳይ አስደንጋጭ እየሆነ መጣ ! ወላጅና የቤተሰብ አባላት የሚይዙ የሚጨብጡት ጠፋባቸው። ህክምናውን ያከናወኑት የሚሰጡት የተስፋ መልስ ጭብጥ እውንት ጠፋበት … ቀናት በቀናት ተተክተው ሳምታት ወርን ሲወልዱ የብላቴናው አለመንቃት በሆስፒታሉ ሃኪሞች ስህተት እንደሆነ ይፋ ተነገረ ! ይህ ሲሆን ታዲያ ከሆስፒታሉ የተሰጠው ምላሽ አስደንጋጭ ነበር ። የሶስት አምት ልጃቸው መሃመድ በህክምና ስህተት ማደንዘዣ በዝቶበት እንዳልነቃነና ይህን ስህተት የፈጸመው ዶር ከስራው መባረሩ ተገልጾላቸው መሃመድ እስኪነቃ አስፈላጊ ህክምናና ክፍል ተሰጥቶት ህክምናውን በነጻ እንደሚቀጥል ለወላጆች መርዶ ተነገራቸው ! ይህንን በደል ለማሰማት ወላጆቹ ከጅዳ ቆንሰል ከፍ እስካሉ የመንግስት መ/ቤቶች ቢደርሱም ሰሚ አላገኙም። እንዲያ ሆኖ ብላቴናው ከሰመመንና ከተኛበት አልጋ ሳይነቃ 11 ኛ አመቱን ዘንድሮ ይዟል …
ጉዳዩ አሳዛኝ ነው ከማለት በላይ ነው … ይህ በደል ወደ ሳውዲ ከፍተኛ የመንግስት አካላት ስለመታወቁ ግን አሁንም እጠራጠራለሁ ፣ ይህንኑ ለማጣራት አምድ ወዳጀ ከቤተሰብ አባላቱ ጋር ሊያገናኘኝ ቃል ገብቶልኛል። ያ ሙሉ አሳዛኙን መረጃ በዝርዝር እናወጋዋለን ! .. ባሳለፋቸው የብላቴናውና የወላጆቹ አስከፊ የጨለማ የመከራ አመታት ብላቴናውን የአልጋ ቁራኛ ህክምና በሚሰጠው ክፍል ሄጀ ለማየት ካንድም ሁለት ሶስቴ በሩ ላይ ደረስ ደርሸ ህመሙን መቋቋም ሳልችል ቀርቸ ሳላየው ተመልሻለሁ ! መውለድ ከባድ መሆኑንም የተረዳሁት ያኔ ነበር … የመሃመድ ጉዳይ በአንባሳደር ተክለአብ በአንባሳደር መርዋን እና በቆንስል ጀኔራል ዘነበ እየታወቀ እልባት የሚሰጥ የሚከታተለው ጠፍቶ ጉዳዩ ተድበስብሶ እዚህ ደርሷል ። ይህም ያማል ! ዘንድሮ ግን በቆንስሉ ትጉህ የተሃድሶው መሪዎች መፍትሔ ያገኙለት ዘንድ እንማጸናለን !

ስላለፈው ወቃሹ ታሪክ እንጅ እኛ አይደለንም፣ አንወቃቀስም …

የጀዛኑን ካልድ ለሶስት አመታት የቀጠለ አበሳ ሰሞኑን እልባት ሊያገኝ መሆኑን ሰምቻለሁ ፣ በካልድም ጉዳይም ሆነ በስም አይጠሬውን የአንድ እህት ሬሳ ታሪክ የምናወራው ዛሬ አይደለም ፣ አልነካካውም ! ስላለፈው መብት ጥሰትና የመብት ጥበቃ ጉድለት መረጃዎችን ከመሰብሰብ አልፈን ፣ ያለፈውን ጉዳይ እያነሳን መወቃቀሱ አይጠቅምም !

ዛሬ ሌላ ቀን ነው ፣ ላለፉት 11 ዓመታት እልባት ካልተሰጠው ከመሃመድ ጉዳይ ጀምሮ እስከ ጀዛኑን ካልድ ፣ በአሰሪዋ የፈላ ውሃ የተደፋባትና ላለፉት አንድ አመት ጉዳዩዋን በጅዳ ቆንስል ሆና የምትከታተለው የሄለን ጉዳይ ፣ በቅርብ በጥይት ከተመታችው የሰሚራ ጉዳይ እና መኪና ተገጭታ አካሏ እስከ ጎደለው ሩቅያ የዜጎችን መብት ለማስከበር የመንግስት ተወካዮች የተከፈተው በር እንዳይዘጋ ስንማጸን ፣ መረጃዎችን በማሰባሰቡ ረገድ ግልጽ መረጃ በመለዋዎጥ የመንግስት ተወካዮች መብታችም ያስከብሩልን ዘንድ ደጋግሜ እማጸናችኋለሁ !

በእሳት አደጋ የወደመውን ታሪካዊ የቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያንን በተመለከተ

የካቲት 21 ቀን 2007 ዓ.ም.  በደረሰው ድንገተኛ የእሳት አደጋ ቃጠሎ ምክንያት 106 ዓመታት ዕድሜ ያስቆጠረው ታሪካዊው የሆሳዕና ደብረ ገነት ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን ህንፃ ሙሉ ለሙሉ መውደሙ ይታወቃል፡፡ ስለሆነም በተቃጠለው ቤተክርስቲያን ምትክ አዲስ ህንፃ ቤተክርስቲያን ለማሰራት በይፋ እንቅስቃሴ በመጀመሩ፤ የገንዘብ ድጋፍ ማድረግ ለምትፈልጉ፡-

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣

ባቴና ቅርንጫፍ፤ ሆሳዕና

ዝግ የባንክ አካውንት ቁጥር  100 011 0719 969

መርዳት እንደሚቻል በመጠቆም፤ ለምታደርጉት ድጋፍ ሁሉ በቤተክርስቲያኗ ስም ከወዲሁ ማመስገኑን የህንፃ አሰሪው ኮሜቴ አስታውቋል፡፡

ለበለጠ መረጃ 

ሀገር ውስጥ ላሉ በስልክ ቁጥር 0912- 446829 ወይም 0913-750229

ከውጭ ሀገር ከሆነ  +254 912-446829 ወይም +254 913 750229  ማነጋገር እንደሚቻል የህንፃ አሰሪው ኮሚቴ አስታውቋል፡፡

የሆሳዕከና ከተማ ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን ከመቃጠሉ በፊት

የሆሳዕከና ከተማ ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን ከመቃጠሉ በፊት

የሆሳዕከና ከተማ ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን የእሳት አደጋ በደረሰበት ወቅት

የሆሳዕከና ከተማ ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን የእሳት አደጋ በደረሰበት ወቅት

%d bloggers like this: