Daily Archives: March 25th, 2015

የተቃዋሚ ፓርቲዎች አመራሮች የእምነት ክህደት ቃላቸውን ‘ሰጡ’

“ኢትዮጵያ ውስጥ ብቸኛው አሸባሪ ህወሓት/ኢህአዴግ ነው” አብርሃ ደስታ
“የጦር ችሎት በሚመስል ችሎት እየተንገላታን ነው” የሺዋስ አሰፋ

prisoners

በዘለዓለም ወርቅአገኘሁ የክስ መዝገብ የሽብር ክስ የተመሰረተባቸው የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችና ሌሎች በተመሳሳይ መዝገቡ የተካተቱ ተከሳሾች በተከሰሱበት ድርጊት ላይ የእምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጡ፡፡

የሰማያዊ፣ የአንድነት እና የዓረና ትግራይ ፓርቲ አመራሮችን ጨምሮ 10 ተከሳሾች መጋቢት 10 ቀን 2007 ዓ.ም በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ 19ኛ ወንጀል ችሎት የቀረቡ ሲሆን ተከሳሾች በቀረበባቸው ክስ ላይ የእምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡ በዚህ መሰረት ከአንደኛ ተከሳሽ ዘላለም ወርቃገኘሁ ጀምሮ፣ “በክሱ ላይ የተመለከተውን ድርጊት ፈጽመዋል ወይስ አልፈጸሙም?” የሚል ተመሳሳይ ጥያቄ ለእያንዳንዳቸው የቀረበላቸው ሲሆን ብዙዎቹ ተከሳሾች ምላሻቸውን በቀጥታ ለመስጠት አለመፈለጋቸውን አሳይተዋል፡፡

1ኛ ተከሳሽ ዘላለም ወርቃገኘሁ ለቀረበለት ጥያቄ፣ “በአቃቤ ህግ እና በፖሊስ ተቀነባብሮ የቀረበብኝን ክስ በተመለከተ ለክሱ እውቅና ላለመስጠት ምንም አልልም፡፡ በክሱ ላይ አስተያየት በመስጠት ለጸረ-ሽብር አዋጁ እውቅና መስጠት አልፈልግም” የሚል መልስ በመስጠቱ ፍርድ ቤቱ ክሱን ክዶ ቃል እንደሰጠ አድርጎ መዝግቦታል፡፡

2ኛ ተከሳሽ ሀብታሙ አያሌው በበኩሉ “በክሱ ላይ የተመለከተውን ድርጊት እንዳልፈጸምኩ እንኳን እኔ ከሳሾቼም በደንብ ያውቃሉ፡፡ ከሳሾቼ እኔ ድርጊቱን የመፈፀም ፍላጎቱም ሀሳቡም እንደሌለኝ ያውቃሉ” ብሏል፡፡

3ኛ ተከሳሽ ዳንኤል ሺበሽ ደግሞ፣ “እኔ ስለ ሽብር የሰማሁት ከአልቃይዳው መሪ ኦሳማ ቢላደን እና መለስ ዜናዊ ነው፡፡ እኔ አሸባሪ አይደለሁም፤ ሀሳቡም ሆነ ፍላጎቱም የለኝም፡፡ ባህሌና እምነቴም አይፈቅድልኝም” ሲል ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡

4ኛ ተከሳሽ አብርሃ ደስታ “አሸባሪ ማለት የፖለቲካም ሆነ ሌላ ዓላማውን ሰላማዊ ዜጎችን በማሸበር ለማስፈፀም የሚሰራ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ብቸኛው አሸባሪ ድርጅት ህወሓት/ኢህአዴግ ነው፡፡ እኔ ደግሞ የዚህ አሸባሪ ድርጅት ተቃዋሚ ነኝ” ብሏል፡፡

5ኛ ተከሳሽ የሺዋስ አሰፋ በበኩሉ፣ “በመጀመሪያ ለመጨረሻ ጊዜ ስለሆነ የምናገረው እንዳታቋርጡኝ አደራ እላለሁ፡፡ ክሱ ቅንብር ነው፡፡ ዳኞችም ህጉ የሰጣቸው ነጻነት አይታይባቸውም፡፡ ይህ 19ኛ ወንጀል ችሎት የጦር ችሎት ነው የሚመስለኝ፡፡ ስለሆነም የጦር ችሎት በሚመስል ችሎት እየተንገላታን ነው” ሲል ተናግሯል፡፡ የሺዋስ በዳኞች በተደጋጋሚ ንግግሩ እንዲቅረጥ ተደርጓል፡፡ በመጨረሻም ክሱን ክዶ ቃል ሰጥቷል በሚል ተመዝገቦለታል፡፡

6ኛ ተከሳሽ ዮናታን ወልዴ፣ “የተዘጋጀብኝን ክስ ያለፍቃዴ እንድተውን እየተገደድኩ ነው” ብሏል፡፡

7ኛ ተከሳሽ አብርሃም ሰለሞን ደግሞ፣ “የተቀነባበረ ክስ ላይ ምንም ማለት አይቻልም” ብሏል፡፡

8ኛ ተከሳሽ ሰለሞን ግርማ፣ “ነፃ ሰው ነኝ፡፡”

9ኛ ተከሳሽ ባህሩ ደጉ “ባህሉንና ፈጣሪውን ከሚያከብር ማህበረሰብ ወጥቼ አሸባሪ ልሆን አልችልም” ሲል አስረድቷል፡፡

10ኛ ተከሳሽ ተስፋዬ ተፈሪ ደግሞ፣ “ድርጊቱን አልፈጸምኩም” ብሏል፡፡

በአጠቃላይ ተከሳሾች ክሱ ላይ የተጠቀሰውን ድርጊት ክደው ቃል በመስጠታቸው አቃቤ ህግ ምስክሮችን እንዲያሰማ ለግንቦት 13፣ 14፣ 15 ቀን 2007 ዓ.ም ለተከታታይ 3 ቀናት ምስክር እንዲሰማ ቀጠሮ መሰጠቱን የነገረ ኢትዮጵያ ዘገባ አመልክታል፡፡

የአንድነት ፓርቲ “ቀብር” ላይ እንገናኝ፤ መቃብሩ ላይም እርም እናዉጣና የአንድነት ሃይሎች ዳብረን እንወጣ ዘንድ ትግሉ ግድ ይለናል!

ተክሌ በቀለ  (የአንድነት ፓርቲ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዘዳንት)

ተክሌ በቀለ (የአንድነት ፓርቲ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዘዳንት)

በአብዛኛዎቻችን ኢትዮጵያዉያን አንድ ጥሩ ባህል አለን፡፡የምንወደዉንና የሚመቻንን ሰዉ በሞት ስናጣ እርም የማዉጣት ባህል፤ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ሆኖ አገኘሁት፡፡ሠዉና የፖለቲካ ድርጅ ባይገናኙም በጉልበተኛ ሃይል እንዲገናኙ ሲደረግ ከማገናኘት ዉጪ ምርጫ የለንምና እናገናኛቸዋልን፡፡

አቅምና ሁኔታዎች በፈቀዱት መጠን የወቅቱን ያገራችን ችግር በመፍታት በኩል የራሱን አስተዋፅኦ እንደሚያበረክት፤ የኢህአዴግ ሰዎችን ጨምሮ ያብዛኛዉ ተራማጅ ኢትዮጵያዊ ቤት እንዲሆን አድርገን ስንገነባዉ(ሲፈጥሩትም ለዚህ ኣላማ ነበር ተብሎ ይታመናል) የነበረዉን አንድነት ፓርቲን በፖለቲካዊ ዉሳኔ የሆነዉ እንዲደርስበት ተደርጓል፡፡አማራጭ እንዲኖር የማይፈልጉት በከፍተኛ የመንግስት ሃላፊነት የተመደቡቱ ጥቂት የህወሓት ቡድኖች የማይጠቅማቸዉን ዉሳኔ እንደወሰኑ ይታወቃል፡፡ ተዉኔቱ በማን ተዘጋጅቶ እነማን እንደተጫወቱትና እነማን ደግሞ ለህዝቡ እንዳደረሱት በተደጋጋሚ ገልጸነዋል፡፡

ፓርቲዉን በተለያዩ ስሞች ሲከሱና ሲፈርጁ ቆይተዉ አመራሩንም በእስርና ድብደባ እያሹ እንዳልተንበረከከና ይበልጥ መጠናከሩን ሲያረጋግጡ ለዚህ ዉሳኔ በቅተዋል፡፡ በ40 ዓመታት ታሪኩ ፓርቲዎችን በመብላትና ከዉስጥና ከዉጭ የሚነሳ ልዩነትን በማቻቻል ሳይሆን በማጥፋት የሚታቀወቀዉ ጥቂት የህወሓት ቡድን አንድነት ፓርቲን ከማጥፋት አሁን ወደ መረጠዉ ደረጃ እንዲወርድ አድርጓል፡፡ታሪክ ሁሉን ይፈርዳል፡፡በጨለማዉ ዘመን ግፍ የተፈፀሞባቸዉ ቡድኖችና የፈሰሰዉ ደምም ተደብቆ ኣልቀረም፡፡ፖለቲካችንን ለማዘመንና ያለፈዉ ግፍ ሁሉ ባይረሳም በይቅር መታለፍ አለበት ብለን ለተነሳን ሃይሎችም እድሉን (በጉልበት በህዝብ ሃብትና በያዙት ስልጣን ተጠቅመዉ) ዘግተዉብናል፡፡ በደም መጨማለቅ በዚህ ያበቃ ዘንድ አሁንም እንታገላለን፡፡የፖለቲካ ትግሉ ሂደትም አይቆምም፡፡ያዉም ይብልጥ የመጠናከር እድል አግኝቷል ተብሎ ይታመናል፡፡የሚያቆመዉ ሃይል የለም፤መጪዉ ግዜ የለዉጥ ነዉ፡፡ለዉጡ እንደይሰረቅና ለሁሉም ይመች ዘንድ የጋራ ትስስርን እንደሚጠይቅ እሙን ነዉ፡፡

ለግዜዉ ከጀርባ ያለዉን ፖለቲካዊ ግፊት ለሌላ ፖለቲካዊ ትግል ትተን የምርጫ ቦርድ ዉሳኔን በመቃወም ክስ መስርተን ወደ ፍርድ ቤት ተብየዉ ወስደንዋል፡፡ ወደ ህግ ለመዉሰድ ስንወስን የፓርቲ ስምና አርማ አስጨንቆን አይደለም፡፡ የደጋፊዎችና አባላት ንብረት ለይምሰልም ቢሆን ያለፍርድ ቤት ትእዛዝ ፖለቲካዊ ዉሳኔ እንግበዉ በመጡ ከህዝብ ግብር በተሰበሰበ ደሞዝ የሚተዳደሩ የክፍለ ከተማ ፖሊስ ሃይሎች ( ህዝባዊ ሃለፊነትን የተሸከመ ተቋም በፖለቲካ እዝና ዉሳኔ የፓርቲን ንብረት ይዘርፋል የሚል እምነት አልነበረንም) ስለተዘረፈብን ሃላፊነታችንን ለመወጣትና ታሪካዊ እልባት እንዲኖረዉ ለማስቻል ነዉ፡፡እንጂማ ራእያችን በእያነዳንዳችን ዉስጥ ቢሆንም የወቅቱ ትግል ግን የነፃነት መሆኑን አጥተነዉ አይደለም፡፡

በወቅቱ የብሔራዊ ስራ አስፈፃሚዉ የወሰነዉ ዉሰኔ የመድብለ ፓርቲ ስርኣቱ ከምን ግዜዉም በላይ ፈተና ላይ መዉደቁና አዲስ ፓርቲ መመስረት ችኮላና ህዝቡን ስርአቱ ለመድብለ ፓርቲ አሁንም ይመቻል፤ጥፋቱ የኛ ነዉ ብሎ መዋሸት መሆኑ፤እስኪያጠፋቸዉ ድረስ ሌሎች ፓርቲዎች ጋ መቀላቀል በተላይም ከምርጫዉ እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ ተስፋ ያላቸዉ አባላት የግል ምርጫቸዉ መሆኑንና አመራሩም ይህን እንደማይቃወም፤የፓርቲዉ አባላት ጉዳዩ በፍ/ቤት እስኪቋጭ ድረስ አመራሩን እንዲጠብቁ ይሀም ለብሔራዊ  ምክር ቤቱ ከሰዓት እንዲቀርብና ተወያይቶ ዉሰኔ እንዲሰጥበት የተስማማ ሲሆን በወቅቱ ሁለት አባላት ብቻ አልተገኙም፡፡ከሰኣት ቢሮዉ የፖሊስ ደንብ በለበሱ የመንግስት አካላት ተዘረፈ፡፡ይህ ደግሞ አእላፍ ወንድሞቻችን ላለፉት 40-50 አመታት በተለያየ ጉራ ተሰልፈዉ በተሰዉለት በተላይም በትግረዋይ ደም/ የትግል ዉጢት ሌላዉ ቀልድ እንደመሆኑ ጉዳዩ አብዛሃዉ የአንድነት ደጋፊና አባል በመሆኑ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት እንወስደዋለን ባልነዉ መሰረትእየታየ ይገኛል፡፡በመሆኑም ጉዳዩን መከታተል የእያነዳንዱ የአንድነት አባልና ደጋፊ የህሊና እዳ ይመስለኛል፡፡በአንድነት ቀብር ላይ አሁንም አንድነታችንን በማረጋገጥ ባብዛሃ ዉሳኔ ቀጣዩን መንድ መጓዝ እንጂ ልንለያይ የሚጋብዝን መንገድ መከተል ያለብን አይምስለኝም፡፡ካለፉት የተቃዉሞ ጎራ በጎዉን ትምህርት መቅሰም የሚኖርብን እንዳለ ይሰማኛል፡፡በችኮላ ፓርቲ ለመመስረት የሚደረግ ሩጫ የስልጣን ሀይልነትን ከማረጋገጥ ባለፈ ለህዝባችን ፋይዳ አለዉ ብየ አልገምትም፡፡ ምርጫቸዉ ላደረጉት ጓዶቼ ግን ስህተት ቢሆን ምርጫቸዉን አከብራለሁ፡፡

udj2best

ጉዳያችንን ወደ ፍርድ ቤት ስንወስደዉ በፍትህ ተቋማቱ ምናልባትም በሰላማዊ ትግል ስልት ስርኣቱን ለመለወጥ ከሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች መካከል ከቀድሞዉ ቅንጅት ቀጥሎ የግፍ ፍርድ ሲበየንበት የነበረዉ ፓርቲ አንድነት እንደሆነ ስተነዉም አይደለም፡፡ ዱባና ቅል አበቃቀሉ ለየቅል የሚለዉ ብሂል እንዳለ ሆኖ ብርቱኳን መደቅሳ፤ዳኛ ፍረህይወት እና ሌሎች (ለህሊናቸዉ የተገዙ ዳኞች አልፎ አልፎም ቢሆን) የተገኙት በዚህ አፋኝ ስርኣት በዘረጋዉ መዋቅርና በህዝባችን ዘንድ እምነት በታጣባቸዉት የፍትህ ተቀዋማት ውስጥ ነዉ፡፡ታድያ እየተፈተኑ የሚወድቁትን ተቋማት ሳይሆን ግለሰብ ዳኞችንም ለመፈተን ይህን ታሪካዊ ክስ ስናቀርብ የግለሰቦችን የህሊና ዳኝነትንም ተስፋ ባለመቁረጥ ጭምር ይሆናል፡፡ ሁሌም እንደምንለዉ ፓርላማ ተቀምጦ የተከበሩ እየተባሉ ለመጠራት ሳይሆን ትግላችን ለለዉጥ ነዉና ድንክየዉን አንድነት ቢመለሱልንም ባይመሉሱልንም፤  የህዝብ ከሆነዉ ትግል መሃል ሆነን ፖለቲካዉን ከመስራት አንታቀብም፡፡ዉሳኔዉም በሁሉም የለዉጥ ሃይሎች ቀጣይ እንቅስቃሴ የራሱ የሆነ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡የአንድነት ልጆች ህወሓት ለመደዉ የጥባጥቤ ጨዋታዉ ቦታ ይኖረናል ተብሎ አይታሰብም፡፡አንድነታቸንን እንደ ጠበቅን የሚቀብሩት ከሆነ የአንድነት ፓርቲ “ቀብር” ላይ እንገናኝ፤ መቃብሩ ላይም እርም እናዉጣና የአንድነት ሃይሎች ዳብረን እንወጣ ዘንድ ትግሉ ግድ ይለናል!

ላለፉት አምስት አመታት ብዙዎቹ በእስር የሚማቅቁበት የተሰደዱለትና የቆሰሉ፤ የደሙለት ፓርቲ አንድነት ነዉ፡፡የብዙ ወገኖችን እና ተቋማትን የፍትህ ጥያቄ በማዉሳት ባደባባይ የጮኸዉ ፓርቲ አንድነት ነዉ፡፡በኢትዮጵያዊነት ማእቀፍ ዉስጥ የብሄረሰቦችን እና የቡድኖችን መሰረታዊ የፖለቲካ ጥያቄ ለመመለስ ቁርጠኝነት የነበረዉ ፓርቲ አንድነት ነዉ፡፡ የህዝብን ጥያቄዎች በጠራ መልኩ በማዉሳት ድምጻቸዉን ከሚያሰሙ ፓርቲዎች ዉስጥ ተጠቃሹ ፓርቲ አንድነት ነዉ፡፡የቅርርብ፤የመደማመጥና የመከባበር ፖለቲካ እንዲኖር ባሳለፋቸዉ አጭር አመታት ጥረት ያደረገ ፓርቲ አንድነት ነዉ፡፡ በዚህም ከህዝብ ብቻ ሳይሆን ለሃገራቸዉ በጎዉን ለዉጥ የሚሹ በርካታ የኢህኣዴግ ተራ አባላትና አንድንድ ባለስልጣናትም ጭምር በበጎ አይን ይመለከቱት እንደነበር ገምግመናል፡፡ በዚህ ወቅት አወንታዊ ተፅእኖ ያመጣል ተብሎ በመፈራቱ ግን ከ40 አመት በኃላም ትቂቱ የህወሓት ቡድን በለመደዉ ስልቱ በልቶታል፡፡

ይህን ድርጊት ለዉጥ ፈላጊ ሃይሎች በጥሞና ይከታተሉታል ተብሎ ይገመታል፡፡የምትችሉ ሁሉ ፍርድ ቤት በመገኘት እስከ ታሪካዊዉ ዉሳኔ እለት ድረስ ሂደቱን ለመዘገብና ለታሪክ ምስክር ለመሆን፤ እንዲሁም አጋርነታችሁን ለመግለፅ ትገኙ ዘንድ የክብር ጥሪ ተላልፏል፡፡እዉነተኛ አንድነት ነባር አመራር፤አባለትና ደጋፊዎች ጉዳዩን በአንድነት እንቋጭኛ እንደስማቸን በአንድነት ቦይ እንፈስ ዘንድ ጥሪ አቀርባለሁ፡፡

አቶ ተክሌ በቀለ (የአንድነት ፓርቲ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዘዳንት)

የ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር ለህዝባዊ ሰልፍ የመረጣቸውን 15 ከተሞች ይፋ አደረገ

  • ሰልፉ እሁድ መጋቢት 20 ቀን 2007 ዓ.ም ይደረጋል
ከግራ ወደ ቀኝ ኢ/ር ይልቃል ጌትነት ከ(ሰማያዊ) እና አቶ ግርማ በቀለ ከ(ኦህዴህ)

ከግራ ወደ ቀኝ ኢ/ር ይልቃል ጌትነት ከ(ሰማያዊ) እና አቶ ግርማ በቀለ ከ(ኦህዴህ)

የ9ኙ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ትብብር ህዝባዊ የድጋፍ ሰልፍና የምርጫ ቅስቀሳ ለማካሄድ የመረጣቸውን 15 ከተሞች ይፋ አደረገ፡፡ ትብብሩ በተመሳሳይ ሰዓት በ15 ዋና ዋና የሀገሪቱ ከተሞች ህዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ ለማድረግ ቀደም ብሎ አሳውቆ እንደነበር ይታወሳል፡፡

በዚህ መሰረት የ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር መጋቢት 20/2007 ዓ.ም በተመሳሳይ ሰዓት ሰልፉን የሚያካሂድባቸው ከተሞች የሚከተሉት ሆነዋል፡፡ እነዚህም አዳማ፣ ባህር ዳር፣ አርባ ምንጭ፣ ደብረ ታቦር፣ ሐዋሳ፣ ጅማ፣ ደብረ ብርሃን፣ ወልቂጤ፣ አሰበ ተፈሪ (ጭሮ)፣ ወላይታ ሶዶ፣ ደሴ፣ ዱራሜ፣ ደብረ ማርቆስ እና ሆሳዕና ናቸው፡፡

ትብብሩ “መጋቢት 20 በፍፁም አይቀርም” በሚል ለህዝቡ የድጋፍ ሰልፍ ጥሪ ያደረገ ሲሆን፣ ከተሞቹ የተመረጡትም ፓርቲዎቹ በየአካባቢዎች ባቀረቡት እጩ ብዛት መሰረት እንደሆነ ገልጹዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ደግሞ በዋና ከተማዋ አዲስ አበባ የሚደረገው የድጋፍ ሰልፍ በተመረጡት ከተሞች የሚደረገው ሰልፍ በተከናወነ በሳምንቱ ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ምንጭ፡- ነገረ-ኢትዮጵያ

የጋዜጠኞቹ እና ብሎገሮቹ አቤቱታዎች ውድቅ ተደረጉ

zone9

በሶልያና ሽመልስ የክስ መዝገብ የሽብር ክስ ተመስርቶባቸው የሚገኙት የዞን ዘጠኝ ጦማርያንና ሦስቱ ወዳጅ ጋዜጠኞች መጋቢት 15 ቀን 2007 ዓ.ም ከሰዓት 8፡00 የፌደራሉ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት ቀርበዋል፡፡

መዝገቡ ተቀጥሮ የነበረው ተከሳሾች ባቀረቧቸው ሁለት አቤቱታዎች ላይ ፍርድ ቤቱ መርምሮ ብይን ለመስጠት ነበር፡፡ በዚህም አንደኛ አቃቤ ህግ በተከሳሾች ላይ አለኝ ካለው ማስረጃ ዝርዝር ውስጥ 12 የኦዲዮ-ቪዲዮ ሲዲዎች አያይዞ ያቀረበ ቢሆንም፣ ሲዲዎቹ ለተከሳሾች እስካሁን ባለመድረሳቸው ተከሳሾች የቀረበባቸውን ማስረጃ ተመልክተው መልስ ለማዘጋጀት ሲዲዎቹ እንዲሰጧቸው ያቀረቡት አቤቱታ ሲሆን፣ ሁለተኛው ጉዳይ ደግሞ 4ኛ ተከሳሽ ማህሌት ፋንታሁን እና 9ኛ ተከሳሽ ኤዶም ካሳዬ በቃሊቲ እስር ቤት አስተዳደር ላይ ከጎብኝዎቻቸው መከልከል ጋር በተያያዘ አቅርበውት በነበረው አቤቱታ ላይ ብይን መስጠት ነበር፡፡ ፍርድ ቤቱም ሁለቱንም አቤቱታዎች ውድቅ አድርጓል፡፡

የሲዲ ማስረጃውን በተመለከተ አቃቤ ህግ ማስረጃዎችን ኢግዚቪት ብሎ ስላስመዘገበ አሁን በዚህ ደረጃ ሲዲዎቹ ለተከሳሾች የሚደርሱበት አግባብ የለም በሚል ፍርድ ቤቱ የተከሳሾችን አቤቱታ እንዳልተቀበለው ገልፀዋል፡፡ በመሆኑም ተከሳሾች ማስረጃ በመስማት ሂደት ወቅት ማስረጃዎችን እየተመለከቱ መልስ እንዲሰጡ እንጂ ቀድሞ እጃቸው የሚደርስበት አሰራር የለም ብሏል ፍርድ ቤቱ፡፡
ፍርድ ቤቱ የቃሊቲ እስር ቤት አስተዳደር ላይ በሁለቱ ሴት ተከሳሾች የቀረበውን አቤቱታም ሳይቀበለው ቀርቷል፡፡ በተከሳሾች የቀረበውን አቤቱታ እና የእስር ቤቱ አስተዳደር የሰጠውን መልስ መመልከቱን የገለጸው ፍርድ ቤቱ፣ “ለቀረበው አቤቱታ ማስረጃ ተያይዞ ያልቀረበ በመሆኑ…” በሚል አቤቱታውን ቅድቅ አድርጓል፡፡ ጦማርያኑ እና ጋዜጠኞች ላይ የአቃቤ ህግ ምስክሮች ከሰኞ መጋቢት 21 ቀን 2007 ጀምሮ ለሦሰት ቀናት ይሰማሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የነገረ-ኢትዮጵያ ዘገባ አመልክቷል፡፡

የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጆች ሹመት ፓትርያርኩንና ረዳት ሊቀ ጳጳሱን እያወዛገበ ነው

  • ረዳት ሊቀ ጳጳሱ የፓትርያርኩን ምደባዎች በደብዳቤ ተቃውመዋል
  • ቋሚ ሲኖዶሱ የጠቅላይ ቤተክህነቱ ሥራ አስኪያጁ ያቀረቡትን አቤቱታ መመልከት ጀምሯል
ብፁዕ አቡነ ቀሌምኒጦስ

ብፁዕ አቡነ ቀሌምኒጦስ

ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አዲስ ዋና ሥራ አስኪያጅ እና ምክትል ሥራ ስኪያጅ መሾማቸውን ተከትሎ ከሀገረ ስብከቱ ረዳት ሊቀ ጳጳስ እና ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ተቃውሞ እንደገጠማቸው ተገለጸ፡፡ኹለቱ ሥራ አስኪያጆች ለሀገረ ስብከቱ መመደባቸው የተገለጸው፣ ከትላንት በስቲያ ኀሙስ ከፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት ለጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ በደብዳቤ በተሰጠ መመሪያ ነው፡፡የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የፓትርያርኩ ልዩ ሀገረ ስብከት እንደኾነና ከረዳት ሊቀ ጳጳሱ ጀምሮ በሀገረ ስብከቱ የሚመደቡ ኃላፊዎችን የመምረጥና የመመደብ ጉዳይ ከብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ጋራ መያያዙን፣ በዚህም መሠረት ሲሠራ እንደቆየ በመመሪያው የተጠቀሰ ሲኾን፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ለኹለቱ ሥዩማን ሥራ አስኪያጆች ምደባቸውን የሚገልጽ ደብዳቤ እንዲያደርሷቸውና ሥራቸውን እንዲጀምሩ ይደረግ ዘንድ ይጠይቃል፡፡ ለጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ በአድራሻ የተጻፈው ይኸው ደብዳቤ፣ በሀገረ ስብከቱ የፓትርያርኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስ ለኾኑት ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ በግልባጭ እንዲያውቁት መደረጉ ተገልጧል፡፡

ረዳት ሊቀ ጳጳሱ የሥራ አስኪያጆቹ ሹመት ከሕገ ቤተ ክርስቲያን፣ ከቃለ ዐዋዲው እና ከሀገሪቱ የሕግ አሠራር ውጭ መኾኑን በመግለጽ ምደባውን በትላንትናው ዕለት ለፓትርያርኩ በጻፉት ደብዳቤ የተቃወሙ ሲኾን፣ ፓትርያርኩ ከሕግ አግባብ ውጭ የሰጡትን መመሪያ እንደገና እንዲያጤኑት መጠየቃቸውም ታውቋል፡፡ በሕገ ቤተ ክርስቲያኑ መሠረት፣ የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ እና ምክትል ሥራ አስኪያጅ ተጠሪነታቸው ለረዳት ሊቀ ጳጳሱ እንጂ ለፓትርያርኩ ኾኖ እንደማያውቅና ሊኾንም እንደማይችል የገለጹት አቡነ ቀሌምንጦስ፣ የፓትርያርኩ አካሔድና የሥራ አስኪያጆች ምርጫ “የሕግ ድጋፍ የሌለው፣ ያልተለመደና የቤተ ክርስቲያኒቱን መዋቅራዊ አሠራር በእጅጉ የሚፃረር ነው” ብለዋል፡፡ አቡነ ማትያስ የሰጡት መመሪያ ተቀባይነት የሚኖረውም ተሿሚዎቹ በሀገረ ስብከቱ ረዳት ሊቀ ጳጳስ ተመርጠው ከቀረቡ በኋላ ምርጫቸው ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ጋር የጋራ ስምምነት ተደርሶበት በፓትርያርኩ ሲሾሙ እንደኾነ በተቃውሟቸው አስረድተዋል፡፡ ፓትርያርኩ ከልዩ ጽ/ቤታቸው በሰጡት መመሪያና በሥራ አስኪያጆች ምርጫዎቻቸው እንደማይስማሙና ምደባውንም ለማስተናገድ እንደሚቸገሩ ያስታወቁት ረዳት ሊቀ ጳጳሱ፣ “ይህ አሠራር ከትዝብት ላይ የሚጥል መኾኑን ተረድተውልን ለቤተ ክርስቲያን ሰላማዊ አሠራርና ለኹላችንም ሰላም ሲባል ውሳኔዎን እንደገና እንዲያጤኑ በታላቅ አክብሮት አሳስባለኹ” ብለዋል – በተቃውሞ ደብዳቤአቸው፡፡
የፓትርያርኩን መመሪያ እንዲያስፈጽሙ በአቡነ ማትያስ መመሪያ የተሰጣቸው የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቡነ ማቴዎስ በበኩላቸው፣ ትላንት ከቀትር በፊት በተደረገው የቋሚ ሲኖዶሱ ሳምንታዊ ስብሰባ መመሪያውን በመቃወም አስተያየታቸውን በቃል ማቅረባቸው ተጠቁሟል፡፡

ስብሰባውን በሊቀ መንበርነት የሚመሩት ፓትርያርኩም አጀንዳው ውሳኔአቸውን የሰጡበት በመኾኑ መታየት የለበትም በሚል ቢቃወሙም ቋሚ ሲኖዶሱ ዋና ሥራ አስኪያጁ ተቃውሟቸውን በጽሑፍ እንዲያቀርቡ ማዘዙ ተገልጧል፡፡ ከትላንት በስቲያ በድንገት ይፋ የኾነው የሀገረ ስብከቱ ተተኪ ሥራ አስኪያጆች ምደባ፥ ‹‹የመልካም አስተዳደር ሒደቱን ማቀላጠፍ›› በሚል ከኹሉ አቀፍ የትምህርት ዝግጅት፣ ከሥነ ምግባርና ከብሔር ተዋፅኦ መስፈርቶች አንጻር ፓትርያርኩንና ረዳት ሊቀ ጳጳሳቸውን ላለፉት ሦስት ወራት ሲያወዛግብ መክረሙን የዜናው ምንጮች ተናግረዋል፡፡

ምንጭ፡- አዲስ አድማስ ጋዜጣ

%d bloggers like this: