በአዲስ አበባ አቃቂ በሚገኘው ቂሊንጦ ወህኒ ቤት በደረሰ የእሳት አደጋ ከ25 ያላነሱ እስረኞች ህይወት አለፈ
(አዲስ ሚዲያ)ዛሬ ነሐሴ 28 ቀን 2008 ዓ.ም. አዲስ አበባ አቃቂ በሚገኘው ቂሊንጦ ወህኒ ቤት በደረሰ የእሳት ቃጠሎ ከ25 ያላነሱ እስረኞች መሞታቸው ተጠቆመ፡፡ በጥበቃ ላይ የነበሩ ወታደሮችም ከእሳቱ ለማለጥ የሞከሩ እስረኞች ላይ ሲተኩሱ እንደነበር ምንጮች አረጋግጠዋል፡፡
ከቃጠሎው በፊት በነበረው ተኩስ ምን ያህል እስረኞች ላይ ጉዳት እንደደረሰ እስካሁን ማረጋገጥ ባይቻልም፤ በነጋታው ጠዋት በነበረው የእሳት አደጋ ከ25 ያላነሱ ሰዎች መሞታቸውን ከቅዱስ ጳውሎስ፣ ሜክሲኮ በሚገኘው ፖሊስ ፣ ጥሩነሽ ቤጂንግ እና የካቲት 12 ሆስፒታል ምንጮች ለማወቅ ተችሏል፡፡ በቃጠሎው ጉዳት የደረሰባቸውና በህይወት የተረፉትም አብዛኞቹ ፖሊስ ሆስፒታልና የካቲት 12 ሆስፒታል በጥበቃ ስር ሆነው ህክምና እየተደረገላቸው እንደሚገኝ ተጠቁሟል፡፡

በወህኒ ቤቱ ታስረው ከሚገኙት መካከል ስመጥር እና ህዝባዊ ተቀባይነት ያላቸው በርካታ የፖለቲካ እስረኞች ያሉበት ሲሆን በተለይም፤ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፣ ፖለቲከኞች፣ የመብት አራማጆች እና ጋዜጠኞች እንደሚገኙበት ይታወቃል፡፡
በያዝነው 2008 ዓ.ም. ብቻ ከአዲስ አበባ አቃቂ ከሚገኘው ቂሊንጦ ወህኒ ቤት በተጨማሪ በርካታ የፖለቲካ እስረኞች የሚገኙባቸው ጎንደር፣ አምቦና ደብረ ታቦር ወህኒ ቤት በተመሳሳይ መልኩ የእሳት አደጋ ሰለባ መሆናቸው አይዘነጋም፡፡ በነበሩ አደጋዎች መንስኤ እና ጉዳትን በተመለከተ የሚመለከተው የመንግሥት አካልም ከመግለፅ መቆጠቡ ይታወቃል፡፡
በተለይ የአቃቂ ቂሊንጦውን እሳት ቃጠሎ ተከትሎ በርካታ የታሳሪ ቤተሰቦች፣ ወዳጆች እና ደጋፊዎች ስጋት እንዳደረባቸው በተለያየ መድረክ ከመግለፅ በተጨማሪ በአዲስ አበባና አጎራባች አካባቢ ያሉ ሰዎች የቤተሰቦቻቸውን ደህንነት ለማጣራት ሙከራ ቢያደርጉም በወህኒ ቤቱ አስተዳደር እንዳልተፈቀደ ተረጋግጧል፡፡ በወህኒ ቤቱ የታሰሩ ቤተሰቦቻቸውን ለመጠየቅ ከተለያዩ የክልል ከተሞች የመጡ ሰዎችም ወደ እስር ቤቱ ግቢም ሆነ ከግቢ ውጭ በቅርብ ርቀት እንዳይጠጉ በመከልከላቸው ወደየመጡበት መመለሳቸውን ምንጮች አረጋግጠዋል፡፡
በአደጋው የደረሰውን ጉዳትና ምክንያት በተመለከተ የወህኒ ቤቱ አስተዳደርም ሆነ መንግሥት እስካሁን የሰጡት መረጃ የለም፡፡ ይሁን እንጂ የተለያዩ ሰዎች አደጋው በመንግሥት ሆን ተብሎ የተቀነባበረና የፖለቲካ እስረኞችን ለመጉዳት የታሰበ የገዥው ስርዓት የተለመደ ስልት እንደሆነ የሚገልፁ ቢኖሩም፤ ስለ አደጋውና አጠቃላይ መረጃ ከገለልተኛ አካልም ሆነ ከመንግሥት ለማወቅ አልተቻለም፡፡
በአማራ ክልል የተቀሰቀሰው ህዝባዊ ተቃውሞ አድማሱን እያሰፋ ቀጥሏል፤ በኦሮሚያ ኢኮኖሚ ተኮር ተቃውሞ እንደሚጀመር ይፋ ተደረገ
ብስራት ወልደሚካኤል
(አዲስ ሚዲያ)የወልቃይት የአማራ ማንነት መብት ጥያቄን መነሻ አድርጎ በጎንደር ፋሲል ከተማ የተጀመረው ህዝባዊ ተቃውሞ፤ የተለያዩ የሰሜን እና ደቡብ ጎንደር ወረዳና ከተሞችን ጨምሮ ወደ ምስራቅና ምዕራብ ጎጃም እንዲሁም ወደ ሰሜን ወሎ መቄት እና ሸዋ ሮቢት መስፋፋቱን እማኞች ለአዲስ ሚዲያ ተናግረዋል፡፡
በተለይ ነሐሴ 18 ቀን 2008 ዓ.ም. በምዕራብ ጎጃም ፍኖተ ሰላም ከተማ፣ ነሐሴ 20 ቀን 2008 ዓ.ም. ቡሬ ወምበራ ወረዳ ቡሬ ከተማ የፀረ አገዛዝ ህዝባዊ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፎች ተካሂደዋል፡፡ በሰሜን ጎንደር በተለያዩ ወረዳዎች እና ከተሞች ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ድረስ ተቃውሞዎች እና የመንግሥት የኃይል ርምጃዎችም የቀጠሉ መሆናቸው ተረጋግጧል፡፡
በጎንደር፣ ባህርዳር እና ደብረማርቆስ ከተሞች ከቤት ያለመውጣት ተከታታይ ህዝባዊ ተቃውሞች የተደረጉ ሲሆን ከነሐሴ 22-25 ቀን 2008 ዓ.ም. ደግሞ በተመሳሳይ ምልኩ በደቡብ ጎንደር ደብረ ታቦር ከተማ ከቤት ያለመውጣት ተቃውሞ እንደሚደረግ መረጃዎች አመልክተዋል፡፡
በአማራ ክልል ባሉ ሰሞንኛ ተቃውሞች በተለይ በማክሰኝት፡በገደብዬ፡በእንፍራንዝ፣ በአብደራፊ፣ በአርማጭሆ፣ በፍኖተ ሰላም፡ቡሬ፡ ጅጋ እና ማንኩሳ በተባሉ ወረዳዎች ህዝባዊ ተቃውሞዎች የበረቱባቸው መሆኑን ያገኘነው መረጃ አመልክቷል፡፡ በነኚህ ስፍራዎች የነበሩ ተቃውሞች መካከልም የተወሰኑ በማኀበራዊ ሚዲያዎች ሲሰራጩ መዋላቸውን ለመታዘብ ተችሏል፡፡
በነበሩ የአማራ ክልል ህዝባዊ ተቃውሞች ሁለት ሰላማዊ ሰዎች በመንግሥት መገደላቸው የተጠቆሙ ሲሆን፤ በተለይ በሰሜን ጎንደር ዞን ባሉ ወረዳዎች በነበሩ ተቃውሞች ጉዳት የደረሰባቸው ዜጎች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል ተገምቷል፡፡
በኦሮሚያ ክልልም ህዝባዊ የፀረ አገዛዝ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ ተቃውሞች የቀጠሉ ሲሆን፤ በዚህም በምዕራብ ሐረርጌ መሰላ ወረዳ በሚገኙ ዋልተሲስ እና ጎሮ በተባሉ መንደሮች በነበረው ህዝባዊ ተቃውሞ አራት ሰላማዊ ዜጎች በመንግሥት በተወሰደ የኃይል ርምጃ መገደላቸው ታውቋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ በሀገሪቱ ያለውን የመንግሥትን ግድያ፣ እስርና እና አፋና በመቃወማቸው በአዲስ አበባ ቂሊንጦ ወህኒ ቤት ለእስር የተዳረጉ የፖለቲካ እስረኞች በተለይም እነ አቶ በቀለ ገርባ በሀገሪቱ ከነሐሴ 19-21 ቀን 2008 ዓ.ም. ብሔራዊ የሀዘን ቀን በሚል ታስቦ እንዲውል ያደረጉት ጥሪ ከወዲሁ በተለያዩ ደጋፊዎቻቸው ተግባራዊ መደረግ መጀመሩ ታውቋል፡፡
የመንግሥት የኃይል ርምጅና ግፍ በመቃወም በሚደረግ ብሔራዊ የሀዘን ቀንም ፀጉር መላጨት፣ ጥቁር ልብስ መልበስ፣ ጥቁር ባንድራ(ጨርቅ) ማውለብለብ፣ ሻማ ማብራት፣ በተቃውሞ ትግሉ የተገደሉ ሰላማዊ ዜጎች ቤተሰቦችን መጎብኘት እና ተሰብስቦ ህዝባዊ ውይይት በማካሄድ እንዲተገበር ጥሪ ማስተላለፋቸውን ተከትሎ በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ ባሉ ዜጎች ከወዲሁ ተግባራዊ መደሩ የሚያመለክቱ የተለያዩ ምስሎች በማኀበራዊ ሚዲያዎች ላይ መሰራጨታቸውን ማየት ተችሏል፡፡
በኦሮሚያ ያለው ህዝባዊ ተቃውሞ ካለው የፖለቲካና ማኀበራዊ ጉዳዮች በተጨማሪ ከጳጉሜ 1 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ የኢኮኖሚ ተኮር ህዝባዊ ተቃውሞችም እንደሚተገበሩ የኦሮሞ ተቃውሞ አስተባባሪዎች እና የመብት አራማጆች ይፋ አድርገዋል፡፡ ይሁን እንጂ የአኮኖሚ ተኮር ህዝባዊ ተቃውሞው ምን ላይ እንደሚያተኩር በዝርዝር የተቀመጠ ነገር ባይኖርም፤ ወደፊት ይፋ እንደሚደረግ የደረሰን መረጃ አመልክቷል፡፡
በታቀደው መሰረት በኦሮሚያ የኢኮኖሚ ተኮር ህዝባዊ ተቃውሞ ተግባራዊ የሚደረግ ከሆነ መንግሥት በክፍተኛ ደረጃ የውጭ ምንዛሪ እጥረትና አደጋ ላይ እንደሚወድቅ ይጠበቃል፡፡ በተለይም መንግሥት ከክልሉ በከፍተኛ ደረጃ የውጭ ምንዛሪና የሀገሪቱ ዋነኛ የገቢ ምንጭ የሆኑት እንደ ቡና፣ የጫት፣ የአበባ፣ የቁም እንሰሳትና፣ የቆዳና ሌጦ እንዲሁም የምግብ ነክ የሆኑ የብግርና ምርቶች እንዲሁም ወርቅና የመሳሰሉ የማዕድን ሃብቶች ከክልሉ እንዳይወጡና ወደ ማዕከላዊም ሆነ የክልሉ ገበያ ንግድ ላይ የማይውሉ ከሆነ ምን አልባትም በሀገሪቱ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ከባድ ፈተና በመንግሥት ላይ ሊደርስ እንደሚችል ይጠበቃል፡፡
የኢኮኖሚ ተኮር ህዝባዊ ተቃውሞ በቀጣይ ወደሌሎች ክልሎች በተለይም አማራ እና ደቡብ ክልል የሚዛመት ከሆነ ደግሞ የመንግሥት 90% የገቢ ምንጭ በማድረቅ ስርዓቱን ሙሉ ለሙሉ አደጋ ላይ እንደሚጥለው ይገመታል፡፡ በተለይ ኦሮሚያ እና አማራ ክልል ብቻ የሀገሪቱን 54% የሆነውን ህዝብ ቁጥር እንደሚሸፍኑ እና ከ65% የሀገሪቱ የውጭ ምንዛሪና የገቢ ምንጭም መሆናቸው ይታወቃል፡፡
ከባለፈው ህዳር 22 ቀን 2008 ዓ.ም. በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ የተቀጣጠለው የፀረ አገዛዝ ህዝባዊ ተቃውሞ መላው ኦሮሚያ ክልልን በማዳረስ፤ ከሐምሌ 5 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ ወደ አማራ ክልል ተዛምቷል፡፡ በሁለቱም ክልሎች ዘገባው እስከተጠናቀረበት ድረስ ህዝባዊ ተቃውሞዎቹ በተለያዩ ወረዳዎችና ከተሞች ቀጥሏል፡፡ እስካሁን ባለው መረጃ በሁለቱም ክልሎች ባሉ የተለያዩ ቦታዎች መደበኛ የመንግሥት ስራን ጨምሮ የተለያዩ ፖለቲካዊ፣ ማኀበራዊና ኢኮኖሚያዊ አለመረጋጋቶች እየታዩ ነው፡፡
አስረኛ ወሩን ባስቀጠረው ህዝባዊ ተቃውሞ በሁለቱም ክልሎች ከ650 በላይ ሰላማዊ ዜጎች በመንግሥት በተወሰደ የኃይል ርምጃ ሲገደሉ፣ ከ 1,250 ያላነሱ ዜጎች ቆስለው በግምት ከ35,000 በላይ ሰዎች ለእስር ተዳርገዋል፡፡ በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች የተገደሉ እና የቆሰሉ ሰዎች በተለያየ ጊዜ ስማቸውና ምስላቸው በሰፊው በማኀበራዊ ሚዲያ እየተገለፀ ይገኛል፡፡ በሁለቱም የኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች ህዝባዊ ተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ የወጣው ህዝብ አንዱ ለሌላው በተለያዩ ጊዜና ቦታ ያሳዩት የርስ በርስ አጋርነት፤ መንግሥትን ከፍተኛ ድንጋጤ ላይ እንደጣለው ባለስልጣናቱ በስራቸው ባሉ መገናኛ ብዙኃን ሲናገሩ የተደመጡ ሲሆን፤ በዚህም ስጋት እንዳደረባቸው ባለስልጣናቱና ደጋፊዎቻቸው በይፋ የሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎችና ከሚሰነዝሯቸው አስተያየቶች መረዳት ተችሏል፡፡
በኦሮሚያ ክልል ህዝባዊ ተቃውሞ ፤የአዲስ አበባ እና የኦሮሚያ ክልል ፊንፊኔ ዙሪያ ልዩ ዞን ”የጋራ ልማት የተቀናጀ ማስተር ፕላን” በአዲስ አበባ ዙሪያ ያሉ ገበሬዎች የሚያፈናቅልና ለጎዳና ህይወት የሚዳርግ ነው በሚል ቀደም ሲል የነበረውን ተቃው ከዓመት በኋላ በማገርሸት በምዕራብ ሸዋ ጊንጪ ከተማ መጀመሩ ይታወቃል፡፡ በአማራ ክልል ደግሞ የወልቃይት ጠገዴ የአማራ ማንነት መብት ጥያቄ ህዝባዊ ወኪሌ ኮሚቴ አባላት ላይ መንግሥት በሌሊት በመኖሪያቸው አካባቢ የፀጥታ ኃይሎችን በመላክ የኃይል ርምጃ መውሰዱን ተከትሎ በጎንደር ከተማ መጀመሩ ይታወሳል፡፡
መንግሥት በወሰደው የኃይል ርምጃ ስለደረሱ አጠቃላይ ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳቶች በተመለከተ በመንግሥት ጉዳዩን ለመሸፋፈን ከመሞከር በዘለለ ትክክለኛውን ቁጥርና የጉዳት መጠለን ለመናገር አልደፈረም፡፡ ቀደም ሲል ሀገር በቀል በሆነው የሰብዓዊ መብት ጉባዔ (ሰመጉ) እና ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች በሆነው ሂውማን ራይትስ ዎች (HRW) አማካኝነት በተወሰኑ ወረዳዎችና አካባቢዎች የተደረጉ ምርመራዎች ይፋ ከመደረጋቸው በስተቀር አጠቃላይ በደረሱ የሰብዓዊ እና ቁሳዊ ጉዳቶች የተደረገ ምርመራም ሆነ ሪፖርት የለም፡፡ ይህን በተመለከተ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ምት ኮሚሽን ጉዳዩ በገለልተኛ አካል ምርመራ እንዲደረግ በይፋ ጥያቄ ቢያቀርብም በስልጣን ላይ ያለው መንግሥት በበኩሉ የመንግሥታቱን ድርጅት ጥያቄ ውድቅ በማድረግ ምላሽ መስጠቱ ይታወሳል፡፡
በጎንደር የሰላማዊ ሰው ግድያ የቀጠለ ሲሆን፤ በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ህዝባዊ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ ተጠርቷል
(አዲስ ሚዲያ) ዛሬ ነሐሴ 14 ቀን 2008 ዓ.ም. በአማራ ክልል ጎንደር ከተማ መንግሥት ሰላማዊ ዜጎችን ተኩሶ 1 ወጣት መግደሉን ተከትሎ ዳግም ህዝባዊ ተቃውሞ ተቀስቅሷል፡፡ በሌላ የከተማዋ አካባቢም በተመሳሳይ መልኩ በመንግሥት በተወሰደ ወታደራዊ የኃይል ርምጃ የቆሰሉ እንዳሉም ተጠቁሟል፡፡ እንደ መብት አራማጆች ከሆነ፤ ነጭ ለብሰው በመንቀሳቀሳቸው ብቻ ዛሬ በጎንደር የተገደሉ ዜጎች ቁጥር 4 ደርሷል፡፡ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ድረስ ከተገደለው አንድ ሰላማዊ ዜጋ በስተቀር ሌሎች ጉዳቶችን ማረጋገጥ አልተቻለም፡፡
የዓይን እማኞች እንደተናገሩት፤ዛሬ ግድያው የተፈፀመው የጎንደር ህዝብ በመንግሥት ቀጥተኛ ትዕዛዝ በግፍ የተገደሉባቸውን ሰላማዊ ሰዎችን ለመዘከር ነጭ የመልበስ መርሃ ግብርን ተከትሎ ነጭ ለብሶ ሲንቀሳቀስ የነበረ ወጣት በድብደባ ሲገደል፣ ሌሎች 3 ሰላማዊ ዜጎች ደግሞ ከወታደሮች በተተኮሰ ጥይት ተገድለዋል፡፡ ይህንንም ተከትሎ ጋብ ብሎ የነበረው የጎንደር ህዝባዊ ተቃውሞ ዳግም ተቀስቅሷል፡፡
ህዝቡም ዛሬ በግፍ የተገደለ ወጣት አስከሬን በአደባባይ ይዞ በመዞር ተቃውሞውን እያሰማ ይገኛል፡፡ ጎንደር ባለፈው ሳምንት እሁድ ጀምሮ ለ3 ቀናት ከቤት ያለመውጣት ተቃውሞ ማድረጉ አይዘነጋም፡፡

በከተማው ከሐምሌ 5 ቀን 2008 ዓ.ም. የወልቃይት የአማራ ማንነት መብት ጥያቄን ተከትሎ መንግሥት አስተባባሪ የኮሚቴ አባለት ላይ የወሰደውን የኃይል ርምጃ ተከትሎ በነበሩት የፀረ አገዛዝ የህዝባዊ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፎች በመቀጠላቸው ስጋት የገባው መንግሥት፤ በርካታ የታጠቁ መከላከያ፣ ፌደራል ፖሊስ እና የፌደራል ልዩ የፀጥታ ኃይሎችን በከተማው ማስፈሩ ይታወቃል፡፡
በተያያዘ ዜና፤ በኦሮሚያ እስካሁንም ድረስ የቀጠለውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ ትናንት ነሐሴ 13 ቀን 2008 ዓ.ም. በምዕራብ ወለጋ ደንቢዶሎ አንድ ሰላማዊ ወጣት በመንግሽት አልሞ ተኳሾች መገደሉ የታወቀ ሲሆን፤ በምስራቅ ሷ ዝዋይ ከተማ እቤቱ የነበረ አንድስ ሰላማዊ ዘጋም በመንግሥት የፀጥታ ኃይል ወታደራዊ ርምጃ መገደሉ ታውቋል፡፡
ለነገ ጠዋት በአዲስ አበባ መዳረሻውን መስቀል አደባባይ ያደረገና ሁሉም ኢትዮጵያዊ የተጋበዘበት ህዝባዊ ታላቅ የተቃውሞ ሰልፍ ተጠርቷል፡፡የተቃውሞ ሰልፉ ዋነኛ ዓላማ፤ መንግሥት በሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚወስደውን ግድያ ህዝቡ በተለይም በኦሮሚያና በአማራ ክልል ተቃውሞው የቀጠለ ሲሆን፤ መንግሥት በኦሮሚያ እና አማራ ክልል ሰላማዊ ዜጎች ላይ እየፈፀመ ያለውን ግድያና የፀረ አገዛዝ ተቃውሞ፤ ነገ እሁድ ጠዋት ነሐሴ 15 ቀን 2008 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ታላቅ የተባለለት የተቃውሞ ሰልፍ መዘጋጀቱን የተቃውሞ አስተባባሪዎችና የመብት አራማጆች አስታውቀዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን በሀገር ቤት እየጠፈፀመ ያለውን የመንግሥት ግድያ፣ እስራትና አገዛዝ ድርጊትን በመቃወም በተለያዩ የአሜሪካ፣ አውሮፓ እና አፍሪካ ሀገሮችና ከተሞች ህዝባዊ ተቃውሞ እያደረጉ እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል፡፡
መንግሥት ሰላማዊ ዜጎችን በአደባባይ መግደሉ እንዳሳሰበው በመጠቆም ምርመራ ማድረግ እንደሚፈልግ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ቢያስታውቅም አገዛዙ የመንግሥታቱ ድርጅትን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ምርመራን እንደማይቀበልና ከላከው ምላሽ ማረጋገጥ ተችሏል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ ጉዳዩ ያሳሰባቸው የአሜሪካና የተለያዩ የአውሮፓ ሀገራት መንግሥት እየፈፀመ ያለውን ግድያ በማውገዝ ጉዳዩን በጥብቅ እየተከታተሉት እንደሆነ ማስታወቃቸው ይታወሳል፡፡
ከህዳር 22 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ የህወሓት/ኢህአዴግ መንግሥት በወሰደውና እየወሰደ ባለው ወታደራዊ የኃይል ርምጃ በኦሮሚያ ክልል በነበሩት ህዝባዊ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፎች ላይ ከ500 በላይ ሰላማዊ ዜጎች ሲገደሉ፤ ሁለተኛ ወሩን ባስቆጠረው የአማራ ክልል ህዝባዊ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ ደግሞ ከ100 በላይ ሰላማዊ ዜጎች መገደላቸው ታውቋል፡፡
የወልቃይት የአማራ ማንነት መብት ጥያቄ ተቃውሞ አድማሱን እያሰፋ ቀጥሏል
ትናንት ቅዳሜ ነሐሴ 7 ቀን 2008 ዓ.ም. በምስራቅ ጎጃም ደብረማርቆስ ከተማ እና ዛሬ እሁድ ነሐሴ 8 ቀን 2008 ዓ.ም. በሰሜን ወሎ መቄት ከተማ ህዝባዊ የፀረ አገዛዝ ተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፎች ተካሂደዋል፡፡ ህዝቡም በነበረው የተቃውሞ ህዝባዊ ሰላማዊ ሰልፍ ላይ ወልቃይት ጠገዴ የአማራ ነው፣ የወልቃይት የአማራ ማንነት መብት ጥያቄ መንግሥት ምላሽ እንዲሰጥ፣ ወልቃይት ጠገዴ ወደነበረበት አማር መመለስ አለበት፣ የህወሓት የበላይነት ይቁም፣ የታሰሩ የፖለቲካና የህሊና እስረኞች ይፈቱ፣ መብትን መጠየቅ አሸባሪነት አይደለም፣በኦሮሚያ የሚፈሰው ደም የእኛም ደም ነው፣ ፍትህ ለወገኖቻችን፣ ጭቆና በቃን፣…..የሚሉ መፈክሮች በስፋት ተደምጠዋል፡፡

የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፉ እንዳይደረግ መንግሥት ቀደም ሲል በደህንነቱ እና የፀጥታ ኃይሉ አማካኝነት ከፍተኛ ጥበቃና ማስፈራሪያ ቢያደርግም፤ በተለይ የደብረ ማርቆስ እና አካባቢው ነዋሪ መነሻውን ከከከተማዋ የተለያየ አካባቢ በማድረግ መዳረሻው ወደ ንጉስ ተክለኃይማኖት አደባባይ ሲያደርግ ተስተውሏል፡፡ ይሁን እንጂ መንግሥት የተቃውሞ ሰልፉ መዳረሻ ጋ ከመድረሱ በፊት በህዝቡ ላይ በወሰደው ወታደረዊ ርምጃ 4 ሰዎችን በፅኑ መቁሰላቸው ታውቋል፡፡ መንግሥት ሰልፉን ለመበተን በወሰደው የኃይል ርምጃ የተበሳጩ ሰዎች በሁለት የፀጥታ ኃይሉ ላይ የአፀፋ ርምጃ መውሰዳቸውን መረጃዎች አመልክተዋል፡፡
እሁድ ነሐሴ 8 ቀን በወሎ እና ሰሜን ሸዋ ከተሞች አጠቃላይ የአማራ ተጋድሎ ተቃውሞ ጥሪ መተላለፉን ተከትሎ በሰሜን ወሎ መቄት ከተማ ተመሳሳይ ህዝባዊ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ ተደርጓል፡፡ በሌሎች ከተሞችም በተለይ በደሴ፣ ወልዲያ፣ ከሚሴ፣ ኮምቦልቻ፣ ላሊበላ፣ ደብረ ብርሃን፣ ሸዋ ሮቢትን ጨምሮ በሌሎችም የወሎና ሴመን ሸዋ ከተሞች ተመሳሳይ የተቃውሞ ሰልፍ ጥሪ የነበረ ቢሆንም ፤መንግሥት በወሰደው ጥብቅ ወታደራዊ ቁጥጥርና አፈና ምክንያት ህዝቡ መውጣት እንዳልቻለ ተጠቁሟል፡፡ ህዝባዊ ተቃውሞውችን ከተክትሎም በአማራ ክልል ባሉ የተለያዩ ከተሞች በርካታ ወጣቶች ከቤታቸውና ከስራ ገበታቸው ላይ እየታፈኑ በመታሰር ላይ መሆናቸውን የአዲስ ሚዲያ ምንጮች አረጋግጠዋል፡፡
የተቃውሞ አድማሱን እያሰፋ የመጣው የአማራ ተጋድሎ ህዝባዊ ተቃውሞ ባለፈው ሐምሌ 5 ቀን 2008 ዓ.ም. መነሻውን በሰሜን ጎንደር ያደረገው የወልቃይት የአማራ ማንነት መብት ጥያቄ፣ ወደ ደቡብ ጎንደር ደብረ ታቦር እና ጋይንት ከዚያም ወደ ምዕራብ ጎጃምና የአማራ ክልል መዲና ወደሆነችው ባህርዳር ከተማ መደረጉ አይዘነጋም፡፡ ዘጠነኛ ወሩን ያስቆጠረው የኦሮሚያም ህዝባዊ የፀረ አገዛዝ ተቃውሞ በተለያዩ የክልሉ ከተሞች እንደቀጠለ ሲሆን፤ በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች እየጠወሰደ ባለው ወታደራዊ የኃይል ርምጃ የሚገደሉ፣ የሚቆስሉ እና የሚታሰሩ ዜጎች ቁጥርም እየጨመረ መሄዱ ታውቋል፡፡
እነ በቀለ ገርባ የእምነት ክህደት ቃላቸውን ለመስጠት ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ገለፁ
”ፍርድ ቤቱ ገለልተኛ ነው ብዬ ስለማላምን ቃሌን አልሰጥም” አቶ በቀለ ገርባ

በፌደራል አቃቤ ህግ የሽብር ክስ የቀረበባቸው የኦፌኮ አመራሮችና አባላት በቀረበባቸው ክስ ላይ የእምነት ክህደት ቃላቸውን ለመስጠት ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ጉዳያቸውን ለሚያየው ችሎት ገልጸዋል፡፡
የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት ነሐሴ 5 ቀን 2008 ዓ.ም መዝገቡን የቀጠረው የተከሳሾችን የእምነት ክህደት ቃል ለመቀበል ሲሆን፣ ችሎቱ ተከሳሾችን አንድ በአንድ በስማቸው እየጠራ የቀረበባቸውን የወንጀል ድርጊት ስለመፈጸም አለመፈጸማቸው የእምነት ክህደት ቃላቸውን እንዲሰጡት ጠይቋል፡፡
1ኛ ተከሳሽ አቶ ጉርሜሳ አያኖ የቀረበባቸውን ክስ የወንጀል ድርጊት ፈጽመዋል ወይስ አልፈጸሙም ተብለው ሲጠየቁ፣ ‹‹ይሄ ክስ ለእኔ ግልጽ አይደለም፡፡ በመቃወሚያ ላይ ይህን ገልጫለሁ፡፡ እኔ በሰላማዊና በህጋዊ መንገድ የሚታገል ፓርቲ አባል ሆኜ ስታገል የኦነግ አባል ሆነሃል ተብዬ መከሰስ የለብኝም፡፡ ይህ የምታገልለትን ህዝብ እንደመወንጀል ይቆጠራል፡፡ የኦሮሞ ህዝብ አሸባሪ ከተባለ እኔም አሸባሪ ነኝ፡፡ ይህ በደል ነው፡፡ ስለዚህ እኔ እዚህ ቆሜ ቃሌን መስጠት አያስፈልገኝም›› በማለት ተናግረዋል፡፡
2ኛ ተከሳሽ አቶ ደጀኔ ጣፋ በበኩላቸው ‹‹እኔ የምታገልለት ህዝብ በመንግስት ጦር እያለቀ ባለበት ሰዓት እኔ እዚህ ቆሜ ቃሌን መስጠት አልፈልግም፡፡ ይህ ፍርድ ቤትም ህገ-መንግስቱን የጣሰ ውሳኔ ስላሳለፈብኝ ለዚህ ፍርድ ቤት ቃሌን መስጠት ታሪካዊ ስህተት ነው የሚሆነው፡፡ ድጋሜ እዚህ ፍርድ ቤት መቅረብም አልፈልግም›› የሚል መልስ ሰጥተዋል፡፡
3ኛ ተከሳሽ አቶ አዲሱ ቡላላም በተመሳሳይ ቃላቸውን ለመስጠት እንደማይፈልጉ ተናግረዋል፡፡ ‹‹የደረሰን በክስ መልክ የቀረበ ድረሰት ግልጽ አይደለም፡፡ በባህላችን ውሻ እንኳ ዝም ተብሎ አይነካም፡፡ ከተነካም ባለቤቱን መናቅ ነው የሚሆነው፡፡ እኔ ለኦሮሞ ህዝብ በሰላማዊና በህጋዊ መንገድ እታገላለሁ፡፡ የተሰጠኝ ድርሰት ግን የኦነግ አባል ሆነሃል የሚል ነው፡፡ እኔ የኦፌኮ አባል እንጂ የኦነግ አባል አይደለሁም፡፡ ስለዚህ በፍርድ ቤቱ ወንጀሉን ፈጽመሃል አልፈጸምህም ተብዬ ስጠየቅ ያሳፍረኛል፡፡ ከዚህ በኋላ አስገዳጅ ሁኔታ ካልተፈጠረ በቀር እዚህ ችሎት መቅረብ አልፈልግም፡፡ ውሳኔያችሁን ልትልኩልኝ ትችላላችሁ›› በማለት ለችሎቱ ተናግረዋል፡፡
የችሎቱ ሰብሳቢ ዳኛ አቶ ታደለ ተገኝ ተከሳሾቹ በአጭሩ ድርጊቱን ስለመፈጸም አለመፈጸማቸው ብቻ መልስ እንዲሰጡ፣ ሌላ ረጂም ንግግር ማድረግ ተገቢ እንዳልሆነ በተደጋጋሚ ማሳሰቢያ ሲሰጡ ተደምጠዋል፡፡
ከማሳሰቢያው በኋላ፣ 4ኛ ተከሳሽ የሆኑት የኦፌኮ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ በቀለ ገርባ ደግሞ፣ ‹‹በክስ መቃወሚያችን ወንጀሉ ተፈጸመ በተባለበት ቦታ እንዳኝ ብለን ጠይቀን ይህ ችሎት ውድቅ አድርጎታል፡፡ ጥያቄያችን ህገ-መንግስታዊ ነበር፡፡ ግን አልተቀበላችሁትም፡፡ ስለዚህ ይህ ፍርድ ቤቱ ገለልተኛ ነው ብዬ ስለማላስብ ቃሌን ለመስጠት አልፈልግም፡፡ ካሁን በፊትም የሀሰት ማስረጃ ቀርቦብኝ ስምንት አመት ፈርዶብኛል፡፡ የዚህንም ውሳኔ ባለሁበት ልትልኩልኝ ትችላላችሁ›› ብለዋል፡፡
ከ5ኛ ተከሳሽ ጀምሮ እንዲሁ በተመሳሳይ ቃላቸውን እንዲሰጡ እየተጠየቁ በአብዛኛው ተመሳሳይ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ከተከሳሾች መካከል 10ኛ እና 12ኛ ተከሳሾች ብቻ ‹‹ድርጊቱን አልፈጸምንም›› የሚል ቀጥተኛ የክህደት ቃላቸውን ሲሰጡ 13ኛ ተከሳሽ በበኩሉ የዝምታ ምላሽን ሰጥቷል፡፡ 7ኛ ተከሳሽ ‹‹ክሱ ንቀትና ጥላቻ የታጨቀበት ስለሆነ መልስ አልሰጥም›› ሲል ቀሪዎቹ ክሱ ግልጽ አይደለም፣ ፍርድ ቤቱም ገለልተኛ ነው ብለን አናምንም በሚል የእምነት ክህደት ቃላቸውን ለመስጠት ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ለችሎቱ ገልጸዋል፡፡
በሌላ በኩል የቂሊንጦ እስር ቤት አስተዳደር 11ኛ እና 19ኛ ተከሳሾችን ‹‹በስራ ጫና ምክንያት ቆጥረን አረጋግጠን ማቅረብ አልቻልንም›› የሚል መልስ በሰጠበት ምክንያት ሳያቀርባቸው ቀርቷል፡፡ ይህን በተመለከተ ጠበቃቸው በሰጡት አስተያየት ደበኞቻቸው ላይ የደህንት ስጋት ተጋርጦባቸው ሊሆን እንደሚችል ስጋታቸውን ገልጸው ፍርድ ቤቱ ይህንኑ ስጋታቸውን እንዲመዘግብላቸው አሳስበዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ በበኩሉ አስተዳደሩ በነገው ዕለት እንዲያቀርባቸው በማዘዝ የእምነት ክህደት ቃላቸውን ለመቀበል ቀጠሮ ይዟል፡፡
ፍርድ ቤቱ ዛሬ የቀረቡት ተከሳሾች ቃላቸውን ለመስጠት ፍቃደኛ አለመሆናቸውን ከመዘገበ በኋላ ‹‹ወንጀሉን አልፈጸምንም›› እንዳሉ ተቆጥሮ ክደው እንደተከራከሩ በመመዝገብ ያለ አቃቤ ህግ አሳሳቢነት የአቃቤ ህግ ምስክሮችን ለመስማት በሚል ከህዳር 02-16 ቀን 2009 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ ፍርድ ቤቱ የአቃቤ ህግ የሰው ምስክሮች በርካታ በመሆናቸው ተከታታይ የቀጠሮ ቀናትን መስጠቱን ገልጹዋል፡፡
በዛሬው የችሎት ውሎ ተከሳሾቹ ዳኞች ወደ ችሎት ሲገቡም ሆነ ችሎቱ ጉዳያቸውን ሲያይ በችሎቱ ላይ ያላቸውን ተቃውሞ ለመግለጽ ከመቀመጫቸው ሳይነሱ ቀርተዋል፡፡
ምንጭ፡-EHRP