Category Archives: News

በዛሬው ኢሬቻ ክብረ በዓል ላይ ከታደሙት መካከል ከ250 በላይ ሰላማዊ ዜጎች ተገደሉ

ዛሬ እሁድ መስከረም 22 ቀን 2009 ዓ.ም. ከአዲስ አበባ ደቡብ ምስራቅ 40 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ደብረዘይት/ቢሾፍቱ ከተማ በሚገኘው ሆራ ሐይቅ አካባቢ በኦሮሞ ማኀበረሰብ እና በሌሎች ኢትዮጵያውያን እንደቀደሙ ዓመታት ሁሉ ጊዜውን ጠብቆ ዛሬ እየተከበረ ባለው የኢሬቻ ክብረ በዓል ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ድረስ በግማሽ ቀን ብቻ ከ250 በላይ የበዓሉ ታዳሚ ሰላማዊ ዜጎች በገዥው ስርዓት በተወሰደ ወታደራዊ የኃይል ርምጃ መገደላቸው ተጠቆመ፡፡

በስፍራው ተገኝተው የነበሩ የዓይን እማኞች እና የሆስፒታል ምንጮች ከሆነ ከአንድ ሺህ ያላነሱ ንፁሃን ዜጎችም ቆስለው በደብረዘይት እና አዲስ አበባ በሚገኙ ሆስፒታሎች ለህክምና እርዳታ መላካቸው ታውቋል፡፡
ዛሬ ሰላማዊ ዜጎች ላይ በአንድ ቀን ብቻ በመንግሥት የተፈፀመው ግድያ ከህዳር ወር 2008 ዓ.ም. ጀምሮ በተለይ በኦሮሚያ ከ650 በላይ፣ በአማራ ከሐምሌ 2008 ዓ.ም. ጀምሮ ከ200 በላይ ከተገደሉ ንፁሃን በተጨማሪ የተፈፀመ ዘግናኝ ግድያ ነው፡፡ በተለይ በበዓሉ ስፍራ የነበሩ የዓይን እማኞች ከሆነ የተገደሉ ዜጎች ቁጥር ከተጠቀሰው በላይ ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል፡፡ በዘንደሮው በዓል ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢ የመጡ የበዓሉ ታዳሚዎች ቁጥር እስከ 2 ሚሊዮን እንደሚደርስ ተገምቷል፡፡

መንግሥት በሚቆጣጠራቸው መገናኛ ብዙኃን እና በቃል አቀባይ ጽህፈት ቤቱ በኩል በሰጠው መግለጫ ሟቾቹ በተፈጠረ ግርግር እንደሆነ ቢያሳውቅም፤ የዓይን እማኞች በበኩላቸው በበዓሉ ላይ ወጣቶች እጃቸውን በማጣመር ከዚህ ላለፉት 10 ወራት መንግሥት በዜጎች ላይ የፈፀመውን ግድያ እና እስር የሚያወግዝ ተቃውሞ እያቀረቡ ባሉበት ሰዓት በገዥው ስርዓት ወታደሮች አስለቃሽ ጢስን እና ተከታታይ ተኩስ በህዝቡ ላይ እንደተከፈተ ተናግረዋል፡፡ በጥይት ከተገደሉት በተጨማሪ ከተኩሱ ለማምለጥ የሞከሩ ሰዎችም በጥልቅ ጉድጓድ ውስጥ ገብተው የሞቱ፣ የተገዱና የተረፉም እንዳሉ ለማወቅ ተችሏል፡፡

መንግሥት ለንፁሃን መሞት ምክንያቱ አመፅ ቀስቃሾ በፈጠሩት ግርግር በመረጋገጣቸውና ገደል ውስጥ በመግባታቸው ነው ቢልም፤ የበዓሉ ታዳሚዎች በበኩላቸው የበዓሉን ድባብ በማጥፋ ወታደሮች የበዓሉ ታዳሚ ሰላማዊ ዜጎች ላይ ተኩስ በመክፈት ግድያው ሆን ተብሎ የተፈፀሙውና ንፁሃን እንዲሞቱ የተደረገው በገዥው ስርዓት እንደሆነ ከጉዳቱ የተረፉ እማኞች ተናግረዋል፡፡

irrecha-massacre-2016

የኦሮሞ ማኀበረሰብ መብት አራማጆችን ጨምሮ ሌሎች ኢዮጵያውያን የመብት አራማጆች የተገደሉ በርካታ ዜጎችን ምስልና ቪዲዮ በማኀበራዊ ሚዲያ ሲያሰራጩ ተስተውሏል፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ በህዝብ ክብረ በዓል ላይ የዛሬውን ያህል ዜጎች በመንግሥት ወታደራዊ ኃይሎች ሰላማዊ ዜጎች ላይ በወሰዱት ርምጃ ሲገደሉ የመጀመሪያው ነውም ተብሏል፡፡

የኢሬቻ በዓል በኦሮሞ ማኀበረሰብ ዘንድ ጥንታዊ የሆነ ፈጣሪን በጋራ የማመስገን በዓል ሲሆን፤ ከኦሮሞ ማኀበረሰብ በተጨማሪ ከተለያዩ አካባቢዎች ሌሎች ኢትዮጵያውያን በብዛት የሚታደሙበትና የሚያከብሩት ታላቅ ህዝባዊ በዓል መሆኑ ይታወቃል፡፡

በተያያዘ ዜና፤ የኤሬቻ በዓል ጅምላ ግድያን ተከትሎ በአምቦ እና አወዳይ ከተማ ህዝባዊ ተቃውሞ የተቀሰቀሰ ሲሆን፤ በሁለቱም ከተሞች መንግሥት ወታደሮች የኃይል ርምጃ መውሰድ መጀመራቸው ተገለፀ፡፡ በተወሰደው ርምጃ ምን ያህል ዜጎች ጉዳት እንደደረሰባቸው ለጊዜው ማወቅ አልተቻለም፡፡

የአምቦ ዩኒቨርስቲ መምህር እና ብሎገር ስዩም ተሾመ ታሰረ

ስዩም ተሾመ

seyoum-teshome

በአምቦ ዩኒቨርስቲ ቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ወሊሶ ግቢ መምህር እና ብሎገር ስዩም ተሾመ ታሰረ፡፡ መምህር እና ብሎገር ስዩም ተሾመ ከሚኖርበትና ከሚሰራበት ወሊሶ ከተማ ዛሬ ቅዳሜ መስከረም 21 ቀን 2009 ዓ.ም. በፀጥታ ኃይሎች ታፍኖ ከተወሰደ በኋላ መታሰሩ ተጠቁሟል፡፡ ስዩም ተሾመ በአምቦ ዩኒቨርስቲ ወሊሶ ግቢ የማናጅመንት ትምህርት ክፍል ኃላፊ እና መምህር ሲሆን፤ ከማኀበራዊ ሚዲያ በተጨማሪ በ ”ኢትዮቲንክታንክ” እና የገዥው ስርዓት ደጋፊ እንደሆነ በሚታወቀው ”ሆርንአፌይርስ” ድረ-ገፅ ጭምር በመፃፍ ይታወቃል፡፡

በተለይ ከህዳር 2008 ዓ.ም. ጀምሮ በመንግሥት እና በህዝቡ መካከል በተፈጠረው አለመግባባት ችግሮች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ እና ሌሎች ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የተለያዩ መፍትሄ ሊሆኑ ይችላሉ ያላቸውን ምክረ ሐሳቦችን በመሰንዘርም ይታወቃል፡፡

10ኛ ወሩን ባስቆጠረው የኦሮሚያ ህዝባዊ ተቃውሞን ተከትሎ በአማራ እና በደቡብ ኮንሶ ተከታታይ ህዝባዊ ተቃውሞች መቀጠላቸውን ተከትሎ ከ820 ያላነሱ ሰላማዊ ዜጎች በፀጥታ ኃይሉ ወታደራዊ ርምጃ ሲገደሉ፤ በሺህዎች የሚቆጠሩ ቆስለው፣ በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ታፍነው ታስረዋል፡፡ ከተገደሉ፣ ከቆሰሉና ከታሰሩት መካከል ህፃናት እና አዛውንት፣ መምህራን፣ ጋዜጠኞችና ብሎገሮች፣ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች እና ተማሪዎች ይገኙበታል፡፡ በተለይ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ድረስ፤ በተለያዩ ኦሮሚያ እና አማራ ክልል ከተሞችና ወረዳዎች የመንግሥት ግድያና እስር እንደቀጠለ ነው፡፡

ኦሕዴድ ሊቀመናብርቱን አነሳ

ዮሐንስ አንበርብር

workineh-gebeyehu-and-muktar-kedir

– የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ እየተካሄደ ነው

የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦሕዴድ) ሰሞኑን ባካሄደው የማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባው፣ የድርጀቱን ሊቀመንበር አቶ ሙክታር ከድርንና ምክትል ሊቀመንበሯን ወ/ሮ አስቴር ማሞን ከኃላፊነት ማንሳቱን አስታወቀ፡፡

ማዕከላዊ ኮሚቴው ማክሰኞ መስከረም 10 ቀን 2009 ዓ.ም. ምሽት ላይ በፌስቡክ ገጹ እንዳሳወቀው፣ ሁለቱ አመራሮች ያቀረቡትን ጥያቄ በመቀበል ከድርጅቱ ኃላፊነት እንዲነሱ በሙሉ ድምፅ ወስኗል፡፡ በምትካቸውም የጨፌ ኦሮሚያ አፈ ጉባዔ የሆኑን አቶ ለማ መገርሳን የኦሕዴድ ሊቀመንበር አድርጎ ሲመርጥ፣ በፌዴራል መንግሥት የትራንስፖርት ሚኒስትር የሆኑት ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁን ደግሞ የኦሕዴድ ምክትል ሊቀመንበር አድርጎ መርጧል፡፡

ማዕከላዊ ኮሚቴው ባወጣው መግለጫ ሁለቱ የድርጅቱ ሊቀመናብርት ከኃላፊነት የተነሱት ባቀረቡት ጥያቄ መሆኑን ቢገልጽም፣ የሪፖርተር ምንጮች ግን ሁለቱ ሊቀመናብርት በማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባው በኦሮሚያ ተስፋፍተው ዓመቱን ሙሉ ለዘለቁ ግጭቶችና የኅብረተሰቡ ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት ያልቻሉ ናቸው በማለት ሲወቅሳቸው እንደነበርና ሁለቱም አመራሮች ራሳቸውን መከላከል አለመቻላቸውን ገልጸዋል፡፡

አቶ ለማ መገርሳ ወጣት ከሚባሉት የኦሕዴድ አመራሮች ውስጥ አንዱ ሲሆኑ፣ ኦሕዴድን የተቀላቀሉት በ1983 ዓ.ም. እንደሆነና የትውልድ ቦታቸውም ወለጋ መሆኑን ምንጮች አክለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅትም የጨፌ ኦሮሚያ አፈ ጉባዔና በፌዴሬሽን ምክር ቤት የሕገ መንግሥት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እንደሆኑም ይታወቃል፡፡

የኦሕዴድ ምክትል ሊቀመንበር ሆነው በወ/ሮ አስቴር ማሞ ምትክ የተሾሙት ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ የፌዴራል ትራንስፖርት ሚኒስትር ሲሆኑ የትውልድ ቦታቸው ሻሸመኔ ነው፡፡

አቶ ሙክታርና ወ/ሮ አስቴር ከድርጅቱ ኃላፊነት ቢነሱም፣ አቶ ሙክታር የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ሆነው ጨፌ ኦሮሚያ በጥቅምት ወር መጀመርያ ላይ እስከሚሰበሰብ ይቀጥላሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በኦሕዴድ የቆየ የአሠራር ልማድ መሠረት የድርጀቱ ሊቀመንበር የክልሉ ፕሬዚዳንትነት ሥልጣን ያገኛል፡፡ በዚህ አሠራር የሚቀጥል ከሆነ ጨፌው በጥቅምት ወር መጀመርያ ላይ ሲሰበሰብ አቶ ለማ መገርሳን የክልሉ ፕሬዚዳንት አድርጎ ይመርጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ወ/ሮ አስቴር ማሞ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የመልካም አስተዳደር ማሻሻያ ክላስተር አስተባባሪና የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ሚኒስትርነታቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም በጥቅምት ወር መጀመርያ ሳምንት ላይ አዲስ ካቢኔ እስኪያዋቅሩ ድረስ ይቀጥላሉ፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ እየተካሄደ መሆኑን የድርጅቱ መግለጫ ያመለክታል፡፡ በዚህ ስብሰባም ሹም ሽሮች እንደሚኖሩ እየተነገረ ነው፡፡ የደኢሕዴን ምክትል ሊቀመንበርና የትምህርት ሚኒትሩ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ በበኩላቸው ከፌዴራል ተቋማት የተወጣጡ የኢሕአዴግ መካከለኛ አመራሮችን በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በማወያያት ላይ ናቸው፡፡
ምንጭ፡-ሪፖርተር ጋዜጣ

በደብረ ታቦር ማረሚያ ቤት ቃጠሎ በእስረኞች ላይ ጉዳት ደረሰ

በባህር ዳር በአበባ እርሻዎችና በሌሎች ንብረቶች ውድመት ደርሷል

– የአፍሪካ ኅብረት በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ አሳስቦኛል አለ

በአማራ ክልል በደቡብ ጎንደር ዞን ዋና ከተማ ደብረ ታቦር ማረሚያ ቤት በደረሰ ቃጠሎ በእስረኞች ላይ ጉዳት ደረሰ፡፡ የመከላከያ ሠራዊት እስረኞች እንዳያመልጡ ዙሪያውን ከቦ እንደነበርና ሊያመልጡ የነበሩ በርካታ እስረኞች መሞታቸውን ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
የእሳት አደጋው የተከሰተው ሐሙስ ነሐሴ 26 ቀን 2008 ዓ.ም. ከቀትር በኋላ መሆኑን የገለጹት ምንጮች፣ እስረኞቹ ከአደጋው ለማምለጥ መሞከራቸውን አስረድተዋል፡፡ ይሁን እንጂ አካባቢውን በፍጥነት የከበበው የመከላከያ ሠራዊት እስረኞቹ እንዳያመልጡ ሲተኩስ እንደነበር ተናግረዋል፡፡

debre-tabor-prison-fire

በእሳት አደጋው ሳቢያ ከፍተኛ ጉዳት በማረሚያ ቤቱ ላይ መድረሱንና ሊያመልጡ በነበሩ እስረኞች ላይም ጉዳት እንደደረሰ ምንጮች ገልጸዋል፡፡

የደቡብ ጎንደር ማረሚያ ቤቶች መምርያ ኃላፊ ምክትል ኮማንደር መንጌ ከበደ ቃጠሎው የተነሳው በኤሌክትሪክ መስመሮች መገናኘት መሆኑን ገልጸው፣ ሊያመልጡ የነበሩ ሁለት እስረኞች መገደላቸውንና ከእስረኞች ደግሞ ሁለት መቁሰላቸውን አስረድተዋል፡፡
በአማራ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች እየተስፋፋ የሚገኘው አመፅ፣ ከመንግሥት ጋር ቁርኝት አላቸው በተባሉ የግል ባለሀብቶች ንብረቶችና የሕዝብ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ላይ ያነጣጠረ ጉዳት እያደረሰ መሆኑም ተገልጿል፡፡

ኢስመራልዳ (Esmeralda Farms) የተባለው በባህር ዳር የሚገኘው የኔዘርላንድ ባለሀብቶች የአበባ እርሻ በእሳት ሙሉ በሙሉ ወድሟል፡፡
መቀመጫውን በኔዘርላንድ ያደረገው የአበባ ኩባንያው ዋና ቢሮ ባወጣው መግለጫ፣ በፖለቲካ ተቃውሞው ምክንያት በባህር ዳር የሚገኘው የአበባ እርሻ (ኮንዶር ፋርም) በእሳት ሙሉ በሙሉ መውደሙንና የኩባንያው አጠቃላይ ኢንቨስትመንት አሥር ሚሊዮን ዩሮ እንደሆነም አስታውሷል፡፡

በኢትዮጵያ ከሚገኘው ቢሮ ጋር መገናኘት አለመቻሉን የሚገልጸው መግለጫው፣ ‹‹የኢትዮጵያ ሥራ አስኪያጃችን በቀውሱ ምክንያት ከአካባቢው በመልቀቃቸው መረጃዎችን ማግኘት አልተቻለም፤›› ብሏል፡፡

በመንግሥት ላይ የተነሳው ተቃውሞ በአካባቢው በሚገኙ የአበባ እርሻዎች ላይ ጉዳት ማድረስ መቀጠሉንና አሥር ያህል የአበባ እርሻዎች መቃጠላቸውን መረጃዎች አመልክተዋል፡፡

ኮንዶር ፋርም የተባለው የአበባ እርሻ ሲቃጠል በአካባቢው የመንግሥት ፀጥታ ኃይሎች የነበሩ ቢሆንም፣ ጉዳቱን ያደረሱት ከፀጥታ ኃይሎች ቁጥር በብዛት የሚበልጡ በመሆናቸው ማዳን አለመቻሉን ኩባንያው ገልጿል፡፡
መጋዘኖች፣ የማቀዝቀዣ ክፍሎች፣ ትራክተሮች፣ የጭነት ተሽከርካሪዎች፣ ኮንቴይነሮችና ማሸጊያዎች በሙሉ በእሳት መውደማቸውን አስታውቋል፡፡

‹‹ሁሉም ጠፍቷል፡፡ የአሥር ሚሊዮን ዩሮ ኢንቨስትመንትና የረጅም ዓመታት ጥረት በአንድ ቀን ወድሟል፤›› ሲል በመግለጫው የደረሰውን ጉዳት አመልክቷል፡፡

ሌላው በየመኑ ባለሀብት መሐመድ አልካሚን የተቋቋመውና ከ500 በላይ ሠራተኞች የነበረው የአበባ እርሻ ይገኝበታል፡፡
ለባህር ዳር ከተማ የውኃ አቅርቦት ምንጭ የሆነው እንፍራንዝ ከተማ አካባቢ የሚገኘው የጥቁር ውኃ የውኃ ማጠራቀሚያ ጋንም ቃጠሎ ደርሶበታል፡፡ ይህም በከተማዋና በአካባቢዋ የውኃ አቅርቦት ላይ እጥረት እንደሚያስከትል እየተነገረ ነው፡፡
በተያያዘ ዜና በክልሉ ውስጥ ያለው ተቃውሞ እየተባባሰና በሰው ሕይወትና ንብረት ላይ የሚደርሰው ጉዳት እየጨመረ መምጣቱን መረጃዎች እያሳዩ ነው፡፡

በተለይም ማክሰኞ ነሐሴ 24 ቀን 2008 ዓ.ም. ጠቅላይ ሚኒስትሩ በክልሉ የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ ለማስቆም የፀጥታ ኃይሉ ሕግ እንዲያስከብር ትዕዛዝ ማስተላለፋቸውን ከገለጹ ጀምሮ ሰዎች መሞታቸውን፣ የዘር ጥቃት ተፈጸመባቸው የተባሉ ደግሞ ወደ ጎረቤት አገር እየተሰደዱ መሆናቸው እየተገለጸ ነው፡፡

በተለይ በአምባ ጊዮርጊስ፣ በደብረ ታቦር፣ በመተማ ዮሐንስና በአጎራባች አካባቢዎች የሰው ሕይወት መጥፋቱን የሚገልጹ ቁጥሮችም እየጨመሩ ስለመውጣታቸው መረጃዎች እየጠቆሙ ይገኛል፡፡ ነገር ግን በመንግሥት በኩል እስካሁን ምንም ማረጋገጫም ሆነ ማስተባበያ አልተሰጠም፡፡

ሪፖርተር ከምንጮች ማረጋገጥ እንደቻለው በክልሉ የተለያዩ ከተሞች የመከላከያ ሠራዊት እየገባ ሲሆን፣ የከባድ መሣሪያ ተሽከርካሪዎች መታየታቸውን ለማወቅ ችሏል፡፡

የአማራ ክልል የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ንጉሡ ጥላሁን፣ በክልሉ ምዕራባዊ አካባቢዎች ሁከት መከሰቱን ተናግረዋል፡፡ በአንዳንድ ፀረ ሰላም ኃይሎች የተነዛ መረጃ ሕዝቡን ወዳልተፈለገ አቅጣጫ መምራቱንና በተፈጠረው ሁከትም በሰው ሕይወትና ንብረት ላይ ጉዳት ደርሷል ብለዋል፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ የአፍሪካ ኅብረት በኢትዮጵያ እየተከሰተ ያለው ግጭት እያሳሰበው መምጣቱን ጠቁሞ፣ ሁሉም ወገኖች ከማንኛውም ግጭት እንዲቆጠቡ ጥሪ አቅርቧል፡፡

የኮሚሽኑ ዋና ሊቀመንበር ዶ/ር ንኮሳዛና ድላሚኒ ዙማ ዓርብ ነሐሴ 27 ቀን 2008 ዓ.ም. ባወጡት መግለጫ፣ ‹‹በአገሪቱ የማኅበራዊ ፖለቲካው የሰው ሕይወት ማጥፋት፣ በንብረቶች ላይ ውድመት ማስከተል፣ እንዲሁም የቴሌኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት እስከማቋረጥ ደረጃ መድረሱ አሳሳቢ ነው፤›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡ ሊቀመንበሯ አክለው ሁሉም ወገኖች ወደ ሰላማዊ ሁኔታ በማመዘን ለሕግ መከበር እንዲተጉ፣ ሰላማዊ ሠልፍ የማድረግ መብትና የዴሞክራሲ ባህልና መርሆችን እንዲያከብሩ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡
ምንጭ፡- ሪፖርተር ጋዜጣ

በአዲስ አበባ አቃቂ በሚገኘው ቂሊንጦ ወህኒ ቤት በደረሰ የእሳት አደጋ ከ25 ያላነሱ እስረኞች ህይወት አለፈ

(አዲስ ሚዲያ)ዛሬ ነሐሴ 28 ቀን 2008 ዓ.ም. አዲስ አበባ አቃቂ በሚገኘው ቂሊንጦ ወህኒ ቤት በደረሰ የእሳት ቃጠሎ ከ25 ያላነሱ እስረኞች መሞታቸው ተጠቆመ፡፡ በጥበቃ ላይ የነበሩ ወታደሮችም ከእሳቱ ለማለጥ የሞከሩ እስረኞች ላይ ሲተኩሱ እንደነበር ምንጮች አረጋግጠዋል፡፡

ከቃጠሎው በፊት በነበረው ተኩስ ምን ያህል እስረኞች ላይ ጉዳት እንደደረሰ እስካሁን ማረጋገጥ ባይቻልም፤ በነጋታው ጠዋት በነበረው የእሳት አደጋ ከ25 ያላነሱ ሰዎች መሞታቸውን ከቅዱስ ጳውሎስ፣ ሜክሲኮ በሚገኘው ፖሊስ ፣ ጥሩነሽ ቤጂንግ እና የካቲት 12 ሆስፒታል ምንጮች ለማወቅ ተችሏል፡፡ በቃጠሎው ጉዳት የደረሰባቸውና በህይወት የተረፉትም አብዛኞቹ ፖሊስ ሆስፒታልና የካቲት 12 ሆስፒታል በጥበቃ ስር ሆነው ህክምና እየተደረገላቸው እንደሚገኝ ተጠቁሟል፡፡

Addis Ababa Akaki Kilinto Prison

በወህኒ ቤቱ ታስረው ከሚገኙት መካከል ስመጥር እና ህዝባዊ ተቀባይነት ያላቸው በርካታ የፖለቲካ እስረኞች ያሉበት ሲሆን በተለይም፤ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፣ ፖለቲከኞች፣ የመብት አራማጆች እና ጋዜጠኞች እንደሚገኙበት ይታወቃል፡፡

በያዝነው 2008 ዓ.ም. ብቻ ከአዲስ አበባ አቃቂ ከሚገኘው ቂሊንጦ ወህኒ ቤት በተጨማሪ በርካታ የፖለቲካ እስረኞች የሚገኙባቸው ጎንደር፣ አምቦና ደብረ ታቦር ወህኒ ቤት በተመሳሳይ መልኩ የእሳት አደጋ ሰለባ መሆናቸው አይዘነጋም፡፡ በነበሩ አደጋዎች መንስኤ እና ጉዳትን በተመለከተ የሚመለከተው የመንግሥት አካልም ከመግለፅ መቆጠቡ ይታወቃል፡፡

በተለይ የአቃቂ ቂሊንጦውን እሳት ቃጠሎ ተከትሎ በርካታ የታሳሪ ቤተሰቦች፣ ወዳጆች እና ደጋፊዎች ስጋት እንዳደረባቸው በተለያየ መድረክ ከመግለፅ በተጨማሪ በአዲስ አበባና አጎራባች አካባቢ ያሉ ሰዎች የቤተሰቦቻቸውን ደህንነት ለማጣራት ሙከራ ቢያደርጉም በወህኒ ቤቱ አስተዳደር እንዳልተፈቀደ ተረጋግጧል፡፡ በወህኒ ቤቱ የታሰሩ ቤተሰቦቻቸውን ለመጠየቅ ከተለያዩ የክልል ከተሞች የመጡ ሰዎችም ወደ እስር ቤቱ ግቢም ሆነ ከግቢ ውጭ በቅርብ ርቀት እንዳይጠጉ በመከልከላቸው ወደየመጡበት መመለሳቸውን ምንጮች አረጋግጠዋል፡፡

በአደጋው የደረሰውን ጉዳትና ምክንያት በተመለከተ የወህኒ ቤቱ አስተዳደርም ሆነ መንግሥት እስካሁን የሰጡት መረጃ የለም፡፡ ይሁን እንጂ የተለያዩ ሰዎች አደጋው በመንግሥት ሆን ተብሎ የተቀነባበረና የፖለቲካ እስረኞችን ለመጉዳት የታሰበ የገዥው ስርዓት የተለመደ ስልት እንደሆነ የሚገልፁ ቢኖሩም፤ ስለ አደጋውና አጠቃላይ መረጃ ከገለልተኛ አካልም ሆነ ከመንግሥት ለማወቅ አልተቻለም፡፡