የኢህአዴግ መንግስት በሰሜን ጎንደር የአንድነት ፓርቲ አመራሮችን ማሰሩ ተገለፀ
በዛሬው ዕለት ጥቅምት 25 ቀን 2007 ዓ.ም. ከለሊቱ 11:00 ሰዓት ላይ በሰሜን ጎንደር ዞን በምዕራብ አምርማጭሆ አብርሃ ጅራ ከተማ የአንድነት ሰብሳቢ የሆኑት አቶ አንጋው ተገኝ እና የወረዳው ሌላ አመራር አባላት አቶ አባይ ዘውዱ እና አቶ እንግዳው ዋኘው የፌደራል ፖሊሶች የቤታቸውን በር ገንጥለው በመግባት እየደበደቡ ወደ ፖሊስ ጣቢያ እንደወሰዷቸው ተጠቁሟል፡፡ ይህንንም ተከትሎ የአካባቢው ነዋሪም ወደ ሌላ ቦታ እንዳይወስዷቸው ፖሊስ ጣቢያውን ከቦ እየጠበቀ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።
በተያያዘ ዜና በዛው ሰሜን ጎንደር ዞን በመተማ ከተማ የአንድነት ሰብሳቢ የሆኑት አቶ በላይነህ ሲሳይ በፖሊሶች በዛሬው ዕለት ከለሊቱ 11:00 ሰዓት በፖሊሶች ወዳልታወቀ ቦታ መወሰዳቸውን መረጃዎች አመልክተዋል።
ባለፈው ሳምንት በተመሳሳይ መልኩ በወላይታ ዞን የአንድነት አመራሮችም ከፍተኛ ድብደባና ወከባ እንደደረሰባቸው በፍኖተ ነፃነት የተዘገበ ሲሆን፤ መንግስት በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚገኙ የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ በተለይም የአንድነት አመራሮች ላይ በኢህአዴግ የሚፈጠረው ጫና እንደቀጠለ መሆኑን የፓርቲው ልሳን ዘገባ ያመለክታል፡፡
ከዚህ ቀደምም አቶ አንዱዓለም አራጌ፣ አቶ ናትናኤል መኮንን፣ አቶ የሺዋስ ይሁንዓለሙ፣ ሻምበል ዮሐንስ ተረፈ፣ አቶ አንዱዓለም አያሌው ፤በቅርቡ ደግሞ አቶ ዳንኤል ሺበሺ፣ አቶ ሀብታሙ አያሌው ከአረና እና ሰማያዊ
ፓርቲ አመራር ከሆኑት አቶ አብርሃ ደስታና አቶ የሺዋስ አሰፋ ጋር መታሰራቸው አይዘነጋም፡፡
የዞን 9 ብሎገሮችና ጋዜጠኞች ለሳምንት ተለዋጭ ቀነ ቀጠሮ ተጠየቀባቸው
ዛሬ ጥቅምት 25 ቀን 2007 ዓ.ም በፌደራሉ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 9ኛ ወንጀል ችሎት ለ10ኛ ጊዜ ችሎት የቀረቡት የዞን 9 ብሎገሮችና 3ቱ ጋዜጠኞች ለሳምንት ህዳር 3 ቀን 2007 ዓ.ም ተለዋጭ ቀነ ቀጠሮ ተሰጠ፡፡
ፍርድ ቤቱ ዛሬ በብሎገሮቹና በጋዜጠኞቹ ቀደም ሲል የቀረበውን የክስ ማሻሻያ አቤቱታ መርምሮ ውሳኔ ይሰጣል ተብሎ የተጠበቀ ቢሆንም፣ ምርመራው አላለቀም በሚል ምክንያት ለሳምንት አጭር ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
በዛሬው ችሎት ላይ ከተሰየሙት ዳኞች መካከል ሁለቱ አዲሶች በመሆናቸው ምክንያት ተለዋጭ ቀጠሮ መሰጠቱን ጠበቃ አምሃ መኮንን ገልጸዋል፡፡ ከዳኞቹ በተጨማሪ ችሎት ክፍሉም በመቀየሩ ክፍሉ ጠባብ ነው በሚል፣ የተከሳሽ ቤተሰቦችና ጋዜጠኞች ችሎት መግባት አለመቻላቸውም ታውቋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ በነገው ዕለት ጠቅላይ ፍርድ ቤት በተከሳሾች ዋስትና ጉዳይ ውሳኔ ለመስጠት ቀጠሮ መያዙን አቶ አምሃ ጨምረው አስረድተዋል፡፡
ሌላው በተከሳሾች በኩል ሁለቱ ሴት ተከሳሾች ኤዶም ካሳዬ እና ማህሌት ፋንታሁን በቃሊቲ በሚገኘው ወህኒ ቤት ላይ ያነሱትን የመብት ጥሰት አቤቱታ በተመለከተ የእስር ቤቱ አስተዳደር በቀጣይ ቀጠሮ፤ ድጋሚ ቀርቦ እንዲያስረዳ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ ሁለቱ ተከሳሾች በቀን ለ10 ደቂቃ ብቻ ስማቸው ቀድሞ በተመዘገቡ 6 የቀርብ ቤተሰቦች ብቻ እየተጎበኙ እንደሚገኙ ይታወቃል፡፡
ምንጭ፡- ነገረ-ኢትዮጵያ
በእስር ላይ የሚገኙት 10 ወጣቶች የሽብርተኝነት ክስ ተመሰረተባቸው
- አብርሃ ደስታ ከሁለት ድርጅቶች ጋር ግንኙነት አለው የሚል ክስ ተመስርቶበታል
- ወደ አዲስ አበባ ማረሚያ ቤት እንዲዘዋወሩ ታዟል
የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አራተኛ ወንጀል ችሎት ጥቅምት 21 ቀን 2007 ዓ.ም ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት አካባቢ በተሰየመው ችሎት 10 ተከሳሾች በፌደራል አቃቢ ህግ በይፋ ክስ ተመሰረተባቸው፡፡ ተጠርጣሪዎቹ ከ100 ገጽ በላይ የክስ ቻርጅ የተነበበላቸው ሲሆን ከክስ ቻርጁ ጋር ከ300 ገጽ በላይ የምርመራ ሰነድ ቀርቦባቸዋል፡፡
የክሱ መዝገብ የተከፈተው ዘላለም ወርቃገኘሁ በተባለውና ‹‹የግንቦት 7 አመራር ነው፡፡›› ተብሎ ክስ በተመሰረተበት ግለሰብ ሲሆን በዚህ የክስ መዝገብ የተካተቱትም፡-
1ኛ ተከሳሽ ዘላለም ወርቃገኘሁ
2ኛ ተከሳሽ ሀብታሙ አያሌው
3ኛ ተከሳሽ ዳንኤል ሺበሺ
4ኛ ተከሳሽ አብርሃ ደስታ
5ኛ ተከሳሽ የሽዋስ አሰፋ
6ኛ ተከሳሽ ዮናታን ወልዴ
7ኛ ተከሳሽ አብርሃም ሰለሞን
8ኛ ተከሳሽ ሰለሞን ግርማ
9ኛ ተከሳሽ ብርሃኑ ደጉ
10ኛ ተከሳሽ ተስፋዬ ተፈሪ ናቸው
ለሁሉም ተከሳሾች ከዛሬ በፊት ክስ እንዳልደረሳቸውና ዛሬ ፍርድ ቤት ውስጥ እንደተሰጣቸው ታውቋል፡፡ በችሎቱ 6ኛ ተከሳሽ ከሆነው ዮናታን ወልዴ በስተቀር ሁሉም ያለ ጠበቃ የቀረቡ ሲሆን ጠበቃዎቹ ያልቀረቡበት ምክንያትም ጠበቆቹ ደምበኞቻቸው የሚቀርቡበት ቦታና ጊዜ ስላልተነገራቸው እንዲሁም ቀደም ብለው እንዳይገናኙ በመደረጋቸው መሆኑን አቶ ኃብታሙ አያሌው ችሎቱ ላይ ተናግሯል፡፡
ከሳሹ የፌደራል አቃቢ ህግ በ1996 የወጣው የወንጀል ህግ እና የጸረ ሽብር ህግ ጠቅሶ ክስ ያቀረበ ሲሆን ክሶቹ በሁለት ዋና ዋና ጭብጦች ቀርበዋል፡፡ የመጀመሪያው ጭብጥ ‹‹ከሽብርተኛ ቡድኖች ጋር በጋራ በመስራት›› የሚል ሲሆን ‹‹ህገ መንግስቱንና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን በኃይል ለመናድ፣ የመንግስትን መሰረተ ልማት በማፈራረስ፣ ህዝብን ለአመጸ በማነሳሳት መንግስትን መለወጥ አላማው አድርጎ ከሚሰራውና ራሱን ግንቦት 7 ብሎ ከሚጠራው ቡድን ጋር አባል በመሆንና በወንጀል ድርጊቶች በመሳተፍ›› በሚል ቀርቧል፡፡
ሁለተኛው የክስ ጭብጥ ‹‹የሽብር ቡድን አመራር በመሆን›› የሚል ሲሆን በተለይም የአንደኛ ተከሳሽ ዘላለም ወርቃገኘሁ ‹‹የሽብር ቡድኑ አመራር በመሆንና አባል በመመልመል›› በሚል የክስ ጭብጥ ቀርቦበታልል፡፡
ከ2-5ኛ የክስ መዝገብ የሚገኙት ማለትም ሀብታሙ አያሌው፣ ዳንኤል ሺበሽ፣ አብርሃ ደስታና የሸዋስ አሰፋ ‹‹ህጋዊ የፖለቲካ ፓርቲን ከለላ በማድረግ ግንቦት 7 የተባለውን የሽብር ቡድን አላማ ለማሳካት ተንቀሳቅሰዋል፡፡ ፋሲል የኔ ዓለምና ሌሎች የሽብር ቡድኑ አባላት ጋር በስልክ በመነጋገርና በማህበራዊ ድህረ ገጸ የተለያዩ መልዕክቶችን ተለዋውጠዋል›› የሚል ክስ ቀርቦባቸዋል፡፡ አብርሃ ደስታ ከግንቦት 7 በተጨማሪ ‹‹ደምኢት የተባለ ቡድን አባል ነው፡፡›› የሚል ክስ ቀርቦበታል፡፡
በስተመጨረሻም ፍርድ ቤቱ ሁለት ጉዳዮች ላይ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ አንደኛው ረቡዕ ጥቅምት 26/2007 ዓ.ም 3 ሰዓት ተከሳሾቹ ዋስትና ይሰጣቸው አይሰጣቸው በሚለው ጉዳይ ላይ ፍርድ ቤቱ ከተከሳሾቹ ጠበቆች ጋር ተማክሮ ውሳኔ ይሰጣል ተብሏል፡፡ በሁለተኛነት ተጠርጣሪዎቹ ባቀረቡት አቤቱታ መሰረት ቀደም ሲል ለአራት ወራት ወደቆዩበት ማዕከላዊ እስር ቤት እንዳይመለሱ ፍርድ ቤቱን ስለጠየቁ ፍርድ ቤቱ በአዲስ አበባ ማረሚያ ቤት (3ኛ) እንዲቆዩ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡
ተከሳሾቹ ትናንት ጥቅምት 20/2007 ዓ.ም አራዳ ምድብ ችሎት ይቀርባሉ ተብሎ የነበር ቢሆንም ሳይቀርቡ ቀርተዋል፡፡ በተመሳሳይ ዛሬ ጥቅምት 21/2007 ዓ.ም ጠዋት ወደ ልደታ ፍርድ ቤት ተወስደው የነበረ ቢሆንም እንደገና ወደማዕከላዊ ተመልሰው ከሰዓት እንዲቀርቡ ተደርገዋል፡፡
ምንጭ፡- ነገረ-ኢትዮጵያ
ወጣቶቹ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች በድብቅ ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ተደረገ
ከአራት ወራት በፊት በሽብር ስም በአዲስ አበባ የፌደራሉ ወንጀል ምርመራ “ማዕከላዊ” የሚገኙት የአንድነት ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች አቶ አቶ ሀብታሙ አያሌው፣ ዳንኤል ሺበሺ፤ የሰማያዊ እና የአረና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች አቶ የሺዋስ አሰፋና አቶ አብርሃ ደስታ ዛሬ ጥቅምት 20 ቀን 2007 ዓ.ም. ከሰዓት በድብቅ ልደታ ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ መደረጋቸውንና ነገ ጠዋት በድጋሚ ልደታ ፍርድ እንደሚቀርቡ የፍኖተ ነፃነት ዘገባ ያስረዳል፡፡
የህሊና እስረኞቹ እንደተለመደው አራዳ ፍርድ ቤት ይቀርባሉ በሚል የትግል አጋሮችቸው እና ደጋፊዎቻቸውና ጋዜጠኞች ከቀኑ 7 ሰዓት ጀምሮ እስከ 11፡30 በቀጠሮው ስፍራ ቢጠብቁም፤ ፖሊስ በድብቅ ልደታ ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ማድረጉ ተሰምቷል፡፡ ታሳሪዎቹ ልደታ ፍርድ ቤት እንደሚገኙ መረጃ የደረሳቸው የአንድነት ፓርቲ አመራሮች በስፍራው ሲደርሱ አቶ ሀብታሙ አያሌው፣አቶ ዳንኤል ሺበሺ፣አቶ የሺዋስ አሰፋና አቶ አብርሃ ደስታ በመኪና ውስጥ ሆነው ወደ ማዕከላዊ ሲወሰዱ መመልከታቸውን ተናግረዋል፡፡ ቀደም ብሎም የልደታው ፍርድ ቤት “ጉዳዩን የሚያይ ዳኛ የለም” በማለት ለነገ ጠዋት ጥቅምት 21 ቀን 2007 ዓ.ም ቀጠሮ መሰጠቱም ተጠቁሟል፡፡
ምንጭ፡- ፍኖተ ነፃነት
ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በተመሰረተበት ክስ 3 ዓመት ፅኑ እስራት ተፈረደበት
የቀድሞ የፍትህ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅና መስራች፣ የአዲስ ታየምስ መፅሔት፣ የልዕልና ጋዜጣ በመጨረሻም የፋክት መፅሔት ባልደረባና አዘጋጅ የሆነው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በተመሰረተበትና ጥፋተኛ በተባለበት 3 ክሶች መካከል በአንዱ ክስ ብቻ የ3 ዓመት ፅኑ እስራት ተፈረደበት፡፡ጋዜጠኛው በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቃቤ ህግ በመሰረተበት ክስ ጥፋተኛ የሚል ብይን ከሰጠ በኋላ ቅጣት የተጣለበት በ2004 ዓ.ም. በፍትህ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ በነበረበት ወቅት በፃፋቸው ፅሑፎችን መሰረት አድርጎ መሆኑ ታውቋል፡፡
ጋዜጠኛው የተፈረበት፤ዛሬ ጥቅምት 17 ቀን 2007 ዓ.ም. በዋለው ችሎትም ጋዜጠኛው ጥፋተኛ ከተባለበት 3 ክሶች መካከል በአንዱ ክስ ብቻ የ3 ዓመት ፅኑ እስራት ቅጣት ተጥሎበታል፡፡ በዚህም መሰረት ጋዜጠኛ ተመስገን በፀጥታ ኃይሎች ቁጥጥር ስር እንደሆነ፤ወደ አቃቂ ቂሊንጦ ወደሚገኘው ወህኒ ቤት ተወስዷል፡፡
የጋዜጠኛው ተከላካይ ጠበቃ አቶ አምሃ መኮንን ቅጣቱን እና ፍርዱን በሚመለከት ይግባኝ እንደሚጠይቁ የተገለፀ ሲሆን፤ በቅጣት ፍርዱ አቃቤ ህጉም ሆኑ ተከላካይ ጠበቃው የቅጣት ማክበጃም ሆነ ማቅለያ አለመጠየቃቸው ተጠቅሟል፡፡ በኢትዮጵያ ይህ እስከተዘገበበት ድረስ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝን ጨምሮ የታሰሩት ጋዜጠኞች እና ብሎገሮች ቁጥር 18 መድረሱ ታውቋል፡፡
ኢህአዴግ መራሹ የኢትዮጵያ መንግስት በፃፉት ፅሑፍ የተከሰሱ፣የታሰሩም ሆነ የተፈረደባቸው ጋዜጠኞችም የሉም የሚል ተደጋጋሚ ማስተባበያ ቢሰጥም፤ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ጨምሮ ከታሰሩት 18 ጋዜጠኞችና ብሎገሮች መካከል 15ቱ ኢትዮጵያውያን ጋዜጠኞችና ብሎገሮች የቀረበባቸው ክስናም ሆነ ፍርድ ከስራቸው ጋር በተያያዘ በፃፉትና በተናገሩት መሆኑ የተመሰረተባቸው ክስ ያመለክታል፡፡