የተቃዋሚ ፓርቲዎች አመራሮች የክስ መቃወሚያ ውድቅ ተደረገ
በፌደራል አቃቤ ህግ የሽብር ክስ ተመስርቶባቸው ጉዳያቸው በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ወንጀል ችሎት እየታየ የሚገኙት የተቃዋሚ ፓርቲዎች አመራሮችና ሌሎች በተመሳሳይ መዝገብ የተከሰሱት ተከሳሾች በቀረበባቸው ክስ ላይ ያቀረቡት መቃወሚያ ውድቅ ተደረገባቸው፡፡ አመራሮቹ ጥር 26 ቀን 2007 ዓ.ም ችሎት ቀርበዋል፡፡
በእነ ዘላለም ወርቃገኘሁ የክስ መዝገብ የተከሰሱት የአንድነት፣ የሰማያዊና የአረና ፓርቲዎች አመራሮች የሆኑት አቶ ሀብታሙ አያሌው፣ የሺዋስ አሰፋ፣ አብርሃ ደስታ፣ ዳንኤል ሺበሽ እና ሌሎች ስድስት ተከሳሾች መቃወሚያቸው በፍርድ ቤቱ ውድቅ ተደርጓል፡፡
ተከሳሾች በጠበቆቻቸው አማካኝነት የቀረቡባቸው የተለያዩ የክስ ይዘቶች ላይ መቃወሚያቸውን አቅርበው የነበር ቢሆንም ፍርድ ቤቱ አቃቤ ህግ የተከሳሽ መቃወሚያ ውድቅ እንዲደረግለት የጠየቀውን በመቀበል ‹‹በመቃወሚያው ላይ የተነሱት ነጥቦች በአብዛኛው ማስረጃ በማሰማት ሂደት ወቅት ሊረጋገጡ የሚችሉ ስለሆኑ›› በሚል መቃወሚያቸው ውድቅ ተደርጓል፡፡ በመሆኑም ፍርድ ቤት በቀረበው ክስ አግባብ የክስ ሂደቱ እንዲቀጥል ውሳኔ ሰጥቷል፡፡
በሌላ በኩል ተከሳሾች በእስር ላይ በሚገኙበት ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ላይ ‹‹የመብት ጥሰት እየተፈጸመብን ነው›› በሚል አቤቱታ አቅርበው የነበር ሲሆን በአቤቱታው ላይ እስካሁን ከማረሚያ ቤቱ መልስ አለመሰጠቱ ታውቋል፡፡ አቤቱታው በጽሑፍ ተገልብጦ ለማረሚያ ቤቱ መላኩን የገለጸው ፍርድ ቤቱ፣ ለአቤቱታው መልስ ከማረሚያ ቤቱ እየተጠበቀ እንደሆነ ተገልጹዋል፡፡
በመሆኑም ይህንኑ የማረሚያ ቤቱን መልስ ለመስማትና የክሱን ሂደት ለመቀጠል ፍርድ ቤቱ ለየካቲት 11 ቀን 2007 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
ምንጭ፡-ነገረ-ኢትዮጵያ
“የአንድነት ፓርቲ አላማዎችና እሴቶች በገዢው ፓርቲ እና ምርጫ ቦርድ ህገወጥ ሴራ አይጠፋም!!” በምርጫ ቦርድ የፈረሰው አንድነት
በቅርቡ በ”ኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ” ፈርሶ ዋና ጽህፈት ቤቱ በፖሊስና በደህንነት ቁጥጥር ስር ከዋለ በኋላ ፤ የፓርቲው ጽህፈትም “ምርጫ ቦርድ” መርጫቸዋለሁ ላላቸው አካላት ከተላለፈ በኋላ አባላቱና አመራሩ ትግላቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል፡፡ ፓርቲው የአንድነት ዓላማዎችና እሴቶች በገዥው ፓርቲ እና ምርቻ ቦርድ ህገ-ወጥ ሴራ እንደማይጠፋ ጥር 26 ቀን 2007 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡ ሙሉ መግለጫውን ከታች ይመልከቱ፡-
አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት)
UNITY FOR DEMOCRACY AND JUSTICE PARTY (UDJ)
ከአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) የተሠጠ መግለጫ
********************************************************************************
የአንድነት ፓርቲ አላማዎችና እሴቶች በገዢው ፓርቲ እና በምርጫ ቦርድ ህገወጥ ሴራ አይጠፋም!!
***********************************************************************************
ገዢው ፓርቲ ለጻፋቸው ህጎችም ሆነ ይህን እንዲተገብሩ ኃላፊነት የወሰዱትን ሰዎች ክብር በሚያዋርድ መንገድ፤ በየደረጃው ያሉ ምርጫ ቦርድ ኃላፊዎችም ለመዋረድ ፈቃደኛ ሆነው በአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) አባላት አንድ ድምፅ ለማግኘት ለተቸገረ፤ ነገር ግን ለገዢው ፓርቲ ለመላላክ ቁርጠኛ ለሆነ ግለሰብ ዕውቅና ሰጥቻለሁ ማለቱ የሚታወስ ነው፡፡ ይሁን እንጂ አንድነት ፓርቲ የተቋቋመበት መሰረት የምርጫ ቦርድ ዕውቅና ሳይሆን በእያንዳንዱ አባላት ዘንድ የሚቀጣጠለው የነፃነት ስሜት እና ኢትዮጵያዊነት ነው፡፡ የአንድነት ፓርቲን መንፈስ፣ አላማዎቸና እሴቶች በዚህ ዓይነት እኩይ ደባ ከአባላትና ደጋፊ አዕምሮ ማውጣት አይቻለም፡፡
የምርጫ ቦርድ ተብዬው ተቋም በገዢው ፓርቲ ደህንነት የተደራጁ የፓርቲ ጠቅላላ ጉባዔ አባላት ያልሆኑ ሰዎች ያካሄዱትን ህገወጥ ስብሰባ ጉባዔ ነው በማለት እውቅና ሰጥቻለሁ ሲል፤ የተሰበሰቡት ሰዎች የአንድነት አባላት መሆናቸውን እና የጠቅላላ ጉባዔ ተወካይ መሆናቸውን አረጋግጣችኃል ወይ? ለሚል ቀላል የጋዜጠኛ ጥያቄ መልስ መስጠት አልቻሉም፡፡ ዕቅዱም አንድነትን እንደተቋም ማፍረስ ስለነበር ይህን ሊያስፈፅም ለሚችል ተላላኪ መስጠታቸውን በይፋ ከተናገሩ በኋላ በማግስቱም የፓርቲውን ፅ/ቤት በጠብመንጃ አፈሙዝ አስወርረው ለህገወጥ ቡድን በህገወጥ መንገድ አስረክበዋል፡፡
የአንድነት ፓርቲ በዚህ ዓይነት ህገወጥ ድርጊት የሚፈርስ አይደለም፡፡ የአንድነት አባላት በየትም ቦታ የምትገኙ ሁሉ ይህን ህገወጥ እርምጃ በፅኑ እየተቃወማችሁ ለነፃነትና ለኢትዮጵያዊነት የሚከፈለውን መስዋዕትነት ለመከፍል ዝግጁ መሆን ይኖርባቸኋል፡፡ አንድነት ፓርቲ በሰላማዊ ትግል ስልት የሚያምን በመሆኑ ይህን ትግል በላቀ ደረጃ ለማስቀጠል አበክሮ ይስራል፡፡ እያንዳንዱ አባልም አሁን በተፈጠረው ሁኔታ ሳይደናገጥ ለሰላማዊ ትግል ያለውን ፅናት እንደሚያስቀጥል እምነታችን ነው። በአንድነት ስራ አስፈፃሚ እምነት አሁን ባለው ሁኔታ የመድብለ ፓርቲ ፖለቲካ ተቀበረዋል የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሰናል።
በመሆኑም ስርዓቱ ለመድብለ ፓርቲ ፖለቲካ የሚመች የአስተሳሰብ ለውጥ እሰካላመጣ ድረስ ምርጫን በየአምሰት ዓመት የሚደረግ ክብረ በዓል አድርጎ ለማድመቅ እና የህዝብ ሀብት ለማባከን በሚደረግ ሂደት ተሳተፊ ለመሆን አዲስ ፓርቲ መመስረትም ሆኖ አሁን ካሉት ፓርቲዎች ጋር ተቀላቅሎ መታገል የሚያመጣው ለውጥ የለም፡፡ ምክንያቱም እነርሱም ልከ በአንድነት ላይ እንደተደረገው በሀይል እንዲፈርሱ የማይደረጉበት ምንም ዓይነት ዋስትና አለ ብለን ስለማናምን ነው። ከዚህ በኋላ በመድብለ ፓርቲ ሰርዓት ስልጣን ይያዛል ብሎ ማመን ህዝቡን ማታለል ነው የሚል ፅኑ እምነት አለን፡፡ ነገር ግን አሁንም የፓርቲ ፖለቲካ አላበቃም ብለው የሚያምኑ የአንድነት አባላት ካሉ በራሳቸው ነፃ ውሳኔ ወደ ፈለጉት ፓርቲ ተቀላቅለው የመታግል መብታቸው የተጠበቀ ነው።
የኢትዮጵያ ህዝብ አሁን ካለበት አምባገነናዊ ስርዓት ተላቆ ወደ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲሸጋገር ለማድረግ ህዝቡ የትግሉ ባለቤት ሆኖ የስርዓት ለውጥ እንዲመጣ እኛም የበኩላችንን ሀገራዊ ግዴታችንን ለመወጣት ቁርጠኞች ነን፡፡
ድል የህዝብ ነው!!!
አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት)
ጥር 26 ቀን 2007
ብሎገሮቹና ጋዜጠኞቹ ሰብሳቢ ዳኛው ከችሎት እንዲነሱ ጠየቁ
በእነ ሶልያና ሽመልስ የክስ መዝገብ የሽብር ክስ የተመሰረተባቸው የዞን ዘጠኝ ብሎገሮችና ጋዜጠኞች፤ ሰብሳቢ ዳኛው ከችሎት እንዲነሱ ጠየቁ፡፡
ጥር 26 ቀን 2007 ዓ.ም ለ17ኛ ጊዜ በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 1ልደታ ምድብ 9ኛ ወንጀል ችሎት የቀረቡት ብሎገሮቹና ጋዜጠኞቹ የችሎቱ ሰብሳቢ ዳኛ የሆኑት አቶ ሸለመ በቀለ “የተፋጠነ ፍትህ የማግኘት መብታችንን አላስከበሩልንም” በሚል ከችሎት እንዲነሱ በጽሑፍ አቤቱታ አቅርበዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ የተሰየመው ተሻሽሎ ቀርቧል በተባለው የአቃቤ ህግ ክስ ላይ የተከሳሾችን የእምነት ክህደት ቃል ለመስማት እንደነበር ዳኞቹ ቢናገሩም፣ ተከሳሾች አቤቱታ እንዳላቸው በመግለጽ የእምነት ክህደት ቃል ለመስጠት ዝግጁዎች አለመሆናቸውን ለችሎቱ ማስረዳት ችለዋል፡፡
ተከሳሾች ‹‹እኛ በሰብሳቢ ዳኛው ላይ አቤቱታ አለን፤ ፍርድ ቤቱ የራሱን ውሳኔ እንኳ አላከበረም፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆነን የእምነት ክህደት ቃላችንን ለመስጠት ዝግጁዎች አይደለንም›› በሚል ፍርድ ቤቱ አቤቱታቸውን እንዲቀበል ጠይቀዋል፡፡
ዳኛ ሸለመ በቀለ “ፍርድ ቤቱ ቃሉን አላከበረም›› በሚለው ጉዳይ ላይ መልስ ሲሰጡ ‹‹የእኛን ውሳኔ የማትቀበሉ ከሆነ ጉዳዩን በይግባኝ እንዲታይ ማድረግ ይቻላል” ብለዋል፡፡
“ላለፉት ስድስት ወራት በነበረው የክርክሩ ሂደት የችሎቱ ሰብሳቢ ዳኛ አቶ ሸለመ በቀለ ሂደቱን በአግባቡ በመምራት የተፋጠነ ፍትህ የማግኘት መብታችንን አላስጠበቁልንም፡፡ በተለያየ ጊዜም ሐሳባችን ለመግለጽ ስንሞክር ክልከላ አድርገውብናል፡፡ አሁን ደግሞ ችሎቱ ራሱ የሰጠውን ትዕዛዝ ራሱ ሽሮ ፈጽሞ ልንረዳው በማንችለውና የመከላከል መብታችንን በሚያጣብብ የክስ ሁኔታ ክርክሩን እንድንቀጥል ሲበየንብን የችሎቱ ሰብሳቢ ወሳኝ ሚና ነበራቸው” ሲሉ ተከሳሾች በሰብሳቢ ዳኛው ላይ ቅሬታቸውን በአቤቱታቸው ገልፀዋል፡፡
ፍርድ ቤቱም የችሎቱ ሰብሳቢ ዳኛ አቶ ሸለመ በቀለ ከችሎት እንዲነሱ የሚጠይቀውን አቤቱታ አይቶ ነገ ብይን ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል ሲል ነገረ-ኢትዮጵያ ዘግቧል፡፡
አንድነቶች፤ በምርጫ ጨዋታዉ ግጥሚያው ሳይጀመር አሸንፈናቸዋል፤ በሰላማዊ ትግሉም የመጨሻውን ሽንፈት ይጎነጫሉ!!
ተክሌ በቀለ
ምርጫ 2007 ለለዉጥ ብለን ተነሳን፡፡በሙሉ ልብና ዝግጅት ለህዝቡ አማረጭ ለመሆን ለምርጫ የሚየስፈልገዉን ግብኣት ይዘን ተሰለፍን፡፡አጥቂዎችን ከተከላካዮች ለይተን ደጀኖችን ከኃላ አሰልፈን በትምህርት ዝግጅትና በአባላት ጥራት እንዲሁም በሃሳብ የበላይነት ከኢህአዴግ የሚበልለጡ እጩዎችን አዘጋጀን፡፡ከሃቀኛ ፓርቲዎች ጋር ላለመወዳደር በሰጥቶ መቀበል መርህ ለመዳረደርና ለህዝቡ ብቁ ተመራጭ ይዞ ለመቅረብ ተደራዳሪ ኮሚቲም አቋቋምን፡፡
ህወሓት ሃሳብ የለዉም፡፡ቢኖረዉም ያረጀ ነዉ፡፡ለዚህ ትዉልድ አይመጥንም፡፡የሚጮኸዉን ያህል ቀርቶ ከኣባለቱ ሩብ ያህል እንኳን አድማጭ የለዉም፡፡እኛ ብዙ ተምረናል፡፡ከወደቁትና ዛሬም በጽናት ከሚታገሉቱ ቡድኖችና ግለሰቦች ትምህርት ቀስመናል፡፡ ከአሮጌዉ ህወሓትም ይሁን ከወጣቱ ሰማያዊ ፓርቲ የምንቀስመዉን ቀስመናል፤ለመማር ዝግ አይደለንም፡፡ለዉህደትና ለትብብርም እንዲሁ፡፡እደሉም ስላልነበራቸዉ እነሱ የብሄረሰብን ጥያቄ ከነስታሊን መጽሃፍት የቃረሙት ሲሆን እኛ በተግባር አብርን ኖረን የምናዉቀዉ፤በብሄረሰብ መሰረት ከተደራጁ ሃይሎች ጋር ግንባር ፈጥረን ችግረቸዉን ተረድተን የህዝብን ጥያቄ በተግባር ለመመለስ የቆረጥን በህዝብና በሃገር ሉኣለዊነት የማንደራደር የዘመኑ አስተሳሰብ ዉጤት ነን፡፡በመሳሪያና በገንዘብ ሳይሆን በሃሳብ የበላይነት ኮርተን፤ ዳኛዉን ሳይሆን ህዝቡን ተማምነን ለምርጫ ጨዋታዉ ዝግጁ ሆነን ነበር፡፡
ሽንፈቱ ከወዲሁ የገባዉ ህወሓት መጋረጃ ዉስጥ ሆኖ ጨዋታዉን ከወዲሁ አበላሸዉ፤አንድነት ፓርቲን ቢያሸዉ ቢደፈጥጠዉ ጎማ ሆነበት፡፡አልፈርጥለት ሲል የመጨረሻዉን አደረገ፡፡በጠራራ ጸሃይ ከህግ በላይ በጉልበት ዋናዉን ቢሮ ወረረዉ፡፡ምን እንደወሰዱ ምንስ እንዳስገቡብን አናቅም፡፡እርጉዝ ሴት በዱላ መትተዉ የወርቅ ሃብል የወሰዱ፤ጽህፈት ቤት ገብተዉ ምን እንደሚያደርጉ መገመት ይቻላል፡፡ያለ ህግዊና በእማኝ ፊት ርክክብ ሳይደረግ እንደልማዳቸዉ የህዝብ ሃብት ነጥቀዋል፡፡በሂደቱም ግለሰቦችና የህወሓትን ተግባር ለመፈጸም የተቋቋሙ ተቋማት ጥቁር ታሪካቸዉን ሲያኖሩ በእስር እየማቀቁ ያሉቱ የለዉጥ ሃይሎችና በዚህ ሂደት የለዉጥ ሃይሉን ከሚመራዉ ጋር የቆሙ የእንድነት አባላትና ደጋፊዎች ታሪካቸዉን በወርቅ ቀለም ጽፈዉ አኑረዋል፡፡እንዲሆም ድርጊቱን በማዉገዝ ከጎናችን የቆማችሁ ሁሉ በነጻነት ትግሉ የክብር ቦታ አላችሁ፡፡
አንድነቶች በምርጫ ጨዋታዉ ግጥሚያዉ ሳይጀመር አሸንፈናቸዋል፤በሰላማዊ ትግሉም የመጨሻዉን ሽንፈት ይጎነጫሉ፡፡ ዛሬም የነፃ አዉጪን ስም የተሸከመዉ ህወሓት የሚያስበዉ እንደራሱ ነዉ፡፡የፓርቲ ስም፤አርማና ማህተም በዚህ ትዉልድ ቦታ እንደሌላቸዉ አልተረዳዉም፡፡የትውልዱ ጥያቄ በእኩልነት ላይ መሰረትዋን ያኖረች ጠንካራ ሃገር እንጂ እወክለዋለሁ የሚለዉን ህዝብ እንኳን በበለጠ የሚያፍን የፓርቲ ስም አይነት አይደለም፡፡
የአንድነት ፓርቲ ፕሮግራምና የኛ ራዕይና በኛና በህዝብ ልብ እንዲሁም በሌሎች ፓርቲዎች ዉስጥ እንደሚገኝ አልገባቸዉምና ፓርቲን ሲነጥቁ ሰላማዊ ትግሉን የገደሉ፤እኛንም የበተኑ መስሎአችዋል፡፡የለዉጥና የአንድነት ሃይል ይበልጥ ይጠናከራል እንጂ አይበተንም፡፡እርግጥ ነዉ የመድበለ ፓርቲ ስርኣትን አደጋ ላይ ጥለዉታል፡፡ህዝባዊ ሰላማዊ ትግሉ ላይ ግን ጉልበትና ተጨማሪ እድል ጨምረዉለታል፡፡ የአንድነትና የለዉጥ ሃይሎች ዛሬም ይበልጥ ቁርኝነታችንን በማጠንከር ለሰላማዊ ትግሉ መጎልበት ያለንን አቅም ልናበረክት ይገባል፡፡ሁላችንም እድሉን እንጠቀምበት፤የጠበቡ ቤቶችንም ለሁሉም እንዲሆኑ ባፋጣኝ እናስፋቸዉ !
ይህ ተውልድ የቃል እዳ አለበት፤እነአንዷለምም እነ አሞራዉም የሚሉቱና እያሉ ያሉቱ ይህን ነዉ፤ ፍትህና ነጻነት በኢትዮጵያችን በትግላችን ይሰፍናሉ!!
በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉት “ፀረ- ሰላም ህፃናት”
ጌታቸው ሽፈራው
አቶ ቀኖ የሰማያዊ ፓርቲ ጽ/ቤት ውስጥ በጥበቃነት ይሰራሉ፡፡ አቶ ቀኖና ጎረቤቶቻቸው ሰብሰብ ሲሉ ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ በተለይ ኢህአዴግ ስለሚወስዳቸው ህገ ወጥ እርምጃዎች፣ ስለተቃዋሚዎች ጥንካሬና ድክመት… የመሳሰሉት ጉዳዮች ላይ ያወራሉ፣ ይወያያሉ፣ በሚያከራክሯቸው ነገሮችም ይከራከራሉ፡፡ ይህ የእነ አቶ ቀኖ ሰፈር ሰዎች የውይይት መድረክ በእነሱ ብቻ ተወስኖ አልቀረም፡፡ ጉዳዩ በመደጋገሙ ህፃናት ልጆቻቸው ሳይቀር ‹‹ሰማያዊ፣ አንድነት፣ መድረክ፣ ኢህአዴግ…..›› እያሉ የአቅማቸውንና የገባቸውን ያህል ያወራሉ፡፡ ቤተሰቦቻቸው ሲከራከሩና ሲያወሩ ከሰሙት! በዚህ አቋማቸውም ህፃናቱ ‹‹ፀረ ሰላም›› ተብለው ታስረውበታል፣ ተደብድበውና ይቅርታ ጠይቀውም ተለቀዋል፡፡
ማክሰኞ ጥር 19 ቀን 2007 ዓ.ም ነው፡፡ ከቀኑ 11፡30 አካባቢ አራዳ ክፍለ ከተማ የሚገኘው መስከረም 2 ት/ቤት ተማሪዎች የሆኑት 14 ያህል ህጻናት ወደ ቤታቸው እየተመለሱ ነው፡፡ ህፃናቱ እንደወትሯቸው ከት/ቤተ መልስ እየተጨዋወቱ፣ እየተቀላለዱ፣ እየተሯሯጡ ወደ ቤታቸው በመመለስ ላይ ናቸው፡፡ መሃል ላይ ግን ቤተሰቦቻቸው በተደጋጋሚ የሚያነሱትን ጉዳይ አንስተው መከራከር ጀምረዋል፡፡ የ13 አመት እድሜ ያለውና የ6ኛ ክፍል ተማሪ የሆነው የአቶ ቀኖ ልጅ ‹‹ኢህአዴግኮ ፈሪ ነው፡፡ ሰማያዊ ፓርቲን ይፈራዋል›› ይላል፡፡ ጓደኛው ደግሞ ‹‹ኢህአዴግማ የሚፈራው አንድነትን ነው፡፡›› ይላል፡፡ ሌላኛው ደግሞ ‹‹መድረክ የሚባል ፓርቲምኮ አለ፡፡ እሱንም ይፈራዋል፡፡ ኢህአዴግ ፈሪ ነው!›› ይላል፡፡ ሌሎቹም ቤተሰቦቻቸው ውሃ፣ መብራትና ኔትዎርክ ሲጠፋ፣ ኑሮ ሲወደድ፣ ሙስና ሲያስመርራቸው በስርዓቱ ላይ ከሚያሰሙት ሮሮ መካከል የሚያስታውሱትን እየጠቀሱ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ይከራከራሉ፣ ያወራሉ፡፡ ይቀልዳሉ!
ይህኔ ነው አስገራሚው ነገር የተከሰተው፡፡ ፖሊስ 14ቱንም ህፃናት በ‹‹ፀረ ሰላም›› እንቅስቃሴያቸው ከእነ ሙሉ የትምህርት መሳሪያቸው በቁጥጥር ስራ ካዋላቸው በኋላ በጥፊና በእርግጫ እያለ ወደ ወረዳ 7 ፖሊስ ጣቢያ ይወስዳቸዋል፡፡ ፖሊስ ጣቢያ ከደረሱ በኋላም ‹‹ተንበርከክ!›› ተብለው ‹‹ማን ነው ሰማያዊ፣ አንድነት፣ መድረክ እያለ ሲያወራ የነበረው?›› እየተባሉ ህፃናት ላይ ይፈፀማል ተብሎ የማይታሰብ ድብድባ ይፈፀምባቸዋል፡፡ ህፃናቱ ‹‹ፀረ ሰላም›› ለተባለው እንቅስቃሴያቸው ቅጣትና ማስፈራሪያ ከተደረገባቸው በኋላ ‹‹ከአሁን በኋላ አይደግመንም›› ብለው ይቅርታ ጠይቀው በ‹‹ፖሊስ ሆደ ሰፊነት›› ከምሽቱ 1 ሰዓት አካባቢ ከእስር ተለቀዋል፡፡
እነዚህ ህጻናት ‹‹ዳግመኛ አይለምደንም!›› ብለው ይቅርታ ባይጠይቁ ኖሮ ታስረው ሊያድሩም ይችሉ ነበር፡፡ ምን አልባትም ፖሊስ ‹‹ያልተፈቀደ ቅስቀሳ አድርገዋል፣ ህገ መንግስቱን ለመናድ ጥረዋል፣ ህዝብን ለማናወፅና አመጽ ለመቀስቀስ ተደራጅተው ተንቀሳቅሰዋል፣ ምርጫው ሰላማዊ እንዳይሆን እየሰሩ ነው….›› የሚል ክስ እንደማይመሰርት እርግጠኛ መሆን አይቻልም፡፡ እስካሁን ፖሊስ ሲያቀርባቸው ካየናቸው አስቂኝ የቀጠሮ ማራዘሚያ ‹‹ምክንያቶች›› አንጻር ‹‹አብረዋቸው የሚማሩት ሌሎች ግብረ አበሮቻቸው አልተያዙም፣ ቢወጡ አሁንም ተመሳሳይ ‹ፀረ ሰላም› ተግባር ይፈፅማሉ፣ መረጃ ይደብቁብኛል›› በሚል ተጨማሪ ቀን ይሰጠኝ ላለማለቱ እርግጠኛ መሆን አይቻልም፡፡
ስርዓቱን ለመከላከል ሲባል እስሩ እዚህ ደርሷል!




