የዶ/ር መረራ ጉዳይ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ትርጉም እንዲሰጥበት ትእዛዝ ተሰጠ
የእነ ዶ/ር መረራ ጉዲና መዝገብ ለዛሬ የተቀጠረው ከዚህ ቀደም በቀረበው መቃወሚያ ላይ ብይን ለመስጠት ነበር። በመሆኑም ዛሬ – ሰኔ 30/2009 – ዶ/ር መረራ ጉዲና በተመሰረተባቸው 3ት ክሶች ላይ ያቀረቧቸው መቃወሚያዎች ላይ 19ኛው ወንጀል ችሎት ከፊል ብይን ሰጥቶበታል። ችሎቱ፣ ዶ/ሩ ያቀረቡትን ክሱ እንዳይንጓተት ከሌሎቹ በሌሉበት ከተከሰሱት ሶስት ተከሳሾች ይነጠልልኝ የሚለውን መቃወሚያ ጨምሮ ሌሎቹን መቃወሚያዎች በሙሉ ውድቅ ሲያደርግ አንዱን ግን ለትርጉም ወደ ፌደሬሽን ምክር ቤት ለትርጉም መላኩን ተናግሯል።

ዶ/ር መረራ ጉዲና
በእነዶ/ር መረራ መዝገብ የተከፈተው ክስ ላይ አቃቤ ህግ የፀረ ሽብርተኝነት አዋጁን በመጥቀስ፣ የምስክሮች ሥም ሳይጠቀስ የቀረ ሲሆን፣ ይህ በሥራ ላይ ያለው የሥነ ስርዓት ሕግ ተከሳሾች የሚቀርብባቸውን ማስረጃ እና ምስክር የማወቅ መብት አላቸው ከሚለው ጋር የሚጋጭ በመሆኑ እንዲተረጎም ወደፌዴሬሽን ምክር ቤት ተልኳል። የተከሳሹ ጠበቃ አቶ ወንድሙ ኢብሳ በበኩላቸው “እኛ የጠየቅነው፣ ደንበኛችን ባልተከሰሱበት የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ የምስክር ጥበቃው አንቀፅ ሊጠቀስባቸው አይገባም ብለን እንጂ ትርጉም ያስፈልጋል ብለን አይደለም” ብለው ቅሬታቸውን አቅርበዋል።
ዶ/ር መረራም መልእክት አለኝ በማለት የሚከተለውን ለዳኞች ተናግረዋል፣ “የተመሰረተብኝ ፖለቲካዊ ክስ ነው። መንግስት ይዞ የተነሳው ተቃዋሚዎችን በራሱ የተበላሸ አስተዳደር ጥፋት ጉዳይ መወንጀል ስለሆነ እንጂ መንግሥት የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርታ በጠየቀበት ጉዳይ ነው የተከሰስኩት። የተከሰስኩት፣ ለኦሮሞ ሕዝብ መብት በመታገሌ ነው። የተከሰስኩት ለኢትዮጵያ ሕዝብ መብት በመታገሌ ነው። የተከሰስኩት ለእኩልነት እና ሁላችንንም እኩል ለሚመለከት ስርዓት በመታገሌ ነው። የተከሰስኩት ሀቀኛ የፍትህ ስርዓትና የፌዴራል ስርዓት እንዲኖር በመታገሌ ነው። ዳኞች እስካሁን ካላነበባችሁ፣ የአቤ ጉበኛን አልወለድም እና የበአሉ ግርማን ኦሮማይ አንብቡ። ሊወድቅ እየደረሰ መንግስት የሚሰራውን ሥራ የሚያስረዱ መፅሃፍት ናቸው።”
ዳኞች መዝገቡን ለሐምሌ 25/ 2009 የተቀጠሩ ሲሆን፤ በሚቀጥለው ቀጠሮ ችሎቱ የምስክሮች ዝርዝር መገለፅ አለበት በሚል ክሱ እንዲሻሻል ወይም የለበትም በሚል የቃቤ ሕግ ምስክሮችን ለማድመጥ ቀጠሮ ይይዛል ተብሎ ይጠበቃል።
EHRP
እነ ኦሞት አግዋ ካቀረቡት አሰራ አንድ የከስ መቃወሚያ አስሩን ፍርደቤቱ ውድቅ አደረገው
ክሳቸው ከነሐሴ 29 ቀን 2007 ዓ.ም. ጀምሮ በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት አየታየ የሚገኛው የእነ ኦሞት አግዋ ሶስት ተከሳሾች ያሉበት(ኦሞት አጉዋ፣ አሽኔ አስቲን እና ጀማል ኡመር ) ያቀረቡትን የክስ መቃወሚያ አቃቤህግ ከሰጠው ምላሽ ጋር መርምሮ ምላሽ ለመስጠት ለዛሬ ጥር 2 ቀን 2008 ዓ.ም የቀጠረው ፍርድ ቤቱ ተከሳሾች ያቀረቡትን የክስ መቃወሚያዎች ከአንዱ በሰተቀር ሁሉንም አለመቀበሉን እና ውድቅ ማድረጉን የመሃል ዳኛው ታረቀኝ አማረ በንባብ ለችሎቱ አሰምተዋል፡፡

እነ አቶ ኦሞት አግዋ አዲስ አበባ በሚገኘው የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ታስረው ሲቀርቡ
በፍርድ ቤቱ ከአንድ መቃወሚያ በሰተቀር መቃወሚያዎቹ ውድቅ እንዲሆኑ እና ተቀባይነት እንዳያገኙ ምክኒያት የሆነው አቃቤ ህግ በማስረጃ ማሰማት ሂደት ላይ በዝርዝር እንድንሰማቸው ያደረጋል የሚል ነው፡፡
ተከሳሾች ክሳችን በእያንዳዳችን በተናጠል ቀርቦብን ሳለ አቃቤ ህግ በጋራ የከሰሰን ክስ ተነጣጥሎ ለየብቻ እንድንከሰስ ይደረግ የሚለውን የተከሳሾች መቃወሚያ ፍርድ ቤቱ የወንጀል ህጉን አንቀፅ 211 ቁጥር 7/3 በመጥቀስ ወንጀሎቹ የተለያዩ ቢሆንም የጋምቤላ ሕዝቦች ነፃነት ንቅናቄ (ጋሕነን) የጠራው ስብሰባ ላይ ኬንያ ፣ናይሮቢ ለመሳተፍ ሲሄዱ በቁጥጥር ስር የዋሉ መሆናቸውን ጠቅሶ ተከሳሾቹ በአንድ መዝገብ ሊከሰሱ ይችላሉ በማለት ፍርድ ቤቱ የተከሳሾቹን መቃወሚያ አልተቀበለም፡፡
ተከሳሾች አባል ሆነውበታል በሚል የተጠቀሰው የጋምቤላ ሕዝቦች ነፃነት ንቅናቄ (ጋሕነን) ቡድን ህልውና እንዳለው አቃቤ ህግ በክሱ እንዲያስርዳ በተቃውሞቸው የጠየቁት ተከሳሾች፣ ቡድኑ በፍርድ ቤትም ሽብርተኛ ተበሎ አለመሰየሙን ጠቅሰው ከክሱ ላይ እንዲሰረዘላቸው ላቀረቡት መቃወሚያ ፍርድቤቱ የቡድኑን ህልውና እና ዝርዝር ማሰረጃ በክሱ ሂደት የሚሰሙ ናቸው በማለት ተቃውሞውን አለተቀበለም፡፡
በኢሜል አና በስካይፒ የተለያዩ ግንኙነቶችን ፈጥረዋል ብሎ አቃቤ ህግ በክሱ ላይ ያሰቀመጠውን ተከሳሾች ከማን ጋር ግንኙነት እንዳደርጉ ሰላልጠቀሰ በክሱ ከማን ጋር ግንኙነት እንደነበራቸው በዝርዝር እንዲጠቀስ በክስ ተቃወሞው ላይ ያቀረቡትንም ተቃውሞ እንድሌሎቹ የክስ መቃወሚያዎች በተመሳሳይ ፍርድ ቤቱ የክሱ መሰረታዊ ስህተት አይደለም፣በማሰረጃ ማሰማት ሂደት ላይ እምንሰማቸው ዝርዝሮች ናቸው በማለት ተቃውሞውን ውድቅ አድርጓል፡፡
በመጨረሻም ተከሳሾች ካቀረቡት አስራ አንድ መቃወሚያዎች ፍርድቤቱ የተቀበለው በክሱ ላይ አንደኛ ተከሳሽ ኦሞት አግዋ አሰቀጠራቸው የተባሉት የፖሊስ አባላት ስም ዝርዝር በክሱ ተካቶ ይቅረብልን በለው ያቀርቡትን ተቃውሞ ሲሆን ፍርድቤቱ አቃቤህግ ለጥር 17 ቀን 2008 ዓ.ም. በክሱ ላይ የተጠቀሱትን የፖሊስ አባላት ስም ዝርዝር በክሱ አካቶ እንዲያቀርብ ትዕዛዝ ሰጥል፡፡
EHRP
ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ የይግባኙን ጉዳይ በተመለከተ ለሰበር ሰሚ ችሎት አቤቱታ አቀረበ
የቀድሞው የአውራምባ ታይምስ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ የነበረው ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ በ2003ዓ.ም. ሰኔ ወር ላይ ከሌሎች 4 ሰዎች ጋር (ጋዜጠኛ ኤልያስ ክፍሌ፣ ጋዜጠኛ ርዕዮት ዓለሙ፣ አቶ ዘሪሁን ገ/እግዚአብሄር እና ወ/ሮ ሂሩት ክፍሌ) የፀረ ሽብርተኝነት ህጉን ተላልፈሃል ተብሎ ክስ ተመስርቶበት የነበረ ሲሆን፤በዚህም የ14 አመት የእስር ቅጣት እንደተወሰነበት የሚታወስ ነው።

ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ
ቅጣቱ ከተላለፈበት በኋላ ጥፋተኛ መባሉን በመቃወም ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ቢልም መዝገቡ በይቅርታ ጉዳይ እየታየ መሆኑ ተገልፆለት በወቅቱ ይግባኝ ማለት ሳይችል ቀርቷል። ከእርሱ ጋር የይቅርታ ጥያቄ ያቀረቡ የስዊድን ጋዜጠኞች እና በተመሳሳይ መዝገብ የምትገኘው ሂሩት ክፍሌ ከእስር የተለቀቁ ሲሆን፤ የጋዜጠኛ ውብሸት የይቅርታ ጉዳይ ግን እስካሁን ድረስ ተፈፃሚ አልሆነም።
በመሆኑም በቅርቡ በወንጀለኛ መቅጫ ስነስረዓት ህጉ አንቀፅ 191 ስር በተመለከተው መሰረት የይግባኝ ጊዜ ካለፈ በኋላ ይግባኝ ለማቅረብ ፈቃድ ለማግኘት የሚቀርብ ማመልከቻ በማስገባት ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኙን አቅርቦ ነበር። የወንጀለኛ መቅጫ ስነስርአት ህጉ አንቀፅ 196 (1) እና (2)፤ የተፈረደባቸው ብዙ ሰዎች ሆነው አንዱ ብቻ ይግባኝ ያቀረበ እና የተጠቀመ [ከእርሱ ጋር አብራ የተከሰሰችው ጋዜጠኛ ርዕዮት አለሙ ከጋዜጠኛ ውብሸት ጋር ተመሳሳይ የቀረበባት እነወዲሁም የስር ፍርድ ቤት 14 ዓመት ከፈረደባት በኋላ በይግባኝ ወደ 5 አመት እንደተቀነሰላት ይታወቃል።] እንደሆነ ሌሎቹም ይግባኝ እንዳሉ እንደሚቆጠር እንደሚደነግግ በመጥቀስ ነው ይግባኙን ያቀረበው። ይግባኙን የተመለከተው ይግባኝ ሰሚ ችሎት የይግባኙን አቤቱታ ሳይቀበለው ውድቅ አድርጎበታል። ጋዜጠኛ ውብሸትም ይግባኝ ሰሚ ችሎት መሰረታዊ የህግ ስህተት በመጣስ ይግባኙን እንዳልተቀበለው በመግለፅ ያቀረበው አቤቱታ ዛሬ ሰበር ሰሚ ችሎት ቀርቦ ነበር። ዳኞች ጉዳዩን መርምረው ብይኑን ሰኔ 12 ቀን 2009 ዓ ም ቀን እንደሚያደርሱ እና ውሳኔውን ከመዝገብ ቤት ከማግኘት እንደሚቻል ተናግረዋል።
ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ በ2007 ዓ. ም. “የነፃነት ድምፆች” እና “ሞጋች እውነቶች” የተሰኙ መፅሐፍት ለንባብ ያበቃ ሲሆን በመጪው ሰኞ ሰኔ 12/2009 ቀን ከታሰረ 6ዓመት ይሞላዋል።
EHRP
ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው አንድ ዓመት ከ6 ወር እስር ተፈረደበት
(አዲስ ሚዲያ) የነገረ ኢትዮጵያ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው በፌደራል አቃብ ህግ በተመሰረተበት ክስ ከአንድ ዓመት ከ አምስት ወር እስር በኋላ የፌደራሉ ከፍተኛው ፍርድ ቤት አዲስ አበባ ልደታ ምድብ ችሎት ግንቦት 18 ቀን 2009 ዓ. ም. የ 1 ዓምት ከ 6 ወር የቅጣት እስር ፈርዶበታል።

ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው
ጋዜጠኛው ከህዳር 2008 ዓ. ም. ጅምሮ የነበረውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ ሲታሰር፥ ቀደም ሲል የሽብርተኝነት ክስ ተመስርቶበት የነበረ ቢሆንም፤ በመጨረሻም ፍርድ ቤቱ ክሱን ወደ መደበኛ ወንጀል ክስ ዝቅ በማድረግ አመፅ ማነሳሳት በሚል ክስ የቅጣት ውሳኔውን ማሳለፉን አሳውቋል። ይሁን እንጂ ጋዜጠኛው ለተላለፈበት የቅጣት ውሳን ብይን የቅጣት ማቅለያ እንዲያቀርብ ፍርድ ቤቱ ቢጠይቀውም ጋዜጠናው ባልሰራሁት ወንጀል የምጠይቀው የቅጣት ማቅለያ የለም በማለት የፍርድ ቤቱን ጥያቄ ውድቅ ማድረጉ ታውቋል።
ጋዜጠኛው ክስ የተመሰረተበትና የ1 ዓመት ከ6 ወር እስር ቅጣት የተጣለበት፤ በፌስ ቡክ ማኅበራው ሚዲያ በውጭ ከሚገኝ ጋዜጠኛ በተለይም መቀመጫውን ዋሸንግተን ዲሲ ካደረገው ጋዜጠኛ አበበ ገላው ጋር መልዕክት ተለዋውጠሃል፥ አመፅ ቀስቅሰሃል የሚል እንደነበር የቀረበበት ክስ አመልክቷል።
ጋዜጠኛው ህትመቱና ስርጭቱ በመንግሥት እንዲቋረጥ ከተደረገው የነገረ ኢትዮጵያ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ሆኖ ከማገልገሉ በተጨማሪ በተለያዩ መፅሔቶች፥ ጋዜጦችና ድረ-ገፆች ላይም የተለያዩ ፖለቲካዊ፥ ሰብዓዊ መብትና ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያደረጉ በርካታ ፅሑፎችንም ያበረክት እንደነበር ይታወቃል። ይህ በእንዲህ እንዳለ ሰኔ 2006 ዓ ም በመንግሥት እውቅና ተነፍጎት አባላቱና አመራሩ ምንም ዓይነት የስራ እንቅስቃሴ እንዳያደርጉ እግድ የተጣለብት የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች መድረክ (ኢጋመ) መስራችና አስተባባሪ እንደነበር ይታወቃል።
ጋዜጠኛ ጌታቸው ከታህሳሥ 15 ቀን 2008 ዓ ም ጀምሮ በእስር ላይ ይገኛል።
በተለይ መንግሥት ህዝባዊ አመፁን ተከትሎ በወሰደው ርምጃ ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራውን ጨምሮ፥ ሌሎች ጋዜጠኞችና 60 ሺህ ያህል ሰላማዊ ዜጎች መታሰራቸውን የሀገርው ውስጥ የሰብዓዊ መብት አራማጆችና ተሟጋቾች መረጃ አመልክቷል።
የሰማያዊ ፓርቲ አመራር የነበረውና የመብት አራማጅ ዮናታን ተስፋዬ 6 ዓመት ከ6 ወር እስራት ተፈረደበት
(አዲስ ሚዲያ) የሰማያዊ ፓርቲ የቀድሞ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ፥ የ2007 ዓ. ም. በአዲስ አበባ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዕጩና የመብት አራማጅ ወጣት ዮናታን ተስፋዬ ግንቦት 17 ቀን 2009 ዓ ም በዋለው ችሎት 6 ዓመት ከ6 ወር እስር ተፈርዶበታል።

ዮናታን ተስፋዬ
ወጣት ዮናታን ከህዳር 2008 ዓ. ም. ጀምሮ የተነሳውን ህዝባዊ አመፅ ተከትሎ ከታሰሩት በርካታ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና የመብት ተሟጋቾች መካከል አንዱ ነው።
ወጣት ዮናታን ተስፋዬ ደም ልገሳን ጭምሮ በተለያዩ ግብረ ሰናይ ተግባራት ላይም ይሳተፍ የነበረ ቢሆንም፥ ከታህሳሥ 17 ቀን 2008 ዓ ም ጀምሮ በእስር ላይ ይገኛል።
የፌደራል አቃቤ ህግ ክስ የመሰረተበት በፌስ ቡክ ማኅበራዊ ገፅ መንግሥት በዜጎች ላይ እየወሰደ የነበረውን ርምጃ የሚቃወሙና የሚተቹ ፅሑፎችን ፅፏል በሚል እንደሆነ የተመሰረተበት የክስ ሰነድ ያመለክታል።
በመጨረሻም የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የአዲስ አበባ ልደታ ምድብ ችሎት ግንቦት 17 ቀን 2009 ዓ ም በዋለው ችሎት በፌስ ቡክ ማኅበራዊ ገፅ የፃፋቸውን ፅሑፎች ብቻ እንደመረጃና ማስረጃ በመጠቀም 6 ዓመት ከ6 ወር እስራት ፈርዶበታል።