ፍትህ መረገጡን በአደባባይ አስመስክረናል፤ሃላፊነታችንንም ተወጥተናል!
ለኔ እዉነተኛው የአንድነት ፓርቲ ትናንት መጋቢት 23 ቀን 2007 ዓ.ም. በፍርድ ቤት ውሳኔ ተቀብሯል፡፡ዱባና ቅል አበቃቀሉ ለየቅል እንደሆነ ቀድም ሲል አውቀናል፡፡ ዳኛ ብርቱኳንም፣ ፍርህይወትም ዳግም አልተከሰቱም፡፡ እንደ ኢህአዴግ የምርጫ ውጤት 99.6 ከመቶ አመራሩና አባላቱ በምርጫ ቦርድ እንዲበተኑ የተበየነበት እንዲሁም በደጋፊዎች የተገዛ ንብረት ያለፍርድ ቤት ትእዛዝ በመንግስት ታጣቂ ፖሊሶች የተዘረፈበት አንድነት የፍትህ ተቋሙን ለመፈተሸ ምርጫ ቦርዱን መክሰሱ ይታወቃል፡፡
ይሁን እንጂ ምርጫ ቦርድን መክሰሳችን አግባብ እንዳልሆነ አንቀጽ ተጠቅሶ ከማስፈራሪያ ጋር ክሱ ዉድቅ ተደርጓል፡፡ በዚህም ፍትህ መረገጡን ባደባባይ አስመስክረናል፤ሃላፊነታችንንም ተወጥተናል፡፡ ቀጣዩን በቀጣይ ሂደት የምናየዉ ይሆናል፤እንደሚፈልጉት ተበትነን አንቀርም፡፡ አንድነቶች በያለንበት እንረጋጋ!!
ታላቋ ምዕራብ አፍሪካዊት ሃገር ናይጀሪያ እዚህ የደረሰችዉ ዉድ ዋጋ ከፍላ ነዉ፡፡ ከናይጀሪያም በላይ ዋጋ ብንከፈልም በልተዉ በማይጠግቡ በሎች ትግሉ እየተነጠቀ ዛሬም እዛዉ ላይ ነን፡፡ ታላቅዋ የምስራቅ አፍሪካ ኮከብ ሀገረ ኢትዮጵያ በልማት ስም ክብሯ እንዲወርድ እየተደረገች ትገኛለች፡፡ እናም በዲፕሎማሲ፤በዲሞክራሲ፤በኢኮኖሚም ይሁን በሁለንተናዊ ልማት የአለም ማህበረሰብ በአፍሪካ ትኩረት ናይጀሪያ ሆናለች፡፡ ኢትዮጵያ የምትፈለገዉ ለክፍለ አሁጉሩ የደህንነት አጋርነት ብቻ ነዉ፡፡
የናይጀሪያ ተፎካካሪ ፓርቲዎችና(የተቀናቃኝ ፓርቲዎች ትብብርና ዉህደት ያስከተለዉን ዉጤትም ልብ ይሏል) የተወዳዳሪ ግለሰቦች ሚና ቀላል ባይሆንም ለናይጀሪያ ተስፋ የሆናት ግን ህዝቡ ነዉ፡፡ የኢትዮጵያችንም የለዉጥ ተስፋ ህዝቡ ነዉ፡፡ በዚህ ወቅት የተቃዋሚ የፖለቲካ ሃይሎች አሰላለፍም የጎላ ድርሻ ይኖረዋል፡፡
የመድረክ ከፍተኛ አመራርና የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህሩ አቶ በቀለ ገርባ ከእስር ተለቀቁ
የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህርና የቀድሞው የኦሮሞ ፌደራሊስት ንቅናቄ፣ የአሁኑ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረንስ/መድረክ ምክትል ሊቀመንበር የሆኑት አቶ በቀለ ገርባ ከነሐሴ 2003 ዓ.ም. ጀምሮ በእስር ከቆዩ በኋላ መጋቢት 21 ቀን 2007 ዓ.ም. ተለቀዋል፡፡ አቶ በቀለ ገርባ መንግሥት በዜጎች ላይ በፈፀማቸውና እየፈፀማቸው ባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ጉዳይ ከአምንስቲ ኢንተርናል ጋር ቃለ መጠይቅ ካደረጉ በኋላ የኦነግ አባል ናቸው በሚል በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ ወንጀል ችሎት 8 ዓመት ፅኑ እስራት ተፈርዶባቸው ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ተከላካይ ጠበቆቻቸውና አቶ በቀለ የታሰሩት ያለምንም ወንጀል እንደሆነ፣መንግሥት የኦነግ አባል ብሎ የመሰረተባቸው ክስ እንደማይመለከታቸው፣ እሳቸው በወቅቱ በሀገር ውስጥ በሰላማዊ መንገድ እየታገለ ያለው የኦፌዲን/መድረክ አመራር መሆናቸውን በማስረጃ ቢከራከሩም ፍርድ ቤቱ ሳይቀበለው በመቅረቱ ለፌደራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ መጠየቃቸው ይታወሳል፡፡
እነ አቶ በቀለ ገርባ የከፍተኛው ፍርድ ቤት ውሳኔ በመቃወም ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ካሉ በኋላ የ8 ዓመቱ ፅኑ እስራት ወደ 3 ዓመት ከ7 ወር የተቀነሰ ሲሆን፤ ይሄንንም ይግባኝ ብለው ወደ ፌደራሉ ሰበር ሰሚ ችሎት ቢሄዱም የ3 ዓመት ከ7 ወር ፍርድ በመፅናቱ በእስር ቆይተዋል፡፡ አቶ በቀለ ገርባ በህጉ መሰረት በአመክሮ ከእስር መፈታት የነበረባቸው ከአንድ ዓመት በፊት ጥር 2006 ዓ.ም. ቢሆንም፤ ዝዋይ የሚገኘውም ሆነ አቃቂ ቂሊንጦ የሚገኘው ወህኒ ቤት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው 4ኛ ዓመት ድረስ በእስር ሊቆዩ ችለዋል፡፡ መረጃዎች እንደጠቆሙት ከሆነ አቶ በቀለ ገርባ የተለቀቁት ከነበሩበት እስር ቤት ከተለቀቁ በኋላ ከባለቤታቸው ወ/ሮ ሐና ጋር እየተጓዙ ከእስር ቤቱ ብዙም ሳይርቁ፤ በወህኒ ቤቱ ጠባቂዎች ቆይ ሌላ የሚጣራ ጉዳይ አለ በሚል ተመልሰው እስር ቤት ካስገቧቸው በኋላ በጭለማ ሞጆ ከተማ አካባቢ ተወስደው መለቀቃቸው ተጠቁሟል፡፡ አቶ በቀለ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ከማስተማራቸው በተጨማሪ የዶክተሬት ዲግሪ ማጠናቀቂያቸው ላይ መታሰራቸው አይዘነጋም፡፡ በአሁን ወቅት የኦፌኮ/መድረክ አመራር አቶ ኦልባና ሊሊሳን፣ የአድነት ከፍተኛ አመራር አቶ አንዱዓለም አራጌ እና ጋዜጠኛ እስንክንድር ነጋን ጨምሮ በርካታ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፣ ጋዜጠኞች፣ ብሎገሮችና አክቲቪስቶች በእስር ላይ ይገኛሉ፡፡
የተቃዋሚ ፓርቲዎች አመራሮች የእምነት ክህደት ቃላቸውን ‘ሰጡ’
“ኢትዮጵያ ውስጥ ብቸኛው አሸባሪ ህወሓት/ኢህአዴግ ነው” አብርሃ ደስታ
“የጦር ችሎት በሚመስል ችሎት እየተንገላታን ነው” የሺዋስ አሰፋ
በዘለዓለም ወርቅአገኘሁ የክስ መዝገብ የሽብር ክስ የተመሰረተባቸው የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችና ሌሎች በተመሳሳይ መዝገቡ የተካተቱ ተከሳሾች በተከሰሱበት ድርጊት ላይ የእምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጡ፡፡
የሰማያዊ፣ የአንድነት እና የዓረና ትግራይ ፓርቲ አመራሮችን ጨምሮ 10 ተከሳሾች መጋቢት 10 ቀን 2007 ዓ.ም በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ 19ኛ ወንጀል ችሎት የቀረቡ ሲሆን ተከሳሾች በቀረበባቸው ክስ ላይ የእምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡ በዚህ መሰረት ከአንደኛ ተከሳሽ ዘላለም ወርቃገኘሁ ጀምሮ፣ “በክሱ ላይ የተመለከተውን ድርጊት ፈጽመዋል ወይስ አልፈጸሙም?” የሚል ተመሳሳይ ጥያቄ ለእያንዳንዳቸው የቀረበላቸው ሲሆን ብዙዎቹ ተከሳሾች ምላሻቸውን በቀጥታ ለመስጠት አለመፈለጋቸውን አሳይተዋል፡፡
1ኛ ተከሳሽ ዘላለም ወርቃገኘሁ ለቀረበለት ጥያቄ፣ “በአቃቤ ህግ እና በፖሊስ ተቀነባብሮ የቀረበብኝን ክስ በተመለከተ ለክሱ እውቅና ላለመስጠት ምንም አልልም፡፡ በክሱ ላይ አስተያየት በመስጠት ለጸረ-ሽብር አዋጁ እውቅና መስጠት አልፈልግም” የሚል መልስ በመስጠቱ ፍርድ ቤቱ ክሱን ክዶ ቃል እንደሰጠ አድርጎ መዝግቦታል፡፡
2ኛ ተከሳሽ ሀብታሙ አያሌው በበኩሉ “በክሱ ላይ የተመለከተውን ድርጊት እንዳልፈጸምኩ እንኳን እኔ ከሳሾቼም በደንብ ያውቃሉ፡፡ ከሳሾቼ እኔ ድርጊቱን የመፈፀም ፍላጎቱም ሀሳቡም እንደሌለኝ ያውቃሉ” ብሏል፡፡
3ኛ ተከሳሽ ዳንኤል ሺበሽ ደግሞ፣ “እኔ ስለ ሽብር የሰማሁት ከአልቃይዳው መሪ ኦሳማ ቢላደን እና መለስ ዜናዊ ነው፡፡ እኔ አሸባሪ አይደለሁም፤ ሀሳቡም ሆነ ፍላጎቱም የለኝም፡፡ ባህሌና እምነቴም አይፈቅድልኝም” ሲል ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡
4ኛ ተከሳሽ አብርሃ ደስታ “አሸባሪ ማለት የፖለቲካም ሆነ ሌላ ዓላማውን ሰላማዊ ዜጎችን በማሸበር ለማስፈፀም የሚሰራ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ብቸኛው አሸባሪ ድርጅት ህወሓት/ኢህአዴግ ነው፡፡ እኔ ደግሞ የዚህ አሸባሪ ድርጅት ተቃዋሚ ነኝ” ብሏል፡፡
5ኛ ተከሳሽ የሺዋስ አሰፋ በበኩሉ፣ “በመጀመሪያ ለመጨረሻ ጊዜ ስለሆነ የምናገረው እንዳታቋርጡኝ አደራ እላለሁ፡፡ ክሱ ቅንብር ነው፡፡ ዳኞችም ህጉ የሰጣቸው ነጻነት አይታይባቸውም፡፡ ይህ 19ኛ ወንጀል ችሎት የጦር ችሎት ነው የሚመስለኝ፡፡ ስለሆነም የጦር ችሎት በሚመስል ችሎት እየተንገላታን ነው” ሲል ተናግሯል፡፡ የሺዋስ በዳኞች በተደጋጋሚ ንግግሩ እንዲቅረጥ ተደርጓል፡፡ በመጨረሻም ክሱን ክዶ ቃል ሰጥቷል በሚል ተመዝገቦለታል፡፡
6ኛ ተከሳሽ ዮናታን ወልዴ፣ “የተዘጋጀብኝን ክስ ያለፍቃዴ እንድተውን እየተገደድኩ ነው” ብሏል፡፡
7ኛ ተከሳሽ አብርሃም ሰለሞን ደግሞ፣ “የተቀነባበረ ክስ ላይ ምንም ማለት አይቻልም” ብሏል፡፡
8ኛ ተከሳሽ ሰለሞን ግርማ፣ “ነፃ ሰው ነኝ፡፡”
9ኛ ተከሳሽ ባህሩ ደጉ “ባህሉንና ፈጣሪውን ከሚያከብር ማህበረሰብ ወጥቼ አሸባሪ ልሆን አልችልም” ሲል አስረድቷል፡፡
10ኛ ተከሳሽ ተስፋዬ ተፈሪ ደግሞ፣ “ድርጊቱን አልፈጸምኩም” ብሏል፡፡
በአጠቃላይ ተከሳሾች ክሱ ላይ የተጠቀሰውን ድርጊት ክደው ቃል በመስጠታቸው አቃቤ ህግ ምስክሮችን እንዲያሰማ ለግንቦት 13፣ 14፣ 15 ቀን 2007 ዓ.ም ለተከታታይ 3 ቀናት ምስክር እንዲሰማ ቀጠሮ መሰጠቱን የነገረ ኢትዮጵያ ዘገባ አመልክታል፡፡
የአንድነት ፓርቲ “ቀብር” ላይ እንገናኝ፤ መቃብሩ ላይም እርም እናዉጣና የአንድነት ሃይሎች ዳብረን እንወጣ ዘንድ ትግሉ ግድ ይለናል!
በአብዛኛዎቻችን ኢትዮጵያዉያን አንድ ጥሩ ባህል አለን፡፡የምንወደዉንና የሚመቻንን ሰዉ በሞት ስናጣ እርም የማዉጣት ባህል፤ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ሆኖ አገኘሁት፡፡ሠዉና የፖለቲካ ድርጅ ባይገናኙም በጉልበተኛ ሃይል እንዲገናኙ ሲደረግ ከማገናኘት ዉጪ ምርጫ የለንምና እናገናኛቸዋልን፡፡
አቅምና ሁኔታዎች በፈቀዱት መጠን የወቅቱን ያገራችን ችግር በመፍታት በኩል የራሱን አስተዋፅኦ እንደሚያበረክት፤ የኢህአዴግ ሰዎችን ጨምሮ ያብዛኛዉ ተራማጅ ኢትዮጵያዊ ቤት እንዲሆን አድርገን ስንገነባዉ(ሲፈጥሩትም ለዚህ ኣላማ ነበር ተብሎ ይታመናል) የነበረዉን አንድነት ፓርቲን በፖለቲካዊ ዉሳኔ የሆነዉ እንዲደርስበት ተደርጓል፡፡አማራጭ እንዲኖር የማይፈልጉት በከፍተኛ የመንግስት ሃላፊነት የተመደቡቱ ጥቂት የህወሓት ቡድኖች የማይጠቅማቸዉን ዉሳኔ እንደወሰኑ ይታወቃል፡፡ ተዉኔቱ በማን ተዘጋጅቶ እነማን እንደተጫወቱትና እነማን ደግሞ ለህዝቡ እንዳደረሱት በተደጋጋሚ ገልጸነዋል፡፡
ፓርቲዉን በተለያዩ ስሞች ሲከሱና ሲፈርጁ ቆይተዉ አመራሩንም በእስርና ድብደባ እያሹ እንዳልተንበረከከና ይበልጥ መጠናከሩን ሲያረጋግጡ ለዚህ ዉሳኔ በቅተዋል፡፡ በ40 ዓመታት ታሪኩ ፓርቲዎችን በመብላትና ከዉስጥና ከዉጭ የሚነሳ ልዩነትን በማቻቻል ሳይሆን በማጥፋት የሚታቀወቀዉ ጥቂት የህወሓት ቡድን አንድነት ፓርቲን ከማጥፋት አሁን ወደ መረጠዉ ደረጃ እንዲወርድ አድርጓል፡፡ታሪክ ሁሉን ይፈርዳል፡፡በጨለማዉ ዘመን ግፍ የተፈፀሞባቸዉ ቡድኖችና የፈሰሰዉ ደምም ተደብቆ ኣልቀረም፡፡ፖለቲካችንን ለማዘመንና ያለፈዉ ግፍ ሁሉ ባይረሳም በይቅር መታለፍ አለበት ብለን ለተነሳን ሃይሎችም እድሉን (በጉልበት በህዝብ ሃብትና በያዙት ስልጣን ተጠቅመዉ) ዘግተዉብናል፡፡ በደም መጨማለቅ በዚህ ያበቃ ዘንድ አሁንም እንታገላለን፡፡የፖለቲካ ትግሉ ሂደትም አይቆምም፡፡ያዉም ይብልጥ የመጠናከር እድል አግኝቷል ተብሎ ይታመናል፡፡የሚያቆመዉ ሃይል የለም፤መጪዉ ግዜ የለዉጥ ነዉ፡፡ለዉጡ እንደይሰረቅና ለሁሉም ይመች ዘንድ የጋራ ትስስርን እንደሚጠይቅ እሙን ነዉ፡፡
ለግዜዉ ከጀርባ ያለዉን ፖለቲካዊ ግፊት ለሌላ ፖለቲካዊ ትግል ትተን የምርጫ ቦርድ ዉሳኔን በመቃወም ክስ መስርተን ወደ ፍርድ ቤት ተብየዉ ወስደንዋል፡፡ ወደ ህግ ለመዉሰድ ስንወስን የፓርቲ ስምና አርማ አስጨንቆን አይደለም፡፡ የደጋፊዎችና አባላት ንብረት ለይምሰልም ቢሆን ያለፍርድ ቤት ትእዛዝ ፖለቲካዊ ዉሳኔ እንግበዉ በመጡ ከህዝብ ግብር በተሰበሰበ ደሞዝ የሚተዳደሩ የክፍለ ከተማ ፖሊስ ሃይሎች ( ህዝባዊ ሃለፊነትን የተሸከመ ተቋም በፖለቲካ እዝና ዉሳኔ የፓርቲን ንብረት ይዘርፋል የሚል እምነት አልነበረንም) ስለተዘረፈብን ሃላፊነታችንን ለመወጣትና ታሪካዊ እልባት እንዲኖረዉ ለማስቻል ነዉ፡፡እንጂማ ራእያችን በእያነዳንዳችን ዉስጥ ቢሆንም የወቅቱ ትግል ግን የነፃነት መሆኑን አጥተነዉ አይደለም፡፡
በወቅቱ የብሔራዊ ስራ አስፈፃሚዉ የወሰነዉ ዉሰኔ የመድብለ ፓርቲ ስርኣቱ ከምን ግዜዉም በላይ ፈተና ላይ መዉደቁና አዲስ ፓርቲ መመስረት ችኮላና ህዝቡን ስርአቱ ለመድብለ ፓርቲ አሁንም ይመቻል፤ጥፋቱ የኛ ነዉ ብሎ መዋሸት መሆኑ፤እስኪያጠፋቸዉ ድረስ ሌሎች ፓርቲዎች ጋ መቀላቀል በተላይም ከምርጫዉ እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ ተስፋ ያላቸዉ አባላት የግል ምርጫቸዉ መሆኑንና አመራሩም ይህን እንደማይቃወም፤የፓርቲዉ አባላት ጉዳዩ በፍ/ቤት እስኪቋጭ ድረስ አመራሩን እንዲጠብቁ ይሀም ለብሔራዊ ምክር ቤቱ ከሰዓት እንዲቀርብና ተወያይቶ ዉሰኔ እንዲሰጥበት የተስማማ ሲሆን በወቅቱ ሁለት አባላት ብቻ አልተገኙም፡፡ከሰኣት ቢሮዉ የፖሊስ ደንብ በለበሱ የመንግስት አካላት ተዘረፈ፡፡ይህ ደግሞ አእላፍ ወንድሞቻችን ላለፉት 40-50 አመታት በተለያየ ጉራ ተሰልፈዉ በተሰዉለት በተላይም በትግረዋይ ደም/ የትግል ዉጢት ሌላዉ ቀልድ እንደመሆኑ ጉዳዩ አብዛሃዉ የአንድነት ደጋፊና አባል በመሆኑ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት እንወስደዋለን ባልነዉ መሰረትእየታየ ይገኛል፡፡በመሆኑም ጉዳዩን መከታተል የእያነዳንዱ የአንድነት አባልና ደጋፊ የህሊና እዳ ይመስለኛል፡፡በአንድነት ቀብር ላይ አሁንም አንድነታችንን በማረጋገጥ ባብዛሃ ዉሳኔ ቀጣዩን መንድ መጓዝ እንጂ ልንለያይ የሚጋብዝን መንገድ መከተል ያለብን አይምስለኝም፡፡ካለፉት የተቃዉሞ ጎራ በጎዉን ትምህርት መቅሰም የሚኖርብን እንዳለ ይሰማኛል፡፡በችኮላ ፓርቲ ለመመስረት የሚደረግ ሩጫ የስልጣን ሀይልነትን ከማረጋገጥ ባለፈ ለህዝባችን ፋይዳ አለዉ ብየ አልገምትም፡፡ ምርጫቸዉ ላደረጉት ጓዶቼ ግን ስህተት ቢሆን ምርጫቸዉን አከብራለሁ፡፡
ጉዳያችንን ወደ ፍርድ ቤት ስንወስደዉ በፍትህ ተቋማቱ ምናልባትም በሰላማዊ ትግል ስልት ስርኣቱን ለመለወጥ ከሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች መካከል ከቀድሞዉ ቅንጅት ቀጥሎ የግፍ ፍርድ ሲበየንበት የነበረዉ ፓርቲ አንድነት እንደሆነ ስተነዉም አይደለም፡፡ ዱባና ቅል አበቃቀሉ ለየቅል የሚለዉ ብሂል እንዳለ ሆኖ ብርቱኳን መደቅሳ፤ዳኛ ፍረህይወት እና ሌሎች (ለህሊናቸዉ የተገዙ ዳኞች አልፎ አልፎም ቢሆን) የተገኙት በዚህ አፋኝ ስርኣት በዘረጋዉ መዋቅርና በህዝባችን ዘንድ እምነት በታጣባቸዉት የፍትህ ተቀዋማት ውስጥ ነዉ፡፡ታድያ እየተፈተኑ የሚወድቁትን ተቋማት ሳይሆን ግለሰብ ዳኞችንም ለመፈተን ይህን ታሪካዊ ክስ ስናቀርብ የግለሰቦችን የህሊና ዳኝነትንም ተስፋ ባለመቁረጥ ጭምር ይሆናል፡፡ ሁሌም እንደምንለዉ ፓርላማ ተቀምጦ የተከበሩ እየተባሉ ለመጠራት ሳይሆን ትግላችን ለለዉጥ ነዉና ድንክየዉን አንድነት ቢመለሱልንም ባይመሉሱልንም፤ የህዝብ ከሆነዉ ትግል መሃል ሆነን ፖለቲካዉን ከመስራት አንታቀብም፡፡ዉሳኔዉም በሁሉም የለዉጥ ሃይሎች ቀጣይ እንቅስቃሴ የራሱ የሆነ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡የአንድነት ልጆች ህወሓት ለመደዉ የጥባጥቤ ጨዋታዉ ቦታ ይኖረናል ተብሎ አይታሰብም፡፡አንድነታቸንን እንደ ጠበቅን የሚቀብሩት ከሆነ የአንድነት ፓርቲ “ቀብር” ላይ እንገናኝ፤ መቃብሩ ላይም እርም እናዉጣና የአንድነት ሃይሎች ዳብረን እንወጣ ዘንድ ትግሉ ግድ ይለናል!
ላለፉት አምስት አመታት ብዙዎቹ በእስር የሚማቅቁበት የተሰደዱለትና የቆሰሉ፤ የደሙለት ፓርቲ አንድነት ነዉ፡፡የብዙ ወገኖችን እና ተቋማትን የፍትህ ጥያቄ በማዉሳት ባደባባይ የጮኸዉ ፓርቲ አንድነት ነዉ፡፡በኢትዮጵያዊነት ማእቀፍ ዉስጥ የብሄረሰቦችን እና የቡድኖችን መሰረታዊ የፖለቲካ ጥያቄ ለመመለስ ቁርጠኝነት የነበረዉ ፓርቲ አንድነት ነዉ፡፡ የህዝብን ጥያቄዎች በጠራ መልኩ በማዉሳት ድምጻቸዉን ከሚያሰሙ ፓርቲዎች ዉስጥ ተጠቃሹ ፓርቲ አንድነት ነዉ፡፡የቅርርብ፤የመደማመጥና የመከባበር ፖለቲካ እንዲኖር ባሳለፋቸዉ አጭር አመታት ጥረት ያደረገ ፓርቲ አንድነት ነዉ፡፡ በዚህም ከህዝብ ብቻ ሳይሆን ለሃገራቸዉ በጎዉን ለዉጥ የሚሹ በርካታ የኢህኣዴግ ተራ አባላትና አንድንድ ባለስልጣናትም ጭምር በበጎ አይን ይመለከቱት እንደነበር ገምግመናል፡፡ በዚህ ወቅት አወንታዊ ተፅእኖ ያመጣል ተብሎ በመፈራቱ ግን ከ40 አመት በኃላም ትቂቱ የህወሓት ቡድን በለመደዉ ስልቱ በልቶታል፡፡
ይህን ድርጊት ለዉጥ ፈላጊ ሃይሎች በጥሞና ይከታተሉታል ተብሎ ይገመታል፡፡የምትችሉ ሁሉ ፍርድ ቤት በመገኘት እስከ ታሪካዊዉ ዉሳኔ እለት ድረስ ሂደቱን ለመዘገብና ለታሪክ ምስክር ለመሆን፤ እንዲሁም አጋርነታችሁን ለመግለፅ ትገኙ ዘንድ የክብር ጥሪ ተላልፏል፡፡እዉነተኛ አንድነት ነባር አመራር፤አባለትና ደጋፊዎች ጉዳዩን በአንድነት እንቋጭኛ እንደስማቸን በአንድነት ቦይ እንፈስ ዘንድ ጥሪ አቀርባለሁ፡፡
አቶ ተክሌ በቀለ (የአንድነት ፓርቲ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዘዳንት)
ጠበቃ ተማም አባቡልጉ ድብደባ ተፈፀመባቸው
በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት በዘለዓለም ወርቃገኘው የክስ መዝገብ የተከሰሱት የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጉዳይ በመያዝ የሕግ አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙት ጠበቃ ተማም አባቡልጉ ድብደባ ተፈፀመባቸው፡፡ ድብደባው የተፈፀመባቸው ዛሬ መጋቢት 1 ቀን 2007 ዓ..ም. እነ አብርሃ ደስታ በነበራቸው የፍርደ ቤት ቀጠሮ ተገኝተው የሚጠበቅባቸውን የሕግ አገልግሎት ሰጥተው ከፍርደ ቤት ከወጡ በኋላ ብሔራዊ አረቄ ፋብሪካ አካባቢ ወደ አዋሳ ለሌላ የህግ አገልግሎት ለመስጠት እያመሩ በነበረበት ወቅት በማያውቁት ግለሰብ ድብደባ እንደተፈፀመባቸው ከስፍራው የደረሰን መረጃ አመልክታል፡፡
ደብዳቢው ግለሰቡ ድብደባ ከፈፀመ በኋላ እሮጦ ለማምለጥ ሲሞክር በአካባቢው በነበሩ ሰዎች ትብብር የተያዘ ሲሆን፤ በወቅቱም ደብዳቢው የአእምሮ ችግር እንዳለበት ለመምሰል ከሞከረ በኋላ የብአዴን-ኢህአዴግ አባል እንደሆነና 400 ብርም እንደተከፈለው መናገሩን እንዲሁም አዲስ አበባ ለቡ አካባቢ 105 ካሬ ሜትር ቦታ ተሰጥቶት ቤት እየሰራ እንደሆነ መግለፁን በስፍራው የነበሩ የዓይን እማኞች ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ ጠበቃ ተማም ነገ አዋሳ ላይ ሌላ የነ ጋዜጠኛ ጌታቸው ወርቁ የፍርድ ቤት ጉዳይ ስላለ ዛሬ የግድ ሄደው ማደር ስለነበረባቸው ደብዳቢውን እንዲለቀቅ አድርገው ወደ አዋሳ ማምራታቸው ታውቋል፡፡
ጠበቃ ተማም ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጉዳይ በተጨማሪ የሙስሊም መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴዎችን፣ የተለያዩ ጋዜጠኞችን፣በሀገር ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ ተቋማትን እና ሌሎች በርካታ የህግ ነክ ጉዳዮችን በተመለከተ ለማኀበረሰቡ አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡ ከጥብቅና አገልግሎት በተጨማሪ በተለያዩ ጋዜጦች የህግ ነክ ጉዳዮችን በተመለከተ ይፅፉ እንደነበር አይዘነጋም፡፡ በዚህም ከመንግሥትና ከስርዓቱ ደጋፊዎች ከፍተኛ ጫና እየተደረገባቸው እንደሆነ ይታወቃል፡፡




