Tag Archives: TPLF/EPRDF Ethiopia

በጎንደር የሰላማዊ ሰው ግድያ የቀጠለ ሲሆን፤ በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ህዝባዊ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ ተጠርቷል

(አዲስ ሚዲያ) ዛሬ ነሐሴ 14 ቀን 2008 ዓ.ም. በአማራ ክልል ጎንደር ከተማ መንግሥት ሰላማዊ ዜጎችን ተኩሶ 1 ወጣት መግደሉን ተከትሎ ዳግም ህዝባዊ ተቃውሞ ተቀስቅሷል፡፡ በሌላ የከተማዋ አካባቢም በተመሳሳይ መልኩ በመንግሥት በተወሰደ ወታደራዊ የኃይል ርምጃ የቆሰሉ እንዳሉም ተጠቁሟል፡፡ እንደ መብት አራማጆች ከሆነ፤ ነጭ ለብሰው በመንቀሳቀሳቸው ብቻ ዛሬ በጎንደር የተገደሉ ዜጎች ቁጥር 4 ደርሷል፡፡ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ድረስ ከተገደለው አንድ ሰላማዊ ዜጋ በስተቀር ሌሎች ጉዳቶችን ማረጋገጥ አልተቻለም፡፡

የዓይን እማኞች እንደተናገሩት፤ዛሬ ግድያው የተፈፀመው የጎንደር ህዝብ በመንግሥት ቀጥተኛ ትዕዛዝ በግፍ የተገደሉባቸውን ሰላማዊ ሰዎችን ለመዘከር ነጭ የመልበስ መርሃ ግብርን ተከትሎ ነጭ ለብሶ ሲንቀሳቀስ የነበረ ወጣት በድብደባ ሲገደል፣ ሌሎች 3 ሰላማዊ ዜጎች ደግሞ ከወታደሮች በተተኮሰ ጥይት ተገድለዋል፡፡ ይህንንም ተከትሎ ጋብ ብሎ የነበረው የጎንደር ህዝባዊ ተቃውሞ ዳግም ተቀስቅሷል፡፡
ህዝቡም ዛሬ  በግፍ የተገደለ ወጣት አስከሬን በአደባባይ ይዞ በመዞር ተቃውሞውን እያሰማ ይገኛል፡፡ ጎንደር ባለፈው ሳምንት እሁድ ጀምሮ ለ3 ቀናት ከቤት ያለመውጣት ተቃውሞ ማድረጉ አይዘነጋም፡፡

Gonder Amhara Protest

በከተማው ከሐምሌ 5 ቀን 2008 ዓ.ም. የወልቃይት የአማራ ማንነት መብት ጥያቄን ተከትሎ መንግሥት አስተባባሪ የኮሚቴ አባለት ላይ የወሰደውን የኃይል ርምጃ ተከትሎ በነበሩት የፀረ አገዛዝ የህዝባዊ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፎች በመቀጠላቸው ስጋት የገባው መንግሥት፤ በርካታ የታጠቁ መከላከያ፣ ፌደራል ፖሊስ እና የፌደራል ልዩ የፀጥታ ኃይሎችን በከተማው ማስፈሩ ይታወቃል፡፡
በተያያዘ ዜና፤ በኦሮሚያ እስካሁንም ድረስ የቀጠለውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ ትናንት ነሐሴ 13 ቀን 2008 ዓ.ም. በምዕራብ ወለጋ ደንቢዶሎ አንድ ሰላማዊ ወጣት በመንግሽት አልሞ ተኳሾች መገደሉ የታወቀ ሲሆን፤ በምስራቅ ሷ ዝዋይ ከተማ እቤቱ የነበረ አንድስ ሰላማዊ ዘጋም በመንግሥት የፀጥታ ኃይል ወታደራዊ ርምጃ መገደሉ ታውቋል፡፡

ለነገ ጠዋት በአዲስ አበባ መዳረሻውን መስቀል አደባባይ ያደረገና ሁሉም ኢትዮጵያዊ የተጋበዘበት ህዝባዊ ታላቅ  የተቃውሞ ሰልፍ ተጠርቷል፡፡የተቃውሞ ሰልፉ ዋነኛ ዓላማ፤ መንግሥት በሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚወስደውን ግድያ ህዝቡ በተለይም በኦሮሚያና በአማራ ክልል ተቃውሞው የቀጠለ ሲሆን፤ መንግሥት በኦሮሚያ እና አማራ ክልል ሰላማዊ ዜጎች ላይ እየፈፀመ ያለውን ግድያና የፀረ አገዛዝ ተቃውሞ፤ ነገ እሁድ ጠዋት ነሐሴ 15 ቀን 2008 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ታላቅ  የተባለለት የተቃውሞ ሰልፍ መዘጋጀቱን የተቃውሞ አስተባባሪዎችና የመብት አራማጆች አስታውቀዋል፡፡

ኢትዮጵያውያን በሀገር ቤት እየጠፈፀመ ያለውን የመንግሥት ግድያ፣ እስራትና አገዛዝ ድርጊትን በመቃወም በተለያዩ የአሜሪካ፣ አውሮፓ እና አፍሪካ ሀገሮችና ከተሞች ህዝባዊ ተቃውሞ እያደረጉ እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል፡፡

መንግሥት ሰላማዊ ዜጎችን በአደባባይ መግደሉ እንዳሳሰበው በመጠቆም ምርመራ ማድረግ እንደሚፈልግ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ቢያስታውቅም አገዛዙ የመንግሥታቱ ድርጅትን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ምርመራን እንደማይቀበልና ከላከው ምላሽ ማረጋገጥ ተችሏል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ ጉዳዩ ያሳሰባቸው የአሜሪካና የተለያዩ የአውሮፓ ሀገራት መንግሥት እየፈፀመ ያለውን ግድያ በማውገዝ ጉዳዩን በጥብቅ እየተከታተሉት እንደሆነ ማስታወቃቸው ይታወሳል፡፡

ከህዳር 22 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ የህወሓት/ኢህአዴግ መንግሥት በወሰደውና እየወሰደ ባለው ወታደራዊ የኃይል ርምጃ በኦሮሚያ ክልል በነበሩት ህዝባዊ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፎች ላይ ከ500 በላይ ሰላማዊ ዜጎች ሲገደሉ፤ ሁለተኛ ወሩን ባስቆጠረው የአማራ ክልል ህዝባዊ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ ደግሞ ከ100 በላይ ሰላማዊ ዜጎች መገደላቸው ታውቋል፡፡

ተጠየቅ ህወሓት፣ኢህአዴግ እና ብሔራዊ ባንክ፤ በትግራይ ወርቅ ጉዳይ ”በጠራራ ጸሀይ አገር ሲዘረፍ”

አቻምየለህ ታምሩ

በያዝነው የፈረንጆች ዓመት በወርሀ ጥር የወያኔ ካድሬዎችና የአገዛዙ የፕሮፓጋንዳ ተቋማት የሆኑት እነ ኤ.ቢ.ሲ.፣ ዋልታ፣ ፋና፣ ኤ.ዜ.አ. ወዘተ ትግራይ በታሪኳ ስላሉት የወርቅ ምርት መጠን በስፋት ዘግበው ነበር። የአገዛዙ ልሳን ኢ.ቢ.ሲ. እ.አ.አ. ጥር 07 ቀን 2016 ዓ.ም. ባቀረበው ርዕሰ አንቀጽ፤ ዋልታ እ.አ.አ. ጥር 09 ቀን 2016 ዓ.ም. ባስደመጠም የዜና እወጃ ፤ ኤ.ዚ.አ. ጥር 16 ቀን 2016 ዓ.ም. ባስነበበን ሪፖርት ትግራይ እ.ኤ.አ. ከሐምሌ 2012 ዓ.ም. እስከ ታህሳስ 2016 ዓ.ም. ድረስ 597.7 ቶን ወርቅ [በባህላዊ መንገድ] እንዳመረተችና ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እንዳቀረበች ነግረውናል።

EBC Tigray goldFanaBC Tigray gold news

ይህንን «ልማታዊ ዜና» የሰሙ ብዙ ሰዎች «ትግራይ ከየት አምጥታ ነው ይህንን ያህል ወርቅ አምርታ ለብሔራዊ ባንክ የምታቀርበው?» በማለት ከቁጥሩ ጀርባ ያለውን የምጣኔ ሀብት ትርጉም ሳያጤኑ አጣጥለውት አልፈዋል። ሆኖም ግን ከቁጥሩ ጀርባ ወያኔ ትልቅ አገራዊ ዘረፋና ወንጀል ፈጽሟል። ወያኔ በቁጥሩ ቁማር ተጫውቶ የኢትዮጵያን የሁለት አመት ባጀት ያህል ብሔራዊ ሃብት በአንድ ግብይት ብቻ ወደ ትግራይ አሸሽቷል ወይንም አሻግሯል። ነገሩ እንዲህ ነው።

እ.ኤ.አ.ከሐምሌ 2012 ዓ.ም. እስከ ታህሳስ 2016 ዓ.ም. ድረስ 597.7 ቶን ወርቅ ከትግራይ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ቀረበ ማለት በ42 ወር ውስጥ 597.7 ቶን ወርቅ ከትግራይ ለብሔራዊ ባንክ ቀረበ ማለት ነው። ይህ ማለት ትግራይ በአመት በአማካኝ 171 ቶን ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ አቅርባ ነበር ማለት ነው። በኢትዮጵያ የንግድ ህግ መሰረት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ብቸኛው ወርቅ ገዢና አስቀሟጭ ተቋም ነው። ክልሎች በየክልሎ የተመረተውን ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ ሲያቀርቡ ብሔራዊ ባንክ ክልሎች ላቀረቡት የወርቅ መጠን ክፍያ ይፈጽማል። ለምሳሌ ትግራይ 597.7 ቶን ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሲታቀርብ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለትግራይ ክልል የ597.7 ቶን ወርቅ ክፍያ በገንዘብ ይፈጽማል። ያልቀረበ ወርቅ ሪፖርት ተደርጎ ብሔራዊ ባንክ ላልቀረበ ወርቅ እንደቀረበ ተደርጎ ክፍያ ቢፈጽም ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ የሀብት transfter ይኖራል ማለት ነው።

Walta Tigray gold news

ወያኔ የነገረን ትግራይ ለብሔራዊ ባንክ ያቀረበችው 597.7 ቶን ወርቅ ማለት
597, 700 ኪሎ ግራም ወርቅ ማለት ነው።ይህ ማለት ደግሞ 19,216,473 ወቄት ወርቅ ማለት ነው። ከሐምሌ 2012 ዓ.ም. እስከ ታህሳስ 2016 ዓ.ም. ድረስ በነበሩት አመታት ውስጥ አማካኝ የአንድ ወቄት ወርቅ ዋጋ 1,100 የአሜሪካን ዶላር ነው። ይህ ማለት ትግራይ አቀረበችው የተባለው 597.7 ቶን ወርቅ ዋጋ 21. 376 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ይሆናል ማለት ነው።
ይህ ማለት [በወያኔ ዜና መሰረት] ትግራይ ከሐምሌ 2012 ዓ.ም. እስከ ታህሳስ 2016 ዓ.ም. ድረስ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ላቀረበችው 597.7 ቶን ወርቅ ብሔራዊ ባንክ 21. 376 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ከፍሏታል ማለት ነው። የኢትዮጵያ ያለፈው አመት ባጀት አስር ቢሊዮን ዶላር ነው። ይህ ማለት ከሐምሌ 2012 ዓ.ም. እስከ ታህሳስ 2016 ዓ.ም. ድረስ ትግራይ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አቀረበችው ለተባለው 597.7 ቶን ወርቅ የተከፈላት 21. 376 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ከኢትዮጵያ የሁለት አመት በጀት በላይ ነው ማለት ነው።

ዋናውና ቁልፉ ጥያቄ እውነት ትግራይ ከሐምሌ 2012 ዓ.ም. እስከ ታህሳስ 2016 ዓ.ም. ድረስ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ 597.7 ቶን ወርቅ ወይንም ከሐምሌ 2012 ዓ.ም. እስከ ታህሳስ 2016 ዓ.ም. በየአመቱ 171 ቶን ወርቅ አቅርባለች ወይ? የሚለው ነው።
ይህንን ጥያቄ ለመመለስ የአለም አገሮችን የወርቅና የሌሎች ማዕድናትን አመታዊ ምርት ማስረጃ የሚሰበስበውንና የሚያደራጀውን የUnited States Geological Survey (USGS) Minerals Resources Program አመታዊ የአለም ማዕድናት ምርት ሰንጠረዥን ማየት በቂ ነው። ይህ የአሜሪካ ተቋም በአለም ላይ ያሉ ማዕድን አምራች አገሮችን የማእድን አመታዊ ምርት አሃዝ ሰብስቦ ደረጃ ያወጣና የአለም አገሮችን በማዕድን ምርት ያወዳድራል። በዚህ መስሪያ ቤት ማስረጃ መሰረት ከሐምሌ 2012 ዓ.ም. እስከ ታህሳስ 2016 ዓ.ም. ድረስ በአለም ላይ በወርቅ ምርት አንደኛ ቻይና ስትሆን አመታዊ የወርቅ ምርት መጠኗ 403 ቶን ነው።

ሁለተኛዋ የአለም ወርቅ አምራች አገር ደግሞ አውስትራሊያ ስትሆን አመታዊ የምርት መጠኗ ደግሞ 250 ቶን ወርቅ ነው። ሶስተኛ አሜሪካ [235 ቶን ወርቅ በአመት] ፤አራተኛ ሩስያ ፌድሬሽን [217.8 ቶን ወርቅ በአመት] ፤ አምስተኛ ፔሩ [161 ቶን ወርቅ በአመት] ፤ስድስተኛ ደቡብ አፍሪካ [160 ቶን ወርቅ በአመት]፤ ሰባተኛ ካናዳ [103 ቶን ወርቅ በአመት] ፤ ስምንተኛ ሜክሲኮ [96.7 ቶን ወርቅ በአመት] ፤ ዘጠነኛ ኢዝቤኪስታን [ 93 ቶን ወርቅ በአመት] እና ጋና [86.5 ቶን ወርቅ በአመት] በአለም ላይ አስሩ ከፍተኛ ወርቅ አምራች አገሮች ናቸው። የዚህ ምንጭ የሚከተለውን ትር መክፈትና መመልከት ይቻላል… http://www.indexmundi.com/minerals/…።

ወያኔ ኢትዮጵያ ትግራይ ብቻ ከሐምሌ 2012 ዓ.ም. እስከ ታህሳስ 2016 ዓ.ም. ድረስ በየአመቱ 171 ቶን ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ አቅርባለች ያለው እውነት ቢሆን ኖሮ ኢትዮጵያ በወርቅ ምርት በአለም ደረጃ ፔሩን ቀድማ ሩስያን ተከትላ አምስተኛ ደረጃ ላይ ትሆን ነበር። ልብ በሉ ከአንድ እስከ አስር የወጡ አገሮች ሁሉ ወርቅ የሚቆፍሩት በጣም ዘመናዊ በሆነ መሰርሰሪያ ማሽን ነው። ወያኔ ግን ትግራይ በየ አመቱ 171 ቶን ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ አቅርባለች የሚለን በባህላዊ መንገድ አምርታ ነው።

ከፍ ብዬ በለጠፍሁት የUnited States Geological Survey (USGS) Minerals Resources Program አመታዊ የወርቅ ምርት እውነተኛ ደረጃ መሰረት የኢትዮጵያ አመታዊ የወርቅ አምራችነት ደረጃ 29ኛ ሲሆን አመታዊ የወርቅ ምርቷ ደግሞ 12 ቶን ብቻ ነው። ልብ በሉ ይሄ አመታዊ የኢትዮጵያ የወርቅ ምርት ዶዶላ፣ መተከል፣ ለገደንቢና ወለጋ ሜድሮክ በዘመናዊ ቴክኖሎች ታግዞ የሚያመርተውን ይጨምራል። ወያኔ ግን የትግራይን አመታዊ ምርት ብቻ 171 ቶን ይለናል።

ሜድሮክ በዶዶላ፣ በመተከል፣ በለገደንቢና በወለጋ የሚያመርታቸውን ዜሮ አድርገን ኢትዮጵያ ያመረተችውን 12ቱን ቶን ወርቅ ከትግራይ ብቻ ለብሔራዊ ባንክ የቀረበ የወርቅ መጠን አድርገን ብንወስድ፤ ብሔራዊ ባንክ ከትግራይ በየአመቱ 171 ቶን ወርቅ እንደቀረበለት ተደርጎ ለትግራይ በጠቅላላ ከከፈለው 21.3 ቢሊዮን ዶላር ውስጥ ውስጥ በያመቱ ላልቀረበ 158 ቶን ወርቅ ክፍያ ፈጽሟል። ይህ ማለት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከትግራይ ቀረበ ተብሎ ከፍያ ከፈጸመበት 597.7 ቶን ወርቅ ውስጥ የተረከበው ወርቅ 42 ቶብ ብቻ ነው። የተቀረው 555.7 ቶን ወርቅ ወርቁ ከትግራይ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሳይቀርብ ብሄራዊ ባንክ ግን ለትግራይ ክፍያ የፈጸመበት የውሸት ቁጥር ነው። ይህ ማለት ብሔራዊ ባንክ ለትግራይ ከከፈለው 21.3 ቢሊዮን ዶላር ውስጥ ከ20 ቢሊዮን ዶላር በላይ ለትግራይ የተከፈለው ላልቀረበ የውሸት ወርቅ ነው። ይህ ማለት ወያኔ ያልቀረበ ወርቅን አስታኮ 20 ቢሊዮን ዶላር በላይ ያገር ሀብት ወደ ትግራይ wealth transfter አድርጓል። ይህ ማለት የሁለት አመት የኢትዮጵያ የሁለት አመት አመታዊ በጀት ትግራይ ለብሔራዊ ባንክ ወርቅ ባላቀረበችው ወርቅ ተሳቦ ተከፍሏታል። ይህ ማለት የሁለት አመታት የኢትዮጵያ አመታዊ ሀብት ወደ ትግራይ እንዲሄድ ዘረፋ ተፈጽሟል። This is a huge wealth transfter. ወያኔ ከጥር ወዲህም ማራኪ ቁጥር እያቀረበ የአገር ሀብት ወደ ተስፋዋ ምድሩ እያሸጋገረ ይገኛል።

የሚገርመው ትግራይ በየአመቱ 171 ቶን ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ አቀረበች በተባለ በወሩ የቀረበው ሌላ ዜና የስርዓቱ ዜና ነው። ፋና በየካቲት 11 ቀን 2008 ዓ.ም [እ.ኢ.አ.] ያቀረበው ዜና ርዕስ እንዲህ ይላል…«ለብሄራዊ ባንክ እየቀረበ ያለው ወርቅ በከፍተኛ ደረጃ እየቀነሰ ነው።» ዜናው በዚህ ብቻ አያበቃም። ከ2004 ዓ.ም. እስከ 2008 ዓ.ም.[እ.ኢ.አ.] በየአመቱ 171 ቶን ወርቅ ትግራይ ለብሔራዊ ባንክ አቀረበች እንዳልተባለ «ብሄራዊ ባንክ ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍል በባህላዊም ሆነ በዘመናዊ መልኩ ተመርቶ የሚቀርበለት ወርቅ በእጅጉ ቀንሷል። በ2005 ለባንኩ የቀረበለት 8.1 ቶን ወርቅ ነበር። በ2006 ዓ.ም ደግሞ 7.4 ቶን ሆነ፤ በ2007ም በጣም አሽቆልቁሎ 5.4 ቶንድረስ ወርዷል።» አሉን። ይህ ሁሉ የሚሆነው ከትግራይ ብቻ ለብሔራዊ ባንክ በአመት 171 ቶን ወርቅ ቀረበ ተብሎ 20 ቢሊዮን ዶላር እንደቀላል ወደ ትግራይ transfter እንዲሆን ባደረጉ በአንድ ወር ውስጥ ነው።
አይ አንቺ አገር! ማፍያዎች የውሸት ቁጥር እየቀቀሉ ሌላውን ጾም ደፍተፍና አራቁተው የድሆችን ሀብት ወደ መንደራቸው ያግዛሉ። በአንድ ማጭበርበር ብቻ ሀያ ቢሊዮን ዶላር የአገር ሀብት ወደ መንደራቸው አሸሹ! በቁጥር ሊሸውዱን ሲሞክሩ በትንተና እንዲህ ባጋለጥናቸው ጉዳይ ሀያ ቢሊዮን ዶላር በድብቅ ባልተወለደ አንጀታቸው ከገፈፉ ለሌላው ኢትዮጵያ ምን ያህል ያተርፉለት ይሆን?

የወልቃይት የአማራ ማንነት መብት ጥያቄ ተቃውሞ አድማሱን እያሰፋ ቀጥሏል

ትናንት ቅዳሜ ነሐሴ 7 ቀን 2008 ዓ.ም. በምስራቅ ጎጃም ደብረማርቆስ ከተማ እና ዛሬ እሁድ ነሐሴ 8 ቀን 2008 ዓ.ም. በሰሜን ወሎ መቄት ከተማ ህዝባዊ የፀረ አገዛዝ ተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፎች ተካሂደዋል፡፡ ህዝቡም በነበረው የተቃውሞ ህዝባዊ ሰላማዊ ሰልፍ ላይ ወልቃይት ጠገዴ የአማራ ነው፣ የወልቃይት የአማራ ማንነት መብት ጥያቄ መንግሥት ምላሽ እንዲሰጥ፣ ወልቃይት ጠገዴ ወደነበረበት አማር መመለስ አለበት፣ የህወሓት የበላይነት ይቁም፣ የታሰሩ የፖለቲካና የህሊና እስረኞች ይፈቱ፣ መብትን መጠየቅ አሸባሪነት አይደለም፣በኦሮሚያ የሚፈሰው ደም የእኛም ደም ነው፣ ፍትህ ለወገኖቻችን፣ ጭቆና በቃን፣…..የሚሉ መፈክሮች በስፋት ተደምጠዋል፡፡

Debre-MarkosAnit-gov-protest

የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፉ እንዳይደረግ መንግሥት ቀደም ሲል በደህንነቱ እና የፀጥታ ኃይሉ አማካኝነት ከፍተኛ ጥበቃና ማስፈራሪያ ቢያደርግም፤ በተለይ የደብረ ማርቆስ እና አካባቢው ነዋሪ መነሻውን ከከከተማዋ የተለያየ አካባቢ በማድረግ መዳረሻው ወደ ንጉስ ተክለኃይማኖት አደባባይ ሲያደርግ ተስተውሏል፡፡ ይሁን እንጂ መንግሥት የተቃውሞ ሰልፉ መዳረሻ ጋ ከመድረሱ በፊት በህዝቡ ላይ በወሰደው ወታደረዊ ርምጃ 4 ሰዎችን በፅኑ መቁሰላቸው ታውቋል፡፡ መንግሥት ሰልፉን ለመበተን በወሰደው የኃይል ርምጃ የተበሳጩ ሰዎች በሁለት የፀጥታ ኃይሉ ላይ የአፀፋ ርምጃ መውሰዳቸውን መረጃዎች አመልክተዋል፡፡

እሁድ ነሐሴ 8 ቀን በወሎ እና ሰሜን ሸዋ ከተሞች አጠቃላይ የአማራ ተጋድሎ ተቃውሞ ጥሪ መተላለፉን ተከትሎ በሰሜን ወሎ መቄት ከተማ ተመሳሳይ ህዝባዊ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ ተደርጓል፡፡ በሌሎች ከተሞችም በተለይ በደሴ፣ ወልዲያ፣ ከሚሴ፣ ኮምቦልቻ፣ ላሊበላ፣ ደብረ ብርሃን፣ ሸዋ ሮቢትን ጨምሮ በሌሎችም የወሎና ሴመን ሸዋ ከተሞች ተመሳሳይ የተቃውሞ ሰልፍ ጥሪ የነበረ ቢሆንም ፤መንግሥት በወሰደው ጥብቅ ወታደራዊ ቁጥጥርና አፈና ምክንያት ህዝቡ መውጣት እንዳልቻለ ተጠቁሟል፡፡ ህዝባዊ ተቃውሞውችን ከተክትሎም በአማራ ክልል ባሉ የተለያዩ ከተሞች በርካታ ወጣቶች ከቤታቸውና ከስራ ገበታቸው ላይ እየታፈኑ በመታሰር ላይ መሆናቸውን የአዲስ ሚዲያ ምንጮች አረጋግጠዋል፡፡

የተቃውሞ አድማሱን እያሰፋ የመጣው የአማራ ተጋድሎ ህዝባዊ ተቃውሞ ባለፈው ሐምሌ 5 ቀን 2008 ዓ.ም. መነሻውን በሰሜን ጎንደር ያደረገው የወልቃይት የአማራ ማንነት መብት ጥያቄ፣ ወደ ደቡብ ጎንደር ደብረ ታቦር እና ጋይንት ከዚያም ወደ ምዕራብ ጎጃምና የአማራ ክልል መዲና ወደሆነችው ባህርዳር ከተማ መደረጉ አይዘነጋም፡፡ ዘጠነኛ ወሩን ያስቆጠረው የኦሮሚያም ህዝባዊ የፀረ አገዛዝ ተቃውሞ በተለያዩ የክልሉ ከተሞች እንደቀጠለ ሲሆን፤ በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች እየጠወሰደ ባለው ወታደራዊ የኃይል ርምጃ የሚገደሉ፣ የሚቆስሉ እና የሚታሰሩ ዜጎች ቁጥርም እየጨመረ መሄዱ ታውቋል፡፡

እነ በቀለ ገርባ የእምነት ክህደት ቃላቸውን ለመስጠት ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ገለፁ

”ፍርድ ቤቱ ገለልተኛ ነው ብዬ ስለማላምን ቃሌን አልሰጥም” አቶ በቀለ ገርባ

Bekele Gerba

በፌደራል አቃቤ ህግ የሽብር ክስ የቀረበባቸው የኦፌኮ አመራሮችና አባላት በቀረበባቸው ክስ ላይ የእምነት ክህደት ቃላቸውን ለመስጠት ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ጉዳያቸውን ለሚያየው ችሎት ገልጸዋል፡፡
የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት ነሐሴ 5 ቀን 2008 ዓ.ም መዝገቡን የቀጠረው የተከሳሾችን የእምነት ክህደት ቃል ለመቀበል ሲሆን፣ ችሎቱ ተከሳሾችን አንድ በአንድ በስማቸው እየጠራ የቀረበባቸውን የወንጀል ድርጊት ስለመፈጸም አለመፈጸማቸው የእምነት ክህደት ቃላቸውን እንዲሰጡት ጠይቋል፡፡

1ኛ ተከሳሽ አቶ ጉርሜሳ አያኖ የቀረበባቸውን ክስ የወንጀል ድርጊት ፈጽመዋል ወይስ አልፈጸሙም ተብለው ሲጠየቁ፣ ‹‹ይሄ ክስ ለእኔ ግልጽ አይደለም፡፡ በመቃወሚያ ላይ ይህን ገልጫለሁ፡፡ እኔ በሰላማዊና በህጋዊ መንገድ የሚታገል ፓርቲ አባል ሆኜ ስታገል የኦነግ አባል ሆነሃል ተብዬ መከሰስ የለብኝም፡፡ ይህ የምታገልለትን ህዝብ እንደመወንጀል ይቆጠራል፡፡ የኦሮሞ ህዝብ አሸባሪ ከተባለ እኔም አሸባሪ ነኝ፡፡ ይህ በደል ነው፡፡ ስለዚህ እኔ እዚህ ቆሜ ቃሌን መስጠት አያስፈልገኝም›› በማለት ተናግረዋል፡፡

2ኛ ተከሳሽ አቶ ደጀኔ ጣፋ በበኩላቸው ‹‹እኔ የምታገልለት ህዝብ በመንግስት ጦር እያለቀ ባለበት ሰዓት እኔ እዚህ ቆሜ ቃሌን መስጠት አልፈልግም፡፡ ይህ ፍርድ ቤትም ህገ-መንግስቱን የጣሰ ውሳኔ ስላሳለፈብኝ ለዚህ ፍርድ ቤት ቃሌን መስጠት ታሪካዊ ስህተት ነው የሚሆነው፡፡ ድጋሜ እዚህ ፍርድ ቤት መቅረብም አልፈልግም›› የሚል መልስ ሰጥተዋል፡፡

3ኛ ተከሳሽ አቶ አዲሱ ቡላላም በተመሳሳይ ቃላቸውን ለመስጠት እንደማይፈልጉ ተናግረዋል፡፡ ‹‹የደረሰን በክስ መልክ የቀረበ ድረሰት ግልጽ አይደለም፡፡ በባህላችን ውሻ እንኳ ዝም ተብሎ አይነካም፡፡ ከተነካም ባለቤቱን መናቅ ነው የሚሆነው፡፡ እኔ ለኦሮሞ ህዝብ በሰላማዊና በህጋዊ መንገድ እታገላለሁ፡፡ የተሰጠኝ ድርሰት ግን የኦነግ አባል ሆነሃል የሚል ነው፡፡ እኔ የኦፌኮ አባል እንጂ የኦነግ አባል አይደለሁም፡፡ ስለዚህ በፍርድ ቤቱ ወንጀሉን ፈጽመሃል አልፈጸምህም ተብዬ ስጠየቅ ያሳፍረኛል፡፡ ከዚህ በኋላ አስገዳጅ ሁኔታ ካልተፈጠረ በቀር እዚህ ችሎት መቅረብ አልፈልግም፡፡ ውሳኔያችሁን ልትልኩልኝ ትችላላችሁ›› በማለት ለችሎቱ ተናግረዋል፡፡

የችሎቱ ሰብሳቢ ዳኛ አቶ ታደለ ተገኝ ተከሳሾቹ በአጭሩ ድርጊቱን ስለመፈጸም አለመፈጸማቸው ብቻ መልስ እንዲሰጡ፣ ሌላ ረጂም ንግግር ማድረግ ተገቢ እንዳልሆነ በተደጋጋሚ ማሳሰቢያ ሲሰጡ ተደምጠዋል፡፡
ከማሳሰቢያው በኋላ፣ 4ኛ ተከሳሽ የሆኑት የኦፌኮ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ በቀለ ገርባ ደግሞ፣ ‹‹በክስ መቃወሚያችን ወንጀሉ ተፈጸመ በተባለበት ቦታ እንዳኝ ብለን ጠይቀን ይህ ችሎት ውድቅ አድርጎታል፡፡ ጥያቄያችን ህገ-መንግስታዊ ነበር፡፡ ግን አልተቀበላችሁትም፡፡ ስለዚህ ይህ ፍርድ ቤቱ ገለልተኛ ነው ብዬ ስለማላስብ ቃሌን ለመስጠት አልፈልግም፡፡ ካሁን በፊትም የሀሰት ማስረጃ ቀርቦብኝ ስምንት አመት ፈርዶብኛል፡፡ የዚህንም ውሳኔ ባለሁበት ልትልኩልኝ ትችላላችሁ›› ብለዋል፡፡

ከ5ኛ ተከሳሽ ጀምሮ እንዲሁ በተመሳሳይ ቃላቸውን እንዲሰጡ እየተጠየቁ በአብዛኛው ተመሳሳይ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ከተከሳሾች መካከል 10ኛ እና 12ኛ ተከሳሾች ብቻ ‹‹ድርጊቱን አልፈጸምንም›› የሚል ቀጥተኛ የክህደት ቃላቸውን ሲሰጡ 13ኛ ተከሳሽ በበኩሉ የዝምታ ምላሽን ሰጥቷል፡፡ 7ኛ ተከሳሽ ‹‹ክሱ ንቀትና ጥላቻ የታጨቀበት ስለሆነ መልስ አልሰጥም›› ሲል ቀሪዎቹ ክሱ ግልጽ አይደለም፣ ፍርድ ቤቱም ገለልተኛ ነው ብለን አናምንም በሚል የእምነት ክህደት ቃላቸውን ለመስጠት ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ለችሎቱ ገልጸዋል፡፡

በሌላ በኩል የቂሊንጦ እስር ቤት አስተዳደር 11ኛ እና 19ኛ ተከሳሾችን ‹‹በስራ ጫና ምክንያት ቆጥረን አረጋግጠን ማቅረብ አልቻልንም›› የሚል መልስ በሰጠበት ምክንያት ሳያቀርባቸው ቀርቷል፡፡ ይህን በተመለከተ ጠበቃቸው በሰጡት አስተያየት ደበኞቻቸው ላይ የደህንት ስጋት ተጋርጦባቸው ሊሆን እንደሚችል ስጋታቸውን ገልጸው ፍርድ ቤቱ ይህንኑ ስጋታቸውን እንዲመዘግብላቸው አሳስበዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ በበኩሉ አስተዳደሩ በነገው ዕለት እንዲያቀርባቸው በማዘዝ የእምነት ክህደት ቃላቸውን ለመቀበል ቀጠሮ ይዟል፡፡

ፍርድ ቤቱ ዛሬ የቀረቡት ተከሳሾች ቃላቸውን ለመስጠት ፍቃደኛ አለመሆናቸውን ከመዘገበ በኋላ ‹‹ወንጀሉን አልፈጸምንም›› እንዳሉ ተቆጥሮ ክደው እንደተከራከሩ በመመዝገብ ያለ አቃቤ ህግ አሳሳቢነት የአቃቤ ህግ ምስክሮችን ለመስማት በሚል ከህዳር 02-16 ቀን 2009 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ ፍርድ ቤቱ የአቃቤ ህግ የሰው ምስክሮች በርካታ በመሆናቸው ተከታታይ የቀጠሮ ቀናትን መስጠቱን ገልጹዋል፡፡
በዛሬው የችሎት ውሎ ተከሳሾቹ ዳኞች ወደ ችሎት ሲገቡም ሆነ ችሎቱ ጉዳያቸውን ሲያይ በችሎቱ ላይ ያላቸውን ተቃውሞ ለመግለጽ ከመቀመጫቸው ሳይነሱ ቀርተዋል፡፡
ምንጭ፡-EHRP

ወልቃይት ላለፉት ሺህ ዓመታት በትግራይ ስር ተዳድራ አታውቅም – የታሪክ ማስረጃዎች

(Ze Addis)

የኢትዮጵያ መንግስት (ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ) አዲስ አበባን ከተቆጣጠረ በኋላ ከወሰዳቸው ዓብይ ኩነታት አንዱ፤ የሀገሪቱን የፖለቲካን የአስተዳደር ካርታን መቀየሩ እንደሆነ ይታወቃል:: የኢትዮጵያ ክፍላተ ሀገራት ካርታ እ.ኤ.አ. በ1994 ቢቀየርም፤ አዲሱ ካርታ ብዙ የማንነት ጥያቄዎችን አስነስቷል:: ይህ የዳግም መካለል ጥያቄ ከሚነሳባቸው ቦታዎች ውስጥ ወልቃይት አንዱ ነው።

እንዲህ አይነት የማንነትና የመካለል ጥያቄ ሲቀርብ ዋና መፍትሄ የሚሆኑት የታሪክ ሰነዶች ናቸው:: የታሪክ ሰነዶች ስለ ወልቃይት ግን ምን ይላሉ? ላለፉት ብዙ መቶ ዓመታት የተጻፉ የታሪክ ሰነዶች ምን እንደሚሉ እንመርምር::

1/ ወልቃይት ጠገዴና አላማጣ ኮረም በአጼ ዮሓንስ ዘመን በትግራይ ሥር አልነበሩም – የታሪክ ሰነድ ማስረጃ

አጼ ዮሓንስ ከ 1871 ዓ.ም እስከ 1889ዓ.ም (እ.ኤ.ኣ) ኢትዮጵያን የመሩ ንጉስ ናቸው:: ንጉሰ በንግሥና ዘመናቸው የራሳቸው ጠንካራና ደካማ ጎን ቢኖራቸውም፣ ከጠላት ደርቡሽ ጋር በመፋለም ለሀገራቸው ክቡር ሕይወታቸውን የሰጡ ንጉሰ ናቸው:: ጥቂት የማይባሉ የሕወሀት ሰዎች፣ ከወልቃይትና ጠገዴ ጋር በተያያዘም የሚጠቅሱት እሳቸውን ነው:: “ወልቃይት እና ጠገዴ ፣ ጥንት በአጼ ዮሓንስ ዘመነ መንስግት በትግራይ ስር ነበረች” በማለት እንደ ዋና መከራከርያ ሲያቀርቡት ይደመጣል:: እውነታውን የዘገቡት የታሪክ ሰነዶች ናቸውና የታሪክ ሰነዶችን እንመርምር::

በአጼ ዮሓንስ ዘመን የነበረው የትግራይ ግዛትና፣ አጠቃላዩ የኢትዮጵያ ግዛት ምን እንደሚመስል በዝርዝር በሀገር ውስጥና በውጭ ሊቃውንት ተጽፏል:: ስለ ወልቃይትም አስተዳደር በማን ስር እንደነበረ በዝርዝር ጽፈውታል:: ለዚህም የእውቁን የፈረንሳዊ የጂኦግራፊ ፕሮፌሰር ኤሊስ ሬክለስ መጽሓፍን በዋቢነት መጥቀስ ይቻላል::

በዩንቨርሲቲ ኦፍ ብረስልስ የኮምፓራቲቭ ጂኦግራፊ (University of Brussels, Professor of Comparative Geography) ፕሮፌሰርና የዴፓርትመንቱ ሀላፊ የነበረው ይሄው ፕሮፌሰር ፤ በ1880 ጀምሮ በርካታ መጽሓፎችን በዓለም ጂኦግራፊ ላይ ጽፏል:: እነዚህም መጽሓፍቱ ከለንደንና ፓሪስ ጆኦግራፊካል ሶሳይቲ የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ አድርገውታል::

ከነዚህ መጻሕፍት አንዱ በ 1880 የተጻፈው The Earth and its Inhabitants የሚለው ሲሆን፤ ዘጠኝ ተከታታይ ክፍሎች አሉት። የዚሁ መጽሓፍ ክፍል አራት በገጽ 443 ላይ የሰሜን እና ምስራቅ አፍሪካን የወቅቱን ጂኦግራፊ በዝርዝር ይተነትናል:: በአጼ ዮሓንስ ዘመን የነበረውንም የኢትዮጵያን ክፍላተ ሀገራት በዝርዝር ቁልጭ አድርጎ እንዲህ ጽፎታል::

“The Amhara government provinces are: Dembia, Chelga, Yantangera, Dagossa, Kuarra, Begemidir, Guna, Saint, Wadla, Delanta, Woggera, Simen, Tselemt, Armachiho,Tsegede, Kolla Wogerra፣ Waldiba and Wolkait”

Table-Tigray-territories-from-the-book-The-Earth-and-its-Inhabitants-768x363

Table – Tigray territories from the book – The Earth and its Inhabitants

ከላይ ለመግለጽ እንደሞከርኩት ይህ ጽሁፍ የተጻፈው በ1880ዎቹ አጼ ዮሃንስ የሀገሪቱ ንጉስ በነበሩበት ዘመንና የተጻፈውም በግዜው ከነበሩ ከተለያዩ የጂኦግራፊካል ሶሳይቲዎች የወርቅ ሜዳይ ተሸላሚ በሆነ ባለሙያ ፕሮፌሰር ነው:: ይህ በ1880ዎቹ የተጻፈው መጽሓፍ እንደሚያስረዳው በአጼ ዮሓንስ ዘመን ወልቃይት: ጠለምት : ዋልድባ : አላማጣ : በሙሉ በትግራይ ስር አልነበሩም:: እነዚህን ቦታዎች በስም ጠቅሶ እንደሚነግረን በትግራይ ስር ሳይሆን በጎንደር ስር ነበሩ::

“በአጼ ዮሓንስ ዘመን ወልቃይትና ጠግዴ በትግራይ ስር ስለነበሩ ነው አሁን ወደ ትግራይ የጠቀለልናቸው ” የሚለው መሰረት የሌለው መሆኑን ይሄ መረጃ ያሳየናል:: ከአጼ ዮሓንስ በፊትስ እነዚህ ቦታዎች ይተዳደሩ የነበሩት በማን ነው? የሚለውን እንመልከት። ወደ አጼ ቴዎድሮስ ዘመን እንጓዝ፡፡

2/ በኣጼ ቴዎድሮስም ዘመን ወልቃይት ጠገዴ በትግራይ ስር አልነበሩም – የታሪክ ማስረጃ ሰነዶች

በኣጼ ቴዎድሮስ (1818 – 1868 እ.ኤ.አ) የነበሩ ስመ ገናና ኢትዮጵያዊ ንጉስ ነበሩ:: በየቦታው የነበሩ መሳፍንትን አሸንፈው፣ ማዕላዊ መንግስት ከመሰረቱ በኋላ፣ ቀጣይ ራዕያቸው የምዕራብያውያንን ቴክኖሎጂ እዚሁ ኢትዮጵያ እንዲመረት ማድረግ ነበር:: ለዚህም ከበርካታ አውሮፓ ሀገራት ጋር ግንኙነት መስርተው ነበር:: የአውሮፓውያን ጥበበኞችን ኢትዮጵያ ለማስቀረት እና ጥብቅ ግንኑነት ለመመስረት፣ አጼ ቴዎድሮስ ልጃቸውን ለአንድ ስዊስ ኢንጂነር እስከመዳር ደርሰው ነበር:: በዚህም ምክንያት በርካታ አውሮፓውያን ጠቢባን በአጼ ቴዎድሮስ ዘመን ኢትዮጵያ መጥተዋል:: እነዚህም ባለሙያዎች ኢትዮጵያ መጥተው ስለ ሀገሪቱ በዝርዝር ጽፈዋአል:: የእንግሊዝ መንግስትና የኢትዮጵያ ግንኑነት መሻከር ሲጀምር፣ እንግሊዞች ስለኢትዮጵያ ይበልጥ የማወቅ ፍላጎታቸው ጨመረ::

የእንግሊዝ መንግስት የintelligence ሰዎችም የእንግሊዝ መንግስት ፓርላማና የጸጥታው ኃይል ኢትዮጵያን በሚገባ ያውቃት ዘንድ ትዕዛዝ ወጣ:: የእንግሊዙ Topographical and Statistical Department of The War Office ኤ . ሲ ኩክ (A. C. Cook) በተባለ እንግሊዛዊ ኮሎነል አማኻኝነት ስለ ኢትዮጵያ ከ15ኛው ክፍለ ዘመን ጀመሮ በተለያዩ እውሮፓውያን ተጻፉ መጻሕፍት ባንድ ላይ እንዲጠርዘ ተደረገ:: የሚደንቀው ይሄ መጽሓፍ በ 1867 ዓ.ም እ.ኤ.ኣ የታተመው በግስቲቷ ጥያቄ ለእንግሊዝ ሀውስ ኦፍ ኮመን ሎወር ሀውስ ግብአት (House of Common lower House) ይውል ዘንድ መሆኑ ነው:: በዚሁ መጽሓፍ ውስጥ፤ የወቅቱ የኢትዮጵያ ዝርዝር ጉዳይ ተጽፏል:: ይሄውም መጽሓፍ ስለ ወልቃይትና ጠገዴም በኣጼ ቴዎድሮስም ይሁን ከሳቸው በፊት በማን ስር ይተዳደሩ እንደነበር በዝርዝር ያትታል::

“The Provinces of Amhara are : Simen, Waldibba, Wolkait,Wogera,Chilga, Kuara, Belesa, Fogerra, Damot, Gojjam, Begemidir, Beshilo ….. Waldiba situated to the NW of Semein between the Tekeze and the Angereb, extends as far as the junction of the two rivers. Welkait is to the west Of Waldiba it is intersected through its whole length by the two river tekuar and guang. It is more wooded than waldiba..” (Routes in Abyssinia (printed in 1867 G.C) page 188)

ይሄው ታሪካዊ መጽሓፍ በወቅቱ የነበረውንም የትግራይ ክፍለሀገር ድንበር እና ግዛት እነማን እንደነበሩ በማያሻማ ቋንቋ እንዲህ ይነግረናል፡፡

“The territory of Tigre whose capital is Adwa, is bounded on the West by Shire, on the Southwest by Temben and Adet on the South by Geralta on the South –East by Haramat, on the East by Agame, and on the North by the rivers of Mereb and Belessa”

የትግራይ ግዛትስ? ብሎ ለሚጠይቅ ወገን ፤ ይሄው መጽሓፍ በወቅቱ የነበርቸው ትግራይ ምን እንደምትመስል እንዲህ ሲል አስፍሮታል በዚሁ መጽሓፍ ላይ ገጽ 187 – 188 የትግራይን ግዛት እንዲህ ሲል ይገልጸዋል

“The territory of Tigray whose capital is Adwa is bounded on the west by Shire, on the south west by Temben and Adet, on the south by Geralta, on the South East by Haramat, on the East by Agamae, and on the North by the Rivers Mereb and Belessa”

Map-northern-Ethiopia-areas-768x362

Map – northern Ethiopia areas

እዚህ ላይ በ 18ተኛው ክፍለ ዘመን የትግራይን ወሰኖች በማያሻማ ሁኔታ በግልጽ አስቀምጦታል:: የትግራይ ወሰን በምዕራብ – ሽሬ ፤ በምዕራብ ደቡብ – ተምቤን እና አዴት ፤ በደቡብ – ገር አልታ ፤ በምስራቅ – አጋሜ ፤በሰሜን – መረብና በለሳ ናቸው:: የታሪክ ሰነዶች በአጼ ቴዎድሮስም ዘመን እንደሚነግረን ፤ ወልቃይትና ጠገዴ በትግራይ ስር አልነበሩም::

ከዛስ በፊት ወልቃይትና ጠገዴ በትግራይ ስር ነበሩን? አሁንም የታሪክ ሰነድ እንመርምር::

3/ በዘመነ መሳፍንት ዘመንም ወልቃይትጠገዴ በትግራይ ስር አልነበሩም – የታሪክ ማስረጃ ሰነዶች

እንደሚታወቀው ከአጼ ኢዮአስ ሞት ጀምሮ ፤ አጼ ቴዎድሮስ እስኪነሱ የነበረው ዘመን ዘመነ መሳፍንት ይባላል:: በዚህ ዘመን ኢትዮጵያ ማዕከላዊ መንግስት አልነበራትም:: መሳፍንቶች የገነኑበትና በሀገሪቱ ማዕከላዊ አስተዳደር የጠፋበት ዘመን ነበር:: በዚህ ማዕከላዊ የመንግስት ሕግ በሌለበት ወቅት እንኳን ወልቃይት፥ጠገዴ፥ ዋልድባ ፥ አላማጣ፥ ኮረም እና የመሳሰሉ ቦታዎች በትግራይ ስር አልነበሩም:: አሁንም ማስረጃ እነሆ!

ጀምስ ብሩስ የተባለው ስኮትላንዳዊ ፥ በዘመነ መሳፍንት ኢትዮጵያ መጥቶ ኢትዮጵያ በዘመነ መሳፍንት ምን ትመስል እንደበረ፥ ቁልጭ አድርጎ አስቀምጦታል:: እያንዳንዱ መስፍን ግዛቱ የት ድረስ እንደነበረ፥ የትኛው መስፍን ማንን ይገዛ እንደነበረ በሰፊው ተንትኖታል:: በዚህም መሰረት ስለ ትግራይ ግዛትና እንዲህ ሲል ምስክርነቱን ይሰጣል :: Travel to discover source of the Nile Volume 3 page 582 ላይ

“Tigre is bounded by the territory of the Bahirenegash that is by the river Mereb on the East and Taccazze upon the west. It is about one hundred and twenty miles broad from E. to W. and two hundred from N. to S. “

ጀምስ ብሩስ በዚሁ መጽሓፉ Chapter 10 ላይ Geographical division of Abyssinia into province በሚለው አንቀጹ ላይ በይበልጥ ቁልጭ አድርጎ እንዲህ ያስቀምጠዋል

The first division is called Tigre, between Red Sea and the river Tekeze. Between that River (Tekeze) and the Nile Westwards where it bounds the Oromo, it is called Amhara.

ካለ በኋላ ወረድ ብሎ ይበልጥ ጉዳዩን ሲያስረዳ “Tekezze is the natural boundary between Tigre and Amhara”

ከላይ ለአብነት ያስቀመጥኳቸው ሊቃውንት በግዜ፣ በቦታና በዜግነት አይገናኙም:: ለምሳሌ በአጼ ዮሓንስ ዘመን የነበረው አሊስ ሬክለስ ፈረንሳዊ (French) ነው:: በአጼ ቴዎድሮስ ዘመን የነበረውን የኢትዮጵያ ግዛት የጻፈው ደግሞ እንግሊዛዊ ነው (British):: ጀምስ ብሩስ ደግሞ ስኮትሽ (Scottish)ነው:: ግን ሁሉም በተለያየ ግዜ መጥተው ያዩትና የተገነዘቡትን ጽፈዋል:: የሚናገሩት አንድ ና ተመሳሳይ ነው:: እውነት ምን ግዜም አንድ ናትና!

4/ ወልቃይት በ1630ዎቹስ በማን ስር ነበረች?

በ16ኛው መቶ አጋማሽ ላይ ያሉ ያታሪክ መዛግብትም የሚናገሩት ተመሳሳይ ነገር ነው:: በተለያዩ ወገኖች ተደጋግሞ የሚጠቀሰው የ ማኑኤል በሬዳም መጽሓፍ የሚተነትነው ያንኑ ነው:: ይሄ መጽሓፍ የተጻፈው በ1634 ሲሆን ጸሓፊውም ኢማኑኤል በሬዳ ይባላል:: በወቅቱ የነበረውን የትግራይ ግዛት በዝርዝር አስቀምጧል:: እሱም እንደሌሎቹ ጸሓፍት የትግራይ ድንበር ተከዜ እንጂ ተከዜን ተሻግረው ያሉት ወልቃይትና ጠገዴ ናቸው አይልም::

«Tractatus tres historico-geographici (1634): A seventeenth century historical and geographical account of Tigray, Ethiopia (Aethiopistische Forschungen) 1634» መጽሀፍ የመጀመሪያ ምዕራፍ ስለ ትግራይ ግዛት እንዲህ ይላል::

“Among all the kingdoms that the Emperor of Ethiopia possesses today one of the greatest if not the greatest and the most important is the kingdom Tigre. From north to south, that is from the limits of the Hamasen to Enderta, it covers an areas of from ninety to one hundred leagues (3.2 miles); and from the east, which is besides Dancali, located at the entrance to the Red sea to the southern end of the Red Sea, to the west bounded by the Tekezze River beside the Semen, it covers an area of similar size, so that the Kingdom has a nearly circular shape.”

አሁንም ወደኋላ እየራቅን እንሂድና ወልቃይት ጠገዴ በነ አጼ ዘርዓ ያዕቆብ ዘመን በማን ስር ነበርች? የሚለውን እንመልከት

5/ በኣጼ ዘርዓ ያዕቆብ ( 14ኛው ክፍለ ዘመን) ዘመንም ወልቃይትጠገዴ በትግራይ ስር አልነበሩም – የታሪክ ማስረጃ ሰነዶች

አጼ ዘርዓ ያዕቆብ በኢትዮጵያ ታሪክ ከተነሱ ሃያልና ሊቅ ነገስታት ውስጥ አንዱ ነበሩ:: በቀድሞ ስሙ ፈጠጋር በአሁን ስሙ ኦሮሚያ አዋሽ ወንዝ አካባቢ የተወለዱት አጼ ዘርዓ ያዕቆብ፥ የሀድያ ሲዳሞ ንጉስ ልጅ የሆነችውን እሌኒን አግብተው፥ በ37 ዓመታቸው ከነገሱ ጀምሮ በርካታ ዓበይት ስራዎችን አከናውነው አልፈዋል:: እኒሁ ንጉስ ከፍተኛ የጥበብ ፍቅር የነበራቸውና ከመሆናቸው ባሻገር፥ ራሳቸው ብዙ መጻሕፍትን ጽፈዋል:: በሳቸው ዘመንም ብዙ መጻሕፍት እንዲጻፉ ድጋፍ በመስጠታቸው አያሌ መጻሕፍት በሳቸው ዘመን ተጽፈዋል:: ከነዚህ መጻሓፍት አንዱ በአክሱም ንቡረ ዕድ የተጻፈው ዜና አክሱም መጽሃፍ አንዱ ነው:: ዜና አክሱም ከሃይማኖያትዊ ሐተታው ባለፈ ስለ 14ኛዋ ክፍለ ዘመን ኢትዮጵያ በዝርዝር ጽፎታል:: ይህ መጽሓፍ የኢትዮጵያን አጠቃላይ ወሰንና ታሪክ ብቻ ሳይሆን የክፍላተ ሀገራቱንም ድንበር ጥንቅቅ አድርጎ ዘግቦታል:: የትግራይንም ክልል በካርታና በጽሁፍ ከዚህ እንደሚከተለው ይገልጸዋል::

Chart-List-of-Tigrai-areas-on-Zena-Axum-book

Chart – List of Tigrai areas on Zena Axum book

ይህም መጽሓፍ በተመሳሳይ መልኩ የሚነግረን፣ ወልቃይትና ጠገዴ በፍጹም ፣ የትግራይ አካል አንዳልነበሩ ነው::

ዮሓንስ መኮንን Ethiopia: the land, its people , History and Culture በሚለው መጽሓፉ Page 351 በአጼ ዘርዓ ያ ዕቆብ ዘመነ መንግስት የነበረውንና በመጽሓፍ አክሱም የተተነተውን የትግራይን ካርታ እንዲህ ያቀርበዋል

“The Book of Axum.. Shows a traditional schematic map of Tigray with its city Axum at its center surrounded by the thirteen principal provinces: Tembein, Shire, Seraye, Hamasen, Bur, Sama, Agame, Amba Senait, Geralta, enderta, Sahart and Abergele”

በተመሳሳይ ሁኔታም The World through Maps: A History of Cartography (ገጽ 352 ይመልከቱ)፡፡ በJohn R. Short የተጻፈው የዓለም ጂኦግራፊን የሚተርከው መጽሓፍ በ15ኛው ክፍለዘመን የነበሩ የትግራይ ግዛቶች ከላይ የተጠቀሱት መሆናቸውን መጽሓፈ አክሱምን በመጥቀስ ያስረዳል:: ይህም መጽሓፍ በተመሳሳይ መልኩ የሚነግረን፣ ወልቃይትና ጠገዴ በፍጹም የትግራይ አካል አንዳልነበሩ ነው::

6/ ቋንቋን መሰረት ወዳደረገ ክለላን አንመልከት

የኢትዮጵያውያን ወጣቶችና አርበኞች ቁጣ ያሳሰበው ጣልያን፣ ኢትዮጵያን በቋንቋና በዘር በትኖ ለመግዛት ያቀደውን መርዝ ይፋ አወጣ:: የዚህ እቅድ ፊታውራሪ ከሆኑት አንዱ ፋሺስቱ Baron Roman Prochàzka አቢሲንያ ዘ ፓውደር ባረል (Abyssinia: the Powder barrel) በሚል መጽሓፉ ላይ እንዳስቀመጠው፣ ኢትዮጵያውያንን ለመግዛት በዘር መከፋፈልና በመሀከላቸውም ጥላቻን በመዝራት እርስ በርስ ለማናከስ፣ ሀገራቸውን በዘር መከለል የሚለውን እቅድ መተግበር ጀመረ:: በዚሁም መሰረት፣ ዘርንና ቋንቋን መሰረት ባደረገ ሽንሸና ኢትዮጵያን አምስት ቦታ ከፈላት::

እነዚሁም ክልሎች አማራ: ኤርትራ(ትግሬ); ሐረር: ኦሮሞ-ሲዳማ: ሸዋና ሶማሌ ናቸው:: ጣልያን ይሄንን የግዛት ሽንሸና ሲያካሂድ መሰረት ያደርገው ዘርና ቋንቋን ነበር:: የሚከተለውም ሰማንያ በሃያ የሚለውን መርህ ነበር:: ከሰማንያ በመቶ በላይ ሕዝቡ የሚናገረውን ቋንቋ መሰረት በማድረግ ወደየ ክልሉ ይደለደላል:: ሸዋን ግን ለብቻው ለይቶ መቆጣጠር ይገባል ብሎ በማመኑ ሸዋን ና ሀረርን ለብቻ ለይቶታል:: ወደ ነጥባችን ስንመጣ በዚህ የቋንቋ ሽንሸና መሰረት ወልቃትና ጠገዴና ጠለምት ወደ ትግራይና ኤርትራ አልተካተቱም:: በጎንደር ስር ነበሩ::

እዚህ የጣልያን ቋንቋንና ዘርን መሰረት ያደረገ ካርታ ላይ በግልጽ እንደሚታየው ፣ የትግራይ ድንበት ተከዜ እንጂ – ከተከዜ ተሻግሮ አይደለም:: ላልፉት 25 ዓመታት ተቃዎሞ ሲካሄድባቸው የከረሙት ወልቃይት – ጠገዴ – አላማጣ ኮረም በፍጹም በትግራይ ስር እንዳልነበሩ በግልጽ ያሳየናል::

Map-Tigray-during-Fascist-Italy-768x664 (1)

Map – Tigray during Fascist Italy

7/ አንዳንድ ሚድያዎች ደጋግመው የሚያነሱት ነጥብ አለ:: ይሄውም ወልቃይት ጸገዴና ሌሎች ወደ ትግራይ የተካለሉ ቦታዎች ጥንት የትግራይ እንደነበሩና አጼ ኃይለ ሥላሴ የምስራቃዊ ትግራይ ገዥ ከነበሩት ከደጃዝማች ኃይለሥላሴ ጉግሳ አርዓያ ጋር በመጣላታቸው – ወልቃይትና ጠገዴን ወደ ጎንደር ወሰዱት የሚል ነው:: ሌላው የማያስማማው ነጥብ ደግሞ – የቀዳማይ ወያኔን አመጽ ምክንያት በማድረግ ትግራይን ለመቅጣት – ወልቃይትንና ጠገዴን ወደ ጎንደር ከለሉት የሚል ነው::

እስካሁን ከላይ የገለጽኳቸው ሰነዶች ለዚህ ነጥብ በቂ ማስረጃ ቢሆኑም : ካርታን መሰረት ያደረገ መረጃ ለሚጠይቅ ሰው – እነሆ:: ይህ ካርታ በጣልያኖች በ1928 ዓ.ም የተሰራ ነው:: ኢትዮጵያን በደምብ ካጠኑ በኋላ ለያንዳንዱ ክፍለሀግር ካርታ ሰርተዋል:: ያኔ ገና ኃይለሥላሴ ጉግሳ አልከዳም:: ያኔ የቀዳማይ እንቅስቃሴ አልነበረም:: የቀዳማይ እንቅስቃሴ በ1943 ነበር፡፡ ይህ ካርታ ግን ከዛ ብዙ ዓመታት በፊት የተሰራ ነው:: አንባቢው አይቶ ይፍረድ:: ወልቃይት ጠገዴን ነጥለን ስንመለት ካርታው ይሄንን ይመስላል::

Map-north-west-Ethiopia-in-1928

Map – north west Ethiopia in 1928

8/ በዘመነ መንግስቱ ኃይለማርያም ወልቃይትና ጠገዴ

በካምብሪጅ ዩንቨርሲቲ በአፍሪካ ጉዳዮች ላይ ይበልጡንም በኢትዮጵያ ታሪክና ፖለቲካ ላይ ከፍተኛ ምርምር ካደሩት ሰዎች ውስጥ በዋነኝነት የሚጠቀሱት ፕሮፌሰር ክሪስቶፈር ክላፓም: እንደ ኤሮፓ አቆጣጠር 1990 ( ህወሀት አዲስ አበባብ ከመያዙ አንድ አመት በፊት) ድንቅ የሆነ መጽሓፍ አሳትመው ነበር:: በዚሁ መጽሓፋቸው ላይም ስለ ወልቃይትና ጠግዴ እንዲህ ሲሉ ይተርኩታል

“the area concerned (welkait -Tsegede) separated from Tigray by impressive natural barrier of Setit Tekezze river has never been governed as part of Tigray at any period in the past, but has come under Gonder and Semein.” (Christopher Clapham: Transformation and continuity in revolutionary Ethiopia (Cambridge: Cambridge university press 1988 pp 259)

ስናጠቃልለው

1. 1420ዎቹ እንደተጻፈ የሚታመነው መጽሓፈ አክሱም በግልጽ እንደሚያሰረዳን የትግራይ ግዛቶችና ወሰኖች 13 ነበሩ:: እነርሱም Tembein, Shire, Seraye, Hamasen, Bur, Sama, Agame, Amba Senait, Geralta, enderta, Sahart and Abergele ናቸው::

ማስረጃ : መጽሓፈ አክሱም , Ethiopia: the Land, Its People, History and Culture By Yohannes Mekonnen. The World through Maps: A History of Cartography (ገጽ 352 ይመልከቱ) By John R. Short

2. 1634 ዓ.ም የተጻፈው የ እማኑኤል በሬዳ መጽሓፍ Tractatus tres historico-geographici (1634): A seventeenth century historical and geographical account of Tigray, Ethiopia (Aethiopistische Forschungen) 1634» እንደሚያስረዳው የትግራይ ወሰን ተከዜ እንጂ ተከዜን ተሻግረው ያሉት ወልቃይትና ጠገዴ አይደሉም

3. በዘመነ መሳፍንት ኢትዮጵያን ጎብኝቶ የነበረው የጀምስ ብሩስ መጽሓፍም በግልጽ የሚናገረው የትግራይ ወሰን ተከዜ እንጂተከዜን ተሻግረው ያሉት ወልቃይትና ጠገዴ አይደሉም፡፡ Travel to discover source of the Nile Volume 3 page 582

4. በአጼ ዮሓንስ ዘመንም የታሪክ ማስረጃዎች የሚያስረግጡት ያንኑ ነው:: የትግራይ ደንበር ተከዜ ነው:; ወልቃይትና ጠገዴ በጎንደር ስር እንደነበሩ በግልጽ ፈረንሳዊው ፕሮፌሰረ ሬክለስ ጽፎታል

5. በአጼ ቴዎድሮስ ዘመንም ወልቃይትም ይህን ጠግዴ በትግራይ ስር አልነበሩም::

6. በጣልያን ግዜም የትግራይ ወሰን በደቡብ እንዳምሆኒ, በደቡብ ምስራቅ አበርገሌ ;በም ዕራብ ሽሬና አዲያቦ ነበሩ እንጂ ወልቃይት ጠግዴ ዋጃ ኮረም እና መሰል ቦታዎች በትግራይ ስር አልነበሩም

7. ወልቃይትንና ጠገዴን ወደ ትግራይ የከለሉት አጼ ኃይለሥላሴ ናቸው:; ይህም በ1943 ዓ.ም የተካሄደውን የቀዳማይ ወያኔን አብዮት ለመበቀልና ሕዝቡንም ለመቅጣት ነው የሚለው: መሰረት እንደሌለው እነሆ ይህ ማስረጃ:: ጣልያን ይሄን ካርታ የሰራው በ1928 ዓ.ም ነበር:: ያኔም በአጼው ግዜም የትግራይ ወሰን ያው ነበር

8. የህዝብ ቁጥርና በሚነገሩት ቋንቋ ነው ወልቃይትንና ጠግዴን ወደ ትግራይ የከለልነው ለሚለውም – የዘርና የቋንቋ ክልልን ለመጀመርያ ግዜ ኢትዮጵያ ላይ የመሰረተው ጣልያን ነው:: ጣልያን ይህን ካርታ ሲሰራ የራሱን የዘርና የቋንቋ ጥናት አድርጎ ነበር:: በዚህም መሰረት ወልቃይትና ጠግዴን ወደ ትግራይ ሳይሆን ያካለላቸው ወደ ጎንደር ነበር:: ይሄ ከሆነ አንድ ትውልድ እንኳን አላለፈው:: ታድያ ያኔ አብላጫ የነበረው ቋንቋና ሕዝብ አሁን ወዴት ገባ?

9. በዚህ ዘመን ያሉ እውቅ የኢይዮጵያ ነክ ፕሮፌሰሮችም ምስክርነታቸው ያው ነው:: የካምብሪጅ ዩኒቨርስቲው ክሪስቶፈር ክላፕማን እንዳጠቃለሉት

“the area concerned ( welkait -Tsegede) separated from Tigray by impressive natural barrier of Setit Tekezze river has never been governed as part of Tigray at any period in the past, but has come under Gonder and Semein.

10. የአጼ ዮሓንስ የልጅ ልጅ ልዑል ራስ መንገሻ ስዩምም እንዳረጋገጡት ” የትግራይ ወሰን ተከዜ እንጂ ተከዜን ተሻግረው ያሉት ወልቃይትና ጠግዴ አይደሉም”

አሁንም ቢሆን የወልቃይት የማንነት ጠያቂዎች የ ሃምሳ ሺህ ሰው ፊርማ አሰባስበው ነው ፌዴሬሽን ምክር ቤት ድረስ የሄዱት:: እንግዲህ ይሄ ሁሉ ጫና: ወከባና ግድያ ባለበት በዚህ ወቅት ሃምሳ ሺህ ሰው ፊርማ ማሰባሰብ ከቻሉ ነጻነት አግኝተው ሁሉም ቦታ ቢንቀስቀሱ የምን ያህል ሰው ፊርማ ማሰባሰብ እንደሚችሉ መገመቱ ቀላል ነው:: ያለው እውነታ ይሄው ነው::

ማጠቃለያ

አሁንም ከላይ የጠቀስኳቸውን የፕሮፌሰር ክላፕማንን ቋንቋ ልጠቀምና ” ወልቃይትና ጠግዴ በኢትይኦጵያ ታሪክ በትግራይ ስር ሆነው አያውቁም”:: ለመጀመርያ ግዜ በትግራይ ስር : እንዲካተቱ የተደረገው በ1994 ነው::

እኔን የሚያሳሰበኝ ግን ሌላ ነው:: በአንድ ሀገር ውስጥ ሆነን ስለ ድንበር እያወራን ነው:: ከዚህ የማንነት ጥያቄም ጋር በተያያዘ በርካታ ሰዎች መገደላቸውን የሰባዊ መብቶች ጉባኤ አሳውቋል:: ወዴት እየሄድን ይሆን?

———–

ዋቤ መጻሕፍትና ሊንኮች

1. ‘ልዝብን ምኽሪን ጥራሕ’ያ መድሓኒታ’ ኢሎም ዶ/ር ገላዴዎስ ኣርኣያ

2. The Earth and its Inhabitants, Africa: South and east Africa, by Elisée Reclus 1890

3. Routes in Abyssinia (printed in 1867 G.C)

4. Travels to Discover the Source of the Nile: In the Years 1768 …, Volume 3. By James Bruce

5. Tractatus tres historico-geographici (1634): A seventeenth century historical and geographical account of Tigray, Ethiopia (Aethiopistische Forschungen) 1634

6. Ethiopia: the Land, Its People, History and Culture, By Yohannes Mekonnen

7. Christopher Clapham: Transformation and continuity in revolutionary Ethiopia (Cambridge: Cambridge university press 1988 pp 259

8. The World through Maps: A History of Cartography : John R Short

9. https://archive.org/details/liberaxumae00pari (the Book of Axum part one)

10. Library of Congress የኢትዮጵያ ካርታ 1955 ዓ.ም (በ1963 እ.ኤ.ኣ)

11. የኢትዮጵያ ካርታ 1966 ዓ.ም (በ1974 እ.ኤ.ኣ ወይም) Library of Congress

12. Library of Congress የኢትዮጵያ ካርታ 1979-81 ዓ.ም

13. በ1928 ዓ.ም ( 1933 እ.ኤ.አ) ጣልያን የሰራው የኢትዮጵያ ካርታ

14. በ1928 ዓ.ም (1933 እ.ኤ.አ) ጣልያን የሰራው የኢትዮጵያ ካርታ

15. CIA maps 1961 E.C and 1969 G.C

Source:- http://hornaffairs.com/am/2016/06/08/tigray-wolkait-historical-accounts