የተቃዋሚ ፓርቲዎች አመራሮች የክስ መቃወሚያ ውድቅ ተደረገ
በፌደራል አቃቤ ህግ የሽብር ክስ ተመስርቶባቸው ጉዳያቸው በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ወንጀል ችሎት እየታየ የሚገኙት የተቃዋሚ ፓርቲዎች አመራሮችና ሌሎች በተመሳሳይ መዝገብ የተከሰሱት ተከሳሾች በቀረበባቸው ክስ ላይ ያቀረቡት መቃወሚያ ውድቅ ተደረገባቸው፡፡ አመራሮቹ ጥር 26 ቀን 2007 ዓ.ም ችሎት ቀርበዋል፡፡
በእነ ዘላለም ወርቃገኘሁ የክስ መዝገብ የተከሰሱት የአንድነት፣ የሰማያዊና የአረና ፓርቲዎች አመራሮች የሆኑት አቶ ሀብታሙ አያሌው፣ የሺዋስ አሰፋ፣ አብርሃ ደስታ፣ ዳንኤል ሺበሽ እና ሌሎች ስድስት ተከሳሾች መቃወሚያቸው በፍርድ ቤቱ ውድቅ ተደርጓል፡፡
ተከሳሾች በጠበቆቻቸው አማካኝነት የቀረቡባቸው የተለያዩ የክስ ይዘቶች ላይ መቃወሚያቸውን አቅርበው የነበር ቢሆንም ፍርድ ቤቱ አቃቤ ህግ የተከሳሽ መቃወሚያ ውድቅ እንዲደረግለት የጠየቀውን በመቀበል ‹‹በመቃወሚያው ላይ የተነሱት ነጥቦች በአብዛኛው ማስረጃ በማሰማት ሂደት ወቅት ሊረጋገጡ የሚችሉ ስለሆኑ›› በሚል መቃወሚያቸው ውድቅ ተደርጓል፡፡ በመሆኑም ፍርድ ቤት በቀረበው ክስ አግባብ የክስ ሂደቱ እንዲቀጥል ውሳኔ ሰጥቷል፡፡
በሌላ በኩል ተከሳሾች በእስር ላይ በሚገኙበት ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ላይ ‹‹የመብት ጥሰት እየተፈጸመብን ነው›› በሚል አቤቱታ አቅርበው የነበር ሲሆን በአቤቱታው ላይ እስካሁን ከማረሚያ ቤቱ መልስ አለመሰጠቱ ታውቋል፡፡ አቤቱታው በጽሑፍ ተገልብጦ ለማረሚያ ቤቱ መላኩን የገለጸው ፍርድ ቤቱ፣ ለአቤቱታው መልስ ከማረሚያ ቤቱ እየተጠበቀ እንደሆነ ተገልጹዋል፡፡
በመሆኑም ይህንኑ የማረሚያ ቤቱን መልስ ለመስማትና የክሱን ሂደት ለመቀጠል ፍርድ ቤቱ ለየካቲት 11 ቀን 2007 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
ምንጭ፡-ነገረ-ኢትዮጵያ
ወጣቶቹ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች በድብቅ ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ተደረገ
ከአራት ወራት በፊት በሽብር ስም በአዲስ አበባ የፌደራሉ ወንጀል ምርመራ “ማዕከላዊ” የሚገኙት የአንድነት ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች አቶ አቶ ሀብታሙ አያሌው፣ ዳንኤል ሺበሺ፤ የሰማያዊ እና የአረና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች አቶ የሺዋስ አሰፋና አቶ አብርሃ ደስታ ዛሬ ጥቅምት 20 ቀን 2007 ዓ.ም. ከሰዓት በድብቅ ልደታ ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ መደረጋቸውንና ነገ ጠዋት በድጋሚ ልደታ ፍርድ እንደሚቀርቡ የፍኖተ ነፃነት ዘገባ ያስረዳል፡፡
የህሊና እስረኞቹ እንደተለመደው አራዳ ፍርድ ቤት ይቀርባሉ በሚል የትግል አጋሮችቸው እና ደጋፊዎቻቸውና ጋዜጠኞች ከቀኑ 7 ሰዓት ጀምሮ እስከ 11፡30 በቀጠሮው ስፍራ ቢጠብቁም፤ ፖሊስ በድብቅ ልደታ ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ማድረጉ ተሰምቷል፡፡ ታሳሪዎቹ ልደታ ፍርድ ቤት እንደሚገኙ መረጃ የደረሳቸው የአንድነት ፓርቲ አመራሮች በስፍራው ሲደርሱ አቶ ሀብታሙ አያሌው፣አቶ ዳንኤል ሺበሺ፣አቶ የሺዋስ አሰፋና አቶ አብርሃ ደስታ በመኪና ውስጥ ሆነው ወደ ማዕከላዊ ሲወሰዱ መመልከታቸውን ተናግረዋል፡፡ ቀደም ብሎም የልደታው ፍርድ ቤት “ጉዳዩን የሚያይ ዳኛ የለም” በማለት ለነገ ጠዋት ጥቅምት 21 ቀን 2007 ዓ.ም ቀጠሮ መሰጠቱም ተጠቁሟል፡፡
ምንጭ፡- ፍኖተ ነፃነት
የፖለቲካ አመራሮቹ ችሎት ያለ ተከላካይ ጠበቃ ሲታይ፤ቀጣይ ቀጠሯቸው ግልፅ አይደለም
ዛሬ መስከረም 22 ቀን 2007 ዓ.ም. ፒያሳ አራዳ በሚገኘው የፌደራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጉዳይ በዝግ ችከሎት ያለ ተከላካይ ጠበቃ ቀጠሮ መስጠቱ ተጠቆመ፡፡ የፖለቲካ አመራሮቹ አቶ ሀብታሙ አያሌው የአንድነት ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ፣ አቶ ዳንኤል ሺበሺ የአንድነት ፓርቲ ምክትል የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ፣ አቶ አብርሃ ደስታ የመቀሌ ዩኒቨርስቲ መምህርና የአረና ፓርቲ ምክትል የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ እንዲሁም አቶ የሺዋስ አሰፋ የሰማያዊ ፓርቲ ምክትል የምክር ቤቱ ሰብሳቢ ከተከላካይ ጠበቆቻቸው ጋር ሳይገናኙ ከቀጠሮ ሰዓታቸው አርፍደው ከቀኑ 10 እና 11 ሰዓት ፍርድ ቤት መቅረባቸውን ነገረ ኢትዮጵያ ዘግቧል፡፡
በነበረው የፍርድ ቤት ችሎት ተከላካይ ጠበቃ ደንበኞቻቸውን ህጉ በሚፈቅደው መሰረት በማዕከላዊ ሄደው መጎብኘትና መነጋገር ቢፈልጉም፤ በፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ማዕከል “ማዕከላዊ” ፖሊስ ስላልተፈቀደላቸው ፍርድ ቤት መገኘቱ ለፕሮፖጋንዳ ካልሆነ ከህግ አግባብ ትርጉም ስለሌለው እንደማይገኙ አስቀድመው ማሳወቃቸው ተጠቁሟል፡፡ በችሎትም ቤተሰብ፣ ጋዜጠኛ፣ ዲፕሎማቶች እና ወዳጅ ዘመድ እንዳይከታተል መከልከሉም ታውቋል፡፡ የእስረኞቹ ቀጣይ ቀጠሮ መቼ እንደሆነ እስካሁን ከፍርድ ቤቱ ማግኘት ባይቻልም፤ እንደ ነገረ ኢትዮጵያ ዘገባ ከሆነ የማዕከላዊ ምርመራ ኃላፊ አቶ ተክላይ ሹመት ተጠርጣሪዎቹ የተቀጠሩት ለጥቅምት 20 ቀን 2007 ዓ.ም. ሲሉ፤ ሌላ ፖሊስ ደግሞ ለጥቅምት 22 ቀን 2007 ዓ.ም. ነው የሚል ጥቆማ መስጠታቸውን የነገረ ኢትዮጵያ ጋዜጣ ምንጮች አስታውቀዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ እስረኞቹ እስካሁን በነበረው ምርመራ ፖሊስ ምንም ዓይነት ለወንጀል ክስ የሚያበቃ መረጃ ባለማግኘቱ፤ ወደ ኃይል እርምጃ በመሄድ ፖሊስ የሚፈልገውን ቃል እስረኞቹ ያልፈፀሙትን አስገድዶ የእምነት ቃል እንዳስፈረማቸው የማዕከላዊ ምንጮች አስታውቀዋል፡፡ ይሄም ለህዝቡና ለመገናኛ ብዙኃን እንዳይገለፅና ፍርድ ቤትም በቅሬታ መልክ እንዳይቀርብ ስለተፈለገ ነው ተከላካይ ጠበቆቹ እንዳይጎበኙ የተከለከሉት ሲሉ ምንጮች አስታውቀዋል፡፡ በዚህም የዛሬው ችሎት ያለጠበቃ ጭምር በዝግ ችሎት መካሄዱ የተጠቆመ ሲሆን፤ የቀጠሯቸው ቀንም ከላይ ከተጠቀሰው ውጭ እስካሁን ትክክለኛውን ከፍርድ ቤቱ ማረጋገጥ እንዳልተቻለ መረጃዎእ አመልክተዋል፡፡ ችሎቱን ለመታደም ወደ ስፍራው ያቀኑ ሰዎችም ፍርድ ቤቱ ግቢ ሲገቡ ከወትሮ በተለየ በፖሊሶች ከፍተኛ ፍተሻ፣ እንግልትና ወከባ እንደተፈፀመባቸው የዓይን እማኞች ገልፀዋል፡፡
