በእነ በቀለ ገርባ የሰብዓዊ መብት ጥሰት አቤቱታ ላይ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ አስተላለፈ

*ወህኒ ቤት ለአቶ በቀለ ገርባ የታዘዘውን መድሃኒት ፈልጌ ማግኘት አልቻልኩም ብሏል

Bekele Gerba

በእነ ጉርሜሳ አያኖ የክስ መዝገብ በሽብር ተከሰው በቂሊንጦ እስር ቤት የሚገኙት እነ በቀለ ገርባ (22 ሰዎች) የእስር ቤቱ አስተዳደር የሰብዓዊ መብት ጥሰት እያደረሰባቸው መሆኑን ሰኔ 15 ቀን 2008 ዓ.ም ለፍርድ ቤት ባቀረቡት አቤቱታ ላይ ችሎቱ ውሳኔ አሳልፏል፡፡

ሐምሌ 12 ቀን 2008 ዓ.ም የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት (ጉዳያቸውን ያይ የነበረው 19ኛ ወንጀል ችሎት እንደነበር ይታወሳል 19ኛ ችሎት ለሁለት ተከፍሎ አዲስ 4ተኛ ችሎት የሽብር ጉዳዮችን ማየት ጀምሯል) በተከሳሾች የቀረበውን አቤቱታና በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት አስተዳደር ሰኔ ቀን 2008 ዓ.ም የሰጠውን መልስ ተመልክቶ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡

ተከሳሾች ግንቦት 26 ቀን 2008 ዓ.ም ወደ ፍርድ ቤት ሲወሰዱ ድብደባ እንደደረሰባቸው፣ ልብሶቻቸው እንደተወሰዱባቸው፣ በጨለማ ቤት ስለመታሰራቸው፣ በህክምና የታዘዘን መድሃኒት እንዳያገኙ ስለመደረጋቸው፣ ቤተ መጽሐፍት እንዳልተሟላላቸው፣ በቤተሰቦቻቸው እንዳይጎበኙ ገደብ እንደተጣለባቸው፣ ገንዘብ እንደተወሰደባቸው እና ሌሎች የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት እንደደረሱባቸው አቤቱታ ማቅረባቸው የሚታወስ ሲሆን፣ የቂሊንጦ እስር ቤት አስተዳደር በበኩሉ አቤቱታቸውን ‹‹የተቋሙን ስም ለማጥፋት›› የቀረበ ነው ሲል አጣጥሎ መልስ መስጠቱ ይታወቃል፡፡

በዚህ ላይ ፍርድ ቤቱ ዛሬ ውሳኔውን አሳውቋል፡፡ በዚህ መሰረት በሀኪም የታዘዘን መድሃኒት ማግኘት አልቻልንም በሚል ተከሳሾች ላቀረቡት አቤቱታ ፍርድ ቤቱ የእስር ቤቱ አስተዳደር ተጠርጣሪዎቹ መድሃኒቱን እንዲያገኙ እንዲፈቅድ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ ተከሳሾች ድብደባ ደርሶብናል፣ ገንዘብም ተወስዶብናል በሚል ያቀረቡት አቤቱታን በተመለከተ ፍርድ ቤቱ ድርጊቱ ተፈጽሞ ከሆነ ወንጀል ስለሆነ አስፈላጊውን ማጣራት አድርገው ተከሳሾች በህግ ሊጠይቁ የሚገባቸው ስለሚሆን በዚህ የክስ መዝገብ ውሳኔ ሊሰጥበት አይችልም ብሏል፡፡
ተከሳሾች በጨለማ ክፍል መታሰራቸው ህግን ያልተከተለና የሰብዓዊ መብት ጥሰት መሆኑን በተመለከተ ያቀረቡት አቤቱታ ላይ ፍርድ ቤቱ ‹‹በማረሚያ ቤቱ በኩል ጨለማ ቤት የለም ተብሏል፤ ተከሳሾች ደግሞ ጨለማ ክፍል ታስረናል ብለዋል፡፡ ይህ ጉዳይ ማጣራትን የሚጠይቅ ስለሆነ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ጉዳዩን አጣርቶ ለሐምሌ 25 ቀን 2008 ዓ.ም አስተያየቱን ይስጥበት›› የሚል ውሳኔ አስተላልፏል፡፡

የቤተ መጽሐፍትና የቴሌቪዥን አለመሟላትን እና የቤተሰብ ጥየቃ ሰዓትን በተመለከተ በተከሳሾች የቀረበውን አቤቱታ ፍርድ ቤቱ ‹የማረሚያ ቤቱን አስተዳደራዊ አሰራር የሚመለከት ስለሆነ ውሳኔ አንሰጥበትም› በሚል አልፎታል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ አቶ ደጀኔ ጣፋ በቤተሰብ መጎብኘት ህገ መንግስታዊ መብታችን እንጂ የአስተዳደር ጉዳይ ነው ተብሎ የሚታለፍ እንዳልነበር በመጥቀስ በውሳኔው ላይ ቅሬታቸውን ለችሎቱ አሰምተዋል፡፡

ሌላ የተሰሙ አቤቱታዎች

ፍርድ ቤቱ ቀደም ብሎ በተከሳሾች ለቀረቡት አቤቱታዎች ውሳኔ ቢያሳልፍም ዛሬም ሌሎች አቤቱታዎች ቀርበውለታል፡፡ በዋናነት አቶ በቀለ ገርባ የታዘዘላቸውን መድሃኒት አለማግኘታቸውን በተመለከተ የቀረበ አቤቱታ ሲሆን፣ አቶ በቀለ መድሃኒት ከታዘዘላቸው ሁለት ወራት ቢቆጠርም መድሃኒቱን ማግኘት አለመቻላቸውን ገልጸዋል፡፡

የቂሊንጦ እስር ቤት አስተዳደር ዋና ኦፊሰር የሆኑት ተሾመ ስዩም በጽሁፍና በቃል በሰጡት መልስ እንደተመለከተው ለአቶ በቀለ ገርባ በሀኪም የታዘዘላቸው መድሃኒት በአስተዳደሩ ባለሙያዎች በመንግስትና በከነማ መድሃኒት ቤቶች ተፈልጎ ሊገኝ አልቻለም፡፡ ‹‹መድሃኒቱ ተፈልጎ አለመገኘቱንና የሚችሉ ከሆነ በቤተሰብ በኩል እንዲሞክሩ ለአቶ በቀለ ነግሬያቸዋለሁ›› ብለዋል ዋና ኦፊሰሩ፡፡

አቶ በቀለ ገርባ በበኩላቸው በኦፊሰሩ የተሰጠው መልስ ስህተት ነው ብለዋል፡፡ ‹‹ዛሬ ፍርድ ቤት እንደምቀርብ አውቀው የተዘጋጁበት መልስ ነው፡፡ ለእኔ የነገሩኝ ነገር የለም›› ብለዋል አቶ በቀለ፡፡ ፍርድ ቤቱ ይህን በተመለከተ ማረሚያ ቤቱ በቤተሰብ በኩል መድሃኒቱ ተገዝቶ እንዲገባ እንዲፈቅድ ማሳሰቢያ በመስጠት አልፎታል፡፡

ሌላው አቶ በቀለን ከሚኖሩበት አዳማ ከተማ ተመላልሰው ከሚጠይቋቸው ቤተሰቦቻቸው መካከል ልጃቸው ቦንቱ በቀለ ባለተገለጸ ምክንያት አባቷን በእስር ቤት እንዳትጠይቅና ምግብ እንዳታደርስላቸው መከልከሏን የአቶ በቀለ ጠበቃ ለችሎት በመግለጽ፣ ልጃቸው አባቷን እንድትጠይቅና ስንቅ እንድታቀብላቸው እንዲፈቀድላት ችሎቱን ጠይቀዋል፡፡ ችሎቱ ዋና ኦፊሰር ተሾምን ስለጉዳዩ ቢጠይቅም፣ ኦፊሰሩ ‹የማውቀው ነገር የለም፣ ግን ለሚመለከታቸው አካላት አሳውቃለሁ› የሚል መልስ ሰጥተዋል፡፡

በሌላ በኩል 22ኛ ተከሳሽ የስዋህሊኛ ቋንቋ አስተርጓሚ እንዲመደብላቸው በተደጋጋሚ አቤቱታ ማቅረባቸው የሚታወስ ሲሆን፣ ስዋህሊኛ አስተርጓሚ ኬንያ ኤምባሲ ጭምር ተፈልጎ ማግኘት እንዳልተቻለ ተገልጹዋል፡፡ በመሆኑም ተከሳሹ በመጠኑ እግሊዝኛ ቋንቋ ስለሚረዱ የእንግሊዝኛ አስተርጓሚ እንዲመደብላቸው በጠበቃቸው በኩል አሳስበዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ የመቃወሚያ ብይን ለማሰማት ለሐምሌ 25 ቀን 2008 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠቱ ይታወሳል፡፡

ምንጭ፡- EHRP

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: