Category Archives: Politics

ሶስቱ የሰማያዊ ፓርቲ እንስት አባላት በዓለም አቀፍ ደረጃ ዘመቻ እየተደረላቸው ነው

የአሜሪካ መንግስት ኦፊሳላዊ ድረ ገጽ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ጉዳይ አስተባባሪነት በዓለም ላይ ለተመረጡ 20 ሴት የፖለቲካ እስረኞች መካከል ሶስት የሰማያዊ ፓርቲ አባላት ዘመቻና ማስታወሻ እየተደረላቸው ነው፡፡

ከዛሬ 20 ዓመት በፊት ሴቶችን ለማብቃት፣ የጾታ እኩልነትን ለማስፈን እና የልጃ ገረዶችን ሰብዓዊ መብት ለማስጠበቅ የቤጂንግ መርሃ ጉዞ ተቀምጦ እንደነበር ይታወሳል፡፡ በእነዚህ 20 አመታት ልክ ከዓለም ሀገራት በፖለቲካ እስረኝነታቸው የተመረጡ 20 ሴት እስረኞችን ለማሰብ የሚደረገው ዘመቻ መነሻው ይህ መርሃ ጉዞ ነው፡፡

በዚህ መሰረት ከኢትዮጵያ ብሌን መስፍን፣ ንግስት ወንዲፍራው እና ሜሮን አለማየሁ የተካተቱ ሲሆን ከቻይና እንዲሁ ሦስት ሴት የፖለቲካ እስረኞች ተመርጠው እየታወሱ ነው፡፡

Blue member
http://www.humanrights.gov/freethe20
ምንጭ፡ ነገረ-ኢትዮጵያ

የዞን 9 ብሎገሮች ብይን በድጋሚ ለመስከረም 27 ቀን 2008 ዓ.ም. ተቀጠረ

ዛሬ ሰኞ ጳጉሜ 2 ቀን 2007 ዓ.ም. ለ36ተኛ ጊዜ፤ ለብይን ደግሞ ለ4ተኛ ጊዜ ተቀጥሮ የነበረው የዞን9 ብሎገሮች ጉዳይ በድጋሚ ለመስከረም 27 ቀን 2008 ዓ.ም. ተቀጠረ።

ዞን 9
በሶልያና ሽመልስ የክስ መዝገብ ለዛሬ በተደጋጋሚ የተላለፈው የብይን ፤ በድጋሚ ዳኞች አልተሟሉም በሚል ለ37ተኛ ጊዜ ተቀጥሯል።
በዳኞች አለመሟላት የተነሳ ችሎቱን ማስቻል አልችልም ብለው በቢሮ ተከሳሾችን እና ጠበቆችን የጠሩት ዳኛ ዘሪሁን ብይኑ ቢሰራም፤ ለማሳወቅ ሁሉም ዳኞች መገኘት ስላለባቸው ለመስከረም 27 ቀን 2008 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥተናል ብለዋል ።
ከአንድ ወር በኃላ በመደበኛው የፍርድ ቤት መከፈቻ የተቀጠረው ችሎት ተከሳሾች መከላከል ሳያስፈልጋቸው በነፃ ይሰናበቱ ወይስ ይከላከሉ የሚለውን ውሳኔ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል።
ምንጭ፡፤ ዞን 9 ማኀበራዊ ሚዲያ ገፅ

አቶ ማሙሸት አማረ ለውሳኔ ተቀጠሩ

“ምስክርነቱ የሐሰትና የተጠና ነው!” ጠበቃቸው

Mamushet Amare

አይ ኤስ አይ ኤስን ለመቃወም መንግስት ከጠራው ሰልፍ አንድ ቀን ቀድሞ ከለቅሶ ቤት ወደ ቤተ መንግስት ለተደረገውና ለዋናው (ለሚያዝያ 14 ቀን 2007 ዓ.ም) ሰልፍ አነሳስቷል በሚል ክስ የተመሰረተባቸው የቀድሞው የመላው ኢትዮጵያውያን አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ፕሬዘዳንት አቶ ማሙሸት አማረ ዛሬ ነሃሴ 20 ቀን 2007 ዓ.ም አራዳ ምድብ ችሎት ቀርቦ ለነሃሴ 22 ቀን 2007 ዓ.ም ለውሳኔ ተቀጠሯል፡፡ አቶ ማሙሸት አማረ ሚያዝያ 14 ቀን 2007 ዓ.ም በተካሄደው ሰልፍ ላይ ሁከትና ብጥብጥ ፈጥሯል በሚል ተከሶ የነበር ቢሆንም በወቅቱ ከምርጫ ቦርድ ጋር በነበረው ክርክር ሰልፉ ላይ አለመገኘቱን የሚያጋግጥ መረጃ በማቅረቡ በነፃ እንዲለቀቅ ተወስኖ ነበር፡፡ ነገር ግን ክሱ ወደማነሳሳት ተቀይሮ እስር ቤት እንዲቆይ ተደርጓል፡፡

አቶ ማሙሸት በአዲሱ ክስ የአቃቤ ህግን ምስክሮች ለመስማት ከ5 ጊዜ በላይ ፍርድ ቤት እንደተመላለሰ የተገለፀ ሲሆን በተለይ አንዱ ምስክር በፖሊስ ተይዞ እንዲመጣ ቢጠየቅም ፖሊስ ሳያስፈፅም ቀርቷል፡፡ ከአራቱ ምስክሮች መካከል ሶስቱ ዛሬ የመሰከሩ ሲሆን “አቶ ማሙሸት አማረ 300 ብር ከፍሎ ሰልፍ እንድንወጣ አድርጎናል” ሲሉ መስክረዋል፡፡

ይሁንና ምስክሮቹ ከማሙሸት ጋር በተገናኙበት ወቅት እንዲሁም ገንዘቡ ሲሰጣቸው፣ ሰልፉ ያለፈባቸውን ቦታዎችና ስለ ሌሎችም ጉዳዮች ሲጠየቁ ‹‹አላስታውሰውም›› ከማለት ባለፈ ዝርዝር የምስክርነት ቃል ሳይሰጡ ቀርተዋል፡፡ ከምስክሮቹ መካከል ሁለቱ አቶ ማሙሸትን ያስያዙ ደህንነቶች መሆናቸውን አቶ ማሙሸትና ጠበቃው በችሎቱ የገለፁ ሲሆን ምስክሮቹ በበኩላቸው ስራቸውን ሲጠየቁ ‹‹የግል›› እያሉ ከመመለስ ውጭ የመንግስት ስራ እንደማይሰሩ ተናግረዋል፡፡ ሆኖም የመንግስት ሰራተኛ መሆናቸውን የሚያሳይ መታወቂያ ሲጠየቁ ሊያሳዩ አልቻሉም፡፡ ከሶስቱ ምስክሮች መካከል አንደኛው ስራውን ሲጠየቅ “የግል” ብሎ የነበር ቢሆንም በመስቀለኛ ጥያቄ የቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 01 ጥቃቅንና አነስተኛ አመራር መሆኑን አምኗል፡፡

ከምስክሮቹ መካከል ሁለቱ የመኢአድ ደጋፊዎች መሆናቸውን ሲጠቅሱ አንደኛው አቶ ማሙሸት ባቀረቡበት የመስቀለኛ ጥያቄ ከምርጫ በኋላ የወጣቶች ሊግና የኢህአዴግ አባል መሆኑን አምኗል፡፡ የኢህአዴግ አባል ሆኖም ቢሆን መኢአድን እንደሚደግፍም ገልጾአል፡፡ ዳኛው “በሁለት ወር ውስጥ እንዴት ብለህ የወጣቶች ሊግ አባል መሆን ቻልክ?” ሲሉት መልስ ሳይሰጥ አልፎታል፡፡

የአቶ ማሙሸት አማረ ጠበቃ ሶስቱም ምስክሮች አብዛኛዎቹን ጉዳዮች እንደማያስታውሱ በመግለፃቸው የተጠና የምስክርነት ቃል መሆኑን ለችሎቱ አስረድተዋል፡፡ በተጨማሪም ከ7 አመት በላይ አዲስ አበባ ውስጥ ኖረው መስቀል አደባባይን ጨምሮ ሰልፉ አመራባቸው የተባሉትን ቦታዎች አናውቃቸውም ማለታቸው፣ መተዳደሪያ ስራቸውን መደበቃቸውና መታወቂያ ለማሳየትም ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ምስክርነቱ የሀሰት እንደሆነ ስለሚያረጋግጥ ደንበኛቸው በነፃ እንዲለቀቁ መጠየቃቸውን የነገረ ኢትዮጵያ ዘገባ አመልክቷል፡፡
አቶ ማሙሸት አማረ ሚያዝያ 14 ቀን 2007 ዓ.ም. አይ ኤ አይ ኤልን ለመቃወም በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ በተጠራው ሰልፍ ላይ ረብሻ አንስተዋል በሚል በተመሰረተባቸው ክስ ሰዓትና ቀን፤ ፓርቲያቸው መኢአድ በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለሌላ እንዲሰጥ መወሰኑን በመቃወም ፍርድ ቤት ክስ መስርተው ለክርክር በተጠቀሰው ሰዓትና ዕለት ችሎት ላይ እንደነበሩ የሚያስረዳ ደብዳቤ ፍርድ ቤቱ መፃፉ ይታወሳል፡፡

ኢ/ር ይልቃል ጌትነት በድጋሚ የሰማያዊ ሊቀመንበር ሆነው ተመረጡ

አንደኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን ለሁለት ቀናት በአዲስ አበባ ያደረገው ሰማያዊ ፓርቲ ኢ/ር ይልቃል ጌትነትን በድጋሜ የፓርቲው ሊቀመንበር አድርጎ መርጧል፡፡
ትናንት ነሀሴ 16/2007 ዓ.ም ጉባኤውን የጀመረው ፓርቲው በዛሬው ሁለተኛና የማጠቃለያ ውሎው የፓርቲውን ሊቀመንበር፣ የብሄራዊ ምክር ቤት አባላት እንዲሁም የኦዲትና ምርመራ ኮሚሽን አባላት ምርጫን አድርጓል፡፡
ኢ/ር ይልቃል ጌትነት በድጋሜ ለቀጣዩ ሦስት አመታት ፓርቲውን እንዲመሩ የተመረጡ ሲሆን፣ አምስት የኦዲትና ምርመራ ኮሚሽን አባላትም በጉባኤው ተመርጠዋል፡፡ ጉባኤው የፓርቲውን የብሄራዊ ምክር ቤት አባላትንም መርጧል፡፡

የሰማያዊ ፓርቲ የ2007 ዓ.ም. 1ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ

የሰማያዊ ፓርቲ የ2007 ዓ.ም. 1ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ

ለፓርቲው ሊቀመንበርነት ቀደም ብለው ፓርቲውን ለሁለተኛ ዙር ለመምራት ራሳቸውን በእጩነት ያቀረቡት ኢ/ር ይልቃል ጌትነት ብቻ ሲሆኑ፣ ጉባኤው ተጨማሪ እጩዎችን ለመቀበል ባቀረበው ሀሳብ መሰረት ራሱን በእጩነት የሚያቀርብ ይኖራል ተብሎ ቢጠበቅም በእጩነት ራሱን ያቀረበ አልነበረም፡፡
በመሆኑም በፓርቲው ህገ ደንብ መሰረት ጉባኤው ተጨማሪ እጩዎችን በጥቆማ ለማወዳደር ተገድዷል፡፡ በዚህም ጉባኤው ስድስት እጩዎችን የጠቆመ ቢሆንም አምስቱ ‹‹አንወዳደርም›› በማለታቸው ከተጠቆሙት መካከል አቶ ዮናታን ተስፋዬ ብቻ ለመወዳደር ፍላጎታቸውን ገልጸዋል፡፡ አቶ ዮናታን ተስፋዬ ፓርቲውን በህዝብ ግንኙነት ማገልገላቸው የሚታወስ ሲሆን ዛሬ ደግሞ ለሊቀመንበርነት መወዳደር ችለዋል፡፡
ለሊቀመንበርነት እጩ ሆነው የቀረቡት ሁለቱ እጩዎች በጉባኤው ፊት በተመደበላቸው ጊዜ ገደብ ውስጥ ራሳቸውን ካስተዋወቁና የምረጡኝ ቅስቀሳ ካደረጉ በኋላ ወደ ድምጽ መስጠት መግባት ተችሏል፡፡ በተሰጠው ድምጽ መሰረትም ኢ/ር ይልቃል ጌትነት ሰማያዊ ፓርቲን ለቀጣይ ሦስት አመታት እንዲመሩ በአብላጫ ድምጽ ተመርጠዋል፤ በዚህም ኢ/ር ይልቃል ከተሰጠው ድምጽ 136 ድምጽ አግኝተው ሲያሸንፉ፣ አቶ ዮናታን ተስፋዬ በበኩላቸው 60 ድምጽ በማግኘት ፉክክር አድርገዋል፡፡

ይልቃል ጌትነት ቃለ መሐላ ሲፈፅሙ

ይልቃል ጌትነት ቃለ መሐላ ሲፈፅሙ

የምርጫ ውጤቱ ይፋ መሆኑን ተከትሎ ንግግር ያደረጉት ተመራጩ ሊቀመንበር ኢ/ር ይልቃል ጌትነት ሰማያዊ ፓርቲ በሁለቱ ቀናት ጉባኤው ያነሳቸውን ችግሮች ለመፍታት እንደሚሰሩ ገልጸዋል፡፡
የሰማያዊ ፓርቲ ጠቅላላ ጉባኤ በዛሬው ውሎው ቀጣይ የፓርቲውን እንቅስቃሴ አስመልክቶም በጉባኤው አባላት አጠቃላይ ውይይት አድርጓል፡፡ በዚህም ፓርቲው ወደፊት ማደራጀት ላይ አተኩሮ መስራት እንደሚገባው ጉባኤው አጽንኦት ሰጥቶበታል፡፡
ጠቅላላ ጉባኤው የብሄራዊ ምክር ቤትና የፓርቲው ኦዲትና ምርመራ ኮሚሽን ያቀረቡት ሪፖርት ላይ ተወያይቶ ሪፖርቶቹ የፓርቲው ሰነድ ሆነው እንዲፀድቁ በአብላጫ ድምፅ ወስኗል፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ ለሁለት ተከታታይ ቀናት ያካሄደውን ጉባኤ ዛሬ ነሐሴ 17 ቀን 2007 ዓ.ም ማጠናቀቁን የነገረ ኢትዮጵያ ዘገባ አመልክቷል፡፡

ሰበር ዜና፤ በእስር ላይ የነበሩት የቀድሞ የአንድነት፣ የሰማያዊና የአረና ፓርቲ አመራሮች እና አንድ ሌላ ተከሳሽ በነፃ እንዲሰናበቱ ተወሰነ

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት፤ ዛሬ ነሐሴ 14 ቀን 2007 ዓ.ም. በዘለዓለም ወርቅአገኘሁ የክስ መዝገብ በፌደራሉ አቃቤ ህግ በሽብርተኝነት ከአንድ ዓመት ከአንድ ወር አካባቢ ታስረው ከነበሩት መካከል አራት የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች እና አንድ መምህር በነፃ እንዲሰናበቱ ወሰነ፡፡

Politicians
ከተመሰረተባቸው ክስ በነፃ እንዲሰናበቱ የተወሰነላቸው የአንድነት ፓርቲ የቀድሞ አመራሮች አቶ ሀብታሙ አያሌውና አቶ ዳንኤል ሺበሺ፣ የአረና ፓርቲ አመራር አቶ አብርሃ ደስታ፣ የሰማያዊ ፓርቲ አመራር አቶ የሺዋስ አሰፋና የቤተል ትምህርት ቤት መምህርና የሀገር አቀፍ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ሀገር አቀፍ አሸናፊ የነበረው መምህር አብርሃም ሰለሞን በነፃ የተሰናበቱት፣ የቀረበባቸው የሽብርተኝነት ክስ ከጥርጣሬ ባለፈ ተሳትፎአቸውን ማረጋገጥ ባለመቻሉ መሆኑን ፍርድ ቤቱ በውሳኔው አስታውቋል፡፡
በውሳኔው መሠረት አቶ ሀብታሙ የሚጠየቁበት ወይም ሌላ የሚፈለጉበት ጉዳይ ከሌለ በዛሬው ዕለት እንዲፈቱ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ አቶ አብርሃ ደስታ፣ አቶ ዳንኤል ሺበሺና አቶ የሺዋስ አሰፋ ከዚህ ቀደም ችሎት በመድፈር የተፈረደባቸውን ቅጣት እንዳጠናቀቁ እንዲፈቱ ሲል መወሰኑ ታውቋል፡፡

አብርሃም ሰለሞን

አብርሃም ሰለሞን

በዚሁ ክስ መዝገብ በተመሳሳይ ተከሰው ከነበሩት 10ሩ መካከል ከላይ የተጠቀሱት 5ቱ እንዲፈቱ ሲወሰን፤ ቀሪዎቹ 5ቱ እንዲከላከሉ እንተበየነባቸው ተጠቁሟል፡፡
በአሁን ወቅት በርካታ ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞች፣ ብሎገሮች እና የኃይማኖት ነፃነት ጠያቂዎች በእስር ላይ እንደሚገኙ የሚታወቅ ሲሆን፤ ባለፈው ሶስት ጋዜጠኞች፤ ተስፋዓለም ወልደየስ፣ አስማማው ኃይለጊዮርጊስ እና ኤዶም ካሳዬ እንዲሁም የዞን 9 ብሎገሮች መካከል ሁለቱ ዘለዓለም ክብረት እና ማህሌት ፋንታሁን ከተመሰረተባቸው ክስ በነፃ ሲሰናበቱ፤ የተፈረደባቸውን ፍርድ ከጨረሱት መካከል ጋዜጠኛ ርዕዮት አለሙ እና የኦፌኮ/መድረክ አመራር አቶ በቀለ ገርባ ከእስር መፈታታቸው አይዘነጋም፡፡