በኢትዮጵያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታወጀ፤ ህዝባዊ ተቃውሞውም አድማሱን እያሰፋ ቀጥሏል
(አዲስ ሚዲያ)በኢትዮጵያ ለተከታታይ አስር ወራት የፈጀው የፀረ አገዛዝ ህዝባዊ ተቃውሞ ተጠናክሮ መቀጠሉን ተከትሎ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ከትናንት ቅዳሜ መስከረም 28 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ ለ6 ወር ተግባራዊ የሆነ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማውጣቱን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ መስከረም 29 ቀን 2009 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ዝርዝር ጉዳይን በተመለከተ ወደፊት ይገለፃል ከማለት በስተቀር አጠቃላይ ይዘቱን በተመለከተ ያሉት ነገር የለም፡፡
በሌላ በኩል በጠቅላይ ሚኒስተሩ በሚመራ ኮማንድ ፖስት ስር የህግ አስከባሪዎችም መከላከያ ሰራዊት፣ ፌደራል ፖሊስ፣ የፌደራል የፀረ ሽብር ግብረ ኃይል፣ የአካባ ሚሊሻዎች እና ንብረት ጠባቂ የፀጥታ ኃይሎች የሚያካትት መሆኑን ደግሞ ጠቅላይ አቃቤ ህጉ አቶ ጌታቸው አምባዬ አብራርተዋል፡፡ አስቸኳይ አዋጁ በአጠቃላይ ሀገሪቱ ላይ ተግባራዊ መደረጉንም ጠቅላይ አቃቤ ህጉ አስታውቀዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ
በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አተገባበር መሰረት የተጠረጠረ ማንኛቸውም ሰው ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሊታሰር እንደሚችል፣ ቤቶችና አካባቢዎችም ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ብርበራ ሊካሄድባቸው እንደሚችልም እና ማንኛውም ዓይነት መገናኛ ብዙኃን ሊዘጋ እንደሚችልም ጠቅላይ አቃቤ ህጉ ይፋ አድርገዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ተቃውሞን ሊገልፁ የሚችሉ ምልክቶችን መጠቀምንም አዋጁ እንደሚከለክል፣ አዋጁን ተላልፎ የተገኘም ቅጣት እንደሚጠብቀው አስታውቀዋል፡፡
በተለይ ከህዳር 22 ቀን 2008 ዓ.ም. በኦሮሚያ እንዲሁም ከሐምሌ 5 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ በአማራ ክልል የተነሱ የፀረ አገዛዝ ህዝባዊ ተቃውሞች መንግሥት በወታደራዊ ኃይል ግድና፣ እስርና አፈና ለማስቆም መሞከሩን ተከትሎ ያለማቋረጥ ተቃውሞዎቹ ተጠናክረው መቀጠላቸው ስርዓቱን ስጋት ላይ ጥሎታል፡፡ በተለይ እንደ ማዕከላዊ ስታስቲክስ ኤጀንሲ መረጃ ከሆነ ከሀገሪቱን አጠቃላይ ህዝብና የቆዳ ስፋት 62% የሚሸፍነው የሀገሪቱ ህዝብ በአደባባይ የስርዓት ለውጥ እንደሚፈልግና በስልጣን ላይ ባለው ስርዓት መገዛት ለከፍተኛ ግድያ፣ እስር፣ በደልና ጭቆና እንደዳረገው በአደባባይ እየገለፀ ይገኛል፡፡ ለህዝቡ ጥያቄ የመንግሥት ምላሽ ግድያ፣ እስርና ማሰቃየት መሆኑ ደግሞ ህዝቡን የበለጠ እንዲቆጣና የተቃውሞ አድማሱን እንዲያሰፋ እንዳስገደደው ይነገራል፡፡
በተለይ ባለፈው እሁድ መስከረም 22 ቀን 2008 ዓ.ም. በኦሮሞ ማኀበረሰብ ዘንድ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠውና በርካታ ኢትዮጵያውያን የሚታደሙበት የኢሬቻ በዓል በደብረዘይት/ቢሾፍቱ ሆራ አርሰዲ ሐይቅ እየተከበረ ባለበት ወቅት ህዝቡ በሰላማዊ መንገድ አገዛዙ ላይ ተቃውሞውን ማሰማቱን ተከትሎ በተወሰደው ርምጃ አጠቃላይ ከ678 በላይ ሰላማዊ ዜጎች መገደላቸው በመላው ኢትዮጵያ የበለጠ ቅሬታን ፈጥሯል፡፡ በዚህም በኦሮሚያ ክልል የነበረው ህዝባዊ ተቃውሞ ወደ ህዝባዊ አብዮት መሸጋገሩንም የኦሮሞ መብት አራማጆች ይፋ ማድረጋቸውን ተከትሎ፤ ህዝቡ የአገዛዙ ሰዎች፣ ደጋፊዎችና ተባባሪዎች ናቸው የተባሉ ንበረቶች እና አገዛዙ የሚጠቀምባቸው የተለያዩ መንግሥታዊ ተቋማት ላይ ርምጃ መውሰዳቸው ታውቋል፡፡ የኦሮሞ ህዝባዊ ተቃውሞ አሁንም ተጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን፤ የመንግሥት ወታደራዊ የኃይል ርምጃም ተጠናክሮ በመቀጠል የበርካታ ሰላማዊ ዜጎች ህይወት ጠፍቷል፡፡
በተመሳሳይ በአማራ ክልል ባለው ህዝባዊ ተጋድሎ የቀጠለ ሲሆን፤ የመንግሥት ወታደራዊ እርምጃ በርካታ ሰላማዊ ዜጎችን ህይወት ቀጥፏል፡፡ በኦሮሚያ እና አማራ ክልል በተጨማሪ በደቡብ ክልል ኮንሶ ወረዳም ተመሳሳይ የፀረ አገዛዝ ህዝባዊ ተቃውሞ እና የመንግሥት የኃይል ርምጃ የቀጠለ ሲሆን፤ በዚህም በርካታ ሰላማዊ ዜጎች ተገድለዋል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ በዛው ደቡብ ክልል ጌዲዮ ዞን ባሉ ወረዳዎችና ከተሞች ከፍተኛ ተቃውሞና ግጭቶች ተቀስቅሰዋል፡፡ በዚህም የሰው ህይወት መጥፋትን ጨምሮ የበርካታ ሰላማዊ ዜጎች የንግድ ሱቆችና መኖሪያ ቤቶች ተቃጥለዋል፡፡ የተለያዩ የኃይማኖት ተቋማትም ላይ ጥቃት መሰንዘሩን ምንጮች አረጋግጠዋል፡፡
ከህዳር 2008 ዓ.ም. ጀምሮ አጠቃላይ በኦሮሚያ እና በአማራ ክልል እንዲሁም በደቡብ ክልል ኮንሶ ወረዳ ባሉ ህዝባዊ ተቃውሞዎች በመንግሥት ወታደራዊ የኃይል ርምጃ የተገደሉ ሰላማዊ ዜጎች ቁጥር ከ 1,420 በላይ መድረሳቸውን መረጃዎች አመልክተዋል፡፡ መንግሥት በበኩሉ ህዝባዊ ተቃውሞቹ በውጭ ኃይል የተቀነባበሩ ናቸው በማለት ለመሸፋፈን ቢሞክርም ከህዝቡ፣ ከመብት አራማጆችም ሆነ ከዓለም አቀፉ ማኀበረሰብ ተቀባይነት አላገኘም፡፡
የኦሮሞ ቻርተር ጉዳይ ወዴት ያደርሰናል?

ሰማሀኝ ጋሹ (ዶ/ር)
የኦሮሞ ቻርተርና ወታደራዊ ክንፍ መቋቋምን በተመለከተ የሚመክር በአትላንታ የሚካሄድ ስብሰባ ዜና እና ሰነድ ይፋ ከተደረገ በሗላ በተለያዩ ወገኖች ዘንድ ጥርጣሬና ጥያቄ አስነስቷል። ጋዜጠኛ ሳዲቅ አህመድ አቶ ጃዋርንና ፕ/ር ህዝቄልን የኦሮሞ ቻርተርን በተመለከተ ውይይትም አካሂዷል። በውይይቱ ወቅት የመገንጠል ጥያቄዉን በተመለከተ ጥሩ ማብራርያ የተሰጠ ቢሆንም አሁንም በርካታ መልስ የሚሹ ጉዳዮች አሉ። በተለይ አትላንታ ይካሄዳል ተብሎ የታሰበዉን ስብሰባ በተመለከተ የወጣዉ መግለጫ በብዙዎች ዘንድ ያልተጠበቀ ነገር ነዉ። በጎንደር በተካሄዳዉ የተቃዉሞ ሰልፍ ወቅት ህዝቡ ‘ የኦሮሞ ደም የኛ ደም ነዉ’ ፥ ‘ በቀለ ገርባ መሪያችን ነዉ’ በማለት ለኦሮሞ ህዝብ የተቃዉሞ እንቅስቃሴ ያለዉን አጋርነት ከገለፀ በሗላ በህዝቦች መካከል የነበረዉንና በህወሓት ለዘመናት የሚዘወረዉን የከፈፍልህ ግዛ (divide and conquer) ፖለቲካ በማዳከም ከፍተኛ የትግል አንድነት ያመጣ መሆኑ ይታወቃል። ህዝቡ ይህንን የተፈጠረዉን አንድነት የሚያጠናክር የፖለቲካ ሀይሎች የጋራ መድርክ ሲጠብቅ የተናጥል ስብሰባ መጠራቱ በብዙዎች ዘንድ ጥርጣሬ መጫሩ የሚጠበቅ ነዉ። ከዚህ አኳያ የተፈጠረዉን የህዝብ አንድነት ሊያጠናክር የሚችል ስራ ላይ ማተኮር ሲገባ የተናጠል የስብሰባ ጥሪ መጠራቱ በጋራ ትግሉ ላይ የራሱን ተፅእኖ ማሳደሩ የማይቀር ነዉ።
ከዚህ የከፋዉ ደግሞ የቀረበዉ ሰነድ ስለ ህዝቡ የጋራ ትግልና የደረሰበትን ደረጃ ጨርሶ አያነሳም። ሰነዱ ወደፊት የኦሮሞ ህዝብ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ስርአት ዉስጥ የሚኖረዉን ሚና በተመለከተም ምንም አይነት ፍንጭ ያልሰጠ ሲሆን የኦሮሞን ህዝብ በደሴትነት ተነጥሎ የተቀመጠ ያስመስለዋል። እንደዉም ሰነዱ የኦሮሞ ህዝብ ከኢትዮጵያ ጋር ያለዉን ግንኙነት የቅኝ ግዛት አድርጎ ያቀርበዋል። የቅኝ ግዛት ትንታኔዉን (colonial thesis) በርካታ የኦሮሞ ምሁራንና ፖለቲከኞች እንደማይደግፉት እየታወቀ ሁሉንም የኦሮሞ መሪዎች ላማሰባሰብ ያለመ ሰነድ ለምን ያአንድ ወገን አቋም ብቻ ለማንፀባርቅ እንደፈለገ ግልፅ አይደለም። የኦሮሞ ህዝብ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ያለዉን ግንኙነት የቅኝ ግዛት ጥያቅ እንዳልሆነ የሚያምኑትን የኦሮሞ ፖለትከኞችና ምሁራን የሚያገል ያሰመስለዋል። የኦሮሞን ህዝብ ቅኝ እንደተገዛ አድርጎ ማቅረቡ የኦሮሞ ህዝብ ከሌላዉ ህዝብ ጋር ያለዉን የባህልና የታሪክ ትስስርና የኦሮሞ ህዝብ ለኢትዮጵያ አንድነትና ህልዉና ያበረከተዉን አስተዋፅኦ የሚያሳንስ ነዉ። ከዚህም በተጨማሪ ይህን አይነቱ ትንታኔ አንዱን ማህበረሰብ ጨቋኝ ሌላዉን ተጨቋኝ በማድረግ የሚቀርበዉን የታሪክ ትንታኔ ህያዉ ሆኖ እንዲቆይ የሚፈልግ ያስመስለዋል። ይህም እስካሁን የሄድንበትን የጋራ አለመተማመን (mutual suspicion) በማስቀጠል ልንፈጥረዉ ለምናስበዉ ዴሞክራሲያዊ ስርአት እንቅፋት ይሆናል።
በተለይ በኢትዮጵያን አንድነትና በግለሰብ መብት ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ ስርአት እንዲቋቋም የሚፈልጉ ዜጎችን የቀድሞዉ ስርአት ናፋቅዎችና ምኒልካዉያን እየተባለ መስደብ የተለመደ ነዉ። ያሁኑን ተዉልድ የፖለቲካ አስተሳሰብ መተቸት ካስፈለገ በራሱ በትዉልዱ አስተሳሰብ ላይ ተመስርቶ መተቸት ሲገባ ከቀደሙት ስርአቶች ጋር በማያያዝ አንገት ለማስደፋት የሚደረገዉ እንቅስቃሴ ያደባባይ ሚስጥር ነዉ። የዚህ ፅሁፍ አቅራቢ ከወራት በፊት ያደረገዉን የሬድዮ ዉይይት አስመልክቶ የቀድሞዉ ስርአት ናፋቂ የሚል ስድብና ዛቻ የኦሮሞ አክቲቪስቶች ነን ከሚሉ ወገኖች አስተናግዷል። ለዚህም ነዉ የአማራ ወጣቶች ሁሉም የብሄር ድርጅቶች አማራን በጠላትነት የሚፈርጁ በመሆኑ ተደራጅተን እራሳችንን እንከላከል እያሉ ያሉት። ምንም እንኳን ያለፈዉን ታሪካችንን በተመለከተ ብሄራዊ መግባባት ላይ መድረስ አስቸጋሪ ሊሆን ቢችልም እንዲህ አይነት የታሪክ ትንታኔዎችን ለፖለቲካ ፍጆታ ባለመጠቀም የተሻለ የፖለቲካ ድባብ ለመፍጠር ጥረት እንዳልተደረገ ግን ከቀረበዉ ሰነድ መረዳት ይቻላል።
ከዚህም በጠጨማሪ የቀረበዉ ሰነድ ባለፉት አስርተ አመታት የብሄረሰቦችን እኩልነት ለማምጣት የተሄደበትን መንገድ፥ ዉጤቱንና ችግሮቹን ሳያነሳ የኦሮሞ ህዝብ ከዛሬ አርባ አመት በፊት በነበረበት ሁኔታ እንዳለ አድርጎ ያቀርበዋል። ከሁሉም ብሄረሰቦች የተወጣጡ ወጣቶች በተማሪዎች እንቅስቅሴ ወቅት ያነሱት የመሬት ላራሹና የራስን እድል በራስ የመወሰን ጥያቄ በደቡብ ኢትዮጵያ የነበረዉን የጭሰኝነት ስርአት ያስወገደ ሲሆን ይህም ለኦሮሞ ህዝብ ታላቅ ለዉጥ አምጥቷል። ደርግም ሆነ ወያኔ ስታሊናዊ በሆነ መንገድ ችግሮቹን ለመፍታት የሄዱበት መንገድ ዉጤቱ አመርቂ ባይሆንም ሙከራዎች ግን ተደርገዋል። ይህ ሁሉ የፖለቲካ ለዉጦች በተካሄዱበት ሀገር አሁንም ቅኝ እንደተገዛን ነን የሚል እድምታ ያለዉ አቀራረብ በጣም ጨለምተኛና ካላፈዉ ስህተቶች ተምሮ የቀረዉን የእኩልነት ጥያቅ ለማሳካት በሚያስችል መልኩ አለመቀረፁ በኢትዮጵያ ያለዉን አስቸጋሪ የፖለቲካ ሁኔታ ለመፍታት ያለዉን ቁርጠኝነት ዉሱን ያስመስለዋል።
የኦሮሞ መሪዎች ስብሰባ ያስፈለገበትን ምክንያት አቶ ጃዋር ሲያስረዳ ወደፊት ለሚደረገዉ የሽግግር ወቅት እያንዳንዱ ማህበረሰብ የራሱን ቻርተር አዘጋጅቶ መምጣት ስላለበት የኦሮሞን ቻርተር ለማዘጋጀት በማስፈለጉ ነዉ ይላል። ለዚህም የደቡብ አፍሪካዉን ብሄራዊ ኮንግረስና የህንዱ ጃዋራላል ኔህሩ በትግል ወቅት እንዲህ አይነት ቻርተር አዘጋጀተዉ ነበር ሲል ያስረዳል አቶ ጃዋር። እያናንዳንዱ ማህብረስብ የራሱን ቻርተር አዘጋጅቶ ይምጣ ከተባለ ሁሉም ብሄረሰቦች አንዳንድ ቻርተር በማዘጋጀት ሲመጡ ቢያንስ ከ 80 ያላነሱ ቻርተሮች ተዝጋጅተዉ ሊቀርቡ ነዉ ማለት ነዉ( ያዉም እያንዳንዱ ማህበረሰብ በአንድ ድርጅት ይወከላል ብለን ካሰብን ነዉ።) እንዲህ ያለ ሁኔታን እንዲኖር መፈለግ አላማዉ ዴሞክራሲያዊ ስርአት ወይስ የባቢሎንን ግንብ ለመገንባት ነዉ? ሁሉም ብሄር የራሱን መብት እንዲከበር በሚል በሚያደርገዉ ፍላጎት ሁሉንም የሚያረካ መፍትሄ ማግኘት የሚክብድ ከመሆኑም በተጨማሪ የፈለገዉን ያላገኘዉ ወገን ‘የራሴን እድል በራሴ’ እወስናለሁ ወደሚል ሌላ ዙር ግጭት ይገባል። በተለይ ወታደራዊ ክንፍ ያለዉ የብሄር ድርጅት የሚበረታታ ከሆነ በጉልበት የፈለገዉን ለማድረግ ማንገራገሩ የማይቀር ነዉ። ወያኔም በ1983 ዓም ባደረገዉ የሽግግር መንግስት ምስረታ ወቅት በብሄር የተደራጁትን ብቻ ተቀብሎ ህብረ ብሄር የሆኑትን ግን አልቀበልም ነበር ያለዉ። ለዚህም የተማመነዉ የነበረዉን ጉልበት ነዉ። ኦነግንም ከሽግግሩ መንግስት እንዲወጣ ያደረገዉ ይሄዉ የወያኔ እብሪተኝነት ነዉ። አሁንም በብሄር ተደራጅታችሁ የራሳችሁን ቻርተር አዘጋጅታችሁ ኑ ማለት ተመሳሳይ አካሄድ ያለዉ ነዉ። በርካታ ማህበረሰቦችም በተለያየ ምክንያት ተደራጅተዉ ቻርተር አዘጋጅተዉ ላይቀርቡ ይችላሉ። በዚህ ጊዜ የነዚህ ማህበረሰቦች እድል ቻርተር አዘጋጅተዉ በመጡት ሊወሰን ነዉ ማለት ነዉ? ይህስ አካሄድ ወያኔ በ1983 ካደረገዉ በምን ይለያል? ወታደራዊ ክንፍ ያላቸዉ የፖለቲካ ሃይሎች እኛ ባልነዉ ካለተስማማችሁ ዞር በሉ ቢሉ ዋስትናዉ ምንድን ነዉ? አልሸሽም ዞር አሉ እንደሚባለዉ ተመልሶ ወደ ግጭት አያስገባንም ወይ?
አቶ ጃዋር ያቀረባቸዉ የደቡብ አፍሪካ፤ ህንድና ቱኒዝያ ምሳሌዎች አሁን ከተጠራዉ የኦሮሞ የነፃነት (freedom) ቻርተር ጉዳይ በጣም የተለዩ ናቸዉ። በነዚህ ሃገሮች የቀረቡት የነፃነት (freedom) ቻርተሮች ሆነ ድርድሮች ሃገራዊና የሁሉንም ማህበረሰብ ፍላጎት የሚያንፅባርቁ እንጂ የአንድ ብሄርን ብቻ የሚመለከቱ አልነበሩም። እንዲሁም በህንድ የተካሄደዉ የፀረ ቅኝ ግዛት ትግልና በደቡብ አፍሪካ የተካሄደዉ የፀረ አፓርታይድ ትግል አሁን ኢትዮጵያ ዉስጥ ካለዉ የፖለቲካ ሁኔታ ጋር ያላቸው ዝምድናና እና ልዩነት በግልፅ አልቀረበም ። የምናቀርባቸዉ ምሳሌዎች ተገቢ ትርጉማቸዉን የያዙ ቢሆኑ የምናቀርበዉን ሃሳብ ተአማኒነት ያጠናክረዋል። አቶ ጃዋር ስለ ቱኒዝያ የተናገረዉም እኛ እየሄድንበት ካለው ጋር የሚገናኝ አይደለም። ከሌሎች አብዮት ከተካሄደባቸዉ የአረብ ሃገራት በተለየ የተሻለ የፖለቲካ ሽግግር በቱንዝያ የተፈጠረዉ እንደ ሊቢያና ሶርያ በሃይማኖትና በጎሳ ለመከፋፈል ባለመፍቀዳቸዉ ነዉ። ወታደራዊ ክንፍ ያላቸዉ የብሄር ድርጅቶችን የምናበረታታ ከሆነ ግን ለጊዜዉ በአንድ ጠላት ላይ ሲያተኩሩ ልዩነት የሌላቸዉ የሚመስሉ የፖለቲካ ህይሎች ያ ጠላት ከስፈራዉ ሲነሳ እርስ በርሳቸዉ መበላላታቸዉ የማይቀር ነዉ። ሊብያ ዉስጥ በተካሄደዉ አብዮት ወቅት ሁሉም ጎሳዎች ጋዳፊን ለመጣል ሰምና ወርቅ ሆነዉ ከሰሩ በሗላ አሁን ሁሉም በየፊናዉ ወታደራዊ ቀጠና አቋቁሞ እየተጋጨ ሲሆን ማዕከላዊ መንግስት በስምምነት ለመመስረት አልቻሉም።
በእዉነት የኢትዮጵያን የፖለቲካ ችግሮች ለመፍታት ቅንነቱና ቁርጠኝነቱ ካለ እንደ ኑክልየር ሳይንስ ዉስብስብ ስላልሆነ 80 ቻርተር ማዘጋጀት አያስፈልገዉም። የኢትዮጵያ የፖለቲካ መሰረታዊ ችግሮች እንዴት ብሄራዊ አንድነትንና የብሄር መብትን፥ የግለሰብና የቡድን መብትን አጣጥመን እንቀጥል፥ እንዴት ብሄራዊ መግባባትን እንፍጠር፥ ዴሞክራሴያዊ ባህልና ተቋማት እንዴት እንገንባና ማህበራዊና ኤኮኖምያዊ ፍትህ እንዴት እናረጋግጥ የሚሉት ናቸዉ። እነዚህን የፖለቲካ ጥያቄዎች ለመመለስ ዋናዉ መነሻ የተናጥል አካሄድን በተቻለ መጠን በማስቀረት ሁሉም የፖለቲካ ሃይሎች በጋራ የሚመክሩበትን ሁኔታ ማመቻቸት ነዉ። ነገር ግን አሁንም የሽግግር ሂደቱን በበላይነት ለመቆጣጠር የሚካሄደዉ ፉክክር ስር የሰደደዉን የፖለቲካ ሃይሎች አለመተማመን እንዲቀጥል የሚያደርገዉ ከመሆኑም በተጨማሪ የግጭትንና የእኔ አውቅልሃለሁን የቆየ የፖለቲካ ባህል ለመለወጥ የሚኖረዉን እድል ያደበዝዘዋል።
በዛሬው ኢሬቻ ክብረ በዓል ላይ ከታደሙት መካከል ከ250 በላይ ሰላማዊ ዜጎች ተገደሉ
ዛሬ እሁድ መስከረም 22 ቀን 2009 ዓ.ም. ከአዲስ አበባ ደቡብ ምስራቅ 40 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ደብረዘይት/ቢሾፍቱ ከተማ በሚገኘው ሆራ ሐይቅ አካባቢ በኦሮሞ ማኀበረሰብ እና በሌሎች ኢትዮጵያውያን እንደቀደሙ ዓመታት ሁሉ ጊዜውን ጠብቆ ዛሬ እየተከበረ ባለው የኢሬቻ ክብረ በዓል ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ድረስ በግማሽ ቀን ብቻ ከ250 በላይ የበዓሉ ታዳሚ ሰላማዊ ዜጎች በገዥው ስርዓት በተወሰደ ወታደራዊ የኃይል ርምጃ መገደላቸው ተጠቆመ፡፡
በስፍራው ተገኝተው የነበሩ የዓይን እማኞች እና የሆስፒታል ምንጮች ከሆነ ከአንድ ሺህ ያላነሱ ንፁሃን ዜጎችም ቆስለው በደብረዘይት እና አዲስ አበባ በሚገኙ ሆስፒታሎች ለህክምና እርዳታ መላካቸው ታውቋል፡፡
ዛሬ ሰላማዊ ዜጎች ላይ በአንድ ቀን ብቻ በመንግሥት የተፈፀመው ግድያ ከህዳር ወር 2008 ዓ.ም. ጀምሮ በተለይ በኦሮሚያ ከ650 በላይ፣ በአማራ ከሐምሌ 2008 ዓ.ም. ጀምሮ ከ200 በላይ ከተገደሉ ንፁሃን በተጨማሪ የተፈፀመ ዘግናኝ ግድያ ነው፡፡ በተለይ በበዓሉ ስፍራ የነበሩ የዓይን እማኞች ከሆነ የተገደሉ ዜጎች ቁጥር ከተጠቀሰው በላይ ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል፡፡ በዘንደሮው በዓል ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢ የመጡ የበዓሉ ታዳሚዎች ቁጥር እስከ 2 ሚሊዮን እንደሚደርስ ተገምቷል፡፡
መንግሥት በሚቆጣጠራቸው መገናኛ ብዙኃን እና በቃል አቀባይ ጽህፈት ቤቱ በኩል በሰጠው መግለጫ ሟቾቹ በተፈጠረ ግርግር እንደሆነ ቢያሳውቅም፤ የዓይን እማኞች በበኩላቸው በበዓሉ ላይ ወጣቶች እጃቸውን በማጣመር ከዚህ ላለፉት 10 ወራት መንግሥት በዜጎች ላይ የፈፀመውን ግድያ እና እስር የሚያወግዝ ተቃውሞ እያቀረቡ ባሉበት ሰዓት በገዥው ስርዓት ወታደሮች አስለቃሽ ጢስን እና ተከታታይ ተኩስ በህዝቡ ላይ እንደተከፈተ ተናግረዋል፡፡ በጥይት ከተገደሉት በተጨማሪ ከተኩሱ ለማምለጥ የሞከሩ ሰዎችም በጥልቅ ጉድጓድ ውስጥ ገብተው የሞቱ፣ የተገዱና የተረፉም እንዳሉ ለማወቅ ተችሏል፡፡
መንግሥት ለንፁሃን መሞት ምክንያቱ አመፅ ቀስቃሾ በፈጠሩት ግርግር በመረጋገጣቸውና ገደል ውስጥ በመግባታቸው ነው ቢልም፤ የበዓሉ ታዳሚዎች በበኩላቸው የበዓሉን ድባብ በማጥፋ ወታደሮች የበዓሉ ታዳሚ ሰላማዊ ዜጎች ላይ ተኩስ በመክፈት ግድያው ሆን ተብሎ የተፈፀሙውና ንፁሃን እንዲሞቱ የተደረገው በገዥው ስርዓት እንደሆነ ከጉዳቱ የተረፉ እማኞች ተናግረዋል፡፡

የኦሮሞ ማኀበረሰብ መብት አራማጆችን ጨምሮ ሌሎች ኢዮጵያውያን የመብት አራማጆች የተገደሉ በርካታ ዜጎችን ምስልና ቪዲዮ በማኀበራዊ ሚዲያ ሲያሰራጩ ተስተውሏል፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ በህዝብ ክብረ በዓል ላይ የዛሬውን ያህል ዜጎች በመንግሥት ወታደራዊ ኃይሎች ሰላማዊ ዜጎች ላይ በወሰዱት ርምጃ ሲገደሉ የመጀመሪያው ነውም ተብሏል፡፡
የኢሬቻ በዓል በኦሮሞ ማኀበረሰብ ዘንድ ጥንታዊ የሆነ ፈጣሪን በጋራ የማመስገን በዓል ሲሆን፤ ከኦሮሞ ማኀበረሰብ በተጨማሪ ከተለያዩ አካባቢዎች ሌሎች ኢትዮጵያውያን በብዛት የሚታደሙበትና የሚያከብሩት ታላቅ ህዝባዊ በዓል መሆኑ ይታወቃል፡፡
በተያያዘ ዜና፤ የኤሬቻ በዓል ጅምላ ግድያን ተከትሎ በአምቦ እና አወዳይ ከተማ ህዝባዊ ተቃውሞ የተቀሰቀሰ ሲሆን፤ በሁለቱም ከተሞች መንግሥት ወታደሮች የኃይል ርምጃ መውሰድ መጀመራቸው ተገለፀ፡፡ በተወሰደው ርምጃ ምን ያህል ዜጎች ጉዳት እንደደረሰባቸው ለጊዜው ማወቅ አልተቻለም፡፡
የአምቦ ዩኒቨርስቲ መምህር እና ብሎገር ስዩም ተሾመ ታሰረ
ስዩም ተሾመ

በአምቦ ዩኒቨርስቲ ቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ወሊሶ ግቢ መምህር እና ብሎገር ስዩም ተሾመ ታሰረ፡፡ መምህር እና ብሎገር ስዩም ተሾመ ከሚኖርበትና ከሚሰራበት ወሊሶ ከተማ ዛሬ ቅዳሜ መስከረም 21 ቀን 2009 ዓ.ም. በፀጥታ ኃይሎች ታፍኖ ከተወሰደ በኋላ መታሰሩ ተጠቁሟል፡፡ ስዩም ተሾመ በአምቦ ዩኒቨርስቲ ወሊሶ ግቢ የማናጅመንት ትምህርት ክፍል ኃላፊ እና መምህር ሲሆን፤ ከማኀበራዊ ሚዲያ በተጨማሪ በ ”ኢትዮቲንክታንክ” እና የገዥው ስርዓት ደጋፊ እንደሆነ በሚታወቀው ”ሆርንአፌይርስ” ድረ-ገፅ ጭምር በመፃፍ ይታወቃል፡፡
በተለይ ከህዳር 2008 ዓ.ም. ጀምሮ በመንግሥት እና በህዝቡ መካከል በተፈጠረው አለመግባባት ችግሮች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ እና ሌሎች ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የተለያዩ መፍትሄ ሊሆኑ ይችላሉ ያላቸውን ምክረ ሐሳቦችን በመሰንዘርም ይታወቃል፡፡
10ኛ ወሩን ባስቆጠረው የኦሮሚያ ህዝባዊ ተቃውሞን ተከትሎ በአማራ እና በደቡብ ኮንሶ ተከታታይ ህዝባዊ ተቃውሞች መቀጠላቸውን ተከትሎ ከ820 ያላነሱ ሰላማዊ ዜጎች በፀጥታ ኃይሉ ወታደራዊ ርምጃ ሲገደሉ፤ በሺህዎች የሚቆጠሩ ቆስለው፣ በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ታፍነው ታስረዋል፡፡ ከተገደሉ፣ ከቆሰሉና ከታሰሩት መካከል ህፃናት እና አዛውንት፣ መምህራን፣ ጋዜጠኞችና ብሎገሮች፣ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች እና ተማሪዎች ይገኙበታል፡፡ በተለይ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ድረስ፤ በተለያዩ ኦሮሚያ እና አማራ ክልል ከተሞችና ወረዳዎች የመንግሥት ግድያና እስር እንደቀጠለ ነው፡፡
የኮንሶ ብሔረሰብ የዞን ምሥረታ ጥያቄ ከሕግ አንጻር ሲፈተሸ

ውብሸት ሙላት
ኮንሶ፣ በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል በሰገን ሕዝቦች ዞን ውስጥ የምትገኝ ወረዳ ናት፡፡ ቀደም ሲል ግን ልዩ ወረዳ ነበረች፡፡ ኮንሶ አስተዳደር እርከን ብቻ ብቻ አይደለችም፤ብሔረሰብም ጭምር እንጂ! የሰገን ሕዝቦች ዞን ደግሞ በፊት የኮንሶ፣ የደራሼ፣ የአማሮ እና የቡርጂ ልዮ ወረዳዎች የነበሩትን በማጠቃለል የተመሠረተ ነው፡፡
በደቡብ ክልል ሕገ-መንግሥት መሠረት ልዩ ወረዳ ከዞን ጋር አቻ ሥልጣን አለው፡፡ ተጠሪነቱም ቀጥታ ለክልሉ ነው፡፡ ልዩ ወረዳ፣ ብዙ ጊዜ በአንድ ብሔር ብቻ ስለሚመሠረት የአንድ ብሔር ብቻ አባላት ያሉበት የወረዳ ምክር ቤት ይኖረዋል፡፡ የራሱ የልዩ ወረዳው የሥራ ቋንቋ እንዲኖረው መወሰን ይችላል፡፡ በዞን ደረጃ የሚኖሩትን መንግሥታዊ መዋቅሮችን በወረዳው በማቋቋም በርካታ የብሔረሰቡ ተወላጆች የሥራ ዕድል እንዲኖራቸው ያስችላል፡፡
መደበኛ ዞኖች ሕግ አውጪ የላቸውም፡፡ የዞን ሥራ አስፈጻሚዎችም የሚሾሙት በቀጥታ በክልሉ ሥራ አስፈጻሚ በመሆኑ የክልል ውክልና እንጂ በምርጫ የተገኘ ሥልጣን አይደለም፡፡ ወረዳዎችም ቢሆኑ ለአስተዳደር ቅልጥፍና፣ ድጋፍና ክትትል ሲባል በተጨማሪነት ለዞን ተጠሪነት ያለባቸው ቢሆንም ይህ ሁኔታ የመነጨው የክልሉ አስፈጻሚ አካላት በሚሰጠው ውክልና ላይ ተመሥርቶ እንጂ ሕገ-መንግሥታዊ መነሻ የለውም፡፡ ለዚያም ነው የወረዳ አስተዳዳሪዎችና ከንቲባዎች በዞን አስተዳዳሪዎች የማይሾሙትም ሆነ የማይወርዱት፡፡
በልዩ ዞኖች ግን የብሔረሰብ ምክር ቤት ስላላቸው፣ የዳኝነት መዋቅርና ሹመት በክልል ደረጃ ቢከናወንም እንኳን ከዞኑ የሚጠቆሙትና የሚሾሙት ዳኞች ላይ አስተያየት የመስጠት መብት አላቸው፡፡
የኮንሶ ብሔረሰብ፣ የዞንነት ጥያቄ በማንሳት ተቃውሞ ከጀመረ አንድ ዓመት አለፈው፡፡ ከተቃውሞው ጋር በተያያዘ ቀላል የማይባል የሰው ሕይወት ጠፍቷል፡፡ የክልሉ የኮሚኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ሓላፊ ለአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ በቅርቡ በተናገሩት መረጃ እንኳን ከ1500 ቤቶች በላይ ተቃጥለዋል፡፡ ከአንዳንድ መገናኛ ብዙኃን እንደሚሰማው የዞንነት ጥያቄው ካልተሳካ ወደ ኦሮሚያ ክልል የመካለል ጥያቄንም በአማራጭነት ሕዝቡ እያነሳ ነው፡፡
ይህ ጽሑፍ ዞን የሚመሠረትበትን ሕጋዊ አሠራር ይፈትሻል፡፡ የራስን ዕድል በራስ ከመወሰን መብት ጋር የሚኖረውን ግንኙት በማየት የኮንሶ ብሔረሰብ ጥያቄ ከክልሉ እና ከፌደራሉ ሕገ-መንግሥት እንዲሁም ከሌሎች አግባብነት ካላቸው ሕጎች አንጻር ዳሰሳ ያደርጋል፡፡ እግረ-መንገዱንም አንድ ወረዳ ወይንም ሌላ አስተዳደረዊ መዋቅር ከአንድ ክልል ወደ ሌላ ክልል መጠቃለል የሚችልበትን ሕገ መንግሥታዊ ሁኔታም ካለ ምጥን ፍተሻ ያደርጋል፡፡
ኮንሶ ከሌሎች ዞኖች ጋር በሕዝብ ብዛት ስትነጻጸር፤
የኮንሶን የዞን ምሥረታ ጥያቄን በአግባቡ ለመረዳት በኢትዮጵያ ውስጥ ካሉት ዞኖች ጋር፣ በ1999 ዓ.ም. የተደረገውን የሕዝብና ቤት ቆጠራን መሠረት በማድረግ እናነጻጽራለን፡፡ በዚህ የሕዝብና ቤት ቆጠራ ውጤት መሠረት የኮንሶ ልዩ ወረዳ ወደ 235 ሺህ የሚጠጋ ሕዝብ ነበረው፡፡ የዛሬ አስር ዓመት የነበረው የወረዳው ሕዝብ ብዛት ማለት ነው፡፡ ከወረዳው ውጭም የሚኖሩትን ጨምሮ፣ የኮንሶ ብሔረሰብ ብዛት ከ250 ሺህ በላይ ነው፡፡ ዞን ለመመሥረት በአንድ አካባቢ መኖርን ስለሚጠይቅ፣ ለዞን ምሥረታ ጥያቄው ተገቢው ቁጥር መኖር ቅድመ-ሁኔታ ነው ማለት ይቻላል፡፡
የኮንሶ ወረዳ ሕዝብ፣ ከሀረሪ ክልል ሕዝብ ይበልጣል፡፡ የዛሬ አስር ዓመት የክልሉ ሕዝብ ብዛት፣ ገና 200 ሺህ እንኳን አልሞላም ነበር፡፡ የኮንሶ ወረዳ በሕዝብ ብዛት፣ ከትግራይ ክልል የመቀሌ ልዩ ዞንን፣ ከአፋር ክልል የዞን ሦስት እና አምስትን፣ ከአማራ እና ከኦሮሚያ ክልሎች ከዞኖች ጋር አቻ ከሆኑት የባሕር ዳር፣ የደሴ፣ የጎንደር፣ የአዳማ እና የጅማ ከተሞችን፣ ከቤኒሻንጉል-ጉሙዝ፣ የካማሼ ዞንን፣ የጋምቤላ የሁሉንም ዞኖችን፣ እንዲሁም ከራሱ ከደቡብ ክልል ደግሞ የሸካ ዞንን በሕዝብ ብዛት ይበልጣል፡፡ የጋምቤላ ክልል ከኮንሶ ሕዝብ ወደ 80 ሺህ በሚጠጋ ቁጥር ብቻ ነው የሚበልጠው፡፡

ራስን በራስ የማስተዳደር መብት፤
የኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 89(1)፣ መንግሥት በዴሞክራሲያዊ መርሆች ላይ በመመሥረት ሕዝቡ በሁሉም ደረጃዎች ራሱን በራሱ የሚያስተዳደርበትን ሁኔታ ማመቻቸት ያለበትን ስለመሆኑ የፖለቲካዊ ፖሊሲው በጥቅሉ አስቀምጦታል ፡፡ ማንኛውም የብሔርነት፣ የብሔረሰብነት ወይንም ደግሞ የሕዝብነት ዕውቅና ያገኘ ማኅበረሰብ ራሱን በራሱ የማስተዳደር መብቱን ተግባራዊ የሚያደርግበትን አስተዳደራዊ መዋቅር የመመሥረት ገደብ የሌለው ሕገ-መንግሥታዊ መብት እንዳለው የፌደራሉም የክልሎችም ሕገ መንግሥት አንቀጽ 39 (3) ላይ ተደንግጓል፡፡
ራስን የማስተዳደር ሙሉ መብት በክልል ላይ ብቻ የተንጠለጠለ አይደለም፡፡ ይህ መብት ውጤታማ እንዲሆን ያልተማከለ አስተዳደር ተግባራዊ መሆን አለበት፡፡ ያልተማከለ አስተዳደርን እንደ አንድ ፕሮግራም ብናየው ብዙ የሚያካትታቸው ነጥቦች አሉት፡፡ ከሚያካትታቸው ነጥቦች ውስጥ በባሕርያቸው የአካባቢው መንግሥት ሥልጣንና ሥራ የሆኑትን ለአካባቢው መተው፣ እንዲሁም ባሕርያቸው አካባቢያዊ ባይሆኑም እንኳን እነሱ ቢፈጽሟቸው የሚሻል ከሆነም ለአካባቢው መንግሥት መተው አለባቸው፡፡
እንዲህ መሆኑ ከታመነበት ግጭትን ለመቀነስም ሆነ በልበ-ሙሉነት ለመሥራት ሲባል ሥልጣንና ተግባራቸው በግልጽ ተለይቶ መቀመጥን ይፈልጋል፡፡
የአካባቢ መንግሥታት (Local Government) የራሳቸውን ጉዳይ በራሳቸው የመጨረስ፣ ፖሊሲ የመንደፍ፣ ለፖሊሲያቸው የሕግ ማዕቀፍ የመስጠት የመጨረሻ የሥልጣን ባልተቤት መሆን ያሻቸዋል፡፡
አካባቢያዊ መንግሥታት፣ አስተዳደራዊ ተቋሞችን የማቋቋምና ለሥራ ምቹ በሚሆን መንገድ በነጻነት የማዋቀርና የሰው ሃይል የመቅጠርም የማባረርም ሥልጣንን ይይዛል፡፡ ስለሆነም አካባቢያዊ መንግሥታት ፖለቲካዊ፣ የገቢና ወጭ፣ እንዲሁም አስተዳደራዊ ሥልጣንን ያካትታል ማለት ነው፡፡ ይህ አሠራር የማእከላዊ መንግሥት ድጋፍና ቁጥጥር እንዲሁም በይነመንግሥታዊ ትብብርንም አያስቀርም፡፡
ፖለቲካዊ ራስ ገዝነት ባልተማከለ አስተዳደርም ይሁን ራስን በራስ በሚያስተዳድሩ ብሔሮች ዘንድ ቁልፍ የሆነ ጉዳይ ነው፡፡ ማእከላዊም ይሁን የክልል መንግሥታት ባሰኛቸው ጊዜ የሚያፈርሷቸው ሲመቻቸው ደግሞ የሚያቋቁሟቸው ልዩ ዞኖች፣ ወረዳዎች፣ ቀበሌዎች ሊኖሩ አይገባም፡፡ ቀጣይ መሆን አለባቸው፡፡ በመኖርና በመፍረስ በስጋት እየወላወሉ የሚኖሩ ተቋማት ሊሆኑ አይገባቸውም፡፡ ወይንም ደግሞ እንዴት እንደሚቋቋሙም ይሁን እንደሚፈርሱ ግልጽ ሕግ፣ሁሉም የተስማሙበት ኖሮ በዚያው መሠረት መፈጸም አለበት፡፡ የኮንሶ ነገርም፣ በአንድ ወቅት ልዩ ዞን የነበረች ሲሆን አሁን ግን መደበኛ ወረዳ ብቻ በመሆን በሰገን ሕዝቦች ሥር ትገኛለች፡፡
በሕገ-መንግሥቱ በአንቀጽ 50(4) ከተገለጸው አንጻር ቋሚነት አላቸው ማለት ቢቻልም በተግባር እንደታየው ግን፣ ከ1994 ዓ.ም. በፊት ይህ ዓይነት ሥልጣን የሌላቸው ሲሆን፣ በኋላ ደግሞ መለወጡ ብሎም በአንዳንድ ክልሎች ሥልጣናቸው በሕገ-መንግሥት ሳይሆን በአዋጅ መገለጹ ወይንም በግልጽ አለመቀመጡ አጠራጣሪ አስመስሎታል፡፡
በተጨማሪም እንዴት ወረዳዎች እንደሚመሠረቱና እንደሚታጠፉ፣ ድንበራቸው እንደሚካለልና እንደሚደካ አለመገለጹ፤ መሥፈርቶቹን አንዳንድ ክልሎች በአዋጅ (ለምሳሌ ደቡብና ኦሮሚያ) ሌሎቹ ደግሞ ለአስፈጻሚው አካል መተው (ለምሳሌ ቤኒሻንጉል ጉሙዝና አማራ) ጉራማይሌ አድርገውታል፡፡ በመሆኑም ለልዩ ዞኖችም ይሁን ወረዳዎች የተሻለ ዋስትና መስጠት ያስፈልጋል፡፡ የዚህ ዋስትና አለመኖር ነው ኮንሶን በአንድ ወቅት ልዩ ወረዳ፣ በሌላ ጊዜ መደበኛ ወረዳ በመሆን ምንአልባትም ለተለያዩ ተቃውሞዎች መነሻ የሆነው፡፡
የልዩ ዞንና ወረዳ ምሥረታ ሂደት፤
በሽግግሩ ዘመን ሥራ ላይ በነበረው አዋጅ ቁጥር 7/1984 መሠረት ወረዳን ጨምሮ ወደ ላይ ያሉ መስተዳድሮችን ማቋቋም የማይችሉት በግልጽ ተዘርዝረው ነበር፡፡ በሕገ-መንግሥቱ ይህ ገደብ ተነስቷል፡፡ በተጨማሪም ክልል መመሥረት እንደመገንጠል ሁሉ ገደብ የለውም፡፡ ለነገሩ ክልል መመሥረትም ጉዳዩ ከክልል መሆኑ ነው እንጂ ያው መገንጠል ነው፡፡ ገደብ አለመኖሩን ለማመልከት “በማናቸውም ጊዜ” የሚል ቃል ተጠቅሟል፡፡
በሕገ-መንግሥቱ እንዲህ ዓይነቱ “መድልኦ” ተወግዷል ብንልም እንኳን በጋምቤላ አኙዋ፣ ኑዌርና መዠንግር ልዩ ዞን ሊያቋቁሙ እንደሚችሉ ሲገለጽ ኡፖና ኮሞ አይችሉም በማለት የክልሉ ሕገ-መንግሥት ገልጿል፡፡ በዚህም ከብሔረሰቦች መርጦ ለዞንና ለወረዳ አለ ማለት ነው፡፡ ቁጥራቸው አናሳ (በ1999ኙ ዓ.ም. በተደረገው ቆጠራ በክልሉ ውስጥ የሚኖሩት ማኦ 64፣ ኡፖ ደግሞ 990) መሆናቸው አንድ ነገር ሆኖ በሕገ-መንግሥት መከልከል ደግሞ ሌላ ነገር ነው፡፡
የአሁኑ ደቡብ ክልል ከመመሥረቱ በፊት አራት ክልሎች ነበሩ፡፡ አንድ ክልል ከሆኑ በኋላ ዞኖችና ወረዳዎች በተለያዩ ጊዜያት እንደገና ተዋቅረዋል፡፡ ለምሳሌ ሰሜን ኦሞ (ወላይታ፣ ጋሞ-ጎፋ፣ዳውሮ) ወደ ሦስት ብሔረሰብ ዞኖች ተከፋፈለ (ወላይታ፣ ጋሞ-ጎፋ እና ዳውሮ ) ተብለው፡፡ እንዲሁም ሁለት ልዩ ወረዳዎች ተጨመሩ ባስኬቶና ኮንታ፡፡ ሌላ ካፋ-ሸካ የሚል እንደ አንድ ልዩ ዞን ቢቋቋሙም ውሎ አድሮ ካፋ እና ሸካ ልዮ ዞኖች ተብለው ራሳቸውን ቻሉ፡፡ ቤንችና ማጂ ይባሉ የነበሩት ሁለት ዞኖች፣ ኋላ ላይ ቤንች-ማጂ ተብለው አንድ ዞን ሆኑ፡፡ ስልጤ ዞንም ከጉራጌ ተነጥሎ ራሱን ቻለ፡፡ ቀደም ሲል ስምንት ልዩ ወረዳዎች የነበሩ ሲሆን አሁን አራቱ (ኮንሶ፣ደራሼ፣ ቡርጂ እና አማሮ) በአንድነት ሰገን ዞንን መሥርተዋል፡፡
ቋንቋ፣ማንነት፣ የአሰፋፈር ሁኔታና ፍቃደኝነት ላይ መሠረት በማድረግ የሚቋቋሙ አካባቢያዊ መስተዳድሮች (local territorial autonomy) ጉዳትም እንዳላቸው የሚገልጹ አሉ፡፡ ከእነዚህም ጉዳቶች መካከል ክፍፍልን ያባብሳል፣ ክልሎች በአብዝኃኛው ወጥ የሆነ አንድ ብሔር ስለማይኖርባቸው አሁንም ቢሆን በኢትዮጵያ የአናሳና የብዙኃንን ግንኙነት ማስቆም አያስችልም፤ በተጨማሪም አሁን ባለው ሁኔታ ዞኖችና ወረዳዎች ሲዋቀሩም ይሁን ሲዋሃዱ ወጥ የሆነ የታወቀ ሕገ-መንግሥታዊ መርሕ የለውም፤ እንደገዥው ፓርቲ የፖለቲካ ግምገማና ድምዳሜ የሚወሰን ነው፤ ዘፈቀዳዊም ነው የሚሉ ክሶች ይቀርባሉ፡፡
የዞንና ምሥረታ በደቡብ፤
ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ማንነታቸው ከታወቀ እንደቡድን ማንኛውንም አስተዳደራዊ እርከን የመመሥረት መብት አላቸው ብለናል፡፡ ከደቡብ ውጭ ያሉት ክልሎች፣ በውስጣቸው የሚገኙት ነባር ብሔረሰቦች ቁጥራቸው ዝቅተኛ ስለሆነ፣ ወይ መሥርተዋል፤ አሊያም ትተዋቸዋል፡፡ መመሥረት ቢፈልጉ ደግሞ እንዴት ጥያቄያቸውን እንደሚያቀርቡ፣ ለማን እንደሚያቀርቡ፣ ምን ምን ሁኔታዎችን ማሟልት እንዳለባቸው ወዘተ የሚያሳይ ሕግ የላቸውም፡፡ ደቡብ ግን አለው፡፡
የደቡብ ክልል የብሔረሰቦች ምክር ቤት ስላለው፣ የዞንም ይሁን የወረዳ አመሠራረት ጥያቄ እንዴት መስተናገድ እንዳለበት፣ ይህንን ምክር ቤት ለማጠናከርና ሥልጣንና ተግባሩን ለመወሰን በወጣው አዋጅ ላይ ተገልጿል፡፡ ሥነ-ሥርዓቱ ከክልል ምስረታ ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ ልዩነቱ ጥያቄውን ያቀረበው በአስተዳደራዊ መዋቅር ተደግፎ ከሆነ (ለምሳሌ ልዩ ወረዳ የነበረው ልዩ ዞን መሆን ቢፈልግና ጥያቄው የቀረበው የወረዳው መስተዳደር ቢሆን) የመስተዳድሩ ምክር ቤት በሁለት ሦስተኛ ድምፅ ከደገፈው ወይንም ጥያቄውን ያቀረበው፤ ሕዝቡ ከሆነ (5% የሚሆነው ስምና ፊርማ አስፍሮ) ሕዝቡ በአብላጫ ድምፅ ሲደግፈው እና የክልሉ የብሔረሰቦች ምክር ቤት ሲወስን ተፈጻሚ ይሆናል፡፡
በዚህ ሕግ መሠረት ሕዝቡ በአብላጫ ድምፅ ወስኖ እንኳን ምክር ቤቱ ተጨማሪ ማስረጃ የማሰባሰብ ሥልጣን ስላለው አሰባስቦ ከመረመረ በኋላ ነው ውሳኔውን የሚያሳውቀው፡፡ ውሳኔውን ያሳውቃል ማለት ሕዝቡ በአብላጫ ድምፅ የወሰነውንም ሊሽረው ይችላል ማለት ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ አሠራር ወለፈንድ ይመስላል፡፡ ድምፅ ሳይሰጡ ቢሆን እንኳን ይሻላል፤ ድምፅ ሰጥተው ከጨረሱ በኋላ የሌሎች ብሔረሰቦች ተወካዮች የሕዝብን ውሳኔ ካላከበሩ የት ላይ ነው ታዲያ የራስን ዕድል በራስ መወሰኑ? ይሔው ሕግ ይሔንኑ ጉዳይ በሚደነግግበት ክፍሉ ስለየራስን ዕድል በራስ መወሰን ነው የሚያወራው፡፡ በራሳቸው የወሰኑት ከተሻረ የትኛው ዕድላቸው ላይ ወሰኑ?
ሌላው ይህ ሕግ በዝርዝር ባያብራራውም በውሳኔው መሠረት ለብቻቸው ተለይተው ራሳቸውን ማስተዳደር የሚጀምሩት ብሔረሰቦች ቀድሞ ከነበሩበት ዞን ወይንም ወረዳ ፍትሐዊ የሆነ የሀብት ክፍፍል ሊያደርጉ እንደሚችሉ አስቀምጧል፡፡ ክልል ሲመሠርቱ ያልተቀመጠውን፣ በደቡብ ክልል ውስጥ ዞንና ወረዳ (ልዩም ይሁን አይሁን) ሲመሠርቱ የንብረት ክፍፍል እንዲደረግ ያስቀምጥና ስለተግባራዊነቱም የብሔረሰቦች ምክር ቤት እንደሚከታተል ገልጿል፡፡ ፌደሬሽን ምክር ቤት አዋጅ ወይንም የፌደራሉ ሕገ-መንግሥት ስለ ክልል ምሥረታ ያላስቀመጠውን በሥሩ ለሚገኙ መስተዳድሮች ማስቀመጡ ለፌደራሉም መንግሥት ትምህርት ነው፡፡
የክልሉ ብሔረሰቦች እና የፌደሬሽን ምክር ቤቶች ሚና ሲገመገም፤
ከላይ በጥቅሉ ባስቀመጥነው መሠረት የኮንሶን ጉዳይ እንመልከተው፡፡ የኮንሶ ሕዝብ ከጠቅላላው አምስት ፐርሰንት ድጋፍ ካገኘ በክልሉ የብሔረሰቦች ምክር ቤት አማካይነት ሕዝበ-ውሳኔ ይካሄዳል፡፡ የልዩ ዞንነቱን ጥያቄ አብዝኃኛው ድምጽ ሰጪ ከደገፈው ውጤቱ ለክልሉ ብሔረሰቦች ምክር ቤት ቀርቦ ከጸደቀ በኋላ የዞን ምሥረታው ተግባራዊ ይሆናል፡፡ ምክር ቤቱ፣ ስለ ድምጽ አሰጣጡ እና በአጠቃላይ ስለ ነበረው ሁኔታ እና ሂደት ካጣራ በኋላ ሊያጸድቅም ሊሽረውም ይችላል፡፡
ጥያቄው አዲስ ክልል የመመሥረት ቢሆን ኖሮ ግን፣ ጥያቄውን ያቀረበው ብሔረሰብ ምክር ቤት፣ለምሳሌ ሲዳማ ቢሆን የሲዳማ ምክር ቤት፣ በሁለት ሦስተኛ ድምጽ ድጋፍ ካገኘ ይሄንኑ ውሳኔ በጽሑፍ ለክልል ምክር ቤት ያቀርባል፡፡ ጥያቄው የቀረበለት የክልል ምክር ቤት ሕዝበ-ውሳኔ ከማዘጋጀት የዘለለ በሕግ የተቀመጠ የመከልከል ወይንም ሌላ ሥልጣን የለውም፡፡ ጥያቄውን ለማብረድ ፖለቲካዊ ሥራ ሊሰራ ይችል ይሆናል፡፡ ጥያቄው በደረሰው በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ድምፀ-ውሳኔ ማዘጋጀት አለበት፡፡
የኮንሶን በተመለከተ፣ የደቡብ ክልል የብሔረሰቦች ምክር ቤት አንድም ሙሉ በሙሉ ጥያቄውን ካልተቀበለ አሊያም ተቀብሎ ሕዝበ-ውሳኔ ካላዘጋጀ ወይንም ደግሞ የሕዝበ-ውሳኔውን ውጤት ከሻረው ጉዳዩን በይግባኝ ወደ ፌደሬሽን ምክር ቤት ማምጣት ይቻላል፡፡ምክር ቤቱ ጥያቄውን በአወንታ ተቀብሎ ሕዝበ-ውሳኔ ሊያዘጋጅ መሆኑን የሚያሳዩ መረጃዎች መኖራቸውን ስለማይታወቅ ወደ ፌደሬሽን ምክር ቤት ሊመጣ ይችላል ማለት ነው፡፡
የክልሉ የብሔረሰቦች ምክር ቤት አወቃቀሩ ልክ እንደ ፌደሬሽን ምክር ቤት በክልሉ ውስጥ የሚገኙ ከእያንዳንዱ ብሔር አንድ አባል ያለበት፣ ነገር ግን ከአንድ ሚሊዮን በላይ ቁጥር ካለው ለእያንዳንዱ አንድ ሚሊዮን ሌላ ተጨማሪ አንድ አባል ለምክር ቤቱ ይጨመርለታል፡፡
አባላቱ የሚመረጡት የብሔረሰቡ ዞኖች ወይንም ወረዳዎች ምክር ቤት መካከል ሆኖ መሥተዳድር ከሌላቸው ግን በቀጥታ ከብሔረሰቡ ተመርጠው ይወከሉበታል፡፡ የፌደሬሽን ምክር ቤት ደግሞ ለክልል ምክር ቤት ከተመረጡ ተወካዮች ውስጥ በክልሉ አሸናፊ የሆነው የፖለቲካ ፓርቲ የፈለገውን ሰው ከምክር ቤቱ አባላት መርጦ ይልካል፡፡ ስለሆነም፣ የደቡብ ክልል ብሔረሰቦች ምክር ቤት የሚኖረው የአባላት ብዛት እና ክልሉ በፌደሬሽን ምክር ቤት የሚኖረው ውክልና እኩል ነው፡፡
የኮንሶ ብሔረሰብ፣ ቢያንስ 65 አባላት በሚኖሩት የብሔረሰቦች ምክር ቤት አንድ ወኪል ይኖረዋል፡፡ በፌደሬሽን ምክር ቤትም እንዲሁ፡፡ ከሕገ መንግሥታዊነት እና ሕጋዊነት ይልቅ፣ ከሕገ መንግሥቱ ጋር አብሮ በማይሄደው ፓርቲያዊ የሆነው ዴሞክራሴያዊ ማእከላዊነት ላይ በመመርኮዝ ውሳኔዎች እንደሚሰጡ ስለሚታወቅ፣የብሔረሰቦቹ ምክር ቤት አባላትም ለተመረጡበት ፓርቲ መታመን ስለሚጠበቅባቸው በክልል እና በፌደሬሽን ምክር ቤቶች መካከል የተለያዩ ውሳኔዎችን መጠበቅ አይቻልም፡፡
የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች በክልሉ የብሔረሰቦች ምክር ቤት ላይ የሚኖራቸው ተጽእኖ በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ የበለጠ የሚከፋው ደግሞ እነዚህ የክልል ከፍተኛ አመራሮች፣ የክልሎቹን ርዕሰ መስተዳደር ጨምሮ፣የፌደሬሽን ምክር ቤት አባል መሆናቸው ነው፡፡ ክልል ላይ ላደረሱት በደል አቤቱታ ሲቀርብባቸው፣ በፌደሬሽን ምክር ቤት በዳኝነት ይሰየማሉ፡፡
የፌደሬሽን ምክር ቤት ካሉት 153 አባላት ውስጥ፣ ከ65 የማያንሱ ከደቡብ ክልል የተወከሉ ናቸው፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች የክልሉ አቋም ለኮንሶ የዞን ጥያቄን አለመቀበል ከሆነ፣ የፓርቲውን ጫና እና የተማከለ ውሳኔውን እንኳን ብንተወው፣ የፌደሬሽን ምክር ቤት ላይ አብላጫ ድምጽ ለማግኘት በጣት የሚቆጠሩ ደጋፊዎችን ማፍራት ብቻ ነው የሚጠበቅበት፡፡
የኮንሶ ብሔረሰብ ወደ ኦሮሚያ ክልል ለመጠቃለል …..
የፌደራሉ ሕገ መንግሥት እንዴት መገንጠል እንደሚቻል እንጂ ሌሎች አገራት ከኢትዮጵያ ጋር መዋሃድ ቢፈልጉ እንዴት ሊቀላቀሉ እንደሚችሉ የሚገልጽ ሥነ-ሥርዓት አላስቀመጠም፡፡ አንድ ክልል ከሌላ ክልል ጋር መዋሐድ ቢፈልግ ወይንም አንድ ብሔር ከአንድ ክልል ወጥቶ ወደ ሌላ ክልል መካለል ቢፈልግ፣ ይሄንን ማስተናገድ የሚችል ግልጽ የሆነ ሕግ የለንም፡፡ እንደ አዲስ ክልል መመሥረት ለሚፈልግ ሥርዓት አለው፡፡ ግንኙነቱም በተገንጣዩ እና በቀሪው ክልል መካከል ይሆናል፡፡ ወደሌላ ክልል መጠቃለል ከሆነ ግን የሌላ ክልል ተሳትፎን ይጠይቃል፡፡
የኮንሶ ሕዝብ በኦሮሚያ ክልል ከቦረና፣ሊበን ከሚባለው አካባቢ መጣን ብለው ስለሚያምኑ፣ የቋንቋው ቤተሰብም ኩሽቲክ በመሆኑ፣ ከኦሮሞ ሕዝብ ባህል ጋር የሚመሳሰሉ ልምዶች ስላላቸው ይመስላል ይህ ዓይነት አማራጭ ሊነሳ የቻለው፡፡ የሁለቱ ክልሎች ቅንነት እስካለ ድረስ የድንበር ግጭት ሊፈታ በሚችልበት መንገድ በስምምነት መጨረስ ይቻላል፡፡ በተጨማሪም፣ የድንበር ማካለል ጥያቄ በማንሳት በሕዝበ ውሳኔ መፍታት ይቻላል፡፡
ይህን ለማድረግ ግን፣በኮንሶ ጉዳይ፣የኦሮሚያ ክልል የድንበር ጥያቄ ማንሳት ወይንም የሕዝቡን ጥያቄ መቀበል አለበት፡፡ ከወልቃይት ጉዳይ የሚለየው የኮንሶ ሕዝብ የኦሮሞነት ጥያቄ አለማንሳቱ ነው፡፡ ሁለቱም ቢሆኑ የድንበር ማካለል ብቻ አይደሉም፡፡ እንደዚህ ዓይነት ጥያቄዎችም ሕጋዊ አሠራር የሚያስፈልጋቸው ይመስላል፡፡
ሲጠቃለል፣ ሁሉም ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በማናቸውም ጊዜ ክልል የመመሥረት ሕገ-መንግሥታዊ የሆነ መብት አላቸው፡፡ ነገር ግን ከሰማኒያ በላይ ክልል የማቋቋም አቅም አለን ወይ? እንኳን ክልልና ወረዳና ዞን መቋቋምም ከወጭ አንጻር ከባድ ነው፡፡
በኢትዮጵያ ውስጥ ከ50 በላይ የሚሆኑት ብሔረሰቦች ቁጥራቸው ከ100,000 በታች ሲሆኑ ሃያ አንዱ ደግሞ ከ10,000 በታች ናቸው፡፡ ለቀበሌና ለወረዳ የመሳሰሉት አስፈላጊ የሆኑ ተቋማትንስ መቋቋም ይቻላልን? የበጀት፣ የሰው ኃይል እና የመሳሰሉትን ፍላጎቶች መሸፈን መቻሉ አጠራጣሪ ነው፡፡ይሁን እንጂ፣ መተግበር የማይቻል መብት ውሎ አድሮ ቅያሜ ማምጣቱ አይቀርም፡፡ የኮንሶም ጉዳይ ይሄው ነው፡፡ እናም የአሰፋ አባተን ግጥም ልዋስና ልደምደም፡፡
“የማትበላ ወፍ ተይዛ በጭራ፣
ልቤን አደማችው ሞጭራ ሞጫጭራ፤”
እንዳለው የማይተገበር መብት አስቀምጦ የሰው ሕይወት እና ንብረት እንዲጠፋ ምክንያት ከመሆን እንደ አዋጅ ቁጥር 7/1984 በግልጽ የትኞቹ ብሔረሰቦች ምን ዓይነት መስተዳደር ማቋቋም እንደሚችሉ አስቀድሞ ሕገ መንግሥቱን በማሻሻል ማስቀመጥ፣ ወይንም ደግሞ መብቶቹን ተግባራዊ ማድረግ ነው፡፡ አንድ ጊዜ ልዩ ወረዳ፣ ሌላ ጊዜ እንደ ኮንሶ፣ ከሌሎች ጋር በመቀላቀል ዞን ማድረግ ግጭትን መጥራት ነው፡፡ ተመጣጣኝ የሕዝብ ቁጥር እያላቸው፣ አንዱን መርጦ ዞን እንዲኖረው ማድረግ ፍትሐዊ አይደለም፡፡