በአማራ ክልል በአገዛዙ ወታደሮችና በነፃነት አርበኞች መካከል ውጊያ እየተካሄደ ሲሆን፤ ከሁለቱም ወገን ጉዳት መድረሱ ተገለፀ
(አዲስ ሚዲያ)በአማራ ክልል በተለይም በሰሜንና ደቡብ ጎንደር ዞን ባሉ የተለያዩ ወረዳዎች የገዥው ስርዓት በደል እና ጭቆናን የተቃወሙ የአማራ ተጋድሎ አርበኞች እና የአርበኞች ግንቦት 7 ንቅናቄ ድርጅት የነፃነት ኃይሎች ከመንግሥት ወታደሮች ውጊያ ማካሄዳቸው ተገለጠ፡፡ በተለይ ካለፈው ሐሙስ ህዳር 8 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ በዋናነት በሰሜን ጎንደር ምዕራብ እና ላይ አራማጭሆ፣ ሳንጃ፣ ደንብያ፣ ጃን አሞራ፣ ዳባት፣ ደባርቅ እና ወገራ ወረዳዎች፤ እንዲሁም በወልቃይት አካባቢ ቃፍታ ሑመራ እና ጠገዴ ተከታታይ ውጊያ መደረጉን እና አሁንም በተጠቀሱ አካባቢዎች ውጊያዎቹ የቀጠሉ መሆናቸውን ምንጮች አረጋግጠዋል፡፡

የአማራ ተጋድሎ መብት አራማጆችም በተለያዩ የሰሜን ጎንደር ዞን ባሉ የተለያዩ ወረዳዎች የተጋድሎው አርበኞች ከአገዛዙ ወታደራዊ ኃይሎች ጋር ውጊያ መግጠማቸውን እና ከ70 ያላነሱ የአገዛዙ መንግሥት ወታደሮች ሲገደሉ ከአማራ ተጋድሎ በኩል 2 ያህል አርበኞች መገደላቸውን ይፋ አድርገዋል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ አገዛዙን ስርዓት ለመጣል በይፋ ሁለገብ ትግል እያደረገ የሚገኘውና በፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ የሚመራው የአርበኞች ግንቦት 7 ለፍትህና ለነፃነት ንቅናቄ በተለያዩ የሰሜን ጎንደር ዞን ወረዳዎች አውደ ውጊያዎች በአገዛዙ ወታደራዊ ኃይሎች ላይም ተደጋጋሚ ጥቃት በመክፈት ድል መቀዳጀቱን በመግለፅ ከንቅናቄው ወገን በወቅቱ አዛዥ የነበሩት ሻለቃ መሳፍንት ጥጋቡን (ገብርዬ) ጨምሮ የተወሰኑ ታጋዮቹ እንደተሰዉ ይፋ አድርጓል፡፡ በነበረው ውጊያም ንቅናቄው በርካታ የአገዛዙ ወታደሮችን መግደሉን፣ ማቁሰሉን እና መማረኩንም ይፋ አድርጓል፡፡
ገዥው መንግሥት በበኩሉ በሰሜን ጎንደር ዞን እና በምዕራብ ትግራይ ዞን የአርበኞች ግንቦት 7 ንቅናቄ ኃይሎች ጋ ውጊያ መኖሩን እና በወቅቱ የንቅናቄው መሪ የነበሩት ሻለቃ መሳፍንት ጥጋቡን ገድሎ 70 ያህል የንቅናቄው ወታደሮችን መማረኩን በስሩ በሚቆጣጠረው የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ይፋ አድርጓል፡፡ ይሁን እንጂ ከአገዛዙ በኩል ስለደረሰ ጉዳት የጠቀሰው ነገር የለም፡፡ እንደ አካባቢው የዓይን እማኞች በበኩላቸው አገዛዙ ተጨማሪ በርካታ ወታደሮችን ከነ ሙሉ ትጥቃቸው ወደ ስፍራው ማንቀሳቀሱን እንደተመለከቱ ይናገራሉ፡፡ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ድረስ በርካታ የአገዛዙ ወታደራዊ ተሸከርካሪዎች ጎንደር ከተማን ጨምሮ በተለያዩ የክልሉ የዞን እና የወረዳ ከተሞች እንደሚታዩ ተጠቁሟል፡፡

አገዛዙ ተግባራዊ ያደረገውን የ6 ወር አስቸኳይ አዋጅ ተከትሎ ከአማራ ክልል ብቻ ከ 19 ሺህ ያላነሱ ሰላማዊ ዜጎችን በተለያዩ የክልሉና የፌደራል እስር ቤቶች በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ኮማንድ ፖስቱ መታሰራቸውን የአማራ ተጋድሎ የመብት አራማጆች እና የአካባቢው የፖሊስ መረጃ ምንጮች የጠቆሙ ሲሆን፤ የተጠቀሰው አሀዝ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በፊት በነበሩ ሰላማዊ ህዝባዊ ተቃውሞ ወቅት የታሰሩትን ቁጥር ሳይጨምር እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡ የአገዛዙ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ኮማንድ ፖስቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የአንድ ወር የወሰደውን ርምጃን ይፋ ባደረገበት ወቅት በአጠቃላይ 11,706 ያህል ዜጎች መታሰራቸውን ይፋ ማድረጉ አይዘነጋም፡፡
እንደ መረጃ ምንጮች ጥቆማ ከሆነ፤ በአማራ ክልል ከሐምሌ 5 ቀን 2008 ዓ.ም. የወልቃይት ጠገዴ ሁመራ የአማራ ማንነት የመብት ጥያቄ መነሻ አድርጎ በነበረው ህዝባዊ የፀረ አገዛዝ ተቃውሞ ተከትሎ በአገዛዙ በርካታ ሰላማዊ ዜጎች መገደላቸው፣ መታሰራቸውና ለከፋ ስቃይ መዳረጋቸው ያስቆጣቸው የአማራ ማኀበረሰብ አባላት መካከል በርካታ ሰዎች ራሳቸውን ” ከፋኝ” በሚል በየአካባቢው የጎበዝ አለቃ በሚመራ የአማራ ተጋድሎ ራሳቸውን አደራጅተው በአገዛዙ ላይ የአፀፋ እርምጃ መውሰድ እንደጀመሩ ለማወቅ ተችሏል፡፡
በኢትዮጵያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታወጀ፤ ህዝባዊ ተቃውሞውም አድማሱን እያሰፋ ቀጥሏል
(አዲስ ሚዲያ)በኢትዮጵያ ለተከታታይ አስር ወራት የፈጀው የፀረ አገዛዝ ህዝባዊ ተቃውሞ ተጠናክሮ መቀጠሉን ተከትሎ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ከትናንት ቅዳሜ መስከረም 28 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ ለ6 ወር ተግባራዊ የሆነ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማውጣቱን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ መስከረም 29 ቀን 2009 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ዝርዝር ጉዳይን በተመለከተ ወደፊት ይገለፃል ከማለት በስተቀር አጠቃላይ ይዘቱን በተመለከተ ያሉት ነገር የለም፡፡
በሌላ በኩል በጠቅላይ ሚኒስተሩ በሚመራ ኮማንድ ፖስት ስር የህግ አስከባሪዎችም መከላከያ ሰራዊት፣ ፌደራል ፖሊስ፣ የፌደራል የፀረ ሽብር ግብረ ኃይል፣ የአካባ ሚሊሻዎች እና ንብረት ጠባቂ የፀጥታ ኃይሎች የሚያካትት መሆኑን ደግሞ ጠቅላይ አቃቤ ህጉ አቶ ጌታቸው አምባዬ አብራርተዋል፡፡ አስቸኳይ አዋጁ በአጠቃላይ ሀገሪቱ ላይ ተግባራዊ መደረጉንም ጠቅላይ አቃቤ ህጉ አስታውቀዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ
በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አተገባበር መሰረት የተጠረጠረ ማንኛቸውም ሰው ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሊታሰር እንደሚችል፣ ቤቶችና አካባቢዎችም ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ብርበራ ሊካሄድባቸው እንደሚችልም እና ማንኛውም ዓይነት መገናኛ ብዙኃን ሊዘጋ እንደሚችልም ጠቅላይ አቃቤ ህጉ ይፋ አድርገዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ተቃውሞን ሊገልፁ የሚችሉ ምልክቶችን መጠቀምንም አዋጁ እንደሚከለክል፣ አዋጁን ተላልፎ የተገኘም ቅጣት እንደሚጠብቀው አስታውቀዋል፡፡
በተለይ ከህዳር 22 ቀን 2008 ዓ.ም. በኦሮሚያ እንዲሁም ከሐምሌ 5 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ በአማራ ክልል የተነሱ የፀረ አገዛዝ ህዝባዊ ተቃውሞች መንግሥት በወታደራዊ ኃይል ግድና፣ እስርና አፈና ለማስቆም መሞከሩን ተከትሎ ያለማቋረጥ ተቃውሞዎቹ ተጠናክረው መቀጠላቸው ስርዓቱን ስጋት ላይ ጥሎታል፡፡ በተለይ እንደ ማዕከላዊ ስታስቲክስ ኤጀንሲ መረጃ ከሆነ ከሀገሪቱን አጠቃላይ ህዝብና የቆዳ ስፋት 62% የሚሸፍነው የሀገሪቱ ህዝብ በአደባባይ የስርዓት ለውጥ እንደሚፈልግና በስልጣን ላይ ባለው ስርዓት መገዛት ለከፍተኛ ግድያ፣ እስር፣ በደልና ጭቆና እንደዳረገው በአደባባይ እየገለፀ ይገኛል፡፡ ለህዝቡ ጥያቄ የመንግሥት ምላሽ ግድያ፣ እስርና ማሰቃየት መሆኑ ደግሞ ህዝቡን የበለጠ እንዲቆጣና የተቃውሞ አድማሱን እንዲያሰፋ እንዳስገደደው ይነገራል፡፡
በተለይ ባለፈው እሁድ መስከረም 22 ቀን 2008 ዓ.ም. በኦሮሞ ማኀበረሰብ ዘንድ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠውና በርካታ ኢትዮጵያውያን የሚታደሙበት የኢሬቻ በዓል በደብረዘይት/ቢሾፍቱ ሆራ አርሰዲ ሐይቅ እየተከበረ ባለበት ወቅት ህዝቡ በሰላማዊ መንገድ አገዛዙ ላይ ተቃውሞውን ማሰማቱን ተከትሎ በተወሰደው ርምጃ አጠቃላይ ከ678 በላይ ሰላማዊ ዜጎች መገደላቸው በመላው ኢትዮጵያ የበለጠ ቅሬታን ፈጥሯል፡፡ በዚህም በኦሮሚያ ክልል የነበረው ህዝባዊ ተቃውሞ ወደ ህዝባዊ አብዮት መሸጋገሩንም የኦሮሞ መብት አራማጆች ይፋ ማድረጋቸውን ተከትሎ፤ ህዝቡ የአገዛዙ ሰዎች፣ ደጋፊዎችና ተባባሪዎች ናቸው የተባሉ ንበረቶች እና አገዛዙ የሚጠቀምባቸው የተለያዩ መንግሥታዊ ተቋማት ላይ ርምጃ መውሰዳቸው ታውቋል፡፡ የኦሮሞ ህዝባዊ ተቃውሞ አሁንም ተጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን፤ የመንግሥት ወታደራዊ የኃይል ርምጃም ተጠናክሮ በመቀጠል የበርካታ ሰላማዊ ዜጎች ህይወት ጠፍቷል፡፡
በተመሳሳይ በአማራ ክልል ባለው ህዝባዊ ተጋድሎ የቀጠለ ሲሆን፤ የመንግሥት ወታደራዊ እርምጃ በርካታ ሰላማዊ ዜጎችን ህይወት ቀጥፏል፡፡ በኦሮሚያ እና አማራ ክልል በተጨማሪ በደቡብ ክልል ኮንሶ ወረዳም ተመሳሳይ የፀረ አገዛዝ ህዝባዊ ተቃውሞ እና የመንግሥት የኃይል ርምጃ የቀጠለ ሲሆን፤ በዚህም በርካታ ሰላማዊ ዜጎች ተገድለዋል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ በዛው ደቡብ ክልል ጌዲዮ ዞን ባሉ ወረዳዎችና ከተሞች ከፍተኛ ተቃውሞና ግጭቶች ተቀስቅሰዋል፡፡ በዚህም የሰው ህይወት መጥፋትን ጨምሮ የበርካታ ሰላማዊ ዜጎች የንግድ ሱቆችና መኖሪያ ቤቶች ተቃጥለዋል፡፡ የተለያዩ የኃይማኖት ተቋማትም ላይ ጥቃት መሰንዘሩን ምንጮች አረጋግጠዋል፡፡
ከህዳር 2008 ዓ.ም. ጀምሮ አጠቃላይ በኦሮሚያ እና በአማራ ክልል እንዲሁም በደቡብ ክልል ኮንሶ ወረዳ ባሉ ህዝባዊ ተቃውሞዎች በመንግሥት ወታደራዊ የኃይል ርምጃ የተገደሉ ሰላማዊ ዜጎች ቁጥር ከ 1,420 በላይ መድረሳቸውን መረጃዎች አመልክተዋል፡፡ መንግሥት በበኩሉ ህዝባዊ ተቃውሞቹ በውጭ ኃይል የተቀነባበሩ ናቸው በማለት ለመሸፋፈን ቢሞክርም ከህዝቡ፣ ከመብት አራማጆችም ሆነ ከዓለም አቀፉ ማኀበረሰብ ተቀባይነት አላገኘም፡፡
በዛሬው ኢሬቻ ክብረ በዓል ላይ ከታደሙት መካከል ከ250 በላይ ሰላማዊ ዜጎች ተገደሉ
ዛሬ እሁድ መስከረም 22 ቀን 2009 ዓ.ም. ከአዲስ አበባ ደቡብ ምስራቅ 40 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ደብረዘይት/ቢሾፍቱ ከተማ በሚገኘው ሆራ ሐይቅ አካባቢ በኦሮሞ ማኀበረሰብ እና በሌሎች ኢትዮጵያውያን እንደቀደሙ ዓመታት ሁሉ ጊዜውን ጠብቆ ዛሬ እየተከበረ ባለው የኢሬቻ ክብረ በዓል ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ድረስ በግማሽ ቀን ብቻ ከ250 በላይ የበዓሉ ታዳሚ ሰላማዊ ዜጎች በገዥው ስርዓት በተወሰደ ወታደራዊ የኃይል ርምጃ መገደላቸው ተጠቆመ፡፡
በስፍራው ተገኝተው የነበሩ የዓይን እማኞች እና የሆስፒታል ምንጮች ከሆነ ከአንድ ሺህ ያላነሱ ንፁሃን ዜጎችም ቆስለው በደብረዘይት እና አዲስ አበባ በሚገኙ ሆስፒታሎች ለህክምና እርዳታ መላካቸው ታውቋል፡፡
ዛሬ ሰላማዊ ዜጎች ላይ በአንድ ቀን ብቻ በመንግሥት የተፈፀመው ግድያ ከህዳር ወር 2008 ዓ.ም. ጀምሮ በተለይ በኦሮሚያ ከ650 በላይ፣ በአማራ ከሐምሌ 2008 ዓ.ም. ጀምሮ ከ200 በላይ ከተገደሉ ንፁሃን በተጨማሪ የተፈፀመ ዘግናኝ ግድያ ነው፡፡ በተለይ በበዓሉ ስፍራ የነበሩ የዓይን እማኞች ከሆነ የተገደሉ ዜጎች ቁጥር ከተጠቀሰው በላይ ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል፡፡ በዘንደሮው በዓል ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢ የመጡ የበዓሉ ታዳሚዎች ቁጥር እስከ 2 ሚሊዮን እንደሚደርስ ተገምቷል፡፡
መንግሥት በሚቆጣጠራቸው መገናኛ ብዙኃን እና በቃል አቀባይ ጽህፈት ቤቱ በኩል በሰጠው መግለጫ ሟቾቹ በተፈጠረ ግርግር እንደሆነ ቢያሳውቅም፤ የዓይን እማኞች በበኩላቸው በበዓሉ ላይ ወጣቶች እጃቸውን በማጣመር ከዚህ ላለፉት 10 ወራት መንግሥት በዜጎች ላይ የፈፀመውን ግድያ እና እስር የሚያወግዝ ተቃውሞ እያቀረቡ ባሉበት ሰዓት በገዥው ስርዓት ወታደሮች አስለቃሽ ጢስን እና ተከታታይ ተኩስ በህዝቡ ላይ እንደተከፈተ ተናግረዋል፡፡ በጥይት ከተገደሉት በተጨማሪ ከተኩሱ ለማምለጥ የሞከሩ ሰዎችም በጥልቅ ጉድጓድ ውስጥ ገብተው የሞቱ፣ የተገዱና የተረፉም እንዳሉ ለማወቅ ተችሏል፡፡
መንግሥት ለንፁሃን መሞት ምክንያቱ አመፅ ቀስቃሾ በፈጠሩት ግርግር በመረጋገጣቸውና ገደል ውስጥ በመግባታቸው ነው ቢልም፤ የበዓሉ ታዳሚዎች በበኩላቸው የበዓሉን ድባብ በማጥፋ ወታደሮች የበዓሉ ታዳሚ ሰላማዊ ዜጎች ላይ ተኩስ በመክፈት ግድያው ሆን ተብሎ የተፈፀሙውና ንፁሃን እንዲሞቱ የተደረገው በገዥው ስርዓት እንደሆነ ከጉዳቱ የተረፉ እማኞች ተናግረዋል፡፡

የኦሮሞ ማኀበረሰብ መብት አራማጆችን ጨምሮ ሌሎች ኢዮጵያውያን የመብት አራማጆች የተገደሉ በርካታ ዜጎችን ምስልና ቪዲዮ በማኀበራዊ ሚዲያ ሲያሰራጩ ተስተውሏል፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ በህዝብ ክብረ በዓል ላይ የዛሬውን ያህል ዜጎች በመንግሥት ወታደራዊ ኃይሎች ሰላማዊ ዜጎች ላይ በወሰዱት ርምጃ ሲገደሉ የመጀመሪያው ነውም ተብሏል፡፡
የኢሬቻ በዓል በኦሮሞ ማኀበረሰብ ዘንድ ጥንታዊ የሆነ ፈጣሪን በጋራ የማመስገን በዓል ሲሆን፤ ከኦሮሞ ማኀበረሰብ በተጨማሪ ከተለያዩ አካባቢዎች ሌሎች ኢትዮጵያውያን በብዛት የሚታደሙበትና የሚያከብሩት ታላቅ ህዝባዊ በዓል መሆኑ ይታወቃል፡፡
በተያያዘ ዜና፤ የኤሬቻ በዓል ጅምላ ግድያን ተከትሎ በአምቦ እና አወዳይ ከተማ ህዝባዊ ተቃውሞ የተቀሰቀሰ ሲሆን፤ በሁለቱም ከተሞች መንግሥት ወታደሮች የኃይል ርምጃ መውሰድ መጀመራቸው ተገለፀ፡፡ በተወሰደው ርምጃ ምን ያህል ዜጎች ጉዳት እንደደረሰባቸው ለጊዜው ማወቅ አልተቻለም፡፡
አቶ ኃይለማርያም በኦሮሚያ የተነሳው ተቃውሞ ምክንያት መንግሥታቸው እና ፓርቲያቸው መሆኑን ቢገልፁም፤ ህዝባዊ ተቃውሞው እንደቀጠለ ነው
ባለፈው ህዳር አጋማሽ 2008 ዓ.ም. በድጋሚ የጀመረው የኦሮሚያ ህዝባዊ ተቃውሞ በተለያዩ የክልሉ ከተሞች እና ወረዳዎች ቀጥሏል፡፡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከሆነ በተቃውሞው ላይ መንግሥት እየወሰደ ያለው የኃይል እርምጃም ተጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን፤ በዚህም የሟቾች ቁጥር መጨመሩ ታውቋል፡፡ በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ተቃውሞን ለማፈን እና ለማርገብ እየተወሰደ ባለው የኃይል እርምጃ ከሚገደሉት በተጨማሪ ጉዳት የደረሰባቸውና የታሰሩ ሰዎች ቁጥርም ጨምሯል፡፡ ተቃውሞን እና የርሃቡን ሁኔታ ለመዘገብ ባለፈው የካቲት 28 ቀን 2008 ዓ.ም.ወደ ምስራቅ የሀገሪቱ ክፍል ለዘገባ ተንቀሳቅሰው የነበሩት የብሉምበርግ ዘጋቢ ዊሊያም ዳቪሰን እና ለተለያየ መገናኛ ብዙኃን በኢትዮጵያ ወኪል ሆና የምትሰራው ጄሲ ፎርትንና አስተርጓሚያቸው በኢትዮጵያ የፀጥታ ሃይሎች ያለምንም ማብራሪያ ከአዋሽ ከተማ ወደ አዲስ አበባ በፌዴራል ፖሊስ ታጅበው እንዲመለሱ ከተደረገ በኋላ አዳር ታስረው መለቀቃቸውን አስታውቀዋል፡፡ ጋዜጠኞቹም ለአንድ ቀን ከታሰሩ በኋላ መለቀቃቸውንም ጋዜጠኞቹ በማኀበራዊ ገፆቻቸው ላይ ይፋ አድርገዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርም ደሳለኝ ባለፈው ሳምንት መጋቢት 2 ቀን 2008 ዓ.ም. የመንግሥታቸውን የ6 ወር የስራ አፈፃፀም ሪፖርት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡበት ወቅት፤ በኦሮሚያውም ሆነ በአማራ ክልል ጎንደር እና በሌሎች አካባቢዎች የተፈጠረው ችግር በመንግሥታቸው አስተዳደር ውስጥ ባለ የመልካም አስተዳደር አለመኖር፣ ሙስና እና ኪራይ ሰብሳቢነት ችግር መሆኑን እና በሌላ አካል ላይ ጣት መቀሰር እንደማይፈልጉ በመጥቀስ ለዚህም መንግሥትና እና ፓርቲያቸው ኢህአዴግ ኃላፊነቱን እንደሚወስድ ተናግረዋል፡፡ ከዚህ ቀደም ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና የመንግሥት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ሚኒስተር አቶ ጌታቸው ረዳን ጨምሮ የተለያዩ የመንግሥት ኃላፊዎች ከህዝባዊ ተቃውሞው ጀርባ ኦነግ፣ አርበኞች ግንቦት 7 ፣ የኤርትራ መንግሥት እና በሀገር ቤት በይፋ የሚንቀሳቀሰውን ኦፌኮ/መድረክን ተጠያቂ ሲያደርጉ የነበረ ቢሆንም፤ በፓርላማው የሪፖርት ውሎ ግን የተለየ ምክንያት ሲሰጡ ተስተውሏል፡፡
እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አባባል ከሆነ የህዝባዊ ተቃውሞ ምክንያት ማንም ላይ ማላከክ አይቻልም፣ ኦሮሚያ ስለተነሳ ሌላ ቦታ ችግር የለም ማለት አይደለም፣ ይሄ ሁሉ ባለው ብልሹ አሰራር የተፈጠረ ችግር ነው፣ ለዚህም መንግሥት ኃላፊነቱን በመውሰድ ህዝቡን ይቅርታ ይጠቃል ብለዋል፡፡ ምንም እንኳ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኦሮሚያም ሆነ በአማራ ክልል በተለይ የቅማንት ማኀበረሰብ የማንነት ጥያቄ ጋ ተያይዞ ለተፈጠረው ችግር መንግሥታቸውና ፓርቲያቸው ኃላፊነቱን እንደሚወስድ ቢገልፁም ህዝባዊ ተቃውሞውን ተከትሎ መንግሥት የወሰደውን እና እየወሰደ ያለውን የኃይል እርምጃ ሲቃወሙ የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲ አባላትና አመራሮች፣ ጋዜጠኞች እና ተማሪዎችን ጨምሮ ከ4 ሺህ በላይ ስለታሰሩት፣ ከ270 በላይ ስለተገደሉትና በርካቶች ስለቆሰሉ ዜጎች ጉዳይ ከመናገር ተቆጥበዋል፡፡
በተለይ በኦሮሚያ ክልሉን ያስተዳድራል የሚባለውና የኢህአዴግ አባል ድርጅት የሆነው ኦህዴድ መዕከላዊ ኮሚቴ ህዝባዊ ተቃውሞን ተከትሎ በቅርቡ በአዳማ/ናዝሬት ባደረገው ድንገተኛ ልዩ ስብሰባ አቶ ዳባ ደበሌ እና አቶ ዘለዓለም ጀማነህ የተባሉ የክልሉና የፌደራል ከፍተኛ ኃላፊዎችን ከነበሩበት የክልሉም ሆነ የፌደራል ስልጣን ማንሳቱን ይፋ ቢያደርግም ህዝባዊ ተቋውሞው ግን ይህ እስከተጠናቀረበት ድረስ ቀጥሏል፡፡
ህዝባዊ ተቃውሞ መቀጠሉን ተከትሎ መንግሥት በቅርቡ የካቲት 16 ቀን 2008 ዓ.ም ሌሊት በምዕራብ ሸዋ ዞን ቶኬ ኩታዬ ወረዳ ጎሮሶሌ ከተማ ውስጥ ሞቱማ ፈዬራ የተባለ የ20 ዓመት ወጣትና የ10ኛ ክፍል ተማሪን ጨምሮ የተለያዩ ዜጎች መገደላቸው ተጠቁሟል፡፡
ለአራት ወራት የዘለቀውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ በፀጥታ ኃይሉ የሚወሰደው የኃይል እርምጃዎች እንዳሳሰበቸው የገለፁ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ባለፈው የካቲት 30 ቀን 2008 ዓ.ም. “እኛ ሽብርተኞች አይደለንም ፤ የኦሮሞ ሕዝብን መግደል አቁሙ” የሚሉ መፈክሮችን በመያዝ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ 6 ኪሎ ዋናው ግቢ አካባቢ ተነስተው ወደ አሜሪካ ኤምባሲ ሲያቀኑ የነበሩ ተማሪዎች በፖሊስ ድብደባ ሰልፉ እንደተበተነ እና በርካታ ተማሪዎችም ታፍሰው መታሰራቸው ተጠቁሟል፡፡ ተማሪዎችም ሰላማዊ መሆናችንን ለመግለፅ ነጭ ጨርቅ እያውለበለብን ነበር ያሉ ሲሆን መንግሥት ለምን ሰልፉን እንደበተነ እና ተማሪዎችን እንዳሰራቸው እስካሁን የገለፀው ነገር የለም፡፡
የጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ እናት ደብዳቤ
የጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ እናት ደብዳቤ
ቀን 02/06/2007 ዓ.ም
ለኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን
አዲስ አበባ
ጉዳዩ፡- የልጄ ተመስገን ደሳለኝን ጉብኝት ይመለከታል
ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ከአብራኬ የወጣ ሁለተኛ ልጄ ነው፡፡ ገና ከህፃንነቱ ጀምሮ ለሰው አሣቢ፣ ሀገር ወዳድና ታታሪ ስለመሆኑ ከእኔ በላይ የሚያውቁት ይመሰክራሉ፡፡ ልጄ ተመስገን ለወገኔ አሰብኩ ባለ በእስር ቤት ያለጎብኚ እየተሰቃየብኝ ይገኛል፡፡ መቼም፣ የእናት ሆድ አያስችልምና እባካችሁ ልጄን ታደጉት፡፡ እባካችሁ ቢያንስ ካለበት እየሄድኩ የልጄን አይን እንዳይ እንዲፈቀድልኝ ተባበሩኝ፡፡ የልጄን ድምጽ ከሠማሁ ይኸዉ አንድ ወር ሞላኝ፡፡ ታናሽ ወንድሙ ታሪኩ ደሳለኝ ለወንድሙ ብሎ የቋጠረዉን ምሣ ይዞ ዝዋይ ማረሚያ ቤት ቢሄድም በማረሚያ ቤቱ ጠባቂዎች ተደብድቦ የያዘውን ምግብ እንኳ ሣያደርስ ሜዳ ላይ ተደፍቶ ተመልሷል፡፡ መቼም እናንተም ልጆች ይኖራችኋል፤ ደግሞም የልጅን ነገር ታውቁታላችሁ፡፡ እኔ አሁን በእርጅና ዕድሜዬ ላይ እገኛለሁ፡፡ ከአሁን በኋላ ብቆይም ለትንሽ ጊዜያት ነው፡፡ በዚህች ጊዜ ውስጥ ልጄን እየተመላለስኩ እየጠየኩ፣ ድምፁን እያሰማሁ፣ አይዞህ እያልኩ ብኖር ለእኔ መታደል ነበር፡፡ እባካችሁ እርዱኝ የልጄ ድምጽ ናፈቀኝ፡፡ እሱን መጎብኘት የተከለከለበት ምክንያት ምን እንደሆነ እንኳን እስካሁን አላወቅሁም፡፡ ከወንድሙ ድብደባ በኋላም ጥር 10 ወደ ጠዋት አካባቢ የሄዱት ጓደኞቹ እና ወንድሞቹ ሳያዩት ተመልሰዋል፡፡
ተምዬ ስታመም የሚያስታምመኝ፣ “አይዞሽ እማዬ” የሚለኝ ረዳቴ ነው፡፡ ሌላ ዘመድ የለኝም፡፡ የምተዳደረውም ልጆቼ ለፍተውና ደክመው በሚያመጧት ትንሽ ብር ነው፡፡ ዛሬ ግን ይኸዉ ልጆቼም ወንድማቸውን ለማየት እየተንከራተቱ ነው፡፡
በእናታችሁ ይዣችኋለሁ፤ ከቻላችሁ ልጄ እንዲፈታልኝ እና እኔም ያለችኝን ቀሪ የእድሜ ዘመን አይን አይኑን እያየሁ እንድኖር እንድታደርጉልኝ፤ ይህን ማድረግ ከአቅም በላይ ከሆነ ደግሞ ካለበት ድረስ እየተመላለስኩ እኔና ሌሎች ልጆቼ እንዲሁም ወገኖቹ እንዲጠይቁት ቢደረግልኝ ስል በአክብሮት እጠይቃችኋለሁ፡፡ ልጄን አውቀዋለሁ፡፡ አንድ ነገር ሲገጥመዉ ሆድ ይብሰዋል፡፡ ቢያንስ እንኳን ቤተሰቦቹን ሲያይ ስለሚፅናና ይኸዉ እንዲፈቀድልኝ እማፀናለሁ፡፡ እኔ ምንም አቅም የሌለኝ አሮጊት ነኝ፡፡ ሁሉንም ለናንተ ሠጥቻችኋለሁ፡፡ ከእግዚአብሄር ጋር እንደምታስተካክሉልኝ እና እንደገና የልጄን ፊት እንዳይ እንደምታደርጉኝ ሙሉ ተስፋ አለኝ፡፡
እንግዲህ የየካዉ ቅዱስ ሚካኤል ይከተላችሁ፡፡ መቼም የእናትን ሆድ ታውቁታላችሁ፤ የልጅ ነገር አያስችልም፡፡ ሆድም ቶሎ ይሸበራል፡፡ ስለዚህ እባካችሁ እኔንም ልጆቼንም እርዱን እንላለን፡፡
ግልባጭ
_ ለጠ/ሚኒስተር ፅ/ቤት
_ የህግና፣ ፍትህና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ
_ ለአፈ-ጉባኤ ፅ/ቤት
_ የሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ሰመጉ)
_ ለእምባ ጠባቂ
_ ለአሜሪካ ኢምባሲ
_ ለእንግሊዝ ኢምባሲ
ከሰላምታ ጋር
ወ/ሮ ፋናዬ እርዳቸው
