ሰማያዊ ፓርቲ የምርጫ ቦርድ የፓርቲዎች ሚዲያ አጠቃቀም ድልድል ፍትሃዊ አለመሆኑን አስታወቀ
ሰማያዊ ፓርቲ የምርጫ ቦርድ ያወጣው ረቂቅ የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ውድድር የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ሰዓት አጠቃቀም ድልድል ፍትሃዊና በእኩልነት ላይ የተመሰረተ አለመሆኑን አስታወቀ፡፡
ጥር 25 ቀን 2007 ዓ.ም የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሀገር አቀፍ ፓርቲዎችን በረቂቅ የሰዓት ድልድሉ ላይ ጊዮን ሆቴል ጋብዞ ውይይት አድርጓል፡፡ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢብኮ) ኃላፊዎች ረቂቁን ለውይይት ያቀረቡ ሲሆን፣ የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ እና ሌሎች ኃላፊዎችም በውይይቱ ተገኝተዋል፡፡
የኢብኮ/ኢቴቪ ኃላፊዎች ባቀረቡት የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚዲያ አጠቃቀም ረቂቅ ድልድል መሰረት 55 ፐርሰንት በፓርላማ መቀመጫ ወንበር ላላቸው ፓርቲዎች፣ 20 ፐርሰንት ፓርቲዎቹ በሚያቀርቧቸው ዕጩዎች ብዛት እንዲሁም ቀሪ 25 ፐርሰንቱ ለሁሉም ፓርቲዎች በዕኩል የሚከፋፈል እንደሆነ ተገልጹዋል፡፡
ሰማያዊ ፓርቲን በመወከል በውይይቱ ላይ የተገኙት የፓርቲው የህግ ጉዳይ ኃላፊ አቶ ይድነቃቸው ከበደ ለነገረ ኢትዮጵያ እንደገለጹት፣ ረቂቅ የሚዲያ አጠቃቀሙ ድልድል ሲወጣ እንደ መስፈርት የተጠቀሙባቸው ነጥቦች ችግር ያሉባቸው ናቸው፡፡
‹‹በእኛ እምነት መስፈርቱም ልክ አይደለም፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ የሚዲያ ሰዓት አጠቃቀም ድልድል ሲወጣ ሁለት መስፈርቶች በቂና ትክክለኛ ናቸው ብሎ ያምናል፡፡ እነዚህ ነጥቦች በሚቀርቡ እጩዎች ብዛት እና በእኩልነት የሚከፋፈል የድልድል መስፈርት መሆን አለባቸው›› ብለዋል አቶ ይድነቃቸው፡፡
በእርግጥ ረቂቁን ያቀረበው ኢብኮ እንደ መመዘኛ መስፈርት የተጠቀመው ‹‹እኩልነትና ፍትሃዊነት›› የሚሉ መርሆዎችን ነው፡፡ ‹‹ኢብኮ በቃላት ደረጃ የገለጻቸው ‹ፍትሃዊነትና እኩልነት› በተግባር ረቂቅ ድልድሉ ላይ አልታዩም፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ በእኩልነትና ፍትሃዊነት መርሆዎች ላይ ችግር የለበትም፡፡ መርሁን መሰረት አድርጎ ወጣ የተባለው የሚዲያ ድልድል መጠን ግን በትክክል መርሁን የተከተለ አይደለም፡፡ ስለሆነም ለውጥ ሊደረግበት ይገባል›› ብለዋል አቶ ይድነቃቸው፡፡
አቶ ይድነቃቸው የሰዓት አጠቃቀም ድልድሉ ላይ ስንወያይ ነጻ ሚዲያ በሌለበት፣ ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት በተገደበበት፣ ጋዜጠኞች በታሰሩበትና በተሰደዱበት፣ አማራጭ የሚዲያ ተቋማት በሌሉበት በዚህ አጣብቂኝ ወቅት ላይ በህዝብ ሀብት በሚተዳደሩ ሚዲያዎች ላይ የፍትሃዊነት ችግር ይዘን መወያያታችን አሳዛኝ ነው ብለዋል፡፡ ‹‹ሳንሱር በህገ-መንግስቱ ተነስቷል፤ ይሁን እንጂ ኢብኮ የፖለቲካ ፓርቲዎች በተለያዩ ጊዜያት ለህዝብ የሚያስተላልፏቸው አማራጭ ሀሳቦችና ፖሊሲዎቻቸውን በቆርጦ ቀጥል ሲያዛባ እናስተውላለን፤ ይህ ሁኔታ መወገድ ያለበት ነው፡፡››
በውይይቱ ላይ ኢህአዴግ የድልድሉ መስፈርት ላይ እንደሚስማማ በመግለጽ፣ በፐርሰንቱ የተቀመጠው መጠን ላይ ግን መሻሻል እንዲደረግ እንደሚፈልግ መግለጹ ታውቋል፡፡
የተቃዋሚ ፓርቲዎች አመራሮች የክስ መቃወሚያ ውድቅ ተደረገ
በፌደራል አቃቤ ህግ የሽብር ክስ ተመስርቶባቸው ጉዳያቸው በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ወንጀል ችሎት እየታየ የሚገኙት የተቃዋሚ ፓርቲዎች አመራሮችና ሌሎች በተመሳሳይ መዝገብ የተከሰሱት ተከሳሾች በቀረበባቸው ክስ ላይ ያቀረቡት መቃወሚያ ውድቅ ተደረገባቸው፡፡ አመራሮቹ ጥር 26 ቀን 2007 ዓ.ም ችሎት ቀርበዋል፡፡
በእነ ዘላለም ወርቃገኘሁ የክስ መዝገብ የተከሰሱት የአንድነት፣ የሰማያዊና የአረና ፓርቲዎች አመራሮች የሆኑት አቶ ሀብታሙ አያሌው፣ የሺዋስ አሰፋ፣ አብርሃ ደስታ፣ ዳንኤል ሺበሽ እና ሌሎች ስድስት ተከሳሾች መቃወሚያቸው በፍርድ ቤቱ ውድቅ ተደርጓል፡፡
ተከሳሾች በጠበቆቻቸው አማካኝነት የቀረቡባቸው የተለያዩ የክስ ይዘቶች ላይ መቃወሚያቸውን አቅርበው የነበር ቢሆንም ፍርድ ቤቱ አቃቤ ህግ የተከሳሽ መቃወሚያ ውድቅ እንዲደረግለት የጠየቀውን በመቀበል ‹‹በመቃወሚያው ላይ የተነሱት ነጥቦች በአብዛኛው ማስረጃ በማሰማት ሂደት ወቅት ሊረጋገጡ የሚችሉ ስለሆኑ›› በሚል መቃወሚያቸው ውድቅ ተደርጓል፡፡ በመሆኑም ፍርድ ቤት በቀረበው ክስ አግባብ የክስ ሂደቱ እንዲቀጥል ውሳኔ ሰጥቷል፡፡
በሌላ በኩል ተከሳሾች በእስር ላይ በሚገኙበት ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ላይ ‹‹የመብት ጥሰት እየተፈጸመብን ነው›› በሚል አቤቱታ አቅርበው የነበር ሲሆን በአቤቱታው ላይ እስካሁን ከማረሚያ ቤቱ መልስ አለመሰጠቱ ታውቋል፡፡ አቤቱታው በጽሑፍ ተገልብጦ ለማረሚያ ቤቱ መላኩን የገለጸው ፍርድ ቤቱ፣ ለአቤቱታው መልስ ከማረሚያ ቤቱ እየተጠበቀ እንደሆነ ተገልጹዋል፡፡
በመሆኑም ይህንኑ የማረሚያ ቤቱን መልስ ለመስማትና የክሱን ሂደት ለመቀጠል ፍርድ ቤቱ ለየካቲት 11 ቀን 2007 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
ምንጭ፡-ነገረ-ኢትዮጵያ
“የስርዓቱን አረመኔያዊ እርምጃ እናወግዛለን!”- የ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር ጥምረት
በተቃውሞ ሰልፉ በአንድነት ፓርቲ አመራርና አባላት እንዲሁም ሌሎች ዜጎች ላይ በፖሊስ የተፈፀመውን ድብደባ የ9ኙ ትብብር ፓርቲዎች ጥምረት አውግዟል፡፡ የ9ኙ የትብብር ፖለቲካ ድርጅት መኢአድ፣ሰማያዊ፣የኦሞ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት፣ የከንባታ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅትና ሌሎች አባላትን ያቀፈ የፖለቲካ ጥምረት ድብደባውን በፅኑ አውግዟል፡፡ ሙሉ መግለጫውን ከዚህ በታች ይገኛሉ፡-
የስርዓቱን አረመኔያዊ እርምጃ እናወግዛለን!
ከ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር የተሰጠ መግለጫ
የ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር አብሮ ስለመስራትና ሌሎቹም ትብብሩን እንዲቀላቀሉ በየጊዜው የሚወተውተው አገራችን በዚህ ዘመን በማይመጥን አምባገነንና የጭካኔ ስርዓት ውስጥ የምትገኝ መሆኑን በመረዳቱ ነው፡፡ ይህ የህወሓት/ኢህአዴግ አምባገነንና ጨካኝ ስርዓት ህዳሩ 27/28 2007 ዓ.ም የአዳር ሰላማዊ ሰልፍ ላይ በወጡት አመራሮቻችን፣ አባላቶቻችን፣ ደጋፊዎቻችንና በየጎዳናው የተገኙት ንፁሃን ላይ ከፍተኛ ድብደባና የጅምላ እስር በመፈፀም ስርዓቱን ለመታገል የተነሳነበትን አላማ ትክክለኝነት አረጋግጦልናል፡፡
በዛሬው ዕለትም ገዥው ፓርቲ በፓርቲያቸው የውስጥ ጉዳይ ገብቶ የሚፈፅመውን ደባ፣ ምርጫ ቦርድንና የህዝብ ሚዲያን ተጠቅሞ ፓርቲውን ለመከፋፈልና አሳንሶ ለማሳየት የሚያደርገውን እኩይ ተግባር በመቃወም ሰልፍ የወጡ የአንድነት አመራሮች፣ አባላት፣ ደጋፊዎችና የፓርቲው ጽ/ቤት ፊት ለፊት የሚገኘው ቤተ ክርስትያን አካባቢ የነበሩ አዛውንት ምዕመናንን ሳይቀር በመደብደብ ጭካኔውን ዳግመኛ አሳይቶናል፡፡ ፖሊስ በትዕዛዝ በአንድነት አባላት ላይ ከፍተኛ የጭካኔ እርምጃ ወስዷል፡፡ አብዛኛዎቹንም በጅምላ አስሯል፡፡
ስርዓቱ በእነዚህ ሰላማዊ ዜጎች ላይ አሁንም የጭካኔ እርምጃውን መድገሙ ስልጣኑን የማጣት ከፍተኛ ስጋት ውስጥ እንዳለ እና ከይስሙላ ያለፈ ለሰላማዊ ትግሉ ዝግጁ አለመሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ ትብብራችን የስርዓቱን ጨካኝነት እያወቁም ቢሆን በሰላማዊ መንገድ ጥያቄያቸውን ለማቅረብ በስርዓቱ የማይከበረውን ህገ መንግስታዊ መርህ ተከትለው ሰልፍ ለወጡ ቆራጥ የአንድነት አመራሮች፣ አባላትና ደጋፊዎች አድናቆቱን መግለጽ ይወዳል፡፡ መስዋዕትነታችሁ ለነገ ድላችን ስንቅ በመሆኑ ይበልጡን ተጠናክራችሁ በጋራ ትግላችን እንደምናጠናክርም እምነታችን ነው፡፡
በተቃራኒው ገዥው ፓርቲ ህግ የማክበርና የማስከበር ሚናውን ረስቶ ፖሊስ፣ ደህንነትንና ሌሎች ተቋማትን ለራሱ ስልጣን ማስጠበቂያ በማዋል በአንድነት አመራሮች፣ አባላት፣ ደጋፊዎች ላይ የፈፀመውን ለዘመኑ የማይመጥንና በሰላማዊ መንገድ መብታቸውን ለጠየቁት ኢትዮጵያውያንም የማይገባ የጭካኔ እርምጃ በጥብቅ እናወግዛለን፡፡
ኢትዮጵያውያንን የማስተዳደር አቅምና ሞራል ያጣው ገዥው ፓርቲ የዜጎችን ጥያቄ በኃይል ማዳፈን የማይቻል መሆኑንና አገራችን ወደባሰ ችግር እንደሚከታት ተረድቶ ከዚህ የጭካኔ እርምጃው እንዲቆጠብ፣ እርምጃውን የወሰዱትን አካላት በህግ ተጠያቂ እንዲሆኑና የታሰሩትን በአስቸኳይ እንዲፈታ እናሳስባለን፡፡ ፖሊስ፣ ደህንነት፣ መከላከያና ሌሎች ተቋማት ገዥው ፓርቲ አላፊ መሆኑን በመገንዘብና ከገዥው ፓርቲ ታዛዥነት በመውጣት ወገኖቻቸሁ ላይ እንዲህ አይነት የጭካኔና አሳፋሪ እርምጃ ከመውሰድ ተቆጥባችሁ ከህዝብ ጎን እንድትቆሙ ጥሪያችን እናቀርባለን፡፡
ያለ መስዋዕትነት ድል የለም!
ጥር 17/2007 ዓ.ም
አዲስ አበባ
በተከሳሽ የፓርቲ አመራሮችና በአቃቂ ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት መካከል ያለው አቤቱታ ምላሽ አላገኘም
∙በቃል የቀረበው አቤቱታ ከድምጽ ክምችት ክፍል ጠፍቷል ተብሏል
በእነ ዘላለም ወርቃገኘሁ የክስ መዝገብ የሽብር ክስ ተመስርቶባቸው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ የሚገኙት የተቃዋሚ ፓርቲዎች አመራሮች እና ሌሎች በተመሳሳይ መዝገብ ያሉ የሽብር ተከሳሾች በቂሊንጦ እስር ቤት አስተዳደር መካከል ያለው አቤቱታ እስካሁን እልባት ሊያገኝ አልቻለም፡፡
ዛሬ ጥር 7 ቀን 2007 ዓ.ም ከፍተኛው ፍርድ ቤት የሰማያዊ፣ የአንድነትና የአረና ፓርቲዎች አመራሮች የሆኑት አቶ የሺዋስ አሰፋ፣ አቶ ሀብታሙ አያሌው፣ አቶ ዳንኤል ሺበሺ እና አቶ አብርሃ ደስታ እንዲሁም አንደኛ ተከሳሽ ዘላለም ወርቅአገኘሁን ጨምሮ ሌሎች ተከሳሾች ማረሚያ ቤቱ የመብት ጥሰት እየፈጸመባቸው እንደሆነ ለፍርድ ቤቱ አቤት ማለታቸው የሚታወስ ሲሆን፣ በዛሬ ዕለት በጉዳዩ ላይ የማረሚያ ቤቱ አስተዳዳሪ ችሎት ቀርበው መልስ ይሰጣሉ ተብሎ ቢጠበቅም ሳይቀርቡ ቀርተዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ ቀደም ባለው ቀጠሮ ወቅት አቤቱታው በቃል ተሰምቶ በመቅረጸ ድምጽ ተቀድቶ እንደገና በጽሑፍ ተገልብጦ ከመልስ ጋር እንዲቀርብ ታዝዞ የነበር ቢሆንም ድምጹ ከፍርድ በቱ ድምጽ ክምችት ክፍል ሊገኝ ስላልቻለ በወረቀት ተገልብጦ መልስ እንዲሰጥበት ለማረሚያ ቤቱ አለመድረሱ ተገልጹዋል፡፡
በዚህ የተነሳም ፍርድ ቤቱ ለጥር 26 ቀን 2007 ዓ.ም የቂሊንጦ ማረሚያ ቤት አስተዳደር ችሎት ቀርቦ መልስ እንዲሰጥ ለማስቻል፣ በቀጣዩቹ ቀናት ውስጥ አቤቱታው እንደገና በጽሑፍ ለፍርድ ቤቱ እንዲቀርብ ውሳኔ ተሰጥቷል፡፡
በተመሳሳይ በቀድሞው የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ኦኬሎ አኳይ የክስ መዝገብ በተከሰሱ ሰዎች ላይ የአቃቤ ህግ ምስክሮች የሰጡት ምስክርነት ከድምጽ ክምችት ክፍል ስለጠፋ እንደገና በሌላ ተለዋጭ ቀጠሮ ድጋሜ ምስክሮቹ እንዲቀርቡ ፍርድ ቤቱ መወሰኑን የነገረ-ኢትዮጵያ ዘገባ አመልክቷል፡፡
ምርጫ ቦርድ በሶስቱ የተፎካካሪ ፓርቲዎች ላይ ውሳኔ ማሳለፉን አስታወቀ
ዛሬ ጥር 5 ቀን 2007 ዓ.ም. ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ በአንድነት፣ በመኢአድ እና ሰማያዊ ፓርቲዎች ላይ ውሳሳለፉን አስታውቋል፡፡ ቦርዱ ውሳኔ ብሎ ያስተላለፈው ፤ አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) እንዲሁም የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) የውስጥ ችግራቸውን መፍታት አልቻሉም በሚል ለዛሬው ውሳኔ እሰጣለሁ ብሎ የነበረው ምርጫ ቦርድ ሁለቱ ፓርቲዎች በሁለት ሳምንት ውስጥ የውስጥ ችግራቸውን ፈትተው ሌላ ጠቅላላ ጉባኤ እንዲያደርጉ የመጨረሻ ጊዜ ሰጥቻቸዋለሁ ሲል ገልጾአል፡፡
ቦርዱ ዛሬ ከሰዓት በሰጠው መግለጫ በአንድነትና መኢአድ ስም የተለያዩ ጉባኤዎች በመደረጋቸው ሁለቱ ፓርቲዎች ጥር 3 ያደረጉትን ጠቅላላ ጉባኤ ላይ አለመገኘቱን፣ አንድነት የ2004 ዓ.ም እንዲሁም የመኢአድን የ2001 ዓ.ም ደንብን እንጅ ከዛ በኋላ ያሉትን የፓርቲውን ደንቦች እንደማያውቅ በመግለጽ በሁለት ሳምንት ውስጥ ጠቅላላ ጉባኤ አድርገው ችግራቸውን እንዲፈቱ የመጨረሻ ጊዜ ሰጥቻለሁ ብሏል፡፡
በሌላ በኩል መድረክ ረግጦ በመውጣት፣ ሌሎች ፓርቲዎች እንዲያድሙ በማድረግ፣ ቦርዱ የማያውቀው ትብብር በመመስረት በሚል በምርጫ ቦርድ ክስ የቀረበበትና ይቅርታ እንደማይጠይቅ በደብዳቤ ለገለጸው ሰማያዊ ፓርቲ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ሰጥቻለሁ ብሏል፡፡ ማስጠንቀቂያውን የማያከብር ከሆነም ቦርዱ ህጋዊ እርምጃ እወስዳለሁ ብሏል፡፡
የቦርዱ ባለስልጣናት ‹‹ሰማያዊ ፓርቲን ህገ ወጥ ትብብር በመመስረት ስትከሱ ሌሎቹን የትብብሩን አባል ፓርቲዎች ለምን አልከሰሳችሁም?›› በሚል ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ፕሮፌሰር መርጋ በቃና ‹‹ፓርቲዎቹ 9 መሆናቸውን የሰማሁት አሁን ነው፡፡›› ብለዋል፡፡ በተመሳሳይ ‹‹እስካሁን ሌሎች ትብብሮችን ምርጫ ቦርድ አያውቃቸውም ብላችሁ ከሳችሁ አታውቁም›› በሚል የ9ኙን ፓርቲዎች ትብብር ህገ ወጥ ነው ካሉ ገዠው ፓርቲ ከአጋሮቹ ጋር ያለውን ግንኙነትን ለምን ህገ ወጥ ነው እንደማይሉ ለቀረበላቸው ጥያቄም ፕሮፌሰር መርጋ በቃና ‹‹ኢህአዴግ እንደገዥ ፓርቲ አጋር ፓርቲዎች ሊኖሩት ይቻላል፡፡ እንደ ገዥ ፓርቲ ከአጋሮች ጋር መስራት ይችላል፡፡ እንዲህ አይነት ነገሮችን ቦርዱ አይመለከተውም›› ሲሉ መልሰዋል፡፡
አንድነትና መኢአድ በሁለት ሳምንት ውስጥ ችግራቸውን እንዲፈቱ ተጨማሪ ጊዜ ሰጥቻለሁ ያለው ምርጫ ቦርድ በሁለት ሳምንት ውስጥ ችግራቸውን ካልፈቱ ቦርዱ ተሰብስቦ ውሳኔውን አሳውቃለሁ ማለቱን የነገረ-ኢትዮጵያ ዘገባ ያመለክታል፡፡ አንድነት እና መኢአድ ምርጫ ቦርድ እስከ ጥር 4 ቀን 2007 ዓ.ም. ጠቅላላ ጉባዔ አድርጉ ባለው መሰረት ያለፈው እሁድ ጥር 3 ቀን 2007 ዓ.ም. ባደረጉት ጠቅላላ ጉባኤ አንድነት ፓርቲ በድጋሚ አቶ በላይ ፈቃዱን ፕሬዘዳንት አድርጎ ሲመርጥ፤ መኢአድም እንዲሁ በተመሳሳይ ቀን ጠቅላላ ጉባዔ ያደረገ ሲሆን፤ በዕለቱ ምርጫ ቦርድ በህጉ መሰረት በሁለቱም ፓርቲዎች ጠቅላላ ጉባኤ ላይ እንዲገኝ የጥሪ ደብዳቤ ቢደርሰውም በሁለቱም ጉባኤ ላይ የቦርዱ ተወካይ እንዳልተገኘ ታውቋል፡፡ ይሁን እንጂ ቦርዱ አሁንም ለሶስተኛ ጊዜ ሁለቱም ፓርቲዎች ጠቅላላ ጉባዔ እንዲያደርጉ የሁለት ሳምንት ጊዜ ሰጥቻቸዋለሁ ሲል ዛሬ በፅህፈት ቤቱ ለጋዜጠኞች በሰጠው መግለጫ አስታውቋል፡፡
…….





