ዶክተር መረራ ጉዲና እና ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ክስ ተመሰረተባቸው
(አዲስ ሚዲያ) ከ3 ወር በፊት በአውሮፓ ፓርላማ ስለ ኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ተጋብዘው ንግግር ያደረጉት ዶ/ር መረራ ጉዲና ወደ ሀገር ቤት ሲመለሱ ከአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ተይዘው ለ 3 ወራት በማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ ከታሰሩ በኃላ የካቲት 16 ቀን 2009 ዓ።ም በገዥው መንግሥት ጠቅላይ አቃቤ ህግ አማካኝነት በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ወንጀል ችሎት ክስ ተመሰረተባቸው።

ዶክተር መረራ ጉዲና እና ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ
የቀድሞ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር የነበሩት እና የኦፌኮ ሊቀመንበር እንዲሁም የመድረክ ምክትል ሊቀመንበር የሆኑት ዶክተር መረራ ክስ የተመሰረተባቸው፥ በአውሮፓ ህብረት በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ንግግር ለማድረግ ተጋብዘው ሲመለሱ የአርበኞች ግንቦት ሰባት አመራር እና ሊቀመንበር ከሆኑት ከፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ጋር ታይተዋል በሚል እንደነበር ይታወቃል።
በዶ/ር መረራ ስም የተከፈተው በዚሁ የክስ መዝገብ ፥ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ሁለተኛ ተከሳሽ ፣ አቶ ጃዋር መሃመድ ሶስተኛ ተከሳሽ በመሆን በልይሉበት ክስ ተመስርቶባቸዋል፡፡ ሶስቱም ተከሳሾች የተከሰሱት በወንጀለኛ መቅጫ ህጉን የተለያዩ አንቀጾች በመተላለፍ ሲሆን አራተኛ እና አምስተኛ ተከሳሽ የሆኑት የኢትዮጵያ ሳተላይ ቴሌቪዥን ( ኢሳት) እና ኦሮሞ ሚዲያ ኔትወርክ ( ኢኤም ኤን) ሲሆኑ፥ ተቋማቱ የፀረ ሽብር ህጉን በመተላለፍ ተከሰዋል፡፡
ዶ/ር መረራ ሌላ ተጨማሪ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን መተላፍ በሚል ክስ ተመስቶባቸዋል፡፡ የክሱ ጭብጥም ተከሳሾች በዋና አድራጊነት ሽብር ተግባር መፈጸማቸውን እና ለኦሮሚያ እና አማራ ክልል አመጾች ማነሳሳት እና ንብረት መውደም ተጠያቂ መሆናቸው በክሱ ላይ ተጠቅሷል።
የፌደራሉ ከፍተኛው ፍርድ ቤትም ክሱን ለማየት ለየካቲት 24 ቀን 2009 ዓ ም ቀነ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
በተለይ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ከዚህ በፊት በሌሉበት በነ ጄነራል ተፈራ ማሞ የክስ መዝገብ የሞት ፍርድ የተፈረደባቸው ሲሆን፥ በነ አቶ አንዱዓለም አራጌ የክስ መዝገብ ደግሞ የዕድሜ ልክ ፅኑ እስራት የተፈረደባቸው ሲሆን፥ የአሁኑ ከነ ዶ/ር መረራ ጉዲና ጋር የተመሰረተባቸው ክስ ለሶስተኛ ጊዜ መሆኑ ታውቋል።
መንግሥት ከህዳር 2008 ዓ ም ጀምሮ በተለይ በኦሮሚያ ፥ በአማራ ክልል እና በደቡብ ክልል ኮንሶ ከአንድ ዓመት በላይ የዘለቀ ህዝባዊ አመፅን ተከትሎ በርካታ ሰላማዊ ሰዎች በመንግሥት ወታደራዊ ኃይል ሲገደሉ፥ በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ሲታሰሩ ከ15 ሺህ ያላነሱ በተለያየ ጊዜ ከእስር መልቀቁን መንግሥስት ቢያስታውቅም አሁንም ድረስ ህዝባዊ አመፁን ተከትሎ የታሰሩና ሰብዓዊ መብቶቻቸው እየተጣሰ ያሉ ዜጎች መንግሥስት ከእስር ልቅቄያቸዋለሁ ክሚለው ቁጥር እንደሚልቅ ይግመታል።
ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በፊት መንግሥት በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ አማካኝነት ለህዝባዊ አምፁ ተጠያቂ ራሱ መንግሥት እና አመራሮች እንደሆኑ ቢይሳውቁም፥ ለግድያ፥ እስርና እንግልት የተዳረጉት ግን ሰላማዊ ዜጎች መሆናቸውን የሀገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች መግለፃቸው ይታወሳል።
በቂሊንጦ ለደረሰው ቃጠሎ ተጠያቂዎች ናችሁ በሚል በሽብር የተከሰሱት እስረኞች ላይ የሚደርሰው ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት ቀጥሏል
*ለፍርድ ቤት አቤቱታ ማሰማታቸውን ተከትሎ ጨለማ ቤት እንዲታሰሩ ተደርገዋል

ዶ/ር ፍቅሩ ማሩ ፎቶ ከሲውድን ሬዲዮ
ነሐሴ 28 ቀን 2008 ዓ.ም በአዲስ አበባ ቂሊንጦ እስር ቤት የደረሰውን የእሳት ቃጠሎ ተከትሎ ለጠፋው የሰው ህይወትና ለደረሰው የንብረት ውድመት ተጠያቂዎች ናችሁ በሚል የፌደራል አቃቤ ህግ በፍይደራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት የሽብር ክስ መስርቶባቸው በእስር ላይ የሚገኙት 38 ተከሳሾች ላይ የሚፈጸምባቸው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ቀጥሏል፡፡
ተከሳሾች ታህሳስ 14 ቀን 2009 ዓ.ም በነበረው የችሎት ውሎ ወቅት በእስር ቤት እየደረሰብን ነው ያሉትን ኢ-ሰብዓዊ አያያዝ በተመለከተ አቤቱታ ማሰማታቸውን ተከትሎ ወደ እስር ቤቱ ሲመለሱ ጨለማ ክፍል፣ በጠባብ ቤት ውስጥ ታጭቀው እንዲታሰሩ መደረጋቸውንም ለማወቅ ተችሏል፡፡
በህክምና ላይ የሚገኙት የ66 ዓመቱ ኢትዮ- ሲውድናዊው የልብ ህክምና ባለሙያ እና የ “አዲስ የልብ ህክምና ሆስፒታል” መስራች ዶ/ር ፍቅሩ ማሩን ጨምሮ በእነ ማስረሻ ሰጤ የክስ መዝገብ የሽብር ክስ የቀረበባቸው 38 ተከሳሾች፣ የጸረ-ሽብር ህጉን አንቀጽ 3 (1፣ 2፣ 4 እና 6) ስር የተመለከተውን የወንጀል ድርጊት ተላልፈዋል በሚል አቃቤ ህግ በህዳር 13 ቀን 2009 ዓ.ም በይፋ ክስ እንደመሰረተባቸው ይታወሳል፡፡ ከዚህ ክስ በተጨማሪም ሌሎች 131 ሰዎች ላይ በተመሳሳይ ክስ መከፈቱ ለመንግስት ቅርበት ባላቸው መገናኛ ብዙሃን ተዘግቦም ነበር፡፡
ተከሳሾቹ በምርመራ ወቅት እጅግ የከፋ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ይፈጸምባቸው እንደነበር በተደጋጋሚ ይፋ መደረጉ የሚታወስ ሲሆን፣ ይህንኑ የተፈጸመባቸውን ድርጊት ለችሎት ለማስረዳት መሞከራቸውን ተከትሎ ደግሞ አሁን ላይ በጨለማ ክፍል እንዲታሰሩ ተደርገዋል፡፡
በታህሳስ 14 ቀን 2009 ዓ.ም በነበረው የችሎት ውሎ ዳኞቹ ወደ ችሎት ሲገቡ ሁሉም ተከሳሾች ከመቀመጫቸው በመነሳት፣ ‹‹በእሳት ቃጠሎው ወቅት ህይወታቸውን ላጡ በእስር ላይ የነበሩ ወንድሞቻችን የህሊና ጸሎት እናደርጋለን›› በማለት ጸሎት አድርገው መቀመጣቸውና በወቅቱ ለደረሰው ቃጠሎም ተጠያቂው ያሰራቸው አካል መሆኑን መናገራቸው አሁን ላይ በጨለማ ክፍል ለመታጎር እንደዳረጋቸው ቤተሰቦቻቸው እምነታቸውን ይገልጻሉ፡፡
የተከሳሽ ቤተሰቦች በተከሳሾች ላይ እየደረሰ ያለው ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት እንዲቆም የከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንትን ቢያነጋግሩም፣ ‹‹ጉዳያችሁን ወደ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ውሰዱ›› የሚል መልስ እንዳገኙ ታውቋል፡፡ በዚህም የተከሳሽ ቤተሰቦች ጠቅላይ አቃቤ ህግ በማምራት ዋና ጠቅላይ አቃቤ ህግ አቶ ጌታቸው አምባየንና ምክትል ዋና ጠቅላይ አቃቤ ህግ አቶ ብርሃኑ ወ/አገኝን አነጋግረዋል፡፡ አቶ ጌታቸው ለተከሳሽ ቤተሰቦች ‹‹ጉዳያችሁን በጽሁፍ አቅርቡ›› በማለት አቤቱታቸውን በጽሁፍ የተቀበሉ ሲሆን፣ በጉዳዩ ላይ ታህሳስ 21 ቀን 2009 ዓ.ም ምላሽ ለመስጠት ቀጠሮ ሰጥተው ነበር ፡፡ ነገር ግን ከቀናት በኋላም ፍርድ ቤቱ ውሳኔ የሚሰጥበት ጉዳይ ነው የሚል ሰበብ ምላሽ እንዳላገኙ ተናግረዋል፡፡
ለፍርድ ቤቱ የቀረበው የተከሳሾችን አቤቱታ ከታች ይመልከቱ


ምንጭ፦ ኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ፕሮጀክት
የመብት አራማጅ ንግስት ይርጋ የሽብር ክስ ተመሰረተባት
በአማራ ክልል የተቀሰቀሰውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ ጎንድር ውስጥ ለእስር ተዳርጋ ወደ ማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ ተዛውራ ከአራት ወራት በላይ ያሳለፈችው አክቲቪስት ንግስት ይርጋና ሌሎች አምስት ሰዎች የሽብር ክስ ተመስርቶባቸዋል፡፡

ንግስት ይርጋ
የፌደራል አቃቤ ህግ ታህሳስ 28 ቀን 2009 ዓ.ም. በጻፈውና ለተከሳሾች ጥር 1 ቀን 2009 ዓ.ም. እንዲደርሳቸው በተደረገው የክስ ቻርጅ ላይ እንደተመለከተው ንግስት ይርጋ ‹‹ከአርበኞች ግንቦት ሰባት የሽብር ድርጅት ጋር ግንኙነት በመፍጠር፣ በሰሜን ጎንደርና በሌሎች የአማራ ክልል አካባቢዎች አመጽ በማስነሳት፣ አመጹን በበላይነት በመምራትና በማስቀጠል…›› የሽብር ወንጀል ድርጊት ተሳታፊ በመሆን ክስ ቀርቦባታል፡፡
ንግስት ይርጋ 1ኛ ተከሳሽ በተደረገችበት የክስ ዝርዝር ላይ እንደተመለከተው፣ ተከሳሾች በ2001 ዓ.ም የወጣውን የጸረ ሽብር አዋጅ አንቀጽ 3/4/6ን በመተላለፍ ተከሰዋል፡፡
የመብት አራማጅ ንግስት ይርጋ ነሐሴ ወር ላይ በጎንደር ከተማ በነበረው ሰላማዊ ሰልፍ ወቅት ‹‹የአማራ ህዝብ አሸባሪ አይደለም›› የሚል ጽሁፍ የሰፈረበት ቲሸርት ለብሳ በሰልፉ ላይ መታየቷ ይታወሳል፡፡
ክሱ የቀረበለት የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት የቀረበውን ክስ በንባብ ለማሰማት ለጥር 10 ቀን 2009 ዓ.ም ቀጠሮ ይዟል፡፡
ምንጭ፦ EHRP
በእነጉርሜሳ አያኖ መዝገብ 5ት ቀሪ የአቃቤ የህግ ምስክሮችን ለመስማት ተጨማሪ ቀን ተሰጠ
አቃቤ ህግ ታህሳስ 27 ቀን 2009 ዓ. ም. ቀሪ ምስክሮች ቀርበው እንደሆነ ሲጠየቅ፤ አምስት ምስክሮች እንደሚቀሩት እና ተገቢውን ጥረት ቢያደርግም ሊቀርቡ እንዳልቻሉ በመግለፅ የበለጠ ጉዳዩን እንዲያስረዱለት ከፓሊስ የቀረቡትን ረዳት ኢንስፔክተር ቴድሮስ አዳነ ጠይቋል።

አቶ በቀለ ገርባ
ረዳት ኢንስፔክተሩ የተሰጣቸው ጊዜ አጭር በመሆኑ በተሰጠው ቀጠሮ ሁሉንም ማቅረብ አለመቻላቸውን፤ ምስክሮቹ አካባቢያቸውን አበመልቀቃቸው በአዲሱ አድራሻቸው እያፈላለጓቸው በመሆኑ፤ ራቅ ያለ ቦታ ያሉ ምስክር በመኖራቸው ከፍተኛ የጊዜ እጥረት ስለገጠማቸው በመሆኑ ጊዜ እንዲጨመርለት ጠይቋል። በመቀጠልም አቃቤ ህግ ከቀሩት 5ት ምስክሮች ውስጥ አንዱ ጉጂ ዞን የሚገኝ፣ አንዱ ፀበል ላይ እንደነበረ እና ማስረጃ እስኪያመጣ ጊዜ ስላጠረ፣ አንደኛው አድራሻ ቀይሮ ሌላ ቦታ በመሄዱ በተሰጠው ጊዜ ቀርበው መመስከር እንዳልቻሉ ተናግሮ የተቀሩት ሁለቱ ግን የአዲስ አበባ ነዋሪ መሆናቸውን መመስከር ስላልፈለጉ አድራሻቸውን እየቀያየሩ እንዳስቸገሯቸው ተናግሯል። እስካሁን ይመሰክራሉ ከተባሉ 42 ምስክሮች ውስጥ 37ቱን እንዳሰማ የተናገረው አቃቤ ህግ የተከሰሱበትን የክስ ክብደት እንዲሁም ከፍተኛ ጉዳት ያስከተለ ተግባር መሆኑን ከግምት ውስጥ በማስገባት ቀሪ ምስክሮችን አቅርበው እንዲያሰሙ ተጨማሪ ጊዜ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።
የተከሳሽ ጠበቆች የተሰሙት ምስክሮች በችሎቱ ግፊት እንጂ አቃቤ ህግ ዳተኛ እንደነበረ፤ ምስክሮቹን ማቅረብ ስላልፈለገ እንጂ በቂ ጊዜ ተሰጥቶት እንደነበረ፤ የፍትህ ሂደት የሚለካው በሂደቱም ጭምር መሆኑን፤ ከባለፈው ቀጠሮ ጀምሮ በሰበብ አስባቡ ምስክሮችን ለማምጣት በሚል ቀጠሮ መሰጠቱን ተቃውመው እንደነበረ እና የዛሬው ቀጠሮም የመጨረሻው በሚል የተያዘ እንደሆነ ገልፀው ተጨማሪ ቀጠሮ መሰጠት እንደሌለበት ተናግረዋል።
“እንደሚታወቀው ከታሰርን ሁለት ወራችን አይደለም። አንድ አመት አልፎናል። እነሱ ቤታቸው እያደሩ እኛን እያሾፉብን ነው። በአንድ ቀን ብዙ ሺዎችን እያሰረ ያለ መንግስት፤ እንዴት ነው 5ት ምስክሮችን ማቅረብ ያልቻሉት? ” በማለት የኦፌኮ ም/ፕሬዝዳንት አቶ በቀለ ተጨማሪ ቀጠሮ መኖር የለበትም ሲሉ ተከራክረዋል። አቶ ደጀኔ ጣፋም ተቃውሟቸውን ለችሎቱ አሰምተዋል። “አቃቤ ህግ ሲናገር 2ቱ አዲስ አበባ ናቸው ብሏል። ለምን አልቀረቡም እስካሁን? ክሳችን መጀመሪያም የፓለቲካ ክስ ነው አሁንም የፓለቲካ ድምዳሜ ነው የምንሰማው። እንዲሁ እንደከሰሳችሁን እንዲሁ ፍረዱብን። ወይስ ፍትህ አለ ለማስባል ነው? የኛን እና የናንተን ጊዜ ለምን ይፈጃሉ? ጉጂ እኮ ወርቅ የሚዘረፍበት ነው። እንዴት ከዛ አንድ ሰው ማምጣት ይከብዳቸዋል? አቃቤ ህግ ሌላ ጫና ከሌለባቸው በህጉ አግባብ ይስሩ። ፍርድ ቤት በየጊዜው እያሳሰሰባቸው ነው ምስክር ይዘው ሚቀርቡት። ያልቀረቡ ምስክሮችን በተመለከተ ከቀበሌ ደብዳቤ ይዘው ቀርበዋል ወይ? አልቀረቡም! የፍርድ ቤት ትእዛዝ እየተከበረ አይደለም። እናንተም የካድሬ አይነት ሳይሆን የባለሙያነት አሰራር ስሩልን።” በማለት ሌላ ቀጠሮ መሰጠቱን እንደሚቃወሙ ተናግረዋል።
“አቃቤ ህግ ዛሬ አጭር ጊዜ ነው የተሰጠን ብሏል በወቅቱ ቀጠሮ ሲሰጥ ለምን አጭር ጊዜ ነው የተሰጠን አይበቃንም አላለም? ከቀበሌ ይቅረብ የተባለው ማስረጃ አልቀረበም። የችሎቱ ብይን መከበር አለበት። ማእከላዊ ሲያሰቃዩን የነበሩ ፓሊሶች ናቸው ዛሬ ቀርበው ያልተገባ ተጨማሪ ቀጠሮ እየጠየቁ ያሉት።” ሲል የተጨማሪ ቀጠሮውን ጉዳይ ተቃውሞ አሰተያየታቸውን የሰጡት አቶ አዲሱ ቡላላ ናቸው።
ዳኞች ከተማከሩ በኋላ አቃቤ ህግ ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራ፤ ተከሳሾችን ደግሞ የፓለቲካ እስረኛ ብሎ ነገር እንደሌለ፣ ያሉበትን ሁኔታ እንደሚረዷቸው፣ እንዲያውም ማነፃፀር ባይገባም ከሌላው መዝገብ ሲተያይ በፍጥነት እየሄደ መሆኑን፣ እነሱም [ተከሳሾች] መከላከያ ምስክር በሚያሰሙበት ጊዜ ምስክሮችን ለመስማት ጊዜ እንደሚሰጡ በመግለፅ ፓሊስ በ15 ቀን ውስጥ ከየትም ፈልጎ ምስክሮቹን እንዲያመጣ፤ የማይገኙ ከሆነም ይኖሩበት ከነበረው ቀበሌ ደብዳቤ እንዲቀርብ ትእዛዝ ሰጥተዋል። አቃቤህግ የተሰጠው ጊዜ አጭር እንደሆነ በመግለፅ ትንሽ ረዘም ያለ ቀጠሮ እንዲሰጠው ቢጠይቅም ዳኞች ጥያቄውን ሳይቀበሉት፤ ፓሊስ የተቻለውን ሁሉ ጥረት በማድረግ በቀጠሮው ቀን እንዲያቀርብ አዘዋል።
የተከሳሽ ጠበቃ የሆኑት አቶ መልካሙ የሚሰጠው ቀጠሮ የመጨረሻ እንዲሆን በሚል ላቀረቡት ሃሳብ፤ የመጨረሻ ቀጠሮ የሚባል እንደሌላ አሳማኝ ምክንያት ከተገኘ ሌላ ቀጠሮ ሊሰጥ እንደሚችል፤ አሳማኝ ምክንያት ካልተገኘ የመጨረሻ ባይባልም የምስክር የመስማት ሂደት ሊቋረጥ እንደሚችል በመጥቀስ ቀጣዩ ቀጠሮ የመጨረሻ መባል የለበትም ሲሉ ዳኞች መልስ ሰጥተዋል።
ቀሪ የአቃቤ ህግ ምስክሮችን ለመስማት ለጥር 15 ቀን 2009 ዓ. ም. ቀጠሮ ተይዟል።
ምንጭ፦EHRP
በማንነት ፖለቲካው ምስቀልቅል የአማራ ብሔረተኛነት ተጽዕኖና ተግዳሮቶቹ
የሱፍ ያሲን
yussuf.yassin @gmail.com

የሱፍ ያሲን
1. አማራ ከሰኔ (1983) ኮንፊረንስ እስከ ጥቅምት (2009) ስብሰባ
አማራ ወያኔ ኢሕዴአግ በጠራው የአዲስ አበባ 1983ቱ (1991) የሰኔ ኮንፊረንስ አልተወከለም ነበር። በቅርቡ በዋሽንግተኑ የጥቅምት 2009 (2016) በኢትዮጵያ ሃገራዊ ንቅናቄ (ኢሃን) ስብሰባ ላይም አልተወከለም ተባለ። በሁለቱም ስብሰባዎች አማራ ተገቢ ውክልና አላገኘም ነው አንዱ ቅሬታው። በመጀመሪያው ኮንፊረንስ ውክልና የተነፈገው በብሔረሰቡ ስላልተደራጀ ነው የሚል ምክንያት ነበር በኮንፈረንሱ አዘጋጆች የተሰጠው። ላሁኑ “አለመወከል” የተሰጠው ምክንያትም የአማራ ብሔረተኞችን አላረካም እንዲያውም አስቆጣ እንጂ። እንዲያውም የሚወክለው ሰው ጠፍቶ አማራ ባንድ ሰው ተወክሎ ነበር መባሉን በቅርቡ በሲያትል የተሰበሰቡት የአማራ ድርጅቶች ወኪሎች እንደ ስድብ ነው የቆጠርነው ነበር ያሉት። የመጀመሪያው ወይም የ 1983 ቱ “አለመወከል” አማራን አዲሱ መንግሥት እነሱን የሚመለከትበትን መነጽር አመላካችና የመከራ ደወል ጅማሮ ነበር ማለት ይቻላል። ምናልባት ፕሮፌሰር አሥራት ወልደየስ አማራ በራሱ መደራጀት እንዳለበት የተገነዘቡበት የመጀመሪያው አጋጣሚ ነው ማለት ይቻል ይሆናል። ለሁለተኛ ግን አማራ ከ25 ዓመት በኋላ በራሱ እንዲደራጅ ተጨማሪ አንደርዳሪ ግፊት አሳርፎ አልፏል። በተጨማሪም ምናልባት ሰሞኑን በማሕበራዊ ሜዲያ ለሚንመለከተው እንካ ስላንቲያና መፈራረጅ ቀጥተኛ ምክንያት ሆኗል ማለትም ያስኬዳል።
በሁለቱ ስብሰባዎች መሃል ግን በድልድዩ ሥር ብዙ ውሃ ፈሷል (so much water has passed under the bridge) ፈረንጆች እንደሚሉት። በሁለቱ ስብሰባዎችና መካከሎች የአማራ ማንነት በርካታ ውጣ ውረዶችን አስተናግዷል። በርካታ እንግልቶች በማህበረሰቡ ላይ ደርሰዋል። የአማራ የማንነት ትግሉ በርካታ አባጣና ጎርባጣ መንገዶችን ተጉዟል።
የአማራን በአማራነት አደረጃጀት እና ብሔረተኛነት ከፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ እስከ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ አመራር በርካታ የእድገት እርከኖች ተረማምዷል። ኢህዴንን ወደ ብአዴን ከቀዳማዊ መአሕድ እሰከ ዳግማዊ መአሕድ ከበደኖ ፍጅት እስከ ከጉራፈርዳና የቤን ሻንጉል መፈናቀሎች እንዳሉ ሆነው፡፡ በመሃሉ የእስታቲስትክስ ዋና መሥሪያ ቤት የአማራ ሕዝብ ቁጥር የመቀነሱ ዘገባ (ሪፖርት) በዚያ መሃል የተከሰተ ነበር። ሴቶች እንዳይወልዱ ከማምከን እስከ ጄኖሳይድ የሚደርሱ ሰቅጣጭ ወንጀሎች ድረስ ይሄዳሉ ክሶቹ። ወደ ኋሊት ተኬዶ እስከ ስመጥፉው የሕወሓት 1968ቱ ማኒፈስቶ ድረሰ መመለስ ይቻላል ይሆናል። እንዲያውም ትንሽ የኋሊት እንድርድሮሹን እስከ የ1969ኙ የዋለልኝ መኮነን “የብሔረሰቦች ጉዳይ” አርቲክል ድረስም መሄድም ይቻል ይሆናል። እነዚህ ሁለት ሰነዶች አማራን እንደ ጠላት የፈረጁና ለተከተለው ጥፋት ያመቻቹ ዋቢ መጣቀሻዎች ተብለው የሚገመቱት ናቸውና፣ በነገዱ ብሔረተኞች። የወልቃይት-ጠገዴ አማራ ማንነት ኮሚቴ አባላት በቁጥጥር ሥር መዋልን ተከትሎ የተቀጣጠለው የጎንደርና የጎጃም ገበሬና የከተማ ሕዝብ መነሳሳት ትግሉን ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋገረ ኹነት ነው በተለይም ከኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ ወደ ትግራይ መወሰድ በኋላ መፈክሩ አማራ ተደራጅ ሳይሆን ተነስ፣ ተባበር፣ መክት ነው! እንደ ወልቃይት ጠገዴ የአማራ ማንነት ጥያቄ የአማራ ማንነት ተጋድሎና ብሔረተኛነትን ያጦዘው ጉዳይ አልነበረም ቢባል ምንም ማጋነን የለበትም። ዛሬ አማራ በነገዱ ይደራጅ ወይስ?… የሚለው ጥያቄ የአማራ ተወላጆችንም ሆነ ቀሪውን ኢትዮጵያዊ አያሳስብም። መነጋገሪያ ርእስም አይደለም፣ ብዙዎቹ ዘንድ። ምክንያቱም አማራ ካንድ ድርጅት በላይ ተደራጅቶ ይገኛል። አዲስ የተቆጡ አማራ ወጣቶች (Angry Amhara Young Men) አመራር የተቆናጠጡበት ከግማሽ ደርዘን ያላነሱ የአማራ ድርጅቶች ተመስርተዋልና። ከፊሎቹም ሰሞኑን በአሜሪካ እየተዋሃዱ ይገኛሉ።
በ1983ቱ አለመወከልና በ 2009 “አለመወከል” ቅሬታ መሃል በአማራ አደረጃጀት መሠረታዊ ለውጥ ተካሄዶበታል። በቅርጽም በይዘትም። በአቅጣጫውም፣ ገላጭ ባሕርያቶቹም። አማራ አለ ወይም የለም የሚለው ክርክርም ሆነ በማንነቱ ይደራጅ ወይስ አይደራጅ እሰጥ አገባም ካበቃ ሰንበትበት ብሏል። አማራ በምን መልኩ ተደራጅቶ ነው ከአጥቂዎች ራሱን መጀመሪያ መከላከል ብሎም በስሙ የተደራጁትን እንዴት ተግባራቸውን አቀናጅተውና አስተባብረው እንዲያውም ተዋህደው ነገዱን በወያኔ ከተደገሰለት ጥፋት የማዳኑን ተግባር የቅድሚያ ቅድሚያቸው አድርገው መንቀሳቀሱን የሚያያዙት? የወቅቱ ጥያቄ አማራ አለ? የለም? የሚልም ወይም ይደራጅ? አይደራጅ? ሳይሆን የተቀጣጠለው የአማራ ተቃውሞና ተጋድሎ አቅጣጫው ወዴት ነው? በሃገሪቷ የነጻነት ትግል ላይም ምን ዓይነት ተፅዕኖ ያሳርፋል። አልፎ ተርፎ በኢትዮጵያ የወደፊት እጣ ፋንታ ላይ ምን ዓይነት እንደምታ ይኖረዋል? እየሆነ መምጣቱ ግልጽ ነው።
የእነዚያ እድገቶችና ክሶች ትክክለኛነትንም ማጣራትም ሆነ መመርመር ከዚች አጭር መጣጥፍ ማቀፍና አቅም ውጭ ነው። የአማራ ብሔረተኛነት እንቅስቃሴን ውልደት፣ እድገትና ውጣ ውረዶቹን ቃኝተን እንቅስቃሴው በአሁኑ ወቅት ያለበትን ደረጃ በዚህ መጣጣፍ በሰፊው ለመተንተን መሞከር አስቸጋሪ ይሆናል፣ እዚህ የአማራ “ብሔረተኛነት” የደረሰበትን እድገት ደረጃ ተመልክቶ፣ በሃገሪቷ ለውጥ ብሎም በሕልውናዋ ላይ የሚያሳርፈውን ተጽእኖ፣ ጫናና የሚጫወተውን ሚና መቃኘቱ አስፈላጊ ነው። በተለይም በምንገኝበት ባሁኑ በአተረማማሹ የማንነት ፖለቲካ ምስቅልቅል ውስጥ ሆነን።
የአማራ “ብሔረተኛነት” እና የተደቀኑበት ተግዳሮቶች
በአሰባሳቢ ማንነት መጽሓፌ የኦሮሞ ብሔረተኛነት ራሱን በቻለ ምዕራፍ (የኦሮሞ ብሔረተኛነት፣ የማንነት ፖለቲካና ተፈታታኝ ተግዳሮቶቹ) እንዲፍታታ የተመረጠበት ምክንያት ብዙ አያመራምርም። የኦሮሞ ብሔርተኞች ጥያቄ ኢትዮጵያ አንደ አገር የመቀጠል ወይም የመበታተን ወሳኝ ሚና አለው ከሚለው እሳቤ በመነሳት ነው። በተባለው ምዕራፍ እንደተደረገው አዲሱን የአማራ ማንነት ታጋድሎና ብሔረተኛነት ከኦሮሞ ማንነት ተጋድሎና ብሔረተኛነት ጋር ማነጻጸሩ ማስኬዱ አጠያያቂ ነው። በምዕራፉ የተፍታቱት የኦሮሞ ብሔረተኛነት እድገት፣ አነሳስ፣ የወል የሰቆቃ ታሪክ፣ የኦሮሙማ አይድዮሎጂ ቀረጻና የታጋረጠበት ተግዳሮቶቹ ከሥር መሠረቱ ይለያሉ። ዛሬ በኢትዮጵያ ከሚታዩት የብሔረሰብ (ነገድ) ብሔረተኛነት ጋርም ቢሆን ማወዳደሩም ሆነ ማነጻጸሩ አግባብነቱም አጠያያቂ ነው። እንዲያውም በሌሎች ሃገራት ከተመለከትናቸው ከየትኛው ሃገር ብሔረተኛ እንቅስቃሴ የሚመሳሰልበት ገላጭ ባሕሪያት በቀላሉ ማግኘት አይታሰብም። ማንኛውም የሃገሪቷ አስተዳደር ያልተማከለ (Decentralize) የማድረጉ ጥረት በጥርጣሬ ዓይን በመመልከቱ ረገድ የአማራ ብሔረተኛነት ከቀድሞ ዩጎስላቪያው የሰርብ ሕዝብ ብሔረተኛነት ጋር የሚጋራው ገጽታ አለው። ሰርቦች ከቀድሞ ዩጎስላቪያ ሕዝብ 40% በመሆናቸው በጀርመንኛው ሊተረቸር ስታቲስ-ቮልክ (Staatsvolk) ወይም የሃገሬው ዋልታ ሕዝብ ይሰኙ ነበር። እርግጥ የቁጥር አብላጫ የሆነው ኦሮሞ ሳይሆን የኢትዮጵያ የሀገር-መንግሥት መሠረተ-ሕዝብ አማራ ነው ሊባል የሚቻል ይመስለኛል።
አማራው በዋናነት የተጋረጠበት ተግዳሮት ከኢትዮጵያዊነትና ከኢትዮጵያ ማንነት ጋር ያለው ቁርኝት ነው። የአማራ ብሔረተኛነት ከኦሮሞም ሆነ ከሌላ ሃገር ብሔረተኝነቶች ጋር የማይመሳሰልበት ገላጭ ባሕሪያትን ደግሞ መመልከት ተገቢ ነው። ከዚያ በፊት ራሱ የአማራ “ብሔረተኛነት” የብሔረተኛነት ፍቺ፣ ትርጉምና መመዘኛዎች ያሟላል ወይ መባሉ ሊያስፈልግ ነው። ለምን ቢባል? የአማራ ማንነት ትግልና ተጋድሎ ከራስ መንግሥት ወይም የራስ ትድድር መመሥረት ጋር የተቆራኘ ስሜት፣ እንቅስቃሴና ኢድዮሎጂ ባለቤት አለመሆኑን በእሳቤ ከወሰድን። አንዱና ዋነኛው የብሔርተኝነት መገለጫ የአንድ ማኀበረ ፖለቲካዊ ስብስብ በአንድ የራሱ መንግሥት ሥር ወይም የራሱ ራስ-ገዝ አሃድ ወይም ፌደራላዊ አሃድ መጠቃለል ከስሜት አልፎ ወደ ፖለቲካዊ አይድዮሎጂ የተቀየረ ፍላጎትና ምኞት መላበሱ ሂደት ነው። በኦሮሞ ብሔረተኞች ዘንድ የተመለከትነው “ኦሮሙማ” ዓይነቱ ርዮተ ዓለም መሰል አማራነት የሚሰኝ አይድዮሎጂ መመልከት እስካሁን አልቻልንም። ከኢትዮጵያዊነት በስተቀር የምትል ሓረግ መጨመር ሊያስፈልግ ነው።
አሁን ባለበት ሰዓት አማራ አለ ወይስ የለም ሙግት አብቅቶ፣ አማራ ይደራጅ ወይስ አይደራጅም ሙግትም እልባት አግኝቶ፣ ብዙዎቹ አማሮች የመደራጀቱን አስፈላጊነት ከተዋሃዷቸው በኋላም ቢሆን የአማራን ስሜት፣ እንቃስቃሴ እንደ ብሔረተኛ እንቅስቅሴ ራሱን የሚመለከትበት መነጸር ከሌላው ይለያል። የሞረሹ አቶ ተክለ የሻው አንድ የአሮሞ ነጻነት ግንበር ተወካይ Welcome to the club ባለው ጊዜ እኛ የተደራጀነው እናንተ ለተራጃችሁበት ዓላማ አይደለም ብዬ መለስኩለት ነበር ያለው ። ሁሉም አማራ በማንነት ወገንተኛነቱ የተደራጀው የደረሰበትን ጥቃት ለመመከት ነው የምትለዋን ልዩነት ሊያሰምርበትና አጽንኦት ለመስጠት ይሻል።
የአማራ ማንነትና ለማንነቱ ያቀጣጠለው ተጋድሎ ጥንካሬው እሱ ነው። ተግዳሮቱም እሱ ነው። ከአንድነት ኃይሎች ጋር የፈጠረው አለመግባባት ምንጩ ይኸው አስቸጋሪ ትስስር ነው ቢባል ምንም ማጋነን የለበትም። አብዛኛው የአማራ ኤሊት በኢትዮጵያዊነቱ እስከ ተደራጀ ድረስ እኔ አማራ በማንነቱ ቢደራጅ ግድ የለኝም ማለቱ ለእነዚህ በአማራ ድርጅት ለታቀፉ ወጣት አደራጆች ተግባር ቀላል አይሆንም። አልሆነምም።
ብሔርተኝነት አንድ ስብስብ የራሴ ናቸው የሚላቸውን አባላት በአንድ መንግሥት አሃድ ወይም (ትድድር) ሥር ለማጠቃለል ያለው ምኞት ተግባራዊ የሚያደርግበት ስሜት፣ እንቅስቃሴና አይድዮሎጂ ነው ብለን ከተቀበለን ዘንዳ ከመንግሥት ማዕቀፍ ውጭ ሊታሰብ የሚችል ብሔርተኛነት እምብዛም አያጋጥምም።
የራስ ስብስብ ጠቅልል መንግሥት እንደ መዳረሻ ግብ ያላደረገ እንቃስቃሴን እንደ አንድ ብሔረተኛ እንቅስቃሴ መመልከቱ ያስኬድ እንደ ሆነ ራሱን የቻለ የቲዮሪ ጉዳይ ነው። አንድ ጉዳይ ግን ግልጽ ነው። በአማራው ወገንተኛነት ላይ የተመሰረተ ስሜትና እንቅስቃሴ ብንመለከትም ቅሉ የራሱን መንግሥት የማቋቋም ትልምና ዓላማ አንግቦ የተነሳ የአማራ ኃይል በቦታው የለም። የአማራ ብሔረተኛ እንቅስቃሴ የራሱን መንግሥት የመመሥረት ዓላማ የለውም። አንዳንዶች የአማራ የራሱን መንግሥት ምስረታ እንደ አንድ አማራጭ ዕቅድ “Plan B” አድርገው ይዘዋል የሚሉ ወገኖች መኖራቸው እንደተጠበቀ ሆኖ። አማራ ከኢትዮጵያዊ ማንነትና ብሔረተኛነት ጋር ያለው ቁርኝት አሁንም በቦታው እንዳለ ነው። ይህ ነው የአማራ ትግልንም ሆነ ብሔረተኛነት ከቀሪዎቹ ኢትዮጵያውያን ጋር ያለውን የትግል አጋርነት ውስብሰብ ያደረገው። ወደ ቲዮሪ ብዙ ሳንዘፈቅ በመሬት ላይ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ በግምት ብንወስድ እንኳን። እርግጥ ወልቃይት ጠገዴ የአማራ ማንነት ጥያቄ የማንነት እውቂያ ጥያቄ ቢሆንም ቅሉ ያንድ በሌላ ክልል የተከለለ መሬቴ ወደ ራሴ ክልል እንደ ገና ተመልሶ ይካለልልኝ ባሕርዩና ገጽታው ነው ጎልቶ የሚታየው። ድንበራችን ተከዜ ነው የምትለው መፈክርም ድንበር አካላይ ይዘት አላት። ስለዚህ የእኛ መሬት ቁራጭ አካል የነበረው መሬት ይመለሰልን ነው ጥያቄው። ፈረንጆች irredentist የሚሉት መሬት አስመላሽ እንቅስቃሴ ነው። One who advocates the recovery of territory culturally or historically related to one’s nation but now subject to a foreign state ይላል irredentis ፍቺው። እሱም ቢሆን ለሰፊ የፖለቲካ ዓላማ መቀስቀሻ መሣሪያነቱ ነው የሚጎላው። ማንኛውም ሃገሪቷን ያላማከለ የአስተዳደር አወቀቃቀር የመጠርጠር ዝንባሌው ከቀድሞ ዩግስላቪያ ከሰርብ ብሔረተኛነት ጋርም ያመሳስሏል። ልክ ሰርቦች እንደሞከሩት ግዛታዊ አይደፈርነትና ሙሉነት (territorial integrity) አማራው በወልቃይት-ጠገዴ ወደ አማራ ክልል ተመልሶ እንደገና ይካለልልኝ የሚል ጥያቄ መልክ ተላብሷል።
ከላይ እንደተመለከትነው በአሮሞ ብሔረተኞች “Welcome to the Club” እንኳን ደህና መጡ! አቀባባልም ሆነ ስለ አማራ ብሔረተኛነት ዲሞክራሲያዊነት የተቸራቸውም ውዳሴም ሆነ የምስክር ወረቀት በጸጋ የተቀበሉ አይመስሉም። አንዱ የአማራ ብሔረተኛ ድርጅት እንዲያውም “አማራ የሚደራጀው እንደ ኦነግና ወያኔ ዘረኛ ለመሆን አይደለም። አማራ የሚደራጀው የተጋረጠበትን አደጋ ተቋቁሞ በሰፊው ያባቶቹ አገር የአገሩ ባለቤት ሆኖ ለመኖር የሚያስችለውን አቅም ለመፍጠር ነው። አማራ የሚደራጀው ለዚህ ቅዱስ ተግባር ነው!” ይላል። ይህ ዓይነቱ የራስን አደረጃጀት ልዩ መሆን ለይቶ ማመስገን ሥር የሰደደውን አለመተማመን የበለጠ ያጎላ እንደሆነ ነው እንጂ እምነትንና የትግል አጋርነትን አያጸናም መቼም። ብሔረተኛነትን ላይ “ቅድስና” መደረቡ ደግሞ ተጨማሪ ጥያቄን ይጭራል። “ቅዱስ” ብሔረተኛነት ካለ የግድ ተቃራኒው ሊኖር ነው መባሉ አይቀሬ ነው። ”ያልተቀደሰ ብሔረተኛነት” ማለቴ ነው። የአማራ ብሔረተኛነት መደረሻው ግቡ ኢትዮጵያዊነት ነው ይሉናል። ሌላው ብሔረሰብ ብሔረተኛነትስ መዳረሻ ግቡ ምን ሊባል ነው? የአማራ ብሔረተኛነት ዲሞራሲያዊ እየሆነ ነው እየተባለም ነው። እሱም በራሱ አጠያያቂ ነው። ልክ “ቅዱስ” ብሔረተኛነት ብርቅ እንደሆነ “ዲሞክራሲያዊ” ብሔረተኛነት እምብዛም አያጋጥምም። አልፎ ተርፎ ብሔረተኛነት ራሱ ዲሞራሲያዊ ሊሆን ይችላልን? መባሉንም ያስከትላል። “አማራነት ማንነታችን ኢትዮጵያዊነት ዜግነታችን ነው” የሚለው መፈክር ለሁሉም 80 በላይ ለሆኑት የሃገሪቷ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እኩል የሚመለከት መፈክር መሆን አለበት ወይም ይገባዋል። አማራ ብቻ አይደለም በነገድ ማንነቱ ወገንተኛ የሚሆነው። መቼም ሁሉም በዜግነቱ “ኢትዮጵያዊ” ነኝ ባይ ነው። ምክንያቱ ዜግነት ግለሰብ ዜጋው ከሃገረ መንግሥቱ (State) ጋር ያለው ቁርኝት ነው እስከተባለ ድረስ።
የአማራነትና ኢትዮጵያዊነት ቁርኝት የአማራ “ብሔረተኛነትን” ወሰብሰብ አድርጎታል። አሁንም ከኢትዮጵያዊነት ጋር ያለው ቁርኝት የማይቆራረጠው ኢትዮጵያዊነት ዋልታና ማገር፣ ማግና ድር፣ ደምና ስጋ ስለሆነ ነው። እንደማይነጣጠሉ ለመግለጽ። “…. አማራና ኢትዮጵያዊነትን እለያያለሁ ማለት በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት ዓይነት አብ፣ ወልድ መንፈስ ቅዱስን እንለይ እንደ ማለት ነው“ ይላሉ አቶ ተክሌ የሻው። ዶር ተክሉ አባተ ደግሞ ሁለቱን መለያየት መመኮሩ ” ጸጉር ለመሰንጠቅ” መሞከር ያህል ነው ብለው ያምናሉ። የአማራ ማንነት ትግል ተግዳሮት የደቀነው ይህ ኢትዮጵያዊነቱና ማንነቱን መለያየት አለመቻሉ ነው። ጉዳዩ እንደ የኢትጵያዊነት ባለ አደራና የበላይ ጥበቃ ብቻ ሳይሆን ከሌላው ኢትዮጵያዊ ይበልጥ ኢትዮጵያዊ ነኝ ብሎ መመጻደቅ ተደርጎ በሌሎች ኢትዮጵያውያን መታየቱ ነው። ይህ ደግሞ በሌላው ኢትዮጵያዊ አማሮችን ኢትዮጵያዊነትን የራሳችሁ ብቻ አደረጋችሁት ተብሎ የሚሰማው ቅሬታ አለመተማመኑና በጥርጣሬ ዓይን የመተያየቱ ምንጭ ነው። ይህ ደግሞ አማራ በነገዱ ከተደራጀ በኋላም የሚከተለው መከራ ነው። እርግማን መባሉ ያስኬድ ይሆን? እነዚህ አባባሎች አማራ ኢትዮጵያዊነትን ከሌላው ጋር “ለመጋራት” ፈቃዳኝነት እንደሌለው ያስመስልበታል። ምንም እንኳን አማራ የሚደራጀው በራሱ ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለመመከት ነው መባሉ ትክክል ብቻ ሳይሆን ሁሉም ዛሬ የሚቀበለው ጉዳይ ቢሆንም ቅሉ ከሌሎች ብሔረሰብ ልሂቃን ጋር የነበረው አለመጣጣም አሁንም እንዳለ ነው። አማራ በኢትዮጵያዊነት ሽፋን ለተቀዳጀው የበላይነት ማስከበርያና ማዝለቂያ ነው እያሉ በውስጠ ታዋቂነት ጣታቸውን የሚቀስሩት ወደ አማራው ብሔረሰብ ነበር። አሁንም ይህንን አካሄድ ይህንኑ አለመተማመን ያጠናክር እንደሆነ ነው እንጂ አያለዝበውም። ዞሮ ዞሮ ከመጀመሪያው ክስና ጣት መቀሳሰር ጋር ይገናኝና ወደ መነሻ ነጥቡ ጋር ይመለሳል። የዚህ ሁሉ ጥቃት ዒላማ ያስደረገኝ ያው ከኢትዮጵያዊነት ጋር ያለኝ ቁርኝት ነው ከተባለው ጋር ግጥም ይላል። ለሌላው ይህ ኢትዮጵያዊነትን የእኔ የብቻዬ ንብረት ነው፣ የበላይ አደራ ጠባቂውም እኔው ነኝ ዓይነት መመጻደቅ ተደርጎ ይታያል።
ትልቁ የአማራ ብሔረተኛነት ተግዳሮት ከኢትዮጵያዊ ብሔረተኛነትና ማንነት ጋር የነበረውና ያለው እትብትና ትስስር መበጠስ ወይም አለመበጠስ ሁለት ልብነት ነው ቢባል ምንም ማጋነን የለበትም። አጠቃላይ ጥንካሬው እንደ የተጠበቀ ሆኖ ለውድቀት ሊዳርግ የሚችል ተጋላጭ ስስ ብልትና የአቺለስ ተረከዝ (Achilles’ heel) መሆኑ ነው። ጥንካሬውም እሱ ነው፣ ስስ ብልቱም እሱ ነው ማለት የሚቻል የመስለኛል። የሁለቱ ዲያሌክቲካዊ (ተቃርኗዊ ዝምድና?) ትስስር የዳይሌማው ወይም የመንታ ልብነት ምንጭ ነው። አማራው ከኢትዮጵያዊነት ጋር ያለው ያልተበጠሰ ቁርኝትና ትስስር ጋር መቆራረጡ ወይም መፋታቱ (disengage) አይታሰብም፡፡ ዛሬ ሁሉን እያተረማመሰ የሚገኘው የማንነት ፖለቲካ የአማራ ተወላጆችን ይበልጡኑ ድብልቅልቃቸውን ያወጣል፣ የማንነታቸውን ትግልም ይበልጡኑ ያወሳስበዋል። አወሳስቦት፣ እያናቆረን ነው። የአማራ ኤሊቶችን ብቻ ሳይሆን ውሎ-ገብ ዜጎችንም ጭምር በተመሰቃቀለው የማንነት ፖለቲካ ይበልጥ እያተተረማመሱ ናቸው።
ከ1983 ወዲህ ከላይ እንደተመለከትነው አማራ ልክ እንደ ሌላው በነገዱ እንዲደራጅ የተፈለገበት ምክንያት ነበር። ከኢሕአፓ የተገነጠለው የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ኢሕዲን) ወደ ብሔረ አማራ ዲሞራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) እንዲለወጠ የተደረገበት ምክንያት አንድ ነው። ማንንም እሰከ ምርጫ 97 ድረስ በማንነት ወገንተኛነት ካልሆነ በስተቀር በሃገራዊ ማንነቱ ወይም በሕብረ ብሔራዊነትና በኢትዮጵያዊነት ዙሪያ እንዳይደራጅ የተፈለገበትም ምክንያትም ያው ነው። በግለሰብ ካርድ መታወቂያ ላይም የጎሳ (የዘር?) ማንነት እንዲመዘገብ የተፈለገበት የፖሊሲ መመሪያም ያው ነው። ሁሉም በዘሩ ወይም በነገዱ እንጂ አደረጃጀቱ የሕብረብሔር ቅርጽም ሆነ ይዘት እንዲኖረው አልተፈለገም። ባጭሩ መመሪያው በሥልጣን ያለው ፖለቲካዊ ኃይል ንድፍና እቅድ ሆኖ በመተግበር ላይ ስለሆነም ነው።
ይህ ሁሉ ድብልቅልቅ የወያኔ ተንኮልና ሴራ ውጤት ብቻ ነው ማለት የሚያስኬድ አይመስለኝም። በአማራ ማንነት ትግልና ብሔረተኛነት ተግዳሮት የደቀነው ይህ ኢትዮጵያዊነቱና ማንነቱን የመለየቱ ችግር ብቻም አይደለም። ይህ በተራው ካንድነት ኃይሎች ጋርም በተቃራኒነት እንዲቆም አድርጎታል። ይህ ዛሬ በግልጽ እየወጣ ነው። ከኢትዮጵያዊነት ጋር ባይቆራረጥም ቅሉ ካንድነት ሃይሉ ጋር እየተራራቀ መጥቷል። ይህን በተራው በርካታ ያለመተማመኑን ንብብሮሽን እያገዘፈ ይገኛል። ይህ ሁሉ ተደምሮ እያራራቃቸው እንደሆነ ነው እንጂ የተቀራረቡና የትግል አንድነታቸው እየጸና አይደለም። ድሮ ያንድነት ኃይል የአማራ ማንነት ማሽሞንሞኛ አባባል ነው ወይ ብዬ እኔ ራሴ የጠየቅኩበትን ጊዜ አስታውሳለሁ። ዛሬ በመሬት ላይ የምንመለከተውን እውነታ እንደ ገና እንድፈትሽ እያስገደደኝ ነው። “አማራውን ከሌሎች ብሄር ብሄረሰቦች ልሂቃን እና ከሌሎች ድርጅቶች ጋር ማጋጨት የታክቲክም የስትራቴጂም ጥቅም የለውም” (ፈቃደ ሸዋቀና) ቢባልም አማራ በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከእነዚህ ጋር እየተጋጨ ነው።
በምርጫውና ፊያስኮው ሳቢያና በማግሥቱ በቅንጅት ድርጅቶችና መሪዎቻቸው መካከል የተከሰቱ አይነቱ አለመግባባቶቹና የክስ ጣት መቀሳሰሩ እንደ ገና አገርሽቶበታል። ፍርስራሻቸው የወጣ የቀድሞ ትብብሮችና ሕብረት ተሞክሮዎች ትምህርት የተቀሰመባቸው አይመስልም።
ለጥርጣሬው ምክንያቶችን መፈተሽ ተገቢ ነው። ሞረሽ ወገኔ የአማራ አርበኞች ግንቦት ሰባት ድርጅትን በማሰመልከት “የድርጅቱን እንቅስቃሴ ከጅምሩ እስካሁን ድረስ በሚገባ ተከታትለናል። በቅርቡ በአንድ የአማራ ድርጅት የወጣውና በክትትላችን ያገኘነው ውጤት አርበኞች ግንቦት ሰባት በራሱ ማንነት ላይ ያልቆመ፣ ማንነቱን ከሌሎች ጋር በሚፈጥረው ጥምረት፣ ውሕደት፣ ቅንጅት ወዘተ ለማሳደግ የሚጥር፣ ተፈጠረ የሚባለው ጥምረት የት እንደ ደረሰ ሳይታወቅና የመጀመሪያው ጥምረት ፊርማ ሳይደርቅ፣ ሌሎች ጥምረቶች የሚፈሉበት መሆኑን ታዝበናል። ከሁሉም በላይ የሚገርመው ጥምረት የሚመሠረተው አማራውን በዐውራ ጠላትነት ከፈረጁ ብሔርተኛ ድርጅቶች ጋር መሆኑ እርሱም በተዘዋዋሪ መንገድ የአማራው ጠላት መሆኑን እያሳየ መጥቷል” ይላል። ከዚህ አንጻር ጉዳዩ እየከረረ መጥቶ ወደ መፈራረጁ ደረጃ ተደርሷል ማለት ነው። ቀላል ክስ አይደለም።
ባንጻሩ በአርበኞች ግንቦት 7 አመራር እናንተ የአንድነት ኃይሎች የእኛዎች ናቸሁ (የት ትሄዱብናላችሁ) ብለን በቅድሚያ ካንድነት ጎራ ያፈነገጡትን ወደ አንድነት በረት እንመልስ ብለን ነው ከእነሱ መደራደሩን ያስቀደምነው መባሉ እንደ ሽንገላ ቢወሰድ አይገርምም። በተግባር የታየውም ይህው ነው። የት ትሄዱብናላችሁ የተባሉት የአንድነት ኃይሎች በእጅ የሉም ዛሬ። አሁን እነሱን ፍለጋ ሊኬድ ነው። “የእንትና ብሄር አልተወከለም አትበሉን ይህ ፓርላማ አይደለም” መባሉም እንዲሁ አለመተማመኑን ያጸና እንደሆነ እንጂ አያቀራርብም። የአማራ ብሔረተኞች ከአርበኞች ግንቦት 7 ጋር ያላቸው ቅራኔ ይህ ብቻ አይደለም። የወልቃይት-ጠገዴ ማንነት እውቂያ ጉዳይ፣ በሰሜን (ጎንደርና ጎጃም) የተቀጣጠለው የመሣሪያ ተጋድሎ ባለቤትነትና በስሙ አለመጥራት በግንባር ቀደም የሚጠቀሱ ናቸው። ጣት መቀሳሰሩን አቁመን፣ የኋላ ታሪኮችም በቅጡ ፈትሸን ለዚህ ችግር መፍትሔ በአስቸኳይ መፈለግ አለበት።
3 ማጠቃለያ
ከላይ የተመለለከትናቸው ተግዳሮቶቹ ከኢትዮጵያዊነት ጋር ተያያዥነት ያላቸው ናቸው። በአማራ ብሔረተኛነት ላይ ሌሎች ተጨማሪ ግን ቀላል የማይባሉ ተግዳሮቶች ተጋርጦበታል። የወያኔ የቆየ ሤራ፣ ቂምና እቅድ ማለቴ ብቻም አይደለም። የአማራ ብሔረተኛ እንቅስቃሴ በክልሉ በውስጡ ባቀፋቸው እንደ አማራ የሚቆጥራቸው አገው፣ ቅማናት፣ ወይጦ፣ አርጎባ ፣ሺንሻ ያላቸው ተሳትፎ፣ በድርጅቶች መሃል ያለው ሽኩቻ፣ የአመራሮቹ ልምድ ማነስ፣ ወዘተ እንደ ተግዳሮት በግምት አልተወሰዱም። በጸረ አማራነት ከመደቧቸው ድርጅቶች ጋር ያላቸው ትስስር ይወዛገባሉ። ባንድነት ኃይሉ መሃል ያለ አለ መተማመን፣ የብሔረሰቦቹ ኤሊቶች ብቻ ሳይሆን በአንድነት ኃይሎች መካከል መካሰስ፣ መሸነጋገል ዛሬም እንዳለ ነው።
የሁሉት ታላላቅ ነገዶች (አማራ ብሔረተኞች ኦሮምኛ የተሰኘውን ጎሳ ቃል ላለመጠቀም የሚወስዱትን ቃል እንጠቅምና) ማቀራረብ የሚችል መግባባት ፈጣሪ ድርጀት ወይም መሪ ማስፈለጉ የማይታበል ሃቅ ነው። ምክንያቱም ዶር መረራ ጉዲና ብዙ ጊዜ የሚያነሷቸው የሦስቱ ብሔረሰቦች ኤሊቶች ወደ መሃል የማገናኘቱ ከባድ ኃላፊነትና አደራ እስካሁን ሊወጣ የቻለ ግለሰብም ሆነ ፖለቲካዊ ኃይል አይታይም። ደጉ ዜና ወያኔና አንዳንድ የኦሮሞ ድርጅቶች ወደ ኢትዮጵያዊነት የማምራት አዠማሚያ እያሳዩ ነው። ባንጻሩ የአማራ ወጣቶች በብዛት ወደ ነገድ አደረጃጀት እየነጎዱ ነው። ምናልባት በመሃል በመንገድ ከተገናኙ መልካም ነው። የተራራቁ ጫፎችን መሃል ላይ እንዲገናኙ ማድረግ ካልተቻለ ግን ተደጋግሞ የሚወሳው የወያኔ ኢሕዴአግ የሥልጣን ዕድሜ ማራዘሙ አይቀሬ ነው የሃገሪቷ እጣ ፋንታ ጉዳይ ይበልጥ ሊያሳስብ ነው ማለት ነው።
ወያኔ ኢሕዴአግ አደርጋለሁ የሚለው “ጥልቅ ተሃድሶ” ፣ የሕገ መንግሥት ማሻሻል፣ ከተቃዋሚዎች ጋር መነጋገር ፣ የሃይማኖት ድርጅቶች የእርቅ ሰላም የማውረዱ ሚና ወዘተ ሁሉ በመሃል የማገናኘቱ በጎ እርምጃዎች ተደርገው ሊታዩ ይገባል።
የ “ቆም ብለን እናስብ!” እና “ሰከን በል” ጥሪዎች ከሁሉም አቅጣጫ ቢዥጎደጎዱም በመጯጯህ ጫጫታ እየተዋጡ ናቸው። ቆም ብሎ ማሰብ አልተቻለም። ሁላችን ቆም ብለን እናስብ! በመጨረሻ ሁሉ ሰክኖ የትግል ስልቶቹና ሥሌቶቹን መርምሮ እኩልነትን ተቀብሎ፣ በመሃል ተገናኝተው፣ መሸነጋገል፣ጥርጣሬና ፍራቻ አስወግደው ባንዲት አገር በኢትዮጵያዊነት አስተሳሳሪ አቃፊ-ደጋፊ ሃገራዊ ሽርክና ለመጀመር ያለንን ቁርጠኝነት አንዱ ማሳያው ቆም ብሎ መነጋገርና መግባባት ነው፡፡
በበርካታ እርስ በርስ ጦርነቶች በበጣጠቋቸው ሃገራት እንደሚንመለከተው ማንም በማንም ላይ በጦር ሜዳ በላይነትም ሆነ የማያዳግም ድል ቢቀናው እንኳን የማታ የማታ ማሳረጊያው በክብ ጠረጴዛ ዙሪያ ላይ የተደረሰ ተኩስ አቁምና የሰላም ስምምነት ነው። በዚያ ላይ አንዱ ወገን በተፋላሚው ላይ የተወሰነ ነጥቦች በደም ካስመዘገበ በኋላ መሆኑንም አሁንም አልሳትኩም። እርግጥ ይህ ሁኔታ በኃይል ሚዛን መለወጡ ነው አንዱ ተፋላሚ በፊት አሻፈረኝ የሚለውን እውነታ በመቀበል የአቋም መንፏቀቅ አስፈላጊነትና አስገዳጅነት የሚመነጨውም ከእዚህ ነው። ይህንንም አልሳትኩም።
አማራን ከጥቃት ለመከላከል ብቻ ሳይሆን “አማራው የራሱን ሕልውና አስከብሮ ከዚያም የኢትዮጵያዊነቱን ግዴታ ከሌሎች ጎሣዎች ጋር በእኩልነት እንዲወጣ ማድረግ የመላው አማራ ህዝብ ድርጅት ተልዕኮ ነው” ነበር ፕሮፌሰር አሥራት በባህርዳሩ መአሕድ መስራች ጉባኤ ላይ ያሉት። ደግማዊ መአሕድም ሆነ ሌሎች የአማራ ድርጅቶች ከዚህ የተለየ ተልዕኮ ይኖራቸዋል ብዬ አልገምትም። የሰሞኑ ተከታታይ የአማራ አቀፍና ሃገር አቀፍ ኃይሎች፣ የኢትዮጵያ አንድነት ኃይሎች ምክክር ጉባኤ ዓይነቶቹ ምናልባት ለዚህ መተማመን እርሾ መፍጠር ቀዳሚ ሥራ ሊይዝ ይገባል። “ካልደፈረሰ፣ አይጠራም” በሚለው ብሂል ድፍርስርሱን ባወጣ ማግሥት ለመልካም እድል አጋጣሚ ሊፈጠር ነው ከተባለም ሁሉ ሰከን ብሎ በምር መነጋገር ይጀመር! የሰሞኖቹ የዋሽንግተን ጉባኤዎችና ስብስባዎች መልካም አጋጣሚዎች ናቸው። ሌሎች መወያያ መድረኮችም ውይይቶችን ያስተናግዱ። ሰሞኑን ኢሳት በእንወያይ ፕሮግራሙ በአማራ ወጣቶች መካከል እንዳስተናገደው ማለቴ ነው ፡፡የሺ ማይል ጉዞ ባንድ እርምጃ ነው የሚጀመረው የሚሉት ቻይናውያን ናቸውን? እኛም ረዥሙን መንገድ በቀላሉ እርምጃዎች እንያያዘው!!