በኢትዮጵያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታወጀ፤ ህዝባዊ ተቃውሞውም አድማሱን እያሰፋ ቀጥሏል
(አዲስ ሚዲያ)በኢትዮጵያ ለተከታታይ አስር ወራት የፈጀው የፀረ አገዛዝ ህዝባዊ ተቃውሞ ተጠናክሮ መቀጠሉን ተከትሎ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ከትናንት ቅዳሜ መስከረም 28 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ ለ6 ወር ተግባራዊ የሆነ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማውጣቱን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ መስከረም 29 ቀን 2009 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ዝርዝር ጉዳይን በተመለከተ ወደፊት ይገለፃል ከማለት በስተቀር አጠቃላይ ይዘቱን በተመለከተ ያሉት ነገር የለም፡፡
በሌላ በኩል በጠቅላይ ሚኒስተሩ በሚመራ ኮማንድ ፖስት ስር የህግ አስከባሪዎችም መከላከያ ሰራዊት፣ ፌደራል ፖሊስ፣ የፌደራል የፀረ ሽብር ግብረ ኃይል፣ የአካባ ሚሊሻዎች እና ንብረት ጠባቂ የፀጥታ ኃይሎች የሚያካትት መሆኑን ደግሞ ጠቅላይ አቃቤ ህጉ አቶ ጌታቸው አምባዬ አብራርተዋል፡፡ አስቸኳይ አዋጁ በአጠቃላይ ሀገሪቱ ላይ ተግባራዊ መደረጉንም ጠቅላይ አቃቤ ህጉ አስታውቀዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ
በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አተገባበር መሰረት የተጠረጠረ ማንኛቸውም ሰው ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሊታሰር እንደሚችል፣ ቤቶችና አካባቢዎችም ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ብርበራ ሊካሄድባቸው እንደሚችልም እና ማንኛውም ዓይነት መገናኛ ብዙኃን ሊዘጋ እንደሚችልም ጠቅላይ አቃቤ ህጉ ይፋ አድርገዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ተቃውሞን ሊገልፁ የሚችሉ ምልክቶችን መጠቀምንም አዋጁ እንደሚከለክል፣ አዋጁን ተላልፎ የተገኘም ቅጣት እንደሚጠብቀው አስታውቀዋል፡፡
በተለይ ከህዳር 22 ቀን 2008 ዓ.ም. በኦሮሚያ እንዲሁም ከሐምሌ 5 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ በአማራ ክልል የተነሱ የፀረ አገዛዝ ህዝባዊ ተቃውሞች መንግሥት በወታደራዊ ኃይል ግድና፣ እስርና አፈና ለማስቆም መሞከሩን ተከትሎ ያለማቋረጥ ተቃውሞዎቹ ተጠናክረው መቀጠላቸው ስርዓቱን ስጋት ላይ ጥሎታል፡፡ በተለይ እንደ ማዕከላዊ ስታስቲክስ ኤጀንሲ መረጃ ከሆነ ከሀገሪቱን አጠቃላይ ህዝብና የቆዳ ስፋት 62% የሚሸፍነው የሀገሪቱ ህዝብ በአደባባይ የስርዓት ለውጥ እንደሚፈልግና በስልጣን ላይ ባለው ስርዓት መገዛት ለከፍተኛ ግድያ፣ እስር፣ በደልና ጭቆና እንደዳረገው በአደባባይ እየገለፀ ይገኛል፡፡ ለህዝቡ ጥያቄ የመንግሥት ምላሽ ግድያ፣ እስርና ማሰቃየት መሆኑ ደግሞ ህዝቡን የበለጠ እንዲቆጣና የተቃውሞ አድማሱን እንዲያሰፋ እንዳስገደደው ይነገራል፡፡
በተለይ ባለፈው እሁድ መስከረም 22 ቀን 2008 ዓ.ም. በኦሮሞ ማኀበረሰብ ዘንድ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠውና በርካታ ኢትዮጵያውያን የሚታደሙበት የኢሬቻ በዓል በደብረዘይት/ቢሾፍቱ ሆራ አርሰዲ ሐይቅ እየተከበረ ባለበት ወቅት ህዝቡ በሰላማዊ መንገድ አገዛዙ ላይ ተቃውሞውን ማሰማቱን ተከትሎ በተወሰደው ርምጃ አጠቃላይ ከ678 በላይ ሰላማዊ ዜጎች መገደላቸው በመላው ኢትዮጵያ የበለጠ ቅሬታን ፈጥሯል፡፡ በዚህም በኦሮሚያ ክልል የነበረው ህዝባዊ ተቃውሞ ወደ ህዝባዊ አብዮት መሸጋገሩንም የኦሮሞ መብት አራማጆች ይፋ ማድረጋቸውን ተከትሎ፤ ህዝቡ የአገዛዙ ሰዎች፣ ደጋፊዎችና ተባባሪዎች ናቸው የተባሉ ንበረቶች እና አገዛዙ የሚጠቀምባቸው የተለያዩ መንግሥታዊ ተቋማት ላይ ርምጃ መውሰዳቸው ታውቋል፡፡ የኦሮሞ ህዝባዊ ተቃውሞ አሁንም ተጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን፤ የመንግሥት ወታደራዊ የኃይል ርምጃም ተጠናክሮ በመቀጠል የበርካታ ሰላማዊ ዜጎች ህይወት ጠፍቷል፡፡
በተመሳሳይ በአማራ ክልል ባለው ህዝባዊ ተጋድሎ የቀጠለ ሲሆን፤ የመንግሥት ወታደራዊ እርምጃ በርካታ ሰላማዊ ዜጎችን ህይወት ቀጥፏል፡፡ በኦሮሚያ እና አማራ ክልል በተጨማሪ በደቡብ ክልል ኮንሶ ወረዳም ተመሳሳይ የፀረ አገዛዝ ህዝባዊ ተቃውሞ እና የመንግሥት የኃይል ርምጃ የቀጠለ ሲሆን፤ በዚህም በርካታ ሰላማዊ ዜጎች ተገድለዋል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ በዛው ደቡብ ክልል ጌዲዮ ዞን ባሉ ወረዳዎችና ከተሞች ከፍተኛ ተቃውሞና ግጭቶች ተቀስቅሰዋል፡፡ በዚህም የሰው ህይወት መጥፋትን ጨምሮ የበርካታ ሰላማዊ ዜጎች የንግድ ሱቆችና መኖሪያ ቤቶች ተቃጥለዋል፡፡ የተለያዩ የኃይማኖት ተቋማትም ላይ ጥቃት መሰንዘሩን ምንጮች አረጋግጠዋል፡፡
ከህዳር 2008 ዓ.ም. ጀምሮ አጠቃላይ በኦሮሚያ እና በአማራ ክልል እንዲሁም በደቡብ ክልል ኮንሶ ወረዳ ባሉ ህዝባዊ ተቃውሞዎች በመንግሥት ወታደራዊ የኃይል ርምጃ የተገደሉ ሰላማዊ ዜጎች ቁጥር ከ 1,420 በላይ መድረሳቸውን መረጃዎች አመልክተዋል፡፡ መንግሥት በበኩሉ ህዝባዊ ተቃውሞቹ በውጭ ኃይል የተቀነባበሩ ናቸው በማለት ለመሸፋፈን ቢሞክርም ከህዝቡ፣ ከመብት አራማጆችም ሆነ ከዓለም አቀፉ ማኀበረሰብ ተቀባይነት አላገኘም፡፡
የኮንሶ ብሔረሰብ የዞን ምሥረታ ጥያቄ ከሕግ አንጻር ሲፈተሸ

ውብሸት ሙላት
ኮንሶ፣ በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል በሰገን ሕዝቦች ዞን ውስጥ የምትገኝ ወረዳ ናት፡፡ ቀደም ሲል ግን ልዩ ወረዳ ነበረች፡፡ ኮንሶ አስተዳደር እርከን ብቻ ብቻ አይደለችም፤ብሔረሰብም ጭምር እንጂ! የሰገን ሕዝቦች ዞን ደግሞ በፊት የኮንሶ፣ የደራሼ፣ የአማሮ እና የቡርጂ ልዮ ወረዳዎች የነበሩትን በማጠቃለል የተመሠረተ ነው፡፡
በደቡብ ክልል ሕገ-መንግሥት መሠረት ልዩ ወረዳ ከዞን ጋር አቻ ሥልጣን አለው፡፡ ተጠሪነቱም ቀጥታ ለክልሉ ነው፡፡ ልዩ ወረዳ፣ ብዙ ጊዜ በአንድ ብሔር ብቻ ስለሚመሠረት የአንድ ብሔር ብቻ አባላት ያሉበት የወረዳ ምክር ቤት ይኖረዋል፡፡ የራሱ የልዩ ወረዳው የሥራ ቋንቋ እንዲኖረው መወሰን ይችላል፡፡ በዞን ደረጃ የሚኖሩትን መንግሥታዊ መዋቅሮችን በወረዳው በማቋቋም በርካታ የብሔረሰቡ ተወላጆች የሥራ ዕድል እንዲኖራቸው ያስችላል፡፡
መደበኛ ዞኖች ሕግ አውጪ የላቸውም፡፡ የዞን ሥራ አስፈጻሚዎችም የሚሾሙት በቀጥታ በክልሉ ሥራ አስፈጻሚ በመሆኑ የክልል ውክልና እንጂ በምርጫ የተገኘ ሥልጣን አይደለም፡፡ ወረዳዎችም ቢሆኑ ለአስተዳደር ቅልጥፍና፣ ድጋፍና ክትትል ሲባል በተጨማሪነት ለዞን ተጠሪነት ያለባቸው ቢሆንም ይህ ሁኔታ የመነጨው የክልሉ አስፈጻሚ አካላት በሚሰጠው ውክልና ላይ ተመሥርቶ እንጂ ሕገ-መንግሥታዊ መነሻ የለውም፡፡ ለዚያም ነው የወረዳ አስተዳዳሪዎችና ከንቲባዎች በዞን አስተዳዳሪዎች የማይሾሙትም ሆነ የማይወርዱት፡፡
በልዩ ዞኖች ግን የብሔረሰብ ምክር ቤት ስላላቸው፣ የዳኝነት መዋቅርና ሹመት በክልል ደረጃ ቢከናወንም እንኳን ከዞኑ የሚጠቆሙትና የሚሾሙት ዳኞች ላይ አስተያየት የመስጠት መብት አላቸው፡፡
የኮንሶ ብሔረሰብ፣ የዞንነት ጥያቄ በማንሳት ተቃውሞ ከጀመረ አንድ ዓመት አለፈው፡፡ ከተቃውሞው ጋር በተያያዘ ቀላል የማይባል የሰው ሕይወት ጠፍቷል፡፡ የክልሉ የኮሚኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ሓላፊ ለአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ በቅርቡ በተናገሩት መረጃ እንኳን ከ1500 ቤቶች በላይ ተቃጥለዋል፡፡ ከአንዳንድ መገናኛ ብዙኃን እንደሚሰማው የዞንነት ጥያቄው ካልተሳካ ወደ ኦሮሚያ ክልል የመካለል ጥያቄንም በአማራጭነት ሕዝቡ እያነሳ ነው፡፡
ይህ ጽሑፍ ዞን የሚመሠረትበትን ሕጋዊ አሠራር ይፈትሻል፡፡ የራስን ዕድል በራስ ከመወሰን መብት ጋር የሚኖረውን ግንኙት በማየት የኮንሶ ብሔረሰብ ጥያቄ ከክልሉ እና ከፌደራሉ ሕገ-መንግሥት እንዲሁም ከሌሎች አግባብነት ካላቸው ሕጎች አንጻር ዳሰሳ ያደርጋል፡፡ እግረ-መንገዱንም አንድ ወረዳ ወይንም ሌላ አስተዳደረዊ መዋቅር ከአንድ ክልል ወደ ሌላ ክልል መጠቃለል የሚችልበትን ሕገ መንግሥታዊ ሁኔታም ካለ ምጥን ፍተሻ ያደርጋል፡፡
ኮንሶ ከሌሎች ዞኖች ጋር በሕዝብ ብዛት ስትነጻጸር፤
የኮንሶን የዞን ምሥረታ ጥያቄን በአግባቡ ለመረዳት በኢትዮጵያ ውስጥ ካሉት ዞኖች ጋር፣ በ1999 ዓ.ም. የተደረገውን የሕዝብና ቤት ቆጠራን መሠረት በማድረግ እናነጻጽራለን፡፡ በዚህ የሕዝብና ቤት ቆጠራ ውጤት መሠረት የኮንሶ ልዩ ወረዳ ወደ 235 ሺህ የሚጠጋ ሕዝብ ነበረው፡፡ የዛሬ አስር ዓመት የነበረው የወረዳው ሕዝብ ብዛት ማለት ነው፡፡ ከወረዳው ውጭም የሚኖሩትን ጨምሮ፣ የኮንሶ ብሔረሰብ ብዛት ከ250 ሺህ በላይ ነው፡፡ ዞን ለመመሥረት በአንድ አካባቢ መኖርን ስለሚጠይቅ፣ ለዞን ምሥረታ ጥያቄው ተገቢው ቁጥር መኖር ቅድመ-ሁኔታ ነው ማለት ይቻላል፡፡
የኮንሶ ወረዳ ሕዝብ፣ ከሀረሪ ክልል ሕዝብ ይበልጣል፡፡ የዛሬ አስር ዓመት የክልሉ ሕዝብ ብዛት፣ ገና 200 ሺህ እንኳን አልሞላም ነበር፡፡ የኮንሶ ወረዳ በሕዝብ ብዛት፣ ከትግራይ ክልል የመቀሌ ልዩ ዞንን፣ ከአፋር ክልል የዞን ሦስት እና አምስትን፣ ከአማራ እና ከኦሮሚያ ክልሎች ከዞኖች ጋር አቻ ከሆኑት የባሕር ዳር፣ የደሴ፣ የጎንደር፣ የአዳማ እና የጅማ ከተሞችን፣ ከቤኒሻንጉል-ጉሙዝ፣ የካማሼ ዞንን፣ የጋምቤላ የሁሉንም ዞኖችን፣ እንዲሁም ከራሱ ከደቡብ ክልል ደግሞ የሸካ ዞንን በሕዝብ ብዛት ይበልጣል፡፡ የጋምቤላ ክልል ከኮንሶ ሕዝብ ወደ 80 ሺህ በሚጠጋ ቁጥር ብቻ ነው የሚበልጠው፡፡

ራስን በራስ የማስተዳደር መብት፤
የኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 89(1)፣ መንግሥት በዴሞክራሲያዊ መርሆች ላይ በመመሥረት ሕዝቡ በሁሉም ደረጃዎች ራሱን በራሱ የሚያስተዳደርበትን ሁኔታ ማመቻቸት ያለበትን ስለመሆኑ የፖለቲካዊ ፖሊሲው በጥቅሉ አስቀምጦታል ፡፡ ማንኛውም የብሔርነት፣ የብሔረሰብነት ወይንም ደግሞ የሕዝብነት ዕውቅና ያገኘ ማኅበረሰብ ራሱን በራሱ የማስተዳደር መብቱን ተግባራዊ የሚያደርግበትን አስተዳደራዊ መዋቅር የመመሥረት ገደብ የሌለው ሕገ-መንግሥታዊ መብት እንዳለው የፌደራሉም የክልሎችም ሕገ መንግሥት አንቀጽ 39 (3) ላይ ተደንግጓል፡፡
ራስን የማስተዳደር ሙሉ መብት በክልል ላይ ብቻ የተንጠለጠለ አይደለም፡፡ ይህ መብት ውጤታማ እንዲሆን ያልተማከለ አስተዳደር ተግባራዊ መሆን አለበት፡፡ ያልተማከለ አስተዳደርን እንደ አንድ ፕሮግራም ብናየው ብዙ የሚያካትታቸው ነጥቦች አሉት፡፡ ከሚያካትታቸው ነጥቦች ውስጥ በባሕርያቸው የአካባቢው መንግሥት ሥልጣንና ሥራ የሆኑትን ለአካባቢው መተው፣ እንዲሁም ባሕርያቸው አካባቢያዊ ባይሆኑም እንኳን እነሱ ቢፈጽሟቸው የሚሻል ከሆነም ለአካባቢው መንግሥት መተው አለባቸው፡፡
እንዲህ መሆኑ ከታመነበት ግጭትን ለመቀነስም ሆነ በልበ-ሙሉነት ለመሥራት ሲባል ሥልጣንና ተግባራቸው በግልጽ ተለይቶ መቀመጥን ይፈልጋል፡፡
የአካባቢ መንግሥታት (Local Government) የራሳቸውን ጉዳይ በራሳቸው የመጨረስ፣ ፖሊሲ የመንደፍ፣ ለፖሊሲያቸው የሕግ ማዕቀፍ የመስጠት የመጨረሻ የሥልጣን ባልተቤት መሆን ያሻቸዋል፡፡
አካባቢያዊ መንግሥታት፣ አስተዳደራዊ ተቋሞችን የማቋቋምና ለሥራ ምቹ በሚሆን መንገድ በነጻነት የማዋቀርና የሰው ሃይል የመቅጠርም የማባረርም ሥልጣንን ይይዛል፡፡ ስለሆነም አካባቢያዊ መንግሥታት ፖለቲካዊ፣ የገቢና ወጭ፣ እንዲሁም አስተዳደራዊ ሥልጣንን ያካትታል ማለት ነው፡፡ ይህ አሠራር የማእከላዊ መንግሥት ድጋፍና ቁጥጥር እንዲሁም በይነመንግሥታዊ ትብብርንም አያስቀርም፡፡
ፖለቲካዊ ራስ ገዝነት ባልተማከለ አስተዳደርም ይሁን ራስን በራስ በሚያስተዳድሩ ብሔሮች ዘንድ ቁልፍ የሆነ ጉዳይ ነው፡፡ ማእከላዊም ይሁን የክልል መንግሥታት ባሰኛቸው ጊዜ የሚያፈርሷቸው ሲመቻቸው ደግሞ የሚያቋቁሟቸው ልዩ ዞኖች፣ ወረዳዎች፣ ቀበሌዎች ሊኖሩ አይገባም፡፡ ቀጣይ መሆን አለባቸው፡፡ በመኖርና በመፍረስ በስጋት እየወላወሉ የሚኖሩ ተቋማት ሊሆኑ አይገባቸውም፡፡ ወይንም ደግሞ እንዴት እንደሚቋቋሙም ይሁን እንደሚፈርሱ ግልጽ ሕግ፣ሁሉም የተስማሙበት ኖሮ በዚያው መሠረት መፈጸም አለበት፡፡ የኮንሶ ነገርም፣ በአንድ ወቅት ልዩ ዞን የነበረች ሲሆን አሁን ግን መደበኛ ወረዳ ብቻ በመሆን በሰገን ሕዝቦች ሥር ትገኛለች፡፡
በሕገ-መንግሥቱ በአንቀጽ 50(4) ከተገለጸው አንጻር ቋሚነት አላቸው ማለት ቢቻልም በተግባር እንደታየው ግን፣ ከ1994 ዓ.ም. በፊት ይህ ዓይነት ሥልጣን የሌላቸው ሲሆን፣ በኋላ ደግሞ መለወጡ ብሎም በአንዳንድ ክልሎች ሥልጣናቸው በሕገ-መንግሥት ሳይሆን በአዋጅ መገለጹ ወይንም በግልጽ አለመቀመጡ አጠራጣሪ አስመስሎታል፡፡
በተጨማሪም እንዴት ወረዳዎች እንደሚመሠረቱና እንደሚታጠፉ፣ ድንበራቸው እንደሚካለልና እንደሚደካ አለመገለጹ፤ መሥፈርቶቹን አንዳንድ ክልሎች በአዋጅ (ለምሳሌ ደቡብና ኦሮሚያ) ሌሎቹ ደግሞ ለአስፈጻሚው አካል መተው (ለምሳሌ ቤኒሻንጉል ጉሙዝና አማራ) ጉራማይሌ አድርገውታል፡፡ በመሆኑም ለልዩ ዞኖችም ይሁን ወረዳዎች የተሻለ ዋስትና መስጠት ያስፈልጋል፡፡ የዚህ ዋስትና አለመኖር ነው ኮንሶን በአንድ ወቅት ልዩ ወረዳ፣ በሌላ ጊዜ መደበኛ ወረዳ በመሆን ምንአልባትም ለተለያዩ ተቃውሞዎች መነሻ የሆነው፡፡
የልዩ ዞንና ወረዳ ምሥረታ ሂደት፤
በሽግግሩ ዘመን ሥራ ላይ በነበረው አዋጅ ቁጥር 7/1984 መሠረት ወረዳን ጨምሮ ወደ ላይ ያሉ መስተዳድሮችን ማቋቋም የማይችሉት በግልጽ ተዘርዝረው ነበር፡፡ በሕገ-መንግሥቱ ይህ ገደብ ተነስቷል፡፡ በተጨማሪም ክልል መመሥረት እንደመገንጠል ሁሉ ገደብ የለውም፡፡ ለነገሩ ክልል መመሥረትም ጉዳዩ ከክልል መሆኑ ነው እንጂ ያው መገንጠል ነው፡፡ ገደብ አለመኖሩን ለማመልከት “በማናቸውም ጊዜ” የሚል ቃል ተጠቅሟል፡፡
በሕገ-መንግሥቱ እንዲህ ዓይነቱ “መድልኦ” ተወግዷል ብንልም እንኳን በጋምቤላ አኙዋ፣ ኑዌርና መዠንግር ልዩ ዞን ሊያቋቁሙ እንደሚችሉ ሲገለጽ ኡፖና ኮሞ አይችሉም በማለት የክልሉ ሕገ-መንግሥት ገልጿል፡፡ በዚህም ከብሔረሰቦች መርጦ ለዞንና ለወረዳ አለ ማለት ነው፡፡ ቁጥራቸው አናሳ (በ1999ኙ ዓ.ም. በተደረገው ቆጠራ በክልሉ ውስጥ የሚኖሩት ማኦ 64፣ ኡፖ ደግሞ 990) መሆናቸው አንድ ነገር ሆኖ በሕገ-መንግሥት መከልከል ደግሞ ሌላ ነገር ነው፡፡
የአሁኑ ደቡብ ክልል ከመመሥረቱ በፊት አራት ክልሎች ነበሩ፡፡ አንድ ክልል ከሆኑ በኋላ ዞኖችና ወረዳዎች በተለያዩ ጊዜያት እንደገና ተዋቅረዋል፡፡ ለምሳሌ ሰሜን ኦሞ (ወላይታ፣ ጋሞ-ጎፋ፣ዳውሮ) ወደ ሦስት ብሔረሰብ ዞኖች ተከፋፈለ (ወላይታ፣ ጋሞ-ጎፋ እና ዳውሮ ) ተብለው፡፡ እንዲሁም ሁለት ልዩ ወረዳዎች ተጨመሩ ባስኬቶና ኮንታ፡፡ ሌላ ካፋ-ሸካ የሚል እንደ አንድ ልዩ ዞን ቢቋቋሙም ውሎ አድሮ ካፋ እና ሸካ ልዮ ዞኖች ተብለው ራሳቸውን ቻሉ፡፡ ቤንችና ማጂ ይባሉ የነበሩት ሁለት ዞኖች፣ ኋላ ላይ ቤንች-ማጂ ተብለው አንድ ዞን ሆኑ፡፡ ስልጤ ዞንም ከጉራጌ ተነጥሎ ራሱን ቻለ፡፡ ቀደም ሲል ስምንት ልዩ ወረዳዎች የነበሩ ሲሆን አሁን አራቱ (ኮንሶ፣ደራሼ፣ ቡርጂ እና አማሮ) በአንድነት ሰገን ዞንን መሥርተዋል፡፡
ቋንቋ፣ማንነት፣ የአሰፋፈር ሁኔታና ፍቃደኝነት ላይ መሠረት በማድረግ የሚቋቋሙ አካባቢያዊ መስተዳድሮች (local territorial autonomy) ጉዳትም እንዳላቸው የሚገልጹ አሉ፡፡ ከእነዚህም ጉዳቶች መካከል ክፍፍልን ያባብሳል፣ ክልሎች በአብዝኃኛው ወጥ የሆነ አንድ ብሔር ስለማይኖርባቸው አሁንም ቢሆን በኢትዮጵያ የአናሳና የብዙኃንን ግንኙነት ማስቆም አያስችልም፤ በተጨማሪም አሁን ባለው ሁኔታ ዞኖችና ወረዳዎች ሲዋቀሩም ይሁን ሲዋሃዱ ወጥ የሆነ የታወቀ ሕገ-መንግሥታዊ መርሕ የለውም፤ እንደገዥው ፓርቲ የፖለቲካ ግምገማና ድምዳሜ የሚወሰን ነው፤ ዘፈቀዳዊም ነው የሚሉ ክሶች ይቀርባሉ፡፡
የዞንና ምሥረታ በደቡብ፤
ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ማንነታቸው ከታወቀ እንደቡድን ማንኛውንም አስተዳደራዊ እርከን የመመሥረት መብት አላቸው ብለናል፡፡ ከደቡብ ውጭ ያሉት ክልሎች፣ በውስጣቸው የሚገኙት ነባር ብሔረሰቦች ቁጥራቸው ዝቅተኛ ስለሆነ፣ ወይ መሥርተዋል፤ አሊያም ትተዋቸዋል፡፡ መመሥረት ቢፈልጉ ደግሞ እንዴት ጥያቄያቸውን እንደሚያቀርቡ፣ ለማን እንደሚያቀርቡ፣ ምን ምን ሁኔታዎችን ማሟልት እንዳለባቸው ወዘተ የሚያሳይ ሕግ የላቸውም፡፡ ደቡብ ግን አለው፡፡
የደቡብ ክልል የብሔረሰቦች ምክር ቤት ስላለው፣ የዞንም ይሁን የወረዳ አመሠራረት ጥያቄ እንዴት መስተናገድ እንዳለበት፣ ይህንን ምክር ቤት ለማጠናከርና ሥልጣንና ተግባሩን ለመወሰን በወጣው አዋጅ ላይ ተገልጿል፡፡ ሥነ-ሥርዓቱ ከክልል ምስረታ ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ ልዩነቱ ጥያቄውን ያቀረበው በአስተዳደራዊ መዋቅር ተደግፎ ከሆነ (ለምሳሌ ልዩ ወረዳ የነበረው ልዩ ዞን መሆን ቢፈልግና ጥያቄው የቀረበው የወረዳው መስተዳደር ቢሆን) የመስተዳድሩ ምክር ቤት በሁለት ሦስተኛ ድምፅ ከደገፈው ወይንም ጥያቄውን ያቀረበው፤ ሕዝቡ ከሆነ (5% የሚሆነው ስምና ፊርማ አስፍሮ) ሕዝቡ በአብላጫ ድምፅ ሲደግፈው እና የክልሉ የብሔረሰቦች ምክር ቤት ሲወስን ተፈጻሚ ይሆናል፡፡
በዚህ ሕግ መሠረት ሕዝቡ በአብላጫ ድምፅ ወስኖ እንኳን ምክር ቤቱ ተጨማሪ ማስረጃ የማሰባሰብ ሥልጣን ስላለው አሰባስቦ ከመረመረ በኋላ ነው ውሳኔውን የሚያሳውቀው፡፡ ውሳኔውን ያሳውቃል ማለት ሕዝቡ በአብላጫ ድምፅ የወሰነውንም ሊሽረው ይችላል ማለት ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ አሠራር ወለፈንድ ይመስላል፡፡ ድምፅ ሳይሰጡ ቢሆን እንኳን ይሻላል፤ ድምፅ ሰጥተው ከጨረሱ በኋላ የሌሎች ብሔረሰቦች ተወካዮች የሕዝብን ውሳኔ ካላከበሩ የት ላይ ነው ታዲያ የራስን ዕድል በራስ መወሰኑ? ይሔው ሕግ ይሔንኑ ጉዳይ በሚደነግግበት ክፍሉ ስለየራስን ዕድል በራስ መወሰን ነው የሚያወራው፡፡ በራሳቸው የወሰኑት ከተሻረ የትኛው ዕድላቸው ላይ ወሰኑ?
ሌላው ይህ ሕግ በዝርዝር ባያብራራውም በውሳኔው መሠረት ለብቻቸው ተለይተው ራሳቸውን ማስተዳደር የሚጀምሩት ብሔረሰቦች ቀድሞ ከነበሩበት ዞን ወይንም ወረዳ ፍትሐዊ የሆነ የሀብት ክፍፍል ሊያደርጉ እንደሚችሉ አስቀምጧል፡፡ ክልል ሲመሠርቱ ያልተቀመጠውን፣ በደቡብ ክልል ውስጥ ዞንና ወረዳ (ልዩም ይሁን አይሁን) ሲመሠርቱ የንብረት ክፍፍል እንዲደረግ ያስቀምጥና ስለተግባራዊነቱም የብሔረሰቦች ምክር ቤት እንደሚከታተል ገልጿል፡፡ ፌደሬሽን ምክር ቤት አዋጅ ወይንም የፌደራሉ ሕገ-መንግሥት ስለ ክልል ምሥረታ ያላስቀመጠውን በሥሩ ለሚገኙ መስተዳድሮች ማስቀመጡ ለፌደራሉም መንግሥት ትምህርት ነው፡፡
የክልሉ ብሔረሰቦች እና የፌደሬሽን ምክር ቤቶች ሚና ሲገመገም፤
ከላይ በጥቅሉ ባስቀመጥነው መሠረት የኮንሶን ጉዳይ እንመልከተው፡፡ የኮንሶ ሕዝብ ከጠቅላላው አምስት ፐርሰንት ድጋፍ ካገኘ በክልሉ የብሔረሰቦች ምክር ቤት አማካይነት ሕዝበ-ውሳኔ ይካሄዳል፡፡ የልዩ ዞንነቱን ጥያቄ አብዝኃኛው ድምጽ ሰጪ ከደገፈው ውጤቱ ለክልሉ ብሔረሰቦች ምክር ቤት ቀርቦ ከጸደቀ በኋላ የዞን ምሥረታው ተግባራዊ ይሆናል፡፡ ምክር ቤቱ፣ ስለ ድምጽ አሰጣጡ እና በአጠቃላይ ስለ ነበረው ሁኔታ እና ሂደት ካጣራ በኋላ ሊያጸድቅም ሊሽረውም ይችላል፡፡
ጥያቄው አዲስ ክልል የመመሥረት ቢሆን ኖሮ ግን፣ ጥያቄውን ያቀረበው ብሔረሰብ ምክር ቤት፣ለምሳሌ ሲዳማ ቢሆን የሲዳማ ምክር ቤት፣ በሁለት ሦስተኛ ድምጽ ድጋፍ ካገኘ ይሄንኑ ውሳኔ በጽሑፍ ለክልል ምክር ቤት ያቀርባል፡፡ ጥያቄው የቀረበለት የክልል ምክር ቤት ሕዝበ-ውሳኔ ከማዘጋጀት የዘለለ በሕግ የተቀመጠ የመከልከል ወይንም ሌላ ሥልጣን የለውም፡፡ ጥያቄውን ለማብረድ ፖለቲካዊ ሥራ ሊሰራ ይችል ይሆናል፡፡ ጥያቄው በደረሰው በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ድምፀ-ውሳኔ ማዘጋጀት አለበት፡፡
የኮንሶን በተመለከተ፣ የደቡብ ክልል የብሔረሰቦች ምክር ቤት አንድም ሙሉ በሙሉ ጥያቄውን ካልተቀበለ አሊያም ተቀብሎ ሕዝበ-ውሳኔ ካላዘጋጀ ወይንም ደግሞ የሕዝበ-ውሳኔውን ውጤት ከሻረው ጉዳዩን በይግባኝ ወደ ፌደሬሽን ምክር ቤት ማምጣት ይቻላል፡፡ምክር ቤቱ ጥያቄውን በአወንታ ተቀብሎ ሕዝበ-ውሳኔ ሊያዘጋጅ መሆኑን የሚያሳዩ መረጃዎች መኖራቸውን ስለማይታወቅ ወደ ፌደሬሽን ምክር ቤት ሊመጣ ይችላል ማለት ነው፡፡
የክልሉ የብሔረሰቦች ምክር ቤት አወቃቀሩ ልክ እንደ ፌደሬሽን ምክር ቤት በክልሉ ውስጥ የሚገኙ ከእያንዳንዱ ብሔር አንድ አባል ያለበት፣ ነገር ግን ከአንድ ሚሊዮን በላይ ቁጥር ካለው ለእያንዳንዱ አንድ ሚሊዮን ሌላ ተጨማሪ አንድ አባል ለምክር ቤቱ ይጨመርለታል፡፡
አባላቱ የሚመረጡት የብሔረሰቡ ዞኖች ወይንም ወረዳዎች ምክር ቤት መካከል ሆኖ መሥተዳድር ከሌላቸው ግን በቀጥታ ከብሔረሰቡ ተመርጠው ይወከሉበታል፡፡ የፌደሬሽን ምክር ቤት ደግሞ ለክልል ምክር ቤት ከተመረጡ ተወካዮች ውስጥ በክልሉ አሸናፊ የሆነው የፖለቲካ ፓርቲ የፈለገውን ሰው ከምክር ቤቱ አባላት መርጦ ይልካል፡፡ ስለሆነም፣ የደቡብ ክልል ብሔረሰቦች ምክር ቤት የሚኖረው የአባላት ብዛት እና ክልሉ በፌደሬሽን ምክር ቤት የሚኖረው ውክልና እኩል ነው፡፡
የኮንሶ ብሔረሰብ፣ ቢያንስ 65 አባላት በሚኖሩት የብሔረሰቦች ምክር ቤት አንድ ወኪል ይኖረዋል፡፡ በፌደሬሽን ምክር ቤትም እንዲሁ፡፡ ከሕገ መንግሥታዊነት እና ሕጋዊነት ይልቅ፣ ከሕገ መንግሥቱ ጋር አብሮ በማይሄደው ፓርቲያዊ የሆነው ዴሞክራሴያዊ ማእከላዊነት ላይ በመመርኮዝ ውሳኔዎች እንደሚሰጡ ስለሚታወቅ፣የብሔረሰቦቹ ምክር ቤት አባላትም ለተመረጡበት ፓርቲ መታመን ስለሚጠበቅባቸው በክልል እና በፌደሬሽን ምክር ቤቶች መካከል የተለያዩ ውሳኔዎችን መጠበቅ አይቻልም፡፡
የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች በክልሉ የብሔረሰቦች ምክር ቤት ላይ የሚኖራቸው ተጽእኖ በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ የበለጠ የሚከፋው ደግሞ እነዚህ የክልል ከፍተኛ አመራሮች፣ የክልሎቹን ርዕሰ መስተዳደር ጨምሮ፣የፌደሬሽን ምክር ቤት አባል መሆናቸው ነው፡፡ ክልል ላይ ላደረሱት በደል አቤቱታ ሲቀርብባቸው፣ በፌደሬሽን ምክር ቤት በዳኝነት ይሰየማሉ፡፡
የፌደሬሽን ምክር ቤት ካሉት 153 አባላት ውስጥ፣ ከ65 የማያንሱ ከደቡብ ክልል የተወከሉ ናቸው፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች የክልሉ አቋም ለኮንሶ የዞን ጥያቄን አለመቀበል ከሆነ፣ የፓርቲውን ጫና እና የተማከለ ውሳኔውን እንኳን ብንተወው፣ የፌደሬሽን ምክር ቤት ላይ አብላጫ ድምጽ ለማግኘት በጣት የሚቆጠሩ ደጋፊዎችን ማፍራት ብቻ ነው የሚጠበቅበት፡፡
የኮንሶ ብሔረሰብ ወደ ኦሮሚያ ክልል ለመጠቃለል …..
የፌደራሉ ሕገ መንግሥት እንዴት መገንጠል እንደሚቻል እንጂ ሌሎች አገራት ከኢትዮጵያ ጋር መዋሃድ ቢፈልጉ እንዴት ሊቀላቀሉ እንደሚችሉ የሚገልጽ ሥነ-ሥርዓት አላስቀመጠም፡፡ አንድ ክልል ከሌላ ክልል ጋር መዋሐድ ቢፈልግ ወይንም አንድ ብሔር ከአንድ ክልል ወጥቶ ወደ ሌላ ክልል መካለል ቢፈልግ፣ ይሄንን ማስተናገድ የሚችል ግልጽ የሆነ ሕግ የለንም፡፡ እንደ አዲስ ክልል መመሥረት ለሚፈልግ ሥርዓት አለው፡፡ ግንኙነቱም በተገንጣዩ እና በቀሪው ክልል መካከል ይሆናል፡፡ ወደሌላ ክልል መጠቃለል ከሆነ ግን የሌላ ክልል ተሳትፎን ይጠይቃል፡፡
የኮንሶ ሕዝብ በኦሮሚያ ክልል ከቦረና፣ሊበን ከሚባለው አካባቢ መጣን ብለው ስለሚያምኑ፣ የቋንቋው ቤተሰብም ኩሽቲክ በመሆኑ፣ ከኦሮሞ ሕዝብ ባህል ጋር የሚመሳሰሉ ልምዶች ስላላቸው ይመስላል ይህ ዓይነት አማራጭ ሊነሳ የቻለው፡፡ የሁለቱ ክልሎች ቅንነት እስካለ ድረስ የድንበር ግጭት ሊፈታ በሚችልበት መንገድ በስምምነት መጨረስ ይቻላል፡፡ በተጨማሪም፣ የድንበር ማካለል ጥያቄ በማንሳት በሕዝበ ውሳኔ መፍታት ይቻላል፡፡
ይህን ለማድረግ ግን፣በኮንሶ ጉዳይ፣የኦሮሚያ ክልል የድንበር ጥያቄ ማንሳት ወይንም የሕዝቡን ጥያቄ መቀበል አለበት፡፡ ከወልቃይት ጉዳይ የሚለየው የኮንሶ ሕዝብ የኦሮሞነት ጥያቄ አለማንሳቱ ነው፡፡ ሁለቱም ቢሆኑ የድንበር ማካለል ብቻ አይደሉም፡፡ እንደዚህ ዓይነት ጥያቄዎችም ሕጋዊ አሠራር የሚያስፈልጋቸው ይመስላል፡፡
ሲጠቃለል፣ ሁሉም ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በማናቸውም ጊዜ ክልል የመመሥረት ሕገ-መንግሥታዊ የሆነ መብት አላቸው፡፡ ነገር ግን ከሰማኒያ በላይ ክልል የማቋቋም አቅም አለን ወይ? እንኳን ክልልና ወረዳና ዞን መቋቋምም ከወጭ አንጻር ከባድ ነው፡፡
በኢትዮጵያ ውስጥ ከ50 በላይ የሚሆኑት ብሔረሰቦች ቁጥራቸው ከ100,000 በታች ሲሆኑ ሃያ አንዱ ደግሞ ከ10,000 በታች ናቸው፡፡ ለቀበሌና ለወረዳ የመሳሰሉት አስፈላጊ የሆኑ ተቋማትንስ መቋቋም ይቻላልን? የበጀት፣ የሰው ኃይል እና የመሳሰሉትን ፍላጎቶች መሸፈን መቻሉ አጠራጣሪ ነው፡፡ይሁን እንጂ፣ መተግበር የማይቻል መብት ውሎ አድሮ ቅያሜ ማምጣቱ አይቀርም፡፡ የኮንሶም ጉዳይ ይሄው ነው፡፡ እናም የአሰፋ አባተን ግጥም ልዋስና ልደምደም፡፡
“የማትበላ ወፍ ተይዛ በጭራ፣
ልቤን አደማችው ሞጭራ ሞጫጭራ፤”
እንዳለው የማይተገበር መብት አስቀምጦ የሰው ሕይወት እና ንብረት እንዲጠፋ ምክንያት ከመሆን እንደ አዋጅ ቁጥር 7/1984 በግልጽ የትኞቹ ብሔረሰቦች ምን ዓይነት መስተዳደር ማቋቋም እንደሚችሉ አስቀድሞ ሕገ መንግሥቱን በማሻሻል ማስቀመጥ፣ ወይንም ደግሞ መብቶቹን ተግባራዊ ማድረግ ነው፡፡ አንድ ጊዜ ልዩ ወረዳ፣ ሌላ ጊዜ እንደ ኮንሶ፣ ከሌሎች ጋር በመቀላቀል ዞን ማድረግ ግጭትን መጥራት ነው፡፡ ተመጣጣኝ የሕዝብ ቁጥር እያላቸው፣ አንዱን መርጦ ዞን እንዲኖረው ማድረግ ፍትሐዊ አይደለም፡፡
ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ እና አቶ አንዱዓለም አራጌ 5 ዓመት እስር እንደዋዛ
ጋዜጠኛና ጦማሪ እስክንድር ነጋ እና የሰላማዊ ትግል አቀንቃኝ ፖለቲከኛ አቶ አንዱአለም አራጌ በሽብር እና በሃገር ክህደት ወንጀል ፅኑ እስራት ተፈርዶባቸው እስር ቤት ከገቡ መስከረም 3 ቀን 2009 ዓ.ም ድፍን አምስት ዓመት ሆናቸው፡
እስክንድር “ንፁህ ስለሆንኩኝ፣ የቀረበብኝ ማስረጃ የሌለ በመሆኑ እንዲሁም ፍርድቤቶችን የሚያህሉ የተከበሩ ተቋማት የበቀል የአፈናና የጭቆና መድረክ መሆን ስለሌለባቸው በነፃ እንድለቀቅ የተከበረውን ፍርድቤት እጠይቃለሁ” ብሎ በፌደራል ጠቅላይ ፍርድቤት ይግባኙን በነሐሴ 2004 ዓ.ም ያቀረበ ቢሆንም የከፍተኛው ፍርድቤት የፈረደበትን የአስራ ስምንት ዓመት ፅኑ እስራት እና አምስት አመታት ህዝባዊ መብቶች እግድ ጠቅላይ ፍርድቤቱም አፅንቶበት የፍርዱን ሩብ አመታት በእስራት አሳልፏል፡፡
በፌደራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር አዲስ አበባ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት አምስት አመታትን በእስር ሲያሳልፍ ዘንድሮ የ48 አመት ጎልማሳ የሚሆነው ጦማሪው እስክንድር ነጋ በየኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራያዊ ግንባር /ኢህአዴግ/ መንግስት ለሰባተኛ ጊዜ ሲታሰር በበርካታ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብተ ተሟጋች ድርጅቶች እስራቱ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደሆን ደምፃቸውን ከፍ አድርገው አምስቱንም አመታት ለኢትዮጵያ መንግስት ውትወታቸውን አስምተዋል፡፡
ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ የፍርድቤት የችሎት ሂደቱን በመከታተል ላይ እያለ በግንቦት ወር 2004ዓ.ም ፔን አሜሪካ ከተባለ አለማቀፍ ድርጅት በአደገኛ የመገናኛ ብዙሐን ድባብ ውስጥ ሆኖ በመፃፍ ላደረገው አስታዋፅኦዖ “የመፃፍ ነፃነት ሽልማትን” አግኝቷል፡፡ በዚሁ አመት አለማቀፉ የሰብዓዊ መብት ተማጋች ድርጅት አምነስቲ ኢንተርናሽናል እስክንድር ነጋ የህሊና እስረኛ ስለመሆኑ አውጇል፡፡
ለሰባተኛ ጊዜ ለእስር በተዳረገ በአንድ አመት ከአራት ወራት ጊዜ ውስጥ በታህሳስ 2005ዓ.ም ደግሞ የሂውማን ራይትስ ዎች የነፃ ንግግር ሽልማት አሸናፊ ከመሆኑ በተጨማሪ በ36ተኛው አለማቀፍ የፀሃፊዎች ፌስቲቫል ላይ እስክንድር ነጋ የፔን ካናዳ “የአንድ ስብዓዊነት ሽልማት” አሸናፊ ሆኗል፡፡
በጋዜጠኝነት ሙያው በሚሰራው ስራ የኢትዮጵያ የፀረ ሽብር አዋጅ ቀደምት ሰለባ የሆነው ጋዜጠኛ እስክንድር በ1997 ዓ.ም የተደረገውን አገር አቀፍ ምርጫ ተከትሎ መንግስት በአገር ክህደት፣ አመፅ በመቀስቀስ፣ህገ መንግስት እና ህግ መንግስታዊ ስርዓቱን በሃይል በመናድ ወንጀል ተከሶ ፍርድ ቤት የፈረደበት ቢሆንም አንድ አመት ከአምስት ወራት እሰራት በኃላ ክሱ ተቋርጦ መለቀቁ ይታወሳል፡፡
የኢንተርናሽናል ወመንስ ሚዲያ አሶሴሽን “የብርቱ ጋዜጠኛ” ሽልማት አሸናፊ የጋዜጠኛ እስክንድር ባለቤት ጋዜጠኛ ሰርክዓለም ፋሲልም የ1997 ዓ.ም ምርጫን ተከትሎ ከባለቤቷ ጋር በተመሳሳይ ክስ በአንድነት ታስራ በቃሊቲ እስር ቤት ሳለች የመጀመሪያ እና ብቸኛ ልጃቸውን ናፍቆት እስክንድርን ተገላገላለች፡፡
የያኔው ስድስተ አመት ህፃን ልጁን ከትምህርትቤት ወደ ቤት እያመጣ ሳለ በድንገት ያለምንም ማስጠንቀቂያ በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋለው እስክንድር ነጋ እነሆ ዛሬ አብረውት ከተከሰሱት 23 አባሪዎቹ ጋር አምስት አመትን ሲደፍን የቀደሞ የአንድነት ፓርቲ ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበርና የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አንዷለም አራጌም የእድሜ ልክ እስራቱን በቃሊቲ ማረሚቤት እየገፋ ይገኛል፡፡
‹ምርጫ 97ን›› ተከትሎ ወህኒ ከወረደው የቅንጅት አመራር አንዱ የነበረው የያኔው ወጣት የአሁኑ ጎልማሳ፣ በብዙዋች ዘንድ የሰላማዊ ትግል አርበኛ ተበሎ የሚወደሰውአንዷለም አራጌ የቅጥት ማቅለያ እንዲያቀርብ በፍርድቤት ሲጠየቅ አንዷለም አራጌ እንዲህ ብሎ ነበር ማቅለያውን ያቀረበው፡፡ “እኔም ለልጆቼ፣ ለወገኖቼ፣ ለአገሬ እና ለራሴ በመረጥኩት ሰላማዊ ትግል ስታገል ቆይቻለሁ፡፡ የበደልኩት ህዝብ አለ ብዬ አላምንም፡፡ ወንጀል ሰርቻለሁ ብዬ አላሰብም፡፡ ውስጤ ፍፁም ሠላማዊ ነው ከሳሾቼ የሚስጡኝን የግፍ ፅዋ ለመጠጣት ዝግጁ ነኝ፡፡”
አቶ አንዷለም አራጌ “ያልተሄደበት መንገድ” የሚል የመጀመሪያ መጸሐፉን በእስር ላይ ሆኖ ከቃሊቲ ማረሚያ ቤት ለአንባቢያን አደርሷል፡፡ በ2007 ዓ.ም ሰኔ ወር ደግሞ “የሀገር ፍቅር እዳ” የተሰኘው ሁለተኛ መጽሐፋ ዳግም ለህትመት በቅቷል፡፡
እስካሁንም ድረስ በእስር ላይ የሚገኙት እነዚህ የሰላማዊ ትግል አርበኞ አዲሱን አመት 2009 ዓ.ም የተቀበሉት አምስተኛ አመታቸውን በማሰብ ነው፡፡
እስክንድር ነጋ እና አንዷዓለም አራጌ በፍትህ እጦት አመታትን በእስር እንዲያሳልፉ ሲገደዱ እስራቸው አገሪቷ በዓለም አቀፍ ህግ መደረክ ተገዢ እሆናለሁ ብላ ቃል የገባችባቸውን የቃልኪዳን ሰነዶች ሁሉ የናደ ሰለመሆኑ የሰበዓዊ መብት ተሟጋቾች በተደጋጋሚ ሲሞግቱ አምስት አመታት አልፈዋል፡፡
ዛሬም አስራቸው ህገ መንግስቱን የጣሰ፣ አላግባብ፣ ኢፍታዊ እና የሰብዓዊ መብቶቻቸውን ያላከበረ ነው ፡፡ አንዱአለም በተለምዶው ቅጣት ቤት ተብሎ የሚጠራው ከፍተኛ ጥበቃ የሚደረግበት ክፍል ውስጥ ታስሮ ሲገኝ እስክንድር በቃሊቲ የተለያዩ ዞኖች ታስሯል፡፡ ሁለቱም እስረኞች ከቅርብ ቤተሰብ ውጪ ማንም እንዳይጠይቃቸው የተከለከሉ ሲሆን ከእስራቸው እስከ አያያዛቸው ኢሰብአዊነትን እያስተናገዱ አምስት አመት አስቆጥረዋል፡፡
ምንጭ፡- EHRP
በአማራ ክልል የተቀሰቀሰው ህዝባዊ ተቃውሞ አድማሱን እያሰፋ ቀጥሏል፤ በኦሮሚያ ኢኮኖሚ ተኮር ተቃውሞ እንደሚጀመር ይፋ ተደረገ
ብስራት ወልደሚካኤል
(አዲስ ሚዲያ)የወልቃይት የአማራ ማንነት መብት ጥያቄን መነሻ አድርጎ በጎንደር ፋሲል ከተማ የተጀመረው ህዝባዊ ተቃውሞ፤ የተለያዩ የሰሜን እና ደቡብ ጎንደር ወረዳና ከተሞችን ጨምሮ ወደ ምስራቅና ምዕራብ ጎጃም እንዲሁም ወደ ሰሜን ወሎ መቄት እና ሸዋ ሮቢት መስፋፋቱን እማኞች ለአዲስ ሚዲያ ተናግረዋል፡፡
በተለይ ነሐሴ 18 ቀን 2008 ዓ.ም. በምዕራብ ጎጃም ፍኖተ ሰላም ከተማ፣ ነሐሴ 20 ቀን 2008 ዓ.ም. ቡሬ ወምበራ ወረዳ ቡሬ ከተማ የፀረ አገዛዝ ህዝባዊ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፎች ተካሂደዋል፡፡ በሰሜን ጎንደር በተለያዩ ወረዳዎች እና ከተሞች ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ድረስ ተቃውሞዎች እና የመንግሥት የኃይል ርምጃዎችም የቀጠሉ መሆናቸው ተረጋግጧል፡፡
በጎንደር፣ ባህርዳር እና ደብረማርቆስ ከተሞች ከቤት ያለመውጣት ተከታታይ ህዝባዊ ተቃውሞች የተደረጉ ሲሆን ከነሐሴ 22-25 ቀን 2008 ዓ.ም. ደግሞ በተመሳሳይ ምልኩ በደቡብ ጎንደር ደብረ ታቦር ከተማ ከቤት ያለመውጣት ተቃውሞ እንደሚደረግ መረጃዎች አመልክተዋል፡፡
በአማራ ክልል ባሉ ሰሞንኛ ተቃውሞች በተለይ በማክሰኝት፡በገደብዬ፡በእንፍራንዝ፣ በአብደራፊ፣ በአርማጭሆ፣ በፍኖተ ሰላም፡ቡሬ፡ ጅጋ እና ማንኩሳ በተባሉ ወረዳዎች ህዝባዊ ተቃውሞዎች የበረቱባቸው መሆኑን ያገኘነው መረጃ አመልክቷል፡፡ በነኚህ ስፍራዎች የነበሩ ተቃውሞች መካከልም የተወሰኑ በማኀበራዊ ሚዲያዎች ሲሰራጩ መዋላቸውን ለመታዘብ ተችሏል፡፡
በነበሩ የአማራ ክልል ህዝባዊ ተቃውሞች ሁለት ሰላማዊ ሰዎች በመንግሥት መገደላቸው የተጠቆሙ ሲሆን፤ በተለይ በሰሜን ጎንደር ዞን ባሉ ወረዳዎች በነበሩ ተቃውሞች ጉዳት የደረሰባቸው ዜጎች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል ተገምቷል፡፡
በኦሮሚያ ክልልም ህዝባዊ የፀረ አገዛዝ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ ተቃውሞች የቀጠሉ ሲሆን፤ በዚህም በምዕራብ ሐረርጌ መሰላ ወረዳ በሚገኙ ዋልተሲስ እና ጎሮ በተባሉ መንደሮች በነበረው ህዝባዊ ተቃውሞ አራት ሰላማዊ ዜጎች በመንግሥት በተወሰደ የኃይል ርምጃ መገደላቸው ታውቋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ በሀገሪቱ ያለውን የመንግሥትን ግድያ፣ እስርና እና አፋና በመቃወማቸው በአዲስ አበባ ቂሊንጦ ወህኒ ቤት ለእስር የተዳረጉ የፖለቲካ እስረኞች በተለይም እነ አቶ በቀለ ገርባ በሀገሪቱ ከነሐሴ 19-21 ቀን 2008 ዓ.ም. ብሔራዊ የሀዘን ቀን በሚል ታስቦ እንዲውል ያደረጉት ጥሪ ከወዲሁ በተለያዩ ደጋፊዎቻቸው ተግባራዊ መደረግ መጀመሩ ታውቋል፡፡
የመንግሥት የኃይል ርምጅና ግፍ በመቃወም በሚደረግ ብሔራዊ የሀዘን ቀንም ፀጉር መላጨት፣ ጥቁር ልብስ መልበስ፣ ጥቁር ባንድራ(ጨርቅ) ማውለብለብ፣ ሻማ ማብራት፣ በተቃውሞ ትግሉ የተገደሉ ሰላማዊ ዜጎች ቤተሰቦችን መጎብኘት እና ተሰብስቦ ህዝባዊ ውይይት በማካሄድ እንዲተገበር ጥሪ ማስተላለፋቸውን ተከትሎ በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ ባሉ ዜጎች ከወዲሁ ተግባራዊ መደሩ የሚያመለክቱ የተለያዩ ምስሎች በማኀበራዊ ሚዲያዎች ላይ መሰራጨታቸውን ማየት ተችሏል፡፡
በኦሮሚያ ያለው ህዝባዊ ተቃውሞ ካለው የፖለቲካና ማኀበራዊ ጉዳዮች በተጨማሪ ከጳጉሜ 1 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ የኢኮኖሚ ተኮር ህዝባዊ ተቃውሞችም እንደሚተገበሩ የኦሮሞ ተቃውሞ አስተባባሪዎች እና የመብት አራማጆች ይፋ አድርገዋል፡፡ ይሁን እንጂ የአኮኖሚ ተኮር ህዝባዊ ተቃውሞው ምን ላይ እንደሚያተኩር በዝርዝር የተቀመጠ ነገር ባይኖርም፤ ወደፊት ይፋ እንደሚደረግ የደረሰን መረጃ አመልክቷል፡፡
በታቀደው መሰረት በኦሮሚያ የኢኮኖሚ ተኮር ህዝባዊ ተቃውሞ ተግባራዊ የሚደረግ ከሆነ መንግሥት በክፍተኛ ደረጃ የውጭ ምንዛሪ እጥረትና አደጋ ላይ እንደሚወድቅ ይጠበቃል፡፡ በተለይም መንግሥት ከክልሉ በከፍተኛ ደረጃ የውጭ ምንዛሪና የሀገሪቱ ዋነኛ የገቢ ምንጭ የሆኑት እንደ ቡና፣ የጫት፣ የአበባ፣ የቁም እንሰሳትና፣ የቆዳና ሌጦ እንዲሁም የምግብ ነክ የሆኑ የብግርና ምርቶች እንዲሁም ወርቅና የመሳሰሉ የማዕድን ሃብቶች ከክልሉ እንዳይወጡና ወደ ማዕከላዊም ሆነ የክልሉ ገበያ ንግድ ላይ የማይውሉ ከሆነ ምን አልባትም በሀገሪቱ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ከባድ ፈተና በመንግሥት ላይ ሊደርስ እንደሚችል ይጠበቃል፡፡
የኢኮኖሚ ተኮር ህዝባዊ ተቃውሞ በቀጣይ ወደሌሎች ክልሎች በተለይም አማራ እና ደቡብ ክልል የሚዛመት ከሆነ ደግሞ የመንግሥት 90% የገቢ ምንጭ በማድረቅ ስርዓቱን ሙሉ ለሙሉ አደጋ ላይ እንደሚጥለው ይገመታል፡፡ በተለይ ኦሮሚያ እና አማራ ክልል ብቻ የሀገሪቱን 54% የሆነውን ህዝብ ቁጥር እንደሚሸፍኑ እና ከ65% የሀገሪቱ የውጭ ምንዛሪና የገቢ ምንጭም መሆናቸው ይታወቃል፡፡
ከባለፈው ህዳር 22 ቀን 2008 ዓ.ም. በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ የተቀጣጠለው የፀረ አገዛዝ ህዝባዊ ተቃውሞ መላው ኦሮሚያ ክልልን በማዳረስ፤ ከሐምሌ 5 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ ወደ አማራ ክልል ተዛምቷል፡፡ በሁለቱም ክልሎች ዘገባው እስከተጠናቀረበት ድረስ ህዝባዊ ተቃውሞዎቹ በተለያዩ ወረዳዎችና ከተሞች ቀጥሏል፡፡ እስካሁን ባለው መረጃ በሁለቱም ክልሎች ባሉ የተለያዩ ቦታዎች መደበኛ የመንግሥት ስራን ጨምሮ የተለያዩ ፖለቲካዊ፣ ማኀበራዊና ኢኮኖሚያዊ አለመረጋጋቶች እየታዩ ነው፡፡
አስረኛ ወሩን ባስቀጠረው ህዝባዊ ተቃውሞ በሁለቱም ክልሎች ከ650 በላይ ሰላማዊ ዜጎች በመንግሥት በተወሰደ የኃይል ርምጃ ሲገደሉ፣ ከ 1,250 ያላነሱ ዜጎች ቆስለው በግምት ከ35,000 በላይ ሰዎች ለእስር ተዳርገዋል፡፡ በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች የተገደሉ እና የቆሰሉ ሰዎች በተለያየ ጊዜ ስማቸውና ምስላቸው በሰፊው በማኀበራዊ ሚዲያ እየተገለፀ ይገኛል፡፡ በሁለቱም የኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች ህዝባዊ ተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ የወጣው ህዝብ አንዱ ለሌላው በተለያዩ ጊዜና ቦታ ያሳዩት የርስ በርስ አጋርነት፤ መንግሥትን ከፍተኛ ድንጋጤ ላይ እንደጣለው ባለስልጣናቱ በስራቸው ባሉ መገናኛ ብዙኃን ሲናገሩ የተደመጡ ሲሆን፤ በዚህም ስጋት እንዳደረባቸው ባለስልጣናቱና ደጋፊዎቻቸው በይፋ የሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎችና ከሚሰነዝሯቸው አስተያየቶች መረዳት ተችሏል፡፡
በኦሮሚያ ክልል ህዝባዊ ተቃውሞ ፤የአዲስ አበባ እና የኦሮሚያ ክልል ፊንፊኔ ዙሪያ ልዩ ዞን ”የጋራ ልማት የተቀናጀ ማስተር ፕላን” በአዲስ አበባ ዙሪያ ያሉ ገበሬዎች የሚያፈናቅልና ለጎዳና ህይወት የሚዳርግ ነው በሚል ቀደም ሲል የነበረውን ተቃው ከዓመት በኋላ በማገርሸት በምዕራብ ሸዋ ጊንጪ ከተማ መጀመሩ ይታወቃል፡፡ በአማራ ክልል ደግሞ የወልቃይት ጠገዴ የአማራ ማንነት መብት ጥያቄ ህዝባዊ ወኪሌ ኮሚቴ አባላት ላይ መንግሥት በሌሊት በመኖሪያቸው አካባቢ የፀጥታ ኃይሎችን በመላክ የኃይል ርምጃ መውሰዱን ተከትሎ በጎንደር ከተማ መጀመሩ ይታወሳል፡፡
መንግሥት በወሰደው የኃይል ርምጃ ስለደረሱ አጠቃላይ ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳቶች በተመለከተ በመንግሥት ጉዳዩን ለመሸፋፈን ከመሞከር በዘለለ ትክክለኛውን ቁጥርና የጉዳት መጠለን ለመናገር አልደፈረም፡፡ ቀደም ሲል ሀገር በቀል በሆነው የሰብዓዊ መብት ጉባዔ (ሰመጉ) እና ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች በሆነው ሂውማን ራይትስ ዎች (HRW) አማካኝነት በተወሰኑ ወረዳዎችና አካባቢዎች የተደረጉ ምርመራዎች ይፋ ከመደረጋቸው በስተቀር አጠቃላይ በደረሱ የሰብዓዊ እና ቁሳዊ ጉዳቶች የተደረገ ምርመራም ሆነ ሪፖርት የለም፡፡ ይህን በተመለከተ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ምት ኮሚሽን ጉዳዩ በገለልተኛ አካል ምርመራ እንዲደረግ በይፋ ጥያቄ ቢያቀርብም በስልጣን ላይ ያለው መንግሥት በበኩሉ የመንግሥታቱን ድርጅት ጥያቄ ውድቅ በማድረግ ምላሽ መስጠቱ ይታወሳል፡፡
በኢትዮጵያ በሁለት ቀናት ብቻ በተቀሰቀሰው የፀረ ጭቆና አገዛዝ ህዝባዊ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ 132 ዜጎች ተገደሉ
(አዲስ ሚዲያ) በኢትዮጵያ ትናንት ሐምሌ 30 ቀን 2008 ዓ.ም. እና ዛሬ ነሐሴ 01 ቀን 2008 ዓ.ም. በኦሮሚያ እና አማራ ክልል በተቀሰቀሰው የፀረ ጭቆና ህዝባዊ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ ላይ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች በወሰዱት የኃይል ርምጃ ህፃናት እና ሴቶችን ጨምሮ በርካታ ሰላማዊ ንፁሃን ዜጎች ተገደሉ፡፡ በተለይ እንደ መብት አራማጆች እና የአካባቢው ምንጮች መረጃ ከሆነ በሁለቱ ቀን የኦሮሚያ እና አማራ ክልል የፀረ ጭቆና አገዛዝ ህዝባዊ ተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ 132 ንፁሃን ዜጎች መገደላቸው ተጠቁሟል፡፡
በተለይ እንደ መብት አራማጆች መረጃ ከሆነ፤መነሻውን የአዲስ አበባ እና የኦሮሚያ ልዩ ዞን የተቀናጀ የጋራ ማስተር ፕላን በማድረግ ወደ ጠቃላይ ሀገራዊ ይዘት የስርዓት ለውጥ ጥያቄ ያደገው የኦሮሞ ተቃውሞ ትናንት ሐምሌ 30 ቀን 2008 ዓ.ም. አዲስ አበባን ጨምሮ በኦሮሚያ ክልል ባሉ ከተሞች አጠቃላይ በተጠራው የረ ጭቆና አገዛዝ ህዝባዊ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ ህፃናት እና ሴቶችን ጨምሮ 67 ያህል ዜጎች በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች በተወሰደ ወታደራዊ ርምጃ ሲገደሉ፤ ከ500 ያላነሱ በፅኑ ቆስለው በክምና ላይ መሆናቸውን የደረሰን መረጃ አመልክቷል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ትናንት በነበረው የኦሮሚያ ክልል እና የአዲስ አበባ ተቃውሞ ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ በርካታ ዜጎች መታሰራቸውም ተጠቁሟል፡፡

በትናንትናው ተቃውሞ በኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ ግድያ ከተፈፀመባቸው የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፎች መካከል በምዕራብ አርሲ አሳሳ፣ በምስራቅ ሐረርጌ አወዳይ እና ሐረማያ እንዲሁም በምስራቅ ወለቃ ነቀምት ከተሞች ዋነኛ ተጠቃሾች ናቸው፡፡ በነበረው የኦሮሚያ ተቃውሞም የህወሓት መንግሥት በቃን፣ የኦሮሞን ህዝብ መግደል ይቁም፣ የታሰሩ የፖለቲካ እስረኞች በአስቸኳይ ይፈቱ፣አሸባሪ አይደለንም፣ አማራ የእኛ ነው፣ የጎንደር አማራዎችን መግደል ይቁም፣ የወልቃይት ጥያቄ ሕገ መንግሥታዊ ነው፣ወያኔ ሌባ፣…የሚሉ መፈክሮች ተሰምተዋል፡፡ በነበሩ የተቃውሞ ሰልፍ ከተሞች እና አካባቢዎች በርካታ ሰዎች መሳተፋቸውን ከኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ ዘገባ፣ ማኀበራዊ ሚዲያ እና ከተለያዩ አካባቢዎች ያገኘናቸው የዓይን እማኞች መረጃ ማወቅ ተችሏል፡፡
በተመሳሳይም በአማራ ክልል በተለይም በደቡብ ጎንደር ዞን ደብረ ታቦር ሐምሌ 30 ቀን 2008 ዓ.ም. በተጠራው የፀረ ጭቆና አገዛዝ ህዝባዊ ተቃውሞ ሰልፍ ላይ መንግሥት በወሰደው ወታደራዊ የኃይል ርምጃ ከ6 ያላነሱ ሰዎች ወዲያው ሲገደሉ በርካቶች በመቁሰላቸው፣ በሰሜን ጎንደር ዞን ባሉ ወረዳዎች እና በደቡብ ጎንደር ጋይንት ጨምሮ የተለያዩ ወረዳቸዎች ነዋሪዎች በመቆጣት በድንገት የተቃውሞ ሰለፍ ማድረጋቸው ታውቋል፡፡ መነሻውን የወልቃይት የአማራ ማንነት መብት ጥያቄ በማድረግ ወደ አጠቃላይ የስርዓት ለውጥ ጥያቄ ያደገው የአማራ ተቃውሞን ተከትሎ መንግሥት ከደብረ ታቦር በተጨማሪ የተቃውሞ ሰልፎች በነበሩበት ስፍራዎች ሁሉ ወታደራዊ የኃይል ርምጃ በመወሰዱ የህዝቡ ቁጣ ተባብሱ የህወሓት ደጋፊና ተባባሪ ናቸው የተባሉ የንግድ ተቋማት፣ የመንግሥት ተሸከርካሪዎች እና ተቋማት ላይ እንዲሁም በጎንደር አዘዞ የሚገኘውን የመከላከያ ወታደራዊ ካምፕ ከጥቅም ውጭ ማድረጋቸው ተሰምቷል፡፡
በሰሜን ጎንደር ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ድረስ በሰሜን ጎንደር ሳንጃ፣ ቆላ ድባ፣ ዳባት፣ አርማጭሆ፣…በመሳሰሉ ቦታዎች በመንግሥት ወታደሮች እና በህዝቡ መካከል ውጊያ መኖሩን እና የመንግሥት ወታደሮችን እና ከህዝቡም በርካታ ሰዎች መሞታቸውን እና መቁሰላቸውን ምንጮች አረጋግጠዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ዛሬ ነሐሴ 01 ቀን 2008 ዓ.ም. በባህርዳር ከተማ በነበረው የአማራ የፀረ ጭቆና ህዝባዊ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ ከ30 ያላነሱ ሰዎች በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች መገደላቸው ታውቋል፡፡ በአማራ ክልል ዛሬ የተገደሉ 30 ያህል እና ትናንት ደብረ ታቦር ከተገደሉ 6ቱ በተጨማሪ ሰሜን ጎንደር ዞን ባሉ የተለያዩ ወረዳዎች በተደረገ የትናንት እና የዛሬ ተቃውሞ 29 ሰዎች በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች መገደላቸው ተጠቁሟል፡፡ ህዝቡም በባህርዳር የተለያዩ ህዝባዊ ተቋማት ሰንደቅ ላይ የብአዴን እና በኢህአዴግ የፀደቀውን የፌደራሉን ሰንደቅ ዓላማ በማውረድ የቀድሞውን አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ሰንደቅ ዓላማ ሲሰቅሉ እና ሲያውለበልቡ ተስተውሏል፡፡ በአጠቃላይ በሁለቱ ቀን የአማራ ክልል ተቃውሞ 65 ያህል ዜች ሲገደሉ፤ ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ በርካታ ዜጎችም መቁሰላቸውን እና የህክምና ርዳታ እየተደረገላቸው መሆኑን የዓይን እማኞች አረጋግጠዋል፡፡

በተለይ በደብረ ታቦር እና ባህርዳር በተደረገው የአማራ ክልል ህዝባዊ ተቃውሞ፤ ወልቃይት የአማራ እንጂ የትግሬ አይደለም፣ ወልቃይት አማራ ነው፣ ለሱዳን የተሸጠው መሬታችን ይመለስ፣ የታሰሩት ይፈቱ፣ በኦሮሞ ወገኖቻችን ላይ የሚደረገው ግድያ ይቁም፣ በቀለ ገርባ መሪያችን እንጂ አሸባሪ አይደለም፣ ኢትዮጵያዊነት አሸባሪነት አይደለም፣በኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ አንደራደርም፣ወያኔ ሌባ፣አንዳርጋቸው ጽጌ መሪያችን እንጂ አሸባሪ አይደለም፣ የህወሓት አገዛዝ በቃን፣ ግድያ ይቁም፣….የሚሉ መፈክሮች ተሰምተዋል፡፡
በኦሮሚያ እና አማራ ክልል እየተካሄደ ባለው የፀረ ጭቆና አገዛዝ ህዝባዊ ተቃውሞ ምክንያት የኢንተርኔት አገልግሎት በመቋረጡ በርካታ መረጃዎች በመታፈናቸው በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች በተወሰደ ወታደረዊ የኃይል ርምጃ የተገደሉ እና የቆሰሉ ዜጎች ቁጥር ከተጠቀሰው ሊጨምር እንደሚችል ይገመታል፡፡
በኦሮሚያ እና በአማራ ክልል በነበሩ ህዝባዊ ተቃውሞዎች በጠፋው የሰው ህይወት እና በወደሙ ንብረቶች ዙሪያ እስካሁን ከገለልተኛ አካል የተጣራ ይፋ ማብራሪያም ሆነ መግለጫ የለም፡፡ ይሁን እንጂ በሁለቱም ክልሎች ባሉ በርካታ ወረዳዎችና ከተሞች ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ድረስ አለመረጋጋቱ እንደቀጠሉ ለማወቅ ተችሏል፡፡