“ያልተሄደበት መንገድ” – ሊነበብ የሚገባው ድንቅ መጽሐፍ!
ነፃነት ዘለቀ
ይህን የአንዱአለም አራጌን በራሱ አገላለጽ ከጠባቧ የቃሊቲ እስር ቤት የተጻፈ ግሩም መጽሐፍ ሳነብ የተሰማኝን ስሜት ባጭሩ ለመግለጽ እንጂ ሥነ ጽሑፋዊ ደንብ የተከተለ ሂስ ወይም የመጽሐፍ ግምገማ ለመስጠት አለመነሳቴን መግለጽ እፈልጋለሁ – መሆኑን እንዴት ከረማችሁ?
ከሁሉ በፊት ግን ከሰሞነኛ ጉዳዮች መካከል ቂላቂሉ ወያኔ በአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ላይ የሠራውን አስቂኝ ድራማ ስመለከት እያዘንኩ የታዘብኩትን በዓለም ወደር የማይገኝለት ምርጥ የምርመራ ውጤት በሚመለከት ትንሽ ልበል፡፡
የኢትዮጵያን ቴሌቪዥን በውነቱ አልመለከትም፤ አለመመልከቴ ስህተት መሆኑ ቢገባኝም ጤንነቴን አጥብቄ ስለምፈልገው ይሁነኝ ብዬና ቁም ነገር አገኝበታለሁ ብዬ ኢቲቪን አላየውም – ብዙዎች እኔን መሰሎች ስላሉ “የዐዋጁን በጆሮ” እንዳትሉኝ እንጂ፡፡ የሆኖ ሆኖ በቀደምለታ ከሰዎች ጋር የሆነ ቦታ ቁጭ ብዬ ቁርስ ቢጤ ስንቀምስ በፖሊስ ፕሮግራም የተከታተልኩት በዓይነቱም ሆነ በይዘቱ ድንቅ የሆነ የወያኔ የወንጀል ምርመራ ቴክኒክና ውጤት ያጫረብኝን ልዩ ስሜት በዚህ አጋጣሚ ሳላነሳው መቅረት አልፈለግሁም፡፡ ከእውነት ሰው መሆኔን ጠላሁ፡፡
“መርማሪው” ወያኔ አይታይም፤ ይህን የለመድነው ነው፡፡ ወያኔዎች ራሳቸውን እንደወንጀለኛ አድርገው ስለሚቆጥሩና ከአልቃኢዳ ጋር የሚያመሳስሏቸውን ድርጊቶች የሚፈጽሙ መሆናቸውን ሕዝቡ የተረዳው መሆኑን ስለለተገነዘቡ ይመስለኛል የመንግሥትን ሥልጣንና ኃይልም የጨበጡ “ምሁራኑ መርማሪዎች” በግልጽ በሚዲያ መታየትን የሚወዱ አይመስሉም ፤ እነዚህ ጭራቅ ገራፊዎችና ሀዘን አምላኪዎች (ሳዲስቶች) በራሳቸውም በመንግሥታቸውም የሚተማመኑ እንዳልሆኑና በሆዳቸውና በዘረኝነት ቁርኝታቸው ብቻ ተለክፈው በስሜት ፈረስ የዕውር ድምብር ግልቢያ ዜጎችን የሚያሰቃዩ ናቸው – ቀናቸው ሲደርስ ምን እንደሚውጣቸው ፈጣሪ ብቻ ነው የሚያውቀው፤ አሣር አለባቸው – የቁናው ሥፍር እየተንደረበበ ይጠብቃቸዋል – እዚህ ወይም እዚያ፡፡ ከሞራል ዕሤቶቻችንና ከምርመራ ህግ በወጣ ሁኔታ አቡበከር የሚባለውን የሙስሊም ተቃውሞ አመራር አባል እጆቹን በእጀሙቅ አስረው የሚያካሂዱትን “ምርመራ” በአደባባይ በቲቪ ለዓለም ሕዝብ ሲያሳዩም “መርማሪው ሊቅ” መታየትን አልወደደም – አስጠሊታ ሣቁ ግን ከአንጀቱ ጥርስ ሳይሆን ከማተብ የለሽ አንገቱ ይሰማ ነበር፡፡ ስለዚህ የአንዲ ልዩነት እጆቹ አለመታሰራቸው እንጂ ሂደቱ ልክ እንደአቡቦከር ነው፡፡ ይህ የምርመራ ሂደትና ውጤቱ የሀገራችን የለየለት ውርደትና የወያኔን ማንአለብኝነት ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው፡፡ ወያኔዎች ከግዑዝ ድንጋይ የማይሻሉ የመጨረሻ ደደቦች መሆናቸውን ምናልባትም ለሚሊዮንኛ ጊዜ የገለጡበት ማፈሪያ ድርጊት ነው፡፡ የሚታዘነው በተመርማሪዎቹ ሳይሆን በመርማሪ ተብዬዎቹ ነው፡፡ ከመነሻው የዘረኝነት ልክፍት ያሽመደመደውና ከዘር ማዕቀፍ ውጭ የማያስብ ደንቆሮ ማይምና ሳዲስት እንዴት አንድን የተማረን ሰው ይመረምራል? እንዲያው ትንሽም ቢሆን የተማረ ዘረኛ ወያኔ ጠፍቶ ነው ወይ? ይህ ዓይነቱ የአደባባይ ግፍ ሄዶ ሄዶ የሚያስከትለውን መዘዝ እንዴት አጡት? ድንቁርና ይህን ያህል በጀብደኝት ያሳውራል?
ወደአስቂኙ ድራማ ልለፍ፡፡ አንዳርጋቸው በ“ነፃ ኅሊናው” የሰጠውና ለኢትዮጵያ ሕዝብ በደናቁር የወያኔ ወንበዴዎች እሳቤ ሊተላለፍ የተፈለገው መልእክት ይህን ይመስላል፤ “የግንቦት ሰባት ኅልውና ከእንግዲህ ግፋ ቢል ለሁለት ወራት ቢዘልቅ ነው፤ ወዲያም አለ ወዲህ ዕድሜው ከሁለት ወር አይበልጥም፡፡ የአውሮፓና አሜሪካ ምቾቱን ትቶ እንደኔ በረሃ ወርዶ የሚያታግል ቆራጥ ሰው አይኖረውም፡፡…” የግንቦት ሰባት ቀሪ ዕድሜ ሁለት ቀንም ይሁን ሁለት ወር እሱ ሌላ ጉዳይና ወደፊትም የሚታይ ሆኖ ይህን የተናገረው ግን አንዳርጋቸው ጽጌ መሆኑን ልብ ይሏል – አንዲን በሚዲያም ቢሆን ባላውቀው ኖሮ ከአሁን በፊት “የተናገረውን”ና ገና ወደፊት “እንደሚናገረው በጉጉት” የሚጠበቀውን ሁሉ በበኩሌ ሳላንገራግር በሙሉ ልቤ አምኜ በተቀበልኩና ከወያኔ የሸፈተውን ልቤን ወደወያኔ በመለስኩ ነበር – ይህ ሁሉ ድካማቸው ታያ የማንን ቀልብ ለመሳብ ? በመሠረቱ እስካሁን ወያኔ የነበረ በአንዳርጋቸው ንግግር ምክንያት የወያኔነት ደረጃው አይጨምርም – በተቃራኒውም እስካሁን ወያኔ ያልነበረ በዚሁ የአንዲ ንግግር ምክንያት ንዴቱና ቁጭቱ ይጨምርና ወደድርጊት ይገባ እንደሆነ እንጂ ከተቃዋሚነቱ የሚያፈገፍግ አይመስለኝም፤ እናም የወያኔዎች የጅልነት ምጥቀት ያሳዝነኛል ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያውያንንና ዓለምን በጠቅላላው እስከዚህን ያህል መናቃቸው ምን ያህል ወራዳዎች – እደግመዋለሁ ምዕመናን – ምን ያህል ወራዳዎች መሆናቸውን ከማሳየት በስተቀር የአንዲ ስቃይና የሙሌት ኑዛዜ የሚጨምርላቸው አንዳችም አወንታዊ ነገር የለም – ይህን ነባራዊ እውነት ለመናገር ደግሞ የክር ወይም የሃቂቃ ጉዳይ እንጂ የግንቦት ሰባት አባልም ሆነ ደጋፊ መሆንን አይጠይቅም፡፡ የወያኔዎችን ውስጠ ምሥጢርና የግፍ ታሪክ በየመድረኮች ሲዘከዘክ ሚሊዮኖችን በዕንባ ሲያራጭና በትካዜ ባህር ሲያሰምጥ የምናውቀው አንዳርጋቸው ጽጌ በምትሃታዊ ፍጥነት ወደማፊያው መንግሥት ተገልብጦ ተናገረው የተባለውን እንዲያ ሲናገር ይታያችሁ፡፡ የምናውቀው አንዳርጋቸው የምናውቅለትን ጽኑ ፀረ-ወያኔ አቋሙን በሻጥርና በብዙ ገንዘብ ክፍያ በየመኖች ተይዞ በወያኔዎች እጅ በገባ በሁለት ሣምንታት ጊዜ ውስጥ ሲለውጥ በዐይነ ኅሊናችሁ ይታያችሁ፡፡
ግሩም የምርመራ ውጤት! ዓለምን የሚያስደምም ሣይንሳዊ የወንጀል ምርመራ ግኝት! በዚህ በአንዳርጋቸው ቃልና የመከራ ኑዛዜ ማፈር ያለበት ቀደም ሲል ለመጠቆም እንደሞከርኩት ወያኔ ብቻ ነው፡፡ ከወያኔ ውጭ ማንንም ሊያሳፍር አይችልም፡፡ እንዲያውም እኔ ብሆን ኖሮ “ግንቦት ሰባት የሚባል ድርጅት ከነአካቴው በሕይወት አለ እንዴ? አሁን እናንተ ስትሉ ሰማሁ፡፡ ማን ተናገር እንዳለኝ አላውቅም ዝም ብዬ ነበር እኮ በኢሳት ያንን ሁሉ ንግግር የምዘባርቀው፡፡ ደግሞ ብርሃኑን ብሎ ግንቦት ሰባት! ከመነሻው ግንቦት ሰባት ብሎ ነገር ሲኖር አይደለም ወርቆቼ! …” ብዬ አስደስታቸው ነበር እንጂ የሌለን ምሥጢር ለመደበቅ በመሞከር ሰውነቴን ለስቃይ አልዳርግም – ሊያውም በዚያ ኑዛዜየም ስቃዩን ቢቀንሱልኝ አይደል? ግን አይቀንሱልኝም – ስለዚህ ብናገርም ባልናገርም ለውጥ የለውም፤ ጠባችን በደም የሚጠራ እንጂ በውሃ ታጥቦ የሚጸዳ አይደለምና፡፡
እንደውነቱ ታዲያ አንዳርጋቸው ሊሰጠው የሚችለው የማይታወቅ የተከደነ አዲስ ምሥጢር ሊኖር ይችላል? ሁሉም ነገር እኮ ግልጽ ነው፤ ወያኔ የሚባል ሀገር አጥፊና ፀረ-ሕዝብ የሆነ የማፊያዎች ቡድን አራት ኪሎ ቤተ መንግሥት ውስጥ መሽጎ አለ – እሱን ለማስወገድ ደግሞ ዜጎች በተበታተነ ሁኔታም ቢሆን በየፊናቸው ጥረታቸውን እያደረጉ ነው፤ ምሥጢር ከተባለ ይህ ነው ምሥጢሩ፡፡ አንዳርጋቸው የትግል መስመሩ ስላበሳጫቸውና እየሠራ ያለው ነገር ለኅልውናቸው አስጊ ሆኖ ክፉኛ የሚያሳስባቸው በመሆኑ እርግጥ ነው እሱን ከመድረክ ገለል እንዲል ማድረግ ቢፈልጉ ያንን መቀበል ይቻላል – ሰይጣናዊ ፍላጎታቸውን ለማርካት የሄዱበት ርቀት ብዙ የሕግና የሞራል ችግር ማስነሳቱ እንዳለ ሆኖ፡፡ ከዚያ ውጪ ምሥጢር አውጣ ብሎ የዓለማችን ቤት ባፈራው የማሰቃያ ዘዴ ሁሉ ሰውን ማሰቃየት፣ በዚያም ሂደት ራስን ለትዝብትና ለስላቅ የሚያጋልጥ ነውረኛ የምርመራ ሂደት ማካሄድና ተመርማሪዎች የማያምኑበትን ነገር እንዲናገሩ ማድረግ በእግረ መንገድም “በሰላም አንገዛም፣ አንገብርምም ያሉንንና ሕዝብን የሚያሳምጹብንን ቀንደኛ ጠላቶቻችንን ‹እንዲህ አሸናናቸው!›፣ የወንዶች ወንዶች መሆናችንን ብልታቸውን እየቆረጥን አሳየናቸው…” በማለት ስብዕናን ለማዋረድ መሞከር ወደራስ የሚዞር አሉታዊ ውጤትን መጋበዝ መሆኑን መረዳት ይገባቸው ነበር፡፡ ለነገሩ ወያኔ ልብሱም ጉርሱም ቅሌትና ውርደት በመሆኑ በዚህ ረገድ የሚሰማው አንድም የሀፍረትም ሆነ የይሉኝታ ስሜት የለም፡፡ ጃዝ ብለው የለቀቁት 13 እና 33 ቁጥሮችም እየሳቁበትና እየተዝናኑበትም ቢሆን ወያኔ ለሚሠራው ግፍና በደል ሁሉ ቡራኬያቸውን አይነፍጉትም፡፡ እነሱስ ቢሆን በጭፍሮቻቸው አማካይነት በጓንታናሞና ኢራቅ ውስጥ አስከሬኖች ላይ እስከመሽናት በሚዘልቅ ኢሰብአዊነት ስንትና ስንት ግፍ ይፈጸሙ የለም? ልጅ ከአባት ቢማርና የጭካኔ ደረጃውን አዘምኖ ምሥኪን ኢትዮጵያውያንን ምድራዊ ገሃነም ውስጥ ቢዘፍቃቸው ዋኖቹ ሀዘን አምላኪዎች ይደሰታሉ እንጂ ከከንፈር ሽንገላ ባለፈ ሕዝቡን ሊታደጉት አይፈልጉም – ይህንንም አሳምረን እናውቃለን፡፡ ጭምብሉን ፖለቲካዊ የተለሳለሰ የሚመስል አካሄድም አንዘነጋም – አገም ጠቀሙን፡፡
በነገራችን ላይ 13 እና 11 ወይም 33 ደግሞ ተመሳሳይነት አላቸው፡፡ ለሚያምንበት ሁሉም የትልቁ ቁጥር የአውሬው መገለጫ የ666 ቅንስናሾች ናቸው፡፡ አሥራ አንዶች በ110 የለበጣ ቀመር ቢያላግጡም እውነቱ ቀፎ የመለዋወጥ – የትሮይን ፈረስ ቅርጽ የማሻሻል ጉዳይ እንጂ ሲሙ ያው ነው – አሥራ አንድ፡፡ ለነገሩ ዝናር ባንገቴም ይሁን 11 ወይም ዜሮም ይሁን አንድ ሽንትር ዋናው ነገር ተግባር ነው፡፡ ሌላው ትርፍና ጨዋታን ለማሳመር ያህል በአጃቢነት የገባ ነው፡፡ እናም በሀገራችን ሁኔታ የሰውዬው ማንነት ምንም ይሁን ምን በስቃይና በግድያ የሚያምን ሁሉ እናት ክፍሉና ጥንተ አመጣጡ ከአውሬው መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ ክፉና ደግ መንፈሶች ኅብረት የላቸውም፡፡ ሩህሩህ መሐሪና አረመኔ/ጨካኝ ገዳይ አንድነት የላቸውም፡፡ መጽሐፉም ጣፋጭ ፍሬ በዛፍ ላይ ሳለ ይታወቃል እንደሚል ማን የማን ወገን መሆኑ በተለይ በዘመናችን በግልጽ ይታወቃል፡፡ ማን ነው የበሽታ ሕዋሳትን በቤተ ሙከራ እየፈለሰፈና እያራባ ለዓለም በተለይም ለኋላቀር ሀገሮች እንደ ዕርዳታ ስንዴ የሚያከፋፍል? ማን ነው የዓለማችንን የአየር ንብረት እያዛባና ዕድሜዋን በብርሃን ፍጥነት እያሳጠረ የሚገኘው? የዓለምን ጠቅላይ ገዢነት በትረ መንግሥት በጉልበት የተቆጣጠረውና “ለኔ ካልሰገዳችሁ ሀብትና ሥልጣን አይኖራችሁም” ብሎ ሁሉን እያስደገደገ የሚገኘውና በትዕምርተ ኅቡኣታዊ ባለአንድ ዐይን ፒራሚዳዊ ቅርጽ ወይም በፔንታጋራማቲን የኮከብ ቅርጽ የሚታወቀው ምሥጢራዊ ኃይል ማን ነው? ማን ነው አሁንም ሆነ ከአሁን በፊት መካከለኛውን ምሥራቅ እያተራመሰ ያለው? መፍለቂያው የሆነችን የአንዲት ትንሽዬ ሀገር ኅልውናና የበላይነት ለማስጠበቅ ሲል ድምጽን በድምጽ የመሻር መብቱ የዓለምን የመንግሥታት ኅብረት እንደአሽከር ሰጥ ለምበጥ አድርጎ የሚገዛ ማን ነው? አይኤም ኤፍ፣ ዩኤን፣ ወርልድባንክ፣ ኔቶ፣ ሲአርኤፍ፣ … የማን አድቃቂ ክንዶች ናቸው? ለመሆኑ የዚህ ሞገደኛ የወቅቱ የዓለማችን ገዢ ዋና መሥሪያ ቤትና ቅርንጫፍ ቢሮዎቹ የት የት ናቸው? ጽዮንና ሀማስ የማን ልዑካን ናቸው? የግጭቶች መንስኤና የምክንያታዊነት ሚዛኑ ለማንም ያጋድል ዋናው የሁለቱም ተልእኮ ግና ለአውሬው ግብር የሚሆን ብዙ የደም ባህር ማቆር መሆኑን መዘንጋት የዓለም ነገር አያገባኝም ብሎ እንደመመነን ይቆጠራል፡፡ በየትኛውም የዓለም ክፍል – ማን ነው የጦር ኃይሎችን በሁለት ጎራ እየከፈለ በተፃራሪነት በማሰለፍ የሚሊዮኖችን ደም በከንቱ እያፋሰሰ ያለው? ኢራንና አሜሪካ በርግጥም ባላንጣዎች ይሆኑ እንዴ? በፍጹም፡፡ ጠላቶች መስለው ትያትር በመከወን ለአንድ ዓላማ ስኬት የሚተጉ የአንድ ገዢ አንድ አምሳል አንድ አካል ናቸው፡፡ ማን ነው በአራት ወራት ጊዜ ውስጥ ብቻ ከአፍ እስከገደፋቸው በንጹሃን ተሣፋሪዎች ጢም ብለው የሞሉ የሲቪል አውሮፕላኖችን(የማሌዥያን) ባልታወቀ ዕፀ መሠውርና በሚሳኤይል ድራሻቸውን ያጠፋው? ምን ዓይነት ወያኔያዊ ጨካኝ አንጀት ያለው ፍጡር ይሆን ይህን ያደረገ? ለምን ዓላማ? ቫቲካንንና መለስተኛ አውሮፕላን የምታህል የነጭ እርግብ ምስል ለማስመሰል ያህል በሰላም ምልክትነት በዋና የፓትርያርክ ጸ/ቤቱ በር ላይ ያቆመውን የኛኑ ኦርቶዶክስ ሳይቀር ከሞላ ጎደል ሁሉንም የሃይማኖት ተቋማት ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ ተቆጣጥሮ ሁሉንም ሃይማኖት አለኝ ባይ በአውሬው ትዕዛዝ ሥር ያደረገው ማን ነው? ለመሆኑ በአሁኑ ሰዓት ቅዱስ ሊባል የሚችል ቦታና ሰው አለ ወይ? ፖፕ ጆን ፖል አንደኛ፣ ፖፕ ቤኔዲክት 16ኛ፣ ‹አቡነ› ጳውሎስ የኛ… ሌሎችም የማን ወኪል ነበሩ? ፍየሎች በበጎች ጋጣ ውስጥ መሽገዋል፡፡ በጎች እያለቁ ነው፡፡ አውሬው ሆሊውድና ቦሊውድን ብቻ ሳይን ገዳማትንና ካቴድራሎችንም ከተቆጣጠረ ምዕተ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ጭካኔን በሚያስተምሩ ፊልሞች፣ በልቅና ባልተገሩ ኢ-ሞራላዊም በሆኑ ፖርኖግራፊዎች በተለይ የዓለምን ወጣት ትውልድ ጡጦ ከመጣሉ በእንጭጩ ለማምከን ይህችን ዓለም ማንና ከየትስ ሆኖ እየገዛት እንዳለ መች አጣነው? የዚያ ‹ታላቅ› የጨለማ ንጉሥ የእጅ ሥራዎች የሆኑ ወያኔዎችም ባቅማቸው ቅድስቲቱን ሀገር ድራሽዋን ቢያጠፏት ከድጋፍ በስተቀር ማን ከልካይ አላቸው? በጎችስ ቢጮኹ አለጊዜው ማን ይደርስላቸዋል? ግን ግን አይዞን፤ የፍየሎችና የበጎች የመጨረሻ ዕድል ተለይቶ የሚታወቅበት የፍርድ ቀን በፍጥነት እየመጣ ነው፡፡ ብሎም ቢሆን ሥጋዊም ሆነ መንፈሳዊ ድል በምኞት ሊገኝ እንደማይችል ልብ ማለት ይገባናል፡፡ ብቻ ይህን መሰሉን ነገር በሆድ ይፍጀው ለሌላ ቀን በይደር ማቆየቱ ሳይሻል አይቀርም፡፡ ለነገሩ እኛን ምን አገባን? ሁሉም ከልኩ አይዘል፡፡
ከሰው ተውሼ እያነበብኩት ነበር – “ያልተሄደበት መንገድ”ን፡፡ በቅርብ ካነበብኳቸው በሀገር ችግር ዙሪያ ከሚያጠነጥኑ የቅርብ ጊዜ መጻሕፍት ውስጥ በኔ ዕይታና ለኔ ፍጆታ ይሄኛውን ወደር አላገኘሁለትም፡፡ አንዱአለም አራጌ ዋለ የተዋጣለት መጽሐፍ በመጻፉ – ሊያውም በዚህ አፍላ የጎልማሳነት ዕድሜውና በመከራ ውስጥ ሆኖ – ባለበት አድናቆቴ ይድረሰው፡፡ ወላድ በድባብ ትሂድ የሚባለው በዚህ ዓይነት አጋጣሚ ነው፡፡ ሚሊዮኖች ፈርተንና ለሥጋችን አድረን በየሽርንቁላው ተወትፈን በፍርሀት ቆፈን ስንርድ ሊያውም በእስር ቤት ውስጥ ሆኖ ይህን የመሰለ አብሪ መጽሐፍ ካለበቂ ማጣቀሻና ዋቢ መጻሕፍት በአዩኝ አላዩኝ ሰቀቀን ሌሊት ሌሊት እየተደበቁ መጻፍ ልዩ ጀግንነትና ተሰጥዖም ነው፡፡ አንዱአለምና መሰል የብዕርና የፖለቲካ ታጋዮች ለነፃይቱ ኢትዮጵያ በሕይወት እንዲደርሱ እግዚአብሔር ይታደገን፤ ይታደጋቸው፡፡ ቤተሰባቸውንም ይባርክ፡፡ ለእኛም ለባከንነውና ለራሳችን ጥቅምና ፍላጎት ስንል በ‹እስኪያልፍ ያለፋል› ተረት ራሳችንን እያታለልን የወያኔ ባርያ ሆነን ለጠፋነው ዜጎችም ፈጣሪ ረድኤቱንና ወኔውን ይስጠን፡፡ እንደዚህ ያሉ ዜጎች ባይኖሩን ኖሮ ሕይወት በጠቅላላው ለይቶላት ጨለማ በሆነች ነበር፡፡ ከዚህ አንጻር እግዜር የተመሰገነ ይሁን፡፡ እርሱን መሰል ሌሎች ጸሐፊዎችንና ታሳሪዎችንም ጭምር እግዜር ይባርክልን፡፡ ለቤታቸውም ያብቃልን፡፡ የሚሳነው ነገር የሌለው የኢትዮጵያ አምላክ የመከራ ደብዳቤያችንን የሚቀድድና ሃራ የሚያወጣን አንዳች ኃይል ይዘዝልን፡፡ አሜን፡፡
ይህ መጽሐፍ የዋቢ መጻሕፍትን ገጽ ጨምሮ በጠቅላላው 320 ገጾች አሉት፡፡ በአራት ዋና ዋና ክፍሎች ሥር የተካተቱ 18 ርዕሶችንም ይዟል፡፡ ጠቅጠቅ ብሎ የተጻፈ በመሆኑ እንደሌሎች በርካታ መሰል መጻሕፍት በቀላሉ አይገፋም፡፡ የሆኖ ሆኖ በተለይ እስከማገባደጃው ድረስ ስሜትን ቆንጥጦ በመያዝ መነበብ የሚያስችለው ሥነ ጽሑፋዊ ውበትና ይዘታዊ ግርማ ሞገስ አለው፡፡ እናም አንብቡት፡፡ በነገራችን ላይ ይህን መጽሐፍ እያነበብኩ ወደ ገጽ 100 አካባቢ ስደርስ የተዋስኩትን እንደምመልስ ገባኝና ወዲያውኑ ከተማ ወጥቼ ገዛሁት፡፡ ተውሼ ያነበብኩትን ወይም እያነበብኩት ያለሁትን መጽሐፍ ስገዛ ይህ የመጀመሪያ ጊዜየ ነው፡፡ አንጡራ ሀብቴና የመጻሕፍት መደርደሪያየ አንዱ ፈርጥ እንዲሆን ተመኘሁ፡፡ ተመኝቼም አልቀረሁ፡፡ ለልጆቼ ውርስ ይሆናል፡፡ እናንተም አሁኑኑ ግዙና ንብረታችሁ አድርጉት፡፡ መጽሐፉ “ኩሎ አመክሩ ወዘሰናየ አጸንዑ” እንዲል፡፡
አመስጋኝ አማሳኝ እንዳልባል በዚህ መጽሐፍ የታዘብኳቸውን አንዳንድ ግድፈቶችም በዚሁ አጋጣሚ ብጠቁም ደስ ይለኛል፡፡ ጥቂት የማይባሉ የአርትዖት ችግሮች አሉበት፡፡ አሉታዊ መሆን ያለበት በአወንታዊ ወይም የዚህ ተቃራኒ ሆኖ የሚጻፍበት አጋጣሚ አልፎ አልፎ ይስተዋላል፡፡ አማርኛ ላይ ብዙውን ጊዜ የምታስቸግር ነገር አለች – ለምሳሌ “እኔን እንደሚያገባኝ እንዴት ረሳኸው?” በሚለው ዐረፍተ ነገር ውስጥ “ሚ”ን “ማ” ብናደርጋት ትርጉሙ ሙሉ በሙሉ ይለወጣል፡፡ “ጽንፍ” ለማለት “ቅንፍ” ብንል አንዳንዶችን ግር ሊያሰኝ ይችላል፡፡ የአርትዖት ሥራ ሽንፍላ እንደማጠብ ነው፡፡ በተቻለ መጠን ብዙ ሰዎች በብዙ አዳዲስ ዐይኖች ሊተባበሩበት የሚገባው አስቸጋሪ ሥራ ነው፡፡ እንዲያም ሆኖ የማይጠራበት ጊዜ አለ፡፡ ከዚህ አኳያ ይህን ቆንጆና ለታሪክ የሚቀመጥ መጽሐፍ ዐዋቂ ሰው እንደገና “ኤዲት” ቢያደርገው የበለጠ ማለፊያ ይሆናል፡፡ የግሌ አስተያየት ነው፡፡ (አንድ ወዳጄ የነገረኝ አንድ አርትዖታዊ ስህተት በጭንቅላቴ ብልጭ እያለ ‹እዚህ ላይ ካልጻፍከኝ ሞቼ እገኛለሁ!› ብሎ አስቸገረኝ፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው፡፡ የመሥሪያ ቤቱ የብድር ኮሚቴ ስብሰባ ይጠራል፡፡ ለተሰብሳቢዎችም “ከብድር ኮሚቴ…. ለጠቅላላ አባላት” የሚል ጽሑፍ ተበትኗል፡፡ ሁሉን ያስፈገገው ግን ጸሐፊዋ “ከብድር ኮሚቴ” ከሚለው ሐረግ ውስጥ የአንዱን ቃል የመጨረሻ ፊደል ሳትጽፈው መቅረቷና እስከዚያን የስብሰባ ጊዜ ድረስ ማንም ጉዳዩ የሚመለከተው አካል ስህተቱን ልብ አለማለቱ ነበር፡፡ ያቺ “ነገረኛ” ጸሐፊ የትኛዋን ሆሄ እንደዘነጋቻት እኔም አሁን ዘነጋኋት፡፡ )
ከሆሄያት ግድፈትና ሞክሼ ፊደላትን በነባሩ ሰዋስዋዊ ልማድ ከመጠቀም አኳያ ከሚታዩ አንዳንድ ጥቃቅን “ስህተቶች” በተጓዳኝ ጥቂት የመረጃ መዛባትና የዘይቤና ፈሊጥ አጠቃቀም እጅግ አነስተኛ ችግር ሳይኖር እንደማይቀር እገምታለሁ፡፡ ለምሳሌ “ኢሕአፓ” የሚለው ምሕጻረ ቃል ሲፈታ እኔ የማውቀው “የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ፓርቲ” በሚል ነው፡፡ በዚህ መጽሐፍ ግን “የኢትዮጵያ ሕዝብ አደራጅ ፓርቲ” በሚል ከአንዴም ሁለቴ ገደማ ቀርቧል፡፡ ፈሊጥን በተመለከተ “ለያዥ ለገራዥ” ለማለት “ለያዥ ለገናዥ” ተብሏል፡፡ በተጨማሪም የሃሳብ ድግግሞሽ በስፋት ይታይበታል፡፡ በዚያም ምክንያት አንድ አንባቢ በጀመረበት የስሜት ሞቅታ መጨረስ ባይችል ችግሩ ከዚህ የሃሳቦች መደጋገም የሚመነጭ ይመስለኛል፡፡ የሆኖ ሆኖ የመጽሐፉ አጻጻፍና ለኅትመት መብቃት በብዙ ችግር የታጠረ በመሆኑ የአሁኑ ይዘቱ ራሱ ከሚጠበቀው በላይና በአንጻራዊ ሁኔታ ከሌሎች በርካታ መሰል ጸሑፎች(እኔ ካነበብኳቸው) በጣም የተሻለ መሆኑን በበኩሌ ልገነዘብ ችያለሁ፡፡ በመሆኑም ይህ ጥረቱ ደራሲውን በእጅጉ ያስመሰግነዋል፡፡ እዬዬም ሲደላ ነው ጓዶች፡፡ እነኚህንና መሰል ሌሎች እንከኖችን አስተካክሎ በቀጣይ ኅትመት ለንባብ የሚያበቃው ወገን ከተገኘ መልካም ነው፡፡ ደግሞም የማይቻል አይመስለኝም፡፡
አንዱአለምን በዚህ መጽሐፉ ደርቤ እንዳነበብኩት የፕሮፌሰር መስፍን ደቀ መዝሙር ይመስለኛል፡፡ ይህን የምለው ፕሮፌሰሩ አንድ ወቅት እነብርሃኑ ነጋ “ሁለገብ ዘዴን በመጠቀም ወያኔን እንታገላለን” ባሉ ወቅት ክፉኛ ይተቿቸውና “እኛ ወደዚህ ‹የማይረባና ውዳቂ› የአስተሳሰብ ደረጃ አንወርድም” ማለታቸውን በማስታወስና አንዱአለምም በዚያው ቅኝት አሁንም ድረስ በዚህ በኢትዮጵያ ውስጥ ወንዝ ቀርቶ የደረቀ ምንጭ በማያሻግር የሰላማዊ ትግል ሥልት ወያኔን እንጥላለን ብሎ የሚያምን በመሆኑ ነው፡፡ እርግጥ ነው አንዱአለም አሁን ባለበት ሁኔታ በኃይል ወይም በጦር መሣሪያ ወያኔን እንታገል ብሎ ቢጽፍ የሚደርስበትን ተጨማሪ መከራና ፍዳ ስለምንገነዘብ ይህን አቋም ያርምድ ብለን በሰው ቁስል እንጨት አንሰድም፡፡ ይሁንና ቢያንስ ዝም ማለት ሲገባ ወያኔ የፈጠረው የኢትዮጵያ ውጥንቅጥ ችግር የሚፈታው ወያኔን በሰላማዊ መንገድ በመታገል ብቻ ነው የሚል እምነት በጭፍን ማራመዱን አልወደድኩለትም፡፡ (በነገራችን ላይ ኤርምያስ ለገሰ ቅድም በኢሳት አንድ ውይይት ላይ ሲናገር እንደሰማሁት የአንዳርጋቸውን በወያኔዎች መያዝ ኔልሰን ማንዴላ በኢዲያሚን ዳዳ እንደተያዘ ያህል እቆጥረዋለሁ ማለቱን እኔም በጣም እደግፋለሁ፡፡) ሰው ከሰው ጋር ቢታገል አሸናፊውና ተሸናፊው ይለያል፡፡ ከአውሬ ጋር ግን እንዴት መታገል ይቻላል? ውሾች በ“አስተሳሰብ” ከሚበልጡት ወያኔ ጋር እንዴት ስለሰላም መወያየት እንደሚቻል አንዱአለም ቢያስረዳኝ ደስ ባለኝ፤ ውሾ ሲሸናነፉ በሚያሳዩት ተፈጥሯዊ ምልክት ይግባቡና ጦርነቱን ያቆማሉ፤ ከዚያም በመካከላቸው ሰላም ይሰፍናል፡፡ ሁኔታዎችም ወደጥንቱ (statusquo ante) ይመለሱና ማኅበረከልባዊ ሕይወት ትቀጥላለች (“ከልብ” ውሻ ማለት ነው – “ል” ጠብቃ አትነበብም)፡፡ ወያኔ ግን ያሸነፈውን ሁሉ በሕይወት ያለውን ብቻም አይደለም የሞተውን ሳይቀር እስከመቃብር ድረስ የፕሮፓጋንዳ ሠራዊት እያዘመተ የቅርብ አጥንቶችንና የሩቅ አፅሞችን የሚፋለም ዶንኪሾት ነው፡፡ ይህን ባሕርዩን ለማወቅ በግድ እንደነአሥራት ወ/የስ መሞትና እንደነእስክንድር ነጋ መታሰር አያስፈልግም፡፡ ዛሬ ላይ ቁጭ ብሎ ወያኔን በሰላማዊ መንገድ ከሥልጣን አስነሳለሁ ብሎ መቃዠት በርግጥም ቅዠትና ሲያንስም የዋህነት እንጂ አንዱአለምን ከመሰለ በሳል የፖለቲካ ሰውነት የሚጠበቅ አይመስለኝም፡፡ ከዚህ ውሱን ነጥብ አኳያ ምን እንደነካው ሊገባኝ አልቻለም፡፡
አክራሪ ኦርዶቶክሳውያን እንዳይቀየሙኝ እንጂ የአንዱአለም የዋህነት (naivety?) ከ‹ቅድስት› ክርስቶስ ሠምራ ጋር ይመሳሰልብኛል፡፡ ‹ቅ.› ክርስቶስ ሠምራ – በገድሏ ላይ ተጽፎ እንደሚነበበው – ሰይጣንን ከእግዚአብሔር ለማስታረቅ ዕቅድ ትነድፋለች አሉ፡፡ … እርሱ ወዳለበት ሲዖል በቀጥታ ትሄዳለች፡፡ “ስፈልግሽ ኖሮ እዚሁ መጣሽልኝ?” ይላትና የክርስቶስ ሠምራን ነፍስ ይዞ ወደግዛቱ ሊያስገባት ሲል መላእክት ደርሰው ወደመጣችበት ወደገነት ይወስዷታል፡፡ በአጋጣሚው ግን 78 ሺህ የተኮነኑ የሲዖል ነፍሳት በቅድስቲቷ መንፈሳዊ አካል ላይ በመጣበቅ ወደገነት ይገባሉ፡፡ እምነት ነው፡፡ በየዘመናቱ በገዢዎችና በሃይማኖት መሪዎች ፈቃድ እንዲካተቱ የተደረጉና እነዚህን አሳሳች ይዘት ያላቸውንና እርስ በርስ የሚቃረኑ፣ “በእግዚአብሔር መንፈስ የተነዱ” ሰዎች ስለመጻፋቸው የሚጠቁም አንዳችም ማስረጃም የሌላቸውን በመጽሐፍ ቅዱስ የተካተቱ አንዳንድ ጽሑፎችንና ሰይጣናዊ ሳጋዎችን ሳይቀር ላለመቀበል አንድ ሰው መብት ያለው መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ይህን ኢትዮጵያዊ ሃይማኖታዊ ድርሰት ማመን አለማመን የማንም ውዴታ እንጂ ግዴታ ሊሆን አይገባም – እዚያው ውስጥ በሚገኙት ዘንድም ቢሆን፡፡ ታርጋ ሳይለጠፍብኝ ስለሃይማኖቴ ልናገር እንዴ? አይ፣ ለማንም አይጠቅምም፡፡ ግን ማንኛውንም ሃይማኖታዊ አክራሪነትና ጽንፈኝነት የምጠላ አማኝ(theist) መሆኔን ብገልጽ ደስ ይለኛል፡፡ አነሳሴ ወዳልሆነ ነገር በመንሸራተቴ ይቅርታ – ምን ላድርግ ሁሉም ነገር አንሸራታች ሆኖ ዐረፈው እኮ፡፡ ብቻ አንዱአለም የዚህችን ቀና ሴት ባሕርይ የተላበሰ ግን በአፀደ ሕይወት የሚገኝ የማይቻልን ነገር ለመሞከር የሚተጋ የወንድ ክርስቶስ ሠምራ ይመስለኛል፡፡
ሰላማዊ ትግል የራሱ መደላድል አለው፡፡ በቅድሚያ የሀገርህ ሰው ከሆነ ሰው ጋር፣ ዜጋህ ከሆነ ሰው ጋር፣ እንደዜጋው ከሚቆጥርህ ወይም ከሚመለከትህ የአገዛዝ ኃይል ጋር፣ በትንሹ ደግሞ ሰው መሆንህን አምኖ ከሚቀበል ሰው ጋር እንጂ ከአውሬና ከለዬለት የዲያብሎስ መንጋ ጋር በሰላማዊ መንገድ እታገላለሁ ብለህ ወርቃማ የመቶዎች ዓመታት ጊዜህን አታባክንም – አንዱአለም የሚለው ግን ዝንታለሙን እየታሰርንና እየተገደልን ነፃነታችንን ከወያኔ በችሮታ እንቀበል ነው – ምናልባትም በወዲያኛው የምፅዓት ዘመን፡፡ ሰዎች ወያኔን መረዳት እንዴት እንዳልቻሉ ወይም እንደማይችሉ ሳስበው ይገርመኛል፤ እንዲያውም ወያኔዎች፣ ሰዎች እንዲህ እንዲሆኑ – ማለትም በሰላማዊ መንገድ ከነሱ ጋር መታገል እንደሚቻል እንዲያምኑና እንዲያሳምኑ – የሚያደርግ ድግምት ቢጤ ሳይኖራቸው የሚቀር አይመስለኝም፡፡ አለበለዚያስ የሰላማዊ ትግልን ገፈት ቀማሽ ከሆነ አንዱአለምን ከመሰለ ብርቅዬ ዜጋ እንዲህ ያለ ተሳስቶ የሚያሳስት አነጋገርና እምነት ሊደመጥ ባልተገባ ነበር፡፡ ይቅርታ ይደረግልኝና ዝምታ ማንን ገደለ? በከንቱ መነቃቀፍ ከትዝብት በስተቀር ምን አወንታዊ ውጤት ያስገኛል? እንዳለመታደልና እንደርግማንም ሆኖ በኅብረት መታገል ቢያቅት ሁሉም ባመነበት ቢንቀሳቀስ ምን ክፋት አለው? ከአድማስ ማዶ ሊኖር ይችላል ተብሎ በሚታሰብ ሥጋት ከወዲሁ መቆራቆስ አግባብ ነው ወይ? ለዚህማ ወያኔ አለ አይደል? ይህን ስል አንዱአለማውያንና መስፍናውያን – በተወሰነ ደረጃ እኔንም ጨምሮ – ስሜታችን እንደሚጎፈንን ይሰማኛል፡፡ ግን ምርጫ የለኝም፡፡ የሚሰማኝን መናገሬ እንደወንጀል ሊቆጠርብኝ አይገባም፡፡ አውቃለሁ – አንዱአለም እሳት ውስጥ ነው፡፡ አልክድም – እኔም ከርሱ ባልተናነሰ ሁኔታ እሳት ውስጥ አለሁ፡፡ ልዩነታችን እርሱ ባመነበት ገብቷል፡፡ “ደስ”ም ያለው ይመስላል፡፡ የኔ ግን ከሁሉ ያጣ ሆኜ በዕብደትና በስክነት መካከል አንዴ ሰው አንዴ ዐፈር በመሆን እየተቀያየርኩ መረጋጋትና ሰላም የሌለው ሕይወት እገፋለሁ፡፡ ኅሊናህን አፍነህ መኖር ከመታሰር በበለጠ እንደሚጎዳ አውቄያለሁ፡፡ ሰው እንኳን ሳያውቅልህ በአእምሮ ስቃይ ምክንያት ከቤተሰብህም ከጓደኞችህም ‹እየተናጀስክ› ሰላምህን አጥተህ በትልቁ እስር ቤት መኖር በትንሹ እስር ቤት ከመኖር የበለጠ እንደሚያሰቃይ ተረድቻለሁ፡፡ መብላት፣ መጠጣት፣ መዳራትና በሰፊ ጎዳና መመላለስ ትርጉም የሚያጡበትና አንጎልህ ተቀፍድዶ ተይዞ ሰዎችን ሰላም በምትነሳበት ሁኔታ ለመኖር ያህል ብቻ መኖር ከለዬለት ከርቸሌ ያልተሻለ መሆኑን ከተረዳሁ ቆይቻለሁ፡፡ ስለሆነም ከአንዱአለም ባልተናነሰ የኔም እስረኝነት የዋዛ አይደለምና ሁላችንም አንድ ነን፡፡ እንዲህ የምለው ስለኔ ብቻ አይደለም – ስለሌሎች እኔን መሰሎችም እንጂ፡፡ እንዲህ የምለው ግን ለምንድነው? የማንን አንጀት ለማላወስ? ማንስ ነው ሆዴ ላይ ቆሞ ያናዘዘኝ? ሆ!
በውሸት መከሰሱን፣ በውሸት ምሥክር (አዳፍኔ በሚላቸው) ዘብጥያ መውረዱን፣ በውሸት የግንቦት ሰባት አባልና የሽብር ጥቃት ሊፈጽም ከምንደኞች ጋር እያቀነባበረ ነው መባሉን፣ …. ሁሉንም ዘንግቶ ከእባብ ዕንቁላል እርግብ እንደሚፈለፈል ሊያስረዳን መሞከሩ አንዱአለም ወያኔን ለማወቅ ገና ብዙ ጊዜ የሚፈጅበት መሆኑን አመልክቶኛል – ጠሊቅ ሀገራዊና ታሪካዊ ዕውቀት ያለው መሆኑ ተይዞልኝ፡፡ እናም እላለሁ – ሰማይ ዝቅ መሬት ከፍ ቢሉ ወያኔ በሰላማዊ ትግል ሥልጣን አይለቅም፡፡ ይህን ፀሐይ የሞቀውንና ሀገር ያወቀውን ሃቅ በመካድ ከዚህ የተለዬ ህልም ማለም – እንደአካሄድ ባይከለከልም – ትዝብት ላይ ይጥላል፡፡ በነገራችን ላይ ክርስቶስም ለትግስቱና ለፍቅሩ ገደብ ነበረው፤ ለዚህም ነው በመሳም አሳልፎ የሰጠውን ይሁዳን የረገመው – በአንገቱ የወፍጮ መጅ ታስሮ ወደጥልቅ ባህር ቢወረወር እንደሚሻለው በምሬት በመናገር፡፡
ይቅርታችሁንና በዚህስ አንዱአለምን ተናድጀበታለሁ፡፡ ምን ነካው ግን? እንግዲያውስ ያበጠው ይፈንዳ በኢትዮጵያ እንደእስካሁኑ የስግብግብነትና ራስ ወዳድነት በሽታችንና የሥልጣን አራራችን ከሆነ በሰላማዊ መንገድ እንኳንስ ወያኔ ኢንጂኔር ግዛቸው ሽፈራውም ሥልጣን አይለቅም፤ እንኳንስ ወያኔ ኢንጂኔር ኃይሉ ሻውልም አይለቅም (በጤና ምክንያት …ካልሆነ)፤ እንኳንስ ወያኔ ፕሮ. በየነ ጴጥሮስም አይለቅም፤ እንኳንስ ወያኔ ዶር. መረራ ጉዲናም አይለቅም፤ እንኳንስ ወያኔ ዶር. ፍስሐ እሸቱም አይለቅም፤ እንኳንስ ወያኔ በቁሙ የሞተው ከሃዲው ልደቱ አያሌውም አይለቅም … (ዝርዝሩ ብዙና ብዙ ነው – ስንተዋወቅ? ግን እባብ ልቡን ዐይቶ እግሩን ነሣው ሆነና …)፡፡ የኢትዮጵያ መሬት አዲስ በሚፈልቅ ፍቱን ጠበል ካልተረጨ ይሄ የሥልጣንና የገንዘብ እንዲሁም የሴሰኝነት ጠንቆች በቀላሉ አይለቁንም – በኛ ባሱብን እንጂ እርግጥ ነው እነዚህ መሰናከያዎች የአጠቃላዩ የሰው ዘር መደናቀፊያዎች መሆናቸው የታወቀ ነው (ለምሳሌ የሰሞኑንና የቅርብ ሩቅ ጊዜውን የኢራቁን አልማሊኪንና የግብጹን አልሲሲን የሥልጣን ሱስ ብናይ በሰው ልጅ ራስ ወዳድነት መገረማችን አይቀርም – ይህ ነገር ወደኛ መጥቶ ከማይምነታችን፣ ከሥልጣን ወዳድነታችንና ከቦክሰኛው አስተዳደጋችን ጋር ሲደመርማ ምን ያሳይ፡፡) በኛ ሀገር ለሁሉም ነገር በተለይም ለጥላቻችንና ለራስ ወዳድነታችን ልጓም አጣን፤ ለከት ጠፋ፤ በቃኝን ተጸየፍን፤ ጠገብኩን ጠላን፤ ከይሉኝታና ሀፍረት ተፋታን – ስንገርም፡፡ እናም ለነዚህ ነገሮች ያለን ጥብቅ ቀረቤታ ከሌሎች የጥፋት ሰበዞች ጋር ተደማምሮ እንደሀገርም እንደሕዝብም ከናካቴው ከምድረ ገጽ ልንጠፋ – መለኮታዊ ጣልቃገብነት በቅርብ ጊዜ ውስጥ ካልተከሰተ – ዘመኑ ቀረበ፡፡ ውሸት ነው? ውሸት ነው ካልክ እውነት ነው ማለት ነው፡፡ “አልሞትኩም ብዬ አልዋሽም” የሚል መጽሐፍ ዱሮ አነበብኩ ልበል? አዎ፣ ‹ፀጉራም ውሻ አለ ሲሉት ይሞታል› እንዲሉ ካልሆነ ለይቶልን ጠፍናል፡፡ አንወሻሽ፡፡
አንዱአለም ወያኔ በሰላማዊ መንገድ ሥልጣን እንደማይለቅ አሳምሮ ያውቃል፡፡ መጽሐፉ ላይ በገደምዳሜ ገልጾታል፡፡ እንደመፍትሔ በየገጾቹ የሚያቀርበው ግን ያንኑ የሰላማዊ መንገድ የትግል ሥልት ነው፡፡ “የሰላማዊ መንገዱ ካልሠራ” ይላል አንዱአለም ፈገግ ባደረገኝ ሁኔታ “የሰላማዊ መንገዱ ካልሠራ ሌላ የሰላማዊ መንገድ መሞከር ነው፡፡” ከመሰነባበታችን በፊት በመጽሐፉ መጨረሻ አካባቢ ገጽ 312 ላይ የሚገኘውንና ወያኔን በሰላማዊ መንገድ ማስወገድ ባይቻል በማስከተል ምን ማድረግ እንደሚገባ አንዱአለም የመጨረሻ መፍትሔ ብሎ የሚሰነዝረውን እንመልከት – ወጣቱ ፖለቲከኛ አይፈረድበትም፡፡ የት ነው ያለውና? አያድርስ ነው – እነዚህ ሰዎች አስጨንቀው ያዙንና እምንለውንም እያሳካሩ ግራ አጋቡን እኮ፡፡ አንዱ ለጓደኛው “ያዋስኩህን ዕቃ ባትመልስ ዋልህ! አሳይሃለሁ!” ይለዋል፡፡ “ምናባህ ልታደርገኝ አንት የውሻ ልጅ!” ብሎ ቢያፈጥበት “አይ፣ ምን አድርግሃለሁ ያው ታዝቤህ እቀራለሁ እንጂ” አለው ይባላል፡፡ እርግጥ ነው መናገር የማድረግን ያህል እንደማይከብድ አውቃለሁ፡፡ “አይ መሬት ያለ ሰው!” ብሏል አሉ የሚጋልበው ፈረስ የደነበረበት አንድ ሰው – “እንዲህ አድርገው፤ እንዲህ ያዘው” ባሉት ጊዜና፡፡ አሁንም እርግጥ ነው – ለተቀማጭ ሰማይ ቅርብ ነው፡፡ እርግጥ ነው – አታሞ በሰው እጅ ስታምር በገዛ እጅግ ግን ልታደናግር ትችላለች፡፡ ቢሆንም የሚሰማኝን ብናገር ቢያንስ ዴሞክራሲያዊ መብቴን “ባልተሸራረፈ” መልኩ እንደተጠቀምኩበት ከመረዳቴም በተጨማሪ የተወሰነ እፎይታን አገኛለሁ፡፡ ለማንኛውም ወደአንዱአለም የመጨረሻ የችግሮቻችን መፍትሔ እናምራና ለአፍታ እንመልከትለት፤
ትልቁ ጥያቄ ኢሕአዴግ የብሔራዊ ዕርቁን ጥያቄ አሁንም “የባልና የሚስት ፀብ አይደለም” ብሎ ቢያጣጥለው ምን ማድረግ ይቻላል? የሚለው ነው፡፡ በእኔ እምነት ኢሕአዴግ ከዚህ በኋላም (እስካሁን) ለ21 ዓመታት የዳከረበትን መንገድ የሚመርጥ ከሆነ ተቃዋሚዎች ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ሆነው የሚጓዙ(በ)ት የራሳቸው አዲስ መንገድ መፈጠሩ አይቀሬ ይመስለኛል፡፡ ኢትዮጵያን በአስተማማኝ መሠረት ላይ ለመገንባት (የ)ሚያስችለውን የብሔራዊ ዕርቅ መንገድ በመጓዝ ለፍትሃዊ ነፃና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ መንገድ መጥረግ የማይፈልግ ኃይል በኢትዮጵያ ሕዝብ ሰቆቃ ላይ የራሱን ግላዊ ወይም ቡድናዊ ጥቅም ብቻ የሚያስቀድም መሆኑን ያመለክታል፡፡ ኢሕአዴግም ይሄን መንገድ እስከመረጠ ድረስ የኢትዮጵያን ሕዝብ በኃይል ረግጦ የመግዛት ፍላጎቱን አሁንም ለመቀጠል እንደሚፈልግ ያሳያል፡፡ የማንወጣው መንገድ ቢሆንም ከተገደድን ግን ኢትዮጵያውያን በፀና ሰላማዊ ትግል ኢሕአዲግን ልኩን እንዲያውቅ ብሎም ለኢትዮጵያ ሕዝብ ፈቃድ እንዲገዛ ማድረግ አማራጭ የለውም፡፡ … (መስመር የተጨመረ)
ወያኔ ልኩን የሚያውቀው በሰላማዊ ትግል ነውን? ይህ ነገር እውነት ይሆን? ይህች ነገር አጭር የክበበው ገዳን ቀልድ ትመስለኛለች፡፡
በመሠረቱ ጥሩ መመኘት በራሱ መጥፎ አይደለም፡፡ ነገር ግን የምኞትን ገደብ ማወቅ ተገቢ ነው፡፡ አንዱአለም ከዕድሜ አንጻርም ይሁን ከገጠመኝ ማጠጥ/ማጠር የተነሣ በኢትዮጵያ ምድር አይመኙትን ምኞት በመመኘት እርሱን መሳይ የዋሃንን በተስፋ ዳቦ ለመቀብተትና በከንቱ ለማስገሳት ሲጥር እንመለከታለን፡፡ እዚህም ላይ ወያኔን አለማወቁ ያሳዝነኛል፡፡ ማንበብ ጥሩ ነው፤ ማወቅና መመራመርም ጥሩ ነው፡፡ ተስፈኝነት መልካም ነው፡፡ ተስፋ አለመቁረጥና ሩቅ ማሰብም ደግ ነው፡፡ ይሁንና ጓዳችን ውስጥ እንደመዥገር ተለጥፎ በመርዘኛ ጥርስና ምላሱ እያንገበገበን የሚገኘውን ወያኔ በሰላማዊ ትግል ይወገዳል ብሎ ማሰብና መስበክ አንድም ባለማወቅም ቢሆን የወያኔን ዓላማ የማራመድ ያህል ነው አለዚያም ሞኝነት ነው፡፡ ቢሆን በወደድን፡፡ ግን ፈጽሞ አይሆንም – ተምኔታዊነት (ዩቶፒያን መሆን) ነው፡፡ ኔልሰን ማንዴላ ለኢትዮጵያ አብነት ሊሆን አይችልም፤ ማኅተመ ጋንዲ ለኢትዮጵያ አብነት ሊሆን አይችልም፡፡ እነዚህ ምርጥ የዓለማችን ዜጎች የታገሉት ከሰዎች ጋር ነው፡፡ የኛን የሚለየው ትግላችን ከድፍን ቅል ዘረኞችና መቼም በማይበርድ እንዲያዉም እየሰላ በሚሄድ የጥላቻና የቂም በቀል አባዜ ከተሞሉ የባንዳ ልጆች ጋር ነው፡፡ ምናልባት አንዱአለም ያልተገነዘበው ይህንን ሃቅ ሊሆን ይችላል ብዬ እገምታለሁ፡፡ በዚያ ላይ በሰላማዊ ትግል ቀርቶ በመሣሪያም የሚነቀንቃቸው እንዳይኖር ሕዝቡን በማይምነት ጋርደው፣ ፍጹም ከደረጃ በታች በሆነና “A,B,C,D”ን በቅጡ በማያስለይ እንዲሁም ዜጎችን በሚከፋፍል የትምህርት ሥርዓት ትውልድን አደድበው፣ ጥቂት የማይባሉ ኢትዮጵያውያንን በማይረባ የጥቅም ፍርፋሪ ከፋፍለው፣ በዘረኛ የፌዴራል ፖሊስ፣ በደንቆሮ ካድሬና መከላከያ አፍነው፣ በቅንድብ ጥቅሻና በስልክ ቀጭን ትዕዛዝ ወንበዴዎቹ የሚፈልጉትን ፍርድ በሚያስተላልፍ ኮንዶም ዳኞችና ፍርድ ቤቶች ሀገር ምድሩን ሞልተውት፣ ዜጎችን በጎጠኛ የፀጥታና ደኅንነት መዋቅር ቀፍድደው፣ በድህነት ኮድኩደው፣ በተለይ ወጣቱን በልዩ ልዩ ሱሶችና በወሲብ የአዶከብሬ ዛር ዳንኪራ አስረግጠው፣ በመርዘኛ የጎሰኝነትና የዘረኝነት በሽታ ሕዝበ አዳምን በክለው፣ … ከጠማማ ጎጆው ባለፈ – የሰኞን ነፍሱን ወደማክሰኞ በማሳደሩ ከመደሰት በዘለለ ለሀገርና ለወገን የሚቆረቆር ዜጋ እንዳይኖር አድርገው የሀገሪቱን ኅልውና ገደል ጫፍ ላይ ጥለውታል፡፡ ይህን ኃይል በሰላማዊ መንገድ እጥላለሁ ብሎ ማሰብ ዕብደት ነው የምለውም ለዚህ ነው፡፡ የደቡብ አፍሪካው አፓርታይድ ሥርዓት የመጨረሻ ፕሬዝደንት ኤፍ ደብልይው ደክለርክ ጭንቅላቱ ውስጥ ተሸክሞት ይዞር የነበረው ሊማር የሚችል ጤናማ ነጭ አንጎል እንጂ እንደወያኔ በድንቁርና የታጀለ ከመግደልና በሰው ስቃይ ከመደሰት ውጪ ምንም የማያውቅ የገማና የበሸቀጠ ጥቁር ጭቃ አልነበረም፡፡ ወያኔን በሰላማዊ መንገድ እታገላለሁ ማለት ለወያኔ አዲስና ለራሳቸው ለአባላቱም ቢሆን ግርታን የሚፈጥር ልዩ ተፈጥሮን እንደማላበስ ይቆጠራል፡፡…
አፄ ኃ/ሥላሴ ለጉብኝት ይሁን ለሥራ ወዳንድ ቦታ ሲሄዱ አንዲት ችግረኛ ሴት ከነልጆቿ መንገድ ዳር ቆማ “ወድቃ በተነሳችው ባንዲራችን፣ በልዑል እግዚአብሔር ይሁንብዎ…” በማለት ባንዴራ ዘርግታ ታስቆማቸዋለች፡፡ ያኔ እንደዛሬው ዘመን መሪ ሲወጣና ሲገባ ግድግዳ እያስደገፉ (የሚገርም እኮ ነው!) ለገዢዎች የኅለውና መሠረት ከመሆናቸው አንጻር ውድና ብርቅ ሊሆኑ የሚገባቸውን ዜጎች በኢሰብአዊነት ማሰቃየት አልነበረምና ጃንሆይ መኪናቸውን አስቁመው በመውረድ “ችግርሽ ምንድነው?” ብለው ይጠይቋታል፡፡ ሴትዮዋም፣ “ጃንሆይ፣ ለምግብ ያላነሱ ለሥራ ያልደረሱ ስድስት ልጆችን ጥሎብኝ ባለቤቴ ሞተ…” ብላ ችግሯን መናገር ስትጀምር በቀልደኛነት የሚታወቁት የቀድሞው ንጉሣችን አጠገባቸው አጅበዋቸው ወደቆሙ መኳንንት ዘወር ብለው “አግባኝ ነው የምትለው?” ብለው እንደዋዛ ጣል ያደረጓት ቀልድ በሴትዮዋ ጆሮ ገብታ ኖሮ ድሃ መቼም ሞኝ ነውና “ጃንሆይ! ሆኖልኝ ነው! አ’ርጎት ነው!” አለች ይባላል፡፡ ቀልድ በአግባቡ ጥሩ ነው፡፡ ኃ/ሥላሴ ሴትዮዋን እንደማያገቧት ግልጽ ነው – ሴትዮዋ ግን ድሃና በዕውቀትም ዝቅተኛ ናትና በጣለችው ተስፋ አንፈርድባትም፡፡ ከወያኔ ጉያ ሕዝባዊ ሥልጣን በሰላማዊ መንገድ ይገኛል ተብሎ ተስፋ ማድረግ ግን ከሴትዮዋ የበለጠ ጅል መሆንን የሚያመለክት እንጂ የወያኔን ተፈጥሮ ከመገንዘብ የሚመነጭ ገምቢ ዕውቀትና ጥበብ አይመስለኝም፡፡ ይህን የሚመር ቀልድ የሚቀልዱ ሰዎች ራሳቸውን ቢመረምሩ የተሻለ ነው፡፡ ሰላማዊ ትግል ደግሞም በኢትዮጵያ – ሆ!
በጦርነት የሚገኝ ነገር መልካም ነው እያልኩ እንዳልሆነ ግን ይመዝገብልኝ፡፡ ምርጫ ከጠፋ ግና ምን ይደረጋል? ከሁለት መጥፎዎች የተሻለውን መምረጥ የምንገደድበት ጊዜ ይኖራል፡፡ እናም ሰው ካልሆነ አውሬ ጋር እየታገሉ ከማለቅ ቢያንስ የራሴ ነው ከሚሉት ጨካኝና አምባገነን መሪ ጋር መፋለም ይመረጣል – ለዚያም መብቃት እኮ መታደል ነው፡፡ እንደሚመስለኝ አሁን ሰዎችን እያሳሰባቸው ያለው የማያሳስብ ነገር ነው፡፡ ቀድሞ የመቀመጫየን ያለችው ፍጡር ወድዳ እንዳልሆነ መረዳት ተገቢ ነው፡፡ “ሌላውን እሾህ በመቀመጫየ ተቀምጬ ራሴው እነቅለዋለሁ” ማለቷ ነው፡፡ እና ያልበላንን የሚያኩልን ወገኖች አደብ ቢገዙልን ብዙ እንደረዱን ይቆጠራል፡፡ ለነገሩ ወያኔን ማንም ደገፈው ማን – በማወቅም ይሁን ባለማወቅ – ወቅቱን ጠብቆ ወረደ መቃብሩን ሳይወድ በግዱ መቀበሉ አይቀርም፡፡ አንድዬ በመንበሩ ካለ – አለም- ይህን ሁሉ ግፍና በደል የፈጸሙ ሰው መሳይ “ሰዎች” የቁናቸውን ሳይከፈሉ ይቀራሉ ብሎ ማሰብ የታሪክንና የፈጣሪን ፍርድ አለመረዳት ነው፡፡ የሞተ ይነሳል፤ የተኛ ይነቃል፤ የቆመ ይቀመጣል፤ የተጋደመ ይቆማል፡፡ ለሁሉም ጊዜ እንዳለው ዛሬ አይደለም የምናውቀው፡፡ ታሪክና እግዜሩ ወያኔ ላይ ሲደርሱ ሥራቸውን ያቆሙ ይሆን? ለጅላጅሎቹ ወያኔዎች እንዲያ ሳይመስላቸው የሚቀር አይመስለኝም፡፡ ለኔ ግን በፍጹም! ጊዜው ቀርቧል፡፡
አገባቤና አወጣጤ የተምታታ ነገር ያለበት መሆኑ ይሰማኛል፡፡ ለዚህ የተምታታ ነገሬ ማንን ይቅርታ መጠየቅ እንዳለብኝ ግን አላውቅም፡፡ የሆኖ ሆኖ የዚህ ዘመን እውነት ባብዛኛው የተዘበራረቀ በመሆኑ አላግባብ ሊፈርድብኝ የሚቃጣ እንደማይኖር እገምታለሁ፡፡ ሁሉን ቢናገሩት ሆድ ባዶ ይቀራልና ወደማይቀረው ድል እየተጠጋን ስንመጣ እንጫወታለን፡፡ ማርቲን ሉተር ባይቀድመኝ እኔም “ህልም አለኝ!” ብል በወደድኩ፡፡
“ቀኒቷን ማንም አያውቅም፡፡ ከጥቂቶች በስተቀር ብዙኃኑ ጎጋም እንኳን የምፅዓትን የመጨረሻ ቀን አያውቃትም፡፡ እናንተ የሚገባችሁ ታጥባችሁ ታጥናችሁ መጠበቅ ነው – ከሙስናና ከዕድፍ ርቃችሁ፤ ከዘረኝነት አረንቋና ከሆዳምነት ተቆጥባችሁ፤ አስተዋይነትን ተላብሳችሁ፣ በወረተኛ ወጀባዊ ንፋስ እንዳትወሰዱ ተጠንቅቃችሁ … ፡፡ ይሁንና ምልክቶቹን ስታዩ የቀኒቷን መቅረብ ትረዳላችሁ፡፡ ምልክቶቹን ያዬ ትውልድ ከምፅዓት በፊት የምትገለጠዋን የኢትዮጵያን ትንሣኤ ቀን ያያታል፡፡ …” (‹መጽሐፈ ትንሣኤ ኢትዮጵያ› ፣ ምዕራፍና ቁጥር የማይነበብ!)
– See more at: http://www.freeandualemaragie.org/?p=456#sthash.z9etgaIL.dpuf
የአዲስ ጉዳይ መፅሔት ጋዜጠኞች ተሰደዱ
በመንግስት በደረሰባቸው ጫና እና ክስ ምክንያት የ”አዲስ ጉዳይ” መፅሔት ማኔጂንግ ዳይሬክተር እንዳልካቸው ተስፋዬ፣ ምክትል ዋና አዘጋጅ ኢብራሂም ሻፊ፣ ከፍተኛ አዘጋጅ እንዳለ ተሺ እና አዘጋጅ እና የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች መድረክ (ኢጋመ) ገንዘብ ያዥ ሀብታሙ ስዩም ሀገር ጥለው ተሰደዱ፡፡ ጋዜጠኞቹ የተሰደዱት፤ የፍትህ ሚኒስቴር አቃቤ ህግ በኢቴቪ አዲስ ጉዳይ መፅሔትን ጨምሮ 5 መፅሔቶች እና አንድ ጋዜጣ ላይ ክስ መመስረቱ ይፋ መደረጉን ተከትሎ ቢሆንም፤ ቀደም ሲል በመንግስት ደህንነትና ፀጥታ ኃይሎች ተደጋጋሚ ጫና ይደርስባቸው እንደነበርም ተጠቁሟል፡፡
ከአዲስ ጉዳይ መፅሔት ከፍተኛ አዘጋጅ አስማማው ኃይለጊዮርጊስ እና የፎቶ ጋዜጠኛ አዚዛ መሐመድ በቅርቡ መታሰራቸውና ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡ የተሰደዱ ጋዜጠኞች ቁጥርም እየጨመረ ሲሆን፤ በቅርቡ የኢትዮጵ ጋዜጠኞች መድረክ ፕሬዘዳነት ጋዜጠኛ በትረ ያዕቆብ እና የህዝብ ግንኙነቱ ዘሪሁን ሙሉጌታን ጨምሮ እስካሁን የተሰደዱ ጋዜጠኞች ቁጥር ከ15 በላይ መሆኑን መረጃዎች አመልክተዋል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ሌሎችም ጋዜጠኞች ከፍተኛ ጫና ላይ መሆናቸው ታውቋል፡፡
ማሰርና ማሳደድ መፍትሄ ይሆናል?
ብስራት ወልደሚካኤል
afrosonb@gmail.com
በቀድሞ ታጣቂዎች እንደ ጭራቅና አውሬ ይሳል የነበረው የደርግ ስርዓት ወድቆ ስልጣን በአማፂዓን እጅ ከገባ 23 ዓመታት አልፈዋል፡፡ ነገር ግን የታሰበው ለውጥ ዛሬም ቢሆን መናፈቁን አልተወም፡፡ ምክኔቱም ያኔ ማሰር ነበር፤ ዛሬም ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ ያኔም መወንጀልና መፈረጅ ነበር ዛሬ ግን ተባብሷል፡፡ ለእኔ ከድሮ የተለየ ተቀይሮ ያገኘሁት በዋናነት የመሪዎች ስምና ልብሳቸው እንጂ ስራቸው ያው ነው፡፡
በዘመነ ደርግ ጠባብነትና ዘረኝነትን እንዲሁም ኢትዮጵያ ላይ ጥላቻ ያላቸውን በሙሉ ስልጣኑን ሊቀናቀኑ ካሰቡት እኩል በጠላትነት ይፈረጃሉ፡፡ በዘመነ ኢህአዴግ ደግሞ ኢትዮጵያዊነትን ማስቀደምና ለኢትዮጵያውያን በእኩል ዓይን መቆምና መቆርቆር እንደ ወንጀል ይታያል፡፡ሁለቱም ወደ ስልጣን ሲወጡ በጠብመንጃ ሲሆን፤ ስልጣናቸውንም ያስጠበቁትን የሚያስጠብቁት እንዲ በጦር መሳሪያ ነው፡፡ምን አለፋችሁ፤ ልዩነቱን “…ጃሃ ያስተሰርያል” የሚለው የአርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን (የቴዲ አፍሮ) ሙዚቃ በደንብ ይገልፀዋል፡፡
በሁለቱ መካከል ያለው መሰረታዊ ልዩነት ደርግ የማይፈልገውን ነገር በግልፅ በአዋጅ ይደነግጋል፤ከአዋጅ ወይም ህግ ውጭ ይቀጣል፡፡ ኢህአዴግ ደግሞ የሚፈልገውንም ሆነ የማይፈልገውን በህገ መንግስት እውቅና ሰጥቶ የማይፈልገውን በሌላ አዋጅ ይቀጣል፣ያስራል፡፡ ልዩነታቸው የመሪዎች ስም፣ የለበሱት ልብስና አካሄዳቸው እንጂ መሰረታዊ የልዩነት ባህርይ አይታይባቸውም፡፡ ለዚህም አሁን በስልጣን ላይ ያለው ኢህአዴግ ከደርግ በባሰ ያከናወናቸውን እና እያከናወናቸው ካሉት አሉታዊ ተግባራት መካከል በዋናነት የእስር ዘመቻውን ማንሳቱ በቂ ነው፡፡
በተለይ በምርጫ 1997 ዓ.ም. ኢህአዴግ በአደባባይ መሸነፉን እና የህዝብን ድምፅ መቀማቱን የሚያሳብ በርካታ ተግባራትን ሲያከናውን ዋናው ገመናውን የሚያጋልጡና በአብዛኛው ህዝብ ዘንድ ተቀባይነትና ተወዳጅነት ያላቸውን በሰበብ አስባቡ አስሮ ማሰቃየትን እንደ ትልቅ አማራጭ መጠቀም ጀመረ፡፡ ለዚህ በምርጫው ያሸነፉት የቀድሞ ቅንጅት አመራሮችን ከወነጀለበት በኢትዮጵያ 2000 ዓ.ም. ዋዜማ ከእስር ከፈታ በኋላ አዲሱ ቀዳሚ እስረኛ አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ነበር፤ የእስርዓ ምዕት ኢትዮጵያ ጅማሮ እስረኛ፡፡ ይህም አዲስ አበባና አስመራን ጨምሮበመላው ዓለም ጥያቄና ተቃውሞ ከማስነሳቱ በተጨማሪ ከእስር ሲፈታም የህዝብ ድጋፍ በመላው ዓለም ተጠናክሮ እስከዛሬም ድረስ ዘልቋል፡፡
ከዚህ በኋላ የኢህአዴግ ጥላቻ እየተባባሰ፣ ለስልጣን ያለው ጥማት ሰርክ እንደ አዲስ ወይን እየጣመው ይሄድ ጀመር፡፡ ከስልጣናቸው በዕድሜ ይፍታህ የተሰናበቱት ሟቹ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ በስልጣናቸው እስከ መቃብር አፋፍ ዋስትና ይሆናል ያሏቸውን አፋኝ ህጎች ፀድቀው ተግባር ላይ እንዲውሉ ቀን ከሌት ኳተኑ፡፡ በዚህም የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኀበራት አዋጅ፣ የፕሬስ አዋጅ፣ የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅ፣…ይገኙበታል፡፡
በተለይ በተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶች እና የነፃ ጋዜጠኞች ከፍተኛ ተቃውሞ የገጠመው የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅ ሰኔ 30 ቀን 2001 ዓ.ም. ፀድቆ ለምርጫ 2002 ዓ.ም. ማፈኛ ተዘጋጀ፡፡ የዚህም ገፈት የዴሞክራሲ እንቅስቃሴዎችን ገድቦ የነበረውን ተስፋ መቀመቅ ውስጥ ከተተው፡፡ ከዚህ በኋላ በየካቲት 2003 ዓ.ም. በቱኒዚያ መሐመድ ቡዓዚዝ የተጀመረው የአረቡ ፀደይ አብዮት በሰሜን አፍሪካን እና መካከለኛ ምስራቅ አረብ ሀገሮች መቀጣጠሉን የተመለከቱት አቶ መለስና ተከታዮቻቸውና አጋሮቻቸው በኢትዮጵያም ይከሰታል በሚል የአስር አደኑንን አጣደፉት፡፡
የአረቡን አብዮት ተከትሎ በኢትዮጵያ የእስር ሰንሰለቱን የጀመሩት እንደ ታሰበው ጋዜጠኞች እና የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ናቸው፡፡ በቀዳሚነትም በወርሃ ሰኔ 12 ቀን 2004 ዓ.ም. ከፖለቲከኛ አቶ ዘሪሁን ገ/እግዚአብሔር፣ ሰኔ 14 ቀን 2003 ዓ.ም. ደግሞ ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ፣ ርዕዮት አለሙ፤ ከዚያም በክረምት 2003 ዓ.ም. የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህርና የኦፌኮ/መድረክ አመራር አቶ በቀለ ገርባና አቶ ኦልባና ሌሊሳ የእስር ሰለባ ሆኑ፡፡
ሌላው ከኢትዮጵያውያን በተጨማሪ ሁለት ሲውድናውያን ጋዜጠኞች ማርቲን ሸብይ እና ጆሃን ፐርሰን ሽብርተኝነትን ደግፈዋል በሚል በዚሁ የፀረ-ሽብርተኝነት ሰለባ በመሆን ከ14 ወራት የሰቆቃ እስር በኋላ በዓለም አቀፉ ማኀበረሰብ ጫና መስከረም 1 ቀን 2004 ዓ.ም.ተለቀዋል፡፡ በመቀጠል መስከረም 3 ቀን 2004 ዓ.ም. ደግሞ ታዋቂው የፖለቲካ ተንታኝ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፣በብዙ ወጣቶች ዘንድ በቅንነቱና ፍቅርን በመስጠት እንዲሁም ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልን አጥብቆ በመደገፍ የሚከራከረው የአንድነት/መድረክ አመራር አቶ አንዱዓለም አራጌ እና ሌሎች የአንድነት ፓርቲ አመራሮች አቶ ናትናኤል መኮንን፣አቶ ዮሐንስ ተረፈና ሻምበል የሺዋስ ይሁንዓለምንና አቶ አንዱዓለም አያሌውን ጨምሮ አቶ ክንፈ ሚካኤል ደበበና ሌሎች ሰዎችም በሽብርተኝነት ስም ወደ ወህኒ ወረዱ፡፡ በዚህም አፍቃሬ መንበር አቶ መለስ የፈሩትን የአረቡን አብዮት በዚህ ያለፉ ይመስል ጀብደኝነት ተሰምቷቸው፤ ተጠርጣሪዎቹ ገና በፍርድ ቤት ብይን ሳይሰጥባቸው አሸባሪዎች ናቸው ሲሉ ለተወካዮቻቸው አረጋገጡ፡፡
ያሰሯቸው ላይ ቀድመው ወንጀለኛ በማለት ፍርድ በመስጠት መከራን የደገሱት አቶ መለስ ባልጠበቁት ሁኔታ በጠና ታመው በአውሮፓ ቤልጄየም ብራሰልስ አንድ የዩኒቨርስቲ ሪፈራል ሆስፒታል ተኙ፡፡ በመጨረሻም እንደ ሆስፒታሉ ምንጮች ከሆነ ሐምሌ 13 ቀን 2004 ዓ.ም. እንደወጡ ላይለመሱ ብዙ ለመኖር ያሰቡበትን በ21 ዓመታት የስልጣን ዘመናቸው እንደ ግል ርስታቸው ያስቡት የነበረውን ቤተመንግስት ጥለው እስከወዲያኛው ተሰናበቱ፡፡
ይሁን እንጂ አጋሮቻቸውና የቅርብ የኢህአዴግ አመራሮች መታመማቸውን እንኳ ለህዝብ ሳይገልፁ በድንገት የሞቱትን ሰውዬ ከጋዜጠኞች ጥያቄ ቢበረታባቸው በቅርቡ ተመልሰው ስራ ይጀምራሉ የሚል መልስ ሰጡ፡፡ በኋላም የተባለው ሳይሆን ፈጣሪ የወሰነው ሞት እርግጥ መሆኑ እና ነሐሴ 14 ቀን 2004 ዓ.ም. ሌሊት እንዳረፉ ተደርጎ ነሐሴ 15 ቀን 2004 ዓ.ም. ማለዳ አንድ ለእናቱ በሆነው ሀገሪቱ ቴሌቪዥን ኢቴቭ ይፋ ተደረገ፡፡ ከዚያም ነሐሴ 27 ቀን 2004 ዓ.ም. ግብዓተ መሬታቸው እንደ ተከናወነ በግብረ-አበሮቻቸውና በመንግስት ሹማምንት ከተገለፀ በኋላ “…የመለስን ራዕይ እናስቀጥላለን!” የሚል መፈክር መሰማት ጀመረ፤የተባለው ራዕይ ኑዛዜ አሁንም ባያበቃም፡፡
በርግጥ አቶ መለስ ራዕይ ነበራቸው ከተባለ፤ እስከ ህልፈታቸው ድረስ የትኛውንም መንገድ ተጠቅመው ከቤተመንግስት ሳይወጡ ተቀናቃኞቻቸውን በማሰርና በማጥፋት በስልጣን መቆየት ነው፡፡ ነበራቸው የተባለው ራዕይ አሳቸው ሲሞቱ አብሮ ሞቷል፡፡ ይህ ደግሞ ራዕይ ሳይሆን የስልጣን ጥም እንጂ ህዝባዊና ሀገራዊ አይደለም፡፡ ተከታዮቻቸውም እናስቀጥላለን ያሉት ይህንኑ በመሆኑ ልክ እንደሳቸው ተመሳሳይ ድርጊት መፈፀሙትን እንደ ትክክለኛ እና ቅዱስ ተግባር ማከናወን ጀመሩ፡፡ ለአብነትም መጪውን ምርጫ 2007 ዓ.ም. ተከትሎ ለኢህአዴግና አመራሮቹ ስልጣን ማክተሚያ ምክንያት ይሆናሉ ብለው ያሰቧቸውን ማጥመድ፣ ማሰርና መፈረጁን ተያያዙት፡፡ የዚህ ሰለባ ከሆኑት መካከል በሚያዝያ 2006 ዓ.ም. መጨረሻ አካባቢ ጋዜጠኛ አስማማው ኃይለጊዮርጊስ፣ ጋዜጠኛ ተስፋዓለም ወልደየስ፣ ጋዜጠኛ ኤዶም ካሳዬና ጋዜጠኛ አዚዛ መሐመድ፤ እንዲሁም የኢትዮጵያው ዞን 9 ብሎገሮች በፈቃዱ ኃይሉ፣ዘለዓለም ክብረት፣ አቤል ዋበላ፣ ማህሌት ፋንታሁን፣አጥናፍ ብርሃኔ እና ናትናኤል ፈለቀ ቀዳሚዎቹ ናቸው፡፡
በ2004ዓ.ም. ዛሬም ድረስ ምላሽ እንዳላገኘ የሚነገርለት የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ጥያቄ ጋር በተያያዘ የሙስሊሙ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት፣ጋዜጠኛ ዩሱፍ ጌታቸውና ጋዜጠኛ ሰለሞን ከበደ ታስረው እስካሁን በወህኒ ቤት ይገኛሉ፡፡ ምንም እንኳ ጉዳያቸው በፍርድ ቤት የተያዘ ቢሆንም እስካሁን ብይንም ሆነ እልባት አላገኘም፡፡ ይሄ ሁሉ በአቶ መለስ አገዛዝ ዘመን የተጀመረ እስር ነው፡፡
በመቀጠልም በሀገር ውስጥ የኢህአዴግ መንግስት እውቅና ያልተቸረውና በሽብርተኝነት የተፈረጀው የግንቦት 7 የፖለቲካ ማኀበር ዋና ፀሐፊ የነበሩት አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ በየመን ፀጥታ ኃይሎች ታግተው ለኢትዮጵያው ገዥ ተላልፈው ተሰጥተዋል፡፡ አቶ አንዳርጋቸው ቀደም ሲል የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ አድርጋችኋል በሚል በነ ጄነራል ተፈራ ማሞ ክስ መዝገብ ከነ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ጋር በሌሉበት የሞት ፍርድ ተፈርዶባቸውል፡፡ የሞት ፍርድ ተፍርዶባቸው የነበሩት አቶ አንዳርጋቸው እንደገና በ2005 ዓ.ም. ደግሞ በነ አንዱኣለም አራጌና ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ክስ በሌሉበት የዕድሜ ልክ ፅኑ እስራት ተፈርዶባቸዋል፡፡ ይሁን አንጂ ወደፊት ትናው ክስ ተፈፃሚ እንደሚሆንና በቀጣይ ስለሚኖረው የፍርድ ሂደት ዕድሜ ከሰጠን አብረን የምናየው ነው ሚሆነው፡፡
ከላይ የተጠቀሰው እንዳለ እስሩ ተጠናክሮ በመቀጠል በሀገር ውስጥ በገዥው ስርዓት ህጋዊ እውቅና ተችሯቸው የሚንቀሳቀሱየፖለቲካ ፓርቲ ወጣት አመራሮች ተለቅመው ታሰሩ፡፡ እነኚህም መካከል በማኀበራዊ ሚዲያ የተለያዩ በሳል ፅሑፎችን በመፃፍ የሚታወቀው፣ የመቀሌ ዩኒቨርስቲ መምህርና የዓረና ትግራይ/መድረክ አመራር አቶ አብርሃ ደስታ፤ ከአንድነት ፓርቲ አመራሮች አቶ ሀብታሙ አያሌውና አቶ ዳንኤል ሺበሺ እንዲሁም ከሰማያዊ ፓርቲ አቶ የሺዋስ አሰፋ ይገኙበታል፡፡አራቱም ወጣት ፖለቲከኞች በፓርቲያቸውም ይሁን በሀገሪቱ ሰለማዊ የፖለቲካ ትግል በጎ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች መሆናቸው ይነገርላቸዋል፡፡
ሌላው እየተወሰደ ያለውን እስር በመሸሽ ከምርጫ 1997 ዓ.ም. ወዲህ ከ2005 ዓ.ም.ጀምሮ እስከ ያዝነው 2006 ዓ.ም. ድረስ ኢትዮጵያውያን ጋዜጠኞች ተሰደዋል፡፡ ለዚህም በዋነኝነት እንደ አስረጂ ሊጠቀስ የሚችለው በአሁን ሰዓት በጅምላ እየተፈፀመ ያለው እስር ነው፡፡ በአቶ መለስ ዜናዊ የስልጣን ዘመን የተጀመረው የጋዜጠኞችና ብሎገሮች እስር በአሁን ወቅት ሶስት የውጭ ዜጎችን ጨምሮ 20 የደረሰ ሲሆን፤ ከላይ በስም ከተጠቀሱት የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች በተጨማሪ በርካታ የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ ማኀበር አባላትም በእስር ላይ ይገኛሉ፡፡ ይሄ ደግሞ ዴሞክራሲያዊ መብቶች ዝግ ከነበሩበት የደርግ ጊዜ ጋር ሲነፃፀር፤ በኢህአዴግ ጊዜ 20 ጋዜጠኞችና ብሎገሮችን በማሰር በሀገሪቱ ታሪክ ቀዳሚውን አሉታዊ ስፍራ እንድይዝ ያደርገዋል፡፡ በዚህም በፀታ ኃይሉና በፍትህ ተቋማቱ ላይ ተጨማሪ የስራ ጫና ከመፍጠር በዘለለ የታሰበውን የፖለቲካ ትርፍ ያስገኛል ተብሎ አይጠበቅም፡፡
እንደ ገዥው ስርዓት አመራሮች፣ ደጋፊዎችና የፀጥታ ኃይሎች ገለፃ ከሆነ እስሩ የሚቆም አይደለም፡፡ በቀጣይ የዚህ ሰለባ ማን እንደሚሆን ባይታወቅም፤ እንደተባለው የሚተገበር ከሆነ በድጋሚ ቀሪ ጋዜጠኞች እና ፖለቲካኖች የእስር ስለባው ሊሆኑ እንደሚችሉ አያጠያይቅም፡፡ ምክንያቱም ከሌላው በተሻለ መብቶቻቸውን እየተገበሩና እየተጠቀሙ ማኀበረሰቡ ላይ በጎ ተፅዕኖ በመፍጠር የስርዓቱ ስልጣን ፈተና ይተረጎማሉና፡፡ አቶ መለስ ከመሞታቸው በፊት ምርጫ ሲደርስና ለስልጣናቸው የሚያሰጋቸው ነገር ብልጭ ሲልባቸው የሚወስዷቸው ርምጃዎች አሁን በስልጣን ላይ ባሉ ተከታዮቻቸው ተጠናክረው መቀጠላቸው አንዱ የመለስ ራዕይ ነው ሊያስብል ይችላል፡፡ ይህም አመራሮቹ እናስቀጥለዋለን ያሉት የአቶ መለስ ራዕይ አንዱ አካል ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ ምክንያቱም ያኔ በሳቸው ዘመን የተጀመረው ዛሬም በቃ ሊባልና መቋጫ ሊበጅለት አልቻለምና፡፡
አሁን በመንግስት አመራሮች ኢትዮጵያውያን ጋዜጠኞች፣ ብሎገሮችና ፖለቲካኞች ላይ ትኩረት ያደረገ የእስር ዘመቻ ከዚህ በፊት እንደ ተወዳጅ ነጠላ ዜማ ሲዜም የነበረውን “የመለስን ራዕይ እናስቀጥላለን” አባባል የሚታየው የእስር ዘመቻ መሆኑን በማሳበቅ በደጋፊዎቻቸው እንደ ሊቀ ሊቃውንትና ባለራዕይ የተወሰዱት ሟቹ ሰውዬ እንዲኮነኑ ማድረጉ አይቀርም፡፡ በየትኛውም ዓለም እንደሚታየው የፖለቲካ ርምጃና ተሞክሮ ሰዎችን ያውም ዜጎችን አሸባሪ ብሎ ማሰር በስልጣን ለመቆየትም ሆነ ለመረጋጋት መፍትሄ ሊሆን አይችልም፡፡ እንዲህ ዓይነት ርምጅ መፍትሔ ቢሆን ኖሮ የሊቢያው መሪ ኮሎኔል ሙዓመር ጋዳፊ፣ የግብፁ ሆስኒ ሙባረክ፣የየመኑ ዓሊ አብደላ ሳላህ በስልጣን ላይ መቆየት በቻሉ ነበር፤ግን አልሆነም፡፡
ነገርን ግን የህዝቡን ቁጣ በመቀስቀስ በውርደት ከስልጣን እንዲወርዱ አስገደዳቸው እንጂ መፍትሄ አልሆናቸውም፡፡ ስለዚህ በስልጣን ለመቆየት ጉጉቱ ካለ እንኳ የዜጎችን መብት፣ፍላጎትና ጥቅም ማክበርና ማስጠበቅ የተሻለ አማራጭ ነው፡፡ መፍትሔውን ልክ እንደ ጥሎ ማለፍና ፍፃሜ የአትሌቲክስ ውድድር ዜጎችን በማሰርና እንዲሰደዱ በማድረግ ዙሩን ማክረር ታምቆ የቆየውን የህዝብን ስሜት ባልተጠበቀ ሰዓት እንዲፈነዳ በማድረግ ሌላ ችግር ሊወልድ ይችላል፡፡የሚፈራው ችግር የሚከሰት ከሆነ ደግሞ የበለጠ ለገዥዎችም፣ ለህቡም ሆነ ለሀገሪቱ አሉታዊ ተፅዕኖ ማስከተሉ እሙን ነው፡፡
የፌደራሉ ከፍተኛው ፍርድ ቤት በጋዜጠኞችና ብሎገሮች ጉዳይ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጠ
የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት ዛሬ ሐምሌ 28 ቀን 2006 ዓ.ም. በዋለው ችሎት የፌደራሉ አቃቤ ህግ በሽብርተኝነት በሶሊያና ሽመልስ የክስ መዝገብ ክስ የመሰረተባቸው ዘጠኝ ጋዜጠኞችና የኢትዮጵያ ዞን 9 ብሎገሮች ለነሐሴ 14 ቀን 2006 ዓ.ም. ከጠዋቱ 3 ሰዓት ተለዋጭ ቀነ ቀጠሮ ሰጠ፡፡ ጋዜጠኛ አስማማው ኃይለጊዮርጊስ፣ ተስፋዓለም ወልደየስ እና ኤዶም ካሳዬ እንዲሁም የኢትዮጵያ ዞን 9 ድህረ-ገፅ ብሎገሮች በፈቃዱ ኃይሉ፣ ዘለዓለም ክብረት፣ማህሌት ፋንታሁን፣ አጥናፍ ብርሃኔ፣ አቤል ዋበላ እና ናትናኤል ፈለቀ በአካል ፍርድ ቤት የቀረቡ ሲሆን፤ 1ኛ ተከሳሽ ሶሊያና ሽመልስ በአካል ልትቀርብ ስላልቻለች በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋዜጣ ጥሪ እንዲደረግ የተሰጠው ትዕዛዝ አቃቤ ህጉ ማስፈፀም ባለመቻሉ ዛሬ ክሳቸው ሊታይ ባለመቻሉ ፍርድ ቤቱ ተለዋጭ ቀነ ቀጠሮ ሰጥቷል፡:
ይህ በእንዲህ እንዳለ ተከላካይ ጠበቆች በአቃቤ ህግ የተመሰረተው ክስ የህገ መንግስት ጉዳይ ስለሆነ ፤ለህግ መንግስት አጣሪ ጉባዔ እንዲመራ፣አቃቤ ህግ ያቀረበው ክስ የህግ ስነስርዓቱን ባለመከተሉና ግልፅ ባለመሆኑ መቃወሚያ በማቅረብ ተከሳሾች በነፃ እንዲሰናበቱ አሊያም የዋስትና መብታቸው እንዲከበር በሚል ያቀረቡት ክርክር ከፍርድ ቤቱ መቅረፀ- ድምፅ ተገልብጦ አልቀረበም በሚል ፍርድ ቤቱ ብይን ሳይሰጥ ቀርቷል፡፡
ጉዳያቸው ክስ ሳይመሰረት ከ10 ወራት በላይ እንደፈጀ የሚነገርላቸውና እስካሁን ለህዝብ ይፋ ያልተደረገ የበርካታ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ጉዳይም በዕለቱ ችሎት ውሎ ነበር፡፡ በዚህም 8ቱ ከአዲስ አበባ ወደ ወልቂጤ፣ ያለፈው ጥቅምት 2006 ዓ.ም.ለአረፋ በዓል ሲሄዱ፣8ቱ ደግሞ አዲስ አበባ እያሉ በፀጥታ ኃይሎች ተይዘው በቁጥጥር ስር የዋሉት የነ ኤልያስ ከድር የክስ መዝገብ የሚገኙ 15 ወንዶችና አንዲት ሴት በአጠቃላይ 16 ወጣቶች ጉዳይ ለነሐሴ 5 ቀን 2006 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀነ ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡
በተያያዘ ወቅት እንደታሰሩ የሚነገርላቸውና ከአዳማ 4 ወንድ እና አንዲት ሴት በአጠቃላይ 5 ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች በፀጥታ ኃሎች በቁጥጥር ስር የዋሉት ለነሐሴ 12 ቀን 2006 ዓ..ም. ተለዋጭ ቀነቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡ በዚህ ጉዳይ ከተከላካይ ጠበቃ በተለይም በአንድ ወንድ እና በአንዲት ሴት ተጠርጣሪ ላይ በማረሚያ ቤቱ አያያዝ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተፈፅሟል በሚል ቅሬታ ቢቀርብም፤ ፍርድ ቤቱ በቀጠሮ ቀን መርምሮ ውሳኔ እንደሚሰጥ አስታውቋል፡፡ ፍርድ ቤቱም መቼ እንደሚጀመር ባይገልፅም ከነሐሴ 14 ቀን 2006 ዓ.ም. በኋላ ዝግ እንደሚሆን አስታውቋል፡፡
ኢትዮጵያ፣ ጅቡቲ እና ወደብ
ብስራት ወልደሚካኤል
Afrosonb@gmail.com
አንድ መንግስት ዛሬ በሚሰራው ሁሉ ነገንም ያስባል፤ኢትዮጵያ ግን ለዚህ የታደለች አትመስልም፡፡ ለዚህም አሁን በስልጣን ላይ ባለው ስርዓት ላለፉት 23 ዓመታት ከተከናወኑ በርካታ ዘመን እና ታሪክ አይሽሬ ስህተቶች መካከል የሰሞኑን የኢትዮጵያ እና ጅቡቲ ስምምነትን ማየት በቂ ነው፡፡ ስምምነቱ በየትኛውም ዓለም ያሉ ሀገሮች ያልተፈፀመ እና ሊፈፀም የማይችል በኢትዮጵያ ግን እውን ሆኗል፤እስካሁን ምክንያቱ በግልፅ ባይታወቅም፡፡
ገዥው ስርዓት ለህዝቡ ቃል የገባውን ላለመፈፀሙ በተደጋጋሚ ከሚገልፃቸው ቃላቶች እና ምክንያቶች መካከል የአፈፃፀም እንጂ የፖሊሲ ችግር የለብኝም የሚለው ነው፡፡ እውነታው ግን ከሚናገረው በተቃራኒ የፖሊሲ እና የአፈፃፀም ችግር ይስተዋልበታል፡፡ በመጀመሪያ ፖሊሲ ሲነደፍ የሀገሪቱን አቅም፣ ፍላጎት፣ ነባራዊ ሁኔታ፣ የህዝቡ ፍላጎትና አኗኗር እንዲሁም ዓለም አቀፍ ሁኔታን ከግምት በማስገባት የዜጎችን እነ የሀገሪቱን ቁሳዊና ስነልቦናዊ አዎንታዊ ውጤት ታስቦ የሚዘጋጅ የተግባር ሰነድ ነው፡፡ በርግጥ ፖሊሲን ከየትኛውም ሀገር መኮረጅ ይቻል ይሆናል፤ ነገር ግን ውጤታማነቱ የሚለካው የፖሊሲው ትግበራ አፈፃፀም ነው፡፡
ፖሊሲ በራሱ ከሌሎች የተለየ ሙያዊ ስነምግባር የሚጠይቅ በመሆኑ የአስፈፃሚውንም አካል አቅምና ብቃት እንዲሁም የፖለቲካ ቁርጠኝነት የሚፈተሽበት ነው፡፡ ስለሆነም የፖሊሲ ችግር የለም፤የአፈፃፀም እንጂ ሚባል ከሆነ ፖሊሲውን ሊያስፈፅም የሚችል ብቃት ያለው አካል የለም ማለት ነው፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ ችግሩን ለማረም ከሁለቱ አማራጮች አንዱን መውሰድ ግድ ይላል፡፡ ይህም ሚነደፈው ፖሊሲ ከገሪቱ አቅምና ፍላጎት ጋር ሳይሆን ከስራ አስፈፃሚው(ከገዥው ፓርቲ አመራሮች) አቅምና ብቃት ጋር በሚስማማ መልኩ መንደፍ፤ አሊያም ፖሊሲ የማስፈፀም ችግር አለብኝ ብሎ ያለው አካል ፖሊሲ የማስፈፀም አቅምና ብቃት ላለው አካል በሰላም ስልጣን መልቀቅ ብቸኛው መንገድ ነው፡፡ አለበለዚያ በፖሊሲ ንድፍና አፈፃፀም ችግር ምክንያት የሚፈጠሩ ችግሮችን በዘፈቀደ ወዲያው ለማረም መሞከር የበለጠ ሀገርን እና ትውልድን ሊያጠፋ የሚችል ከባድ ስህተት እንዲፈፀም በር ሊከፍት ይችላል፡፡
በተለይ የአንዲት ሀገር የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ተወደደም ተጠላ መሰረታዊ የሚባሉ ሶስት ነገሮችን ፖለቲካዊ፣ ማኀበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታን ታሳቢ በማድረግ የሁለትዮሽ ተጠቃሚነት ላይ መሰረት ያደረገ ነው፡፡ ይህም አንዲት ሀገር ፍላጎቷን፣መብትና ጥቅሟን ለማስፈፀም የምትንቀሳቀስባቸው በመሆኑ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ የሀገሪቱ ሁሉ-አቀፍ ፖሊሲ ግልባጭ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ለየት የሚያደርገው ፖሊሲው ከሀገር ውጭ ትኩረት ማድረጉ ብቻ ነው፡፡
በኢትዮጵያ እየተተገበረ ነው የሚባለው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ በሐሳብ ደረጃ ከላይ ካለው በተቃራኒ ትኩረቱ ኢኮኖሚ ላይመሰረት ያደረገ ነው መባሉ ነው፡፡ ስለዚህ የትኛውም ዓለም ሀገርም ሆነ ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሳይንስ ንድፈ ሐሳብና ትግበራ አንፃር እጅግ ጎዶሎ መሆኑን ያሳያል፡፡ ምክንያቱም ኢኮኖሚ በባህርይው ዛሬን እንጂ ነገን የማይል መሆኑ፣ስለአለውም ሆነ መጪው ጊዜ ፖለቲካዊና ማኀበራዊ ዓለም አቀፍ ሁኔታ እና ግንኙነት ቦታ በጥልቀት ከመገንዘብ ይልቅ ፋይናንስ ላይ የሚያተኩር ነውና፡፡ ከውጭ የሚገኝ የኢኮኖሚ ትብብር በራሱ ደግሞ ያለ ፖለቲካዊ ስራ እና ግንኙነት ሊሆን የማይችል ነው፡፡ ይሄ ደግሞ ገዥው እና አስፈፃሚው ስርዓት አርቆ የማሰብም ሆነ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ምንነት ትርጓሜና ተግባር ላይ ምን ያህል የአቅምና የፖለቲካ ቁርጠኝነት ችግር እንዳለ አመላካች ነው፡፡ የዚህ ውጤት ደግሞ ሀገሪቱንም ሆነ ህዝቡን ለአላስፈላጊ ከፍተኛ መስዋዕትነት መዳረጉ አይቀርም፤ ዳርጓልም፡፡
በቅርቡ 90 ሚሊዮን ከሚሆነው የኢትዮጵያ ህዝብመካከል 4.5 ሚሊዮን የሚሆነው የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልልህዝብ ከራሱ የከርሰ ምድር103 ሺህ ሜትር ኪዩብ ውሃ 800 ሺህ ለሚሆነው የጅቡቲ ነዋሪ ንፁህ የመጠጥ ውሃ በኢትዮጵያ ወጭ ሊቀርብ ነው፡፡ ይህም እ.አ.አ ባለፈው መስከረም 3 ቀን 2012 ዓ.ም. ስምምነት ከተፈፀመ የሰነበተውን ለወጉ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባለፈው ግንቦት 26 ቀን 2006 ዓ.ም. መፅደቁ በብዙዎች ዘንድ አግራሞት ፈጥሯል፤ሊፈጥርም ይገባል፡፡ ምክንያቱም ጉዳዩ ለኢትዮጵያ የሚያስገኘው ፖለቲካዊ፣ ማኀበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም መኖሩን የሚያመላክት ነገር አለ ወይ የሚለውን ጥያቄ እስካሁን በደፈናው ፖለቲካዊ ጥቅም ከሚል በስተቀር ኢኮኖሚያዊ ጥቅም የለም መባሉ በራሱ፤ ስርዓት እከተለዋለሁ ከሚለው ኢኮኖሚያዊ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ጋር ይጋጫል፡፡
በርግጥ እንኳን ቀጥተኛ ትስስር ካላት ከጎረቤት ሀገር ጅቡቲ ቀርቶ ከማንኛውም የውጭ ሀገር መልካም ግንኙነትና ጉርብትና መፍጠር ጠቃሚም ተገቢም ነው፡፡ ይበልጥ ጠቀሜታ ሊኖረው የሚችለው ግን የሁለቱንም ሀገራት ከጥርጣሬ የፀዳ የጋራ ተጠቃሚነት ላይ መሰረት ካደረገ ብቻ ነው፡፡ ይሄ ደግሞ ተለመደና ጤናማ ግንኙነትና ጉርብትና ነው፡፡ ከዚህ ውጭ የራስን ፖለቲካዊ፣ ተፈጥራዊና እና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም አሳልፎ በመስጠት የሚመሰረት ወዳጅነት በሀገሮቹ መካከል የነበረውን ግንኙነት በማሻከር በጥርጣሬ እንዲመሰረት በማድረግ ያልታሰበ ችግር የመፍጠር አጋጣሚ ይኖረዋል፡፡እስኪ ሰሞኑን በኢትዮጵያ እና ጅቡቲ መካከል በተደረገው ስምምነት አለ የተባለው ፖለቲካዊ ጥቅምስ እውን አለን? የሚለውን እና ነገ በኢትዮጵያ ላይ የሚኖረውንፖለቲካዊ፣ማኀበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖ በአጭሩ እንመልከት፡፡
ፖለቲካዊ ፋይዳ
በሁለት ሉዓላዊ ሀገሮች መካከል የሚደረግ ማንኛውም ስምምነት ሁለቱንም የጋራ ተጠቃሚነት ታሳቢ ያደረገ ማንኛውም ስምምነት በቀዳሚነት ፖለቲካዊ ፋይዳው ነው የሚታየው፡፡ ጅቡቲ ከኢትዮጵያ የሶማሌ ክልል አካል አንዱ፤በድሬዳዋ እና ጅቡቲ አዋሳኝ ከሆነው ሽንሌ ዞን ለ30 ዓመታት በ100 ኪሎ ሜትር የድንበር ርቀት ያለውን 20 ሄክታር መሬት ጨምሮ 4ሺህ ሄክታር የከርሰ ምድር ውሃ ያለበትን የተፈጥሮ ሃብት በነፃ እንድታገኝ ተደርጓል፡፡ ይህም ጅቡቲ ለዓመታት ፈተና የሆነባትን የንፁህ ውሃ አገልግሎት ከኢትዮጵያ ያለምንም ውጭ ማግኘቷ ከወደብ ጋር በተያያዘ በፖለቲካው ያላትን የበላይነት የሚያመላክት ነው፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያ ከድህነት ወለል በታች ካሉ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎቿ በንፁህ የመጠጥ ውሃ አገልግሎት እጥረት እየተሰቃዩ ባሉበት ሰዓት ከ800 ሺህ ለማይበልጥ ጎረቤት ሀገር ሚዛናዊ ያልሆነ ወጪ እንድታደርግ አስገዳጅ ነገር መፍጠሯ እና እየፈጠረች መሆኗ ስምምነቱ አሉታዊ የፖለቲካ ፋይዳ እንዲኖረው አስችሏል፡፡
ሌላው የውሃ ቁፋሮው የሚካሄድበት የሽንሌ ዞን ነዋሪዎች እስካሁን ለ23 ዓመታት ንፁህ የመጠጥ ውሃ አገልግሎት በአግባቡ ሳያገኙ ዛሬ በአንድ ጊዜ ለጅቡቲ ህዝብ ጥቅም ሲባል ጭራሽ ነዋሪው እንዲፈናቀል መደረጉ በሶማሌ ክልልም ሆነ በሌላው ኢትዮጵያዊ ዘንድ ስርዓቱ የሀገርና የህዝብን ጥቅም የማስጠበቅ ፖለቲካዊ ቁርጠኝነቱ ጥያቄ ምልክት ውስጥ እንዲገባ ያደርገዋል፡፡ ይሄ ደግሞ በአካባቢው ሌላ ቅራኔ በመፍጠር በቀጠናው ለእስኩኑ በባሰ የፖለቲካ አለመረጋጋት የመፍጠር ዕድል ይኖረዋል፡፡ በርግጥ ገዥው ኢህአዴግ ፖለቲካዊ ጥቅም ይኖረዋል በሚል የጅቡቲ ወደብን በቀጣይነት በተረጋጋ ሁኔታ በዓመት እስከ 1 ቢሊዮን በሚጠጋ የአሜሪካን ዶላር ለመጠቀም ለመደለል ማሰቡ መጭውን ጊዜ ያለማገናዘቡን ከማመልከት በስተቀር በቀጣይ ጅቡቲ ውሳኔ ላይ ያን ያህል የጎላ ፖለቲካዊ ተፅዕኖ ይኖረዋል ተብሎ አይታሰብም፡፡ እዚህ ላይ ኢህአዴግ ያለህዝቡ ፈቃድ ላለፉት 23 ዓመታት የኢትዮጵያን ተፈጥሯዊና ታሪካዊ የሆነውን የአሰብ ወደብን በአሁኑ ለጅቡቲ የሀገሪቱን የተፈጥሮሃብት ከክፍያ ነፃ በሆነ መንገድ እንደሰጠ ያኔ ለኤርትራ መስጠቱ ያመጣውን አሉታዊ ተፅዕኖ ዛሬም መድገሙ ገዥዎቹ አሁንም ከስህተት ፖለቲካዊ ውሳኔ ለመማርዝግጁ አለመሆናቸውን ያሳያል፡፡
ሌላው ኢህአዴግ ህዝብ ሳይመክርበትና ሳይወያይበት እንዲሁም ሳይፈቅድ የሀገሪቱን መሬት ከነተፈጥሮ ሃብቱ በነፃ አሳልፎ መስጠቱ ነገ በሁለቱ ሀገሮች መካከል በሚኖረው ጉርብትና እና ወንድማማችነት መካከል ችግር መፍጠሩ አይቀርም፡፡ ምክንያቱም ነገ በኢትዮጵያ የፖለቲክ መንግስት ስርዓት ለውጥ ቢፈጠርና ይህ ስምምነት አዲስ በሚመሰረተው የመንግስት ቢሻር፤ ለኢትዮጵያ ሌላ አዲስ የጎረቤት ሀገር በጠላትነት የመፍጠር ዕድሉ ሰፊ ነው፡፡ ምክንያቱም የተደረገው ስምምነት ሁለቱንም ሀገሮችና ህዝብ ተጠቃሚ ያደረገ ሚዛናኑን የጠበቀ ስምምነት አልተፈፀመምና፡፡ በርግጥ ኢህአዴግ በአንድ መነፅር ብቻ በመመልከት ለጅቡቲ የኃይል አቅርቦት መብራት እጅግ በቅናሽ ዋጋ ማቅረቡ እና ይህን ውሃ በነፃ መፍቀዱ በቀጣይ ለሚጠቀምበት የወደብ ኪራይ ማረጋጊያ እንደ ማታለያ ለመጠቀም አስቦ ሊሆን ይችላል፡፡ ይሄ ደግሞ ሌላው የዋህነትና ድፍረት ነው፡፡
ጅቡቲ በቀጠናው ካላት መልካዓ ምድራዊ ፖለቲካ አቀማመጥ አንፃር በአሁን ሰዓት ሁሉ ነገሯን በራሷ ትወስናለች ማለት ዘበት ነው፡፡ ቀጠናው በቀይባህርና እና ህንድ ውቅያኖስ ዓለም አቀፍ የንግድ መስመር ላይ እንደመገኘቷ፣ የቀጠናው ፖለቲካዊ አለመረጋጋት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ምዕራባውያንንም ሆነ እንደ ቻይና እና ኢራን ያሉ እስያ ሀገሮችንም መሳቧ እርግጥ ነው፡፡ በተለይ ፈረንሳይ እና አሜሪካ በቀጠናው ሽብርተኝነትን ለመዋጋት በሚል ከአረብ ሀገራት ለሚያጓጉዙት ግዙፍ የቶታል፣ሞቢል እና የመሳሰሉ የነዳጅ ኩባንያዎቻቸው ደህንነት ጅቡቲን በእጅ አዙር መጠበቅና መንከባከብ ስለማይቦዝኑ፤ኢትዮጵያ አሁን ባደረገቸውና ለወደፊቱም ለማድረግ ባሰበችው የማታለል ተግባር ፈረንሳይና አሜሪካንም ጭምር መሆኑን ልታጤን ይገባል፤ይህ ደግሞ የላጭን ልጅ ቅማል በላት ዓይነት ተረት መሆኑ ነው፡፡
ስለዚህ ሚዛኑን ያልጠበቀውና ነገን ታሳቢ ያላደረገው የጅቡቲ ብቻ ተጠቃሚነት የውጭ ጉዳይ ስምምነት ለኢትዮጵያ አሉታዊ የፖለቲካ ፋይዳ እንጂ ከአጭር ጊዜም ሆነ ከረጅም ጊዜ አኳያ ሲሰላ ትርጉም አልባ ይሆናል፡፡ ስለሆነም ስምምነቱ ሙሉ ለሙሉ ከመተግበሩ በፊት ውሃ የሚቆፈርበት ቦታ ግልፅና ገለልተኛ በሆነ አካል የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ በማካሄድ ራስን ከአላስፈላጊ ፖለቲካዊ ኪሳራ ማዳኑ የተሸለ ነው፡፡
ማኀበራዊ ፋይዳ
እንደማዕከላዊ መረጃ ኤጀንሲ ከሆነ ከኢትዮጵያ በህዝብ ብዛት ከኦሮሞ እና አማራ ክልል ነዋሪ ቀጥሎ በ3ኛ ደረጃ የሚገኘው እና 4.5 ሚሊዮን ነዋሪ ያለው የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ህዝብ በቂ ንፁህ የመጠጥ ውሃ ሳያገኝራሷን ለቻለች ሉዓላዊ ጎረቤት ሀገር በኢትዮጵያ ወጪ መደረጉ ስርዓቱ ገዥነት ለጅቡቲ ነው ወይስ ለኢትዮጵያ ያስብላል፡፡ የሶማሌ ክልል ነዋሪ በ 5.6 እጥፍ ከጅቡቲ ህዝብ ይበልጣል፡፡ ይሁን እንጂ ኢህአዴግ መራሹ መንግስት እመራዋለሁ የሚለውን ህዝብ ፍላጎትና ፍጆታ ሳያሟላ፤በኢትዮጵያ ወጭ ለጅቡቲ ማኀበራዊ አገልግሎት የሚውል፤ ውሃ ከሚቆፈርበት የሶማሌ ክልል ሽንሌ ዞን ለድሬዳዋ እና ሐረር በቅርብ ርቀት ቢገኝም የሀብቱ ባለቤት የሆኑት የአከባቢው ኢትዮጵያውያን ነዋሪዎች በንፁህ የመጠጥ ውሃ አገልግሎት ችግር ሲሰቃዩ እስካሁን መፍትሄ ያላቸው የመንግስት አካል የለም፡፡
በአንፃሩ አዲስ አበባን ጨምሮ በአራቱም የሀገሪቱ አቅጣጫዎች ለሚገኙ ነዋሪዎችም ቢሆን ያለው የንፁህ የመጠጥ ውሃ አገልግሎት ችግር ከዕለት ወደ ዕለት እየተባባሰ ነው፡፡ በሌላ በኩል በመንግስት ይህን የማኀበራዊ አገልግሎት ችግር ለመፍታት ከቃላት ባለፈ በተግባር የተሰጠ መፍትሄ ሳይኖር በአሁን ወቅት የኢትዮጵያ አካል ላልሆነቸው ጅቡቲ አብዝቶ መጨነቅና ከድሃ ህዝብ ጉሮሮ በጀት ተነጥቆ መመደቡ ትልቅ የሞራል ኪሳራ ነው፡፡ ይህም የሚያሳየው የኢትዮጵያ መንግስት ለዜጎቹ ያለው ተቆርቋሪናትና ማኀራዊ አገልግሎት ያለው ተነሳሽነት ዝቅተኛ መሆኑን ነው፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ነገ የውሃ ጉድጓድ ቁፋሮውን ተከትሎ የሚፈናቀሉ ዜጎች ለማን ተጠቃሚነት በሚል ከቀያቸው ሊነሱ ነው? እኚህ ዜጎች የነሱ ችግር ሳይፈታ አላቂ የሆነውን የተፈጥሮ ሃብታቸውን ያለፈቃዳቸው ተነጥቀው ለተጨማሪ የማኀበራዊ ቀውስ መዳረጋቸው በጅቡቲና በአዋሳኝ ድንበር ባሉ ኢትዮጵያውን መካከል ቅሬታ መፍጠሩ አይቀርም፡፡ የዚህ ቅሬታ ደግሞ ወደ ግጭት በማምራት ለተጨማሪ ማበራዊ ቀውስ መዳረጉ ከወዲሁ መጤን ያለበት ጉዳይ ቢሆንም፤ በማን አለብኝነት ሊታለፍ መሆኑ ማጣፊያው የሚቸግር ሌላ መዘዝ ይዞ መምጣቱን ካለፉ ስህተቶች መማር ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያ በራሷ ወጭ ለጅቡቲ በነፃ በምትሰጠው የንፁህ የመጠጥ ውሃ አገልግሎት ሀገሪቱም ሆነች ዜጎቿ ከማኀበራዊዘርፍ ከሚያገኙት ጉዳት በስተቀር ምንም ጥቅም የለም፡፡
ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ
በስምምነቱ መሰረት ኢትዮጵያ ያላትን የተፈጥሮ ሃብት ከመስጠቷ በተጨማሪ ሌላ የፋይናንስ ወጪ ለማድረግ መፈራረሟ ሊላ የኢኮኖሚ ኪሳራን ያስከትላል፡፡ ይህ መደረጉ በራሱ ሀገሪቱ እከተለዋለሁ፤ እየተከተልኩ ነው የሚለው የኢኮኖሚ ተኮር የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ጋር በእጅጉ ይቃረናል፡፡ ምክንያቱም ሀገሪቱ በኢኮኖሚ ለተጨማሪ ኪሳራ ከመዳረጓ በስተቀር የሚያስገኝላት አንዳች ጥቅምም የለምና፡፡
ኢትዮጵያ ይህን በማድረጓም ጅቡቲ ለኢትዮጵያ እየሰጠች ባለችው የወደብ ኪራይ
ላይ ተጨማሪ ክፍያ እንዳትጠይቅ የሚከለክል ነገር እንኳ ባለመኖሩ፤ነገ በቅናሽ የቀረበላትን የመብራት ኃይል አገልግሎት እና የጫት ንግድ በነፃ ማግኘት አለብን የሚል ሌላ ኢኮኖሚያዊ ጥያቄንም ይዞ ሊመጣ ይችላል፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያ ሙሉ 90 ሚሊዮን ህዝብ ያላት ኢትዮጵያ 800 ሺህ ባላት ጅቡቲ ላይ ጥገኛ መሆኗን ሳትገነዘብ አትቀርም፤በኢህአዴግ የስልጣን አገዛዝ ሌላ የተሻለ አማራጭ የላትምና፡፡
የመገርመው ኢትዮጵያ ለጅቡቲ ከፍተኛ የወደብ ኪራይ ከመክፈሏ በተጨማሪ ለኢትዮጵያውያን ያልተሰጠው ከክፍያ ነፃ የኢንቨስትመንት መሬት እና በወደቡ አካባቢ ተገነቡ ከፍተኛ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች በኢትዮጵያ ወጪ መከናወኑ ራሱ ሌላው ያልተመለሰ የኢኮኖሚ ኪሳራ ነው፡፡ ይሄ ደግሞ መቼም ከጅቡቲ ጋር ለሚኖረን ወዳጅነት ጥሩ መፍትሄ ሊሆን አይችልም፡፡ ምክንያቱም በዓለም አቀፍ ፖለቲካ ኢኮኖሚ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መሰረት ዘላቂ ወዳጅ እና ዘላቂ ጠላት የሚባል የለምና፡፡ ያውም የዓለም የፖለቲካ ስርዓት በፍጥነት እየተቀያየረ ባለበት ሰዓት፤ እንዲህ ዓይነት ውሳኔ መወሰን እና መስማማት አሁን ከወጣውና ሊወጣ ከታሰበው በወጪ በላይ ተጨማሪ የገንዘብ ኢኮኖሚ ጥያቄን ይዞ መምጣቱ የተገመተ አይመስልም፡፡
መፍትሄ
የኢትዮጵያ መንግስት አሁን የተፈራረመው (የውሃ ጉድጓድ ቁፋሮው መጀመሩ ቢነገርም) ሙሉ ለሙሉ ተጋባራዊ ከመሆኑ በፊት የሚኖረውን ፖለቲካዊ፣ማበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ማጤን አለበት፡፡ ሌላው የሁለት ሀገሮችን ጠጋራ ተጠቃሚነት የማያረጋግጥ ማንኛውም ሰምምነት ነገ ማጣፊያው የሚቸግር ሌላ ችግር ማስከተሉ ከወዲሁ በመገንዘብ ወደ ዘላቂ መፍትሄ መሄዱ ብልህነት ነው፡፡ ለዚህም ኢህአዴግ ያኔ ያለ ህዝብ ፈቃድ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ የሆነውን የባህር በር (አሰብ ወደብን) ራሱ አሳልፎ እንደሰጠ በማመን በዓለም አቀፍ ህግ መሰረት ለማስመለስ ግልፅ ውይይት እና ጥረት ማድረግ አለበት፡፡
ሌላው ከህግ አኳያ ስምምነቱ የህገ መንግስት ጥሰትም አለበት፡፡ እዚህ ላይ የሚያሳፍረው የሀገሪቱንና ህዝቧን ጥቅም በህግ ያስጠብቃሉ የተባሉት እንደራሴዎች በግልፅ ገዥ የሆነውን የሀገሪቱን ህግ ከአስፈፃሚው እኩል ጥሰው ስምምነቱን ማፅደቃቸው ነው፡፡ ይህም በህገመንግስቱ አንቀፅ 86(3) ላይ የውጭ ግንኙነት መርሆች በሚለው ስር “የሀገሪቱ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ በጋራ ጥቅምና በእኩልነት ላይ የተመሰረተ መሆኑን እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚደረጉ ስምምነቶች የኢትዮጵያን ጥቅም የሚያስከብሩ መሆናቸውን ማረጋገጥ::” ይላል፡፡ ነገር ግን ስምምነቱ የማኀበራዊ እሴት መጠበቂያ የሆነው ህገ መንገስት በግልፅ በዚህ መልክ ተጥሶ የጅቡቲን ጥቅም ማስጠበቁን አስፈፃሚዎችም አልካዱትም፡፡ ይሁን እንጂ ፓርላማው ራሱ የህገመንግስት ጥሰትን በመፈፀም ተባባሪ መሆኑን አሳይቷል፡፡ ስለዚህ የፀደቀው አዋጅ ተፈፃሚ ከመሆኑ በፊት የሀገሪቱንም ሆነ የሁለቱን ሀገሮች የጋራ ጥቅም በሚያስጠብቅ መልኩ ሊሻሻል አሊያም ሊሻር ይገባዋል፡፡ አለበለዚያ ህግ ተርጓሚዎች እና አስከባሪዎች ጉዳዩን ወደ ህግ በመውሰድ ተገቢው እርምት እንዲወሰድ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡
የገዥው ፓርቲ ወገንተኝነትን ትቶ የሀገሪቱን እና የህዝቡን ጥቅም ሊያስጠብቁ የሚችሉ ዓለም አቀፍ ኢትዮጵያውያን ዲፕሎማቶችን፣ የታሪክና የህግ ባለሙያዎችን፣ ሀገር ሽማግሌዎችን፣ የኃይማኖት አባቶችን እና ፖለቲከኞችን ያካተተ ግብረ ኃይል በማቋቋም ተግባራዊ እንቅስቃሴ መጀመሩ የሚያዋጣ መንገድ ነው፡፡ ኢህአዴግ ይሄን ማድረግ ፍላጎትና አቅም የለኝም የሚል ከሆነ ስልጣኑን በፈቃዱ ለቆ ለሰላማዊ የስልጣን ሽግግር በር መክፈት አሊያም ሌሎች ኢትዮጵያውያን ተከታትለው እንዲያስፈፅሙ አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ የተሻለና የሰለጠነ አማራጭ መፍትሄ ነው፡፡ ለዚህም ሁሉም ዜጋና እና በቀጥታ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ትኩረት ሊሰጡት ይገባል፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብ አሁን ካለው 90 ሚሊዮን ከአስርና ሃያ ዓመታት በኋላ ቁጥሩ በከፍተኛ ደረጃ ጨምሮ ከ120-150 ሚሊዮን ሲደርስ ችግሩ ከአሁኑ እጅግ የባሰ ይሆናል፡፡ ያኔ የጅቡቲን ወደብ በኪራይመጠቀም ቀርቶ፤ ጅቡቲ በፈቃዷ የኢትዮጵያ መንግስት አንዷ ፌደራላዊ አካል ብትሆን እንኳ ችግሩን መቅረፍ አይቻልም፡፡ ስለዚህ በየዓመቱ በተለያየ መንገድ የኢትዮጵያን ጥቅምና ፍላጎት ለጅቡቲ አሳልፎ እየሰጡ እሽሩሩ ማለቱ ለሌላ ተጨማሪ ችግር በር ከመክፈቱ በስተቀር ለአጭርም ሆነ ለረጅም ጊዜ መፍትሄ ሊሆን አይችልም፡፡
በተደጋጋሚ ተጨማሪ ወጭና ስጋት የማይፈጥር ዘላቂ መፍትው ግልፅና አጭር፤ያም ሀገሪቱ በህገ ወጥ መንገድ ያጣችውን ታሪካዊና ተፈጥሯዊ የሆነውን የአሰብ ወደብንማስመለስ ነው፡፡ ከዚህ ውጭ እንደ ኬኒያ፣ ሶማሊ ላንድ እና ሱዳን ወደቡን በአማራጭነት ማሰቡ ደግሞ ከጅቡቲ የባሰ ፖለቲካዊ፣ ማኀበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር ይዞ መምጣቱ የማይቀር ስለሆነ፤መፍትሄው ኢትዮጵያ የራሷን የባህር በር በዓለም አቀፍ ህግ መሰረት በማስመለስ የወደብ ባለቤት መሆን ብቻ ነው፡፡