Category Archives: News

በእነጉርሜሳ አያኖ መዝገብ 5ት ቀሪ የአቃቤ የህግ ምስክሮችን ለመስማት ተጨማሪ ቀን ተሰጠ

አቃቤ ህግ ታህሳስ 27 ቀን 2009 ዓ. ም. ቀሪ ምስክሮች ቀርበው እንደሆነ ሲጠየቅ፤ አምስት ምስክሮች እንደሚቀሩት እና ተገቢውን ጥረት ቢያደርግም ሊቀርቡ እንዳልቻሉ በመግለፅ የበለጠ ጉዳዩን እንዲያስረዱለት ከፓሊስ የቀረቡትን ረዳት ኢንስፔክተር ቴድሮስ አዳነ ጠይቋል።

Bekele Gerba

አቶ በቀለ ገርባ

ረዳት ኢንስፔክተሩ የተሰጣቸው ጊዜ አጭር በመሆኑ በተሰጠው ቀጠሮ ሁሉንም ማቅረብ አለመቻላቸውን፤ ምስክሮቹ አካባቢያቸውን አበመልቀቃቸው በአዲሱ አድራሻቸው እያፈላለጓቸው በመሆኑ፤ ራቅ ያለ ቦታ ያሉ ምስክር በመኖራቸው ከፍተኛ የጊዜ እጥረት ስለገጠማቸው በመሆኑ ጊዜ እንዲጨመርለት ጠይቋል። በመቀጠልም አቃቤ ህግ ከቀሩት 5ት ምስክሮች ውስጥ አንዱ ጉጂ ዞን የሚገኝ፣ አንዱ ፀበል ላይ እንደነበረ እና ማስረጃ እስኪያመጣ ጊዜ ስላጠረ፣ አንደኛው አድራሻ ቀይሮ ሌላ ቦታ በመሄዱ በተሰጠው ጊዜ ቀርበው መመስከር እንዳልቻሉ ተናግሮ የተቀሩት ሁለቱ ግን የአዲስ አበባ ነዋሪ መሆናቸውን መመስከር ስላልፈለጉ አድራሻቸውን እየቀያየሩ እንዳስቸገሯቸው ተናግሯል። እስካሁን ይመሰክራሉ ከተባሉ 42 ምስክሮች ውስጥ 37ቱን እንዳሰማ የተናገረው አቃቤ ህግ የተከሰሱበትን የክስ ክብደት እንዲሁም ከፍተኛ ጉዳት ያስከተለ ተግባር መሆኑን ከግምት ውስጥ በማስገባት ቀሪ ምስክሮችን አቅርበው እንዲያሰሙ ተጨማሪ ጊዜ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።

የተከሳሽ ጠበቆች የተሰሙት ምስክሮች በችሎቱ ግፊት እንጂ አቃቤ ህግ ዳተኛ እንደነበረ፤ ምስክሮቹን ማቅረብ ስላልፈለገ እንጂ በቂ ጊዜ ተሰጥቶት እንደነበረ፤ የፍትህ ሂደት የሚለካው በሂደቱም ጭምር መሆኑን፤ ከባለፈው ቀጠሮ ጀምሮ በሰበብ አስባቡ ምስክሮችን ለማምጣት በሚል ቀጠሮ መሰጠቱን ተቃውመው እንደነበረ እና የዛሬው ቀጠሮም የመጨረሻው በሚል የተያዘ እንደሆነ ገልፀው ተጨማሪ ቀጠሮ መሰጠት እንደሌለበት ተናግረዋል።

“እንደሚታወቀው ከታሰርን ሁለት ወራችን አይደለም። አንድ አመት አልፎናል። እነሱ ቤታቸው እያደሩ እኛን እያሾፉብን ነው። በአንድ ቀን ብዙ ሺዎችን እያሰረ ያለ መንግስት፤ እንዴት ነው 5ት ምስክሮችን ማቅረብ ያልቻሉት? ” በማለት የኦፌኮ ም/ፕሬዝዳንት አቶ በቀለ ተጨማሪ ቀጠሮ መኖር የለበትም ሲሉ ተከራክረዋል። አቶ ደጀኔ ጣፋም ተቃውሟቸውን ለችሎቱ አሰምተዋል። “አቃቤ ህግ ሲናገር 2ቱ አዲስ አበባ ናቸው ብሏል። ለምን አልቀረቡም እስካሁን? ክሳችን መጀመሪያም የፓለቲካ ክስ ነው አሁንም የፓለቲካ ድምዳሜ ነው የምንሰማው። እንዲሁ እንደከሰሳችሁን እንዲሁ ፍረዱብን። ወይስ ፍትህ አለ ለማስባል ነው? የኛን እና የናንተን ጊዜ ለምን ይፈጃሉ? ጉጂ እኮ ወርቅ የሚዘረፍበት ነው። እንዴት ከዛ አንድ ሰው ማምጣት ይከብዳቸዋል? አቃቤ ህግ ሌላ ጫና ከሌለባቸው በህጉ አግባብ ይስሩ። ፍርድ ቤት በየጊዜው እያሳሰሰባቸው ነው ምስክር ይዘው ሚቀርቡት። ያልቀረቡ ምስክሮችን በተመለከተ ከቀበሌ ደብዳቤ ይዘው ቀርበዋል ወይ? አልቀረቡም! የፍርድ ቤት ትእዛዝ እየተከበረ አይደለም። እናንተም የካድሬ አይነት ሳይሆን የባለሙያነት አሰራር ስሩልን።” በማለት ሌላ ቀጠሮ መሰጠቱን እንደሚቃወሙ ተናግረዋል።

“አቃቤ ህግ ዛሬ አጭር ጊዜ ነው የተሰጠን ብሏል በወቅቱ ቀጠሮ ሲሰጥ ለምን አጭር ጊዜ ነው የተሰጠን አይበቃንም አላለም? ከቀበሌ ይቅረብ የተባለው ማስረጃ አልቀረበም። የችሎቱ ብይን መከበር አለበት። ማእከላዊ ሲያሰቃዩን የነበሩ ፓሊሶች ናቸው ዛሬ ቀርበው ያልተገባ ተጨማሪ ቀጠሮ እየጠየቁ ያሉት።” ሲል የተጨማሪ ቀጠሮውን ጉዳይ ተቃውሞ አሰተያየታቸውን የሰጡት አቶ አዲሱ ቡላላ ናቸው።

ዳኞች ከተማከሩ በኋላ አቃቤ ህግ ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራ፤ ተከሳሾችን ደግሞ የፓለቲካ እስረኛ ብሎ ነገር እንደሌለ፣ ያሉበትን ሁኔታ እንደሚረዷቸው፣ እንዲያውም ማነፃፀር ባይገባም ከሌላው መዝገብ ሲተያይ በፍጥነት እየሄደ መሆኑን፣ እነሱም [ተከሳሾች] መከላከያ ምስክር በሚያሰሙበት ጊዜ ምስክሮችን ለመስማት ጊዜ እንደሚሰጡ በመግለፅ ፓሊስ በ15 ቀን ውስጥ ከየትም ፈልጎ ምስክሮቹን እንዲያመጣ፤ የማይገኙ ከሆነም ይኖሩበት ከነበረው ቀበሌ ደብዳቤ እንዲቀርብ ትእዛዝ ሰጥተዋል። አቃቤህግ የተሰጠው ጊዜ አጭር እንደሆነ በመግለፅ ትንሽ ረዘም ያለ ቀጠሮ እንዲሰጠው ቢጠይቅም ዳኞች ጥያቄውን ሳይቀበሉት፤ ፓሊስ የተቻለውን ሁሉ ጥረት በማድረግ በቀጠሮው ቀን እንዲያቀርብ አዘዋል።

የተከሳሽ ጠበቃ የሆኑት አቶ መልካሙ የሚሰጠው ቀጠሮ የመጨረሻ እንዲሆን በሚል ላቀረቡት ሃሳብ፤ የመጨረሻ ቀጠሮ የሚባል እንደሌላ አሳማኝ ምክንያት ከተገኘ ሌላ ቀጠሮ ሊሰጥ እንደሚችል፤ አሳማኝ ምክንያት ካልተገኘ የመጨረሻ ባይባልም የምስክር የመስማት ሂደት ሊቋረጥ እንደሚችል በመጥቀስ ቀጣዩ ቀጠሮ የመጨረሻ መባል የለበትም ሲሉ ዳኞች መልስ ሰጥተዋል።

ቀሪ የአቃቤ ህግ ምስክሮችን ለመስማት ለጥር 15 ቀን 2009 ዓ. ም. ቀጠሮ ተይዟል።

ምንጭ፦EHRP

በዮናታን ተስፋዬ ላይ መከላከያ ምስክሮች መሰማት ጀመሩ

ቀደም ባሉ ቀናት በዋለው ችሎት በጊዜ እጥረት ምክንያት መከላከያ ምስክሮችን ለመስማት ባለመቻሉ ታህሳስ 26 ቀን 209 ዓ. ም. ተቀጥሮ ነበር። ዮናታን ተስፋዬ እንዲከላከሉለት ከዘረዘራቸው የሰው ምስክሮች ከአንዱ (ዶ/ር መረራ ጉዲና) በስተቀር የተቀሩት መከላከያ ምስክሮች መቅረባቸውን የዮናታን ጠበቃ የሆኑት አቶ ሽብሩ በለጠ ለችሎት አሳውቀዋል፡፡ መከላከያ ምስክሮች መሰማት ከመጀመራቸው በፊት አቶ ዮናታን የራሱን የምስክርነት ቃል አቅርቧል፡፡

yonatan-tesfaye

ዮናታን ተስፋዬ

“በፌስቡክ አካውንቴ እፅፍ የነበረው ሃሳቤን ለመካፈል ፈቃደኛ ለሆኑት ጓደኞቼ ብቻ ነው፡፡ ህዝብ ቀስቅሷል የሚባለው ነገር የማይመስል ነገር ነው፡፡ እድሉን አግኘቼ እንኳን ለህዝብ ደርሶ ቢሆን የሽብርን ድርጊት የሚያበረታታ አይደለም የፃፍኩት ነገር፡፡ በሃገሪቷ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ የሚገልፁ እና የሚዳስሱ ናቸው፡፡ እንዚህን ሃሳቦች ከጓደኞቼ ጋር መወያየቴ ሃሳቤን በነፃነት የመግለፅ መብቴን መጠቀሜ ነው፡፡ “ህግ መጨቆኛ መሳሪያ ሲሆን፡ አመፅ የህሊና ህግ ይሆናል፡፡” የሚለው ሃሳብ የተፈጥሮ እና አለም ዓቀፋዊ ህግ ነው፡፡ ማንም ሊቀይረው አይችልም፡፡ የፍልስፍና መርህም ነው፡፡ ምናልባትም ያን የተናገርኩ ጊዜ የሚሰማ አካል ቢኖር ኖሮ ይሄ ሁላ ችግር ባልደረሰም ነበር፡፡ በህዳር 2008 ዓ.ም. አካባቢ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን የሚገኘው ጭልሞ ጫካ ለባለሃብት ከተሸጠ በኋላ ህብረተሰቡ ተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ አድርገዋል፡፡ ምናልባትም ጥያቄያቸው በትክክለኛው አግባብ ቢያዝ ተቃውሞው አይስፋፋም ነበር፡፡ እኔም የሚደርሰው ጉዳት እንዲቀንስ የበኩሌን አስተዋፅኦ ማድረግ ነበረብኝ፡፡ መንግስት የህብረተሰቡን ደህንነት መጠበቅ ሲኖርበት በተቃራኒው የመንግስት አካል ህብረተሰቡ ላይ ጉዳት ሲያደርስ በተለያየ መንገድ ህዝቡ ራሱን እንዲከላከል የተለያየ ሃሳብ አቅርቤአለሁ፡፡ የአንድ ሰው ህይወት ዋጋ አለው፡፡ እኔ ከመታሰሬ ቀደም ብሎ 62 የዩቨርስቲ ተማሪዎች ተገድለው ነበር፡፡ እነዚህ ተማሪዎች ነገ ይህችን ዓለም ሊቀይሩ ይችሉ የነበሩ ናቸው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያምን ጨምሮ የተለያዩ የመንግስት አካላት ችግሩ የተከሰተው በመልካም አስተዳደር እጦት መሆኑን አምነው ይቅርታም የጠየቁበት ጉዳይ ነው። አንድ ሚሊዮን ብር ከሚያወጣ ንብረት ይልቅ የአንድ ሰው ህይወት ዋጋ አለው፡፡ ለምሳሌ አንድ ሹፌር 20 ተሳፋሪ ይዞ ፍሬን እምቢ ቢለው መኪናውን አጠገቡ የሚገኝ ግንድ ወይም ግንብ አጋጭቶ ቢያቆመው፡ ሹፌሩ መኪናው ላይ በደረሰው አደጋ ሊቀጣ አይገባውም፡፡ በአደባባይ ሰዎች ሲሞቱና ሲገደሉ እነርሱን ዲፌንድ ማድረግ ነበረብኝ፡፡ ይህንንም ሃሳቤን የመግለፅ መብቴን ተጠቅሜ የተለያየ ሃሳብ አቅርቤያለሁ፡፡ ይሄ ጥፋት የሚባል ከሆነ እቀበለዋለሁ፤ ለኔ ክብሬ ነው፡፡ ፍርዱን ከታሪክ እና ከእግዚአብሄር አገኘዋለሁ፡፡” ይህን የምስክርነት ቃሉን ዮናታን ካቀረበ በኋላ የሙያ ምስክርነታቸውን የሚሰጡትን ሶስት ምስክሮች ጠበቃው ዘርዝረዋል፡፡

የህግ ባለሙያ የሆኑት ዶ/ር ያእቆብ ኃይለማርያም እና የፍልስፍና መምህሩ ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ የሙያ ምስክርነታቸውን የሚሰጡ ሲሆን ዮናታን የፃፈው ፅሁፍ ሃሳብን ከመግለፅ ነፃነት አንፃር እና ኢትዮጵያ ከፈረመቻቸው ህጎች አንፃር ገደቡን ያለፈ አለመሆኑን እንደሚያስረዱ፤ እንዲሁም ሶስተኛው የሙያ ምስክር ጦማሪ እና የመብት አራማጅ በፍቃዱ ሃይሉ ደግሞ በፌስቡክ በግለሰብ አካውንት የሚለጠፉ ፖስቶች ከመደበኛ ሚዲያ እና ከዜና ድህረገፆች የሚለይበትን እንደሚያስረዳ ጠበቃው አቶ ሽብሩ በጭብጥነት አስመዝግበዋል፡፡ አቃቤ ህግ በሶስቱም የሙያ ምስክሮች ላይ ተቃውሞ እንዳለው ከተናገረ በኋላ ህግን መተርጎም ያለበት ፍርድ ቤት እንደሆነ ከዚህም ካለፈ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ማየት እንዳለበት ጠቅሶ ምስክሮች የፍርድ ቤቱን ሚና መውሰድ ስለሌለባቸው የመጀመሪያዎቹ ሁለት ምስክሮች [ዶ/ር ያእቆብ እና ዶ/ር ዳኛቸው] መሰማት የለባቸውም በማለት እንዳይሰሙ ሲል ጠይቋል፡፡ በፍቃዱ የሚመሰክርበትን ጭብጥም በተመለከተ ከክሱ ጋር የማይገናኝ ስለሆነ መመስከር የለበትም ብሎ ለችሎቱ ተቃውሞውን አሰምቷል፡፡

ጠበቃ አቶ ሽብሩም “አቃቤ ህግ ዮናታንን ወንጀል ሰርቷል ብሎ ምስክር ሲያሰማ የዳኞችን ሚና ወሰደ አልተባለም፡፡ የደንበኛዬ የመከላከል መብት በሰበብ አስባብ ሊጣስ አይገባም፡፡” ብለው ከተናገሩ በኋላ ዶ/ር ያዕቆብ እና ዶ/ር ዳኛቸው ከልምዳቸው እና ከትምህርት ዝግጅታቸው አንፃር የዮናታን ፅሁፍ ከገደብ አለማለፉን በተረዱት መጠን እንደሚያስረዱ፤ በፍቃዱ የሚመሰክረውም ዮናታን የተከሰሰበት የሽብርተኝነት ህግ አንቀፅ 6 በህትመት ደረጃ ስለሚፃፉ ሽብርተኝነትን የሚያበረታቱ ፅሁፎች ስለሚል ልዩነቱን እንዲያስረዳ ነው በማለት ምስክሮቹ የሚመሰክሩበትን ጭብጥ አግባብነት አስረድተዋል፡፡ ዳኞችም የግራ ቀኙን ሃሳብ ከሰሙ በኋላ ምስክሮች ከተሰሙ በኋላ ቃሉ ተመዝኖ መጨረሻ ላይ የሚታወቅ በመሆኑ ምስክሮች እንዲሰሙ ወስነዋል፡፡

በመጀመሪያ ለመመስከር የቀረቡት ዶ/ር ያዕቆብ ኃይለማርያም ናቸው፡፡ የህግ ምሩቅ መሆናቸውን፣ የህግ አማካሪ እና በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ መምህር መሆናቸውን ገልጸው በሩዋንዳ የዘር ማጥፋት ወንጀል አጣሪ ቡድን አባል ሆነው እንደሰሩ እና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የህግ አማካሪ ሆነው እንደሰሩ ገልፀዋል፡፡ ስለሽብር ወንጀል ምንነት እና ከዮናታን ፅሁፍ ጋር አያይዘው እንዲመልሱ ተጠይቀው፤ “የሽብር ወንጀል አስከፊ ነው፤ ከጦር ወንጀል እና ከዘር ማጥፋት ጋር የሚሰለፍ ነው፡፡ የሽብር ወንጀል ዓለም አቀፍ ወንጀል ነው፡፡ አንድን ሽብር ፈጣሪ የትኛውም ሃገር ቢሄድ የሚጠየቅ ነው የሚሆነው፡፡ በኬኒያ እና ሌሎች የአለማችን ክፍሎች በርካታ ህዝቦች ያለቁበትን ሁኔታዎች በአለም አቀፍ ሁኔታም የሽብር ድርጊት የሚባሉ ናቸው፡፡” ካሉ በኋላ የዮናታንን በፌስቡ ከጓደኞቹ ጋር ለመወያየት የፃፋቸው ሃሳቦች ከጠቀሷቸው አለም አቀፍ የሽብር ድርጊቶች ጋር አንድ ማድረግ የሽብርተኝነት ድርጊትን ማቃለል እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም የፀረ ሽብር ህጉ ህገመንግስቱን እና ኢትዮጵያ በአለም አቀፍ ደረጃ የተቀበለቻቸውን ህጎች እንደሚጥስም ተናግረዋል፡፡

ቀጥሎ ለመመስከር የቀረቡት ዶ/ር ዳኛቸው ናቸው፡፡ የህግ ፍልስፍና ትምህርት የተማሩ መሆናቸውን እና መምህር መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡ እአአ ከ 1948 ዓ. ም. ጀምሮ የተካሄዱ አራት አለም አቀፋዊ የሰብአዊ መብት ድንጋጌዎችን በመጥቀስ እነዚህ ድንጋጌዎች ማእከል ያደረጉት የመናገር መብትን መሆኑን እንዲሁም ንግግር በይዘቱ እንደማይፈተሽ እና ማንም ዜጋ ሃሳብ የማዋቀር መብት እንዳለው ድንጋጌዎቹ በግልፅ ያሰፈሩት ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰዋል -ዶ/ር ዳኛቸው፡፡ እነዚህን ህጎች ኢትዮጵያ ከመቀበል ባለፈ ከመጀመሪያው ጀምሮ በማርቀቁ ሂደት ተሳታፊም እንደነበረች ገልፀዋል። ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት መኖር ለመንግስት ቅቡልነትን እንደሚያመጣ ዲሞክራሲም የሚለካው በዚህ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ “ፅሁፉን አይቼዋለሁ፡፡ እምነቱን አሳይቷል፡፡ የራስክን አይዲዎሎጂ ፃፍክ ነው የሚለው ክሱ፡፡ እኔ እዚህ ሃገር ከመጣሁ ስምንት አመት ሆኖኛል፡፡ ስምንት አመት ሙሉ የራሴን አይዲዮሎጂ መንግስትን እየተቃወምኩ ስፅፍ ነበር፡፡ አልታሰርኩም፡፡ እሱም መታሰር አልነበረበትም፡፡ ልጁ [ዮናታን] የፃፈው ስህተት ሊሆን ይችላል፡፡ እኔ አስተማሪው ብሆን ፅሁፎቹን አይቼ ሲ እና ዲ ልሰጠው እችላለው፡፡ ያ ማለት ግን ወንጀል ሰርቷል ማለት አይደለም፡፡ መንግስት ጥሩ ነው የማለት መብት እንዳለ ሁሉ መንግስት ጥሩ አይደለም የማለት መብትም መኖር አለበት፡፡ ንግግር እና ፅሁፍን በመፍቀድ ከሚመጣው ችግር ንግግር እና ፅሁፍን በመገደብ የሚመጣው ችግር ይበልጣል፡፡” ካሉ በኋላ አቃቤ ህግ ፍርድ ቤት የመመስከር ፍቃድ አሎት ወይ ብሎ ሲጠይቃቸው፡ የትምህርት ዝግጅታቸውን፣ የስራ ልምዳቸውን እና ከዚህ ቀደምም በፍርድ ቤት መስክረው እንደሚያውቁ ገልፀው፤ ፍርድ ቤት ለመመስከር ፍቃድ የት እንደሚሰጥ አላውቅም፤ የሚሰጥ አካል አለ? የት ነው የማገኘው? በማለት በችሎት የነበረውን ሁሉ ፈገግ አሰኝተዋል፡፡

በሶስተኛ ደረጃ የሙያ ምስክርነቱን የሰጠው ጦማሪ እና አክቲቪስት በፍቃዱ ኃይሉ ነው፡፡ አቶ በፍቃዱ በማኔጅመንት ኢንፎርሜሽን ሲስተም የመጀመሪያ ዲግሪ እንዳለው፤ በመደበኛ (ህትመት እና ራዲዮ)፣ በማህበራዊ ሚዲያ እና የዜና ድህረገፆች ያለውን ልምድ ተናግሯል፡፡ማህበራዊ ሚዲያን ለመጠቀም እያንዳንዱ ሰው አካውንት ሊኖረው እንደሚገባ፤ የሚፅፉትንም ለማየት ጓደኞች ሊኖሩ እንደሚገቡ፤ መደበኛ ሚዲያ በዋነኝነት ለሽያጭ የሚቀርብ እና ከማህበራዊ ሚዲያ የበለጠ ተደራሾች እንደሚኖሩት፤ የዜና ድረገፅን ለመጠቀም ኢንርኔት አጠቃቀም ከማወቅ በዘለለ የግል አካውንት መፍጠር እንደማያስፈልግ ተናግሯል፡፡ ስለ ግለሰብ ፌስቡክ አካውንት፣ የፌስቡክ ፔጅ እና ፋን ፔጅ ልዩነቶች አስረድቷል፡፡ ዮናታን ስለፃፈው ፅሁፍ ተጠይቆ፤ ፅሁፎቹን እንደሚያውቃቸው፤ የፖለቲካ ፓርቲ አመራር እንደመሆኑ በኢትዮጵያ ወቅታዊ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ መወያየት እና መፃፍ እንደሚወድ ተናግሯል፡፡ በወቅቱ በነበረው ተቃውሞ በመንግስት የተገደሉ ወጣቶችን በመቃወም ሲፅፍ እንደነበር፤ እንዲያውም የወጣቶችን ደህንነት አደጋ ላይ ለመጣል እና ለማሸበር ሳይሆን በተቃራኒው የወጣቶችን ደህንነት ለማስጠበቅ ሲታገል እንደነበረ ተናግሯል አቶ በፍቃዱ፡፡

መንግስት ወጣቶችን ይገድላል ወይ ተብሎ ለአቶ በፍቃዱ ከዳኞች ለቀረበለት ጥያቄ፤ የመንግስት ፀጥታ አካላት ወጣቶችን መግደላቸው ዩንቨርሳል ትሩዝ እንደሆነ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ባወጣው ሪፓርት እንኳን 173 ሰዎች በፀጥታ አካላት መገደላቸው የተገለፀ መሆኑን ገልፇል። ይህን የሙያ ምስክርነት ለመስጠት ፈቃድ እንዳለው አቃቤ ህግ ጠይቆት፤ በአዲስ አበባ መስተዳደር በሚተላለፍ የራዲዮ ፕሮግራም ፕሮዳክሽን ማኔጀር ሆኖ እንሰራ፤ የውይይት የመፅሄት ዋና አዘጋጅ ሆኖ እንደሰራ፤ የሚፅፋቸው ፅሁፎች በአዘጋጅነት ይሰራበት የነበረውን የውይይት ጋዜጣን ጨምሮ የተለያዩ የህትመት ሚዲያዎች ላይ ይታተሙ እንደነበረ፣ ዞን ዘጠኝ የተባለ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ የሚጦምር ቡድን አባል እንደሆነ እና በቅርቡም አዲስ ስታንዳርድ የሚባል የመፅሄት ድረገፅ ላይ ፅሁፍ እንደታተመለት በመግለፅ ልምዱን በአጭሩ አብራርቷል፡፡ ይህም ልምዱ በጉዳዩ ላይ ለመመስከር ብቁ እንደሚያደርገው ተናግሮ፤ “ምስክርነት ለመስጠት ፈቃድ የሚሰጥ አካል የለም” ብሏል።

በመቀጠል የምስክርነት ቃላቸውን የሚሰጡት የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ አመራር የሆኑት አቶ ሙላቱ ገመቹ እና አቶ በቀለ ገርባ መሆናቸውን የተከሳሽ ጠበቃ አቶ ሽብሩ ተናግረው፤ በህዳር 2008 ዓ. ም. በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ አካባቢዎች የጀመረበትን ምክንያት እና የነበረውን ሁኔታ እንደሚያስረዱለት በጭብጥነት አሲዟል።

አቃቤህግ አሁንም በምስክሮቹ ላይ ተቃውሞ እንዳለው ለፍርድ ቤት አሳውቋል። ምስክሮቹ በህግ ጉዳይ ላይ መመስከር እንደማይችሉ እና ተገቢነት የሌለው መሆኑን በመናገር ምስክሮቹ እንዳይመሰክሩ ጠይቋል። የተከሳሽ ጠበቃ በበኩላቸው ይህን ጉዳይ በተመለከተ የምስክር መስማት ሂደቱ ሲጀምር ተመሳሳይ ጥያቄ አቃቤ ህግ አንስቶ ውሳኔ ተሰጥቶት ያለፈ ጉዳይ መሆኑን በተጨማሪም ምስክሮቹ የፓለቲካ ፓርቲ አመራር እንደመሆናቸው መጠን የሞያውቁትን የሰሙትን እና ያዩትን የሚመሰክሩ መሆናቸውን ገልፀው ምስክሮቹ የሚመሰክሩበትን ጭብጥ አግባብነት አስረድቷል። ዳኞች የግራቀኙን ክርክር አድምጠው የምስክሮቹን የሚመሰክሩበት ጭብጥ ይዘት በኋላ ላይ የሚመዘን በመሆኑ፤ ተከሳሽ እራሱን የመከላከል መብቱን ከመጠበቅ አንፃር ምስክሮቹ ቢሰሙ እንደሚሻል ጠቁመው የምስክሮቹ የመሰማት ሂደት እንዲቀጥል አዘዋል።

በቅድሚያ ለመመስከር የቀረቡት አቶ ሙላቱ ገመቹ ናቸው። አቶ ሙላቱ በ2008 ዓ. ም. ስለተነሳው ኦሮሚያ ስለተነሳው ተቃውሞ መንስኤ ስለሆነው ነገር ሲናገሩ፤ ከ2007 ዓ. ም. ምርጫ በኋላ ተቃውሞ እየበረከተ መምጣቱ፣ በኦፌኮ በኩል ሰላማዊ በሆነ መንገድ የተነሱትን ጥያቄዎች ለመመለስ ጥረት ሲደረግ እንደነበረ፣ ህዳር ወር ላይ 2008 ዓ. ም. በጊንጪ ከተማ የከተማው አስተዳደር 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የነበረውን ለመኖሪያ ቤት መስሪያ ወሰዱ መባሉን ተከትሎ ተማሪዎች ተቃውሞ እንደጀመሩ፤ ተማሪዎቹም ትምህርት ቤቱን ማስመለስ መቻላቸውን፤ የከተማው ስታዲየምም በተመሳሳይ መልኩ ተወስዶ ሲከፋፈሉት ተቃውሞ ተነስቶ እንደነበረ፤ የጭልሞ ጫካ ለባለሃብቶች መሸጥ ህዝብ ላይ ቅሬታ እንደፈጠረ እና ተቃውሞ እንደተነሳ፤ በዚህም ሳቢያ ከጊንጪ አካባቢ ብቻ 70 የኦፌኮ አባላት እንደታሰሩባቸው ገልፀዋል። ይሄ በእንዲህ እንዳለም የተቀናጀ ማስተር ፕላን የተባለው ፕላን ይተግበር መባሉ ብዙ ተቃውሞ ማስነሳቱን ገልፀዋል አቶ ሙላቱ።

ዳኞች ቀጣዩ ምስክር [አቶ በቀለ ገርባ] ጭብጡ ተመሳሳይ ስለሆነ አዲስ ነገር የሚመሰክሩት ከሌላ ባይሰሙ የሚል አስተያየት አቅርበው ነበር፤ ሆኖም ጠበቃ ሽብሩ ቀድመው ከመሰከሩት ምስክር [አቶ ሙላቱ ገመቹ] የተለየ ሚመሰክሩት እንዳለ በመናገራቸው ዳኞችም ባልተመሰከረበት የጭብጥ ሃሳብ ላይ ብቻ እንዲመሰክሩ አዘዋል።

በኦሮሚያ የተነሳው ተቃውሞ ማስተር ፕላኑን ተቃውመው እና ጭልሞ ጫካ ለግለሰቦች በመሰጠቱ ምክንያት እንጂ ዮናታን በፃፈው ፅሁፍ እንዳልሆነ አቶ በቀለ ገልፀዋል። በተጨማሪም ፅሁፎቹ ህዝቡ ያነሳው ተቃውሞ በሰላማዊ መንገድ እንዲመለስ ለማድረግ እንደሆነ ተናግረዋል።

የመከላከያ የምስክርነት ቃላቸውን ለመስጠት ቀርበው የነበሩት አባቱ ቀሲስ ተስፋዬ ረጋሳ፣ ጓደኛው አቶ ኤፍሬም፣ እህቱ ገዳምነሽ እንዲሁም ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ በእለቱ ችሎት ለመስማት ጊዜ ስላለቀ በቀጣይ ቀጠሮ እንዲቀርቡ ተነግሯቸዋል። በዛሬው ቀን ያልቀረቡት ምስክር ዶ/ር መረራ ጉዲና ያሉበትን ቦታ ጠበቃ ሽብሩ ከገለፁ በኋላ ዳኞች መጥሪያ እንዲደርሳቸው እና ፓሊስ በቀጣይ ቀጠሮ ቀን እንዲያቀርባቸው ትእዛዝ ሰጥተዋል።

ቀሪ መከላከያ ምስክሮችን ለመስማት ለጥር 18 ቀን 2009 ዓ. ም. ቀጠሮ ተይዟል።
ምንጭ፦ EHRP

ጋዜጠኛ ጌታቸው ሺፈራው ዋስትና ተከለከለ

ከሽብርተኝነት ክስ ነጻ ተብሎ በመደበኛ የወንጀለኛ መቅጫ ህጉ እንዲከላከል ብይን የተሰጠው የነገረ ኢትዮጵያ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ጌታቸው ሺፈራው የዋስትና ጥያቄው ውድቅ ተደርጎበታል፡፡
የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት ታህሳስ 13 ቀን 2009 ዓ.ም ጋዜጠኛ ጌታቸው ሺፈራው ከቀረበበት የሽብር ክስ ነጻ በማለት ክሱ ወደ መደበኛ የወንጀለኛ መቅጫ ህጉ ተቀይሮ አንቀጽ 257 (ሀ) ላይ የተመለከተውን እንዲከላከል ሲል ብይን መስጠቱ ይታወሳል፡፡

Getachew Shiferaw

ይህን ተከትሎ ጋዜጠኛ ጌታቸው ሺፈራው ቋሚ የመኖሪያ አድራሻ እንዳለውና ለአንድ አመት በእስር መቆየቱን በማንሳት አሁን ተከላከል የተባለበት የህግ ክፍል የዋስትና መብት እንደማይከለክል ጠቅሶ የዋስ መብቱ እንዲከበርለት ታህሳስ 19 ቀን 2009 ዓ.ም ፍርድ ቤቱን ጠይቆ ነበር፡፡ በዕለቱ አቃቤ ህግ ተከሳሹ በዋስ ቢወጣ ከሀገር ሊወጣ ስለሚችል የዋስትና ጥያቄው ውድቅ እንዲደረግለት ተቃውሞውን አሰምቷል፡፡

ፍርድ ቤቱ ታህሳስ 25 ቀን 2009 ዓ.ም በተነሳው የዋስትና ጥያቄ ላይ መርምሮ ብይን ሰጥቷል፡፡ በዚህ መሰረት ተከሳሹ በዋስ ቢወጣ ‹‹ከሀገር ሊወጣ እንደሚችል ግምት የተወሰደ በመሆኑ›› የዋስትና ጥያቄው ተቀባይነት አላገኘም ሲል ፍርድ ቤቱ ዋስትና ከልክሎታል፡፡ ፍርድ ቤቱ ተከሳሹ በዋስ ቢወጣ ከሀገር ሊወጣ ይችላል የሚለውን ግምት ለመውሰድ የቀረበለት ማስረጃ ስለመኖሩ በብይኑ ላይ አላመለከተም፤ አቃቤ ህግ ተቃውሞውን ባስመዘገበበት ወቅትም ተቃውሞውን በማስረጃ አስደግፎ አላቀረበም ነበር፡፡

‹‹ተከሳሹ ተከላከል የተባለበት የህግ አንቀጽ በመርህ ደረጃ ዋስትና ባያስከለክልም፣ በሁኔታ የሚከለከልበት ጊዜ ግን ስለመኖሩ ተመልክቷል፡፡ እኛም ይህን ተከሳሹ ከሀገር ሊወጣ ይችላል የሚለውን ሁኔታ አይተን በሙሉ ድምጽ ተከሳሹ ዋስትናው ይነፈግ ብለን ወስነናል›› ብሏል ችሎቱ የዳኞችን ውሳኔ በተመለከተ ሲገልጽ፡፡

ፍርድ ቤቱም መከላከያ ምስክሮችን ለመስማት ሌላ ተለዋጭ ቀጠሮ ለየካቲት 7 ቀን 2009 ዓ.ም ሰጥቷል፡፡
ምንጭ፦ EHRP

በዝዋይ ወህኒ ቤት እስር ላይ የነበረው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ አሁን የት እንዳለ አለመታወቁን ቤተሰቦቹ አስታወቁ

(አዲስ ሚዲያ) የፍትህ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ እና መስራች የነበረው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ባለፈው ህዳር 2007 ዓ.ም. በመንግሥት በተመሰረተበት ክስ የ3 ዓመት ፅኑ እስር ተፈርዶበት ዝዋይ ወህኒ ቤት የነበረ ቢሆንም፤ ከፋለፈው ማክሰኞ ህዳር 27 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ የነበረበት ዘዋይ ወህኒ ቤትን ጨምሮ ቃሊቲ፣ የአቃቂ ቂሊንጦ እና ሸዋ ሮቢት ወህኒ ቤት ጥበቃ ሰራተኞችና ኃላፊዎች፤ ጋዜጠኛ ተመስገን የት እንዳለ ከቤተሰቦቹ ለቀረበላቸው ጥያቄ በተጠቀሱት ወህኒ ቤቶች እንደሌለ በመግለፅ በአሁን ወቅት የት እንዳለ ግን እንደማያውቁ መናገራቸውን የጋዜጠኛው ቤተሰቦች ይፋ አድርገዋል፡፡

journalist-temesgen-desalegn

ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ፤ ፎቶ ከማኀበራዊ ገፅ

አዛውንቱ ወላጅ እናቱን ጨምሮ ሌሎች የጋዤተኛው ቤተሰቦችና ወዳጆች ቀደም ሲል ታስሮ የነበረበትን እና በፌደራል ደረጃ የሚታወቁ ወህኒ ቤቶች በሙሉ በመሄድ ያለበትን ሁኔታ ለማረጋገጥ ሙከራ ቢያደርጉም ሊያገኙት እንዳልቻሉ የተገለፀ ሲሆን፤ በተለይ በዕድሜ የገፉ አዛውንት ወላጅ እናቱ ወ/ሮ ፋንታዬ እርዳቸው በከፍተኛ ስጋትና ጭንቀት ላይ መሆናቸውን ምንጮች አስታውቀዋል፡፡ ጋዜጠኛው ቀደም ሲል በእስር ላይ እያለ በደረሰበት ህመም ምክንያት የህክምና ዕርዳታ ለማግኘት ጠይቆ በተደጋጋሚ መከልከሉ አይዘነጋም፡፡

የፌደራል አቃቤ ህግ ጋዜጠኛ ተመስገን በፍትህ ጋዜጣ ላይ በፃፋቸው ፅሑፎችን ዋቢ በማድረግ በመሰረተበት ክስ የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት 3 ዓመት ፅኑ እስራት እና የፍትህ ጋዜጣ አሳታሚ ማስተዋል ህትመትና ማስታወቂያ ድርጅትደግሞ 10 ሺህ ብር እንዲቀጣ መበየኑ ይታወሳል፡፡ጋዜጠኛ ተመስገን ከመታሰሩ በፊት መንግሥት ይፈፅማል ያላቸው የመብት ረገጣዎችና ብልሹ አሰራሮችን በግልፅ በመተቸት ይታወቃል፡፡

ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝን ጨምሮ በገዥው የኢህአዴግ መንግሥት 11 ጋዜጠኞችና 1 ብሎገር ኢትዮጵያውያን እንዲሁም 3 የውጭ ዜጋ ጋዜጠኖች በአጠቃላይ 15 ጋዜጠኞችና ብሎገር በእስር ላይ ይገኛሉ፡፡ በተለይ በእስር ከሚገኙ ጋዜጠኞች መካከል ኢትዮጵያውያኑ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፣ ውብሸት ታዬ፣ ተመስገን ደሳለኝ፣ ጌታቸው ሽፈራው፣ ፈቃዱ ምርከና፣ጌታቸው ወርቁ፣ አናኒያ ሶሪ፣ ኤልያስ ገብሩ፣ በፈቃዱ ኃይሉ፣ ከድር መሐመድ፣ ዳርሰማ ሶሪ እና የደ ብርሃን ብሎገር ዘለዓለም ወርቅአገኘሁ ተጠቃሾች ናቸው፡፡

እንደ ሀገር ውስጥ የሰብዓዊና የፕሬስ ነፃነት መብት ተሟጋቾች እና እንደ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች መረጃ ከሆነ፣ ኢትዮጵያ በአሁን ወቅት የፕሬስ ነፃናት ከሌለባቸው የዓለም ሀገራት ተርታ በቀዳሚነት ከሚጠቀሱት አንዷ ስትሆን፤ በርካታ ጋዜጠኞችን በማሰር በአፍሪካ ከጎረቤት ኤርትራ ቀጥሎ በሁለተኛ ደረጃ ላይ የምትገኝ ሀገር ነች፡፡

እውቁ ፖለቲከኛ እና የኦፌኮ/መድረክ ከፍተኛ አመራር ዶ/ር መረራ ጉዲና ታሰሩ

(አዲስ ሚዲያ)የኦሮሞ ፌደራሊስት ሊቀመንበር እና የኢትዮጵ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንደነግ ግንባር (መድረክ) ምክትል ሊቀመንበር የሆኑት ዶ/ር መረራ ጉዲና ታሰሩ፡፡ ዶ/ር መረራ የታሰሩት በቤልጂየም ብራሰልስ የአውሮፓ ህብረት የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ በተጋበዙት መሰረት ንግግር አድርገው ረቡዕ ህዳር 21 ቀን 2009 ዓ.ም. ወደ ሀገር ቤት ሲመለሱ አዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርሱ በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች መታሰራቸው ታውቋል፡፡ ዶ/ር መረራ የታሰሩት አብረዋቸው ከነበሩ ከሁለት የቅርብ ቤተሰቦቻቸው ጋር እንደነበርም ታውቋል፡፡

dr-merera-gudina-aau

ገዥው የህወሓት/ኢህአዴግ መንግሥት በበኩሉ ዶክተር መረራ የታሰሩት “በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መመሪያ ቁጥር አንድ አንቀጽ 2 ላይ የተመለከተውን መመሪያ ተላልፈው በመገኘታቸው እና ከአርበኞች ግንቦት 7 መሪ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ጋር ተገናኝተው መግለጫ ሰጥተዋል“ በሚል መሆኑን በልሳኑ ፋና ብሮድካሲቲንግ ኮርፖሬት ዘገባ ይፋ አድርጓል፡፡

መንግሥት ባለፈው ህዳር 2008 ዓ.ም. የተቀሰቀሰውን የኦሮሚያ ክልል የፀረ አገዛዝ ሰላማዊ ህዝባዊ ተቃውሞ፤ በተመሳሳይ መልኩ ሐምሌ 2008 ዓ.ም. ጀምሮ በአማራ ክልል እና በደቡብብ ክልል ኮንሶ የተዛመተውን ሰላማዊ ህዝባዊ ተቃውሞን ተከትሎ ተከትሎ ከ1400 በላይ ዜጎች ሲገደሉ ከአንድ ሺህ ያላነሱ በፀጥታ ኃይሎች ወታደራዊ ርምጃ የቆሰሉ ሲሆን፤ ከ50 ሺህ ያላነሱ ዜጎች በእስር ላይ እንደሚገኙ የፖሊስ መረጃዎችና የሰብዓዊ መብት አራማጆች መረጃ አመልክቷል፡፡የህወሓት/ኢህአዴግ ደጋፊዎችም ዶ/ር መረራ በአውሮፓ ፓርላማ ንግግር ማድረጋቸውን ተከትሎ እንደሚታሰሩ የሚያመለክት ቅስቀሳ ሲያደሩ እንደነበረም መረጃዎች አመልክተዋል፡፡

በተለይ ከአንድ ዓመት በላይ የዘለቀውን የፀረ አገዛዝ ህዝባዊ ተቃውሞውን ተከትሎ ገዥው መንግሥት መስከረም 28 ቀን 2009 ኣ.ም ጀምሮ ለ6 ወራት ተግባረዊ የሚደረግ የአስቸኳይ ዚጌ አዋጅ አውጥቷል፡፡ አዋጁ ተግባራዊ ከተደረገበት ቀን ጀምሮ ጋዜጠኞች፣ የተለያዩ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና አባላት፣ የመብት አራማጆችንና ሲቭል ማኀበረሰቡን ጨምሮ በአንድ ወር ብቻ ከ11,706 ማሰሩን ይፋ ማድረጉ አይዘነጋም፡፡

ዶ/ር መረራ ጉዲና በቅርቡ በጡረታ እንዲሰናበቱ ከመደረጋቸው በፊት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህርነት ለ28 ዓመታት ያገለገሉና የፓርላማ አባል የነበሩ ሲሆን፤ ላለፉት 20 ዓመታትም በሀገሪቱ ፖለቲካ ባላቸው ተሳትፎ በበርካታ ኢትዮጵያውያን ዘንድ የሚታወቁና ከፍተኛ ተቀባይነት እንዳላቸው ይታወቃል፡፡ ቀደም ሲል የፓርቲያቸው ምክትል ሊቀመንበር አቶ በቀለ ገርባ፣ ዋና ፀሐፊያቸው አቶ ደጀኔ ጣፋ፣ የወጣቶች ጉዳይ ኃላፊ አቶ ደስታ ዲንቃን ጨምሮ በርካታ አመራሮችና አባሎቻቸው ከአንድ ዓመት በፊት መታሰራቸው ይታወቃል፡፡