Category Archives: News

የኢትዮ ምህዳር ጋዜጣ ቢሮ ታሸገ

ethi-mihedarየኢትዮ ምህዳር ጋዜጣ ዛሬ መስከረም 23 ቀን 2007 ዓ.ም ለምሳ ከቢሮ እንደወጡ መታሸጉን ዋና አዘጋጁ አቶ ጌታቸው ወርቁ ለፍኖተ ነፃነት ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ገለጹ፡፡ እንደ አቶ ጌታቸው ገለፃ ህትመት ካቋረጥንበት ነሐሴ 14 ቀን ጀምሮ ወደ ተለያዩ ማተሚያ ቤቶች ሄደን ለማተም ጥረት ብናደርግም ሊሳካልን አልቻለም፡፡ ነገር ግን ከ2 ሳምንት በፊት ማተሚያ ቤት አግኝተን ዝግጅታችንን ካጠናቀቅን በኋላ ወደ ህትመት ልንገባ ስንል ፊውዝ ተቃጠለ በሚል ሰበብ ልትታተም አልቻለችም፡፡ አሁንም ወደ ሌላ ማተሚያ ቤት በመሄድ ለማተም ተስማምተው ዝግጅት በምናደርግበት ሰዓት ከማዕከላዊ ተደውሎ ትፈለጋላችሁ እንድትመጡ የሚል የስልክ መልዕክት እንደደረሳቸው አቶ ጌታቸው ገልጸው፣ ለምን እንደተፈለጉ ቢጠይቁም በስልክ አልነግርክም ማዕከላዊ ቢሮ ቁጥር 75 አቶ አለበል ብለህ እንድትመጣ እንደተባሉ እሳቸውም ሰኞ እንደሚመጡ ለደዋዩ እንደገለጹላቸው ነገር ግን በዛሬው ዕለት ለምሳ እንደወጡ ቢሮዋቸው እንደታሸገ ለፍኖተ ነፃነት ገልጸዋል፡፡

የፖለቲካ አመራሮቹ ችሎት ያለ ተከላካይ ጠበቃ ሲታይ፤ቀጣይ ቀጠሯቸው ግልፅ አይደለም

ዛሬ መስከረም 22 ቀን 2007 ዓ.ም. ፒያሳ አራዳ በሚገኘው የፌደራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት የፖለቲካ  ፓርቲ አመራሮች ጉዳይ በዝግ ችከሎት ያለ ተከላካይ ጠበቃ ቀጠሮ መስጠቱ ተጠቆመ፡፡ የፖለቲካ አመራሮቹ አቶ ሀብታሙ አያሌው የአንድነት ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ፣ አቶ ዳንኤል ሺበሺ የአንድነት ፓርቲ ምክትል የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ፣ አቶ አብርሃ ደስታ የመቀሌ ዩኒቨርስቲ መምህርና የአረና ፓርቲ ምክትል የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ እንዲሁም አቶ የሺዋስ አሰፋ የሰማያዊ ፓርቲ ምክትል የምክር ቤቱ ሰብሳቢ ከተከላካይ ጠበቆቻቸው ጋር ሳይገናኙ ከቀጠሮ ሰዓታቸው አርፍደው ከቀኑ 10 እና 11 ሰዓት ፍርድ ቤት መቅረባቸውን ነገረ ኢትዮጵያ ዘግቧል፡፡

detained politiciansበነበረው የፍርድ ቤት ችሎት ተከላካይ ጠበቃ ደንበኞቻቸውን ህጉ በሚፈቅደው መሰረት በማዕከላዊ ሄደው መጎብኘትና መነጋገር ቢፈልጉም፤ በፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ማዕከል “ማዕከላዊ” ፖሊስ ስላልተፈቀደላቸው ፍርድ ቤት መገኘቱ ለፕሮፖጋንዳ ካልሆነ ከህግ አግባብ ትርጉም ስለሌለው እንደማይገኙ አስቀድመው ማሳወቃቸው ተጠቁሟል፡፡ በችሎትም ቤተሰብ፣ ጋዜጠኛ፣ ዲፕሎማቶች እና ወዳጅ ዘመድ እንዳይከታተል መከልከሉም ታውቋል፡፡ የእስረኞቹ ቀጣይ ቀጠሮ መቼ እንደሆነ እስካሁን ከፍርድ ቤቱ ማግኘት ባይቻልም፤ እንደ ነገረ ኢትዮጵያ ዘገባ ከሆነ የማዕከላዊ ምርመራ ኃላፊ አቶ ተክላይ ሹመት ተጠርጣሪዎቹ የተቀጠሩት ለጥቅምት 20 ቀን 2007 ዓ.ም. ሲሉ፤ ሌላ ፖሊስ ደግሞ ለጥቅምት 22 ቀን 2007 ዓ.ም. ነው የሚል ጥቆማ መስጠታቸውን የነገረ ኢትዮጵያ ጋዜጣ ምንጮች አስታውቀዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ እስረኞቹ እስካሁን በነበረው ምርመራ ፖሊስ ምንም ዓይነት ለወንጀል ክስ የሚያበቃ መረጃ ባለማግኘቱ፤ ወደ ኃይል እርምጃ በመሄድ ፖሊስ የሚፈልገውን ቃል እስረኞቹ ያልፈፀሙትን አስገድዶ የእምነት ቃል እንዳስፈረማቸው የማዕከላዊ ምንጮች አስታውቀዋል፡፡ ይሄም ለህዝቡና ለመገናኛ ብዙኃን እንዳይገለፅና ፍርድ ቤትም በቅሬታ መልክ እንዳይቀርብ ስለተፈለገ ነው ተከላካይ ጠበቆቹ እንዳይጎበኙ የተከለከሉት ሲሉ ምንጮች አስታውቀዋል፡፡  በዚህም የዛሬው ችሎት ያለጠበቃ ጭምር በዝግ ችሎት መካሄዱ የተጠቆመ ሲሆን፤ የቀጠሯቸው ቀንም ከላይ ከተጠቀሰው ውጭ እስካሁን ትክክለኛውን ከፍርድ ቤቱ ማረጋገጥ እንዳልተቻለ መረጃዎእ አመልክተዋል፡፡ ችሎቱን ለመታደም ወደ ስፍራው ያቀኑ ሰዎችም ፍርድ ቤቱ ግቢ ሲገቡ ከወትሮ በተለየ በፖሊሶች ከፍተኛ ፍተሻ፣ እንግልትና ወከባ እንደተፈፀመባቸው  የዓይን እማኞች ገልፀዋል፡፡

አሜሪካ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ተኩስ ተከፈተ

ዛሬ ሰኞ መስከርም 19 ቀን 2007 ዓ.ም. አሜሪካ ዋሸንግተን ዲሲ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ተኩስ ተከፈተ፡፡ በዋሸንገተን ዲሲ አካባቢ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የኢትዮጵያ መንግስት በዜጎቹ ላይ የፈፀመውን እና እየፈፀመ ያለውን ድርጊት የሚገልፅ ደብዳቤ እና ኮከብ የሊለበትን የኢትዮጵያ ሰንደቅዓላማ ይዘው ወደ ኤምባሲው ቅጥር ግቢ ሲገቡ የኢትዮጵያ ኤምባሲ የጥበቃ ኃላፊ እንደሆኑ የሚነገርላቸው አቶ ሰለሞን ወዲ ወይኒ ሁለት ጥይት መተኮሳቸውን እና አንዱ ጥይት ከኤምባሲው ውጭ በሚገኝ አንድ ተሸከርካሪ መኪና ላይ ጉዳት ማድረሱ ተጠቁሟል፡፡

ethio usaበኤምባሲው የጥበቃ ኃላፊ በግቢው የህወሓት ተወካይም ሆነው በኤምባሲው የሚከናወኑ እንቅስቃሴዎችንም በተጓዳኝ እንደሚቆጣጠሩ የተነገረላቸው ሲሆን፤ ኢትዮጵያውያኑ ተቃውሞ አቅራቢዎች ላይ በፈፀሙት ተኩስ አካባቢውን በመረበሻቸው የከተማው ፖሊስ ወደ ኤምባሲው ኢንተርናሽናል ድራይቭ የሚባለውን መንገድ ለተወሰነ ጊዜ የዘጋ ሲሆን ፤ በተመሳሳይም የኢትዮጵያ ኤምባሲ፣ም አገልግሎት እንዳይሰጥ መደረጉ የተለያጠዩ ዓለም አቀፍ የዜና ምንጮች ከአካባቢው ዘግበዋል፡፡ እንደሮይተርስ ዘገባ ከሆነ ደግሞ ጥይት የተኮሱት አቶ ሰለሞን በአሜሪካ ፌደራል ፖሊስ ምርመራ ቁጥጥር ስር መዋላቸው ተጠቅሷል፡፡

ወደ ኤምባሲው ገብተው የነበሩት ኢትዮጵያውያንም በአሁን ወቅት የኢህአዴግ  መንግስት የሚጠቀምበትን ባለኮከብ ሰንደቅዓላማ በማውረድ የቀድሞውን ታሪካዊ የኢትዮጵያ ሰንደቅዓላማ ለተወሰነ ጊዜ ሰቅለው ከግቢ እስኪወጡ ማውለብለባቸው በስፍራው የነበሩ የዓይን እማኞች ጠቁመዋል፡፡ የኤባሲው ባለሙሉ ስልጣን አምባሰደር ግርማ ብሩ ተኩስ የከፈቱትን ግለሰብ ለመደበቅ ሲሚክሩ የሚያሳይ የካሜራ ምስልም ታይቷል፡፡ ክስተቱንም ሮይተርስ፣ ፎክስ ኒውስና ኢሳትን ጨምሮ  የተለያዩ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ከስፍራው የዘገቡት ሲሆን፤ የኢህአዴግ መንግስት በዜጎች ላይ የሚፈፅመውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ እስር፣ ግድያና እንግልት ተቃውሞ በተለያየ የአውሮፓና አሜሪካ ከተሞች በተከታታይ መከናወኑ የሚታወስ ነው፡፡

የፌደራሉ ከፍተኛው ፍርድ ቤት በጋዜጠኞችና ብሎገሮች ጉዳይ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጠ

የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት ዛሬ ሐምሌ 28 ቀን 2006 ዓ.ም. በዋለው ችሎት የፌደራሉ አቃቤ ህግ በሽብርተኝነት በሶሊያና ሽመልስ የክስ መዝገብ ክስ የመሰረተባቸው ዘጠኝ ጋዜጠኞችና የኢትዮጵያ ዞን 9 ብሎገሮች ለነሐሴ 14 ቀን 2006 ዓ.ም. ከጠዋቱ 3 ሰዓት ተለዋጭ ቀነ ቀጠሮ ሰጠ፡፡ ጋዜጠኛ አስማማው ኃይለጊዮርጊስ፣ ተስፋዓለም ወልደየስ እና ኤዶም ካሳዬ እንዲሁም የኢትዮጵያ ዞን 9 ድህረ-ገፅ ብሎገሮች በፈቃዱ ኃይሉ፣ ዘለዓለም ክብረት፣ማህሌት ፋንታሁን፣ አጥናፍ ብርሃኔ፣ አቤል ዋበላ እና ናትናኤል ፈለቀ በአካል ፍርድ ቤት የቀረቡ ሲሆን፤ 1ኛ ተከሳሽ ሶሊያና ሽመልስ በአካል ልትቀርብ ስላልቻለች በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋዜጣ ጥሪ እንዲደረግ የተሰጠው ትዕዛዝ አቃቤ ህጉ ማስፈፀም ባለመቻሉ ዛሬ ክሳቸው ሊታይ ባለመቻሉ ፍርድ ቤቱ ተለዋጭ ቀነ ቀጠሮ ሰጥቷል፡:

zonይህ በእንዲህ እንዳለ ተከላካይ ጠበቆች በአቃቤ ህግ የተመሰረተው ክስ የህገ መንግስት ጉዳይ ስለሆነ ፤ለህግ መንግስት አጣሪ ጉባዔ እንዲመራ፣አቃቤ ህግ ያቀረበው ክስ የህግ ስነስርዓቱን ባለመከተሉና ግልፅ ባለመሆኑ መቃወሚያ በማቅረብ ተከሳሾች በነፃ እንዲሰናበቱ አሊያም የዋስትና መብታቸው እንዲከበር በሚል ያቀረቡት ክርክር ከፍርድ ቤቱ መቅረፀ- ድምፅ ተገልብጦ አልቀረበም በሚል ፍርድ ቤቱ ብይን ሳይሰጥ ቀርቷል፡፡

ጉዳያቸው ክስ ሳይመሰረት ከ10 ወራት በላይ እንደፈጀ የሚነገርላቸውና እስካሁን ለህዝብ ይፋ ያልተደረገ የበርካታ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ጉዳይም በዕለቱ ችሎት ውሎ ነበር፡፡ በዚህም 8ቱ ከአዲስ አበባ ወደ ወልቂጤ፣ ያለፈው ጥቅምት 2006 ዓ.ም.ለአረፋ በዓል ሲሄዱ፣8ቱ ደግሞ አዲስ አበባ እያሉ በፀጥታ ኃይሎች ተይዘው በቁጥጥር ስር የዋሉት የነ ኤልያስ ከድር የክስ መዝገብ የሚገኙ 15 ወንዶችና አንዲት ሴት በአጠቃላይ 16 ወጣቶች ጉዳይ ለነሐሴ 5 ቀን 2006 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀነ ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡
በተያያዘ ወቅት እንደታሰሩ የሚነገርላቸውና ከአዳማ 4 ወንድ እና አንዲት ሴት በአጠቃላይ 5 ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች በፀጥታ ኃሎች በቁጥጥር ስር የዋሉት ለነሐሴ 12 ቀን 2006 ዓ..ም. ተለዋጭ ቀነቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡ በዚህ ጉዳይ ከተከላካይ ጠበቃ በተለይም በአንድ ወንድ እና በአንዲት ሴት ተጠርጣሪ ላይ በማረሚያ ቤቱ አያያዝ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተፈፅሟል በሚል ቅሬታ ቢቀርብም፤ ፍርድ ቤቱ በቀጠሮ ቀን መርምሮ ውሳኔ እንደሚሰጥ አስታውቋል፡፡ ፍርድ ቤቱም መቼ እንደሚጀመር ባይገልፅም ከነሐሴ 14 ቀን 2006 ዓ.ም. በኋላ ዝግ እንደሚሆን አስታውቋል፡፡

ዞን 9 ብሎገሮች ሌላ ቀጠሮ ተጠየቀባቸው፤ የፖሊስየ28 ተጨማሪ ቀናት ጥያቄ ውድቅ ተደርጓል

የፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ጠረጠርኳቸው ያላቸውን 9 ጋዜጠኞች እና ብሎገሮች ሚያዝያ 2006 ዓ.ም.ቢያስርም እስካሁን ምንም ዓይነት ህጋዊ ክስ ሳይመሰርት፤ ዛሬ ሰኔ 22 ቀን 2006ዓ.ም. በድጋሚ ተለዋጭ ቀነ ቀጠሮ ጠይቋል፡፡ ፖሊስ ለፌደራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ 1ኛ ወንጀል ችሎት ዛሬ ቀጠሮ የነበራቸውን እና በማዕከላዊ ያሰራቸውን የዞን 9 ብሎገሮች መካከል በፍቃዱ ኃይሉ፣ ማህሌት ፋንታሁን እና አቤል ዋበላን ይዞ ቢቀርብም፤ እንደተለመደው የቴክኒክ ምርመራዬን አልጨረስኩም፣ ከተሰከሳሾች የተገኙ መረጃዎች ተተርጉመው አላለቁም፣…የሚሉ ምክንያቶችን በመጥቀስ ተጨማሪ የ28 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ እንዲሰጠው መጠየቁ ተሰምቷል፡፡

hgtፍርድ ቤቱ እስካሁን የተሰጠው ጊዜ በቂ ነው በማለት የተጠየቀውን የ28 ቀናት ውድቅ ቢያደርግም፤ ፖሊስ ምርመራው አጠናቆ እንዲቀርብ የ14 ቀናት ጊዜ በመስጠት ለሐምሌ 6 ቀን 2006ዓ.ም.ተለዋጭ ቀነ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ይሁን እንጂ ዕለቱ እሁድ ቀን የሚውል በመሆኑ እና መዝገቡ ከእንግዲህ በተዘዋዋሪ ተረኛ ዳኛ ሳይሆን በመደበኛ ችሎት መታየት ስላለበት ለሰኞ ሐምሌ 7 ቀን 2006 ዓ.ም. ከቀኑ 8፡00ሰዓት ተለዋጭ ቀነ ቀጠሮ መሰጠቱን ከተከላካይ ጠበቃቸው አቶ አምሃ መኮንን መረዳት ተችሏል፡፡ ጉዳዩ ሲታይ የነበረው ከሌሎች ቀናት በተለየ ዛሬ ቤተሰብም በችሎቱ ላይ እንዳይታደም ተከልክሏል፡፡

በፍርድ ቤቱ ግቢ በርካታ የእስረኞቹ ቤተሰቦች፣ ወዳጅ ዘመዶች፣ ዓለም አቀፍ ዲፕሎማቶች እና ጋዜጠኞች ቢገኙም አንዳቸውም ችሎቱን እንዲከታተሉ አልተፈቀደም ነበር፡፡ ፖሊስ ያሰራቸውን ተጠርጣሪዎች ይዞ ወደ ችሎት ሲገባ በፍርድ ቤቱ ግቢ ችሎቱን ለመታደም ከመጡት መካከል ዮናታን ተስፋዬ እና ምኞት የሚባሉ ወጣቶችን በሞባይል ፎቶ ለማንሳት ሞክራችኋል በሚል ወደ ማዕከላዊ ይዟቸው የሄዱ ሲሆን፤ ከሰዓታት በኋላ መለቀቃቸው ታውቋል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ እስካሁን ምንም ክስ ሳይመሰረትባቸው በእስር ላይ የሚገኙት ቀሪዎቹ 6ቱ ጋዜጠኞች እና ብሎገሮች የፊታችን ሐምሌ 5 ቀን 2006 ዓ.ም. ጠዋት ቀነ ቀጠሮ እንዳላቸው ይታወቃል፡፡