Tag Archives: Ethiopian Democracy

በእስር ላይ የሚገኙት 10 ወጣቶች የሽብርተኝነት ክስ ተመሰረተባቸው

  • አብርሃ ደስታ ከሁለት ድርጅቶች ጋር ግንኙነት አለው የሚል ክስ ተመስርቶበታል
  • ወደ አዲስ አበባ ማረሚያ ቤት እንዲዘዋወሩ ታዟል

የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አራተኛ ወንጀል ችሎት ጥቅምት 21 ቀን 2007 ዓ.ም ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት አካባቢ በተሰየመው ችሎት 10 ተከሳሾች በፌደራል አቃቢ ህግ በይፋ ክስ ተመሰረተባቸው፡፡ ተጠርጣሪዎቹ ከ100 ገጽ በላይ የክስ ቻርጅ የተነበበላቸው ሲሆን ከክስ ቻርጁ ጋር ከ300 ገጽ በላይ የምርመራ ሰነድ ቀርቦባቸዋል፡፡

የክሱ መዝገብ የተከፈተው ዘላለም ወርቃገኘሁ በተባለውና ‹‹የግንቦት 7 አመራር ነው፡፡›› ተብሎ ክስ በተመሰረተበት ግለሰብ ሲሆን በዚህ የክስ መዝገብ የተካተቱትም፡-

1ኛ ተከሳሽ ዘላለም ወርቃገኘሁ
2ኛ ተከሳሽ ሀብታሙ አያሌው
3ኛ ተከሳሽ ዳንኤል ሺበሺ
4ኛ ተከሳሽ አብርሃ ደስታ

5ኛ ተከሳሽ የሽዋስ አሰፋ
6ኛ ተከሳሽ ዮናታን ወልዴ
7ኛ ተከሳሽ አብርሃም ሰለሞን
8ኛ ተከሳሽ ሰለሞን ግርማ
9ኛ ተከሳሽ ብርሃኑ ደጉ
10ኛ ተከሳሽ ተስፋዬ ተፈሪ ናቸው

ለሁሉም ተከሳሾች ከዛሬ በፊት ክስ እንዳልደረሳቸውና ዛሬ ፍርድ ቤት ውስጥ እንደተሰጣቸው ታውቋል፡፡ በችሎቱ 6ኛ ተከሳሽ ከሆነው ዮናታን ወልዴ በስተቀር ሁሉም ያለ ጠበቃ የቀረቡ ሲሆን ጠበቃዎቹ ያልቀረቡበት ምክንያትም ጠበቆቹ ደምበኞቻቸው የሚቀርቡበት ቦታና ጊዜ ስላልተነገራቸው እንዲሁም ቀደም ብለው እንዳይገናኙ በመደረጋቸው መሆኑን አቶ ኃብታሙ አያሌው ችሎቱ ላይ ተናግሯል፡፡

politician prisonersከሳሹ የፌደራል አቃቢ ህግ በ1996 የወጣው የወንጀል ህግ እና የጸረ ሽብር ህግ ጠቅሶ ክስ ያቀረበ ሲሆን ክሶቹ በሁለት ዋና ዋና ጭብጦች ቀርበዋል፡፡ የመጀመሪያው ጭብጥ ‹‹ከሽብርተኛ ቡድኖች ጋር በጋራ በመስራት›› የሚል ሲሆን ‹‹ህገ መንግስቱንና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን በኃይል ለመናድ፣ የመንግስትን መሰረተ ልማት በማፈራረስ፣ ህዝብን ለአመጸ በማነሳሳት መንግስትን መለወጥ አላማው አድርጎ ከሚሰራውና ራሱን ግንቦት 7 ብሎ ከሚጠራው ቡድን ጋር አባል በመሆንና በወንጀል ድርጊቶች በመሳተፍ›› በሚል ቀርቧል፡፡

ሁለተኛው የክስ ጭብጥ ‹‹የሽብር ቡድን አመራር በመሆን›› የሚል ሲሆን በተለይም የአንደኛ ተከሳሽ ዘላለም ወርቃገኘሁ ‹‹የሽብር ቡድኑ አመራር በመሆንና አባል በመመልመል›› በሚል የክስ ጭብጥ ቀርቦበታልል፡፡

ከ2-5ኛ የክስ መዝገብ የሚገኙት ማለትም ሀብታሙ አያሌው፣ ዳንኤል ሺበሽ፣ አብርሃ ደስታና የሸዋስ አሰፋ ‹‹ህጋዊ የፖለቲካ ፓርቲን ከለላ በማድረግ ግንቦት 7 የተባለውን የሽብር ቡድን አላማ ለማሳካት ተንቀሳቅሰዋል፡፡ ፋሲል የኔ ዓለምና ሌሎች የሽብር ቡድኑ አባላት ጋር በስልክ በመነጋገርና በማህበራዊ ድህረ ገጸ የተለያዩ መልዕክቶችን ተለዋውጠዋል›› የሚል ክስ ቀርቦባቸዋል፡፡ አብርሃ ደስታ ከግንቦት 7 በተጨማሪ ‹‹ደምኢት የተባለ ቡድን አባል ነው፡፡›› የሚል ክስ ቀርቦበታል፡፡

በስተመጨረሻም ፍርድ ቤቱ ሁለት ጉዳዮች ላይ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ አንደኛው ረቡዕ ጥቅምት 26/2007 ዓ.ም 3 ሰዓት ተከሳሾቹ ዋስትና ይሰጣቸው አይሰጣቸው በሚለው ጉዳይ ላይ ፍርድ ቤቱ ከተከሳሾቹ ጠበቆች ጋር ተማክሮ ውሳኔ ይሰጣል ተብሏል፡፡ በሁለተኛነት ተጠርጣሪዎቹ ባቀረቡት አቤቱታ መሰረት ቀደም ሲል ለአራት ወራት ወደቆዩበት ማዕከላዊ እስር ቤት እንዳይመለሱ ፍርድ ቤቱን ስለጠየቁ ፍርድ ቤቱ በአዲስ አበባ ማረሚያ ቤት (3ኛ) እንዲቆዩ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

ተከሳሾቹ ትናንት ጥቅምት 20/2007 ዓ.ም አራዳ ምድብ ችሎት ይቀርባሉ ተብሎ የነበር ቢሆንም ሳይቀርቡ ቀርተዋል፡፡ በተመሳሳይ ዛሬ ጥቅምት 21/2007 ዓ.ም ጠዋት ወደ ልደታ ፍርድ ቤት ተወስደው የነበረ ቢሆንም እንደገና ወደማዕከላዊ ተመልሰው ከሰዓት እንዲቀርቡ ተደርገዋል፡፡

ምንጭ፡- ነገረ-ኢትዮጵያ

 

ወጣቶቹ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች በድብቅ ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ተደረገ

ከአራት ወራት በፊት በሽብር ስም በአዲስ አበባ የፌደራሉ ወንጀል ምርመራ “ማዕከላዊ” የሚገኙት የአንድነት ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች አቶ አቶ ሀብታሙ አያሌው፣ ዳንኤል ሺበሺ፤ የሰማያዊ እና የአረና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች አቶ የሺዋስ አሰፋና አቶ አብርሃ ደስታ ዛሬ ጥቅምት 20 ቀን 2007 ዓ.ም. ከሰዓት በድብቅ ልደታ ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ መደረጋቸውንና ነገ ጠዋት በድጋሚ ልደታ ፍርድ እንደሚቀርቡ የፍኖተ ነፃነት ዘገባ ያስረዳል፡፡politician prisoners

የህሊና እስረኞቹ እንደተለመደው አራዳ ፍርድ ቤት ይቀርባሉ በሚል የትግል አጋሮችቸው እና ደጋፊዎቻቸውና ጋዜጠኞች ከቀኑ 7 ሰዓት ጀምሮ እስከ 11፡30 በቀጠሮው ስፍራ ቢጠብቁም፤ ፖሊስ በድብቅ ልደታ ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ማድረጉ ተሰምቷል፡፡ ታሳሪዎቹ ልደታ ፍርድ ቤት እንደሚገኙ መረጃ የደረሳቸው የአንድነት ፓርቲ አመራሮች በስፍራው ሲደርሱ አቶ  ሀብታሙ አያሌው፣አቶ ዳንኤል ሺበሺ፣አቶ የሺዋስ አሰፋና አቶ አብርሃ ደስታ በመኪና ውስጥ ሆነው ወደ ማዕከላዊ ሲወሰዱ መመልከታቸውን ተናግረዋል፡፡ ቀደም ብሎም የልደታው ፍርድ ቤት “ጉዳዩን የሚያይ ዳኛ የለም” በማለት ለነገ ጠዋት ጥቅምት 21 ቀን 2007 ዓ.ም ቀጠሮ መሰጠቱም ተጠቁሟል፡፡

ምንጭ፡- ፍኖተ ነፃነት

 

ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በተመሰረተበት ክስ 3 ዓመት ፅኑ እስራት ተፈረደበት

የቀድሞ የፍትህ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅና መስራች፣ የአዲስ ታየምስ መፅሔት፣ የልዕልና ጋዜጣ በመጨረሻም የፋክት መፅሔት ባልደረባና አዘጋጅ የሆነው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በተመሰረተበትና ጥፋተኛ በተባለበት 3 ክሶች መካከል በአንዱ ክስ ብቻ የ3 ዓመት ፅኑ እስራት ተፈረደበት፡፡ጋዜጠኛው በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቃቤ ህግ በመሰረተበት ክስ ጥፋተኛ የሚል ብይን ከሰጠ በኋላ ቅጣት የተጣለበት በ2004 ዓ.ም. በፍትህ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ በነበረበት ወቅት በፃፋቸው ፅሑፎችን መሰረት አድርጎ መሆኑ ታውቋል፡፡

temesegen dጋዜጠኛው የተፈረበት፤ዛሬ ጥቅምት 17 ቀን 2007 ዓ.ም. በዋለው ችሎትም ጋዜጠኛው ጥፋተኛ ከተባለበት 3 ክሶች መካከል በአንዱ ክስ ብቻ የ3 ዓመት ፅኑ እስራት ቅጣት ተጥሎበታል፡፡ በዚህም መሰረት ጋዜጠኛ ተመስገን በፀጥታ ኃይሎች ቁጥጥር ስር እንደሆነ፤ወደ አቃቂ ቂሊንጦ ወደሚገኘው ወህኒ ቤት ተወስዷል፡፡

የጋዜጠኛው ተከላካይ ጠበቃ አቶ አምሃ መኮንን ቅጣቱን እና ፍርዱን በሚመለከት ይግባኝ እንደሚጠይቁ የተገለፀ ሲሆን፤ በቅጣት ፍርዱ አቃቤ ህጉም ሆኑ ተከላካይ ጠበቃው የቅጣት ማክበጃም ሆነ ማቅለያ አለመጠየቃቸው ተጠቅሟል፡፡ በኢትዮጵያ ይህ እስከተዘገበበት ድረስ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝን ጨምሮ የታሰሩት ጋዜጠኞች እና ብሎገሮች ቁጥር 18 መድረሱ ታውቋል፡፡

ኢህአዴግ መራሹ የኢትዮጵያ መንግስት በፃፉት ፅሑፍ የተከሰሱ፣የታሰሩም ሆነ የተፈረደባቸው ጋዜጠኞችም የሉም የሚል ተደጋጋሚ ማስተባበያ ቢሰጥም፤ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ጨምሮ ከታሰሩት 18 ጋዜጠኞችና ብሎገሮች መካከል 15ቱ ኢትዮጵያውያን ጋዜጠኞችና ብሎገሮች የቀረበባቸው ክስናም ሆነ ፍርድ ከስራቸው ጋር በተያያዘ በፃፉትና በተናገሩት መሆኑ የተመሰረተባቸው ክስ ያመለክታል፡፡

ኢ/ር ግዛቸው ሽፈራው በገዛ ፍቃዳቸው ሥልጣናቸውን ሲለቁ፤ አቶ በላይ ፍቃዱ ቀጣዩ ፕሬዘዳንት በመሆን ተመርጠዋል

gizየአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) ብሔራዊ  ምክር ቤት ዛሬ ጥቅምት 2 ቀን 2007 ዓ.ም. በነበረው ስብሰባ ፕሬዚዳንቱ ኢ/ር ግዛቸው ሽፈራው ሪፖርት ካቀረቡ በኋላ፤ ከውስጥና ከውጭ በተፈጠሩ አንዳንድ የማያሰሩ ችግሮች፣ ካለባቸው የሥራ ጫና እና ፓርቲው ወደፊት አንድነቱን ጠብቆ ለ2007 ምርጫ አሸናፊ ሆኖ እንዲወጣ በማሰብ ስልጣናቸውን በቃዳቸው መልቀቃቸውን ይፋ ማድረጋቸው ተጠቁሟል፡፡
ምክር ቤቱም በፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ መሰረት የፕሬዘዳንቱን ጥያቄ በአድናቆት ተቀብሎ፤ ፓርቲውን በፕሬዘዳንትነት በመምራት መጪውን ምርጫ ውጤታማ ለማድረግ እንዲያስችል 1ኛ. አቶ በላይ ፈቃዱ፣2ኛ. አቶ ደረጀ ኃይሉ እና 3ኛ. አቶ ትዕግስቱ አወሉን በዕጩነት በማቅረብ፤አቶ በላይ ፈቃዱን በፕሬዘዳንት መርጧል፡፡ ምርጫውም በምስጢር ድምፅ አሰጣጥ እዛው በፓርቲው ምክር ቤት የተከናወነ ሲሆን፤በመጨረሻም አቶ በላይ ፈቃዱ በከፍተኛ ድምፅ ማሸነፋቸው መረጃዎች አመልክተዋል፡፡

ከምርጫው ውጤት በኋላ አቶ በላይ በቀጣይ የስልጣን ጊዜያቸው ፓርቲውን ለመምራት ቃለ መሐላ የፈፀሙ መሆናቸውን የፍኖተ ነፃነት ዘገባ ያስረዳል፡፡ አቶ በላይ ጠንካራ የፖለቲካ  ልምድና ተሳትፎ ካላቸው የፓርቲው ወጣት አመራሮች መካከል በውጤታማነት ከሚጠቀሱት አንዱ እንደሆኑ የተጠቆመ ሲሆን፤የትምህርት ደረጃቸውም በስታስቲክስ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የመጀመሪያ ድግሪ (BSc) እና በኢኮኖሚ ፖሊሲ አናሊስስ የማስተርስ ድግሪ (MSc) ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ያላቸው ሲሆን፤ በስራ ልምዳቸውም በተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አገልግለዋል፡፡ አቶ በላይ ወደ ፓርቲው ፕሬዘዳንትነት ከመምጣታቸው በፊት፤ በራሳቸው የጥናትና ምርምር ድርጅት በማኔጂንግ ዳይሬክተርነት ያገለግሉ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡

belayፓርቲው መጪውን 2007 ዓ.ም. ምርጫ እንዲያሸንፍ ትልቅ ሚና ይኖራቸዋል በሚል ከአባላትና ከደጋፊዎች ትልቅ ተስፋ እንደተጣለባቸውና ኃላፊነታቸውንም በስኬት ሊወጡ እንደሚችሉ ተገምቷል፡፡

 

 

የኢትዮ ምህዳር ጋዜጣ ቢሮ ታሸገ

ethi-mihedarየኢትዮ ምህዳር ጋዜጣ ዛሬ መስከረም 23 ቀን 2007 ዓ.ም ለምሳ ከቢሮ እንደወጡ መታሸጉን ዋና አዘጋጁ አቶ ጌታቸው ወርቁ ለፍኖተ ነፃነት ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ገለጹ፡፡ እንደ አቶ ጌታቸው ገለፃ ህትመት ካቋረጥንበት ነሐሴ 14 ቀን ጀምሮ ወደ ተለያዩ ማተሚያ ቤቶች ሄደን ለማተም ጥረት ብናደርግም ሊሳካልን አልቻለም፡፡ ነገር ግን ከ2 ሳምንት በፊት ማተሚያ ቤት አግኝተን ዝግጅታችንን ካጠናቀቅን በኋላ ወደ ህትመት ልንገባ ስንል ፊውዝ ተቃጠለ በሚል ሰበብ ልትታተም አልቻለችም፡፡ አሁንም ወደ ሌላ ማተሚያ ቤት በመሄድ ለማተም ተስማምተው ዝግጅት በምናደርግበት ሰዓት ከማዕከላዊ ተደውሎ ትፈለጋላችሁ እንድትመጡ የሚል የስልክ መልዕክት እንደደረሳቸው አቶ ጌታቸው ገልጸው፣ ለምን እንደተፈለጉ ቢጠይቁም በስልክ አልነግርክም ማዕከላዊ ቢሮ ቁጥር 75 አቶ አለበል ብለህ እንድትመጣ እንደተባሉ እሳቸውም ሰኞ እንደሚመጡ ለደዋዩ እንደገለጹላቸው ነገር ግን በዛሬው ዕለት ለምሳ እንደወጡ ቢሮዋቸው እንደታሸገ ለፍኖተ ነፃነት ገልጸዋል፡፡