የኤርትራ መንግስት ባለፈው የካቲት 2001 ዓ.ም. በርካታ ጋዜጠኞች በጅምላ ካሰረቻቸው መካከል በረከት ምስግና፣ ይርጋዓለም ፍስሃ፣ ባሲሎስ ዘሞ፣ ንጉሴ ክፍሉ፣ግርማይ አብርሃም እና ጴጥሮስ ተፈሪ ከ6 ዓመታት እስር በኋላ መፈታታቸውን ድንበርየለሹ የጋዜጠኞች ቡድን (Reporters without Border) ይፋ አድርጓል፡፡
ጋዜጠኞች በሬዲዮ ባና፣ በሬዲዮ ዛራ እና በሬዲዮ ድምጺ ሃፋሽ ይሰሩ የነበረ ሲሆን፣ በተመሳሳይ ወቅት ከታሰሩት ጋዜጠኞች መካከል ባለፈው መጋቤት 2005 ዓ.ም. 7 ጋዜጠኞችን እንዲሁ የኤርትራ መንግስት በዋስ መፍታቱ ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ አሁንም ጋዜጠኛ ዳዊት ይስሃቅ እና ስዩም ፀሐዬን ጨምሮ 16 ጋዜጠኞች በእስር ላይ እንደሚገኙ ድንበር የለሹ የጋዜጠኞች ቡድን አስታውሷል፡፡
ሰሞኑን ከእስር ስለተፈቱት ጋዜጠኞች ያሉበት ሁኔታና የቴንነት ጉዳይን በተመለከተ እስካሁን ለማወቅ እንዳልተቻለና ይህንንም ለማወቅ ክትትል እንደሚያደርጉ የተቋሙ የአፍሪካ ጉዳይ ዳይሬክተር ተናግረዋል፡፡
በተለይ በአፍሪካ ጋዜጠኞችን በማሰር ከጎረቤቷ ኢትዮጵያ ጋር ኤርትራ ቀዳሚ ሀገር እንደሆነች እና ለጋዜተኞች ከማይመቹ የዓለማችን ሀገራት እጅግ አደገኛ በሚል ዝርዝር ውስጥ መግባቷ ይታወሳል፡፡ በዚህም ሀገሪቱ ከኢትዮጵያ ጋር ተመሳሳይ ባህሪ ያላት ሲሆን፤ በኢትዮጵያም ሆነ በኤርትራ መንግስት ስልጣን ላይ ያሉት አካላት በትጥቅ ትግል ወደ ስልጣን እንደመጡ አይዘነጋም፡፡