Monthly Archives: December, 2015

አምስቱ የዞን ዘጠኝ ብሎገሮች ይግባኝ ተጠየቀባቸው

ባለፈው ሚያዝያ 2006 ዓ.ም. አጋማሽ ላይ በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው ታስረው ፣ጉዳያቸው ለአንድ ዓመት ከ5 ወር በላይ ሲታይ ቆይቶ ከበፈቃዱ ኃይሉ በስተቀር ቀሪዎቹ “መከላከል ሳያስፈልጋቸው በነፃ እንዲሰናበቱ” ተብሎ ከሁለት ወራት በፊት የተወሰነላቸው አምስቱ የዞን ዘጠኝ ብሎገሮች ይግባኝ ተጠየቀባቸው፡፡

የፌደራል ዐቃቤ ሕግ በአምስት የዞን ዘጠኝ ብሎገሮች ላይ ባቀረበው ይግባኝ መሠረት ለቃል ክርክር ተዘጋጅተው እንዲቀርቡ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የወንጀል ችሎት ማዘዙ ተሰምቷል፡፡

Federal court charge

ፍርድ ቤቱ በሶልያና ሽመልስ የክስ መዝገብ ለሚከራከሩት አምስት የዞን ዘጠኝ አባላት መጥሪያውን ያወጣው ታህሣሥ 4 ቀን 2008 ዓ.ም ሲሆን፤ ለቃል ክርክር ቀነ-ቀጠሮ የሰጠው ለፊታችን ታህሣሥ 20 ቀን 2008 ዓ.ም. ከጠዋቱ 2፡30 መሆኑን መጥሪያው ያስረዳል፡፡ ይህ እስከተዘገበበት ድረስ መጥሪያው የደረሰው ለበፍቃዱ ኃይሉ ብቻ ሲሆን፤ በተሰጠው የቃል ክርክር ቀነ-ቀጠሮ እንዲቀርቡ መጥሪያ የወጣላቸው በፈቃዱ ኃይሉ፣ አጥናፍ ብርሃኔ፣ አቤል ዋበላ፣ ናትናኤል ፈለቀ እና በሌለችበት ክስ የተመሰረተባት ሶሊያና ሽመልስ መሆናቸውን መረጃዎች አመልክተዋል፡፡

ከዚህ ቀደም፤ በፍቃዱ ኃይሉ የተቀየረለትን “አመፅ የማነሳሳት” የወንጀል አንቀፅ ለመከላከል ለጥር 30 ቀን 2008 ዓ.ም. መቀጠሩ አይዘነጋም።

ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው ታሰረ

የነገረ ኢትዮጵያ ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው ዛሬ ታህሣሥ 15 ቀን 2008 ዓ.ም. ጠዋት ለስራ ከቤቱ ሲወጣ በፌደራል ፖሊሶችና በደህንነት ሰዎች ተይዞ ታስሯል። የፀጥታ ኃይሉ መኖሪያ ቤቱን ከፈተሹ በኋላ ፣ጋዜጠኛውን ወደ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ማዕከል ማዕከላዊ መስደው ማሰራቸው ቢገለፅም፤ መንግሥት ጋዜጠኛውን ለምን እንዳሰረ የገለፀው ነገር የለም፡፡

ጋዜጠኛ ጌታቸው የነገረ ኢትዮጵያ ዋና አዘጋጅ ከመሆኑ በተጨማሪ የእንቁ መፅሔትም ፀሐፊ እንደነበር የሚታወቅ ሲሆን፤ ከዚህ በፊት በመንግሥት ኃይሎች ከፍተኛ ማስፈራሪያና ዛቻ ይፈፀምበት እንደነበርም ታውቋል፡፡ጌታቸው ነገረ ኢትዮጵያ ጋዜጣን እና ደረ- ገፅን ጨምሮ በተለያዩ ድረ-ገፆችና የራሱ ማኀበራዊ ገፅ ላይ የተለያዩ ሐሳቦችን ይፅፍ እንደነበርም ይታወቃል፡፡

ከጋዜጠኛ ጌታቸው በተጨማሪ በተደጋጋሚ ሲታሰሩና ሲፈቱ የነበሩት ሶስቱ የሰማያዊ ፓርቲ አባላት መካከል ዳንኤል ተስፋዬ፣ ኤርምያስ ፀጋዬ እና ቴዎድሮስ አስፋው ዛሬ መታሰራቸውን የደረሰን መረጃ አመልክቷል፡፡

Getachew Shiferaw

በተመሳሳይ ዜና ባለፈው ቅዳሜ ታህሣሥ 9 ቀን 2008 ዓ.ም. ጠዋት አዲስ አበባ ከሚገኘው መኖሪያ ቤቱ በፀጥታ ኃይሎች ተይዞ የታሰረውና የኦሮሚያ ሬዲዮናቴሊቪዥን ዜና አንባቢ ጋዜጠኛ ፈቃዱ ምረከና አለመፈታቱ ታውቋል፡፡ ይህ እስከተዘገበበት ድረስ ጋዜጠኛ ፈቃዱ ምርከናም ሆነ ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው በምን ምክንያት እንደታሰሩ ከመንግሥት በኩል የተገለፀ ነገር የለም፡፡

Fekadu Mirkena

ከጋዜጠኛ ፈቃዱ እና ጌታቸው በተጨማሪ በርካታ ጋዜጠኞች በእስር ላይ እንደሚገኙና በዓለም አቀፍ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋቾች ድርጅቶች፤ ኢትዮጵያም ጋዜጠኞችን በማሰር ከአፍሪካ የሁለተኛ ደረጃን ተቀዳጅታ እንደነበር አይዘነጋም፡፡

አቶ በቀለ ገርባ በድጋሚ ታሰሩ

የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረንስ/መድረክ ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር እና የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህር አቶ በቀለ ገርባ ዛሬ በድጋሚ መታሰራቸው ተገለፀ፡፡ አቶ በቀለ ዛሬ የታሰሩት አዳማ/ናዝሬት ከሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው በ14 የደህንነት አባላት ለሰባት ሰዓታት ያህል ፍተሻ ከተደረገ በኋላ ተይዘው ወደ አዲስ አበባ መምጣታቸውን የኢሳት ዘገባ አመልክቷል፡፡

Bekele Gerbaባለፈው ህዳር 2008 ዓ.ም. ከተቀጣጠለው የኦሮሚያ ክልል ህዝብ ተቃውሞን ተከትሎ የፌደራል ፖሊስ፣ የአጋዚ ልዩ ኃይል እና መከላከያ ሰራዊት በክልል በተቀሰቀሰው ህዝባዊ ተቃውሞ ከ86 በላይ ሰዎች መገደላችን፣ በርካታ ሰዎች መቁሰላቸውን እና መታሰራቸውን ተከትሎ አቶ በቀለ በፓርቲያቸው ኦፌኮ/መድረክ አማካኝነት ከፍተኛ ተቃውሞ ሲያሰሙ ከነበሩ አመራሮች አንዱ መሆናቸው ይታወቃል፡፡

አቶ በቀለ ከዚህ በፊት በሰኔ 2003 ዓ.ም. በኦሮሚያ ክልል በመንግሥት ስለሚፈፀሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በተመለከተ ለአምንስቲ ኢንተርናሽናል ጋር ያደረጉትን አጭር ቆይታ ተከትሎ መንግሥት በሽብር ወንጀል ፈርዶ ለ3 ዓመት ከ7 ወር በኋላ የእስር ፍርድ ጊዜያቸውን ጨርሰው ባለፈው መጋቢት 2007 ዓ.ም. መፈታታቸው አይዘነጋም፡፡ አቶ በቀለ ዛሬ ከመኖሪያ ቤታቸው ተይዘው የታሰሩበት ምክንያት እስካሁን እንዳልተገለፀላቸው ታውቋል፡፡

በተያያዘ ዜና ከአቶ በቀለ ገርባ በተጨማሪ ቀደም ሲል ከኦፌኮ/መድረክ ከፍተኛ አመራሮች አቶ ደጀኔ ጣፋ እና የተለየዩ የፓርቲው አባላትና የዞን አመራሮችም መታሰራቸው ታውቋል፡፡
ለለአንድ ወር የዘለቀው የኦሮሚያ ህዝባዊ ተቃውሞ አዲሱን የአዲስ አበባ እና የኦሮሚያ ልዩ ዞን የተቀናጀ የጋራ ማስተር ፕላንን በመቃወም መነሻ ቢሆንም በተጨማሪ የተለያዩ የመብት ጥያቄዎችን ያካተተ እንደነበር አይዘነጋም፡፡

ጠላት ሰሪዎቹ (The Enemy Makers)

ገመቹ መረራ ፋና

gemechu merera

ብዙውን ጊዜ የራሳችንን ጠላቶች ራሳችን ጠፍጥፈን እንደምንሰራ አምናለሁ። በማድረግም ባለማድረግም (by commission and omission) የምንሰራቸው «ስህተቶች» አሉ። በተለያየ ጊዜ ያቆሰልናቸው ወይም ቆስለው እያየን በቁስላቸው አላግጠን ያለፍናቸው ሰዎች ነገ ወዳጅ ይሆኑናል ብለን የምንጠብቅ የዋሆች አይደለንም። ይሄንን ድርጊታችንን ወይም ተዓቅቦአችንን ተከትሎ የሚመጡብን ችግሮች ከመጋፈጥ ቆም ብሎ ዛሬ ላይ ምን እያደረግኩ ነው ብሎ ማሰብ ሳይበጅ አይቀርም። እስቲ በመጨረሻ ላይ የቆምንበትን/ያለንበትን ሁኔታ ከማየታችን አስቀድመን ጥቂትአብነቶች አንስተን የራሳቸውን ጠላት ጠፍጥፈው የሰሩ አካላትንን እና «ጠላቶቹን» በምሳሌነት እንመልከት፦
1. ጋሳን ፋይዝ ካናፋኒ
ይህ በብዙዎች ዘንድ የአረቡ የምንጊዜም ምርጥ የሥነ-ጽሁፍ ሰው ነው ተብሎ የሚወሰድ ፍልስጤማዊ ደራሲና የነጻነት ታጋይ ከሕልፈቱ በኋላ በ Conference of Afro-Asian Writers የ Lotus Prize for Literatureን አሸንፏል። በልጅነቱ የ1948ቱን የአረብ-እስራኤል ጦርነት ተከትሎ ከትውልድ ስፍራው ከቤተሰቦቹ ጋር ተሰዶ ወደ ሊባኖስ ከዚያም ወደ ሶርያ የኖረው ካናፋኒ በ36 ዓመት እድሜው ሞሳድ ባጠመደው የመኪና ቦምብ ከ17 ዓመቱ የወንድሙ ልጅ ጋር ቢገደልም በትንሹ የሕይወቱ ቆይታ ግን ብዙ ስራ ሰርቶ አልፏል።
Letter from Gaza በመባል በሚታወቀው ለጓደኛው ሙስጠፋ በጻፈው የመልስ ደብዳቤ ካናፋኒ አንድ ነገር ግልጽ ያደርጋል። ይህ ደብዳቤ ሶርያ በስደት እያሉ ብዙ አስቸጋሪ ጊዜያት አብረው አሳልፈው ለነበረውና ወደፊት ሃብታም የመሆን ግብ ሰንቀው ይኖሩ ለነበረው አብሮአደግ ጓደኛው ሙስጠፋ የተጻፈ የመልስ ደብዳቤ ነው። በመጀመሪያው ደብዳቤ አሜሪካ ነዋሪ የሆነው ሙስጠፋ ለካናፋኒ ለኑሮው የሚያስፈልጉትን ሁሉ ነገሮች አመቻችቶ ወደ አሜሪካ (ካሊፎርኒያ- ሳክራሜንቶ) እንዲመጣና የልጅነት ግባቸውን እንዲያሳኩ እየነገረው ነበር። በሲቪል ምህንድስና በካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ ስኮላርሺፕ አግኝቶ ሁሉ ነገር የተስተካከለለት ጋሳን ካናፋኒ ግን ለጓደኛው እኔ ወደ አሜሪካ አልመጣም፣ አንተ ወደ ጋዛ ና እንጂ ይለዋል። «I won’t follow you to “the land where there is greenery, water and lovely faces” as you wrote. No, I’ll stay here, and I won’t ever leave.» በዚህች መስመር እንደተጠቀሰው መቼም ከጋዛ አልወጣም ነበር ያለው። ለምን ይሆን አልመጣም ያለው? ያስብላል።
ናዲያ። ያቺ በጣም አብዝቶ የሚወዳት ናዲያ አይኑን እንደከፈተችለት ይገልጻል። ናዲያ ቆንጅዬ የ13 ዓመት ልጅ ነች። የሙት ወንድሙ ሴት ልጅ። ለበዓል ይኖርበት ከነበረችው ኩዌይት ወደ ጋዛ ሲሄድ የወንድሙ ሚስት እያነባች ልጇ ናዲያን ሄዳ ጋዛ ሆስፒታል እንዲጠይቃት ትለምነዋለች። እናቱ እና የወንድሙ ሚስት የደበቁት ነገር እንዳለ እየተሰማው ወደ ሆስፒታል ክፍሏ ይገባል። የሆስፒታሉ አልጋ ላይ ትልቅ ትራስ ተንተርሳ ጥልቅ ዝምታን በሚናገሩት እና እንባ ባዘሉ አይኖቿ ተመለከተችው። «Her face was calm and still but eloquent as the face of a tortured prophet might be. Nadia was still a child, but she seemed more than a child, much more, and older than a child, much older.» አጎቷን ያየችው ናዲያ በእጆቿ ድጋፍ ቀና ብላ ሰላም ካለችው በኋላ ተኛች። ካናፋኒም አንዲህ ይላታል «ናዲያ ብዙ ስጦታዎች ከኩዌይት ይዤልሽ መጥቻለሁ። ድነሽ ከአልጋ ስትወርጂ እቤት ትመጪና ስጦታዎችሽን ሰጥሻለሁ። ባለፈው በደብዳቤ ጽፈሽ የጠየቅሺኝን ቀይ ሱሪም ገዝቼልሻለሁ። ሱሪውን ይዤልሽ መጥቻለሁ።» ናዲያ ኤሌክትሪክ እንደያዛት ሰውነቷ ተንቀጥቅጦ ዝም አለች። አንባዋ ግራና ቀኝ ወደ ትራሱ ፈሰሰ።
«ሱሪውን አልፈለግሺውም? ምን ሆነሻል?» ብሎ ሲጠይቃት እንደምንም ጥርሷን ነክሳ ከሩቅ የመጣ በሚመስል ድምጽ «አጎቴ!» አለችው። እጇቿን ዘርግታም የሸፈናትን የሆስፒታል ብርድልብስ ገለጠችና በጣቶቿ ጠቆመቸው። ናዲያ እግሯ ከጭኗ መነሻ ጋር ተቆርጦ ነበር!! «ይሄንን ልረሳ አይቻለኝም» ይለዋል በደብዳቤው ለጓደኛው። «ያን ቀን ናዲያ እግሯን ያጣችው ታናናሽ ወንድም እና እህቶቿን ከቦንብና ከነበልባል ልታድን ራሷን ጥላ ከልላቸው ስለነበር ነው ብለው ነገሩኝ። ሮጣ ልታመልጥ እና እግሯን ልታድን ትችል ነበር። ግን ያንን አላደረገችም።» ይልና ከዚያች ቀን በኋላ ሁሉን ነገር በተለየ መልክ ማየት መጀመሩን እና ወደ ሳክራሜንቶም እንደማይመጣ፣ ይልቁንም እርሱ ራሱ እንዲመጣና ለሀገራቸው ትንሳዔ፣ ለህዝባቸው መፍትሄ እንዲሰሩ ይጠይቀዋል። ይሄ መስዋዕትነት ምንን እንደሚጨመር እንግዴህ መዘርዘር አያስፈልግም – ጉዳዩ የእስራኤል እና የፍልስጥዔም ነውና። እስከ ሕልፈተ ሕይወቱ ድረስም ለሃገሩ ሲሰራ ኖሯል። የጋሳን ካናፋኒ ስራዎች ዛሬ በብዙ ፍልስጤማውያን ልብ ውስጥ አለ።
2. ብ/ጄኔራል ታደሰ ብሩ
ጄነራሉ ሙያቸውን ከሚያከብሩ እና ለንጉሱ ታማኝ ከነበሩ ወታደሮቻቸው መካከል ግንባር ቀደሙ ነበሩ። በንጉሱ ጊዜ እንዳገለገሉት አብዛኞቹ ባለሥልጣናት እና ተሿሚዎች ለንጉሱ መልካም አመለካከት እና ታማኝነት የነበራቸው ግለሰብ ነበሩ። ይሄንንም በንጉሱ ላይ የታቀደውን መፈንቅለ መንግስት ባከሸፉበት ስራቸው እንዲሁም ኔልሰን ማንዴላን መጠበቅ እና ማሰልጠንን የሚያህል ትልቅ አደራ በመቀበል አስመስክረዋል። (እዚህ ጋር እንዴት ያንን መፈንቅለ መንግስት ያከሸፈ ግለሰብ በመልካም ይወደሳል የሚል አንድ ጥያቄ ሊነሳ ይቸላል። ነገር ግን እንደወታደር እና ሃላፊነቱ እንደነበረበት ሰው ግዴታቸውን የተወጡ መሆኑ በተለያዩ አጋጣሚዎች ሲገለጽ ነበር። ከውትድርና ሳይንስ አንጻር ከታየና ከወቅቱ ሁኔታ ጋር ከተመዘነ ባይጥምም የሚያስማማ ነው።) የኚህ የተከበሩ ጄነራል ታማኝነት ግን አንድ ቀን ተሸረሸረ።
ከዕለታት በአንዱ ቀን በቤተመንግስት በተዘጋጀ የራት ግብዣ ላይ መኳንንቱ እና መሳፍንቱ እንዲሁም እነጄነራል ታደሰ ብሩ ታድመው ነበር። በራት ግብዣው ላይ ሰው ጨዋታ ይዞ የነበረ ሲሆን ብ/ጄኔራል ታደሰ ብሩ ጨዋታ ይዘው የነበረው ከጠ/ሚ/ሩ አክሊሉ ኃብተወልድ ጋር ነበር። የጨዋታውም ርዕስ ጄነራሉ በወቅቱ ይሰሩት ስለነበረው ስራ ነበር። ጄኔራሉ በወቅቱ በጦር ሰራዊቱ ውስጥ የጀመሩት እና በተለይ ይመሩት የነበረው አንድ ክፍል ነበር። ይህ ክፍል «የፊደል ሰራዊት» የሚባል ሲሆን በሃገራችን የተለያዩ ክፍሎች የመሰረተ ትምህርት ስልጠና ይሰጥ ነበር። በውይይቱ ወቅት ጠ/ሚ/ሩ እጅግ ያስገመታቸውን እና ለጄነራሉ መለወጥ ምክንያት የሆነውን ትዕዛዝ መሰል ምክር ለጄነራሉ ሰጡ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ አቶ አክሊሉ «ታደሰ፤ ኦሮሞ ውቅያኖስ ነው ይውጠናል – ልታስተምረው እንዳትሞክር። እነሱን አንድ ክፍለዘመን ወደኋላ ይዘን መሄድ ነው ያለብን» ነበር ያሉት።
በወቅቱ በዚህ ጊዜ ተመስርቶ የተለያዩ የልማት ስራዎችን እየሰራ የነበረ አንድ ማህበር ነበር፤ የመጫና ቱለማ የመረዳጃ ማህበር። ይህ ማህበር እንደ መቶ አለቃ ግርማ ወልደጊዮርጊስ ያሉ የተለያዩ ትልልቅ ሰዎችን በአባልነት ያቀፈና የተለያዩ የማህበራዊ ፍትህ እና የልማት ስራዎችን የሰራ ማህበር ነበር። ትምህርት ቤቶችን፣ ሆስፒታሎችን/ክሊኒኮችን እና ሌሎች መሰል የልማት ስራ ይሰራ የነበረው ማህበሩ ለዚህ ስራው የሚረዱ ግብዓቶችን ሊሰጡ የሚችሉ ከመላው ሕብረተሰብ የተውጣጡ ሰዎችን የያዘ ሲሆን በውስጡ ደጃዝማቾችን፣ ኮሎኔሎችን፣ ዶክተሮችን ወዘተ በአባልነት ያቀፈ ማህበር ነበር። ለማህበሩ አባልነት ከተጠየቁት እና የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ከተጋበዙ ሰዎች መሃዘከል ደግሞ ብ/ጄኔራል ታደሰ ብሩ አንዱ ነበሩ። ጄነራሉ ግን ማህበሩ የብሄር ተኮር ፖለቲካ ያራምዳል የሚል ዕምነት ስለነበራቸው ግብዣውን ከአንዴም ሁለቴ ሳይቀበሉ ቀርተው ነበር።
ወደ ራት ግብዣው ምሽት ስንመለስ ጠ/ሚ/ሩ ያንን «ምክራቸውን» ለጄነራሉ ሲለግሱ ያላወቁት አንድ ነገር ነበር፤ ጄኔራሉ በእናታቸው ኦሮሞ መሆናቸውን። በዚህ ጊዜ ነበር እያገለገሉ ያሉት ሥርዓት አባላት ያላቸውን የነቀዘ አስተሳሰብ የተገነዘቡት እና ከዚህ በፊት የገፉትን የአባልነት ግብዣ ተቀብለው የመጫና ቱለማ ማህበርን የተቀላቀሉት። ከዚህ ቀን በኋላ በሥርዓቱ የተገፋ ሕዝብ ላሉት የኦሮሞ ሕዝብ በደርግ እስከተገደሉበት ዕለት ድረስ የታገሉ ሲሆን የማህበሩን የትግል ገጽታ በአንድ ደረጃ ከፍ እንዳደረጉ ይነገራል። (በኦላና ዞጋ የተጻፈውን «ግዞት እና ግዝት» የተሰኘው መጽሃፍ ውስጥ በስፋት ስለጄነራሉ ማንበብ ይቻላል።) ዛሬ የብ/ጄነራል ታደሰ ብሩን ትግልና መስዋዕትነትን የማያውቅና በልቡ ያላኖረ የኦሮሞ ወጣት ማግኘት ያስቸግራል።
(ምንም እንኳን ለዚህ ጽሁፍ ከላይ ከተጠቀሰው የሚበልጥ አግባብነት ባይኖረውም ጠ/ሚ/ሩ በሌላ አጋጣሚም ንጉሱ ዘንድ የቀረቡትን የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሰራተኞች ተወካዮች «ንጉሱ እንኳን እናንተን የማንንም ጋላ ያናግራሉ» ብለው መናገራቸው በ «ኮሙኒስቶችም እኛን ይመስላሉና» ላይ ተጽፎልናል)
3. አህመድ ግራኝ (አህመድ ኢብን አል ጋዛሊ)
አህመድ ግራኝ ለዚያ ሁሉ ዘመቻና በቀል እንዲነሳሳ ምን አደረገው? ለዚህ ምላሽ የሚሆን በቂ ጽሁፍ በተክለ ጻድቅ መኩሪያ የታሪክ መጽሃፍት ውስጥ ይገኛል። (በእኔ እይታ ጸሃፊው እንደአብዛኞቹ የሃገሬ ታሪክ ጸሃፊዎች የሚዛናዊነት ችግር ባስተውልባቸውም በዚህ ጉዳይ ላይ ቅሬታ የሚያስቀርብ ነገር አላየሁም። ስለዚህ አንባቢ አንብቦ ይረዳው አሊያ በሌላ ጽሁፍ እመለስበታለሁ ወይም ባለሙያዎቹ ይጽፉበታል።)
4. የኛ ትውልድ
የኔ ትውልድ ያልኩት በዋነኛነት ይሄንን የCyber ትውልድ ነው። በበይነ-መረብ (ኢንተርኔት) ታግዞ የተለያዩ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮችን በማንሳት ያለማቋረጥ የሚያፈሰው ተዋስዖ አጥፊም አልሚም ሊሆን የሚችልበት አጋጣሚ አይጠፋንም። ስንቶቻችን ለሰዎች እና ለነገሮች ያለንን አመለካከት በCyber ላይ ባየነው እና ባጋጠመን ነገር በአሉታዊ መልኩ ተቀይሯል? ስክሪኖች ይቁጠሩት። ይሄ «የአንተም ልክ ነህ፣ አንተም ልክ ነህ» ምክር አይደለም። ጥያቄ ሊሆን ይችላል።
በሰዎች ሳይኮሎጂ ጥናት «የመንጋ ደመነፍስ» ወይም “tribal instinct” መኖሩን ባለሙያዎቹ ይነግሩናል። ይህ ደመነፍስ በየትኛውም አለም ያለ ሲሆን ራሱን በተለያዩ ቡድኖች መኖር ውስጥ ይገልጣል፤ ክርስቲያን-ሙስሊም፣ ዲሞክራት-ሪፐብሊካን፣ ወዘተ . . .እናም ምንም እንኳን የሚፈጸመው በግለሰቦች ቢሆንም በሌላ አቻ ግለሰብ ላይ ያለማገናዘብ ከሚነገሩ/ከሚደረጉ የቃላት ጥቃቶች ይልቅ በነዚህ አይነት ቡድኖች ላይ የሚወረወሩ ያላግባብ አስተያየቶች የበለጠ ትኩረት አግኝተው ውጥረት ይፈጥራሉ። ቅራኔዎችን ያሰፋሉ። የማይታረቁ ልዩነቶችን ብሎም ጠላትነትን ይፈጥራሉ።
ከነዚህ ንግግሮች ወይም የቃላት ምልልሶች መካከል ግን አብዛኞቹ በውይይት ሊፈቱ የሚችሉ፣ የተለየ እሴት የማይጨምሩ በመሆናቸው በውይይት ሊተዉ የሚችሉ አሊያም ሊለወጡ የማይችሉ እውነታዎች በመሆናቸው ከመቀበል ውጪ አማራጭ የሌላቸው ነገር ግን «ለተቃራኒው» ቡድን እንደመሸነፍ እንዳይወሰድ በእልህ የተያዙ ናቸው። ከነዚህ ውስጥ የታሪክ ልዩነት የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳል ብንል ማጋነን/ሐሰት አይሆንም። አንድ ሰበዝ እንምዘዝ።
የሃገር/መንግስት ምስረታም (State Formation) ሆነ ግዛት ማስፋፋት (Expansion) በሰላማዊ መልኩ ወይም ኃይል ሳይጠቀሙ የሚያሳኩት ነገር አይደለም። ስለዚህ በነዚህ ሂደቶች ወቅት የሚፈጸሙ የተለያዩ ጥፋቶች አሉ። ስማቸው ከተራ ግድያ እስከ ጭፍጨፋ እና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ሊሄድ ይችላል። ይሄ አያከራክርም ምክንያቱም «ጽጌረዳን በሌላ ስም ብንጠራው መዓዛው አይቀየርም።» የሚያከራክረው ጉዳይ ግን ያንን የታሪክ ኹነት የመቀበል ወይም ያለመቀበል እንዲሁም ለአሁኑ ትውልድ ወቀሳ ፍጆታ ማዋል ያለማዋል ላይ ነው።
እዚህ ጋር «አፍቃሬ – የቀድሞ መሪዎች» በእርግጥም አሉ ብለን ብዙ ጊዜ እንዳምን የሚያደርገን ነገር አለ። ያለፉትን መሪዎች የምንከላከልበት (Defend የምናደርግበት) አግባብ ግልጽ አይደለም። ይህ መከላከል የመጣው ከገዢው/ሃገር ከሚያስተዳድረው አካል ቢሆን ኖሮ የሕልውና ጥያቄ የሚያስነሳባቸው ብዙ ሁኔታዎች በመኖራቸው ምክንያቱ ግልጽ ይሆናል። ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን እንደ ግለሰብ በታሪክ የተፈጸፈሙ ድርጊቶችን መካድ ግን (ለያውም ለትምህርት/አካዳሚክ/ ዓላማ ባልሆነበት እና በማስረጃ ባልተደገፈበት ሁኔታ) ባላጋራ/ጠላት መፍጠር እንጂ ምንም የሚያመጣው ለውጥ የለም። እውነቱን ተቀብሎ ያ ስህተት ዛሬ ላይ ጥላውን እንዳያጠላ የሚደረግበት ሁኔታ ላይ መወያየት የተሻለ ረብ አለው።
በሌላ በኩል ደግሞ «የአባት እዳ ለልጅ» የማስተላለፍ አባዜ የተጠናወተው ተዋስኦ ያለመታከት ማካሄድም ተመሳሳይ ውጤት ነው የሚኖረው – ጠላት መፍጠር። በዚህ ዘመን የሚኖር ግለሰብ ተጠያቂነት አሁን ላለበት ዘመን እና ለሚመጣው ትውልድ የተተወ እንጂ ላልነበረበት ጊዜ የሚተላለፍ መሆን የለበትም። ከላይ የተጠቀሰው ያለፈውን ስርዓትና መሪዎች የመከላከል «በሽታው» እንደ ግል ድክመት ሊቆጠር እንጂ ያለፈው አካል ላደረሰው በደል ወይም ስህተት ተጠያቂ የሚያደርገው ሊሆን አይገባም። እነኚህ ሁለቱ በየትኛውም የታሪክ ክርክሮች ውስጥ ሊተገበሩ የሚችሉ ቋሚዎች (Constants) ስለሆኑ መርሆዎች ተደርገው ሊወሰዱ የሚችሉ ናቸው።
ምናልባት ከዚህ አለፍ ስንል በቅርቡ የአውስትራሊያው ጠቅላይ ሚኒስትር ከእርሳቸው እጅግ በጣም ረዥም ጊዜ በፊት ለተፈጸመው በደል ነባሮቹን የሃገሬዎቹን ሰዎች {the Aborigins} በይፋ ይቅርታ መጠየቃቸው የሚያስተምረን ነገር ይኖር ይሆን? Let’s watch our words and stop making an enemy out of our brethren!!!

ማን አለ እንዳንተ፣ ታማኝ?

በፈቃዱ ዘ ኃይሉ

Befeqadu  Ze Hailu
የሆነ ጊዜ የሰማኋት ቀልድ ትዝ አለችኝ፤ አንዳንድ የተቃዋሚ ተወካዮች ፓርላማ ውስጥ በነበሩበት በዚያ በደጉ ጊዜ ነው አሉ፡፡ አንድ ተወካይ የሻዕቢያ መንግሥት ላይ ሊደረግ ስለሚገባው እርምጃ ሲናገሩ እንዲህ አሉ፤ “አሁኑኑ ገብተን ድምጥማጣቸውን ማጥፋት አለብን፡፡ አለበለዚያ ካደሩ አይቆረጠሙም፤ እነዚያ ወያኔዎችም ያኔ ሲመሠረቱ ሳንጨፈልቃቸው ዝም ብለናቸው ነው ዛሬ አናታችን ላይ…” አሉና ያሉበት ቦታ ትዝ ሲላቸው ድንግጥ ብለው ወደአቶ መለስ መቀመጫ አማተሩ፡፡ አቶ መለስ በጥሞና ያዳምጣሉ፤ ተወካዩ እንደደነገጡ “…ልጨርሰው ወይስ ትጨርሰኛለህ?” አሉ ይባላል፡፡

የሕወሓት/ኢሕአዴግ ወታደሮች አዲስ አበባ ደርሰው “ሲቪል” መንግሥት ከመመሥረታቸው አስቀድሞ “እኩይ” ናቸው በሚል ሲቃወማቸው የነበረ እና እስካሁንም ስክነቱ ያልተለየው አክቲቪስት ታማኝ በየነ ነው፡፡ የታማኝ የአክቲቪስትነት ሪከርድ ከኮሜዲያንነቱ የሚመዘዝ ነው፡፡ በቀልዶቹ ቢጀምርም አሁን ግን በጣም ‹ሲሪዬስ› ነው፡፡

አሁን እነቪኦኤ፣ ዶቸ ቬሊ፣ ኢሳት በየቤቱ እንደሚደመጡት ከደርግ ማክተሚያ ቀደም ብሎ ብዙ ሰው በየቤቱ ‹ድምፂ ወያነ›ን በድብቅ ያደምጥ ነበር፡፡ የፕሮፓጋንዳ ሚዲያዎች አመል ነውና ያው ውሸታቸው አይጣል ነው፡፡ ታዲያ ታማኝ አዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ቀርቦ የምሩን ሲቀልድ ‹እዚህ ቦታ ይሄን ያክል ሻለቃ ጦር፣ እዚያ ቦታ ደግሞ ይሄን ያክል ሻለቃ ጦር ደመሰስን ይላሉ፡፡ ሲደመር ግን ይሄን ያክላል፡፡ ቆይ እኔ የምለው ወያኔዎቹ የሚደመስሱት ጦር ከጠቅላላ ጦሩ በለጠ እኮ፤ ከየት እያመጡ ነው የሚደመስሱት?› ዓይነት ቀልድ ተናግሮ አላገጠባቸው፡፡ ከዚያ በድምፂ ወያነ መልስ ተሰጠው፤ “ቁጥሩን አዲስ አበባ ስንደርስ እናወራርዳለን” የሚል፡፡ ዛቻ የሽፍትነት ዘመንም አመል ነበረች፡፡
ግንቦት 20/1983 – ኢሕአዴግ አዲስ አበባን ሲረግጥ፣ ሲ ኤን ኤን ካነጋገራቸው ሰዎች አንዱ ታማኝ በየነ ነበር፡፡ “በመሣሪያ ተከበናል፣ ምንም ሠላም የለም…” የሚል ነገር ለጋዜጠኛው ሲነግረው ይታያል፡፡ ታዲያ ታማኝ ሁኔታውን በቀልድ ሲያስታውስ “ጓደኞቼ ከውጪ ደውለው ‹ሲ ኤን ኤን› ላይ አየንህ ሲሉኝ፣ ወዲያውኑ እንግሊዝኛዬ እንዴት ነበር?” አልኳቸው ይላል፡፡

ታማኝ ከአዲሱ ስርዓት ጋር አብሮ መኖር በማይችልበት ሁኔታ የተቀያየመው፣ ካልተሳሳትኩ የወቅቱ ባለሥልጣናት፣ እነታምራት ላይኔ በተገኙበት ስታዲዬም ውስጥ በቀለደው ቀልድ ነው፡፡ እንደማስታውሰው ቀልዱ በማንነት ላይ የተመሠረተ እና ለኢሕአዴግ የማንነት ብያኔ የማይበገር ዓይነት ቀልድ ነው፡፡

ፍቃዱ ማሕተመወርቅ፣ የቀድሞዋ ዕንቁ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ነበር፡፡ በመጽሔትና ጋዜጦች አከፋፋይነትም ይታወቃል፡፡ አሁን መጽሔቱ ተዘግቶ “በታክስ ስም” ፍርድ ቤት እየተመላለሰ ይገኛል፡፡ ፍቃዱ ነጻው ፕሬስ ሲጀመር ጀምሮ ምኅዳሩን ያውቀዋል፤ እናም “እናንተ በደጉ ጊዜ ነው የመጣችሁት” እያለ ይቀልድብኛል፡፡ ያኔ (ማለትም የመጀመሪያው አንቀጼ ላይ ‹ደግ› ባልኩት፣ ለፍቃዱ ግን ‹ክፉ› ግዜ) አንድ ሰው ስርዓቱን የሚያስቀይም ንግግር ሲናገር፣ እንዳሁኑ በሕግ ሥም ፍርድ ቤት አይመላለስም፣ የደረሰበት ይጠፋና ከአራት አምስት ወር በኋላ ተመልሶ ይመጣል፡፡ እንዳይሞት እንዳይሽር ተቀጥቅጦ ማለት ነው፡፡ እንግዲህ ከዚያ ወዲህ ያሻሻልነው ነገር ቢኖር ፍርድ ቤት የመቅረብ ዕድል መፈጠሩ ነው ማለት ነው፡፡ የሆኖ ሆኖ ይህን ያነሳሁት ታማኝ ላይ የደረሰውም እንዲህ ያለው ነገር ነው ለማለት ነው፡፡

ታማኝ ተሰደደ፡፡ ብዙዎች ሲሰደዱ አቅላቸውን ያጣሉ፡፡ የሀገር ቤት ናፍቆት መመለስ ካለመቻሉ ጋር ተደማምሮ ይሁን፣ የሄዱበት አገር ኢሕአዴግ የማይደርስባቸው ከመሆኑ በተጨማሪ የሚያዩት ነጻነት ስለሚያስቀናቸው አላውቅም ብቻ ጠርዝ ይይዛሉ፡፡ ጥቂቶች ብቻ ሚዛናቸውን በጥፍራቸው ቆንጥጠው ይቆማሉ፡፡ ታማኝ ለኔ ከጥቂቶቹ አንዱ ነው፤ ያውም በረዥም ቆይታ ይህንን ማስመስከር የቻለ፡፡ ታማኝ አሁን አክቲቪዝሙን የሚሠራው ብዙ ጊዜ የቪዲዮ ማስረጃዎችን እያቀረበ ነው፡፡ ቪዲዮዎቹን ዩቱዩብ ላይ ሳያቸው በክምችቱ እቀናለሁ፡፡ ለረዥም ጊዜ የአገር ቤት ጉዳይን እየተከታተሉ፣ ማስረጃዎችን እየሰበሰቡ የመቆየት ፅናት የገቡበትን ጉዳይ ርዝመት እና ክብደት ከመረዳት ይመነጫል፡፡

የማስረጃ ነገር ከተነሳ አይቀር፣ አሁን እነ ታማኝ ማስረጃ ዶት ኮም (masreja.com) የተባለ ድረአምባ ፈጥረዋል፡፡ ድረአምባው በአሁኒቷ ኢትዮጵያ ውስጥ በሕግ የበላይነት ፈንታ ራሳቸው ከሕግ የበላይ ሆነው ወንጀል የሚፈጽሙ ሰዎች ላይ ማስረጃ የሚሰበሰብበት ነው፡፡ እንደእውነቱ ከሆነ እኔ በይቅርታ አምናለሁ፤ እስከዛሬ አዲሱ ያለፈውን እየቀጣ የመጣበት ዑደት ቢያንስ የእኛ ትውልድ ላይ ቢቆም እያልኩ እመኛለሁ፡፡

ይህንን በተመለከተ ጓደኛዬ ሶሊያና “ይቅርታ ከፍትሕ ጋር መጋጨት የለበትም” ብላ ሞግታኛለች፡፡ ልክ ነች፤ በወቅቱ የሰጠችኝን ምሳሌ ከወቅታዊው ሁኔታ ጋር አዋህጄ ልናገር፤ “‪#‎OromoProtests‬ ላይ ልጇ የተገደለባት እናት የስርዓት ለውጥ ቢመጣ እና ለገዳዩ ወታደር ይቅርታ አድርጊለት ብትባል ፍትሕ ተደረገልኝ ብላ ታምናለች?” በወቅቱ፣ ሶሊም እኔም ጥያቄውን ከመጠየቅ በቀር መልስ መስጠት አልቻልንም፡፡ እርግጥ ነው ልጁ የሞተው የመጣው ለውጥ እንዲመጣ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን በምሳሌያችን መሠረት አወዛጋቢው ማስተር ፕላን ቢሰረዝ እንኳን ልጁ የለውጡ እሸት ተጋሪ ላይሆን አልፏል፡፡ ይቅርታ ለአገሪቱ ቀጣይ ዕጣ ፈንታ ያስፈልግ ይሆናል፤ የቤተሰቡን አባል ወይም ወዳጁን ላጣው ግለሰብ ግን ፍትሕ ሆኖ ይሰማዋል ማለት አይቻልም፡፡ የሆነ ሆኖ፣ ለይቅርታውም ቢሆን ማስረጃውን መሰብሰብ አስፈላጊ ነው፡፡ አጥፊው ጥፋቱን እንዳይክድ፣ ይቅርታ ጠይቁኝ ባዩም በማስረጃ እንዲሞግት፡፡

ማስረጃ መሰብሰብ ሕገ-ወጥ መስሏችሁ የምትፈሩ ካላችሁ አትሳሳቱ፡፡ ሕጋዊ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው መንግሥት ራሱ በፀረ-ሙስና ኮሚሽን በኩል አላግባብ የተገኘ ሀብት ካለ በሚል የባለሥልጣናቱን ሀብት ምንጭ ሳይቀር የማጣራት ማንዴት አለው፡፡ ቁርጠኝነቱ ስለሌለ አልተሳካላቸውም፤ እኛ ግን ይሳካልናል፡፡ በየቀኑ ከታችኛው እርከን (ወረዳ) እስከ ላይ ድረስ የምንጠየቃቸውን ጉቦዎች፣ ባለሀብቱና ባለሥልጣናቱ (ሁለቱም አንድ ናቸው) ኢ-ርትዓዊ በሆነ መንገድ የሚያካብቱትን ሀብት፤ ከትላልቆቹ እስከ ትናንሾቹ ሹመኞች በሕዝብ ላይ የሚፈፅሙትን ግፍ፤ ትንንሽሽም፣ ትልልቅም ሠላማዊ ተቃውሞዎች በተነሱ ቁጥር በንፁሐን ዜጎች ነፍስ ላይ የሚሰነዘሩትን የኃይል እርምጃዎች የሚያጋልጡ ማስረጃዎች ባገኘን ቁጥር ለማስረጃ ዶት ኮም በመላክ ለኢትዮጵያችን የወደፊት መልካም ዕጣ ፈንታ ሲባል እንዲከማቹ የበኩላችንን እናድርግ፡፡ ማስረጃዎቹን መሰብሰቡ ሌላው ቢቀር አጥፊዎቹን ስለሚያስፈራቸው በደላቸውን ሊያላሉልን ይችላሉ፡፡
ቪቫ ላ ታማኝ!!!

Source: http://befeqe.blogspot.se/2015/12/Tamagn-and-masreja-dot-com.html