Tag Archives: Daniel Shibeshi

የተቃዋሚ ፓርቲዎች አመራሮች ቅጣት ተላለፈባቸው

᎐ተጨማሪ ቅጣትም ይጠብቃቸዋል፡፡
• “እኛ የደፈርነው ችሎት አሻንጉሊት ችሎት ነው” አብርሃ ደስታ
• “ችሎቱ ላይ ያጨበጨብነው በማፌዝ ሳይሆን በምሬት ነው”  የሺዋስ አሰፋ
• “ፍትህ ተጠምተናል፣ ፍትህ ለኢትዮጵያ ህዝብ!”  ዳንኤል   ሺበሽ

politician prisoners

በዘለዓለም ወርቃገኘሁ የክስ መዝገብ የሽብር ክስ ተመስርቶባቸው ከስምንት ወራት በላይ በእስር ላይ የሚገኙት የሰማያዊ፣ የአንድነት እንዲሁም የዓረና ትግራይ ፓርቲዎች አመራሮች ‹ችሎት በመድፈር ወንጀል› ጥፋተኛ በመባላቸው ዛሬ መጋቢት 1 ቀን 2007 ዓ.ም በልደታ ከፍተኛው ፍርድ ቤት በዋለው ችሎት በሦስቱ አመራሮች ላይ እያንዳንዳቸው በሰባት ወራት እስራት እንዲቀጡ ተወስኖባቸዋል፡፡

የካቲት 26 ቀን 2007 ዓ.ም ተከሳሾች በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደተፈጸመባቸውና ንብረትም እንደተወሰደባቸው በመግለጽ አቅርበውት ለነበረው አቤቱታ ፍርድ ቤቱ የማረሚያ ቤቱን ምላሽ ሙሉ ለሙሉ በመቀበል አቤቱታቸውን ውድቅ ማድረጉን ተከትሎ 5ኛ ተከሳሽ አቶ የሺዋስ አሰፋ በማጨብጨቡና 3ኛ ተከሳሽ አብርሃ ደስታና 4ኛ ተከሳሽ አቶ ዳንኤል ሺበሽ ሳይፈቀድላቸው ‹‹ጥሩ ፍርድ፣ ጥሩ ብይን›› በማለት አቶ የሺዋስን በመደገፍ ችሎት ደፍረዋል ተብለው ጥፋተኛ መሰኘታቸው ይታወሳል፡፡ በዚህ መሰረት ፍርድ ቤቱ ለዛሬ የቅጣት ውሳኔ ለመስጠት  ተሰይሞ በአብርሃ ደስታ፣ በየሺዋስ አሰፋ እና ዳንኤል ሺበሽ ላይ የ7 ወራት እስራት በይኖባቸዋል፡፡ ሦስቱም ተከሳሾች ፍርድ ቤቱ የሰጠውን ውሳኔ በመቃወም ድጋሜ ችሎት ውስጥ አጨብጭበዋል፡፡ በዚህም ድጋሜ ጥፋተኛ ተብለዋል፤ ከሁለት ቀናት በኋላም የቅጣት ውሳኔ ይወሰንባቸዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ሦስቱ ተከሳሾች ‹‹እድል ስጡን እንናገር፣ አቤቱታም አለን ተቀበሉን›› ቢሉም ፍርድ ቤቱ ሊሰማቸው አልፈለገም፡፡

በተለይ ዳንኤል ሺበሺ ‹‹ሌላ አቤቱታ አለኝ፣ ፍርድ ቤቱ ያዳምጠኝ›› ብሏል፡፡ ፍርድ ቤቱ አሁንም ችሎቱ ላይ እያፌዛችሁ ነው በሚል ጥፋተኛ ሲላቸው ሦስቱም አመራሮች ፍርድ ቤቱን ማስፈቀድ ሳያስፈልጋቸው አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ ‹‹እኛ የደፈርነው ችሎት አሻንጉሊት ችሎት ነው፡፡ ‹Already› የተደፈረ ችሎት ነው›› ሲል አብርሃ ደስታ ተናግሯል፡፡ በዚህ ጊዜ ዳኞቹ ጣልቃ በመግባት፣ ‹‹የምትናገረው ነገር እንደገና ወደ ማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ የሚወስድህ ጉዳይ ነው፤ ምርመራ ይደረግበታል›› ሲሉ አብርሃ በበኩሉ ‹‹አሁንስ ቢሆን የምናገረውን ፖሊስ እየሰማ አይደለምን?›› ሲል መልሷል፡፡ አቶ የሺዋስ አሰፋ በበኩሉ ‹‹ከስምንት ወር በላይ ታፍነናል፡፡ በህግ አይደለም የተያዝነው፡፡ ደግሞ ማጨብጨባችን በችሎቱ ከማፌዝ ሳይሆን ከምሬት በመነጨ ነው፡፡ ህገ-መንግስታዊ  መብታችን ተጥሷል፡፡ እኔ ለምሳሌ የሰማያዊ ፓርቲ አባል በመሆኔ ነው የታሰርኩት፡፡›› ብሏል፡፡

አቶ ዳንኤል ሺበሽ ድግሞ ‹‹አሁንም ችሎት ደፍራችኋል ካላችሁ ቅጣቱን ጨምሩብንና ሸኙን፡፡ በእርግጥ ዳኞች ላይ ያለውን ጫና እንረዳለን፡፡›› ሲል ችሎት ውስጥ ተናግሯል፡፡
በዚህ ሁኔታ በተከሳሾችና በችሎቱ መካከል ያለው አለመግባባት ሲጨምር ዳኞቹ መጋቢት 3/2007 ዓ.ም ለሁለተኛ ጊዜ የቅጣት ውሳኔ እንደሚሰጥ በመጥቀስ ሦስቱ ተከሳሾች ከችሎት በፖሊስ እንዲወጡ ተደርገዋል፡፡ ከችሎት እየወጡ እያሉም አቶ ዳንኤል ሺበሽ ‹‹ፍትህ ተጠምተናል፤ ፍትህ ለኢትዮጵያ ህዝብ!›› እያለ ችሎቱን ለቅቆ ወጥቷል፡፡

በሌላ በኩል ሦስቱ ተከሳሾች ከችሎት መውጣታቸውን ተከትሎ፣ከዚህ ቀደም በማረሚያ ቤቱ ላይ በቀረበው አቤቱታ ዳኞች በሰጡት አስተያየት ላይ አቤቱታ አቅርቦ እንደነበር በማስታወስ አቤቱታው እንዲመዘገብለት የጠየቀው አቶ ሀብታሙ አያሌው፣ ‹‹በበኩሌ ያሉኝን መረጃዎች እያቀረብኩ ስነ-ስርዓቱን አክብሬ ክርክሩን አቀጥላለሁ›› ሲል ተናግሯል፡፡
ምንጭ፡- ነገረ- ኢትዮጵያ

የተቃዋሚ ፓርቲዎች አመራሮች የክስ መቃወሚያ ውድቅ ተደረገ

prisoners

በፌደራል አቃቤ ህግ የሽብር ክስ ተመስርቶባቸው ጉዳያቸው በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ወንጀል ችሎት እየታየ የሚገኙት የተቃዋሚ ፓርቲዎች አመራሮችና ሌሎች በተመሳሳይ መዝገብ የተከሰሱት ተከሳሾች በቀረበባቸው ክስ ላይ ያቀረቡት መቃወሚያ ውድቅ ተደረገባቸው፡፡ አመራሮቹ ጥር 26 ቀን 2007 ዓ.ም ችሎት ቀርበዋል፡፡

በእነ ዘላለም ወርቃገኘሁ የክስ መዝገብ የተከሰሱት የአንድነት፣ የሰማያዊና የአረና ፓርቲዎች አመራሮች የሆኑት አቶ ሀብታሙ አያሌው፣ የሺዋስ አሰፋ፣ አብርሃ ደስታ፣ ዳንኤል ሺበሽ እና ሌሎች ስድስት ተከሳሾች መቃወሚያቸው በፍርድ ቤቱ ውድቅ ተደርጓል፡፡

ተከሳሾች በጠበቆቻቸው አማካኝነት የቀረቡባቸው የተለያዩ የክስ ይዘቶች ላይ መቃወሚያቸውን አቅርበው የነበር ቢሆንም ፍርድ ቤቱ አቃቤ ህግ የተከሳሽ መቃወሚያ ውድቅ እንዲደረግለት የጠየቀውን በመቀበል ‹‹በመቃወሚያው ላይ የተነሱት ነጥቦች በአብዛኛው ማስረጃ በማሰማት ሂደት ወቅት ሊረጋገጡ የሚችሉ ስለሆኑ›› በሚል መቃወሚያቸው ውድቅ ተደርጓል፡፡ በመሆኑም ፍርድ ቤት በቀረበው ክስ አግባብ የክስ ሂደቱ እንዲቀጥል ውሳኔ ሰጥቷል፡፡

በሌላ በኩል ተከሳሾች በእስር ላይ በሚገኙበት ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ላይ ‹‹የመብት ጥሰት እየተፈጸመብን ነው›› በሚል አቤቱታ አቅርበው የነበር ሲሆን በአቤቱታው ላይ እስካሁን ከማረሚያ ቤቱ መልስ አለመሰጠቱ ታውቋል፡፡ አቤቱታው በጽሑፍ ተገልብጦ ለማረሚያ ቤቱ መላኩን የገለጸው ፍርድ ቤቱ፣ ለአቤቱታው መልስ ከማረሚያ ቤቱ እየተጠበቀ እንደሆነ ተገልጹዋል፡፡

በመሆኑም ይህንኑ የማረሚያ ቤቱን መልስ ለመስማትና የክሱን ሂደት ለመቀጠል ፍርድ ቤቱ ለየካቲት 11 ቀን 2007 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

ምንጭ፡-ነገረ-ኢትዮጵያ

ወጣቶቹ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች በድብቅ ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ተደረገ

ከአራት ወራት በፊት በሽብር ስም በአዲስ አበባ የፌደራሉ ወንጀል ምርመራ “ማዕከላዊ” የሚገኙት የአንድነት ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች አቶ አቶ ሀብታሙ አያሌው፣ ዳንኤል ሺበሺ፤ የሰማያዊ እና የአረና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች አቶ የሺዋስ አሰፋና አቶ አብርሃ ደስታ ዛሬ ጥቅምት 20 ቀን 2007 ዓ.ም. ከሰዓት በድብቅ ልደታ ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ መደረጋቸውንና ነገ ጠዋት በድጋሚ ልደታ ፍርድ እንደሚቀርቡ የፍኖተ ነፃነት ዘገባ ያስረዳል፡፡politician prisoners

የህሊና እስረኞቹ እንደተለመደው አራዳ ፍርድ ቤት ይቀርባሉ በሚል የትግል አጋሮችቸው እና ደጋፊዎቻቸውና ጋዜጠኞች ከቀኑ 7 ሰዓት ጀምሮ እስከ 11፡30 በቀጠሮው ስፍራ ቢጠብቁም፤ ፖሊስ በድብቅ ልደታ ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ማድረጉ ተሰምቷል፡፡ ታሳሪዎቹ ልደታ ፍርድ ቤት እንደሚገኙ መረጃ የደረሳቸው የአንድነት ፓርቲ አመራሮች በስፍራው ሲደርሱ አቶ  ሀብታሙ አያሌው፣አቶ ዳንኤል ሺበሺ፣አቶ የሺዋስ አሰፋና አቶ አብርሃ ደስታ በመኪና ውስጥ ሆነው ወደ ማዕከላዊ ሲወሰዱ መመልከታቸውን ተናግረዋል፡፡ ቀደም ብሎም የልደታው ፍርድ ቤት “ጉዳዩን የሚያይ ዳኛ የለም” በማለት ለነገ ጠዋት ጥቅምት 21 ቀን 2007 ዓ.ም ቀጠሮ መሰጠቱም ተጠቁሟል፡፡

ምንጭ፡- ፍኖተ ነፃነት

 

የፖለቲካ አመራሮቹ ችሎት ያለ ተከላካይ ጠበቃ ሲታይ፤ቀጣይ ቀጠሯቸው ግልፅ አይደለም

ዛሬ መስከረም 22 ቀን 2007 ዓ.ም. ፒያሳ አራዳ በሚገኘው የፌደራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት የፖለቲካ  ፓርቲ አመራሮች ጉዳይ በዝግ ችከሎት ያለ ተከላካይ ጠበቃ ቀጠሮ መስጠቱ ተጠቆመ፡፡ የፖለቲካ አመራሮቹ አቶ ሀብታሙ አያሌው የአንድነት ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ፣ አቶ ዳንኤል ሺበሺ የአንድነት ፓርቲ ምክትል የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ፣ አቶ አብርሃ ደስታ የመቀሌ ዩኒቨርስቲ መምህርና የአረና ፓርቲ ምክትል የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ እንዲሁም አቶ የሺዋስ አሰፋ የሰማያዊ ፓርቲ ምክትል የምክር ቤቱ ሰብሳቢ ከተከላካይ ጠበቆቻቸው ጋር ሳይገናኙ ከቀጠሮ ሰዓታቸው አርፍደው ከቀኑ 10 እና 11 ሰዓት ፍርድ ቤት መቅረባቸውን ነገረ ኢትዮጵያ ዘግቧል፡፡

detained politiciansበነበረው የፍርድ ቤት ችሎት ተከላካይ ጠበቃ ደንበኞቻቸውን ህጉ በሚፈቅደው መሰረት በማዕከላዊ ሄደው መጎብኘትና መነጋገር ቢፈልጉም፤ በፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ማዕከል “ማዕከላዊ” ፖሊስ ስላልተፈቀደላቸው ፍርድ ቤት መገኘቱ ለፕሮፖጋንዳ ካልሆነ ከህግ አግባብ ትርጉም ስለሌለው እንደማይገኙ አስቀድመው ማሳወቃቸው ተጠቁሟል፡፡ በችሎትም ቤተሰብ፣ ጋዜጠኛ፣ ዲፕሎማቶች እና ወዳጅ ዘመድ እንዳይከታተል መከልከሉም ታውቋል፡፡ የእስረኞቹ ቀጣይ ቀጠሮ መቼ እንደሆነ እስካሁን ከፍርድ ቤቱ ማግኘት ባይቻልም፤ እንደ ነገረ ኢትዮጵያ ዘገባ ከሆነ የማዕከላዊ ምርመራ ኃላፊ አቶ ተክላይ ሹመት ተጠርጣሪዎቹ የተቀጠሩት ለጥቅምት 20 ቀን 2007 ዓ.ም. ሲሉ፤ ሌላ ፖሊስ ደግሞ ለጥቅምት 22 ቀን 2007 ዓ.ም. ነው የሚል ጥቆማ መስጠታቸውን የነገረ ኢትዮጵያ ጋዜጣ ምንጮች አስታውቀዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ እስረኞቹ እስካሁን በነበረው ምርመራ ፖሊስ ምንም ዓይነት ለወንጀል ክስ የሚያበቃ መረጃ ባለማግኘቱ፤ ወደ ኃይል እርምጃ በመሄድ ፖሊስ የሚፈልገውን ቃል እስረኞቹ ያልፈፀሙትን አስገድዶ የእምነት ቃል እንዳስፈረማቸው የማዕከላዊ ምንጮች አስታውቀዋል፡፡ ይሄም ለህዝቡና ለመገናኛ ብዙኃን እንዳይገለፅና ፍርድ ቤትም በቅሬታ መልክ እንዳይቀርብ ስለተፈለገ ነው ተከላካይ ጠበቆቹ እንዳይጎበኙ የተከለከሉት ሲሉ ምንጮች አስታውቀዋል፡፡  በዚህም የዛሬው ችሎት ያለጠበቃ ጭምር በዝግ ችሎት መካሄዱ የተጠቆመ ሲሆን፤ የቀጠሯቸው ቀንም ከላይ ከተጠቀሰው ውጭ እስካሁን ትክክለኛውን ከፍርድ ቤቱ ማረጋገጥ እንዳልተቻለ መረጃዎእ አመልክተዋል፡፡ ችሎቱን ለመታደም ወደ ስፍራው ያቀኑ ሰዎችም ፍርድ ቤቱ ግቢ ሲገቡ ከወትሮ በተለየ በፖሊሶች ከፍተኛ ፍተሻ፣ እንግልትና ወከባ እንደተፈፀመባቸው  የዓይን እማኞች ገልፀዋል፡፡

ማሰርና ማሳደድ መፍትሄ ይሆናል?

ብስራት ወልደሚካኤል
afrosonb@gmail.com

በቀድሞ ታጣቂዎች እንደ ጭራቅና አውሬ ይሳል የነበረው የደርግ ስርዓት ወድቆ ስልጣን በአማፂዓን እጅ ከገባ 23 ዓመታት አልፈዋል፡፡ ነገር ግን የታሰበው ለውጥ ዛሬም ቢሆን መናፈቁን አልተወም፡፡ ምክኔቱም ያኔ ማሰር ነበር፤ ዛሬም ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ ያኔም መወንጀልና መፈረጅ ነበር ዛሬ ግን ተባብሷል፡፡ ለእኔ ከድሮ የተለየ ተቀይሮ ያገኘሁት በዋናነት የመሪዎች ስምና ልብሳቸው እንጂ ስራቸው ያው ነው፡፡

በዘመነ ደርግ ጠባብነትና ዘረኝነትን እንዲሁም ኢትዮጵያ ላይ ጥላቻ ያላቸውን በሙሉ ስልጣኑን ሊቀናቀኑ ካሰቡት እኩል በጠላትነት ይፈረጃሉ፡፡ በዘመነ ኢህአዴግ ደግሞ ኢትዮጵያዊነትን ማስቀደምና ለኢትዮጵያውያን በእኩል ዓይን መቆምና መቆርቆር እንደ ወንጀል ይታያል፡፡ሁለቱም ወደ ስልጣን ሲወጡ በጠብመንጃ ሲሆን፤ ስልጣናቸውንም ያስጠበቁትን የሚያስጠብቁት እንዲ በጦር መሳሪያ ነው፡፡ምን አለፋችሁ፤ ልዩነቱን “…ጃሃ ያስተሰርያል” የሚለው የአርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን (የቴዲ አፍሮ) ሙዚቃ በደንብ ይገልፀዋል፡፡

sssበሁለቱ መካከል ያለው መሰረታዊ ልዩነት ደርግ የማይፈልገውን ነገር በግልፅ በአዋጅ ይደነግጋል፤ከአዋጅ ወይም ህግ ውጭ ይቀጣል፡፡ ኢህአዴግ ደግሞ የሚፈልገውንም ሆነ የማይፈልገውን በህገ መንግስት እውቅና ሰጥቶ የማይፈልገውን በሌላ አዋጅ ይቀጣል፣ያስራል፡፡ ልዩነታቸው የመሪዎች ስም፣ የለበሱት ልብስና አካሄዳቸው እንጂ መሰረታዊ የልዩነት ባህርይ አይታይባቸውም፡፡ ለዚህም አሁን በስልጣን ላይ ያለው ኢህአዴግ ከደርግ በባሰ ያከናወናቸውን እና እያከናወናቸው ካሉት አሉታዊ ተግባራት መካከል በዋናነት የእስር ዘመቻውን ማንሳቱ በቂ ነው፡፡

በተለይ በምርጫ 1997 ዓ.ም. ኢህአዴግ በአደባባይ መሸነፉን እና የህዝብን ድምፅ መቀማቱን የሚያሳብ በርካታ ተግባራትን ሲያከናውን ዋናው ገመናውን የሚያጋልጡና በአብዛኛው ህዝብ ዘንድ ተቀባይነትና ተወዳጅነት ያላቸውን በሰበብ አስባቡ አስሮ ማሰቃየትን እንደ ትልቅ አማራጭ መጠቀም ጀመረ፡፡ ለዚህ በምርጫው ያሸነፉት የቀድሞ ቅንጅት አመራሮችን ከወነጀለበት በኢትዮጵያ 2000 ዓ.ም. ዋዜማ ከእስር ከፈታ በኋላ አዲሱ ቀዳሚ እስረኛ አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ነበር፤ የእስርዓ ምዕት ኢትዮጵያ ጅማሮ እስረኛ፡፡ ይህም አዲስ አበባና አስመራን ጨምሮበመላው ዓለም ጥያቄና ተቃውሞ ከማስነሳቱ በተጨማሪ ከእስር ሲፈታም የህዝብ ድጋፍ በመላው ዓለም ተጠናክሮ እስከዛሬም ድረስ ዘልቋል፡፡

ከዚህ በኋላ የኢህአዴግ ጥላቻ እየተባባሰ፣ ለስልጣን ያለው ጥማት ሰርክ እንደ አዲስ ወይን እየጣመው ይሄድ ጀመር፡፡ ከስልጣናቸው በዕድሜ ይፍታህ የተሰናበቱት ሟቹ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ በስልጣናቸው እስከ መቃብር አፋፍ ዋስትና ይሆናል ያሏቸውን አፋኝ ህጎች ፀድቀው ተግባር ላይ እንዲውሉ ቀን ከሌት ኳተኑ፡፡ በዚህም የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኀበራት አዋጅ፣ የፕሬስ አዋጅ፣ የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅ፣…ይገኙበታል፡፡

በተለይ በተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶች እና የነፃ ጋዜጠኞች ከፍተኛ ተቃውሞ የገጠመው የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅ ሰኔ 30 ቀን 2001 ዓ.ም. ፀድቆ ለምርጫ 2002 ዓ.ም. ማፈኛ ተዘጋጀ፡፡ የዚህም ገፈት የዴሞክራሲ እንቅስቃሴዎችን ገድቦ የነበረውን ተስፋ መቀመቅ ውስጥ ከተተው፡፡ ከዚህ በኋላ በየካቲት 2003 ዓ.ም. በቱኒዚያ መሐመድ ቡዓዚዝ የተጀመረው የአረቡ ፀደይ አብዮት በሰሜን አፍሪካን እና መካከለኛ ምስራቅ አረብ ሀገሮች መቀጣጠሉን የተመለከቱት አቶ መለስና ተከታዮቻቸውና አጋሮቻቸው በኢትዮጵያም ይከሰታል በሚል የአስር አደኑንን አጣደፉት፡፡

የአረቡን አብዮት ተከትሎ በኢትዮጵያ የእስር ሰንሰለቱን የጀመሩት እንደ ታሰበው ጋዜጠኞች እና የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ናቸው፡፡ በቀዳሚነትም በወርሃ ሰኔ 12 ቀን 2004 ዓ.ም. ከፖለቲከኛ አቶ ዘሪሁን ገ/እግዚአብሔር፣ ሰኔ 14 ቀን 2003 ዓ.ም. ደግሞ ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ፣ ርዕዮት አለሙ፤ ከዚያም በክረምት 2003 ዓ.ም. የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህርና የኦፌኮ/መድረክ አመራር አቶ በቀለ ገርባና አቶ ኦልባና ሌሊሳ የእስር ሰለባ ሆኑ፡፡

andሌላው ከኢትዮጵያውያን በተጨማሪ ሁለት ሲውድናውያን ጋዜጠኞች ማርቲን ሸብይ እና ጆሃን ፐርሰን ሽብርተኝነትን ደግፈዋል በሚል በዚሁ የፀረ-ሽብርተኝነት ሰለባ በመሆን ከ14 ወራት የሰቆቃ እስር በኋላ በዓለም አቀፉ ማኀበረሰብ ጫና መስከረም 1 ቀን 2004 ዓ.ም.ተለቀዋል፡፡ በመቀጠል መስከረም 3 ቀን 2004 ዓ.ም. ደግሞ ታዋቂው የፖለቲካ ተንታኝ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፣በብዙ ወጣቶች ዘንድ በቅንነቱና ፍቅርን በመስጠት እንዲሁም ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልን አጥብቆ በመደገፍ የሚከራከረው የአንድነት/መድረክ አመራር አቶ አንዱዓለም አራጌ እና ሌሎች የአንድነት ፓርቲ አመራሮች አቶ ናትናኤል መኮንን፣አቶ ዮሐንስ ተረፈና ሻምበል የሺዋስ ይሁንዓለምንና አቶ አንዱዓለም አያሌውን ጨምሮ አቶ ክንፈ ሚካኤል ደበበና ሌሎች ሰዎችም በሽብርተኝነት ስም ወደ ወህኒ ወረዱ፡፡ በዚህም አፍቃሬ መንበር አቶ መለስ የፈሩትን የአረቡን አብዮት በዚህ ያለፉ ይመስል ጀብደኝነት ተሰምቷቸው፤ ተጠርጣሪዎቹ ገና በፍርድ ቤት ብይን ሳይሰጥባቸው አሸባሪዎች ናቸው ሲሉ ለተወካዮቻቸው አረጋገጡ፡፡
ያሰሯቸው ላይ ቀድመው ወንጀለኛ በማለት ፍርድ በመስጠት መከራን የደገሱት አቶ መለስ ባልጠበቁት ሁኔታ በጠና ታመው በአውሮፓ ቤልጄየም ብራሰልስ አንድ የዩኒቨርስቲ ሪፈራል ሆስፒታል ተኙ፡፡ በመጨረሻም እንደ ሆስፒታሉ ምንጮች ከሆነ ሐምሌ 13 ቀን 2004 ዓ.ም. እንደወጡ ላይለመሱ ብዙ ለመኖር ያሰቡበትን በ21 ዓመታት የስልጣን ዘመናቸው እንደ ግል ርስታቸው ያስቡት የነበረውን ቤተመንግስት ጥለው እስከወዲያኛው ተሰናበቱ፡፡

bekይሁን እንጂ አጋሮቻቸውና የቅርብ የኢህአዴግ አመራሮች መታመማቸውን እንኳ ለህዝብ ሳይገልፁ በድንገት የሞቱትን ሰውዬ ከጋዜጠኞች ጥያቄ ቢበረታባቸው በቅርቡ ተመልሰው ስራ ይጀምራሉ የሚል መልስ ሰጡ፡፡ በኋላም የተባለው ሳይሆን ፈጣሪ የወሰነው ሞት እርግጥ መሆኑ እና ነሐሴ 14 ቀን 2004 ዓ.ም. ሌሊት እንዳረፉ ተደርጎ ነሐሴ 15 ቀን 2004 ዓ.ም. ማለዳ አንድ ለእናቱ በሆነው ሀገሪቱ ቴሌቪዥን ኢቴቭ ይፋ ተደረገ፡፡ ከዚያም ነሐሴ 27 ቀን 2004 ዓ.ም. ግብዓተ መሬታቸው እንደ ተከናወነ በግብረ-አበሮቻቸውና በመንግስት ሹማምንት ከተገለፀ በኋላ “…የመለስን ራዕይ እናስቀጥላለን!” የሚል መፈክር መሰማት ጀመረ፤የተባለው ራዕይ ኑዛዜ አሁንም ባያበቃም፡፡

በርግጥ አቶ መለስ ራዕይ ነበራቸው ከተባለ፤ እስከ ህልፈታቸው ድረስ የትኛውንም መንገድ ተጠቅመው ከቤተመንግስት ሳይወጡ ተቀናቃኞቻቸውን በማሰርና በማጥፋት በስልጣን መቆየት ነው፡፡ ነበራቸው የተባለው ራዕይ አሳቸው ሲሞቱ አብሮ ሞቷል፡፡ ይህ ደግሞ ራዕይ ሳይሆን የስልጣን ጥም እንጂ ህዝባዊና ሀገራዊ አይደለም፡፡ ተከታዮቻቸውም እናስቀጥላለን ያሉት ይህንኑ በመሆኑ ልክ እንደሳቸው ተመሳሳይ ድርጊት መፈፀሙትን እንደ ትክክለኛ እና ቅዱስ ተግባር ማከናወን ጀመሩ፡፡ ለአብነትም መጪውን ምርጫ 2007 ዓ.ም. ተከትሎ ለኢህአዴግና አመራሮቹ ስልጣን ማክተሚያ ምክንያት ይሆናሉ ብለው ያሰቧቸውን ማጥመድ፣ ማሰርና መፈረጁን ተያያዙት፡፡ የዚህ ሰለባ ከሆኑት መካከል በሚያዝያ 2006 ዓ.ም. መጨረሻ አካባቢ ጋዜጠኛ አስማማው ኃይለጊዮርጊስ፣ ጋዜጠኛ ተስፋዓለም ወልደየስ፣ ጋዜጠኛ ኤዶም ካሳዬና ጋዜጠኛ አዚዛ መሐመድ፤ እንዲሁም የኢትዮጵያው ዞን 9 ብሎገሮች በፈቃዱ ኃይሉ፣ዘለዓለም ክብረት፣ አቤል ዋበላ፣ ማህሌት ፋንታሁን፣አጥናፍ ብርሃኔ እና ናትናኤል ፈለቀ ቀዳሚዎቹ ናቸው፡፡

mesበ2004ዓ.ም. ዛሬም ድረስ ምላሽ እንዳላገኘ የሚነገርለት የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ጥያቄ ጋር በተያያዘ የሙስሊሙ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት፣ጋዜጠኛ ዩሱፍ ጌታቸውና ጋዜጠኛ ሰለሞን ከበደ ታስረው እስካሁን በወህኒ ቤት ይገኛሉ፡፡ ምንም እንኳ ጉዳያቸው በፍርድ ቤት የተያዘ ቢሆንም እስካሁን ብይንም ሆነ እልባት አላገኘም፡፡ ይሄ ሁሉ በአቶ መለስ አገዛዝ ዘመን የተጀመረ እስር ነው፡፡
በመቀጠልም በሀገር ውስጥ የኢህአዴግ መንግስት እውቅና ያልተቸረውና በሽብርተኝነት የተፈረጀው የግንቦት 7 የፖለቲካ ማኀበር ዋና ፀሐፊ የነበሩት አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ በየመን ፀጥታ ኃይሎች ታግተው ለኢትዮጵያው ገዥ ተላልፈው ተሰጥተዋል፡፡ አቶ አንዳርጋቸው ቀደም ሲል የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ አድርጋችኋል በሚል በነ ጄነራል ተፈራ ማሞ ክስ መዝገብ ከነ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ጋር በሌሉበት የሞት ፍርድ ተፈርዶባቸውል፡፡ የሞት ፍርድ ተፍርዶባቸው የነበሩት አቶ አንዳርጋቸው እንደገና በ2005 ዓ.ም. ደግሞ በነ አንዱኣለም አራጌና ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ክስ በሌሉበት የዕድሜ ልክ ፅኑ እስራት ተፈርዶባቸዋል፡፡ ይሁን አንጂ ወደፊት ትናው ክስ ተፈፃሚ እንደሚሆንና በቀጣይ ስለሚኖረው የፍርድ ሂደት ዕድሜ ከሰጠን አብረን የምናየው ነው ሚሆነው፡፡

ከላይ የተጠቀሰው እንዳለ እስሩ ተጠናክሮ በመቀጠል በሀገር ውስጥ በገዥው ስርዓት ህጋዊ እውቅና ተችሯቸው የሚንቀሳቀሱየፖለቲካ ፓርቲ ወጣት አመራሮች ተለቅመው ታሰሩ፡፡ እነኚህም መካከል በማኀበራዊ ሚዲያ የተለያዩ በሳል ፅሑፎችን በመፃፍ የሚታወቀው፣ የመቀሌ ዩኒቨርስቲ መምህርና የዓረና ትግራይ/መድረክ አመራር አቶ አብርሃ ደስታ፤ ከአንድነት ፓርቲ አመራሮች አቶ ሀብታሙ አያሌውና አቶ ዳንኤል ሺበሺ እንዲሁም ከሰማያዊ ፓርቲ አቶ የሺዋስ አሰፋ ይገኙበታል፡፡አራቱም ወጣት ፖለቲከኞች በፓርቲያቸውም ይሁን በሀገሪቱ ሰለማዊ የፖለቲካ ትግል በጎ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች መሆናቸው ይነገርላቸዋል፡፡
ሌላው እየተወሰደ ያለውን እስር በመሸሽ ከምርጫ 1997 ዓ.ም. ወዲህ ከ2005 ዓ.ም.ጀምሮ እስከ ያዝነው 2006 ዓ.ም. ድረስ ኢትዮጵያውያን ጋዜጠኞች ተሰደዋል፡፡ ለዚህም በዋነኝነት እንደ አስረጂ ሊጠቀስ የሚችለው በአሁን ሰዓት በጅምላ እየተፈፀመ ያለው እስር ነው፡፡ በአቶ መለስ ዜናዊ የስልጣን ዘመን የተጀመረው የጋዜጠኞችና ብሎገሮች እስር በአሁን ወቅት ሶስት የውጭ ዜጎችን ጨምሮ 20 የደረሰ ሲሆን፤ ከላይ በስም ከተጠቀሱት የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች በተጨማሪ በርካታ የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ ማኀበር አባላትም በእስር ላይ ይገኛሉ፡፡ ይሄ ደግሞ ዴሞክራሲያዊ መብቶች ዝግ ከነበሩበት የደርግ ጊዜ ጋር ሲነፃፀር፤ በኢህአዴግ ጊዜ 20 ጋዜጠኞችና ብሎገሮችን በማሰር በሀገሪቱ ታሪክ ቀዳሚውን አሉታዊ ስፍራ እንድይዝ ያደርገዋል፡፡ በዚህም በፀታ ኃይሉና በፍትህ ተቋማቱ ላይ ተጨማሪ የስራ ጫና ከመፍጠር በዘለለ የታሰበውን የፖለቲካ ትርፍ ያስገኛል ተብሎ አይጠበቅም፡፡

እንደ ገዥው ስርዓት አመራሮች፣ ደጋፊዎችና የፀጥታ ኃይሎች ገለፃ ከሆነ እስሩ የሚቆም አይደለም፡፡ በቀጣይ የዚህ ሰለባ ማን እንደሚሆን ባይታወቅም፤ እንደተባለው የሚተገበር ከሆነ በድጋሚ ቀሪ ጋዜጠኞች እና ፖለቲካኖች የእስር ስለባው ሊሆኑ እንደሚችሉ አያጠያይቅም፡፡ ምክንያቱም ከሌላው በተሻለ መብቶቻቸውን እየተገበሩና እየተጠቀሙ ማኀበረሰቡ ላይ በጎ ተፅዕኖ በመፍጠር የስርዓቱ ስልጣን ፈተና ይተረጎማሉና፡፡ አቶ መለስ ከመሞታቸው በፊት ምርጫ ሲደርስና ለስልጣናቸው የሚያሰጋቸው ነገር ብልጭ ሲልባቸው የሚወስዷቸው ርምጃዎች አሁን በስልጣን ላይ ባሉ ተከታዮቻቸው ተጠናክረው መቀጠላቸው አንዱ የመለስ ራዕይ ነው ሊያስብል ይችላል፡፡ ይህም አመራሮቹ እናስቀጥለዋለን ያሉት የአቶ መለስ ራዕይ አንዱ አካል ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ ምክንያቱም ያኔ በሳቸው ዘመን የተጀመረው ዛሬም በቃ ሊባልና መቋጫ ሊበጅለት አልቻለምና፡፡

አሁን በመንግስት አመራሮች ኢትዮጵያውያን ጋዜጠኞች፣ ብሎገሮችና ፖለቲካኞች ላይ ትኩረት ያደረገ የእስር ዘመቻ ከዚህ በፊት እንደ ተወዳጅ ነጠላ ዜማ ሲዜም የነበረውን “የመለስን ራዕይ እናስቀጥላለን” አባባል የሚታየው የእስር ዘመቻ መሆኑን በማሳበቅ በደጋፊዎቻቸው እንደ ሊቀ ሊቃውንትና ባለራዕይ የተወሰዱት ሟቹ ሰውዬ እንዲኮነኑ ማድረጉ አይቀርም፡፡ በየትኛውም ዓለም እንደሚታየው የፖለቲካ ርምጃና ተሞክሮ ሰዎችን ያውም ዜጎችን አሸባሪ ብሎ ማሰር በስልጣን ለመቆየትም ሆነ ለመረጋጋት መፍትሄ ሊሆን አይችልም፡፡ እንዲህ ዓይነት ርምጅ መፍትሔ ቢሆን ኖሮ የሊቢያው መሪ ኮሎኔል ሙዓመር ጋዳፊ፣ የግብፁ ሆስኒ ሙባረክ፣የየመኑ ዓሊ አብደላ ሳላህ በስልጣን ላይ መቆየት በቻሉ ነበር፤ግን አልሆነም፡፡

ነገርን ግን የህዝቡን ቁጣ በመቀስቀስ በውርደት ከስልጣን እንዲወርዱ አስገደዳቸው እንጂ መፍትሄ አልሆናቸውም፡፡ ስለዚህ በስልጣን ለመቆየት ጉጉቱ ካለ እንኳ የዜጎችን መብት፣ፍላጎትና ጥቅም ማክበርና ማስጠበቅ የተሻለ አማራጭ ነው፡፡ መፍትሔውን ልክ እንደ ጥሎ ማለፍና ፍፃሜ የአትሌቲክስ ውድድር ዜጎችን በማሰርና እንዲሰደዱ በማድረግ ዙሩን ማክረር ታምቆ የቆየውን የህዝብን ስሜት ባልተጠበቀ ሰዓት እንዲፈነዳ በማድረግ ሌላ ችግር ሊወልድ ይችላል፡፡የሚፈራው ችግር የሚከሰት ከሆነ ደግሞ የበለጠ ለገዥዎችም፣ ለህቡም ሆነ ለሀገሪቱ አሉታዊ ተፅዕኖ ማስከተሉ እሙን ነው፡፡