በቅርቡ የተሰደደው ጋዜጠኛ ሚሊዮን ሹሩቤ ህይወቱ አለፈ
የማራኪ መፅሔት ባለቤት እና ማኔጂንግ ዳይሬክተር የነበረው ጋዜጠኛ ሚሊዮን ሹሩቤ በስደት በሚገኝበት ናይሮቢ ኬኒያ ጥቅምት 3 ቀን 2007 ዓ.ም. በድንገት ህይወቱ ማለፉን ከማኀበራዊ ገፆች የተገኙ መረጃች እና ምንጮች ጠቁመዋል፡፡ ኢህአዴግ መራሹ የኢትዮጵያ መንግስት በጅምላ ያደረገውን የመፅሔቶች እና ጋዜጣ ክስ እና የበርካታ ጋዜጠኞችን እና ብሎገሮችን እስርን ፍርሃት ተከትሎ በቅርቡ ከተሰደዱ ጋዜጠኞች መካከል ጋዜጠኛ ሚሊዮን ሹሩቤ አንዱ ነበር፡፡
ጋዜጠኛው በስደት ኬኒያ ከሚገኝበት አንድ ናይሮቢ ሆስፒታል በህክምና ሲረዳ ቢቆይም ህይወቱን ማትረፍ እንዳልተቻለ ታውቋል፡፡ ጋዜጠኛው ከኢትዮጵያ ከተሰደደ ገና ሁለት ወር እንኳ እንዳልሞላው ለማወቅ ተችሏል፡፡ ጋዜጠኛው ህይወቱ እስካለፈበት ድረስ በኢትዮጵያ ነፃ ፕሬስ ውስጥ ከ12 ዓመታት በላይ እንዳገለገለና የድርሰት ስራም እንዳለው ተጠቁሟል፡፡
ጋዜጠኛ ሚሊዮን በተወለደ በ33 ዓመቱ በስደት ናይሮቢ ኬንያታ ናሽናል ሆስፒታል ቢያርፍም፤የቀብር ስነስርዓቱ እሁድ ጥቅምት 9 ቀን 2007 ዓ.ም. በትውልድ አካባቢው ይርጋ ጨፌ ከተማ ቅድስት ኪዳነ ምህረት ቤተ ክርስቲያን ተፈፅሟል፡፡ ጋዜጠኛው የአንድ ወንድ ልጅ አባት ነበር፡፡
አዲስ ሚዲያም በጋዜጠኛው ሞት የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን እየገለፀ፤ ለጋዜጠኛ ሚሊዮን ፈጣሪ ነፍሱን በገነት እንዲያኖር፤ ለቤተሰቦቹ፣ለወዳጅ ዘመዶቹና አድናቂዎቹ መፅናናትን ይመኛል፡፡
ኢ/ር ግዛቸው ሽፈራው በገዛ ፍቃዳቸው ሥልጣናቸውን ሲለቁ፤ አቶ በላይ ፍቃዱ ቀጣዩ ፕሬዘዳንት በመሆን ተመርጠዋል
የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) ብሔራዊ ምክር ቤት ዛሬ ጥቅምት 2 ቀን 2007 ዓ.ም. በነበረው ስብሰባ ፕሬዚዳንቱ ኢ/ር ግዛቸው ሽፈራው ሪፖርት ካቀረቡ በኋላ፤ ከውስጥና ከውጭ በተፈጠሩ አንዳንድ የማያሰሩ ችግሮች፣ ካለባቸው የሥራ ጫና እና ፓርቲው ወደፊት አንድነቱን ጠብቆ ለ2007 ምርጫ አሸናፊ ሆኖ እንዲወጣ በማሰብ ስልጣናቸውን በቃዳቸው መልቀቃቸውን ይፋ ማድረጋቸው ተጠቁሟል፡፡
ምክር ቤቱም በፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ መሰረት የፕሬዘዳንቱን ጥያቄ በአድናቆት ተቀብሎ፤ ፓርቲውን በፕሬዘዳንትነት በመምራት መጪውን ምርጫ ውጤታማ ለማድረግ እንዲያስችል 1ኛ. አቶ በላይ ፈቃዱ፣2ኛ. አቶ ደረጀ ኃይሉ እና 3ኛ. አቶ ትዕግስቱ አወሉን በዕጩነት በማቅረብ፤አቶ በላይ ፈቃዱን በፕሬዘዳንት መርጧል፡፡ ምርጫውም በምስጢር ድምፅ አሰጣጥ እዛው በፓርቲው ምክር ቤት የተከናወነ ሲሆን፤በመጨረሻም አቶ በላይ ፈቃዱ በከፍተኛ ድምፅ ማሸነፋቸው መረጃዎች አመልክተዋል፡፡
ከምርጫው ውጤት በኋላ አቶ በላይ በቀጣይ የስልጣን ጊዜያቸው ፓርቲውን ለመምራት ቃለ መሐላ የፈፀሙ መሆናቸውን የፍኖተ ነፃነት ዘገባ ያስረዳል፡፡ አቶ በላይ ጠንካራ የፖለቲካ ልምድና ተሳትፎ ካላቸው የፓርቲው ወጣት አመራሮች መካከል በውጤታማነት ከሚጠቀሱት አንዱ እንደሆኑ የተጠቆመ ሲሆን፤የትምህርት ደረጃቸውም በስታስቲክስ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የመጀመሪያ ድግሪ (BSc) እና በኢኮኖሚ ፖሊሲ አናሊስስ የማስተርስ ድግሪ (MSc) ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ያላቸው ሲሆን፤ በስራ ልምዳቸውም በተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አገልግለዋል፡፡ አቶ በላይ ወደ ፓርቲው ፕሬዘዳንትነት ከመምጣታቸው በፊት፤ በራሳቸው የጥናትና ምርምር ድርጅት በማኔጂንግ ዳይሬክተርነት ያገለግሉ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡
ፓርቲው መጪውን 2007 ዓ.ም. ምርጫ እንዲያሸንፍ ትልቅ ሚና ይኖራቸዋል በሚል ከአባላትና ከደጋፊዎች ትልቅ ተስፋ እንደተጣለባቸውና ኃላፊነታቸውንም በስኬት ሊወጡ እንደሚችሉ ተገምቷል፡፡
የኢትዮ-ምህዳር ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ በአምስት ሺህ ብር ዋስ መለቀቁ ተሰማ
ቀደም ሲል መስከረም 23 ቀን 2007 ዓ.ም. ለምሳ ሲወጡ ቢሯቸው ታሽጎ ሰኞ መስከረም 26 ቀን 2007 ዓ.ም. የተከፈተው እና ለሰባት ሳምንታት ህትመቷ የተቋረጠው የኢትዮ-ምህዳር ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ጌታቸው ወርቁ በፌደራል የወንጀል ምርመራ ማዕከል ማዕከላዊ ፖሊስ ቃሉን እንዲሰጥ በተደረገለት ጥሪ መሰረት ማክሰኞ መስከረም 27 ቀን 2007 ዓ.ም. ማዕከላዊ መቅረቡ ታውቋል፡፡ ጋዜጠኛው ማዕከላዊ የተጠራው የቀድሞው መኢአድ አመራር የነበረው አቶ ማሙሸት አማረ ክስ መሰረት ቃሉን እንዲሰጥ የነበረ ቢሆንም፤ ማዕከላዊ ምርመራ ክፍልም የጋዜጠኛውን ቃል ከተቀበለ በኋላ ጉዳዩ አስፈላጊ ሲሆን እንደሚቀርብ በመጠቆም በ5,000.00 (አምስት ሺህ ) ብር ዋስ መለቀቁ ተጠቁሟል፡፡
ኢትዮ-ምህዳር ጋዜጣ መንግስት በጋዜጠኞች፣ በመፅሔቶች እና ጋዜጦች ላይ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የሚወነጅል ዘጋቢ ፊልም በተደጋጋሚ መስራቱን ተከትሎ አታሚ ቤቶች የነፃ ጋዜጦችን እና መፅሔቶችን እንዳያትሙ በተለያዩ የመንግስት አካላት ጫና በማሳደሩ ለ7 ሳምንታት ከህትመት መቋረጧን ምንጮች ጠቁመዋል፡፡ የጋዜጣው አዘጋጆች በተደጋጋሚ ስራውን አጠናቀው ቀድም ሲል የሚያትምላቸው አታሚ ድርጅትና ሌሎች አታሚዎች ጋር በተደጋጋሚ ቢኬድም እስካሁን ለማተም ፈቃደኛ እንዳልሆኑ መረጃዎች አመልክተዋል፡፡ መንግስት የነፃ መገናኛ ብዙኃን ጋዜጠኞችን፣ ጋዜጦችን እና መፅሔቶችን በተደጋጋሚ መወንጀሉ እና መክሰሱን ተከትሎ የተለያዩ በርካታ ነፃ ጋዜጦችና መፅሔቶች ከህትምት እና አንባቢ ውጭ እንዲሆኑ መደረጉ ይታወቃል፡፡ ይህንንም ተከትሎ ከሚያዝያ 2006 ዓ.ም. እስከ ነሐሴ 2006 ዓ.ም. መጨረሻ ድረስ ከ25 ያላነሱ የነፃው ፕሬስ ጋዜጠኞች የግፍ እስርና ስቃዩን በመሸሽ መሰደዳቸው ይታወቃል፡፡ በአሁን ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ 3 የውጭ ዜጎችን ጨምሮ ከ17 ያላነሱ ጋዜጠኞች እና ብሎገሮች በግፍ ታስረው ይገኛሉ፡፡
፡
ማሰርና ማሳደድ መፍትሄ ይሆናል?
ብስራት ወልደሚካኤል
afrosonb@gmail.com
በቀድሞ ታጣቂዎች እንደ ጭራቅና አውሬ ይሳል የነበረው የደርግ ስርዓት ወድቆ ስልጣን በአማፂዓን እጅ ከገባ 23 ዓመታት አልፈዋል፡፡ ነገር ግን የታሰበው ለውጥ ዛሬም ቢሆን መናፈቁን አልተወም፡፡ ምክኔቱም ያኔ ማሰር ነበር፤ ዛሬም ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ ያኔም መወንጀልና መፈረጅ ነበር ዛሬ ግን ተባብሷል፡፡ ለእኔ ከድሮ የተለየ ተቀይሮ ያገኘሁት በዋናነት የመሪዎች ስምና ልብሳቸው እንጂ ስራቸው ያው ነው፡፡
በዘመነ ደርግ ጠባብነትና ዘረኝነትን እንዲሁም ኢትዮጵያ ላይ ጥላቻ ያላቸውን በሙሉ ስልጣኑን ሊቀናቀኑ ካሰቡት እኩል በጠላትነት ይፈረጃሉ፡፡ በዘመነ ኢህአዴግ ደግሞ ኢትዮጵያዊነትን ማስቀደምና ለኢትዮጵያውያን በእኩል ዓይን መቆምና መቆርቆር እንደ ወንጀል ይታያል፡፡ሁለቱም ወደ ስልጣን ሲወጡ በጠብመንጃ ሲሆን፤ ስልጣናቸውንም ያስጠበቁትን የሚያስጠብቁት እንዲ በጦር መሳሪያ ነው፡፡ምን አለፋችሁ፤ ልዩነቱን “…ጃሃ ያስተሰርያል” የሚለው የአርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን (የቴዲ አፍሮ) ሙዚቃ በደንብ ይገልፀዋል፡፡
በሁለቱ መካከል ያለው መሰረታዊ ልዩነት ደርግ የማይፈልገውን ነገር በግልፅ በአዋጅ ይደነግጋል፤ከአዋጅ ወይም ህግ ውጭ ይቀጣል፡፡ ኢህአዴግ ደግሞ የሚፈልገውንም ሆነ የማይፈልገውን በህገ መንግስት እውቅና ሰጥቶ የማይፈልገውን በሌላ አዋጅ ይቀጣል፣ያስራል፡፡ ልዩነታቸው የመሪዎች ስም፣ የለበሱት ልብስና አካሄዳቸው እንጂ መሰረታዊ የልዩነት ባህርይ አይታይባቸውም፡፡ ለዚህም አሁን በስልጣን ላይ ያለው ኢህአዴግ ከደርግ በባሰ ያከናወናቸውን እና እያከናወናቸው ካሉት አሉታዊ ተግባራት መካከል በዋናነት የእስር ዘመቻውን ማንሳቱ በቂ ነው፡፡
በተለይ በምርጫ 1997 ዓ.ም. ኢህአዴግ በአደባባይ መሸነፉን እና የህዝብን ድምፅ መቀማቱን የሚያሳብ በርካታ ተግባራትን ሲያከናውን ዋናው ገመናውን የሚያጋልጡና በአብዛኛው ህዝብ ዘንድ ተቀባይነትና ተወዳጅነት ያላቸውን በሰበብ አስባቡ አስሮ ማሰቃየትን እንደ ትልቅ አማራጭ መጠቀም ጀመረ፡፡ ለዚህ በምርጫው ያሸነፉት የቀድሞ ቅንጅት አመራሮችን ከወነጀለበት በኢትዮጵያ 2000 ዓ.ም. ዋዜማ ከእስር ከፈታ በኋላ አዲሱ ቀዳሚ እስረኛ አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ነበር፤ የእስርዓ ምዕት ኢትዮጵያ ጅማሮ እስረኛ፡፡ ይህም አዲስ አበባና አስመራን ጨምሮበመላው ዓለም ጥያቄና ተቃውሞ ከማስነሳቱ በተጨማሪ ከእስር ሲፈታም የህዝብ ድጋፍ በመላው ዓለም ተጠናክሮ እስከዛሬም ድረስ ዘልቋል፡፡
ከዚህ በኋላ የኢህአዴግ ጥላቻ እየተባባሰ፣ ለስልጣን ያለው ጥማት ሰርክ እንደ አዲስ ወይን እየጣመው ይሄድ ጀመር፡፡ ከስልጣናቸው በዕድሜ ይፍታህ የተሰናበቱት ሟቹ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ በስልጣናቸው እስከ መቃብር አፋፍ ዋስትና ይሆናል ያሏቸውን አፋኝ ህጎች ፀድቀው ተግባር ላይ እንዲውሉ ቀን ከሌት ኳተኑ፡፡ በዚህም የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኀበራት አዋጅ፣ የፕሬስ አዋጅ፣ የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅ፣…ይገኙበታል፡፡
በተለይ በተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶች እና የነፃ ጋዜጠኞች ከፍተኛ ተቃውሞ የገጠመው የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅ ሰኔ 30 ቀን 2001 ዓ.ም. ፀድቆ ለምርጫ 2002 ዓ.ም. ማፈኛ ተዘጋጀ፡፡ የዚህም ገፈት የዴሞክራሲ እንቅስቃሴዎችን ገድቦ የነበረውን ተስፋ መቀመቅ ውስጥ ከተተው፡፡ ከዚህ በኋላ በየካቲት 2003 ዓ.ም. በቱኒዚያ መሐመድ ቡዓዚዝ የተጀመረው የአረቡ ፀደይ አብዮት በሰሜን አፍሪካን እና መካከለኛ ምስራቅ አረብ ሀገሮች መቀጣጠሉን የተመለከቱት አቶ መለስና ተከታዮቻቸውና አጋሮቻቸው በኢትዮጵያም ይከሰታል በሚል የአስር አደኑንን አጣደፉት፡፡
የአረቡን አብዮት ተከትሎ በኢትዮጵያ የእስር ሰንሰለቱን የጀመሩት እንደ ታሰበው ጋዜጠኞች እና የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ናቸው፡፡ በቀዳሚነትም በወርሃ ሰኔ 12 ቀን 2004 ዓ.ም. ከፖለቲከኛ አቶ ዘሪሁን ገ/እግዚአብሔር፣ ሰኔ 14 ቀን 2003 ዓ.ም. ደግሞ ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ፣ ርዕዮት አለሙ፤ ከዚያም በክረምት 2003 ዓ.ም. የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህርና የኦፌኮ/መድረክ አመራር አቶ በቀለ ገርባና አቶ ኦልባና ሌሊሳ የእስር ሰለባ ሆኑ፡፡
ሌላው ከኢትዮጵያውያን በተጨማሪ ሁለት ሲውድናውያን ጋዜጠኞች ማርቲን ሸብይ እና ጆሃን ፐርሰን ሽብርተኝነትን ደግፈዋል በሚል በዚሁ የፀረ-ሽብርተኝነት ሰለባ በመሆን ከ14 ወራት የሰቆቃ እስር በኋላ በዓለም አቀፉ ማኀበረሰብ ጫና መስከረም 1 ቀን 2004 ዓ.ም.ተለቀዋል፡፡ በመቀጠል መስከረም 3 ቀን 2004 ዓ.ም. ደግሞ ታዋቂው የፖለቲካ ተንታኝ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፣በብዙ ወጣቶች ዘንድ በቅንነቱና ፍቅርን በመስጠት እንዲሁም ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልን አጥብቆ በመደገፍ የሚከራከረው የአንድነት/መድረክ አመራር አቶ አንዱዓለም አራጌ እና ሌሎች የአንድነት ፓርቲ አመራሮች አቶ ናትናኤል መኮንን፣አቶ ዮሐንስ ተረፈና ሻምበል የሺዋስ ይሁንዓለምንና አቶ አንዱዓለም አያሌውን ጨምሮ አቶ ክንፈ ሚካኤል ደበበና ሌሎች ሰዎችም በሽብርተኝነት ስም ወደ ወህኒ ወረዱ፡፡ በዚህም አፍቃሬ መንበር አቶ መለስ የፈሩትን የአረቡን አብዮት በዚህ ያለፉ ይመስል ጀብደኝነት ተሰምቷቸው፤ ተጠርጣሪዎቹ ገና በፍርድ ቤት ብይን ሳይሰጥባቸው አሸባሪዎች ናቸው ሲሉ ለተወካዮቻቸው አረጋገጡ፡፡
ያሰሯቸው ላይ ቀድመው ወንጀለኛ በማለት ፍርድ በመስጠት መከራን የደገሱት አቶ መለስ ባልጠበቁት ሁኔታ በጠና ታመው በአውሮፓ ቤልጄየም ብራሰልስ አንድ የዩኒቨርስቲ ሪፈራል ሆስፒታል ተኙ፡፡ በመጨረሻም እንደ ሆስፒታሉ ምንጮች ከሆነ ሐምሌ 13 ቀን 2004 ዓ.ም. እንደወጡ ላይለመሱ ብዙ ለመኖር ያሰቡበትን በ21 ዓመታት የስልጣን ዘመናቸው እንደ ግል ርስታቸው ያስቡት የነበረውን ቤተመንግስት ጥለው እስከወዲያኛው ተሰናበቱ፡፡
ይሁን እንጂ አጋሮቻቸውና የቅርብ የኢህአዴግ አመራሮች መታመማቸውን እንኳ ለህዝብ ሳይገልፁ በድንገት የሞቱትን ሰውዬ ከጋዜጠኞች ጥያቄ ቢበረታባቸው በቅርቡ ተመልሰው ስራ ይጀምራሉ የሚል መልስ ሰጡ፡፡ በኋላም የተባለው ሳይሆን ፈጣሪ የወሰነው ሞት እርግጥ መሆኑ እና ነሐሴ 14 ቀን 2004 ዓ.ም. ሌሊት እንዳረፉ ተደርጎ ነሐሴ 15 ቀን 2004 ዓ.ም. ማለዳ አንድ ለእናቱ በሆነው ሀገሪቱ ቴሌቪዥን ኢቴቭ ይፋ ተደረገ፡፡ ከዚያም ነሐሴ 27 ቀን 2004 ዓ.ም. ግብዓተ መሬታቸው እንደ ተከናወነ በግብረ-አበሮቻቸውና በመንግስት ሹማምንት ከተገለፀ በኋላ “…የመለስን ራዕይ እናስቀጥላለን!” የሚል መፈክር መሰማት ጀመረ፤የተባለው ራዕይ ኑዛዜ አሁንም ባያበቃም፡፡
በርግጥ አቶ መለስ ራዕይ ነበራቸው ከተባለ፤ እስከ ህልፈታቸው ድረስ የትኛውንም መንገድ ተጠቅመው ከቤተመንግስት ሳይወጡ ተቀናቃኞቻቸውን በማሰርና በማጥፋት በስልጣን መቆየት ነው፡፡ ነበራቸው የተባለው ራዕይ አሳቸው ሲሞቱ አብሮ ሞቷል፡፡ ይህ ደግሞ ራዕይ ሳይሆን የስልጣን ጥም እንጂ ህዝባዊና ሀገራዊ አይደለም፡፡ ተከታዮቻቸውም እናስቀጥላለን ያሉት ይህንኑ በመሆኑ ልክ እንደሳቸው ተመሳሳይ ድርጊት መፈፀሙትን እንደ ትክክለኛ እና ቅዱስ ተግባር ማከናወን ጀመሩ፡፡ ለአብነትም መጪውን ምርጫ 2007 ዓ.ም. ተከትሎ ለኢህአዴግና አመራሮቹ ስልጣን ማክተሚያ ምክንያት ይሆናሉ ብለው ያሰቧቸውን ማጥመድ፣ ማሰርና መፈረጁን ተያያዙት፡፡ የዚህ ሰለባ ከሆኑት መካከል በሚያዝያ 2006 ዓ.ም. መጨረሻ አካባቢ ጋዜጠኛ አስማማው ኃይለጊዮርጊስ፣ ጋዜጠኛ ተስፋዓለም ወልደየስ፣ ጋዜጠኛ ኤዶም ካሳዬና ጋዜጠኛ አዚዛ መሐመድ፤ እንዲሁም የኢትዮጵያው ዞን 9 ብሎገሮች በፈቃዱ ኃይሉ፣ዘለዓለም ክብረት፣ አቤል ዋበላ፣ ማህሌት ፋንታሁን፣አጥናፍ ብርሃኔ እና ናትናኤል ፈለቀ ቀዳሚዎቹ ናቸው፡፡
በ2004ዓ.ም. ዛሬም ድረስ ምላሽ እንዳላገኘ የሚነገርለት የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ጥያቄ ጋር በተያያዘ የሙስሊሙ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት፣ጋዜጠኛ ዩሱፍ ጌታቸውና ጋዜጠኛ ሰለሞን ከበደ ታስረው እስካሁን በወህኒ ቤት ይገኛሉ፡፡ ምንም እንኳ ጉዳያቸው በፍርድ ቤት የተያዘ ቢሆንም እስካሁን ብይንም ሆነ እልባት አላገኘም፡፡ ይሄ ሁሉ በአቶ መለስ አገዛዝ ዘመን የተጀመረ እስር ነው፡፡
በመቀጠልም በሀገር ውስጥ የኢህአዴግ መንግስት እውቅና ያልተቸረውና በሽብርተኝነት የተፈረጀው የግንቦት 7 የፖለቲካ ማኀበር ዋና ፀሐፊ የነበሩት አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ በየመን ፀጥታ ኃይሎች ታግተው ለኢትዮጵያው ገዥ ተላልፈው ተሰጥተዋል፡፡ አቶ አንዳርጋቸው ቀደም ሲል የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ አድርጋችኋል በሚል በነ ጄነራል ተፈራ ማሞ ክስ መዝገብ ከነ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ጋር በሌሉበት የሞት ፍርድ ተፈርዶባቸውል፡፡ የሞት ፍርድ ተፍርዶባቸው የነበሩት አቶ አንዳርጋቸው እንደገና በ2005 ዓ.ም. ደግሞ በነ አንዱኣለም አራጌና ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ክስ በሌሉበት የዕድሜ ልክ ፅኑ እስራት ተፈርዶባቸዋል፡፡ ይሁን አንጂ ወደፊት ትናው ክስ ተፈፃሚ እንደሚሆንና በቀጣይ ስለሚኖረው የፍርድ ሂደት ዕድሜ ከሰጠን አብረን የምናየው ነው ሚሆነው፡፡
ከላይ የተጠቀሰው እንዳለ እስሩ ተጠናክሮ በመቀጠል በሀገር ውስጥ በገዥው ስርዓት ህጋዊ እውቅና ተችሯቸው የሚንቀሳቀሱየፖለቲካ ፓርቲ ወጣት አመራሮች ተለቅመው ታሰሩ፡፡ እነኚህም መካከል በማኀበራዊ ሚዲያ የተለያዩ በሳል ፅሑፎችን በመፃፍ የሚታወቀው፣ የመቀሌ ዩኒቨርስቲ መምህርና የዓረና ትግራይ/መድረክ አመራር አቶ አብርሃ ደስታ፤ ከአንድነት ፓርቲ አመራሮች አቶ ሀብታሙ አያሌውና አቶ ዳንኤል ሺበሺ እንዲሁም ከሰማያዊ ፓርቲ አቶ የሺዋስ አሰፋ ይገኙበታል፡፡አራቱም ወጣት ፖለቲከኞች በፓርቲያቸውም ይሁን በሀገሪቱ ሰለማዊ የፖለቲካ ትግል በጎ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች መሆናቸው ይነገርላቸዋል፡፡
ሌላው እየተወሰደ ያለውን እስር በመሸሽ ከምርጫ 1997 ዓ.ም. ወዲህ ከ2005 ዓ.ም.ጀምሮ እስከ ያዝነው 2006 ዓ.ም. ድረስ ኢትዮጵያውያን ጋዜጠኞች ተሰደዋል፡፡ ለዚህም በዋነኝነት እንደ አስረጂ ሊጠቀስ የሚችለው በአሁን ሰዓት በጅምላ እየተፈፀመ ያለው እስር ነው፡፡ በአቶ መለስ ዜናዊ የስልጣን ዘመን የተጀመረው የጋዜጠኞችና ብሎገሮች እስር በአሁን ወቅት ሶስት የውጭ ዜጎችን ጨምሮ 20 የደረሰ ሲሆን፤ ከላይ በስም ከተጠቀሱት የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች በተጨማሪ በርካታ የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ ማኀበር አባላትም በእስር ላይ ይገኛሉ፡፡ ይሄ ደግሞ ዴሞክራሲያዊ መብቶች ዝግ ከነበሩበት የደርግ ጊዜ ጋር ሲነፃፀር፤ በኢህአዴግ ጊዜ 20 ጋዜጠኞችና ብሎገሮችን በማሰር በሀገሪቱ ታሪክ ቀዳሚውን አሉታዊ ስፍራ እንድይዝ ያደርገዋል፡፡ በዚህም በፀታ ኃይሉና በፍትህ ተቋማቱ ላይ ተጨማሪ የስራ ጫና ከመፍጠር በዘለለ የታሰበውን የፖለቲካ ትርፍ ያስገኛል ተብሎ አይጠበቅም፡፡
እንደ ገዥው ስርዓት አመራሮች፣ ደጋፊዎችና የፀጥታ ኃይሎች ገለፃ ከሆነ እስሩ የሚቆም አይደለም፡፡ በቀጣይ የዚህ ሰለባ ማን እንደሚሆን ባይታወቅም፤ እንደተባለው የሚተገበር ከሆነ በድጋሚ ቀሪ ጋዜጠኞች እና ፖለቲካኖች የእስር ስለባው ሊሆኑ እንደሚችሉ አያጠያይቅም፡፡ ምክንያቱም ከሌላው በተሻለ መብቶቻቸውን እየተገበሩና እየተጠቀሙ ማኀበረሰቡ ላይ በጎ ተፅዕኖ በመፍጠር የስርዓቱ ስልጣን ፈተና ይተረጎማሉና፡፡ አቶ መለስ ከመሞታቸው በፊት ምርጫ ሲደርስና ለስልጣናቸው የሚያሰጋቸው ነገር ብልጭ ሲልባቸው የሚወስዷቸው ርምጃዎች አሁን በስልጣን ላይ ባሉ ተከታዮቻቸው ተጠናክረው መቀጠላቸው አንዱ የመለስ ራዕይ ነው ሊያስብል ይችላል፡፡ ይህም አመራሮቹ እናስቀጥለዋለን ያሉት የአቶ መለስ ራዕይ አንዱ አካል ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ ምክንያቱም ያኔ በሳቸው ዘመን የተጀመረው ዛሬም በቃ ሊባልና መቋጫ ሊበጅለት አልቻለምና፡፡
አሁን በመንግስት አመራሮች ኢትዮጵያውያን ጋዜጠኞች፣ ብሎገሮችና ፖለቲካኞች ላይ ትኩረት ያደረገ የእስር ዘመቻ ከዚህ በፊት እንደ ተወዳጅ ነጠላ ዜማ ሲዜም የነበረውን “የመለስን ራዕይ እናስቀጥላለን” አባባል የሚታየው የእስር ዘመቻ መሆኑን በማሳበቅ በደጋፊዎቻቸው እንደ ሊቀ ሊቃውንትና ባለራዕይ የተወሰዱት ሟቹ ሰውዬ እንዲኮነኑ ማድረጉ አይቀርም፡፡ በየትኛውም ዓለም እንደሚታየው የፖለቲካ ርምጃና ተሞክሮ ሰዎችን ያውም ዜጎችን አሸባሪ ብሎ ማሰር በስልጣን ለመቆየትም ሆነ ለመረጋጋት መፍትሄ ሊሆን አይችልም፡፡ እንዲህ ዓይነት ርምጅ መፍትሔ ቢሆን ኖሮ የሊቢያው መሪ ኮሎኔል ሙዓመር ጋዳፊ፣ የግብፁ ሆስኒ ሙባረክ፣የየመኑ ዓሊ አብደላ ሳላህ በስልጣን ላይ መቆየት በቻሉ ነበር፤ግን አልሆነም፡፡
ነገርን ግን የህዝቡን ቁጣ በመቀስቀስ በውርደት ከስልጣን እንዲወርዱ አስገደዳቸው እንጂ መፍትሄ አልሆናቸውም፡፡ ስለዚህ በስልጣን ለመቆየት ጉጉቱ ካለ እንኳ የዜጎችን መብት፣ፍላጎትና ጥቅም ማክበርና ማስጠበቅ የተሻለ አማራጭ ነው፡፡ መፍትሔውን ልክ እንደ ጥሎ ማለፍና ፍፃሜ የአትሌቲክስ ውድድር ዜጎችን በማሰርና እንዲሰደዱ በማድረግ ዙሩን ማክረር ታምቆ የቆየውን የህዝብን ስሜት ባልተጠበቀ ሰዓት እንዲፈነዳ በማድረግ ሌላ ችግር ሊወልድ ይችላል፡፡የሚፈራው ችግር የሚከሰት ከሆነ ደግሞ የበለጠ ለገዥዎችም፣ ለህቡም ሆነ ለሀገሪቱ አሉታዊ ተፅዕኖ ማስከተሉ እሙን ነው፡፡
ፍርድ ቤቱ ባለፈው ውድቅ ያደረገውን ጉዳይ ዛሬ ያለምንም ይግባኝ ማፅደቁ ተሰማ
ዛሬ ግንቦት 24 ቀን 2006 ዓ.ም. የነበረው የፍርድ ቤት ውሎ አዲስ ክስተትን ይዞ ብቅ ማለቱ ተሰምቷል፡፡ ባለፈው ሚያዚያ 2006 ዓ.ም.ተጠርጥረው ከታሰሩ 3 ጋዜጠኞች እና 6 ብሎገሮች መካከል ዛሬ እሁድ ግንቦት 24 ቀን 2006 ዓ.ም. ቀጠሮ የነበራቸው በፍቃዱ ኃይሉ፣ አቤል ዋበላ እና ማህሌት ፋንታሁን ቀደም ሲል የማዕከላዊ ፖሊስ ጉዳዩን ወደ ፀረ-ሽብርተኝነት የክስ ጉዳይ ለመውሰድ የጠየቀው በፍርድ ቤቱ ውድቅ ተደርጎ የነበረ ቢሆንም፤ ዛሬ በሌላ ተቀያሪ ወንድ ዳኛ እዛው ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ 1ኛ ወንጀል ችሎት ባለፈው በነበረው ቀጠሮ ውድቅ የተደረገው በፀረ-ሽብርተኝነት ክስ ፖሊስ የጠየቀው ተጨማሪ 28 ቀናት የምርመራ ጊዜ ተቀባይነት አግኝቷል፡፡ በዚህም መሰረት ፍርድ ቤቱ በዛሬው ውሎ የነበፍቃዱ ፣ አቤል እና ማህሌት ሂደት ለሰኔ 22 ቀን 2006 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀነ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

በጉዳዩ ላይ ጥያቄ ያቀረብንላቸው ተከላካይ ጠበቃ አቶ አምሃ መኮንን፤ ከህግ አኳያ ፖሊስ ጉዳዩን ወደ ፀረ-ሽብርተኝነት ጠይቆ ውድቅ ተደርጎበታል፣ ስለዚህ በነበረው ውሳኔ ፖሊስ ቅር ከተሰኘ ይግባኝ ማለት እንጂ በተመሳሳይ ችሎት እና ጉዳይ ላይ በፍርድ ቤቱ ውድቅ የተደረገ ጉዳይ እንደገና ቀርቦ የፖሊስ ጥያቄ ተቀባይነት ማግኘቱ እና ተጨማሪ የ28 ቀናት የምርመራ ጊዜ በሚል መፈቀዱ ከህግ አግባብ ውጭ ነው፤ ይሄንንም ለፍርድ ቤቱ ብናቀርብም ተቀባይነት አላገኘም፤ ስለዚህ የህግ አካሄድ (procedure) ስህተት ታይቶበታል ሲሉ የነበረውን ሂደት ተናግረዋል፡፡ ይህን የክስ ሂደት ፖሊስ ጉዳዩን ወደ ፀረ-ሽብርተኝነት ለመውሰድ ውድቅ ያደረገችው ዳኛ ሴት እንደነበረች አይዘነጋም፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ የነገረ-ኢትዮጵያ ጋዜጠኛ በላይ ማናየ ፖሊስ ፍርድ ቤት ያቀረባቸውን እስረኞች ሲያወጣ፤ ለተወሰነ ጊዜ በጠበቂ የፀጥታ ኃይሎች ለጊዜው ታግቶ እንዲቆይ ከተደረገ በኋላ፤ ለነገ ማዕከላዊ እንዲቀርብ ትዕዛዝ በመስጠት ተለቋል፡፡ ለተወሰነ ጊዜ የተደረገው የጋዜጠኛው እገታ ምክንያት እስካሁን አልታወቀም፡፡
